ለመከላከያ ምርጥ ዘር እና የአዘቦተኛ ዘር ልዩነት የሚጠቅም ጉዞ አይደለም። ለዛውም በዞግ ርዕዮት በምትመራ አገረ - ኢትዮጵያ። የኢትዮጵያ እናቶች የአገርም እናቶች ናቸው ክብርም ሽልማትም የሚገባቸው።
ለመከላከያ ምርጥ ዘር እና የአዘቦተኛ ዘር ልዩነት የሚጠቅም ጉዞ አይደለም። ለዛውም በዞግ ርዕዮት በምትመራ አገረ - ኢትዮጵያ። የኢትዮጵያ እናቶች የአገርም እናቶች ናቸው ክብርም ሽልማትም የሚገባቸው።
የአንድ አገር መከላከያ ለእኔ የአገር ሃኪም ነው። ሃኪምነት ሰብአዊነትም ነው የተፈጥሯዊነት ሚስጢርን ለተረዳ አቅም ላለው የአገር ምሶሰነቱን በፖለቲካ ሊቃናት ካልተበወዘ። ሠራዊት፤ ደህንነት፤ የጸጥታ አካላት ጉዳያቸው ሰው ሊሆን ይገባልም። ከግለሰቦች የሥልጣን ፍላጎት ተቋማት ሊሆኑ ይገባልም። በመርኽም በዲስፕሊንም። ይህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሲማጥ የተኖረበት ግን ያልተገላገልነው የፈተና ቋት።
#ምዕራፍ ፲፯
እንዴት አደርን?
ጭምቷ ኢትዮጵያስ እንደምን አደርሽ ይሆን?
እምዬ ሲዊዝሻ እየኖርኩብሽ የምትናፍቂኝ፤ የማልጠግብሽም የከተማ ገዳሜ፤ ደጓ ቪንትዬስ?
ማህበረ ቅንነት የሥርጉትሻ ፔጅ ደጋጎችስ እንዴት ናችሁ።
#እፍታ።
በኢትዮጵያ የችግሮች ሁሉ መነሻ ምንጭ ይሁን መዳረሻ፤ የመፍትሄወች መቃረቢያ ይሁን የስኬት ሲሳይ የተቋማት ግንባታ አትኩሮት ዝቅተኝነት ይመስለኛል። ተቋም የትውልድን ሽግግር ቅብብሎሽ በሥርዓት የመምራት አቅም የሚኖረው ከአመሰራረት #ጥራቱ ይነሳል። የአንድ ተቋም የሂሳብ ሥርዓቱን ሰነድ ካልተዝረከረከ የዛ ተቋም ብቃት መስካሪ አያስፈልገውም። ራዲዮሎጂው ነው። በኢትዮጵያ እራሳቸውን ችለው፤ እራሳቸውንም አስከብረው ከዘለቁት ተቋማት ውስጥ ዕድለኛው፤ በዕውነትም ዕድለኛው ተቋም የኢትዮጵያን አየር መንገድ ማንሳት በቂ ይመስለኛል። ክብሩ ልዕልናው ዝቅ ከፍ ሳይል የቀጠለው የአመሰራረቱ ጥራት ንጥርነት ነው።
በአህጉር ደረጃ የኢትዮጵያን የልቅና ልዕልና አመሳካሪው የፓን አፍሪካኒዝም መዳረሻ የአፍሪካ ህብረትን፤ በፓን ግሎባላይዜሽንም ተመድን ኢትዮጵያ እንደ አገር በመሥራችነት፤ በሃሳብ አፍላቂነት የተሳተፈችባቸውን #ፕላኔታዊ ጉዳዮች በማስተዋል መመርመር ይገባል። በኢትዮጵያ ጉዳይ እራሷን ችላ በምታደርጋቸው ጉዳዮች ላይ እኛም አለንበት የሚሉ የኃያላን አገሮች የበዛ መሻት፤ ሂደቱን እስኪ አደብ ገዝታችሁ መርምሩት።
በዓለም ሊቃናት፤ በጨመቱ የዓለም ህዝብ ዘንድ ዕምቅ አወንታዊ ቅናትም ክብርም ያላት አገር ናት። ጎንደሬወች አንድ አባባል አላቸው። "የቅርብ መዋት የቹቻ መንከሪያ ይሆናል" ይላሉ። ለእኛም ነገረ ኢትዮጵያ እንደዛ ነው የሆነብን።
ኢትዮጵያ በሥነ - ጹሁፍ ዘርፍም ያልተነገረበት የብዙ አገሮች የውጭ ዜጎች መኖራቸውን ያደራጁበት፤ ለክብር የበቁበት ልቅናም አንቱ ነው። በቋንቋ የዕውቀትን ሚስጢር አጋርቶ የዓለምን ሥልጣኔ ፈር በማስያዝ እረገድም የተከደነው ሲሳይያቸው ልዩ አቅም አለው። በጤና ዘርፍ አንደኛ የወጡ አገሮች ሚስጢርን የቀዱት ከመጽሐፈ ፈውስ ነው። በሥነ ክውክብት በዩንበርሱም ዘርፍ ኢትዮጵያ ቀደምትነቷን ያመሳጠረችበት ዕውነት ነው። ባንንቀው፤ ባናቃለው ተዝቆ የማያልቅ የመንፈስ ጸጋ ባለቤቶችም ነን።
ለዛም ነው ኢትዮጵያ ብቅ ማለት ስትጀምር በግራ በቀኝ ወጀብ የሚበዛው። የጹሁፌ ቋሚ ታዳሚወች እንደምታውቁት በኢኮኖሚ፤ በመከላከያ ዘርፍ አልጽፍም። ጨርሶ አልነካካውም። ዘርፋን ለባለሙያወች መተው የሚበጅ ስለሆነ። ባለሙያወችም የትኛውም ሚዲያ ላይ ቃለ ምልልስ ሲደረግላቸው ግን አትኩሬ አዳምጣለሁኝ የግራ ቀኙን። ማወቅ ቢጠቅም እንጂ ጎድቶ ስለማያውቅ።
ሰፊነት የታደሉት ብቻ የሚያገኙት ነው።
ሰፊነት ህግ አክባሪነት ነው።
ሰፊነት አቅላዊነት ነው።
ሰፊነት የእኩልነት ፈላስፋነትም ነው።
ሰፊነት የአደባዊነት አስተምህሮም ነው።
ሰፊነት ደንበር ይሁን ወሰን አልባነት ነው።
ሰፊነት መታበይን የተጠየፈ ነው።
ሰፊነት ሁላዊነት ወይንም ሁሉየነትም ነው።
ሰፊነት ሰብዓዊነትም ነው ተፈጥሯዊነትን ስለሚያጎራርስ።
ሰፊነት አትኩሮትን ያበቀለ፤ ያሰበለም ነው።
