ይድረስ ለቀዳማዊት እመቤት ለወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው

ይድረስ ለቀዳማዊት እመቤት ለወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው
አዲስ አበባ።
"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"
ጉዳዩ፦ ይቅርብኝን አምጦ ስለመውለድ።
 

 
ለቁርጥ ውሳኔ ሂደትን መጀመር የወቅቱ ጥያቄ ይመስለኛል። ጊዜን መሻማት፤ ጊዜን መቅደም ብልህነት ነው። ብልህነቱ ህክምናው እራስን ከማዳን ይጀምራል። ራስን ማዳን ቀዳማይ ዬሰው ልጅ ዬተፈጥሮ ግዴታ ነው። ይህን ግዴታ በራስ ላይ ሲጭኑት ውሳኔ ይሻል። ውሳኔው ሊኮሰኩስ ይችላል። ግን አትራፊነቱ መራራን ገጠመኝን ከመቋቋም ይነሳል።
ኮስኳሳ ውሳኔ #ላምነት ወይንም #ከፈይ ዬመሆን ዕድሉ በጊዜ መጠቀም ሲቻል ብቻ ይሆናል። ወርቅ ከቀለጠ ይፈሳል ጊዜም ካመለጠ ፀፀትን ያፀድቃል። ጊዜ ሲሰጥ ፈቃደ እግዚአብሔርን አጠይቆ ነው። እናም ይህ ጊዜ ሁለቱ የዓራት ኪሎ የቤተ መንግሥት በጋብቻ የተሳሰሩ ጥንዶች በአኃቲ ልቦና መክረው የሚደርሱበት ውሳኔ እራስን፤ ህዝብን፤ ትውልድን፤ ታሪክን የማዳን ታላቅ ተልዕኮ አለው ብዬ በጽኑ አምናለሁኝ። የከፋን አደጋ ለመቅደም ማስተዋልን ማስተዋል።
#ዬተከበሩ ቀዳማዊት እመቤት ወሮ ዝናሽ ታያቸው ሆይ!
ዛሬ የተሰጠን ለዛሬ ብቻ ነው። በዛሬ ውስጥ ያለው ነገ እኛ የምንሠራው ብቻ ሳይሆን የፈጣሪ ፈቃድም ነው። ዬኢትዮጵያ ዛሬ ጣር ላይ ነው ያለው አካላቶቿ ሁሉ። በሞተ ዛሬ ነገን ማግኜት ደግሞ ጋዳ ነው። አይቻልም። መሸቀዳደም ያስፈልጋል። እሽቅድድሙ ለፍውሰት፤ ለድህነት ነው። ተጎድቶም ቢሆን ፍውሰት እና ድህነት ከተገኜ የመንፈስ ትርፍም ነው። አብሮ ያልተፈጠረን፤ ነገ በእዮር ጥሪ ተትቶ ለሚሄድበት ዬድንኳን ቤት ለከፋ ነገሮች ስለምን ተምሳሌት ይኮናል?
እግዚአብሄር እስከ ፈቀደ ድረስ ኢትዮጵያን ያህል የሚስጢር አገር #አካልተአምሳል ሆናችሁ መርታችኋል። ብዙ ጊዚያችሁ በፍሰኃ፤ በሰናይ አሳልፋችኋል። ክብር እና ሞገሱም በአለም አደባባይ ጎልብቶ የታዬበት ዘመን ነበር። በዛ የእናንተ የሐሴት ወቅት ግን የኢትዮጵያ ቀኖች ዕንባ፤ ዋይታ፤ ሞት እዬተመገቡ እዬለቀሙ ነው። መከራን ፊት ለፊት መጋፈጥን ሸሽታችሁ በደስታው ማሳ ብቻ ረጅሙን ጊዜ አሳልፋችኋል። አሁን ግን ያ የሐሴት ጊዜያችሁ እያመለጠ ነው።
ሴት ካገባች በኋላ በተለምዶ ሚስት ትባል እንጂ ላደላት እናትን የሚያስንቅ ፀጋዋ ከፈጣሪያዋ ዬተሰጣት ባለመክሊት ናት። በሚስትነት ውስጥ ያለው ሚስጢር ለትዳር አጋር የውስጥነት ዘብ አደርነት ነው። ይህ በፈቃድ የሚጫን እዮራዊ አመክንዮ ተፈጥሯዊ ስለሆነ የማይበልዝ ነው።
