በትውልድ ግንባታ ላይ መብት ኖረንም አልኖረንም መሳተፋችን አይቀሬ ነው።
በትውልድ ግንባታ ላይ መብት ኖረንም አልኖረንም መሳተፋችን አይቀሬ ነው።
"ዬሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
አጤ ፌስቡክ ከቶ ደስብሎህ ሰነበተን? ግብት ስል ማስጠንቀቂያውን ይዘህ ከቸች ትላለህ። ዬሆነ ሆኖ ዛሬን ዕለቱን በጦቤያው ጥር 6/2015ን ቅኝት ላድርግ ብዬ ጎራ ብያለሁኝ።
ዋርካ ያለው ጥላ ይኖረዋል። ዬተከበረው ዬሁለመና ሁለመና ጋሽ ግርማ በዬነ፤ ዬተከበረው ዬሁለመና ሁለመና ጋሽ ይልማ ገብረአብ መኖራችሁ ተስፋችን ነው። የተስፋ እርግብ በር። ለዝግጅቱ ግርማ ሞገሱ ጉልላቱ ነበራችሁ። ኑሩልን። አሜን።
ዛሬ ዬፋና ላምሮት ዬአሸናፊወች አሸናፊ ውድድር ነበር። ስከታተለው ነበር። አስተያዬትም ስሰጥበት ነበር። ትውልድን ለመቅረጽ ዬሚደረገውን ሁለገብ ጥረት መደገፍ የዜግነት መብት ሳይሆን ግዴታም ነው። ዬእኔ እንደ ጥሪዬ ዬማዬው ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ላይ ይህ መጀመሩ አበረታች ነው። ሙዚቃ ዬመኖር የውስጥ ሙዳይ ነው። ደስታህን፤ መከፋትህን፤ ሲቃህን ቅኔህን፤ ቃናህንም፤ ታሪክህ፤ ማንነትህ፤ ነፃነትህ የሰጠህ የምትገልጽበትም። ሙዚቃ ላይ እኔ እምብዛም ብሆንም ግን በጥበብ ቤተኝነቱ፤ በሥነ - ፁሁፍ ለዛ እና ጣዕሙ መመሰጤ አይቀሬ ነው።
ዬፋና ላምሮት ዬሥራ አስፈፃሚው ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው "ዬእኔ፤ ያገባኛል" ዬሚል ስሜት ፋና ላምሮት ፈጥሯል ሲሉ መግቢያቸው ላይ ገለፁ። አወን ተፈቀደልንም፤ አልተፈቀደልንም እንሳተፋለን። እኔ እርግብ በር፤ ዬተስፋ በር ሁለት መጽሐፌን የፃፍኩት፤ የምክር ዬመነሻ ሃሳቦች ናቸው ዓለም ዓቀፍ ውድድሮችን እዬተመለከትኩ ነበር። ክፍተቶችን አይቼ ገምግሜ ትውልድ እንዴት ይቀረጽ? ትውልድ እንዲቀጥል እንዲህ ያሉ ነፍስ ሆነው ነፍስ ዬሚዘሩ ተግባራት ሊከወኑ ይገባቸዋል።
በመንግሥት ታላላቅ ብሄራዊ ሸንጎወች መሰናዶወች ከማያቸው ክፍተቶች ይልቅ ይህ ዝግጅቱ #ደርባባ ነበር። ዬሰጠው። ዬኮርስፖንዳንስ፤ የስቴዲዮ፤ ዬማህበራዊ ሚዲያ ቅኝት የሚዘግቡ፤ ዋናውን ፕሮግራም ሞደሬት የሚያደርጉ ሁለት ሙሽራ አቶ አዳነ አረጋ እና ምህረቷ ሞደሬተሮች ሥርዓታችሁ ያስተምራል። ምህረቷ አምረሽ ነበር። በድምሩ አምስት ዬመሰናዶው አንደበቶች ቅንጅት ግሩም ነበር። ዬመግቢያ ንግግሩም አጭር እና መሳጭ ዬታሰበበት ነበር። ዬክብር ዳኛ፤ ዬክብር እንግዳ ነበሩ። መደበኛ ዳኞች በትህትና በተቀባው ፀጋቸው ታድመዋል።
