ይድረስ ለኢትዮጵያ ጤና ሚር // ሚር ክብርት #ዶር #መቅደስ #ዳባ። አዲስ አበባ።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።


ጤና ይስጥልኝ ክብርት ዶር መቅደስ ዳባ እንዴት ሰነበቱ። ዕንቅልፍ አጥቼ ያደርኩበትን ውስጤን ልልክለወት እንሆ ወሰንኩኝ። ትናንት የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስተር ያወጣውን መግለጫ ከፌስቡክ ፔጁ ላይ አግኝቼ ደጋግሜ አንብቤዋለሁኝ። በአሉኝ የማህበራዊ ሚዲያወች እና ኢሜሎቼም ተጠቅሜ ሼር አድርጌዋለሁኝ። እንዲህ አይነት ድንገተኛ እና አጣዳፊ ሥም አልቦሽ ወረርሽኝ ሲገጥም ከፍጥነት ጋር እርምጃ ለመውሰድ የተደረገ ንቅናቄ መኖሩን አረጋግጫለሁኝ።
እርግጥ ነው በግንባር ቀደምትነት ለተሰውት የጤና ባለሙያወች መግለጫው ምንም ያለው ነገር የለም የሚል ቅሬታም አንብቤያለሁኝ። በመግለጫው ላይ ሰመዓታቱን ባልደረቦቹን የጤና ሚር አስቦ ቢሆን ቀጣዩን የገዘፈ ፈተና ለመቋቋም አቅምን በቅንነት ለማሰባሰብ ሆነ በተስፋ እነኛ ንጹኃን የህክምና ባለሙያወች ይሠሩ ዘንድ ይረዳቸዋል። ባለሙያወቹ በተቋማቸው ላይም ሙሉ ዕምነት አሳድረው #አለኝታችን የእኛነት ስሜት ፈጥሮ ውስጥነትን በፈቃደኝነትን ሊፈጥር ይችላል።
በሌላ በኩል ይህንን ክፍተት አቻችሎ ችግሩን በወል ለመቋቋም #በሰፊነት ህሊናን ማሰናዳት የሚገባ ይመስለኛል። የጎደለውን ነገር አቅም ያለው እየሞላ፤ የጎበጠውን ነገር እያቃኑ ቢያንስ የአስቸኳይ ጊዜ የወረርሽኙን መከራ ለመግታት በብሄራዊ ጉዳዮች ላይ መረባረብ፤ የተዘናጉ ቦታወች ላይ እንዲህ አክብሮ ማስታወሻ በመላክ መሳተፍ ያስፈልግ ይመስለኛል። "ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት" ለዚህ ጭብጤ ልኩ ይመስለኛል። #የነፍስ #አድኑን እንቅስቃሴ በቅንነት ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህን የገዘፈ ችግር አብረን ሆነንም ከረታነው ዕድሎኞች ነን። #የጋመ ችግር ምድራችን ላይ ተፈጥሯልና። ለዓለም ዓቀፋ የጤና ድርጅትም አቅም ያለው ሁሉ በትህትና ማሳሰብ የሚገባ ይመስለኛል። ነፍስ ማዳን ይቅደም!
#በጣም ተጨንቄ ነው ያደርኩት።
የወረርሽኙን ዜናውን ከሰማሁበት ቅጽበት ጀምሮ እንቅልፍ አልነበረኝም። የኮቢድ ጊዜም እስር ቤት ላሉ ወገኖቼ እጅግ ይጨንቀኝ ነበር። አሞኝ ተኝቼ እማስበው እነሱን ነበር። ቤተሰብ ከአሜሪካ መጥቶ እያስታመመኝ፤ ሙሉ አትኩሮቴ በእስረኞች ላይ ነበር። አስታውሳለሁኝ መአዚ ከ200 እስረኛ ጋር ስለነበረች በጣም በትጋት በዚህ ዙሪያ እሰራ ነበር። ሰፊ የሆነ ንቅናቄም ፈጥሬ ነበር። እሷ ከጉዳይ ባትጥፈውም። እኔ ግን በተሟላ ትጋት ነበር የሠራሁት።
ለወቅቱ ጤና ሚ/ር ለዶር ሊያ ታደሰ በተከታታይ እጽፍ ነበር። በኋላ ለመአዚ ቦታ ቀየሩላት። ከዛም ከእስር ተፈታች። ጥረቴ አብረዋት ለታሠሩት 199 ሴቶችም ነበር። ትልቁ ችግር አሁን እስረኞችን በሚመለከት ምንም ዓይነት የተሟላ መረጃ የለንም። ከ10- 20 ሺህ የፋኖ እስረኞች አፋር በርሃ ላይ ታስረዋል የሚል መረጃ ነበር። ከዛ በኋላ የሁኔታው ዕልባት የት እንደደረሰ አናውቅም።
