29.11.2019 የዱቤ ፓርቲዎች ስሞታ ቋት።
የዱቤ ፓርቲዎች ስሞታ ቋት።
ምን እያሉን ነው የዱቤ ፓርቲዎች? እያሉን ያሉት ልንታገል የሚገባው አቶ ጃዋርን ብቻ መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ተድርሷል። ይህ በድርጅታዊ ሥራ የተሰጠ አብይ አጀንዳ ይመስላል። የሚገርመው የተበዳይ ፍዳ አደባባይ እንዲወጣም አይፈለግም። አድርጊዎችም ሥማቸው አይነሳ እዬተባለ ነው።
ቄሮ ጀግና ሲባል ካልከፋን ቄሮ ገዳይ ሲባልም ሊከፋን አይገባም። ጀግናም ያሰኜው ገዳይም ያሰኜው ድርጊቱ ነው እና። በፎቶ እዬተነሱ የሚለጥፋትም እነሱው እራሳቸው ናቸው።
ግርም የሚለው ካለ መንግሥታዊ አቅም ማህል አዲስ አበባ ላይ አንድ ብሄራዊ መከላከያ፣ የአይር ሃይል፣ የደህንነት፣ የፖሊስ ሙሉ አካል ያላት አገር መዋቅርም፣ ድርጅትም ህጋዊ ዕውቅና ባልተሰጠው አካል ህዝብ መኖሩ እንዲህ ሲጠበስ መንግሥት ነኝ የሚለው አካል በዬለም ደረጃ ነው ያለው። ወይንስ መንግሥት ነኝ የሚለው በዬቀኑ እዬወጣ የሚፎክረው የቀውስ ቤተኛው ነው ወይ? የቱ ነው ለኃላፊነት ቅርቡ?
በአባል የግንባሩ ድርጅት ጫና ለማድረግ ኦነግን፣ ቄሮን በተሟላ የሎጅስቲክስ ድጋፍ እያጠናከረ ያለው ማን ነው? የትኛው አካል ነው። ለምን በዘመነ ህወሃት ይህ መቃናጣት አልታዬም?
በደል በገፍ አለ ተጠያቄ አካል ግን የለም። ኢትዮጵያ በኪነ ጥበቡ ነው ያለችው። ይህ ልፍስፍስ አስተዳደር እንደ መንግሥት ታይቶ አትንኩት፣ ድርሽ አትበሉበት የዱቤ ፓርቲዎች አታሞ ነው። ዛሬ ዓለም እራሱ ሁሉን ነገር በተደሞ እዬተከታተለው ነው።
ይህ ሁሉ ቀውስ ሲመራ፣ ሲደራጅ ምንጭ፣ ደጋፊ መንግሥታዊ አካል አለ። ይህ መንግሥታዊ አካል የዜጋውን የመኖር ዋስትና ማስጠበቅ ካልቻለ ለሚችል ማስረከብ ብቻ ነው ያለው አማራጭ።
የዱቤ ፓርቲዎች አካላት እና ካድሬዎቻቸው፣ ሚዲያዎቻቸውን ጨምሮ ጭንቁ የሰብዕዊ መብት ረገጣው፣ የዕንቡጦች መቀጠፍ፣ የማያባራ ዕንባ እና ሥጋት መኖር አይደለም። ጭንቁ ካለልኩ የተቆለለው የዶር አብይ አህመድ ሰብዕና ግዝፈት ያንሳል ወይንም ያሽቆለቁላል ነው። ከዛ በኋላ እኛ የት እንደርሳለን ነው የዱቤ ፓርቲዎች መሪዎችም ካድሬዎችም ጭንቀት እና ጥበት። እሩቡን የኢትዮጵያ አካል ብቻ ለሚመራ ነፍስ ይህን ያህል የዓይን እርግብ መሆን ይሰቀጥጣል።
አንድ መንግሥት አዲስ አበባ ሥጋት አለ እና ቤተ መንግሥት ብቻ ነው መጥታችሁ መሰብሰብ የምትችሉት ከማለት በላይ ምን አሳፋሪ ተግባር አለና? መንግሥት ሲፈልግ ደግሞ የሞጋሳ እሬቻ ቀኑን ዲል ባለ ድግሥ በመንግስት ወጪ በሰላም ያከናውናል።
የአንድ ጋዜጠኛ ህዝባዊ ስብሰባን ደህንነት ለማስከበር ግን አይፈቅድም። እራሱ ግርግር አደራጅቶ ይመራል። ይህ ጉራማይሌ ላንቁሶ የፖለቲካ ጨዋታ ለዱቤ ፓርቴዎች ድሎት ነው።
መንግሥት ሲኖር እኮ ህግ ለሁሉም እኩል ነው። እንደ መብራት ማብርያ እና ማጥፊያ ኦንና ኦፍ የምታደርገው የግርግር ዝብርቅርቅ ዓውድ አይኖርም። የሆነ ሆኖ ተጠያቂነቱ ሁሉ ተጠቅልሎ አቶ ጃዋርን አብይወለማን ሳይነካ እንዲሆን ይፈለጋል። በማን ትክሻ ነው አቶ ጃዋር መሃመድ እንዲህ የሚዘባነነው? በአብይወለማ አይደለምን?
