29.11.2019 ምን እግር ጣለው ፋኖ ከጠቅላይ አብይ አህመድ አንደበት ለዛውም ለዬምስራች? ለመሆኑ (ፋኖ )የአማራ የህልውና ተጋድሎ የታገለው ለአምልኮተ አብይ ነበርን?

ምን እግር ጣለው ፋኖ ከጠቅላይ አብይ አህመድ አንደበት ለዛውም ለዬምስራች? ለመሆኑ (ፋኖ )የአማራ የህልውና ተጋድሎ የታገለው ለአምልኮተ አብይ ነበርን?
 

 
"የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል" አሉ ሊሂቃኑ። የምሥራቹን ሰማን። ምን እንዲህ እንደሚያጣድፍ አይገባኝም። የምሥራች የሁሉም ለሁሉም ቢሆን እንደለመደብን አብረን በደለቅን። እኛ እንደሳቸው አልደላን። መከራ ሲመጣ ፊት ለፊት ወጥተን ስንሞግት እሳቸው ድብዛቸው አይገኝም። ሽርሽር ይወጣሉ። ለሃኒ ሙን ብቻ የተፈጠሩ ጠሚር። ለጭብጨባ ደግሞ ማን ቀድሟቸው። መጥኔ ብለናል።
"ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዛርማ እንኳን ደስ አላችሁ" ማለታቸውን ሰማን ዶር አብይ አህመድ። ምነው ዛሬ ፋኖ እንዴት ትዝ አላቸው? አንቦ ላይ ሹመታቸውን ሲያስበስሩ "ቄሮ ጀግናው ያሰኙ ዛሬ ደስታውን ልናበስርህ መጥተናል" የተባለው ቄሮ እንጂ ፋኖ አልነበረም። ይልቁንም ሲያሳድዱት ፋኖ ማለት እኔ ነኝ ያሉትን ብጄ አሳምነው ፅጌ፣ በአደባባይ እሬሳውን ሲያንገላቱ የትዳር አጋር አስረው ፅንስ ሲበቀሉ ነው የታዬው። የልዩ ኃይሉም ሲረሸን እዬታደነ ነው ያዬነው።
የአማራ የህልውና ተጋድሎ ለአጤ አብይ የብልፅግና ፓርቲ አልታገለም፣ ለሳቸው የሰብዕና ግንባታም አልነበረም ያን ያህል መራራ መስዋዕትነት የከፈለው፣ እሳቸው ከነመፈጠራቸው ከቶውንም ተጋድሎው አያውቅም ነበር ተጋድሎው አህዱ ሲል።
ለአማራ የህልውና ተጋድሎ አብይ ትናንትም አጀንዳው አይደለም ወደፊትም አይሆንም። የብልፅግና ፓርቲው ምስረታም፣ ክስመት ይሁን ክስለት ለተጋድሎው አጀንዳው አይደለም። የተጋድሎው የህልውና መሰረት መኖርን ለማኖር አማራ የአገር ባለቤትነቱን በዘለቄታ የሚረጋገጥበትን ሥርዓት በብሄራዊ ደረጃ እንዲፈጠር መታገል ነው። አማራ ባበጃት አገር ባይተዋር ሆኖ መኖሩ ማብቃት አለበት።
አሁን የሳቸው ፓርቲ ኦህዴድ ተጋድሎውን ጠልፎ በባሰ ሁኔታ አማራ ከእርስቱ በግፍ እዬተፈናቀለ ነው። ፋኖ በባዕቴ መቶ ሺህ ህዝብ ይፈናቀልልኝ ብሎ አልነበረም ደም የገበረው። ፋኖ በዬሄደበት የአማራ ልጅ እያታደነ በቀስት፣ በድንጋይ፣ በሜጫ እንዲገደል አልነበረም አጥንቱን የከሰከሰው።
ፋኖ የአማራ ሊሂቃን ተነጥለው በቀልሃ በባዕታቸው በግፍ ተጨፍጭፈው እንዲገደሉ አይደለም መኖርን የገበረው፣ ፋኖ ተስፋዬ ያለው የአማራ ሊሂቃን ይመቸናል ባሉት ድርጅት ተደራጅተው በነፃነት እንዲታገሉ እንጂ እዬተለቀሙ ስበብ እዬተፈጠረ የካቴና ስንቅ እንዲሆኑ አልነበረም የታገለው።
ፋኖ የሁሉ መናህሪያ የሆነችው አዲስ አበባ የስጋት ቀጠና እንድትሆን፣ የአንድ ዞግ እንዳሻው የሠርግ እና የመልስ መባ እንዲሆን አልነበረም ከህውኃት ጋር መድፍ እዬረገጠ የተፋለመው። ፋኖ ሉዑላዊነት ይከበር ብሎ ሲታገል ሉዕላዊነቷን ለማይቀበል አማፂ መረጃ የሚያቀብል መሪ ሆኖ እንዲመጣ አልነበረም የታገለው።
በህወኃት ዘመን እስረኛ ልጆቹ ከእስር ተፈተው ወግ ማዕረግ አግኝተው ድረው ኩለው ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ እንጂ እንደገና እነ ፓይለት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በተገኙበት ታድነው እንዲገደሉ ሌላ የሰቀቀን ኑሮ እንዲኖሩ አይደለም የታገለው፣ ፋኖ የዓለም የብዕር ፋና የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የብዕር ብሌኑ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ በመንግሥት ደረጃ ሞት እንዲታወጅባቸው፣ የቁም እስረኛ እንዲሆኑ አይደለም የታገለው።