ሰፊነት የትኛውንም የማንነት ቀውስን ሃራም ማለት ነው።
ተዝች ላይ --- የማንነት ጉዳይ የዞግ ብቻ አይደለም። የሙያ፤ የፆታ፤ የአቅም፤ የልምድ፤ የክህሎት፤ አነስ ካለ ማህበረሰብ መፈጠር ወዘተ ሊሆን ይችላል። የብዙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት ችግርም፤ ችግራቸውን ከውስጥ ሳያድኑ ሰርክ ለቀቅ በሚያደርጉት ፍላጎት ውስጥ ያለው ትርምስም ይኽው ነው።
በሌላ በኩል ሰፊነት ለአድማጭነት መታደልም ነው።
ሰፊነት ለግልብልብ ሁነት አለመበርገግም ነው።
ሰፊነት ርጋታም ነው።
ሰፊነት ስክነትም ነው። ለእኔ በእርጋታ፤ በስክነት እና በጭምትነት መሃል የማይቃረን እርስ በርሱ ልዩነት አለ።
ሰፊነት ኮሽ ባለ ቁጥር አለመደንገጥም ነው።
ሰፊነት በተቀወጠው፤ በጎሼው፤ በተስረከረከው ሁነት ሁሉ አለመዶልም ነው።
ሰፊነት በተፈጠሩበት ሚስጥር ልክ መኖርን የመምራት ክህሎትም ነው።
ሰሞኑን በመከላከያ የሽልማት እና የምስጋና ሥርዓት ሃሳቦች ጠንከር ብለው ውይይት ሲካሄድባቸው ነበር። በአዲስ ኮንፓስ ላይ ሙግት ሳይሆን በመጠነ ሰፊ አድማጭነት የተስተናገደ የልዩነት ሃሳብ ነበር ፤ ግን ተሸላሚወችን አነሳስቶ ሃሳብ የዘመነበት ወቅት ፈጥሯል። የዘመነበት የምለው በሃሳብ ሙግቶች ሲፋፋ ያስደስተኛል። ዳሞክራሲ ህልሙ ዕውን ሊሆን የሚችልበት የሃዲድ ውጥንም እንዲህ ተከባብሮ በሚካሄድ ዲያሎግ እንጂ በመፈክር ስላልሆነ። ዘለፋ፤ ማቃለል፤ ማጣጣል ሳይኖር ሙግት ሊደገፍ፤ ሊበረታታ ይገባል።
አሁን ቲክቶክ ላይ ወጣቶች የሚያደርጉት ውይይት ሊበረታታ ይገባል። ጋሼ ብልጽግናን መደገፍ መብት የመሆኑን ያህል ለስለስ ሲል በሙግት ፋክትን አንጥሮ በማቅረብ፤ ጠንከር ሲል በተቃውሞ ጎራ ተሰልፎ መወያዬት ጤናማ ጉዞ ነው። በተለይ የሴቶች ተሳትፎ መኖር ዘመንን ጸዳልማ ያደርጋል። በሂደቱ የሴቶችን፤ የትውልድን በራስ የመተማመን አቅም ያዳብራል፤ የንግግር አቅማቸውንም ያበረታታል። ይህ መልካም ውጥን ይመስለኛል።
"ጨዋታን ጨዋታ ያነሰዋል" ይላሉ ጎንደሮች እና ……… አቶ ኤርምያስ ለገሰ ልጁ ለአሜሪካ ሠራዊት የሰጠችው ክብር አስደምሞት የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የፃፈውን ጹሁፍ ደጉ ሳተናው ላይ አንብቤዋለሁኝ። ጹሁፋም ይኖረኛል። ዋሽንግተን ብሄድ ልጁን ሳላይ አልመለስም። ፈቃዱ፤ ፈቃዷ ከሆነ። የምትናፍቀኝ ወጣት ናት። እንደነዚህ ዓይነት ኃላፊነት የሚሰማቸው ልጆች ለእኔ የመንፈስ #ማረፊያወቼ ናቸው።
አቶ ኤርምያስ ለገሰ የአዲስ ኮንፓስ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ናፍቆቴ በዚህ ልክ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲከበር ነው ማለቱ የዛሬ አይደለም። የቆየ ነው። ምስክሮች አለንና። ሌላው የአሜሪካ ዜጋ መሆኑን እንደ እሱ የሚያከብረውም ሰውም አድምጬ አላውቅም።
የሆነ ሆኖ በርካታ ጉዳዮች ያልተስማማባቸው ነበሩ ከጋዜጠኛ አቶ አንተነህ ጋር በነበረው ቆይታ። ጨምቶ ነበር ያዳመጠው። የጋዜጠኛ አንተነህን ውስጥም በጥልቀት ሲከታተል እንደ ነበር ግብረ መልሱ ያመሳጥራል። ቅንነትም፤ ገራገርነትም የማይለየው የሚመስለው ጋዜጠኛ አንተነህም ደስታ ሳይሆን በመሸለሙ ሐሤት እርካብ ላይ ደርሷል። ፍንክንክም፤ ፍልቅልቅም ብሎ ነው ያዬሁት።
ከውይይቱ በኋላ የጹሁፍ ሙግቶች ተጨማሪ ጊዜ አግኝተው አዳመጥኩት። በሚዲያም ሞጋቾቹ በድምጽ ያቀረቡትን በአጭሩ አዳመጥኩኝ። አስተያየቶችንም አለፍ አለፍ አድርጌ አነበብኩኝ። የሚገርመኝ ግን መቼውንም ቢሆን በወጥ ሃሳብ አንድ #ዓይነትነት አይመጣም። ይህን ማንኛውም አደባባይ ላይ ያለ ሁሉ ሊገነዘበው ይገባል። በአንድ ጤነኛ ፓርቲ ውስጥ በራሱ አባላት ይሁን በገዛ አካሉ መካከል ልዩነት ይኖራል። ለዚህ በዘመነ ኮረና በእስራኤሉን ፓርቲወች አካላት መሃከል የተፈጠረውን መመርመር ያስፈልጋል።