የተወዳዳሪ ዬአራቱም ቤተሰቦች ነበሩ። ታዳሚውም ህብራዊ ነበር። በዬሳምንቱ በነበረው ውድድር ዳኛ ከነበሩት ውስጥም አንድ ዬክብር ዳኛ አይቻለሁኝ። ባንዱ በሙሉ ውበት በግርማ ነበር። የማይክራፎን ቅድመ መሰናዶውም ብቁ ነበር። ትናንት የዋዜማ ልምምዱንም አይቼው ነበር። ዬተደራጀ፤ የተቀናጀ፤ ጥሩ ካፒቴን ዬነበረው ብቁ መሰናዶ ነበር። በሂደቱ ሁሉ ለመማር ለሚፈቅድ ሁሉ ምቹ ነበር።
#ዬሰከኑት ሦስቱ ዳኞች።
ዳኛ ብሌን፤ ዳኛ፤ አቤል፤ ዳኛ ብሩክ። ይገርሙኛል ትህትናቸው። እርምት ለመስጠት ይቅርታ ይጠይቃሉ። የሙዚቃን ፊደል ያስቆጥራሉ። የውጩን እከታተላለሁኝ። የፋና ላምሮት በልጦብኛል። ዬሙያ ዲስፕሊን ማጥናት ስለምወድ ቁጭ ብዬ እዬፃፍኩ እማራለሁኝ። አይቆጡም። አይበሳጩም። አለስልሰው ያስተምራሉ፤ እያባበሉ ጎባጣን ያቀናሉ።
እኔ እምከታተለው ፕረዘንቴሽን እና ፐርሰናሊቲ፤ እና ኮንፊደንስን ብቻ ነው። እነሱ ግን የሙዚቃ ኢኒስቲቲዩት ናቸው። ዳኛ ብሌን ቁልምጫ አነሰብኝ፤ ማሽሞንሞኑ ተሸራረፈብኝ ወይ ተንሸራተተብኝ ስትል፤ ዳኛ አቤል ተማሪ ለመሆን ፍቀዱ እኔ ዬወደቅኩበትን በእናንተ ተደግሞ ማዬት አልሻም ይላል፤ ዳኛ ብሩክ ደግሞ ቫልዩ አድ ማድረጉ ቀርቶብኝ ትንሽ ከፋኝ ………፤ ብቻ ተናፋቂ፤ አጓጊ ጊዜ ነበር። ተባረኩ መምህሮቼ።
ተወዳዳሪወች ጥሩ ተፎካካሪ ነበሩ። ዬተሰናበቱት ሁሎችም አንስቶች እጅግ ዬሚደንቅ ዲስፕሊን ነበራቸው። ጭምቱ ገረመው ከእነ ፀጋው ዬዛሬ ሁለት ሳምንት ሲሰናበት አዝኜ ነበር። ዬተለዬ መንገድ ዬቀዬሰችው ዮርዳኖስ ካልዘነጋሁ ውብ ነበረች። ብቻ ሁሎችም በዬቀለማቸው ይመስጣሉ ዲስፕሊናቸው ውበቱ ይስባል።
አራቱ ዬዛሬ ተወዳዳሪወች ዳኒ፤ አሉላ፤ ደሱ እና ያለም ብዙ ጥረዋል። ተግተዋል። ፋክክር፤ ውድድር ሆነ እና ተበላለጡ እንጂ በዬቀለማቸው ልዩ ናቸው። ዳኒ እርጋታው፤ ቁመናው፤ ፀጋው ተስፋ ያለው ቀንበጥ ነው። ለቲያትር፤ ለፊልም፤ ለማስታወቂያ ስራም ዬመሆን ሰብዕና አለው። ፋና ላምሮት ቢያግዘው የቲያትር፤ የዳንስ ኮርሶችን ቢወስድ ድፍረቱን፤ በራስ የመተማመን አቅሙን ማመጣጠን ይቻላል። እጅግ ብሩህ ተስፋ ያለው ወጣት ነው። ዬዛሬ ሁለት ሳምንት ከእናቱ ጋር ዬነበረው ሁነት ታትሞብኛል። ሌላ ለፋና ላምሮት እምለምነው ለ2016 ዬፋና ላምሮት ዬአሸናፊወች አሸናፊ እባካችሁን አወዳድሩት። ዕድሜውም ይጨምራል።
አሉላ ተውኔት ላይ የማተኮር ዝንባሌ ስላለው ሙያውም ስለሆነ ዬዛሬን ዬመወዳደሪያ ዬሰላም ሲዲ የራሱ አድርጓል። ዬእሱ ፀጋ ሁሉንም ሥንኛት ያስደምጠናል። አቀራረቡ ደግሞ ለፕረዘንቴሽን ሙሉ ነው። ዬሚያክላቸው ነገሮች እሱን ስለሚደብቁት አትኩሮት ቢያደርግ ኮንሰርት ሲኖረው ጥሩ ነው። የዛሬ ሁለት ሳምንት ገሬ በልጦ ቢሆን የዛሬን ሁለተኛ ዕድል አያገኝም ነበር። ውድድሩ የሙዚቃ መሆኑ ቀርቶ የሥዕል እና የተውኔት፤ የሥነ ግጥም በማድረግ እራሱን ጋርዶት ነበር። ጽፌለትማለሁኝ።