ፋኖ ኢትዮጵያዊ ነፍሰጡር እናት ከአሁን አሁን መጥተው ገደሉኝ በማለት ፅንሷ እንዲታወክ አይደለም የታገለው፣ ፋኖ ባዕድ ህዝብ እና ወገን ህዝብ የሚል ጠቅላይ ሚኒስተር በፍፁም አልናፈቀውም። ፋኖ ነፍጠኛ ሰበርነው መንግሥታዊ ዓዋጅ ሽው አላለው። ፋኖ በራሱ ተጋድሎ ላስገኜው ድል በባይታዋርነት እንዲጠበስ፣ እንዲቁላላ፣ እንዲነድ አልነበረም የታገለው።
ፋኖ አማርኛ ቋንቋ እንዲህ እንዲዋረድ፣ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ እንዲነድ፣ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ደመራ እንድትሆን አልነበረም የተጋው። ፋኖ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የራያ፣ የመተከል ጉዳይ እንዲህ አቧራ እንዲለብስ መዘባበቻ እንዲሆን አልነበረም ።
የታገልነውም፣ ድሉም የኛ ብቻ ነው ለሚል የተራራ ትምህክትም አይደለም ፋኖ የታገለው። ፋኖ ጨለማን ሸኝቶ ያልደከመው ሌላ አረመኔያዊ ጨለማን ለመቀበል አይደለም የታገለው። ወይንም አማራ በገዳ ሥርዓት ጥምቀት ለመፈፀም የሥነ ልቦና፣ የባህ፣ የትውፊት ወረራ ትዝ ብሎት አይደለም የታገለው።
ዴሞግራፊው ለአማራ ነው። ይህ የሚጠፋን ይመስላቸዋል። ልብ አለን። ቀድሞ ነገር ምን ሲል ትዝ አለዎት ፋኖ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ? የሰበራችሁት፣ ከሥልጣን በነቂስ ያራገፋችሁት፣ የማረካችሁት መንፈስ እንዴት የምሥራች ተጋሪ ሆኖ ታሰበ?
ከዶር አንባቸው ህልፈት በኋላ? ይህ አሪዎሳዊ መንፈስ ከኢትዮጵያ ምድር ይተን ዘንድ ፀሎታችን ይቀጥላል። ማጭበርበር ዕድሜ ቢኖረው ለመንፈቅ ነው። ከዛ በኋላ የዶግ አመድ ይሆናል። ንፋስ ናፋቂ የለም። ወይንም የአሰር ቃርሚያ ለቃሚ የለም።
ስለዛርማ ተነስቷል ድሉ ሊገኝ ሁለት ወር ሲቀረው ብቅ አለ፣ አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሲታወጅ ወደ አፎቱ ተመለሰ፣ ከዛ ተደመረ። ያ የአማራ ክልል ድንቅ የድጋፍ ሰልፍ ፈርጥ አልተባለም። የድል አጥቢያ አርበኛው ዛርማ ያደረገው የድጋፍ ሰልፍ ግን ፈርጥ ተብሏል። ከዛ በኋላ ድምፁም የለም። ሁሉም ተመዝግቦ ተይዟል።
አክተሩ ጠቅላይ ሚኒስተር ለባርነት፣ ለሌነት" እንኳን ደስ አላችሁ" ሲሉ ልባቸውን የገጠሙላቸው የዕንባ ሚኒስተሯ ደግሞ በፋኖ ላይ እርምጃ ይወሰድ ሲሉ የጦማሪ ስዩም ተሾሞ ቧንቧ ሆነዋል።
እንዲነገር የሚፈልጉትን ወዘተረፈ አንደየት አላቸው በዛ ያስነግራሉ እሳቸው ደግሞ አዝለኙን በልስልሱ ለብ አድርገው ይለቁታል። እነ ውልቅልቅ ሙርቅርቅ። መቼም እንደዚህ ዘመን አንድ ሰው ወዘተረፈ ካራክተር ወክሎ ሲጫወት የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ገጥሞት አያውቅም።
ፋኖ የሚለው የአማራ የማንነት ተጋድሎ በሚለው ይወሰድልኝ።
ሥርጉተ© ሥላሴ
Sergute©Selassie
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
አማራነት መንጆነት አይደለም።
አማራነት መሟያነትም አይደለም።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።