ጥሞና። የዛሬ የፓርላማ ውሎ በጨረፍታ ዕድምታ። 30.11.1020

ጥሞና። የዛሬ የፓርላማ ውሎ በጨረፍታ ዕድምታ። 
 
 No photo description available.No photo description available.
 
መቅድም።
የተቆለፈባቸው ጠቅላይ ሚኒስተር ዘገባ ከቅድመ እስከ ድህረ ዕድምታ በጨረፍታ። አስፈላጊ ከሆነ እመለስበት ይሆናል።
በር።
ጥሞና የሚጠይቁ ሁለገብ ጉዳዮች አሉ። ዳንኤሏ ኢትዮጵያ በመጠነ ሰፊ ቀውስ ውስጥ ነው የባጀችው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ጥሞና ያስፈልገዋል።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ዝርዝር መግለጫ አሰምተዋል። ለሳቸውም ለተናጋሪው ለአድማጩም መጦመን ያስፈልጋል። መቼ ይሆን የሳቸው የጥሞና ጊዜ?
የሳቸው የሥልጣን ዘመን ችግር ሁሉ ምንጩ፣ መነሻ መድረሻው ህወሃት ብቻ ነው ብለዋል። ዕውነት ይሆን?
እሳቸው እና ካቢኒያቸው ደግሞ በመርዛማው ህውሃትወኦነግ ህገ - መንግሥት ተኮትኩተው ያደጉ አሁንም ያን እናስከብራለን ብቻ ሳይሆን እንደ ቃለ አቀባያቸው እንደ አንባሳደር ሬድዋን ገለፃ እናሰርፃለን ተብለናል። እንዴት እናገናኜው?
ያን ሲኦል ህገ - መንግሥት ለማስቀጠል በኮፒ ራይት እፍግብ ይህ ሁሉ ድቀት ተፈጥሯል። በአጭርም ይቋጫል ብዬ አላስብም። መሬቱ እራሱ ተዋጊ ነው። ዞጋዊ አደረጃጀቱም ገዢ መሬት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ኦህዴድንም ኦነግንም ንክት አላደረጉም። እንዲያውም ለስሜኑ ጦር ደጀን ነበር ኦሮምያ እና ጉምዝ የፀጥታ ኃይል ብለውናል። ቤቴ እስኪነቃነቅ ከትከት ብዬ ስቄያለሁ፣ የታሪክ ሽሚያ። ህም።
በጭልፋ የተሰማኝን።
ዛሬ እንደ ቀደመው ሰው ሳያውቃቸው በ2016/17 ሲያውቃቸው 2018 አዳምጣቸው እንደ ነበረው በጥሞና አዳምጫቸዋለሁኝ።
ከተጀመረ ስለነበር ያገኜሁት፣ በተጨማሪም ረጅም ስለሆነም ደግሜ በጥሞና ማዳመጥ ይኖረብኛል።
ከዚህ ውስጥ የሰባዕዊ መብት ኮሚሽን ላይ ያነሱት ትክክል ነው ብዬ መቀበል እችላለሁ።
የሠራዊቱ የእግር ጉዞ እማውቀው ስለሆነ አምነዋለሁኝ። ማንም አያደርገውም ላሉት ገበሬ አደራጆች ያደርጉታል። እኔ አድርጌዋለሁኝ ሴቷ። ገበሬ አደራጅ ስለነበርኩኝ።
ለዚህም ነው የሞገዱ ንቅናቄ ግንቦት 7 ከኤርትራ ጓንግ ላይ ነዳጅ የያዘ መኪና አጋዬሁ ሲል እያንንዷን ቀበሌ መንደር ስለማውቀው ውሸታም ብዬ በወቅቱ የሞገትኩት።
የስሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ከሰው በላይ ተፈጥሮው ይዋጋል። ህወሃትም የተማመነው ይህን ነበር። ለጎንደሬዎች ደግሞ ውኃ ከወንዝ የመቅዳት ያህል ያን የተፈጥሮ ምሽግ ለማላመድ አይቸግረውም። ውስጡ የተቃኜበት ደሙ ነው።
የድሉ ሚስጢርም በአጭሩ የተደመጠውም ይህ ነው። እንተዋወቃለን ያለ መሪ፣ ያለ አስተርጓሚ።
ስለዚህ የሠራዊቱ የእግር ጉዞ ድካም ሰላማዊ ሳይሆን በጦርነት ለዛውም ቀድሞ ገዢ መሬቱን ለተቆጣጠረ አጥቂ አካል እጥፍ ድርብ ፈተና መሆኑን ስለማውቅ ይህን ዕውነት እንዳለ እቀበለዋለሁ።
ሌላው ስለ ህወሃት የመወቃር ጠቅላይነት ያነሱት ለእኛ በትግል ለቆዬነው፣ ጎርፍ አምጥቶ ላልከመረን የነፃነት ራህብተኞች አዲስ አይደለም እናውቀዋለን። ለዚህም ነበር ሞጥረን የታገልነው። የታገልነውም ለሥር ነቀል ለውጥ ነበር። በአጭሩ ተቀጬ እንጂ ለአቶ ሽሜ የቀረርቶ ቅርሻ አልነበረም።
ህወሃትን አስተሳሰቡን ነው የጠሉት እንደ ገለፃቸው ለዚህም ነው የስልት ለውጥ አድርገው "ጁንታ" የሚሉት። በአንድ ወቅት ደግሞ ህወሃት እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጥላቻ እንደ ሌለ ገልጠዋል። ቃል በቅያሬ በክት እና በዘወትር እንዲህ ይፍነጥዛል።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ዛሬስ የሳቸው ድርጅት ኦህዴድ ምን እዬሠራ ይሆን? የህወሃት ዕጣ ቢገጥመው ብለው ቢያስቡት ጥሩ ነው። ተያይዞ ካቴና።
