#ወዳጃችን ጋሼ ብስጭት እና ጉዟችን።
#ወዳጃችን ጋሼ ብስጭት እና ጉዟችን።
#ምዕራፍ ፲፯

ማህበረ ቅንነት እንዴት ናችሁ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። ትንሽ ነገር ስለ ጋሼ ብስጭት።
ተበሳጭተህ ምግብ ከበላህ ምግቡን ሳይሆን #ብስጭቱን ነው የምትበላው።
አኩርፈህ ምግብ ከተመገብክ ከኩርፊያህ ጋር ነው ምግቡን #የምትውጠው።
ተበሳጭተህ የምትጠጣው ማናቸውም ፈሳሽ ወደ ጉሮሮህ ሲንቆረቆረ ብስጭት #እየገረፈው ይሆናል።
ተበሳጭተህ ከተኛህ እንቅልፋ በብስጭት ተዥጎርጉሮ የተኛህበት የለመድከው ምቹ አልጋ ሲጎረብጥህ፤ የለመድከው አተኛኝ ሲሰለችህ ሰላምህን አጥተህ እንዲሁ ከብስጭትህ ጋር ግብ ግብ እንደገጠምክ የወፎች ዝማሬ ዓዋጅ ይደመጣል። እነሱ ምን አለባቸው፤ የሰው ልጅ ነው የሚያሳድዳቸው እንጂ ሰናይ ናቸው። አቤት ዜማቸው፤ አቤት እንጉርጉሯቸው።
የሆነ ሆኖ ሲነጋ የሰራ አከላት ተቆራርጦ፤ በስትራፖ #እግዚኦ እያለ፤ ቀኑ ደብዝዞ ይቀበልሃል። ይህን ተሸክመህ ወደ ፀሎት አትሰበው፤ ይህን ተሸክመህ ወደ ማህበራዊ ሚዲያም አትወጥነው፤ ይህንኑ እንዳዘልክ ወደ ቁርስ ብታተኩር ሁለመናህን ያጋየዋል። ስለዚህ ከውጥኑ የሚያበሳጭ ነገር ቢገጥምህ እንኳን ሲሆን ሲሆን እንዳላየህ እለፈው። በስተቀር ብስጭትህን ከውስጥህ የሚያወጣ ሆቢ ብትለምድ ምን ይመስልኃል ውዴ እና ክብሬ የአገሬ ልጅ፤ ብትለምጂ ምን ይመስልሻል ተክሊሌ እና ዘውዴ የአገሬ ልጅ እታለም።
#እስቲ።
ጋሼ ብስጭት ፊት ከተሰጠው ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን በራሱ ጊዜ ይከፍት እና ያጣድፋል። ስለዚህ ፊትነሺነት መልካም ይመስለኛል። ይህ ባይቻል ቤትህን ለቀቅ አድርገህ ወጣ በል እና ተፈጥሮን አወጋጋ። ስትመለስ ሻማህን ገዝተህ ወደ ቤትህ ተጓዝ። እንደደረስክ መኖር ትግል ነውና ሌላ መሰናክል ሊገጥምህ ይችላል። እንዳላየህ እለፈው።
ከዛ የገዝሃትን ሻማህን ወደ ቤትህ በሰላም መመለስህ መታደልህ ነውና እግዚአብሄርን አመስግነህ ሻማህን አብራ። ንጋት ላይ እኮ ወፎች በሰላም ስላሰለፋት ሌሊት፤ ቀኑም እንዲባረክላቸው ወፎች ከእኛ ተሽለው በዝማሬ አምላካቸውን አመሰገኑ፤ ለዛውም በአክብሮት። የሆነ ሆኖ ሰውነትህን ስትታጠብ ከቻልክ መስኮቶችህን ዘጋግተህ ሰውነትህን ለቅለቅ በል እና እንደ አየሩ ጸባይ ስትለብሰው ምቾት የሚሰጥህን ልብስ አውጣ እና ከተገኜም ሽቶዋን አክለህ፤ ልበስ።
ይህንጊዜ የውስጥ ሙቀት፤ የውስጥ ንጹህ አየር፤ የውስጥ ወደር የለሽ መረጋጋት ይመጣል። የውስጥ ሰላምህ ከች ሲልልህ መጓጓዣ አይጠይቅህም። የሻማዋን መብራት በሙሉ ዓይንህ በፍቅር እያዬህ ቤት ያፈራውን ቀማምስ። የምትመገበው ምግብ፤ የምትጠጣው ውሃ ቅዱስ ይሆናል።