ደሱ ዳኞችን ከመቀመጫቸው አስነስቶ ያስጨፈረ ነው። ረጋ ያለ። ቅናት የሌለበት ቅን። ዛሬ ፋና ላምሮት ሚስ ያደረገውን እሱ ግን ያበቀለው የንጉሦች ንጉሥ ዬአጤ ቴወድሮስን ቀን በምልሰት ቃኝቶታል። ሸጋ ነበር። በጠቅላላ መሰናዶው በዕለቱ ትንሽ ቀዝቀዝ ያለ ስለነበር አራተኛ ወጥቷል። ቀና ወጣት ነው። የማደግ ተስፋውም ለምለም ነው። ትሁት ስለሆነ። ኦዲዬንስ ስለሚያከብር።
ለደሱ፤ ለዳኒ፤ እና ለአሉላ ዬ 300 መቶ ሺህ ብር ለእያንዳንዳቸው ፋና ላምሮት ልጆቼን ባዶ እጃቸውን አልሰድም ብሎም ሸልሟቸዋል። ም/ ኮማንደር አትሌት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ እና ዶር ሂሩት ካሳ ለሁለት ሽልማቱን ሰጥተዋል። ማለፊያ ነው። ዬፋና ላምሮት ቤተሰብነት ጣዕሙ እንደሚቀጥልም ኃላፊው ገልፀዋል። የሚገርመኝ ፍቅራቸው ነው። እንደ አንድ ቤተሰብ ሲደጋገፋ አያለሁኝ። ውጪ ያለ ጦርነት ብታዩ እንደዚህ ባለ ቲም ወርክ ላይ። ብዙ ተሰጥቶን ግን የምናፈስ ህዝቦች ነን። እንጂ ይህ የውህደት መተሳሰብ በራሱ ዕሴታዊ ፋይዳችን ነው።
ያለም ብዙ ጊዜ በመሰናዶዋ ላይ የፈካ ፊት ይጎድል ነበር። ዛሬ ፊቷ ብርኃን ነበረው። ያው ጎንደር ማደግ ሴት ልጅ ሆኖ ከባድ ነው። ጫና አለ። ባህሉ ከባድ ነው። የእሷ ደግሞ በለሳ አርባያ ነው። ብዙ ጊዜ ከፋኝ ዬሚሉ ሁሉ ዬሚመሽጉበት ነው። ከዛ ወጥታ እዚህ መድረስ ታምር ነው። "ዬልጅ እና የጭስ መውጫው" የሚለው ዕውን ዬሆነበት ነው።
ድምፆዋ ሙዚቃ ትልማቸው ላልሆነ ሁሉ አስገዳጅ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። ቃናው ይነዝራል። ገና ስትጀምረው ውበቱ ይቀዳል። ከጭምትነቷ ጋር፤ ከዲስፕሊኗ ጋር ክህሎቱን በስልጠና ለማገዝ አጫጭር ኮርሶችን ከወሰደች ፀጋዋ ባለ ቅባዓ ነው። መጨረሻውን ያሳምርላት። አሜን። የፋና ላምሮት ዬ2015 ዬአሸናፊወች አሸናፊ ሁና ዋንጫውንም፤ አንድ ሚሊዮን ዬኢትዮጵያ ብርም አሸናፊ ሁናለች። ፋና ላምሮት ብርኃኗ! ፋና ላምሮት ቅኔዋ! ፋና ላምሮት ጎዳናዋ ሆኖላታል።
በዛሬ መሰናዶ ሽልማቱን ስትቀበል ዬፈፀመችው አክብሮታዊ ትህትና ዬትውልድ ነው። በቸለልታ ላለፋት በረከት ሁሉንም በአኃቲ ጎዳና ቀይሳ መስመር አሳያዘችው። ቀጣችው። አሳዳጊዋን ይባርከው። አሜን። ኢትዮጵያ ትኑር ብሎ ፈጣሪ በቃችሁ ቢለን እንዲህ ዝቅ ብለው ተፈጥሮን፤ ፈጣሪን አላህን፤ ፀጋን፤ ቀደምትን፤ ዬሰው ልጆችን ፈቅዶ ማክበር ሲቻል ብቻ ነው።