የሚስት ፈርጀ ብዙ ኃላፊነት እንደ እህት፤ እንደ ጓደኛም፤ እንደ አማካሪም ሁለገብነት አለው ላደላቸው። ባመዛኙ በውጭ በማዬው ሁነት በእርስወ እና በባለቤተወ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መሃል ጤናማ ነገር ውጭ ላይ አያለሁኝ። ያን ጤናማ ውህድ አኃቲ ማንነት እራስን እና አገርን በማዳን ላይ ቢውል እጅግ ጠቃሚው ጎዳና ነው።
ይህን ለማድረግ ቁጣም፤ ብስጭትም፤ አኩራፊነትም መንገዱ ሊሆን አይገባም። ምቹ ጊዜ እና ሰዓት ጠብቆ ሐዲድ ፈጥሮ በማባበል፤ በማቆላመጥ ጎባጣን ማቃናት ይቻላል። አማራጭ መንገዶችንም ማዬት ያስችላል። ሰፊ ጊዜ ሳለ ያልታሰበበት ጉዳይ ባለቀ ሰዓት መዝረክረክን ያዋልዳል። ያ ደግሞ አልባሌ ቦታ ይጥላል።
ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ከእርስወ ሌላ የቀረበ የነፍስ፤ ዬትንፋሽ አጋር ዬለም። በሴትነት የተሰጠወትን ፀጋ እና በረከት ተጠቅመው ጥሞና ወስደው ሃሳቡን ቢያስቡበት በትህትና እና በአክብሮት ለማሳሰብ ነው ዛሬ ሙሉ ቀን ረጅም ጊዜ ወስጄ ሳስብበት ውዬ ይህን የግል ዕይታዬን ልጽፍ የወደድኩት። እንደሚያዩት ፁሁፋን ጨርሼ ፖስት ሳደርገው ለእኛ ንጋት ላይ ነው። ስደቱ ላይበቃን መኖራችን ተቀምተናል። ውስጣችንም ውጪያችንም በአገራችን ጉዳይ ተጎሳቁሏል። ይህን ኤልሻዳይ አምላክ ያውቀዋል።
"እግዚአብሔር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም"
ቀጣዩ ጊዜ ብስጩ እና ገረጭራጫ ሊሆን ይችላል። እባከወን ይቅጡልን። ቀጣዩ ጊዜ ማጣፊያው ያጠረበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። እባከወት ደርዝ ያስዙልን። በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጥልቅ የኢማጅኔሽን ዓለም እና በዕውን ያለው ነጋሪ ሁኔታ አልተገናኜም። እያነሰ ሲሄድ ተስፋቸው ያልተጠበቀ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ይህን ነው በውስጠ ህሊናወት የግል ኃላፊነተወት አድርገው ሊወስዱት ዬሚገባ።
እከሌ ተከሌ ሳይባል ለሁላችንም ኢትዮጵያ ከብዳናለች። ስለሆነም ነው ቅብዓ ጥግ አጥቶ እንዲህ ክልትምትም የሚለው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት እና ጥሪ ይዞ ይወለዳል ዬሚል ዕምነት አለኝ። ጥሪወት ኢትዮጵያን እና ህዝቧን በጥንቃቄ ማዳን ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ዛሬን ማንበብ፤ ዛሬን መተርጎም እና ዛሬን ማመሳጠር ሲቻል ብቻ ነው።
እማከብርልወትን እርጋታወትን ኢንቤስት አድርገው ኢትዮጵያ ዬመጨረሻ ጽዋዋን ተገዳ እንዳትጠጣ መላ እባከወት ይፍጠሩ። ይችላሉ። ትናንት እና ዛሬ፤ ዛሬ እና ነገ የእኛ ስለመሆኑ ውል አላወላወለነም አምላካችን። መዳህኒትዓለም ክርስቶስ አልፈረመልንም። ከፀፀት መዳን ዬሚችሉት ብልሆች ብቻ ናቸው። ብልጠት ትምህርት ቤት አይደለም። ብልህነት ግን የሙሉ ዕድሜ ዩንቨርስቲ ነው።