ቁም ነገሩ በፓርቲው አብላጫ ድምጽ የተደገፈው ሃሳብ፤ የልዩነት ሃሳብ አቅራቢወችም አግልለው ሳይሆን አሸናፊውን ሃሳብ ከውስጣቸው ተቀብለው የመፈጸም ዲስፕሊን ይጠበቅባቸዋል። ዴሞክራሲ #ጣኦት አይደለም። በህይወት፤ በሂደት ውስጥ እራሱን እንዲህ ነው የሚያስከብረው። እራሱን እንዲህም ነው የሚያስከብረው። በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ፤ የምክር ቤት አባልነትን ተምርጦ ወንበር ያላገኜ ሰብዕና በምንም ታምር የሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባል ሊሆን አይችልም። ይህ ለዴሞክራሲ የህልውናው ጉዳይ ነውና።
የሆነ ሆኖ አቶ ኤርምያስ ለገሰ የመከላከያን የሽልማትን ጉዳይ እንደማይምንበት እጅግ #ተጠንቅቆ ነበር ያቀረበው። ወጀቡ ግን የጉድ ነው። የብልጽግናን ጉዞ በአሁኑ ወቅት አቅርቦ እየሞገተለት ያለውን ሰብዕና ሁሉን ካልተቀበልክ ውግዝ ነህ ጎርበጥባጣ መንገድ ነው። ለዛውም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አደም ፋራህ ብልጽግናቸው ጥንቅቅ ብሎ እንደ ተፈጠረ አድርገው እንደሚያደርጉት አይደለም። የአደረጃጀት የመርህ ግድፈት አለበት። በወቅቱ በዚህ ዙሪያ ሙግቴን አቅርቤበታለሁኝ።
አቤቶ ብልጽግና አዲስ ኮንፓስን ማግኜቱ ሎተሪ ነው የደረሰው። ክህሎትም፤ አቅምም፤ ተመክሮም ብቻ ሳይሆን አንባቢም ነው አቶ ኤርምያስ ለገሰ። አያያዝ ዕወቁ ባይ ነኝ ለብልጽግና ካድሬወች። ተቃዋሚወች ደግሞ አምልጧቸዋል። በእኔ ፍልስፍና በትጋት የሚሳተፍ ሰብዕና አይገኝም። ሰሞነኛ ነው ብዙው። አድማጭ ማግኜት እኮ ትርፍ ነው። አይደለም በዚህን ያህል መጠን ዕለት ተዕለት ያን ያህል ቅራኔ ገብቶ መማገድ ፈጽሞ የማይገኝ ሎተሪ።
እኔ አቶ ኤርምያስ ለገሰን በዘመነ ግንቦት 7 ሞጋቹ ነበርኩኝ፤ 360 እያለም ሞግቼዋለሁኝ፤ ሲገለል ደግሞ አቅሙ ከእነክህሎቱ ሊታጣ ስለማይገባ ሞግቸለታለሁ። አቅም ያላቸው ኢትዮጵውያ ሲገኙ ተቃዋሚውም ይሁን ተፎካካሪው፤ ተፎካካሪው ይሁን ተጠማኝ፤ ተጠማኝም ይሁን ተዋህጂ አያያዙን ሊያውቅበት ይገባል። ዕድሉንም መስጠት ብልህነት ነው።
ዘለግ ላለ ጊዜ ልክ እንደ አቶ ጃዋር መሐመድ በርቀትም ቢሆን አጥንቸዋለሁኝ። ብዙ የመረጃ ቋት አለው። የየትኛውም ፕሮ ኢትዮጵያ ተቋም አቅም ያላቸውን አርቆ፤ ሳይሆን አቅርቦ ቢይዝ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም።
አቤቱ ብልጽግና ሚሊዮን ካድሬወች እንዳሉት ሰሞኑን አድምጫለሁኝ። የአደረጃጀት፤ የአሰራር፤ የተቃውሞ አቋም የአያያዝ መርህን አየር ላይም ቢሆን ሜዳ አዘጋጅቶ ቢያስተምር ጥሩ ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሆነ የሚመራቸው ተቋማት ብጹዑ ናቸው፤ አትንኩብን አያስኬድም። እንቆላል ከሌለ ዶሮ የለም እና።
ከሁሉ በላይ በዝምታ የተቀመጠው ክህሎት፤ ልቅና እንዳለው ማሰብ ይገባል። ሙግቱ የኢትዮጵያን መከላከያ ከማህበረሰባዊነት አውጥቶ ደሴት ማድረግ የተገባ አይደለም ነው ጭብጡ የአዲስ ኮንፓስ። እኔም አምንበታለሁኝ። ይህን ሃሳብ ስለማምንበትም ነው የምጽፈው። መከላከያ አግላይነት ከሚባል ጉዳይ ጋር በፍጹም ሊነካካ አይገባም።
ሽልማቱ ያገለለ ነው። ቁጥር ስፍር የሌለው የቁምነገር ሰብዕና አለና። የቅራቅር ህዝብ እና ፋኖ የመጀመሪያውን የህወሃት ምኞት ኩምሽሽ ያደረገ፤ ቅስም የሰበረ ጀግንነት እኮ አዳምጠናል። ቁስለኛን አክሞ፤ አልብሶ፤ ሠራዊትን አፍቅሮ ጭንቅላቱን ላይ ጠረጴዛ ሰርቶ ተንበርክክ ለዕህል ውሃ ያበቃ ህዝብም አለ። ለነገም እርግጠኛ የመንፈስ ስንቅ የሚሆን ሙሉ አቅም ያለው በህዝብ አደባባይ ነው።
#በዞግ ሥርዓት አሳር በምታይ አገር መከላከያን የብሄራዊነት መንፈስ ሸማ ለማጎናጸፍ ይከብዳል። ይህ የማይነቃነቅ ፋክት ነው።
የስብጥሩ እና የአመራሩ ሁነት ሲታይም ይህን ያመሳጥራል። "አልሸሹም ዞር አሉ" እንደሚባለው። በህወሃት ዘመን ከነበረውም በባሰ ሁነት ነው እኔ የበላይ አካላት መዋቅራዊ ይዘት ያዬሁት። የሰሞኑ የመኮነኖች ሹመትም እራሱ ቋንቋ ነበረው። የባህር ኃይሉ አዛዥ ከየትኛው ዞግ እንደሆኑ ባላውቅም የስብጥር ችግር በጉልህ አለበት።