አብን ለአማራ ህዝብ እንደ ስለት ልጅ የሚታይ ነበር። የሱስ ያህል ነበር በብርቅነት ከሊቅ እስከ ደቂቅ መላ የአማራ ልጆች እና የአማራ ወዳጆች ያዩት የነበረው አይዋ አብን። የናፍቆት እሸትነቱን ፈቅዶ እና ወዶ ካለጊዜው አንኮላሸው። የትውልድ መሆኑ ቀርቶ በተከበረው ልክ #መዝለቅ ተሳነው። ማህበራዊ መሠረቱ ጠንካራ፤ የአማራ ተስፋ አቅኚ አሳኪ ተብሎ ታስቦም ነበር። ግን የአያያዝ ሁነት ማነስ እንሆ በሰላም ለሚታገሉት ለታሠሩ ብዕረኞች እንኳን መሆን ተሳነው። መረጃው ነቀል ተከል ነው። አይዋ አብን እንደተደራጀበት ዓላማ አይደለም ለደጋፊወቹ፤ ለሞጋቾቹም ሳይቀር የአብርኃም ቤት ሊሆን በተገባ ነበር። ግን ተሳነው። ክብርን ለማዝለቅ የክብር ግኝትን አክብሮ መገኜት ይገባል።
#የሆነ ሆኖ ………
በ14/2025 "የአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ ኔፓድ የሚኒስትሮች መድረክ ለተዋልዶ ጤና ትኩረት በመስጠት ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማፋጠን እና የአፍሪካን ስነ- ህዝብ አቅም መጠቀም" በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ይታወሳል። ክብርቷም ንግግር አድርገዋል።
የአፍሪካ ተምሳሌት በሆነችው አገራቸው ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ዓይነት ፈተና ሲገጥም ፍጥነት፤ ውስጥነት፤ እናትነት፤ እርህርህና፤ አዛኝነት፤ አይዟችሁ ባይነት ለፓን አፍሪካኒስትነቱ ጸጋውን ያጎላዋል እና እባከውን ክብርት ሆይ መስዋዕትነትን ለተቀበሉ የሥራ ባልደረቦቸወትን መጽናናትን ያገኙ ዘንድ ቤተሰቦቻቸው አይዟችሁን ይመግቧቸው ዘንድ በትህትና እያሳሰብኩኝ ፤ እስር ላይ ለሚገኙት ወገኖቸወትም ልዩ አትኩሮት ይስጡልን ስል በአክብሮት አመለክታለሁኝ።
#ሃሳብ ባይፈራ ቢያንስ በዚህ ዘርፍ ተጨማሪ ጫና ለኢትዮጵያ መንግሥት ባልኖረ ነበር።
የሚገርመኝ ሃሳብ እንደምን ይፈራል የመንግሥት አካላቱ? ፋክት በእጄ አለ ለሚል ለየትኛውም የመንግሥት አካል ነፍስ አድን የሚሆኑለትን ሞጋቾችን ሳያግት ወይንም ሳያስር በፋክቱ ሊረታ ይችላል። ከእነሱ ጠቃሚውን ወስዶ የማይጠቅመውን መጣልም ይችላል። ሁሉ በእጁ ሁሉም በደጁ ነው። #የምድር #አምላክ አይደለምን መንግሥት? ፋክት ካለው ወይንም ከኖረው፤ ምንም ዳገት የለም። ለእኔ ግን የምድር አምላክ ሊሆን የሚገባው የአንድ አገር መንግሥት ሳይሆን፤ የአንድ አገር ጨዋ፤ ጭምት #ህዝብ ሊሆን ይገባል ባይ ነው። ይሄ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ቤት ያለ ዳቦ ነው። ግን በተስፋ አስበዋለሁ፤ ለእናት አገሬ ጭምት ህዝብም እመኝለታለሁ።
እኔ እንኳን በብዙ ውርክብ፤ እንግልት አለ በምለው ዕውነት ዙሪያ በጣም ለተከታታይ ዓመታት የቀረ የፖለቲካ ተቋም፤ የፖለቲካ ሊቃውንት ጥቂት ይመስለኛል በእኔ ብዕር ያልተሞገተው። ሞጋች ሊከበር እንጂ ሊንገላታ አይገባም። ልዩ ሥጦታ ነውና።
1) የሃሳብ የብዕር ይሁን የንግግር ዲያሎግ ሙግት አገር ጠቀም የሆነ #የጠራ ሃሳብን ያፈልቃል፤ ያሰብላልም።
2) የጎሼን ሰንከልካላ መንገድ ያስተካክላል፤ ያርማል። መሃንዲስም ነው።
3) ሙግት ለደፋር ፖለቲከኛ የአቅጣጫው እዮራዊ መኖ ልዩ ሥጦታውም ነው ብዬ አስባለሁኝ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ይፈራል። ሞጋቾችም ይሳደዳሉ።