#ተዝች ላይ።
በነገራችን ላይ ተዝች ላይ፤ ከምግብ በኋላ ንጹህ ውሃ ብቻ ነው መጠጣት ያለበት። በኢትዮጵያ የተለመደው ለስላሳ፤ ጠላ፤ ሻይ ነው። ይህን እኔ አልመክርም። ንጹህ ውሃ። ውሃውን ማስዋብ ትችላለህ። ባለጌጥማ ውሃ ጠጡኝ ብቻ ሳይሆን ጤናህም ነኝ መልዕክት ይልካል። የውሃ ፖስተኛ ፈጣን ፈዋሽም ነው።
#ሌላም።
አደራ! ግን የአደራ ሰብዕና አለህን ውዴ??? ምግቡን አታጣድፈው። ውሃውንም አታሯሩጠውውውውውው። ለሁለቱም ጊዜ ስጣቸው። ምግብ በጣም ሆድ እስኪሞላ መብላት ለውስጥ ኦርጋን ለእኔ #ዲስክርምኔሽን ነው። ውሃም ከመጠኑ ሲያልፍ ስውር ጫና ነው ነጮቹ ሳይለንት ዲስክርምኔሽን የሚሉት ለኦርጋንህ። ከልክ ያለፈ ነገር ለየትኛውም የመኖር ዘይቤ አይጠቅምም። ጎንደሮች "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል ይላሉ።" ቅኔ በዓይነት ነው መቼስ እዛ በዕት።
ኦ! ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ይላሉ አሁንም ጎንደሬወች፤ ስለበዛ ጉዳይ …… ወጣት እያለሁ የፖለቲካ ህይወቴን ከቀረጹት አንዱ አንባሳደር ወንድወሰን ኃይሉ ይባል ነው። አንዲት እህታችን በግራ ቀኝ የእጇ ጣቶች ቀለበት ደርድራ ያያታል። ቀጠሮ ኖሯት ነው ከእሱ የሄደችው። ምን እንዳላት ታውቃላችሁ? "ቤትሽ ውስጥ #ሙዳይ የለሽም ወይ?!" ይህ እራሱን የቻለ መድብል ይወጣዋል። መጫጫን፤ ጭነት ማብዛት በአመጋገብ በአጠጥ ላይ አይገባም። * ቁሮውንምም እያስታገሱ። አትክልቱ፤ ጁሱ ክሬሙ ወዘተ ቀስ እያሉ፤ እያዋዙ ……
ለጤና ብቻ ሳይሆን ለዓይን ፍሰሃም አስታግሶ፤ ማጣጣም።
* #ቁሮ ሲጥ አድርጎ ወይራ ፍልጡን፤ ወይንም አንድ ኩንታል ከሰሉን የአገሬ የበዕቴ የእቴጌ ጎንደር ገበሬ ይጭን እና ከላዩ ደግሞ እንደ ** ጉልማ ነገር፤ ለጥቃቅን ወጪ ተጨማሪ ከሰል፤ ተጨማሪ የማገዶ እንጨት ያክላል። ያ ነው ቁሮ የሚባለው። ቁሮ በተለይ በኑሯቸው ዝቅ ላሉት በጣም ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ አገር በቀል የገብያ የማመጣጠን ብሂል ፍልስፍና ነው።
ዩንቨርስቲ ወይንም ኮሌጅ ያልገባ በየትኛውም ብሄራዊ ዘርፍ ትውር ሊል አይገባ ለሚሉ ሊቃናት ይህን መሰል ዕውቀት ከአገሬ ገበሬ አለ። ሲያመርትም፤ ሲገበያይም ባልተፃፈው የለቱ የገብያ ህግ ደንብ እና ሥርዓት ነው። ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ አገሬም ከየትኛውም ዩንቨርስቲ ያልተመረቁ በተፈጥሯቸው ልቅና በልዕልና የተሰጣቸው ዊዝደሞች ነው ያበዷት።
