#አናባቢ #ሰዋሰው።

"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁ"


 
ጌታ ብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በሥጋ ዬተለዬበት ዕለቱን ሲታሰብ ኢትዮጵያ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች??? በአፀደ ነፍስ የቅኔው ልዑል፦ ፓን አፍሪካኒስቱ ጋሼ ፀጋዬስ በምን ሁኔታ ይገኝ ይሆን? #ይከፋል። በሌላ በኩል ትውልዱ የቀደምትነት ቃናውን በመሻት ላይ ስለሚገኝ ይጽናናልም።
የቅኔው ንጉሥን ጋሼ ፀጋዬን በሥጋ መለዬት መታሰቢያውን በሥሙ በተሰዬመው 15ኛ ዓመቱን በያዘው በሲዊዘርላንድ ዙሪክ ክፍለ አገር ከ20 በላይ ቋንቋወችን በሚያስተናግደው፦ ለ24 ሰዓት አገልግሎት በሚሰጠው በራዲዮ ሎራ በዕለተ ሃሙስ ክፍል አንድ መሰናዶ ቀርቧል። ክፍል ሁለት ደግሞ በቀጣዩ ጊዜ ከዓለም ዓቀፍ ዬሴቶች ቀን ማርች ስምንት ጋር ይቀርባል። ቀኑ ባይገጣጠምም መታሰቢያው ግን ቀድሞ ተከውኗል። ይህ ሳልደክም ለተከታታይ 16 ዓመት ሠርቸበታለሁኝ።
www.lora.ch.tsegaye
ፀጋዬ ራዲዮ በ97.5 መካከለኛ ሞገድ በወር ሁለት ጊዜ በዕለተ ቅዱስ ሃሙስ በወር ሁለት ጊዜ እኤአ ሰዓት አቆጣጠር ከ15.00-16.00 በአማርኛ ቋንቋ ይቀርባል። እጅግ ብዙ ፈተናወችን ትናንትም ዛሬም እያስተናገደም ይገኛል። ብቸኛው የኮሚኒቲ ራዲዮ በሎሬቱ ፀጋዬ ገ/ መድህን ዬሚጠራ ራዲዮም ነው። ፈተናውም ዝልቅ የሆነው ለዚህ ነው። ለትርፍ አይደለም የሚሠራው። እንዲያውም እዬከፈልኩ ነው የምሠራበት። የኢትዮጵያ መንፈስን ጥሪቱ ስላደረገ።
መሰናዶው በብሄራዊ ጉዳይ ላይ ዬሚያተኩር ሲሆን በሰባዕዊነት ላይ አብዝቶ ያተኩራል። በታሰሩ ወገኖች ላይም ተግቶ ሙሉ 15 ዓመቱን ሰርቷል። አንድም ቀን በመሰናዶው የግለሰቦች ሥም አይጠራም። ከሚሞገተው ከኢትዮጵያ መንግሥት፤ ዬዬዘመኑ መሪወች በስተቀር። ዬፀጋዬ ራዲዮ እኤአ በ2008 በወርኃ አድዮ ዕለተ 18 በዙሪክ ከተማ ነበር የመሠረትኩት። ያን ጊዜ ስደተኛ ካንፕ ውስጥ ነበርኩኝ። ኢንተርኔት፤ ኮንፒተር አይታሰቡም ነበር።
በድፍረት ስጀምረው ድህረ ገጽም ነበረው። ግሎባል ነበር ድህረ ገፁ። በቦርድ ይተዳደር ነበር። በወል መሥራት አቅም ይፈትናል። ዬሆነ ሆኖ ለነፃነት ትግሉ ጉልህ ድርሻ ዬተወጣ ድህረ ገጽ ነበር። ድህረ ገፁ ቦርዱ በገጠመው ችግር ማስቀጠል ባይቻልም የፀጋዬ ራዲዮ ግን ቀጥሎ እንሆ ዘንድሮ 15ኛ ዓመቱን ይዟል። ህይወቴ እስከ አለ ድረስ እቀጥላለሁ ብያለሁኝ። ፈጣሪ እገዛው ካልተለዬኝ።
#ትልቅ ሰው አይሞትም። ህያው ነው። ብላቴው #አገርም #አህጉር ነው። #ሥርዓተ ትምህርትም ካሪክለምም ነው። በጋሼ ፀጋዬ ዙሪያ እራሱን የቻለ ዬምርምር ተቋም፦ ሲንፖዚዬም፤ ሙዚዬም ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁኝ። አንድ ሰሞን ኦነጋዊው ኦህዴድ ሲንደፋደፍ አይቼ ነበር። ብላቴው መንፈሱ ከተዋጠ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር አንቧጓሮ አይኖርም ነበር።