በሁሉም አቅጣጫ ነው የሚሳደዱት። ከገዢው ብቻ ሳይሆን ነፍሳቸው ትርትር ከምትል ተፎካካሪ ይሁኑ ተቃዋሚ በፖለቲካ ድርጅቶችም። ከዛም ባለፈ አገር ቤት የሚገኙ ሞጋቾች በገዢወች እንዲህም ይታሰራሉ። ከዚህም በባሰ ሁነት ይሰወራሉ፤ ወይንም ይገደላሉ። ወፍ ያወጣቸውም ይታሰራሉ። ከመሞት መሰንበት ይሻላልና። ይህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መቼ እንደሚቆም አላውቅም።
የኢትዮጵያ #እስር ቤቶች መቼ ከፖለቲካ እስረኞች ነፃ እንደሚሆኑም ፈጣሪ ነው የሚያውቀው። አሁን ለክብርት ጤና ሚኒስተሯ ለዶር መቅደስ ዳባ በትህትና እማሳስበው እስር ቤት ለሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች፤ ተጠርጣሪ የወንጀል ይሁን የፍትኃብሄር እስረኞች፤ ፍርደኞችም ቢሆኑ #ልዩ ትኩረት ይደረግላቸው ዘንድ ነው አቤቱታ እማቀርበው ለኢትዮጵያ ጤና ሚር እንደ ተቋም፤ ለክብርት ዶር መቅደስ ዳባም በግል። ሆስፒታል የነበሩ፤ በማገገም ላይ የሚገኙ እስረኞችም ይኖራሉ። እነኝህ እስረኞች በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ውስን እንደሚሆን አስባለሁኝ። ስለዚህ ለየት ያለ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።
#ፍጹም የሆነ ሰዋዊ ትኩረት ለእስረኞች ከኢትዮጵያ ጤና ሚር እጠብቃለሁኝ። ከዚህ እኔ ከምኖርበት ሲዊዘርላን ማንኛውም የግል፤ የህይወት ጫና አራግፌ እመመጣው በተቀደሰው፤ ሰዋዊ በሆነው የህክምና አያያዛቸው ነው። ነጩ ልብሳቸው ፍጹም የሆነ መጽናናትን በፍቅር ይለግሳል። ገና የቢንተርቱር ሆስፒታል ግርማ ሞገሱን ሳየው ተስፋየ ይሞላል። ከበር ነው ፈገግ ብለው አስተናጋጆች የሚቀበሉት። በዛ በአውቶብስ ሳልፍ እንኳን እንደ ቤተ እግዚአብሄር በልቤ እሳለመዋለሁኝ።
ህንፃውን ሳየው የመኖሬ ግትልትል ፈተና ሁሉ #ሽሽት ይጀምራል። እነሱን መርቆ በምላት የሰጠ አምላክ ለኢትዮጵያም ይሰጥ ዘንድ አዘውትሬም እማጸነዋለሁኝ። ይሁንልን። ይደረግልን። አሜን።
#የማከብራችሁ፤ የምናፍቃችሁ የአገሬ ልጆች ሆይ!
መተዛዘን - አይክበደን። መተዛዘን - አያስጨንቀን። መልካምነት ጉዟችን ቢያቃና እንጂ መሰናክል አይሆንም። ሁልጊዜ ለተፈጠርንበት የሰውነት ታላቅነት በርህርህና እንቁም። ትዕዛዝ አይደለም። ትህትናዊ አክብሮታዊ የግል ዕይታየ ነው።
በሌላ በኩል እዛው ጅንካ ከተማ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞች ሊኖሩ ይችላሉ። ከአዲስ አበባ ውጪም በመላ ኢትዮጵያ ከተሞች እስረኞች ይኖራሉ። እነሱንም በሚመለከት ልዩ ትኩረት ይሰጥ ዘንድ ነው የጤና ሚር በትህትና እማመለክተው። በሽታው እስር ቤት ብቅ ካለ ኢትዮጵያ ከምትቋቋመው በላይ ሆኖ በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል። ከውስጥ ብናስበው በሰው ሰራሽ ችግር በሰው እጅ ሰወች ከሚጨከንባቸው ይልቅ እንዲህ መሰሉ ድንገቴ የተፈጥሮ አደጋ እንዳይገጥመን ውስጣችን ለቸርነት ቢተጋ መልካም ነው። ችሎት የማይኬድበት የእዮር ውሳኔ ከሁሉም ይከብዳልና።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
13/11/2025
ሲዊዘርላንድ ዙሪክ ክ/ አገር ቢንተርቱር ከተማ።
እግዚአብሄር ሆይ! ምህረትን ላክልን። አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