ገበሬው ሜትሮሎጂስት ነው፤ ኢኮኖሚስት ነው፤ ቲወሎጂስትም፤ አግሮኖሚስትም ነው …… ገበሬው ከተፈጥሮ ጋር ያለው የመግባባት ቋንቋ ሰማያዊ ነው። አገልጋዩን በሬውን ጠምዶ ሲያርሰው አያ ሆይ! እያለ እያዜመ፤ እያግባባ ነው። የለት ተግባሩን አጠናቆ ሞፈር ቀንበሩን ሲፈታ ሲደባብሰው፤ ምግቡን ተጣድፎ ሲያቀርብለት ያለው ተፈጥሯዊ ትዕይንት ከዊዝደም በላይ ነው።
ዲግሪ ብቻውን አገር አረጋግቶ ቢያስቀጥል ሙሉ ሃምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ መኖሩ ፓላስ በሆነ ነበር። ዛሬም ጦርነት ላይ??? ትራጀዲ። መማር እና ሥልጣኔ የህዝብን መኖር አቅላይነት እንጂ መርግነት መሆንን ነው ያየነው። በትውስት ይሁን በቅጂ ርዕዮት ዓለም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሊቃናት የዕውቀት ጣዝማን ከአገሬው ሊሂቃን አብዝቶ የላይኛው ከሰጣቸው ዝቅ ብለው ለመማር እንዲፈቅዱ በትህትና በዚህ አጋጣሚ አሳስባቸዋለሁኝ።
በዚህ ድዌ ዘመን ከዘመን የተያዙ ወገኖች አሉንና። መማር ጥሩ ነው፤ አለመማር ግን መወቀሻ፤ መነቀሻ፤ ማቃለያ ሊሆን አይገባም። በተመድ የታወቀችው፤ የተፈረመላት፤ የተመድ መሥራቿ፤ ፓን አፍሪካኒስቷ ኢትዮጵያ ዶክተሬቶች፤ ፕሮፌሰሮች አላበጇትም። የተንጠራሩ ንግግሮች አደምጣለሁ። መነሻን መርምሮ መነሳት ይገባል። ዛሬም ተስፋ የሚወጠነው ከማን ነው? እዛው ለጫማ ካልበቃው ገበሬ።
** #ጉልማ ከሰፊው የቤተሰብ ማሳ ለጎጆ መውጫ ወይንም ለመማሪያ ተብሎ የሚሰጥ የመሬት ዓይነት፤ የእህል ዓይነት። ብዙ ጊዜ በበጌምድር እና ስሜን ክፍለአገር፤ በወገራ አውራጃ የሰቲት ሁመራ ዲታ አራሾች ለልጆቻቸው የጉልማ ማሳ ነበራቸው። የደን ልማት ማሳም ነበራቸው።
"#ወደ ቀደመው።"
በተረጋጋ የአመጋገብ ዘይቤ እንደ እምነት ወይ ቁራንን፤ ወይ ከመጸሐፍ ቅዱስ መዝሙረ ዳዊትን አውጣ እና የቻልከውን አንብብ። ደስታ ብቻ አይምሰልህ በዚህ ጊዜ የምትመገበውም እና የምትጠጣውም። እእ። #ሐሤት ነው። ሁልጊዜ እንደምናገረው እኔ፤ እንደምጽፈውም ደስታ ለእኔ ሰው ሰራሽ እና ጊዚያዊ፤ የገሃዱ ዓለምን ፈተና ማስታገሻ ሲሆን፤ በእኔ ፍልስፍና #ሐሤት ከደስታ በላይ ገሐዱ ዓለምን እና መንፈሳዊውን ዓለም የሚያገናኝ ዘላቂ የእግዚየሩ ድልድያዊ ስጦታ ስለሆነ ዕውነተኛው ሐሤት ጋር ትገናኛለህ።
ከዚህ በኋላ ለራስህ እራስህ የሥነ - ልቦና ሐኪሙ ትሆናለህ። አሁን እኔ እያስተዋልኩት ያለው የተበሳጩ ሹጎች ማዳን እያጋዩት አያለሁኝ። ወደ የትኛውም የህዝብ መድረክ ብቅ ከማለት በፊት፤ ለሰውም ስልክ መደወል ሊሆን ይችላል እራስን ከብስጭት አድኖ መሆን አለበት። የተበሳጨ ሃሳብ ትጥቅ ላይ ከተለቀቀ ብዙ ነገሮችን ያጋያል። ስለሆነም እራስን ቀጥቶ፤ እራስን አርሞ ሳንክ ላለመሆን ተጠንቅቆ መገኜት #ሰብአዊነትም ነው። ለዛውም እራሱን ያዳነ ሰብአዊነት።