ይህን የምለው ለአገር መከላከያ ሚዛን ዞግ ጉዳይ ሊሆን እንደማይገባ፤ ብቃት እና ልቀት መስፈርት ሊሆን እንደሚገባ አውቃለሁኝ። በዘመነ ደርግ ከቁንጮ ጀምሮ በአመዛኙ የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪወች በብልጫ እንደነበሩበት፤ ግን ምንም ጥያቄ ተነስቶበት እንደማያውቅ አውቃለሁኝ። ኦረንቴሽኑ ብሄራዊነት ስለነበር።
ለዛም ነበር ጦርነቱ በህወሃት እና በሻቢያ አሸናፊነት ሲደመደም ባለቤት አልባው ያ ድንቅ የሠራዊት አባል ሲበተን በእግሩ ተጉዞ ጎንደር ለገባው የሠራዊት አባል በነቂስ የጎንደር ህዝብ እንግዶችን በፍጹም ሐሤት ተቀብሎ፤ አስተናግዶ በክብር የሸኜው። ከእኔ ከእናቴ ቤት የሲዳማ ልጆች አባት እና ልጅ ተገናኝተዋል።
በተመሳሳይ የሻቢያ እና የህወሃት የጫጉላ ሽርሽር ሲጠናቀቅም ከኢትዮጵያ ተፈናቅለው ወደ ኤርትራ የተጓጓዙትን ሁሉ የጎንደር ህዝብ ውስጣዊ ተፈጥሯዊ አሸኛኜት አድርጎላቸዋል። ሰሞኑን ጋዜጠኛ ነጋሽ በዳዳ ከሎዛ ሚዲያ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ እናትዋ ጎንደር በልኩ ገልፆታል። "ጎንደር የእናት ቤት" ሲል። ጎንደርን ለማያውቁ ጊዜ አመጣሽ ወጀበኞች ትክክለኛውን መልስ ሰጥቶበታል ጋዜጠኛው። ያልባለቀ፤ የደነገለ ዕይታ ነው። የእኔ ባርች እህቴ ጎንደር እንደ እኛ እንደ ሰወች ምቀኛ አጥታ አታውቅም ትለኛለች።
የሆነ ሆኖ ሠራዊት የህዝብ ነው። ድሬ ላይ ጥሩ ሥራ እንደ ተጀመረ ተረድቻለሁኝ። ለሌላው አብነት ሊሆን የሚገባ ይመስለኛል። ያው የፖሊስ ሠራዊትም በአገር ደህንነት ውስጥ ስለሚካተት።
የእኔ እምነት የአንድ አገር የመከላከያ ሠራዊት እንደ እኛ በየዘመኑ እንደ ጉልት ገብያ የሚሠራ የሚፈርስ ሳይሆን፤ እያንዳንዱ ዜጋ የእኔ፤ ሁሉም የእኛ ሊለው እንደሚገባ ሆኖ ሊደራጅ ይገባል። ይህን ለማድረግ የዞግ ሥርዓት ከሥሩ ሊነቀል ይገባል። ይህ በሌለበት ሁኔታ በከፍ እና ዝቅ፤ በአቅርቦት እና አርቆት ፍልስፍና ለዛውም ቂም እና በቀል ተቋጥሮ ተፈጥሯዊነትን ማምጣት እጅግ ይከብዳል።
ሰሞኑን ተደጋግሞ የሚነገር አንድ ጉዳይ አለ። ስለ ሶፍ ዑመር ዋሻ ድንቅነት፤ ተገልሎ ስለመኖሩ። በህይወታችን ውስጥም እንዳልነበር እንደማንተዋወቅም በአቶ ጌታቸው እረዳም፤ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልሳቸውም ተነስቷል። እኔ ከ15 ዓመት በፊት በ600 እርዕስ ሦስት የግጥም መድበሎች አሳትሜያለሁኝ። ከዛ ላይ ናፈቅሽኝ አገሬ የሚል ዘለግ ያለ ግጥም አለ። ሁለተኛው መክሊት መጸሐፌ ላይ ይመስለኛል። በአውዲዮም አለ።
ሶፍ ኡመር ዋሻው የሚል ሥንኝ አለው። የሚገርማችሁ ቆዳው ነጭ የሆነ የሶፍ ኡዑመር መንታ እንጨት ከአገር እስክወጣ ድረስ ነበረኝ። ዜግነቱን ለጣለ፤ በማንነት ቀውስ ለሚታመስ ይህ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያዊነት ከጽንሰታችን ጀምሮ የትምህርት ገበታችን ለሆነው ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በአንድነት ፓርክ፤ በባሌ ጉዟቸው እና በፕሮጀክታቸው አይደለም እኔ የሶፍ ኡመር ዋሻ በውስጤ የተመዘገበው።
እኔ - የባሌ ልጅ አይደለሁም። የሶፍ ዑመር ዋሻን ቅኔ የተቃኜሁለት። እኔ - የሽዋ ልጅ አይደለሁም የጸጋዬ ራዲዮ ለ17 ዓመታት አደራጅቼ እየመራሁ ያለሁት። አባቴ መምህር እና የቤተ- መፃህፍት ሙያተኛ ስለነበር ባሌም፤ ሽዋም በሥራ ምክንያት ተዛውሮ ሄዶ ቢሆን እና እኔ ከዛ ብወለድ ልለው እችል ነበር። እኔም ቤተሰቦቼም የተወለዱት ያደጉት ጎንደር ከተማ ነው። የጎንደር ከተማ ልጅ ነኝ።
ነገር ግን በህሊናየ ተዘርቶ፤ ተኮትኩቶ፤ አድጎ ያሰበለው ኢትዮጵያዊነት ነው። ወላጆቼ ስለ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ስላላት አቋም፤ ስለ አፄ የኋንስ የተጋድሎ ፍላጎት እና ሰማዕትነቴ በሚገባ አስተምረው አሳድገውኛል። ትምህርቱ #አጥንቴም የተገነባበት ነው። የሚበልጥብኝ አለ። ያም ነገረ - ኢትዮጵያ። ከግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ጋር ንክኪ ያላቸውን ማናቸውም ጉዳዮች ሁሉ እንደ ወረደ ፈጽሞ ልቀበል አልችልም። በጥንቃቄም ነው እምከታተለው። እንደ አልባሌም የማየው ጉዳይ አለመሆኑን ዘለግ ባሉ ጹሁፎቼ ውስጤን አሳይቸበታለሁኝ።