መጣችሁብን ልቀቁልንም አገር ምድሩን አያርሰውም ነበር። ጥላቻም ዶክተሪን አይሆንም ነበር። ውሸትም ራዕይ አይሆንም ነበር። ወረራም ምራን አይባልም ነበር። ተጫኝነትም አንቱ አይባልም ነበር። አስገድዶ ባህልን መጫንም አይታሰብም ነበር። ቀውስም መተዳደሪያ በጀት አይሆንም ነበር። ብቻ ትርትር ነው የሆነው። ብቻ ቱማታበቱማታ አቅምን ያላማከለ የውድመት ናዳ ነው እያታዬ ያለው። ዜና መርዶ በሱናሜ።
ኦነጋውያኑ በጥርሳቸው የያዟትን ኢትዮጵያ ዘመን ሰጣቸው እና እንሆ አይሆኑ እያደረጓት ነው። አማርኛ ቋንቋ #እዬሠሩበት ያፈርሱታል። ኢትዮጵያን እዬኖሩባት ሁለገብ ጦርነት ከፍተውባታል። ኢትዮጵያን ያፀናው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የነፃነት ሰንደቅ ዓላማን ያሳድዱታል። አገርን በፀሎትም በተጋድሎም ያበጀችውን ዬኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ከሥሯ ለመንቀል ግልጽ የሆነ ዬውንብድና ተግባር ይፈጽማሉ። እጬጌውን የሚስጢር ማህደር ግዕዝን እንደ ጣውንታቸው ያዩታል። ቃናቸው ሃሞት ነው ማህበረ ኦነግ።
ሥራው የአማኑኤል ረቂቅ ነውና በዚህ ዓመት ትልቅ ገድል ተከናውኗል። የቅኔው ግሥ ዬብላቴው እመብርኃንን "ምነው እመብርኃን ኢትዮጵያን ረሳሻት" ዬተማፀነበት መንፈስ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የኦሮሞ ልጆች ፊት ለፊት ወጥተው ሰማዕትነትን በእልልታ ሻሸመኔ ላይ በልዕልና፤ በልቅና ተቀበለዋል። ሚዛኑን አስጠብቀዋል። ጊዜ ራዲዮሎጂ ነውና። የብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ጥልቅ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ትውልድ የመፍጠር፤ ዬማፅደቅ አቅሙ ኃያል ነው። ቢሠራበት አይደለም ኢትዮጵያን ሙሉ አፍሪካን በአንድ የወልዮሽ ተፈጥሯዊ የፍቅር ዕውነት በሥርዓተ ተክሊል ሊያዋህድ ይችላል።
ብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን አናባቢነቱ ለሁሉ ኢትዮጵያዊነት በሁለመናነት ነው። ሚስጢሩ ጥልቅ - መንፈሱ ፃድቅ ነው። በጌታ ሎሬት ፀጋዬ መንፈስ ውስጥ ዬሆነ ሰብዕና ርህራሄን፤ አዛኝነትን፤ ለተገፋ መቆምን፤ ህብራዊነትን፤ ጥሞናን፤ መታመንን፤ ኃላፊነት መቀበል እና መስጠትን፤ ተጠያቂነት ፈቅዶ መቀበል ውስጡ ይሆናል። መብት እና ግዴታን በውል አዋዶ መተርጎምን ያካታል።