እራሱን ያዳነ ሰብአዊነት ሌላውንም ይፈውሳል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ መበሳጨት፤ ይሁን ማበሳጨት ታቅዶ የሚከውን ድርጊት ነው። በተለይ ከሁሉም በዓት ጎንደርን አቅዶ ማበሳጨት በየዘመኑ የማየው ሸክም ነው። አይጠቅምም። አለጠቀመም። ወጣቶች ዕድሜያቸው ነው ችኩልነት። በዛ ላይ ብስጭት ሲሰጡ ውስጣቸውም ይጎዳል፤ በሌላ በኩል ሰላማዊ ዜጋውም ይጎዳል። የብስጭት ግብረ ምላሽ ጫን ያለ የበቀል ነዲዲ ነው።
ስለሆነም በአንድም በሌላም የሚያበሳጩ ገጠመኞችን አስታግሶ መነሳት ትውልድን ያድናል። ይህን በህግ፤ በደንብ፤ በጸጥታ ኃይል አታመጣውም። እያንዳንዱ የዓለም ዜጋ እራሱን ከብስጭት አስታግሶ የመነሳት ዘዴን ደፍሮ ሲጀምረው፤ ቀስ እያለ ህይወቱ ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ፤ ለቤተሰቡም ሆነ ለተከታዮቹ መምህር ሲሆን ካለ ልዩ ዓዋጅ የማህበረሰብ ችግሮችን ሃንድል የሚያደርግበት ስልቱ ቀስ እያለ ተፈቅዶ አዕምሮ ላይ ተቋሙ ይገነባል።
በዚህ ነው የተደላደለ፤ ርጉ የማህበረሰብ ለውጥ ማመጣት፤ መምጣትም የሚቻለው። ለውጥ ከራስ የጀመረ ለውጥ ነው ዘላቂ መፍትሄን በስኬት የሚያጎናጽፈው። እሳት እየተፋ፤ ጎመራ እየተለቀ፤ በላርባ መታበይ ተጥለቅልቆ የሚተርፍ የህግ ቋጠሮ አይኖርም። ህግ የሰማይም ይሁን የምድሩ።
ይህ የዮጋ ዲስፕሊን ነው። የትውልድ ጉዳይ የነፍሴ ያህል እምከታተለው ጉዳይ ነው። በብዙ ሁኔታ የጀርመን እና የእምየ ሲዊዘርላንድን የወጣት ታለንት ዝግጅቶችን ስከታተል ቲም ጉዞ ላይ እክሎች አያለሁኝ። በአብሮ መኖር በቲም አባልነት እና መሪነትም። የሚገርማችሁ ከእስያ የተገኙ ፍሬወች ዲስፕሊናቸው ግን ወደርየለሽ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ይህን በጥልቀት ስላየሁ ነበር እኔ ዮጋ ለመሰልጠን ከወሰንኩበት አንዱ መስሬ ይህ የሆነው። እርግጥ ነው የሃይማኖት አበው ዮጋ እንደ ባዕድ አምልኮ ሊዩት ይችላሉ።
ፈላስፊት ቅድስት ኦርቶዶክስ የዕውቀት ዘርፎችን ዕውቅና ሰጥታ ተጠብባታለች። ቤተሰቦቼ የበቁ ሊቀ - ሊቃውንታት ስለነበሩ፤ መሬትን *** አትራገጧት፤ አትደብድቧት #ቀስ ብላችሁ ተራመዱ የሚል ይተባህል የነበራቸው፤ ድንኳን ጥለው አደግድገው ነድያንን ለጌታችን መዳህኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ልደት በፆም መፍቻ ፈሳኪ ስለነበሩ ቅድስቷ የዕውቀት ዘርፎችን አግልላ ሳይሆን አቅርባ ምርምር እንደምታደርግበት በልጅነት ጊዜም ቢሆን ነግረውኛል። ለዚህም ነው ከሰው ጋር ስሰነባበት የእጄ የማጣመር ባህልን የለመድኩት።