አቨይ ሆዴ፤ አባት ዓለምን ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርልኝ። አሜን። ወደ ቤተ - ጥበብንም ገና በ7 ዓመቴ ነው አባቴ ያስገባኝ።
ኢትዮጵያዊነትን እኛ #እምንማረው ቤት ውስጥ ነው። ኢትዮጵያዊነት አብሮን ነው የሚታነጸው። ለእኛ ኢትዮጵያዊነት የዘወትር ጉዳይ ሳይሆን የትንፋሽ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵ አደረገችልን /// አላደረገችልን አጀንዳችን አይደለም። እናት የወለደች ስላደረገች /// ስላላደረገች ሳይሆን ሚስጢሩ እትብታዊነት ነው። የህወሃት ህገ - መንግሥት ይህን ተፈጥሯዊ ጸጋ ነው ያለያዬው። ግፍም እኮ ነው። ያም ሆኖ አለን ውስጣችን አክብረን። ለዚህም ነው አማራ ሲባል "የጥንቷን ኢትዮጵያ ሊያመጡብን" የሚባለው።
በኢትዮጵያ የማንነት አገነባብ ውስጥ አዲስ እና አሮጌ የሚባል የለም። የግንዛቤ መፋፋቅ ነው። ይህው ዛሬ እኮ ቀይ ባህር ናፈቀን እየተባለ ነው፤ ነገ ጁቡቲ ሽው አለንም ሊመጣ ይችላል፤ ኑብያ ትዝ አለንም ሊባልም ይችል ይሆናል። ኢትዮጵያዊነት በግርግር ጎርፍ የተፈጠረ ማንነት አይደለም። ጥልቅ ሚስጢር በክህሎት የተደራጀበት ነው። እስኪ የወጣቶችን የሙዚቃ ውድድር አስተውሉት።
የወጣት የሙዚቃ አርቲስቶች ፈቃድ በዘመናቸው ላይ ሳይሆን የጥንት የጥዋቱን ፍለጋ ላይ ናቸው። ይህን አቅጣጫ ይዛችሁ ስትጓዙ መዳረሻው ተፈሪው ማንነት ላይ እንድትከትሙ ያደርጋችኋል። እናም በየዘመኑ የሚመጣ ወጀብ አይነቀንቀውም። ኢትዮጵያም አቅም አለኝ ማለት የምትችለው በዞግ የመስኖ ውሃ ጠጥቶ ያደገውን ሰብል ሳይሆን፤ በኦርጋኒክ ተፈጥሯዋ ከምንጩ እየጠጣ ያደገውን ሰብል ይሆናል። በዞግ መስኖ ካደጉትም ያፈነገጡ ሚሊዮን ቅን እና ቀና የኢትዮጵያ ልጆች አሉ። ውጭ አገር ተወልደው ያደጉትም እናታቸውን የሚያከብሩበት መጠን መስፈሪያ የለውም።
የሆነ ሆኖ 8 ዓመት ብዙ ነው። በጣም። ዞገኝነትን ነቅሎ ኢትዮጵያዊነትን ሲያስፈልግ ብቻ ከች ማድረግ ሳይሆን፤ ውስጥን ለውጦ፤ ውስጥን ለማስቀየር ሥራ ይጠይቃል። ብርቱ ትጋት። ይህ ሳይሆን አንዱን ተቋም ለይቶ #ብሄራዊ ማድረግ እጅግ ይከብዳል። አወቃቀሩም እንደዛ ስላልሆነ፤ የሥልጣን እርከኑ ተዋረድም የሚመሰክርው ብሄራዊነትን አይደለም። ህገ - መንግሥቱም ዜግነትን ስለማያስቀድም፤ ባልቀደመ ዜግነት የዜግነት ጠባቂ መሆን ፈጽሞ አይቻልም።
በሌላ በኩል መከላከያ የሚያስከብረው ዜግነት ክብራቸው ከሆኑት አገሮች ጋር፤ በዞግ ሥርዓት ከማይናጡ አገሮች ጋር ማነፃጸርም አይገባም። የአመክንዮ ጦርነት እና ግጭት ስላለበት። የመከላከያ ዓመታዊ በዓል ላይ ስለ ሽልማቱ ሲነገር የሌሎች አገሮችን ልምድ እንደ ምሳሌ ተወስዷል። አይገናኙም። ለዛ እኛ አልበቃነም። የሰብአዊነትም ጉዳይ አለ።
እኛ እኮ የግሎባላይዜሽን ቤተኛ ነን ብለን ደፍረን ለመናገር፤ ፓን አፍሪካኒስት ነን ለማለት ድፍረት የሸሸን ነን። አሁን በአገር ውስጥ የተከሰቱት ጦርነቶች እኮ ከዞግ የተነሱ ናቸው። ህውሃት ህወሃት ነው። ፋኖም የአማራ ነው። ኦላም የኦነግ የጫካው ክንፍ ነው። መሠረታቸው ዞግ ነው። በቤንሻንጉል፤ በጋንቤላ መሰሉ ጉዳይ ብቅ ጥልቅ እንደሚል ይደመጣል። የሱማሌ፤ የሲዳማ፤ የኦሮሞ፤ የአማራ፤ የጋንቤላ፤ የቤንሻንጉል ጉምዝ፤ የደቡብ ምዕራብ፤ የመዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብለህ፥፥፥፥፥፥ ብሄራዊነት ድስት ካለ ወስከንቢያ ይሆናል። እኛ ሳንሆን ፋክት ይለፍ አይሰጥም።
#በፍጹም ለመከላከያ የማያስፈልገው ጉድ ካድሬ ነው።