ዕውቀት እና ብልህነት ውህድ ሲሆኑ ጊዜን በቅጡ ማኔጅ ማድረግ ይቻላል። #ጊዜው #አሁን ነው። ዬሚባክን ቅንጥብጣቢ ሰከንድ ሊኖር አይገባም። ስለሆነም በጋራ በራችሁን ዘግታችሁ በጉልቻ ዲስፕሊን ልትወያዩ የምትችሉበት አብይ ብሄራዊ ጉዳይ አለ። እስኪ እሰቡት #ለአፍታ ቤተ መንግሥትን #ስለመልቀቅ። በቀላሉ ሳታካብዱ እሰቡት። ተኝታችሁ እሰቡት። ሰልሱት። ዬላይኛው የማይቀርበትን ጥሪ አስባችሁ ገነት የሆነውን ምድራዊ ቤተ - መንግሥትን፦ ድሎትን፤ መከበርን ከመልቀቅ ጋር በንጽጽር አስቀምጡት። ይኽኛው ከፍፃሜው በሥግ መራራ ስንብት ከሚደረግበት እጅግ የዘመነ፤ በበዛም ሁኔታ ሥልጡን መንገድ ነው። ክብርም ነው አለመቻልን ወዶ እና ፈቅዶ ማስቻል። ምስጉንም ያደርጋል።
#ያልታሰቡ ገጠመኞች ዘመንን የመሪነት አቅም አላቸው።
ሁኔታወች ገዢ አላቸው። የዘመን ስበት እና ክትትል፤ የፈጣሪ ፈቃድ እና ሥራ። የንጉሦች ንጉሥን ዬአጤ ሚኒሊክ ቤተ - መንግሥትን በአስገዳጅ ዬመልቀቅ ሁኔታ ከሚፈጠር፤ እራስ ፈቅዶ እና አስቦ፥ ህዝብን ይቅርታ እና ምህረት ጠይቆ፥ የቀጣዩ ዘመን የመፍትሄ አካል ለመሆን መወሰን የምድርም የሰማይም ፀጋ ነው።
መሪነቱን ሞከራችሁ አልሆነም። ይሻላል የሚባል ነገር ዬለም። የቀረ እንጥፍጣፊ ተስፋም የለም። እርግጥ ነው ዶር አብይ አህመድ ህልመኛ መሆናቸውን አውቃለሁ። ሰው የሚነግራቸውን ከማድመጥ ይልቅ አዲስ ስትራቴጅ #በሰነፈ ሂደት፥ በዛለ ፈንታዚ ላይ ወጥነው አመክንዮውን ሲያነኳኩቱት አምስት ዓመት ሙሉ አይቻለሁኝ።
ዛሬ ዬግርዶሹም ቀኑ ተቀዷል። ህዝብ ፊት ለፊት ከዕውነት፤ ከመርህ፤ ከፋክት ጋር ከእነ ሙሉ ሥልጣናቸው ቃል ጋር ቁጭ አድርጎ ሪሰርች እዬሠራባቸው ነው። ዓለምም - እንዲሁ። ይህ አወንታዊ ቢሆን በበጄ። ግብረ መልሱ #አሉታዊ ነው። እና መቋጫውን እባከወት ያሳምሩት? እባከወት ይለመኑን??? በበቃን ውስጥ ልኑርበት ያዳልጣልና።
በጣም አስፈሪ የሆኑ ቁጣወች፤ በጣም ዬሚከብዱ መመካቶች እና መታበዮች፤ በጣም የተለጠጡ መዳፈሮች፤ እጅግ የሚጨንቁ ንግግሮች ያደርጋሉ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ የኖቤል፤ የዩኒስኮ እና የሄሰን ዬሰላም ተሸላሚ።
በሚፈጠሩ የታቀዱ ቀውሶች ውስጥ የጅረት ተጨማሪ ቀውሶች ፍሰት ሳይሳኩ ሲቀሩ ልተወው አይሉም። በአዲስ በተዘባረቀ፤ ድብልቅልቁ በወጣ ፕሮጀክት መንግሥታዊ ጫናውን ጫን ተደል ጭነው ያውጃሉ። ለዚህ ከቶ ድካም ዝር ዬማይልበት ብቃት የህሊና መሰናዶ እንደ አላቸው ጠቅላይ ሚር አብይን እረዳለሁ።