ይህ ዛሬ ያለም የሠራችው ተግባር ሚሊዮኖች ሲዩት ህፃናት፤ ታዳጊወች በራሱ ትምህርት ቤት ነው። ከእሷ ዬቀደሙት ሽልማታቸውን ተቀብለው ፎቶ አብረው ሲነሱ እሷ ግን ድፍት ብላ፤ በርከክ ብላ እንደ አባት አደሩ፤ እንደ ጥንት ጥዋቱ ምስክር ሆነች። ዳኞች ሆይ! እንኳን ደስ አላችሁ። ይህን መሰል የውስጥ ብቃት ያላትን ኮትኩታችሁ፤ ደክማችሁ ውስጧ ያለውን #ጣፋጭ ማንነት ማዬት ስለቻላችሁ። እኔ ለጋሽ ግርማ በዬነ ያደረገችውን ልዩ ትህትናዊ የዝቅታ ልዕለ ስጦታ ሳይ ዕንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም ነበር። ሽልማት ነው።
ውጤቱን እኔ አስቤው ነበር።ውጤቱ ይህ እንደሚሆን አውቅ ነበር። ግን ሁላችሁም እናሸንፋለን ይሉ ዘንድ በዝምታ ሰነበትኩ። ትክክለኛ ዳኝነት ነበር። ምንም ዝበት በሌለበት ሁኔታ በዬሳምንቱ ሂደቱን ተከታትዬዋለሁኝ። ዳኝነቱ በልኩ ነበር። ዬሚገርመኝ እኔ ከቤቴ ሁኜ የማስበው እና የመጨረሻው ውሳኔ ተመሳሳይ ነው። ዬህዝብ ህሊና ለዳኝነት ብቁ መሆኑን አይቸበታለሁኝ።
#ቃና ያለው ቃና በተባ ቃና ሲከወን።
የፋና ላምሮት ዬቅንጅት ግርማ ሞገሱ አንቱ ነበር። "ዬኔ" ዬማለት "ያገባኛል" ዬማለት ሙሉ ክህሎቱ ኃላፊው አቶ አድማሱ ዳምጠው እንዳሉት ተውጥቶታል። ሁላችሁም አሸናፊ እንደተባለው ዋንጫው ለባለዕድል። ይህን ደግሞ ባለ ቅኔው ገጣሚ ጋሼ ይልማ ገብረአብ እንዳለው ሆነ። አሸናፊወች ሽልማታቸውን በስተጀርባው ይዘውት ጠንቃቃቃዋ ረ/ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ተጎንብሳ ስታስተካክል፤ ሴት ተወዳዳሪ ስላሸነፈችላት ደስታዋን የገለጠችበትን ፎቶ ጨምሬዋለሁኝ።
በትውልድ ግንባታ ላይ ዳር መቆም ዬለም። ዬትናንት ድልድይ ዛሬን አበራከተ። ዬዛሬ ተስፋ ትናንት አዋዶ ዬነገንም ተስፋም አለመለመ። ዛሬ፤ ዬማግስት ድልድይ ዛሬ ጥሩ ካፔቴን ሲያገኝ። መሸቢያ መሰናዶ፤ ማለፊያ ጊዜ ነበር። ሙሉዑ። ቀደምቱም አሻራቸው አበራ። ቦግ አለ። በባህላችን ላይ ያለው ተደሞም ውፅፍተ ወርቅ ነው። ትንሹ ዳንዬ አይዞህ በሩ ተከፍቷል፣ እሺ አባትዬ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ውዶቼ እና ክብሮቼ ይህን ቀይ መብራት ፌስቡክ እስኪያነሳልኝ ድርስ እንታገስ እሺ። ደህና ሰንብቱልኝ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ቸር እንሁን።
ቸር ያሰማን።
አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15/01/2022
ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ ዙሪክ ከኮሽ አይሏ ቪንተርቱር ከተማ።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