ኢትዮጵያ ርዕዮትዓለም ዬትውስት አያስፈልጋትም። ዬራሷ አላት። ቀለማቸው ዬማይተይበው ዬቀደምቶችን ታሪክ በምልሰት ስናዬው ሊቢራል፤ ሪፓብሊክ፤ ዲሞክራት፤ ማርክሲስት ወዘተ ተሻምተው አልተወረጁም ነበር። በራሳቸው ውስጥ መስከናቸው ነበር ዓራት ዓይናማ ያሰኛቸው። ኢትዮጵያዊነት #ፍልስፍና ነው። ኢትዮጵያዊነት #ሳይንስ ነው። #ኢትዮጵያዊነት ትምህርት ነው። ኢትዮጵያዊነት #ዩንቨርስ ነው። ኢትዮጵያዊነት ቅዱስ መንፈስ ነው። ኢትዮጵያዊነት የምርምር ማዕከል ነው።
ኢትዮጵያዊነት በራሱ ህገ መንግሥት ነው። ለናሙና ይሉኝታን ብታወስዱት በውስጡ ስንት ዕምቅ የውሳኔ አፈፃፀም ማሳወች አሉት? በመኖራችን ውስጥ ያልተፃፈው ህግ ስንት ድንጋጌ አሉን። እኔ በግሌ ኢትዮጵያ በተፃፈ እና ባልተፃፈ ህግጋት የምትመራ አገር ናት ብዬ አምናለሁኝ። አገሮች በተፃፈም፤ ባልተፃፈም ህግ ይተዳደራሉ። ኡትዮጵያ ግን ሁለቱንም አጣምራ ትተዳደርበታለች። ለዛውም ከብክባ።
ዬትናንት ዕንቁወቻችን ሁሉ ከሊቅ እስከ ደቂቅ #ዬጨመቱት በኢትዮጵያዊነት ፍሬ ነገር ነው። ስለዚህም ስኬታማ ነበሩ። ስለዚህም ዘመን ተዘመን ቀለማቸው አይደበዝዝም፤ ተምሳሌነታቸው እያሸተ ነው ዬሚሄደው። ዕውቅናቸውም ሉላዊ ነው። ሽልማታቸው ዓለምዓቀፋዊ ነው። ለምን? ስትሉ ኢትዮጵያን አንግሠው ስለሚነሱ። እናታቸውን አይዋሿትም።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ሆኑ ዶር ለማ መገርሳ ከኢትዮጵያ ጋር እርቀሰላም ማውረዳቸውን ባያውጁ አንዲት ስንዝር መራመድ አይችሉም ነበር። ሮል ሞዴላቸው አቶ ሌንጮ ለታ ምን ላይ እንደነበሩ ይታወቃል። ዬቀመሩት ቀመር አናት አናታቸውን ሲወቅረው ዕድሜ ዘመናቸውን ሲድሁ ኖረው በመጨረሻ ኢትዮጵያዊነትን ተጠልለው ለወግ በቁ። ሌሎችም ውስጣቸው በኢትዮጵያዊነን ላይ የሸፈቱ ዘለግ ብለው ወጥተው እንዘጭ ዬሚሉት በውስጣቸው ባለው እናትን የመካድ ድዌ ነው።
ወደፊትም ዛሬ በኢትዮጵያዊነት ሥም የሚሠራው ደባ የድቡሽት ቤት ይሆናል። ስለምን? በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ሁለመናውን ያላሰከነ መንፈስ ሁልጊዜ ድካሙ የድቡሽት ቤት ሆኖ ያከትማል እና። ኢትዮጵያዊነት ሚስጢሩ ጥልቅ፦ ቅጣቱም ሰማያዊ ነው። ሲያከብሩት ያከብራል፤ ሲያወርዱት ያነጥፋል፤ ይፈጠፍጣልም።
ዬብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን ዘመን የማይገድበው #አናባቢነት የእኛዊነቱ መንፈስ ተለጥፎ ሳይሆን ሆኖበት፤ ኖሮበትም ነው። በመሆን ውስጥ ልቅናውን #እርጋ ያለው በፃዕዳ ፓን አፍሪካኒስትነትም ነው። መጠነ ሰፊ ራዕይ፤ ግዙፍ ተጋድሎው ዘመንን እዬቀደሰ፤ ዬዘመንን ፋናውን እያጎለበተ ትምህርታዊ አሻራው ዘላለማዊ ሆኖ ይቀጥላል። ድርሳኑ ዕንቁ ነው። ክህሎቱም አልማዝ።
ብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ኢትዮጵያ አልከበደችውም። አፍሪካም አልከበደችውም። እንዲያውም ቅኝቱ፤ ዜማው ማህሌቱ ሁለመናው አፍሪካን አንድ አድርጎ፤ አስተባብሮ እና መርቶ እኩል የማድረግ ተልዕኮን ነበር ዬተለመው። ለዛም ነው ስለተመረቀ ልብ ያላቸው ዕውነቶች ሁሌም በአካልም በመንፈስም የሚዘክሩት። ሲዘክሩት ሐሴትን ፀንሰው፤ ሐሴትን አቆላምጠው፤ በሐሴት ፈጣሪን አመስግነውም ነው። "አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁ" ብለው። መወለድ ቋንቋ መሆኑን ዬሚያመሳጥርልንም ይህ ተደሟዊ ዬሃቅ እንክብል ነው።
1) ምክንያት የሎሬት ፀጋዬ መንፈስ ከቁም ሙትነት ቅዱስ መንፈሱ ስለሚታደግ።
2) ሰዋዊነትን፤ ተፈጥሯዊነትን ስንኞቹ ያውጃሉ እናም ይገራሉ።
3) ኢትዮጵያዊነትን ያልቃሉ ይፈልቃሉ እናም ያፀድቃሉ።
4) አፍሪካዊነትን ያደምቃሉ ያበራሉ እናም ሰፊ ምልከታን ይለግሳሉ።
5) የራስ እንደራሴነትን ያደጉሳሉ እናም ኮንፊደንስን ይገነባሉ።
6) እኔነትን ሳይሆን እኛዊነትን፤ አብሯዊነትን፦ ህብራዊነትን፤ ብሩኃዊነትን ያፋፋል በዛም ውስጥ ያጨምታል።
7) በኢትዮጵያዊነት ውስጥ አይዞን አለ ስለዚህም ለአጽናኝነት ለጋሽነትን ይመግባል።
9) በኢትዮጵያዊነት ፅንሰት ውስጥ #አይዟችሁ አለ። ይህ ዬሰውነት ማረጋገጫ ሰርትፍኬት ነው። ከዚህ ከተራቀ የጨለማው።
10) #አብረን ነን አለ። ለፍሰኃ ለሃዘንም።
11) ስለሌላው እኔልቅደምለት አለ። ዘመናችን በሰማዕትነት ሺወችን እያያን ነው። ኢትዮጵያ ላይ ዛሬ ሰማዕትነት ዘመኑን እዬባረከው ነው፦
12) አንተ ትብስ አንቺ ትብስ አለ። ዬአክብሮት መፈጠር በርህርህና።
13) በህግ አምላክነት አለ። ህግ ተላላፊነትን አብዝቶ መጠዬፍ። ህግ ሆኖ መኖርን። ድንጋጌን ፈቅዶ መቀበል።
14) በሌላ ዓለም ያላዬሁት ፃድቁ ኖር ኖር አለ።
15) ብሉልኝ ጠጡልኝ አለ። ቤተሰባዊነት።
16) ቆዩልኝ - ዋሉልኝ - እደሩልኝ አለ።
15) ኑልኝ! ናፍቃችሁኛል! አለ።
16) ላድምጣችሁ አለ።
17) ልርዳችሁ ልገዛችሁ አለ።
18) ፍቅር ዘርቶ ፍቅር ዬሚበቅል ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት ውስጥን በፍቅር ገዝቶ እንደ አሻው ዬሚነዳ ነው። ያ ባይሆን ሥማቸውን ሰምተናቸው ዬማናውቀው ተማላ ሰወች "ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው" ሲሉን እንደዛ በአኃቲ መንፈስ ባልተነዳን ነበር። ማነህ? ከዬት ነህ? ዬለም። ንጡሁን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ለለበሰ ሁሉ #ወከክ ነው። ወለላዬ ማርዬ ነው። ይህን በማድረግ፤ በዚህ ውስጥ በመኖር ዬሚያስከፍለው ዋጋ ግን በዚህ አምስት ዓመት የታዬው የሲዖል ዘመን በቂ ነው። እና እነ ማህበረ ሌንጮ አንቦ ላይ የብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን ፕሮጀክት ሲሰሩ እራሳቸውን በሰውኛ መንፈስ ገርተው ሊሆን ይገባ ነበር።