ለዚህ ነው እዮቤል ቤተ - መንግሥት እያሠሩ ዬሚገኙት። ሁሉ ነገር በእጅ አይበጀም። የ110 ሺህ ህዝብ ልቦናን መዳፍ ላይ ሁልጊዜ ማስቀመጥ አይቻልም። በፈለገ መትረዬስ የአዬር ኃይል ጉሪያም ቢታጀብ የማይሆነው አይሆንም? ለምን? ሁሉም የራሱ ገዢ እንደራሴ እራሱ ነውና። መጥኖ ነው የሰው ልጅ ለመንግሥት ሥልጣን ዬሚሰጠው። እያንዳንዱ ሰው በልቡ ውስጥም አንቱ እምታሰኜው ማንም ዬማይነቀንቀው ዙፋን አለችው። እንደ እኔ ፍልስፍና ከሆነ ህዝብ በነፍስ ወከፍ በራሱ ውስጥ ጫካ አለው ብዬ አምናለሁኝ። ልቡ የሸፈተን ህዝብ ዬፈለገው የኃይል እርምጃ አይመራውም። አያስተዳድረውም። ቀጥቶም ገርቶ ማስተዳደር አይቻልም።
እልህም፥ መታበይም - መፍሰስም መቀደድን ያመጣል። በጊዜ እሰቡበት። ከዚህ በላይ ህዝባችን #ሊቀቀል አይገባውም። ዬአምስት ዓመት ገኃነብአዊ የስጋት ዘመነ ፍዳ ሊያከትም ይገባል። ሥርዓት ይዞ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ። በቃው! በቀን በስንት የሃዘን ማቅ ውስጣችን እንደ ጥርጥር ተሸበሸበ? ሁሉም ነገር ዬሰው ልጅ ከሚችለው በላይ ገዝፏል።
ዬውስጥ ሰላማችን ፈጣሪያችን ትቶልን ዬሄደውን ተዘርፈናል። ይህ የውስጣችን መመርቀዝ ሊጠዘጥዘወት ይገባል ብዬ አምናለሁኝ። ለምን? ወገነወት ነን እና። ለዚህ ክብር እና ልዕልና የነፍስ ወከፍ ተዋፆአችንም አንቱ ነውና። እኔ በግሌ ዓለም ዬሚያውቀው በልበ ሙሉነት ሊያናግረኝ የሚችል ጠፈፍ ያለ ተጋድሎ አድርጌያለሁኝ። ባልመከባትም ግን በመሆን ውስጥ የሰከነ ተጋድሎ አቅም ሰጥቶኝ አምላኬ በመፈፀሜ አመሰግነዋለሁኝ። በውነቱ ስኬታማ ነበር። የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ አመራር ያን ሁሉ ድካም በከንቱ አወራረደው እንጂ። የሆነ ሆኖ ይህ ደብዳቤዬ ዬመጨረሻ ነው። እንዲሆን ስለምሻቸው ጥቂት ነጥቦች ግን ፦፦፦
1) ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ፓርቲያቸው እንዲቀጥል ከፈለጉ ከፓርቲያቸው የተሻሉ ሰብዕናወች ሥልጣናቸውን እንዲረከቡ ቢያደርጉ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ፦ መቀጣጫ፤ ማማረሪያ ሳይሆን እግረ እርጥብ።
2) ቅኖች፤ አወንታዊወች፤ አዛኞች በህብረት ያዘነችውን ልዕልት ኢትዮጵያ ሊረከባቸው የሚችሉትን መንገድ ቢያመቻቹ፦
3) ብዙ ጊዜ በተለያዬ ጊዜም ሲቀነቀን የማስተውለው በስምምነት የሽግግር አካል ለመፍጠር ቢታሰብበት መልካም ይሆናል። ዛሬ ፈቃዱ በእጃችሁ ነው። ፈጣሪ በቃ ሲል ግን ይህን የመሰለ ዕድል ላይገኝ ይችላል። እኔ ካቀርብኳቸው የተሻለ አማራጭም ካለ መሞከር ተገቢ ነው።
#እጅግ ዬሚያስፈራኝ።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ "ሥልጣናችን ከተነካ በቀን 100 ሺህ ሰው እናርዳለን" ሲሉ ከሰው ስለመፈጠራቸው ሁሉ ተጠራጥሬያለሁኝ። ሌላው በአልሆነ መንገድ ለውጥ ፈንድቶ በጣም የሚያስፈራኝ አናርኪዝም ከች ካለ ነው። ሥርዓት ያጣ ህውከት የበረከተበት ሁኔታ መፍራት ብቻ ሳይሆን ሳልኖርበት ይዘገንነኛል። ብዙ ንፁኃን ባለቤት ዬላቸውም እና ሊጎዱ ይችላሉ።