የእነ ጮርቃ ማህበር የኦዴፓ መሪ ጠሚሩ መሆኑንም አይቀበሉም። ይነጣጥሉታል። ጠሚሩ የወጡት ከኦዴፓ ነው። የኦዴፓው ሊቀመንበር ዶር አብይ አህመድ በአገሪቱ ህግ መሰረት አማራ ክልልን ግርባው ብአዴንን ሰጥ ለጥ አድርገው እንደሚገዙት፣ ቁጭ ብድግ አስደርገው ጅም እንደሚያሰሩት ይህን በፓርቲያቸው በኦዴፓ ማድረግ ካልቻሉ ተጠያቂው ዬአቶ ጃዋር መሃመድ ኮኦርድኔሽን አቅም ሳይሆን የኦዴፓ መሪው የዶር አብይ ኮኦርድኔተርነት ሬሳ ሳጥን ውስጥ ከትሟል ማለት ነው።
በአንድ የፖለቲካ ድርጅት የግልና የጋራ አመራርን አዋህዶ፣ አስማምቶ መምራት ያልቻለ፣ ይልቁንም ድርጅቱ አባል ላልሆነ መንፈስ ታዛዥ ከሆነ ከዚህ በላይ መፈንቅለ መንፈስ የለም።
ስለዚህ በሌለ ትርክት መፈንቅል ሊደረግብኝ ነበር ብለው አማራ እስከወዲኛው ቤተ መንግሥት ትውር እንዳይል ዓለም አቀፍ ሳቦታጅ በመሥራት የክልሉን ዓይን ባጠፋት ልክ ሰይፋቸውን ለሌላውም ማድረግ የመቻል አቅሙ ሲመዘን ውኃ የበላው ቅል ነው። ትግራይን በልመና ካልሆነ አንዲት ቀን መርተውት አያውቁም። እንኳንስ ኦሮሞ ክልልን።
ሌላው መሪነት ለገበርዲን ለከረባት አይደለም። መሪነት ለህዝብ ነው። ለበጎውም ለመጥፎውም ኃላፊነት መውሰድ ግድ ይላል። ፍትፍት ላይ ጥድፊያ፣ እራህብ ላይ ሽሽት የመሪነት ክህሎቱ አይደለም።
ኢትዮጵያ መከራ ላይ ናት። ባለቤት የሌላቸው ብዙ ነፍሶች አሉ። ስለዚህ እንቅልፍ አያስፈልግም። እንቅልፋን ለዱቤ ወይንም ለቀጠሮ ፓርቲዎች መሸለም ነው።
በዚህ ውስጥ አማራ አቅሙን በቁጠባ ማስተዳደር ይኖርበታል። ሁሉንም እያዬው ነው አንድ አማራ ነፍስ ብቅ ሲል ዘመቻው፣ ስጋቱ፣ ጦሩ በዬአቅጣጫው ነው።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