ይህ ዘመን ግን በሌላ በኩል ሊመሰገን ይገባዋል። ዕድሜያችን ሙሉ ያላገኜነውን #ትምህርት ተምረንበታል። ጭካናው፤ አረማዊነቱ፤ ቅጥፈቱ፤ ቀልዱ፦ መስቃው፤ መታበዩ፤ ዕብለቱ፤ ባኖሩት አለመገኜቱ፤ መገፋቱ፤ መከዳቱ፦ ተልባ ስፍርነቱ፤ ጩሌለነቱ፦ ሞላጫነቱ፤ ሁሉም የህይወት ሌሰን ነው። ከእንግዲህ ማንም? ማንንም? ማታለል ፈፅሞ አይችልም።
ዘመኑ ማንዘርዘርያ- ማንተርተሪያ - ማበጠሪያ ለእያንዳንዳችን እዬሸመተ በዬአድራሻችን ልኮልናል። አቅም እንዳናባክን ድካማችን ቀንሶልናል፤ ሙልጭልጩንም - ውልቅልቁንም - ዝልግልጉንም - ዝርክርኩንም በዬፌርማታው ሲንጠባጠብ ሁሉንም ቁጭ ብለን ተመልክተናል። አቅም አልቦሹም-' ስግብግቡም -: ድልዝ - ድሪቶውን - እንኩቶ - ከንቱውም- ቃል አባዩን አቅማችን በልቶ መንበር ላይ ከወጣ በኋላ ምን ያህል እንደጠጠቀን፤ በምን ያህል መታበይ እንደጨፈላለቀን አስተውለናል። በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ አድራሻዋ ዬት ላይ እንዳለም ተመልክተናል።
ዝልዝሉም- እብደቱም - ግንፍል ግንፍሉም - ወፈፌውም፤ ከህሊናው ብሎን የወለቀበትም ሁሉም በዬፈርጁ ዘርፋም /// ጅረቱም ነጥሮ አይተናል። ትውልዱ ብክነቱ እንደምን እንደባጀ እንደ ከረመ ተምረንበታል። ጊዜው #ድቅድቅ ቢሆንም በጠራ - በነጠረ - ኮለል ባለው መስመር ለመጓዝ ግን ዕድሉ ሰፊ ነው። #ማጭበርበር ተምሶ የተቀበረበት ዘመን በመሆኑ።
ለዚህ ነው ከእኔ የሚያንሱት ሳይቀሩ በግፍ ዬተገፋውን ያን ፍፁም ሰውኛ - ፍፁም ተፈጥሯዊ ቀደምት ኢትዮጵያዊነት ዘመንን አብዝተው እዬናፈቁ ዬሚገኙት። ዬትውልዱ ምርጫ ቀደምት እመው እና አቨው ሆነዋል።
ቀደምቱ አሻራ በባህል፤ በትውፊት፤ በስፖርት፤ በትሩፋት፤ በሥነ - ህንፃ፤ በኪነ ጥበብ፤ በፖለቲካ ጥበብ አመራር #የፊተኞችን ዊዝደም አጉልቶ፦ አጎልብቶ በማወደስ በራሱ ጊዜ ፈቃዱን ሸልሞ ትናንትን በመንከባከብ በመከብከብ ላይ ዬሚገኘው። ትውልዱ ከሙዚቃ እንኳን ዬሚመርጠው የጥንቱን፤ ከባህል የሚመርጠው የቀደመውን መሆኑ #ኢትዮጵያዊነት ዬማያረጅ #እያሸተ ዬሚሄድ ጣዝማ ስለመሆኑ ምስክር ነው።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ሞግቶ እዬረታ ዬሚገኘው። ካህድያነን እያራገፈ ዬሚገኜው። በሰሞኑ የታዬው ገሃዳዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ገድልም ይህንኑ አመክንዮ ያልተፃፈ ብዙኃኑ ዬመከሩበት፤ ዬተስማሙበት #ህገ - መንግሥት ያደርገዋል። ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሮው ህገ - መንግሥት ነው። እሱን ዬተጠጉ ያብባሉ፤ ያጌጣሉ፤ ይዋባሉ። ውበት እንደ አካባቢው ይተረጎማል ብዬ አምናለሁኝ። ውበት ለእኔ የውስጥም ነው።
#ቅኑ ኢትዮጵያዊነት ዬተቀናም ነው።