ኢሠፓ ከወደቀበት በኽረ ጉዳይ አንዱ በመከላከያ የመሠረታዊ ድርጅቶች ነበሩ። የመሠረታዊ ድርጅቱ ተጠሪ ፻አለቃ ሊሆን ይችላል። ፓርቲ የመንግሥት መሪ ነው። ይህ ባህል በዘመነ ህወሃትም፤ በዘመነ ብልጽግናም ቀጥሏል። ብልጽግና የአደረጃጀት ልዩነት እንዳለው አውቃለሁ። እንዳለ ነው የኢህአዲግ አባል ድርጅቶችን የተቀበለው። የጉዞው መሰናክል ምንጩም ይህው ነው። ብቻ አንድ የኢሠፓ ፻ አለቃ ያን የከበረ የእዝ አዛዥ አሻቅቦ ልምራ ሲል ከበደ። መረጃ ለእኔ ይቅደም ሲል መከራ መጣ። እናም ሁለመናው አይህኑ ሆኖ ባክኖም …… ተክኖም ቀረ። ያላተረፈ መንገድ አያስቀናም። ተመራጭም ሊሆን አይገባም።
#ለአገር መከላከያ በፍጹም የማያስፈልገው ፕሮፖጋንዲስት ነው።
የአገር መከላከያ የዓላማው፤ የግቡ እና የምግባሩ ጥራት ነው የሚያስከብረው እንጂ ዲስፕሊኑን የማያውቀው ፕሮፖጋንዲስት አይደለም የሚያስከብረው። ከዚህ ትብትብ ለመውጣት ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት #ግማድ አለበት። እሱም አናቱ፤ መሪው #የዞግ ሥርዓት መሠረቱ የዞግ ህገ መንግሥት ነው።
ይህም ሆኖ ከህዝብ ልጆችን ወስዶ አሰልጥኖ ያሰማራ አካል ሁለት ፍሬ አክቲቢስት፤ በጣት የሚቆጠሩ ፕሮፖጋንዲስቶችን ለይቶ ከሸለመ፤ ለይቶ ካሞካሼ፤ የተለየ ክብር ከሰጠ ምልዕቱ #ባይተዋር ይሆናል። ምልዕቱ ይገለላል ከፍ ሲልም ሳይለንት ዲስክርምናሽን ከውስጡ በሚያከብረው ህዝብ ላይ ይፈጸምበታል። "መከላከያ የእኔ ነው።" "መከላከያ የእኛ ነው" የሚለው ቅንነት ባዕዳዊ ስሜትን ያመነጫል። አኩራፊም --- ያባዛል።
ብዙ ተዘርዝረው የማያልቁ፤ ነዳላን፤ ክፍተትን በሌለ አቅማቸው የሚጠግኑ፤ ልባም ተግባራት የሚከወኑት በአመዛኙ በባለማይኮች ሳይሆን በጨመቱ ኢትዮጵውያን በተለምዶ ሳይለንት ማጆሪቲ በሚባለው ነው። ይህ የተፈጥሮ ጸጋ የተቸረው የአገር ምሩቅ መንፈስ ዝም ስላለ፤ እዩኝ እዩኝ ስላለ በይፋ በአደባባይ ምርጥ ዘሮች ተለይተው ሲሸለሙ ሲመለከት #ውስጡ ይጎዳል።
በሌላ በኩል ለደራሽ ታጋዮች ለድል አጥቢያ አርበኞች፤ በዘለፋ በሚታወቁ ሚዲያወች ሽልማቱ ክብሩ፦ ሞገሱ ማዕረጉ ጎራ በል ከተባለም በዛ ልክ ሸላሚውን ያስገምተዋል። ኦኦ! እግዚአብሄር በአምሳሉ የፈጠረውን ፍጡር ያዋረደ፤ ያቃለለ፤ ያሸማቀቀ አንቱታን ሲያገኝ ጠቅላላ የተቋሙን ማንነትን --- #ያሳጣዋል።
በአዲስ ኮንፓስ ሚዲያ በነበረው ውይይት እንደተረዳሁት ጋዜጠኛ አንተነህ እንዳስገነዘበን "እኛ የቤት ልጆች ነን። በማንኛውም ጊዜ ሃሳባችን ስሙልን ብለን ደጅ አንጠናም። ለፈለግነው አካል፤ በፈለግነው ጊዜ ማቅረብ እየቻል ለምን ሚዲያ ላይ እንጋፋለን፤ በር ቧ ብሎ ተከፍቶልናል፤ ቁልፋም ተሰጥቶናል፤ ለመከላከያ ከዜጋ በVIP ደረጃ ነን" ሲልም ለዛውም የዳበረ ልምድ ያለው ጋዜጠኛ እና ተሸላሚ አቶ አንተነህ ሲናገር ሰምቻለሁኝ።
እህህህ ነው ለዘርፋ ድምፃቸውን አጥፍተው ለሚተጉ የኢትዮጵያ ልጆች። ሌሎቻችን ደጅ አዳሪወች ነን ወይ ሊሉም ይችላሉ? ይህም ብቻ አይደለም የእኔው ካልሰማኝ የሰው ልዩነት ወደማያደርግብኝ ሌሎች ግሎባል ተቋማት መሄድ ያዋጣኛል ሊል ይችላል። በር ሲዘጋ መስኮት፤ መስኮት ሲዘጋ በጣሪያ የሚሞክሩ ትጉኃን አሉ እና። የሰው ልጅ አለኝ የሚለው መጠጌያ ይፈልጋል። እኔ አሁን ከሚሸለሙት፤ ከሚሾሙት ውስጥ አንዲት ዘለላ ሥንኝ የፃፈ የሞገተ አልነበረመ ለለውጥ ትግል ሲደረግ።
አንድም ሰው አልነበረም። በህይወት ያለን ሰወች አለን። ቢያንስ መከላከያ ኢትዮጵያዊ ውስጥነት፤ ቅርጽነት ሳይሆን ይዘትነት እንዲኖረው የክት እና የዘወትር፤ የእዳሪ እና የቤት ልጅ፤ ልጅ እና እና የእንጀራ ልጅ ሊኖረው #ፈጽሞ አይገባም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መከላከያ - ቤቱ፤ ጋሻው፤ መጠለያው፤ ተስፋው፤ ሲከፋው መከፋቱን ካለምንም ልዩነት ሲቃርብ ሊደመጥ ይገባል።
በማንኛውም ጊዜ የኢትዮጵያ ልጆች ስለ አገራቸው የሚያቀርቡት መረጃ ይሁን፤ ስለማይመቻቸው ሁነት ሁሉ በግልጽነት ደፍረው መናገር የመቻል ነፃነታቸውም በዚህ መልክ ማዕቀብ ሊጣልበት አይገባም ባይ ነኝ። እንዲያውም ማዶ ለማዶ ነን፤ ይህ ይስፋ ካልሆነ። የትኛውንም ሃሳብ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በእኩልነት ሊስተናገድ ይገባል ተቋሙ። አንዳንድ ጊዜ ጥንቃቄ የሚጠይቁ በኽረ ጉዳዮች ቢኖሩም።
