29.11.2019የእነ አብረን እናልቅስ ዝልቦ ሬሳዊ ሃሳብ።

 

የእነ አብረን እናልቅስ ዝልቦ ሬሳዊ ሃሳብ።
ሌላ አማራጭ የለም ከአብይወለማ ውጪ እንደ ዓዋጅ የሆነ ይመስለኛል። እኔ ሥርጉተ ሥላሴስ እላለሁ ከእነሱ ውጪ ከአብይወለማ እምስ ዘመን ኢትዮጵያ መሽቶ የማይነጋላት ከሆነ ለምን ተቃዋሚ፣ ተፎካካሪ፣ ተቀናቃኝ፣ ተደማሪ የሚባለው የአቅም ተጠማኝ የፖለቲካ ድርጅት ሁሉ ስለምን ወደ ሲቢክስ ማህበር አይቀዬርም? ምን አደከመው?
ለመሆኑ ይህ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት ሲቋቋም ትንበያ ነበርን? አብይ የሚባል መሪ እስኪመጣ ብቻ ብለው ነበርን ትግል የጀመሩትን? አዬ የአቶ ለማ የዴሞግራፊ የህሊና ነቀላ እና ተከላ ስንቱን ሰው ስልብ አደረገው መሰላችሁ?
ህውኃት ቢኖርበትም ከጅጅጋው መፈናቀል ጀምሮ ያሉ ሰብዕዊ ቀውሶች "ከእነሱ ውጪ" የሚል አዲስ ቀኖና ሳይሆን እንደ ዶግማ እንድንቀበልም ነው ዘመቻው የአብይዝም የካድሬዎች የወግ ቋት።
ዛሬ እኔ እንደምታዘበው ከሆነ ህወሃት የሚወገዝበት ያህል ኦነግ አይወገዝም። በተደማሪ ተቺዎች ተመስጥሮ የተያዘው ኦነግ ወገን ነው። ለምን? ምኑ አዚም ይሆን እንዲህ ልንቁጥቁጥ፣ ልፍስፍስ ያደረገው መንፈሱን ሁሉ።
የተጣበቀ ዕይታ ነው የሚደመጠው። ወላድ በድባብ ትሂድ እንጂ የተሻሉ፣ የበቁ ዓራት ዓይናማዎች ኢትዮጵያ አሏት። መሪ ሊሆኑ የሚችሉ። የሚበልጡም ከአብይወለማም፣ ከታከለወሽመልስም፣ ከንጉሡወደመቀም።
በቅድሚያ ታማኝነት የሚጠይቁ የሉዕላዊነት አመክንዮች አሉ። ኢትዮጵያዊነት በውስጥነት እንጂ በምላስ ገበር አይገለፅም። ኢትዮጵያዊነት የውስጥ ፅላት ሲሆን እንዲህ አይወዛወዝም። የኢትዮጵያ ፓርቲ ለማለት የወለሌ ገበታ የሚል ተልባ ሥፍር ለገናናው ማንነት በፍፁም አይመጥነውም።
ኢትዮጵያዊነት በሰከነ ጥበብ እንጂ ጎርፍ በከመረው ዕድፍ ዕሳቤ የተፈጠረ ማንነት አይደለም። ትውልድ የቆመ ይመስል "ከእነሱ ሌላ" የሚባለው ችኮ አገላለፅ የተጋጠ ሃሳብ ነው። የማህበራዊ ንቃተ ህሊና እና የተፈጥሮ ሂደትንም የከዳ ነው።
መኖር ዕውነት ነው። መኖርን የሚያኖረው የትውልድ ሂደትም መሪ የመፍጠር አቅሙ ሰው ሰራሽ አይደለም ተፈጥሯዊ እንጂ። ኢትዮጵያ የልጅ ድኃ አይደለችም።
ችግሩ የሬሳ ሃሳብ ባይረስ ተሸካሚዎች አቅም ብቅ ባለ ቁጥር አጨዳ ላይ ስለነበሩ አሁንም ስላሉ ነው። ለምሳሌ ዶር አንባቸው መኮነን ጠቅላይ ሚኒስተር ለመሆን ምን ያንሳቸው ነበር?
የተማሩ፣ አንደበተ ርቱዑ፣ በትግል የቆዩ፣ በተመክሮ የሰከኑ፣ ኢትዮጵያን እንደ ነፍሳቸው የሚወዱ፣ ቅርብ፣ ትሁት፣ ደፋር ነበሩ። ግን ቀድሞ መወገድ ነበረባቸው ከምርጫ 2012 ዓም በፊት። ከእነሱ ውጪ ሌላ የለም እንዲባል አማራን በሁሉም መስክ የመመንጠር ተግባር የሆነው የዴሞግራፊ ተልዕኮ ይኽው ነው።
ኢትዮጵያ ዶር አንባቸው መኮንን ለማብቃት ምን ያህል መዋለ ንዋይ፣ መዋለ መንፈስ አወጣች? ምን ያህል ደከመች? መሰሉን ለማፍራት ምንስ ያህል መድከም ይኖርባታል ለወደፊት? እንዲህ ባለ ብክነት ነው አገር ተስፋዋ የሚመክነው። ተስፋዋ የሚሟሟውም።
ሌላው በተለያዬ አቅም ነክ ሁነቶች ሞጋች ሆነው የሚወጡ፣ ብቁ ሆነው ብቅ የሚሉ ነፍሶችም ይታደናሉ። ለዚህ የኢንጅነር ስመኜው አሟሟት እና የታሪክ ሽሚያና ሸፍጥንም ማንሳት ይቻላል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የትንታጉ የወጣት ፖለቲከኛ ክርስትያን ታደለ የሴራ ድርም ብቃት ያለው ትውልድ እንዴት እንደሚፈራ ትልቅ ማስረጃ ነው። ዴሞክራሲን በቁሙ ያከሰለ ሸፍጥ ነው። ፀረ አማራነትንም በግልፅ ያወጀ ጥቁር መርዶ ነው። ስለሆነም የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ትግሉ ይቀጥላል በእልህና በቁጭት።
ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት፣ የገዳ ሞገሳ ተጠማቂዎችን ጨምሮ የሚፈጥሩት ወጀብ ትውልዱ ተስፋ አጥ ሆኖ በአንድ ሰው አምልኮ ብቻ ተንበርካኪ እንዲሆን የሚያደርግ የሥነ ልቦና ዝለት ይመስለኛል። ይህም ትቢያን የናፈቀ ፍግ መንገድ ነው።
ትውልዱ አማራጭ ተስፋ እንዳይኖረው ማድረግ ዳፍንት ዕይታ ነው። ህወሃት ኮትኩቶ ያሳደጋቸውን አብይወለማን መሰል ካድሬዎች ስታመልክ፣ በራሱ መንገድ ነጥሮ የወጣውን ጀግናህን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ብቃት፣ ፅናት፣ ተስፋነት፣ ልቅና ስታብጠለጥል፣ ስታቃል ወይንም ስታንኳስ አይደለም ዛሬ በትናንት ውስጥ አንተ እራስህ ያልነበርክ ስለመሆንህ ዳኛውም ችሎቱም እራስህ መሆንህን መቀበል ግድ ይላል።
አማራጭ የማይኖረው ዓላማ ላልነበረው የወጀብ አምላኪ እንጂ የተፈጥሮን የሂደት ህግጋት ለተቀበለ መንፈስ እያንዳንዱ ቀን፣ ሰዓት፣ ሰከንድ መሪ ይፈጠራል።
ማስተዋል እሮ ሲሆን ነገ ከመምጣቱ በፊት ይደምናል።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።