ያልገባኝ ስለ አባይ ሚዲያን ያነሱበት ሁኔታ ነው። አባይ ሚዲያ ዝንባሌው ግንቦት 7 ነው። እሳቸው የህወሃት ካድሬ ሳሉ ህወሃትን ሞጥሮ የታገለው አባይ ሚዲያ ዛሬ የህወሃት ልሳን የሆነበት ምክንያት አልተረዳኝም። እማውቀውም፣ እምከታተለውም ሚዲያ ስለሆነ። የተደማጭነት አቅሙን ፋክክሩን ካልፈሩት በስተቀር።
ወይ እኔ ለአባይ ሚዲያ ይሁን ለዬትኛው ሚዲያም የውስጥ ስላልሆንኩ እኔ እማላውቀው ነገር ከሌለ በስተቀር። ልጆቹም ሞጋቾች ናቸው። ይህ ደግሞ የሚፈለግ ሥጦታ ነው። አይም እሺም ሁለቱን ለማስተናገድ ከተፈቀደ ማለቴ ነው።
የሆነ ሆኖ ሌሎችም የገቡኝም፣ ያልገቡኝም ፖለቲካዊ ወለምታዎችንም በስክነት ደጋግሜ አዳምጬ ካስፈለገኝ እመለስበታለሁኝ።
ፖለቲካዊ ወለምታ ያልኩት የጥምቅቱ የጃዋር ንቅናቄ ያለፋትን ሰማዕታት በብሄር ነግረውን ዛሬ ደግሞ ሬሳ ብሄር የለውም ይሉናል። ይህ ቅጥፈት ነው።
ሌላው እሳቸው ከዛ ሥርዓት የበቀሉ ስለ መሆናቸውም የዘለሉት በኽረ ጉዳይ ነው። የህወሃትን ቧንቧ አቶ አባ ዱላ ገመዳን አራጊ ፈጣሪ አድርገው ነው ይህን የሚሉን። እሳቸውም እዚህ የደረሱት የህወሃትን ወተት ገጥግጠው ስለመሆኑ እርሱልኝ አይነት ነው። ለዚህም ነው ቄንጠኛ ቃል ያመጡት። "ጁንታ" እራሳቸውን፣ ድርጅታቸውን፣ ቲማቸውን ለማዳን።
የሚገርመው በአንድ ቦይ የሚፈሰው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መስኖ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የፖለቲካ ዕድምታውን የማምለጫ ስልት እና ስትራቴጂ መሆኑን ሳያዳምጥ ሁሉም "ጁንታ" ይላል። ይህ ማለት ህወሃት 46 ዓመት ተደራጅቶ ለፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ አይደለም እንደ ድርጅት ማለት ነው። እሳቸው ቁልፍ ቤተኛም ነበሩ።
የሆነ ሆኖ እራሳቸውን ድርጅታቸውን አግልለው ወይንም ከጁቪተር ላይ እንደ ቆዩ ነግረውናል። ሁሉም ቀውስ የህወሃት ነው እመኑልኝ ልሳነ አብይዝም የባጀበትን የሁለት ዓመት ተኩል የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ በህዝብ ድምፅ እርጋ እንበለው ነው የሚሉት።
ይልቅ በመቶ ቀናቱ ትትርና በተመሰጥኩበት በድጋፍም በወቀሳ ሙግቱ ዘመን ተቆለፈብኝ ያሉት ያሳምነኛል።
መጀመሪያ ላይ ከነገሩን በላይ ችግር ሊኖር እንደሚችል አስባለሁኝ። የ100 ዓመት ህልም 27 ላይ ወገቤን ሲል። ለዚህ ነው እኔ ያረጠውን የብልፅግናቸው 55በ60 አያንጠራሩት የፓርቲ ምሥረታ ህግ ያላሟላ ነው ብዬ የሞገትኳቸው።
የሚገርመው ብልፅግና የማን ነው ይሉናል እኛም የኦሮሞ ነው እንላቸዋለን ያሉንን ረስተው ኢትዮጵያን ለማበልፀግ የተፈጠረ ብለውናል።
መጀመሪያ ከኢማጅኔሽን አውጥተው መሠረታዊ የፓርቲ ህግ እና ደንብ ተከትሎ ይደራጅ። አንድ የእኔ የሚባል አባል የሌለው ይህን ያህል ባይወጥሩት ጥሩ ነው።
ምራቂ።
ኢትዮ 360 ከዬኔታ አቻምዬለህ ጋር በነበረው ቆይታ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ኢትዮጵያዊው አብርኃም ሊንከን እንዲሆኑለት አቶ ኤርምያስ ዬኔታን ጠይቆ "የኔታም በታምር ከሆነ፣ ታምር ስለማምን" ብሎ ነበር።
ይህ ሃሳብ ቀልባቸውን ስቦት፣ መስጧቸው ኑሮ ዛሬ እኔን እንደ አብራህም ሊንከን ቁጠሩኝ የሚል ዕድምታም አቅርበዋል። ለእኔ ምኞታቸው ርቆኛል።
አቶ ኤርምያስም ምኞቱን ሲያነሳ ገርሞኝ ትንሽ ብዬ ነበር። ረሱት ይሆን " እኛ ዝሆን ነን እንሰብራለን፣ እንበላለን፣ እንቀረጥፋለን። ሥልጣናችን ከተነካ 100 ሺህ በቀን እናርዳለን" ይህ ሰባዕዊነት ወይንስ አውሬዊነት?