ሌላው መከላከያ ግድፈት ሲፈጽምም አላየሁም፤ አልሰማሁም ማለትም ከሰብአዊነት ጋር ካላጣላም ………? ይህም ከፍ ያለው ስጋት የአዲስ ኮንፓስ ነበር። ብጹዓን የለም። ፍፁማን የሉም። ምድራዊ መላዕክት የሉም። ሰውና ግድፈት፤ ተቋም እና ስህተት ይኖራሉ። ዳኛውም መስታውቱም ከጊዜ እና ከህዝብ አደባባይ ነው ያለው። እርማት ጠቃሚ አልሚ ንጥረ ነገር ነው። ላወቀበት።
#ሠራዊቱ መገኛው ማህበረሰቡ ነው። ለመከላከያ የስለት ልጆቹ እንዲኖሩት ሊደረግ አይገባም።
መከላከያ ማህረሰቡ የእኛ እንጂ #የእነሱ እንዲለው ሊያበረታታ አይገባም። ይህ ነው የተፈጠረው። ተሸላሚወች ሲስቁ በዝምታ ውስጥ የሚገኙ ሊቀ - ትጉኃን የተገለሉት ሚሊዮኖች ደግሞ የኩርፊያ ጉድብ እንዲምሱ ያደርጋል። ለዛውም ብትንትናችን በወጣ በእኛ። እሰቡት ቅንጅት ስንት እንደሆነ ስንት ማካፈል እንደ ተሠራበት፤ ኢሳት ከስንት እንደ ተረተረ፤ ኢትዮ 360 ከስንት እንደ ተሸነሸነ። ከእነኝህ ተቋማት ከችግራቸውም መማር ይገባል። የመከላከያ ሠራዊቱ አጋ በፍፁም ሊለይ አይገባም። የስለት ልጆቹ ብቻ ዓላማውን ሊያሳኩለት ደግሞ በፋጹም አይችሉም እና።
ሌላው እፍኝ የማይሞሉ ሲቀርቡ፤ #የእኛ ሲባሉ፤ የውስጣችን ሲባሉ ሚሊዮኖች የመገለል ስሜት ያድርባቸዋል። ህመም ይፈጥርባቸዋል። ለሥነ - ልቦና ህመም የሚዳረጉ ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙ በጣም ብዙ ቅኖች አሉ። ውዳሴ ከንቱ የማይሹ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እናት #የልጅ ማገዶ በየዘመኑ በገፍ አቅርባ በቅጡ ያልተረዳች፤ ለሠራዊቱ ተሰልፎ ተገብሮም፤ ጡሮታ የማታገኝ እኮ አለች። በቀይ ባህር ጉዳይ የተሰው የዘመን ጀግኖች ማን አስታዋሽ አላቸው? መሸለም ካለባት፤ መከበር ካለባት፤ መንገሥም ካለባት ድምጽ አልባዋ ሳትታክት ለየዘመኑ የልጅ ማገዶ አቅራቢዋ አይታክቴ፤ ባተሌዋ የኢትዮጵያ እናት ብቻ እና ብቻ ናት።
ሌላው ጋዜጠኛ አንተነህ ቅንም ገራገርም ይመስለኛል። ልምድም ተመክሮም አለው። ሲናገር እንደሰማሁት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊን፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝን፤ የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን ሞግቶ እንደማያውቅ ገለጸልን። እና ምኑን ይሆን የሚሞግተው። ቁንጮወችን ዘሎ የበታቾችን ከሆነስ "አህያውን ፈርቶ መደላድሉን" አይሆንበትንም። ግልጽነቱን ግን ወድጄለታለሁኝ።
የፖሊሲ አመንጪው እያለ ፈፃሚውን እና አስፈፃሚውን ብቻ ከሆነ ሙግቱ የውርንጫ ድካም ይሆናል። እንደ ጋዜጠኛ ትችት መሪወችን ሳይነካ ከዛ ባሻገር ከሆነ ይህም ግንጥል ጌጥም ነው። አናት ተፈርቶ #ቁርጭምጭሚት ላይ ማተኮር የፋክት ትርምስ ይፈጥራል። ለጋዜጠኛ - የመንግሥት ሥልጣን መሪነት፤ ለጋዜጠኛ - የፖለቲካ ድርጅት፤ ለጋዜጠኛ - የሥልጣን መሻት፤ ለጋዜጠኛ ፕሮፖጋንዲስት ከሙያው ተፈጥሮ ጋር ሰርክ ግብግብ የሚፈጥር ይመስለኛል።
ይህ በዚህ እንደ አለ፤ አሁን ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ያገኙት ዕድል እኮ ከሰማይ የተገኜ መና አይደለም። ወይንም ወንዝ ዳር የታፈሰ አሽዋ አይደለም። እስኪበቃቸው አቶ መለስ ዜናዊም፤ አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝም በትጋት እና በተከታታይነት ተሞግተው የተገኜ ውጤት ነው።
በየዘመናቸው የተሻለ ሠሩ የተባለበት ሁነትም ሙግቱ ነው ያሰራቸው። አስታውሳለሁ እኔ በረዶ ተራራ በሚሠራባት ዴንማርክ የኮፐን ሃገን ከተማ እአአ 2008 ታህሳስ ወር ላይ ከመላ አውሮፓ የተውጣጣ የተጋድሎ ቤተኛ ጠቅላይ ሚር መለስ ዜናዊ አፍሪካን ወክለው በሚገኙበት ጉባኤ ላይ እኔም ተገኝቻለሁኝ። ተሞግተዋል።