*** አትራገጧት ጠብቆ ነው የሚነበበው።
የሆነ ሆኖ እኔ የዛሬ ፲፭ ዓመት በፍቅር ተፈጥሮ ላይ ማተኮር ስጀምር፤ የፍቅር ተፈጥሮም ሆነ ህግጋት ለሁሉም በትምህርት ዘርፍ ተካተው ሁሉም ሊማረው ይገባል ብየ ስነሳም፤ ዲስፕሊኑን የዮጋን ልየው ብየ ስልጠና ወሰድኩኝ። እኔ እንደታዘብኩት ምንም ዓይነት ከሃይማኖት ጋር ንክኪ አላገኜሁበትም። የትንፋሽ ማኔጅመንት ስልጠና ነው የወሰድኩት። ጥሞናን በሚመለከትም የመመሰጥ አቅምን የምትማሩበት መስክ ነው።
በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይህ አንዱ የጥበብ ዘርፍ መሆኑን አውቃለሁኝ። ሁለት ፯ አብሶ በፍልሰቲት ሱባኤ ወቅት በስፋት አማንያን ይፈጽሙታል። እኛ ስናድግ በፍልሰቲት መሬት ላይ ይነጠፋል። ኦ! ማርያም በህብረት እናዜማለን። ከዛ በኋላ ድምጽ ማሰማት የለም። ከየተቀመጥንበት ጋደም ነው። ንጋት ላይ ደግሞ ወደ ቤተ - እግዚአብሄር። ቀን ላይ ቅዳሴ። ይህን ነበር በእርጋታ የጥሞናን ባህል ያስተማሩን።
አሁን ዮጋ የአንድ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ይህን የመመሰጥ ጥበብ ዕለት በዕለት እና ህዝባዊ የማድረግ ጥበብ ነው ከዮጋ አማጮች ያስተዋልኩት። ህዝባዊነቱ ግሎባል ሆኗል። አሁን በዩንቨርስቲወች ይሰጣል። የእኔ የዮጋ አሰልጣኝ ዩንቨርስቲም ታስተምር ነበር። እኔ ዮጋ ስሰለጥን የድንግልን አድህኖ ስዕል፤ መስቀል አስሬ ነው። ያገደኝ፤ የከለከለኝ ማንም የለም።
የፈለግኩት በቲም ውስጥ በፍጹም ሁኔታ የእስያ ወጣቶች የመጨመት ዲስፕሊኑን ነበር ያጓጓኝ። ቲያትር ስሰለጥንም፤ ቲያትር ልሰራ ሳይሆን ዲስፕሊኑን ነው የፈለግሁት። በተፈጥሮዬ ፊልም እንኳን አስተካክዬ ማየት የማልችል እጅግ በጣም አፋርተኛ ስለሆንኩኝ ቲያትር ስክሪፕት ውስጥ የሚሰጠኝን የኃላፊነት ቦታ አስመስዬ ለመሥራት በውነት እቸገራለሁኝ።
ከቋንቋ ጋር ሙዚቃ በለብለብ ስማረውም እኔ የሙዚቃ አድማጭ ሆኜ አይደለም። የሥነ ፁሁፍ ውበቱን ነው የሚመስጠኝ። የማስተማር አቅሙ። ድምጼ ለሚዲያ የተመረቀ እንጂ ለመዝሙር፤ ለሙዚቃ ሊሆን የማይችል በመሆኑ የፈለግሁት የሙዚቃ ጥበብ ዲስፕሊኑን ነበር፤ ዳንስም በዓመት ሁለት ጊዜ እሰለጥን ነበር፤ ያም ዲስፕሊኑን ነው። ምክንያቴ የሰው ልጅ ንጹህ ሆኖ ተፈጥሮ ፈቅዶ ውስጡን ለምን በክፋ ሃሳብ ያቆሽሻል የሚለውን ሥረ መሠረቱን ለመመር ብቻ ሳይሆን ወደ ፍቅር ተፈጥሮ የሚወስዱ የዲስፕሊን ዓይነቶች ለመፈታተሽም ነበር።
#ምን ሆኖ ነው የሰው ልጅ ክፋ ሃሳብን የሚመገበው?? ምን አጥቶ ነው ብስጩስ የሚሆነው?
