ዬተከበሩ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚር ክቡር አንቶኒ ብሊንከን በአቀባበሉ እጅግ ሰውነቴ እስኪርድ ድረስ ደንግጫለሁኝ። የኦነግ ልቅነት ሱናሜ ……… ዘፈንብን።

 

በአቀባበሉ እጅግ ሰውነቴ እስኪርድ ድረስ ደንግጫለሁኝ። የኦነግ ልቅነት ሱናሜ ……… ዘፈንብን። እግዚኦ።
ህግ የማያውቁ፤ ህግ የማያውቃቸው ገደሎች። በዬጊዜው አገርን ክብሯን ይቀጣሉ። እንዲህ።
"አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ
በመዓትህም አትገስፀኝ።"
(መዝሙር ፴፯ ቁ ፩)
 





 
ካልልኩ የተሰፋ ሽብሽቦ ወይ ይወጥራል፤ ወይ ያስዋኛል። የኦነግ ፖለቲካ ኢትዮጵያን በተመኛት በስንት ዘመኑ በራሳችን የማስተዋል እርቃን እንሆ እራሳችነን መለመልነው። በጥንት ዘመን ሊጋባ፤ በዛሬው ዘመን ፕሮቶኮል ይባላል። ፕሮቶኮሉንም፤ ሊጋባውንም አክ ያለው ገዳወኦዳ ሥርዕወ እንዲህ አገራችን እና ክብሯን በዲፕሎማሲው ህግ ፊት አዋረዳት። ዬተቀበሉትን እኔ ሥማቸውን ሰምቼ አላውቀውም፦ እንኳንስ የዓለም ማህበረስብ ቀርቶ።
ዬንቀትም ልክ አለው። የመለጠጥም ልክ አለው። የመንጠራራትም ልክ አለው፣ እንደምን አቻ ካልሆነ ጋር ዬአሜሪካ የኃያሏ አገር የውጭ ጉዳይ ሚር አቀበባል እንዲህ ዛቅጦ እንዲታይ ተደረገ??? ኢትዮጵያን ለማዋረድ ከደረጃዋ ለማውረድ ዬሚኳትነው፤ በበታችነት ስሜት ዬሚባዝነው አገዛዝ አሳዛኝ ትራጀዲ ነው።
በውነት ዕንቅልፍ አልወሰደኝም። እኛ ትቢያ ላይ ያለን ዜጎች አረማመዳችን፤ አነጋገራችን፤ አኗኗራችን አርመን፤ አስገድመን እምንጓዘው የታላቅ አገር ልጆች ስለሆን ነው። በእኛ ጉድፍ እናታችን እንዳናስነሳ ብርቱ በጣም ብርቱ ጥንቃቄ እናደርጋለን። እንኳንስ አገር እመራለሁ የሚል በፓርክ እና በአበባ ወረፋ ከፍ እና ዝቅ ውሎ የሚያድር ጉድ። እዮቤል ቤተ መንግሥት እሰራለሁ ብሎ ብድግ ቁጭ የሚልበት እኮ በኃያላኑ፤ በዲታ አገሮች ብድር እና ችሮታ ነው።
እናውቃለን እኮ ጠቅላዩ ሹፌር ሆነው ሲቀበሉ። ዬሚገርመው ከአዋረዱ፤ ከቀጡ፤ ከተበቀሉ በኋላ ደግሞ ሌላ ውዝዋዜ፤ ሌላ አጀብ ይከተላል። አይምጡብን ማለት ይቻላል እኮ። ዘመነኛ ስለሆኑ ኢንባሲውንም መዝጋት ይችላሉ። ተቀብሎ ማዋረድ ግን በቀለኝነት ነው። ዬውስጤን ሃዘን ባሳያችሁ እንደምን ጥሩ በነበረ።
ዲፕሎማሲ ህግ አለው። ዲፕሎማሲ የቻለ ዬአመራር ጥበብ ነው። ዬላቀ ሙያ፤ ዬማህበረሰብ ግንኙነት በሰለጠነ፤ አደብ በገዛ አመክንዮ እና ተመክሮ የሚከወን ብልህ የፖለቲካ ሂደት ነው። መኪና ፓርክ ሠርቶ እንደማስመረቅ አይደለም። ክህሎት - ይጠይቃል። ዊዝደም - ይጠይቃል። አድማጭነትን - ይጠይቃል። መጨመትን ይሻል። መነሻውም መድረሻውም ግን አክብሮት ነው።
ደሃ አገር፤ እራሷን ያልቻለች አገር፤ በልጆቿ የዶላር ፍሰት ተስፈኛ ዬሆነች አገር ቀርቶ እራሳቸውን ችለው ዬሚያድሩ አገሮች እንኳን ይህን ያህል አይቀናጡም። "ህግ ተላላፊወችን ጠላሁኝ።"
ዬተከበሩ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚር ክቡር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያ ባህሏ ይህ አይደለም። በቂም ታቅዶ በበቀል የተከወነው የአቀባበል ሂደት ደረጃውን ያልጠበቀ እና እኛንም አንገት ያስደፋ ክንውን ነው።
በመጨረሻ የተሳካ ጉዞ እንዲኖረወት እመኛለሁ ለቀሪ ሰዓታት። በሰላምም ይመለሱ ዘንድ ፀሎቴ ብርቱ ነው። ገዢወች በክፋ ዓይን ስለተቀበለወት በኦህዴድ ቤተ - መንግሥት አዝኛለሁኝ። ከውስጤ። የኢትዮጵያ መለያ አክብሮት ተፈጥሮ ሲሆን በዲፕሎማሲው ማህበረሰብም ተከብራ የኖረች ዓይነታ አገር ናት። ምን አልባት አንድ ቀን ዬአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢሆኑ እና ከዚህ አናርኪ ሥርዓት ዘመን ጋር ፊት ለፊት ብትገናኙ ምኞቴ ነው። እርስወን በዚህ ደረጃ ያዩ ዜጋውንስ ብለው ይገምቱ ዘንድ በትህትና እና በአክብሮት የቤት ሥራውን ለአቤቱ ዘመን ልሸልም።
ለአገዛዙ ግን የማያክመው፤ ዬማይጠግነው፣ ሊለብጠው የማይችል የፈሰሰ ጉዳይ ሆኗል። መቼውንም ማረም አይችልም። ለነፃነት ፈላጊው ቤተ - መርኽ ይህን መላ ቢስ አናርኪ፤ ህግ የማይገዛው ሥርዓትን ለምንታገል ግን ማህተማችን ነው። ዬሞገትንበትን ዕውነት ቦግ አድርጎ አብርቶልናል እና አምላካችን እናመሰግናለን። የቤርሙዳ ትርያንግሉ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ዘመን እንዲህ በጠራራ ፀሐይ ተፈትኖ ያድጠዋል። ለምን? የሥነ - መንግሥት ትውፊት እና ትሩፋቱ ጋር አራባ እና ቆቦነት አመልካች ስለሆነ። ካልልኩ የተሰፋ፤ ወርደ ጠባብ ጥብቆ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15/03/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።