ለምራቂዬ መከወኛ።
የአቶ ኤርምያስ ሞጋቹም ነኝ። ነገር ግን እጅግ የምወድለት ከምል የሚናፍቀኝ፣ ለዛ፣ ወዘና ቀለማም ያለው የአቶ ኤርምያስ ለገሰ ጭምት አወያይነት በፍፁም ሁኔታ የምደመምበት ነው። ብቁ አድማጭ ነው። የማያውቀውን ለማወቅ የሚያሳዬው ጥሞና ይናፍቀኛል። አለማወቁን ገልጦ ይናገራል። ማስታወሻም ይይዛል።
ሦስት ጉልህ ጎደሎቹን ቢያስተካክል የመሪነት አቅሙ በዚህ አዬዋለሁኝ። ለባልደራስ ድጋፍም ሆላንድ ላይ በነበረው የሰብሳቢነት ሚና እርጋታው መስጦኝ ከሥር ፅፌ ነበር። የዛሬ እርዕሰ ጉዳዬ ስለማድመጥ ልፅፍ ነበር በአጋጣሚ ይህ ቀደመ እንጂ።
ተምሬውማለሁ። አድማጭ የሆነ አለቃዬም ጓድ ገብረመድህን በርጋም ተቋም ነበር። ማድመጥ አርት ነው። የአመራር ልቅና መክሊት። ጥሩ አድማጮች ብቁ መሪዎች ናቸው።
መውጫ።
በጥሞና ጊዜ ወስጄ በድጋሚ አዳምጬ እመለስበት ይሆናል። ኢትዮጵያ ማለት ሰው ነው። ማይካድራን ከሰቀጠጣቸው ጠቅላዩ እስኪ ስለ ኦሮምያ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የተዋህዶ አሳርም ከውስጣቸው ጠብ እንዲል ይፀለይ። ሌላ 30 ሺህ መፈናቀል ምን አላትም ብለውናል።
በመፈናቀል፣ በማፈናቀል ለሚታወቀው ድርጅታቸው ቀላሉ የቤት ሥራ ነው። መፈናቀል? ቧንቧ ውኃ ከፍቶ የመዝጋት ያህል። የሥነ - ልቦና ቀውሱ ቀላል ከሆነ እናዬዋለን። ያው እሳቸው አቅላይ ናቸው።
መፈንቅለ መንግሥት ከሚባል ነገር ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቅ። ፈፅሞ ላቀርበው እማልሻ የሥርዓት አልበኝነት ወይንም የአናርኪዝም መንገድ ነው። እሳቸው ግን ዕውነት ለመሆን ይድፈሩ።
ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ቀርቶበት በድህነት ለመኖር ለህዝቡ ይፍቀዱለት በተለይ በሃርድ ዌራቸው በሰረዙት አማራን።
ለህወሃት ማበጥ፣ መቃተት የራሳቸው ኦህዴድ፣ ኦነግ ምክንያት ናቸው። ግን ይህ ሁሉ ሲሆን የደህንነት ተቋማቸው መኜታ ቤት ነበርን?
ኢትዮጵያ በአንደበታቸው ተሞሽራ ውላለች። ኢትዮጵያዊነት ማሸነፋንም ዕውቅና ሰጥተዋል። ኦሮሙማ ማለት ኢትዮጵያዊነትን ማስገበር አለመሆኑን እኔ ልነግራቸው እሻለሁኝ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር። የ20 ዓመት ሞቶዬ ነው።
መሸቢያ ቀን።
ቸር ወሬ ያሰማን። አሜን።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።