የታሰሩ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ዓለምንም ተማጽነናል። በነገራችን ላይ አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣን እንዲለቁ የሆነበት ትልቁ አመክንዮ የጸጥታ ኃይሉ - ኢሰብአዊነት፤ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ነበር። ይሄ ነገንም ይወልዳል። አሁን ማስተካከል እስከአልተቻለ ድረስ። ለዛሬ ለእሱ ሽልማት የበቃበት አመክንዮ ያ ወደርየለሽ ተጋድሎ ስለተደረገ ነው። አባይ ሚዲያ ዴንማርክ ነበር እዛ በረዶ ሥር እየተንዘፈዘፈ።
በልዩ ሁኔታ ግልጽ አቋም፤ ዘላቂ ትጋት፤ የማይናወጽ ብቃት ያላቸው ዜጎች ሲኖሩ አገር ልትመርቃቸው፤ ልትሸልማቸው፤ ልታከብራቸው ብትችል ጥሩ ነው። ሊበረታታ ይገባል። በሌላ መድረክ። ብልጽግና ሊሸልም ይችላል።
ግን ነገር ግን የሚማገደው የሠራዊቱ አባል፤ እሳቱ ላይ የሚርገበገበው እያለ ……… እንዲህ እና እንዲያ ግን ሚዛናዊ አይደለም። የሠራዊቱ አባላትን ሳይ እራሱ ጫማቸው፤ ልብሳቸው እንኳን በደርግ ጊዜ እንደ ነበረው አይደለም። ያማል። ገፃቸውም የከፋው ነው። ለእነሱ ሁሉም አትኩሮት ቢሆን ይመረጣል። በተጨማሪም የሰብአዊነት ኮርስም በየምድባቸው ሊሰጥ ይገባል። እጅግ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ነውና።
ፕሮፖጋንዳ አሉታዊ እና አወንታዊ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። ፕሮፖጋንዳ የንግግር ጥበብ አካል ነው። የዕውቀት ዘርፍም ነው። ተስጥኦ ጸጋም ነው። ፕሮፖጋንዳ በንግግር ተስጥኦ ያላቸው ሰብዕናወች የሚፈጽሙት ነው። ከአነጋገር ይፈረዳል፤ ከአያያዝም ይቀደዳል እንደሚባለው።
በጦርነት ወቅት ዓራት ዓይናማ ጥንቁቁ አወንታዊ ፕሮፖጋንዲስት ያስፈልጋሉ። ግን ህይወታቸው የሚያስተምር ሊሆን ይገባል። ዘለፋ ስንቁ የሆነ ሰብዕና ጸጋው ቢኖር እንኳን ተመራጭ ሊሆን አይገባም። ለምን? ድል ላይ ተጽዕኖ ስላለው። እንዴት? ድል እኮ ታሪክ ነው። ታሪክ ደግሞ አደራ ነው። አደራ ለሚረከብ ትውልድ ሞራሉ የተስተካከለ የድል አቅርቦት ማውረስ የትውልድ ቅብብሎሽን ተቋማዊ የማድረግ አቅም አለውና።
ቀደም ባለው ጊዜ የጀርመን የሞድ ኢንደስትሪ መልክን፤ ቁመናን ብቻ ነበር የሚያወዳድረው። አሁን ሰብዕናን ሆኗል። ስለዚህ በትጋት ሊሠራ የሚገባው በሰብዕና ላይ ይሆናል። እርግጥ ነው ሽልማት ያበረታታል። ሽልማት ህሊናን ያሰለጥናል።
ሽልማት ኃላፊነት ተቀባይነትን ያለሰልሳል።
ሽልማት የህይወት ታሪክን ያድሳል። ወዘተ። እግዚአብሄር የሰው ልጆችን የፈጠረው ለምስጋና ነው። ምስጋና ደስታን መስጠት ነው። ይህ የጽድቅ ጉዞ ነው። መሸለሙም።
እንዲህ ባለ አገራዊ በገዘፈ ተቋም፤ ስንት ግብር በተከፈለበት ተቋም ለይቶ መሸለሙ አትራፊ አይመስለኝም። ትውልድ እንደ ሹግ በየዘመኑ በተማገደበት ተቋም ከንግግር ጀምሮ ጠንቃቆች፤ ህግ አክባሪወች ሊመሩት ይገባል። የታረመ አንደበት ከሰብአዊነት ጋር ያዋህዱ አብነቶች ያስፈልጉታል። አንድን ተቋም የሚያስከብረው የአቋም ይሁን የግብሩ ጥራቱ እና ጥረቱ ነው። ይህን ካሳካ የግለሰቦች ጥገኛ ሊሆን አይችልም - ተቋሙ። የአገር መከላከያ ሠራዊት መሪወች ከየትኛውም ተቋም በላይ ህብራዊነት፤ ማህበረሰባዊነት፤ ሰብአዊነት፤ ተፈጥሯዊነት እና ህግ አክባሪነት ላይ ቢያተኩሩ በራሱ ጊዜ ህዝብ ያቅፋል፤ ይደግፋል።
መከላከያ ላይ የታረመ አንደበት፤ ሉዓላዊ ምልከታ ያስፈልገዋል። ሰዋዊ ጸጋን ምራኝም ማለት ይኖርበታል። ተፈጥሯዊ ምርቃት ያስፈልገዋል፤ ይህ ደግሞ የሚገኜው እግዚአብሄር ለፈጠረው የሰው ልጅ አብሶ ለራሱ ወገን የሚኖረው ርህራሄ ሲኖር ነው። መከላከያ ለእኔ የአገር #ሃኪም ነው። ሃኪምነት ሰብዓዊነትም ነው። ሰብዓዊነት ደግሞ ከዞግ በላይ ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ደህና ሰንብቱልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
29/10/2025
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