#ቅናው ኢትዮጵያዊነት የረጋ ዬተጠሞነም ነው።
#ኢትዮጵያዊነት የዕድምታም ሊቅ ነው።
#ዘመንን መዝኖ በልኩ ሚዛን አስጠብቆ ዬማኖር ገፊ ኃይል ያለው ኢትዮጵያዊነት ተፈሪም ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማግኔትም ነው። ይስባል። ይመስጣል።
ኢትዮጵያዊነት ፈተናው በውስጥ ክህደት ሲኖር ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ያዋርዳል። ኢትዮጵያዊነትን ተዳፍረው እና ተንጠራርተው የዘለፋት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወዲያው ኩምሽሽ ብለው ማጣፊያ አጥሯቸው ሲወድቁ ሲነሱ ታያላችሁ። ዬ32 ደቂቃ ድፍረት 24 ቀናት እንቅልፍ አልባ አባዘናቸው። አዋጅም አስወጣቸው። ሰጉ። ፈሩ። ራዱ። ኢትዮጵያዊነት ተፈሪም ነው የምለውም ለዚያ ነው።
እነ ብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህ የተፈጠሩባት ምድር ምርቃቷም እርግማኗም ኃያል ነው። እሷን በውስጥ እዬካዱ ቢያረግዱ አፍታ ነው። ቆይታው የጎርፍ ወይንም ዬምራቅ ያህል ይሆናል።
!ኢትዮጵያዊነት ማዕረግም ሞገስም ነው።
!ኢትዮጵያዊነት ክብርም - ልዕልናም ነው።
! ኢትዮጵያዊነት ልቅና - ልምላሜም ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማዕረጉም - ክብሩም - ልቅናውም - ልዕልናውም ፀዳል እና ወዙ የውስጥ አቅም ነው። ሲጠቃለል ኢትዮጵያዊነት ዊዝደም ነው። በዊዝደማቸው ውስጥ የኖሩ ባለ ፀጋ ተስጥዖ አቨው እና እመው ዬዘላለም ናቸው። ህያው - ህልው።
ምንግዜም ታቦቴ አባቴ፦ ብላቴ ጌታ ዬቅኔው ልዑል ስዋሰው የብዕር አጤ ዊዝደም ነህ። ስለሰጠህኝ ቅዱስ ዬጽናት መንፈስ ነፍሴ፦ ትርታዬ እስከአለች ድረስ አመሰግንኃለሁ። አገሬ ኢትዮጵያ በአንተ ብቃት፦ በአንተ ክህሎት ደምቃለች። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ክብሮቼ እንዴት አደራችሁልኝ? ኢትዮጵያስ እንዴት አለሽልኝ። ነገረ ቦረና፤ ነገረ ጉጂ፤ ነገረ አበርገሌ፤ ነገረ አፋር፤ ነገረ አዲስ አበባ፤ ነገረ አማራ፤ ነገረ ጉራጌ እንዴት እና እንዴት እዬሆናችሁ ይሆን? "አይዞን ከመከራ ጀረባ ሁልጊዜ ታላቅ ክብር አለ።"
"ዬንጋት ጨለማ ድቅድቅ ነው። ግን አጭር ነው።"
(ብፁዑ አባ ትምህርት ዶር ጴጥሮስ)
ክብሮቼ ደህና ዋሉልኝ። አሜን።
ደህና አምሹልኝ። አሜን።
መልካም ሰንበት። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/02/2023
ቅኔ አይወይብም። ቅኔ ዕንቁ ነው የምዕት ብርኃን።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ ዬተፈጠረ ሚስጢር ነው።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።