የነፃነት ቃናን ማጣጣም። ዛሬ ያነሳሁት ስለ ብስጭት ስለሆነ፤ የሰው ልጅ መበሳጨቱ ሌላውን ከመጉዳቱ በፊት እራሱን እንደሚጎዳው ስለምን አያስተውለውም ነው የለቱ በኽረ ጉዳይ።
አንድ ሰው ብስጭቱን ተሸክሞ መኖሩን ሲመራ ብክለቱ ከራሱ እንደሚጀምር እንደምን አላገናዘበውም? ብስጭትን ሳያረጋጉ ወደ የትኛውም የለት ተግባር እራስን ማሰማራት የጉዳቱ ጠባሳ ከራስ ይጀምራል ነው ቁምነገሩ። የተበሳጬ ሰብዕና፤ ያ ሰው ቤተሰብ ከኖረው፤ ወይንም አነሰም አደገም ኃላፊነት ከኖረው ያ ሁሉ ውስጡ በጋሼ ብስጭት አብሮ እንደሚጋይ ከውስጣችን፤ ከልባችን ልናስተውለው ይገባል ነው።
የጋሼ ብስጭት ቤተኞች ሁላችንም ነን። ዓለም የፈተናወች ጭማቂ ናት። በፈተና ውስጥ ነው ጨለማነቱ ዕውቅና አግኝቶ እሱን የሚፈውስም መብራት የተበጀው።
በእግር ጉዞ አለመዘለቁ ነው የሰማይ የምድር የባህር የመገናኛ ድልድይ የተሠራው። ፈተና በቅጡ ማኔጅ ቢደረግ መፍትሄ አመንጭ ነው። ግን ከጋሼ ብስጭት ማዳን ከተቻለ። መቅደም ከተቻለ። ላለማዛመት ከተወሰነ። ብስጭት #ክብሪት አምራች ነው። ጦርነት ፈጣሪው ብስጭት ነው። ስለዚህ የተበሳጬ ሰብዕና ከማህበረሰቡ ጋር ሲቀላቀል እሳት የሚተፋ እንዳይሆን ከጋሼ ብስጭት እራስን አድኖ መነሳት #ፍቱን ነው ለዘመን የሰላማዊ ሂደት ጉዞ ቀና - የተቃና - ቅናዊ ጎዳና ነው።
#እርገትን ለለቱ ሲሸለም።
የሰው ልጅ ከጋሼ ብስጭት ጋር ሳይዋዋል ውሎ ለማደር እስኪ እራሱን እንደ አንድ ኦብጀክት ወስዶ ጥናት ይስራ። ፈላስፋ፤ ሳይንቲስትነት እኮ በመማር ብቻ አይገኝም። ሳይንቲስትነት፤ ፈላስፋዊነት የፋክት #አንጣሪነት ክህሎት ነው።
// ማየት እና መመልከት ይለያያሉ።
/// መመልከት እና ማተኮር ይለያያሉ።
//// ማተኮር እና ማስተዋል ይለያያሉ።
///// ማስተዋል እና መመሰጥ ይለያያሉ።
እያንዳንዳቸው በየዘርፋቸው ሲዘረዘሩ የአባታችን የቅዱስ አብርሃም የዘር ሐረግ ያህል ረጅም፤ ጥልቅ፤ ብዙ አውራ አመክንዮ እና ጅረቶች ያላቸው -----የተከማቸ - ያልተጠቀምንበት ግን ሰማያዊ የውስጥ ሰላማችን አንፆ የመዳን፤ የማዳን ተስፋችን ፍሬዘር የተስፋ ብርኃማነትን ፏ ያደርግልናል። ዕንቁነት በምግባር አያጓጓም?
~~~~~~~ በተለይ የአገር መሪወች፤
~~~~~~ ተጽዕኖ ፈጣሪወች፤
~~~~ የሚዲያ ባለሙያወች አማተርይሁን ፕሮፌሽናሎች፤
~~~ ጸሐፍት፤
~~ የተቋም መሪወች እና አስተዳዳሪወች፤
~ የህዝብ ተወካዮች እና ተመራጮች በየትኛውም ሁኔታ ጋሼ በሰጨኝን በውስጣቸው ፈውሰው መድረክ ላይ መውጣት የህይወታቸው ቀኖና ብቻ ሳይሆን ዶግማቸው አድርገው ሊቀበሉት ይገባል።
የብዙ ፍላጎቶች መሳካት ይሁን መክሰል ብስጭትን ጎርሰው ሰውን ያህል ትልቅ ፍጡር ጎድተው፤ ተፈጥሮን ያህል #ጋሻችን አጋይቶ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የዘልማድ ጉዞ፤ ሊታረም ይገባል። ብዙ በጣም ብዙ አስጨናቂ ጉዳዮች ዓለማችን እያመሳት የሚገኘው በብስጭት ፋፍርኬትድ በሆኑ ክስተቶች ነው። ልብ ይስጠን ፈጣሪ አምላክ። አሜን።
አህዱው ከጋሼ ብስጭትን ውስጥን ገለል ከማድረግ ይጀመር። ትዕዛዝ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ። ትህትናዊ ዕይታ ትውልድን በማዳን ትኩረት ለምናደርግ ወገኖች ለዛውም ረጅም መጣጥፌን የማንበብ ጸጋን ለታደሉ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/10/2025
ጋሼ ብስጭትን ሃግ እንበለው።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
እንደ አባቶቻችን የሰማነውን በልቦናችን ያሳድረው ፈጣሪያችን። አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