ዛሬን በቁሙ ቁመናውን ስናጤነው ያን ጊዜ የዛሬ አምስት ዓመት መጋቢት 18/2010 እኢአ የተረከቧት ኢትዮጵያን በዛ ልክ ለማስረከብ እንኳን ዛሬ አይችሉም። የለችም እና። ዛሬ እንደ ደላው ጉዞ ሁሉ በአውሮፕላን ሆኗል። ያልቻለ ደግሞ መክኖ መቅረት። ሁለመናው ተሟጧል። በድህነቱ ሰላም ያልተሰጠው፤ በዝምታ ለመሞት እንኳን ያልተፈቀደለት ህዝብ ነው ያለን። ኢትዮጵያ ለእኔ ዘመነ ቀራንዮ ላይ እንደ አለች አስባለሁኝ። አምናለሁኝም። ግን በእርጋታ፤ በስክነት ከለ ቀጣይ መስዋዕትነት የመፍትሄ መፍቻ ቁልፍ ሊኖር ይገባል። ለዚህ ደግሞ እኔ እርስወን መርጫለሁኝ። ቀስ አድርገው እንደሚሆን አድርገው እንዲያሾልኩን እማፀነወታለሁኝ።
ህዝባችን በቃው። በቁሙ ሰማዕትነትን ተቀብሏል። በስምምነት ለቀጣዩ ሰብዕና ቤተ - መንግሥቱን ለማስረከብ በጥልቀት፤ በጥሞና፤ በፆም በፀሎት ጊዜ ሰጥታችሁ እባካችሁን እሰቡበት። ትዕዛዝ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ፤ ዬአንዲት አነስተኛ ባተሌ አቤቱታ ነው። ሌላ ብልህ ነገር በውነቱ የኢትዮጵያን ህዝብ በፀሎት እንዲረዳችሁ ብትጠይቁት ዓይኑን አያሽም። ሳያውቃችሁ አክብሮ ሁለመናውን እንካችሁ ያለ ንፁህ፤ በጣም ንፁህ፤ ንዑድ ህዝብ ነው ያለን።
ቀጣዩ ጊዜ ሳይታወክ፤ መጪው ጊዜ ሳይሰነጠቅ፤ ዛሬ እና ነገ #ሳይፈረካከስ በመፍቀድ #መሰጠትን ፈቅዶ ለመስጠት ትፈቅዱ ዘንድ ሙሉውን ኃላፊነት ክብርትነተወት ይወስዱ ዘንድ በትህትና እና በአክብሮት አሳስባለሁኝ። ቢያንስ የንጉሦች ንጉሥ የአጤ ሚኒሊክን ቤተ - መንግሥትን ፈቅዶ መልቀቅን #እስክሪብቱን ወይንም #ንድፋን ቀጭ ብላችሁ ምከሩበት፤ ዝከሩበት። አደራ ለልጆቻችሁ የሚሆን የሚደመጥ ነገር ለማውረስም።
ዬልጆቻችሁ ዕጣ ፈንታ በእናንተ ዬሂደት አሉታዊ ይሁን አወንታዊ ዬንቅናቄ አድማስ ይበዬናልና። ከእነሱ ጋርም በሚኒ አዳራሽ መምከርም ይገባል። የዛሬ ልጆች ብስል ናቸው። ሲሆን ሲሆን ከህዝብ ጋር ቢመከርበት፤ ያ ቢቀር ቤት ውስጥ ዬበሰለ፤ ስኬትን አምጦ መውለድ ይገባ ይመስለኛል። ተመራርቆ መለያዬትም መመረቅ ነው። አገራዊም ነው። ዬንደቱ፤ የፍርሰቱ፤ የጭንቅ ገቢያው ጥድፊያው አስፈርቶኛል። ለዝንትዓለሙ እንዳይነጣጥለን ያስፈራል የቆሳሰለው ሂደቱ፥ ያውም አፈራርሶ እና የዓለም መሳቂያ ሆነን።
"የሰው ልብመንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/03/2023
ቪንተርቱር ሲዊዘርላንድ።
ሰዓት ከሌሊቱ 02/03/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥትም ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።