#ማመን #ከዛስ?

 

#የሙሉ ዕድሜ እስረኞች። የኢትዮጵያን ፖለቲካ #ማመን አይቻልም። #እምነተ #ቢስ ነውና።
"የቤትህ ቅናት በላኝ"
 May be an image of 4 people and text
የኢትዮጵያ የትግል አቅጣጫ ሥር ነቀል - ታጋሽ - አስተዋይ - ሰዋዊ -: ቀና -:ቅንም ሊሆን ይገባል። ህወሃት ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ፕሬስ ነፃነቱ ታወጄ። ህወሃት መሠረቱን ሲይዝ ግን ነፃ ፕሬስ #ለካቴና ተሰጠ። ህወሃት ወደ ሥልጣን ሲመጣ በፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት ነው። ከዛ በኋላ ግንፋዊ ጉዞውን ቀጠለ። አልዘለቀም። ለነገሩ ተፈጥሮው ጭካኔ እና ክህደት ነው። ይህ እንደጣለው አለመረዳቱ ነው የሚገርመኝ። 
 
ዛሬም በህዝብ ስቃይ ፌስታ???
የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሥርዓት ሲመጣም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል መብት እንዳላቸው ዓወጀ። እስር ቤቶች ወንጀልን ከመከላከል ውጪ በፖለቲከኞች፤ በፕሬስ ላይ ምንም ጭነት እንደማያመጡ ሰበኩ። የለውጥ ሐዋርያ የነበሩት 
 
1) አቶ #ለማ መገርሳ (ዶር)፤
2) አቶ ደመቀ መኮነን፤
3) አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤
4) #ተገዳዩ ዶር አንባቸው መኮነን።
 
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ መፈናቀል፤ በጦርነት፤ በሴቶች መደፈር፤ በፕሬስ አፈና፤ በተጽዕኖ ፈጣሪወች ግድያ፤ በዘረኝነት እና ጭካኔያዊ አመራር፤ በራህብም፦ በኢኮኖሚ ድቀት፤ በጀምላ እስር እና ግድያ፤ በዲፕሎማሲ የምትብጠለጠል አገር ሆነች።
 
የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ቃል #የሳሙና #አረፋ ነው። የተገባው ቃል ኪዳን ወዲያው ተኩረፍርፎ ወዲያው ይጠፋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስሜታዊ፤ ጭካኔ - ዘለቅ፤ ቂመኛ፤ በቀለኛ፤ #ፍፁም #የማይታመን፤ ምህረት - የማያውቅ፤ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የማይሰማው፦ በቃሉ ፈፅሞ የማይገኝ፤ #አድመኛ፤ ኢጎን መሠረቱ ያደረገ፦ #ሂስ ፈፅሞ የማይፈቅድ፤ ጥላቻ ገበሩ የሆነ፤ #ዕለታዊ፤ ለትውልድ የማያስብ፤ ሴራ የሚበዛበት፤ ኢንትሪግ - ያዬለበት፤ ከመልካምነት ይልቅ ለክፋነት የሚያደላ፤ ተፈጥሯዊነቱ የሳሳ፤ ከሰባዕዊነት ጋር የተፋታ፤ አይዟችሁን የማያውቅ፤ በድሎ እንኳን ለማፅናናት የማይፈቅድ፤ ለልጆች #ህሊና ፈፅሞ የማይጠነቀቅ፤ #ወረተኛ፤ ብቁወችን አድኖ የሚያጠፋ፤ ልቅና ያላቸውን #የማይፈልግ፤ ዊዝደም የራቀው፤ ስለ ልጆች አጀንዳው ያልሆነ፤ ታሪኩን የማያከብር፤ ለቀደምት ባህላት ንቀት የሚታይበት፤ ኢትዮጵያኒዝምን አብዝቶ የሚያገል፤ ጥላቻ መርሆ የሆነ፦ በፀረ አማራ ዶክተሪን የሚመራ፤ ለቤተሰብ ትርጉም የሌለው ነው።
 
ስለሆነም ሙሉ 60 ዓመታት በሚራመደው የሶሻሊስት ርዕዮት በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ዴሞክራሲ #እንዳይጠነሰስ የጉሮሮ አጥንት ሆኖ የበቀለ #ሲነቅል ኖሯል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በውራጅ ርዕዮት ኢትዮጵያኒዝምን ወርውሮ ማርክሲስታዊ፤ ስታሊናዊ፤ ማኦኢዝምን መስጥሮ ሲተገብር ኖሯል። በዚህ ሂደት ትውልድ አልቋል ከምል #ታጭዷል ብል ይቀለኛል።
 
የመጀመሪያ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ተብሎ የሚነገርለት ኢህአፓ ነው። የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ግንባር። ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ምንጫቸው መንፈሱ ከኢህአፓ የተቀዳ ነው ይባላል። የታክቲክ ለውጥ ቢለያያቸው ሶሻሊዝም የማረካቸው እንደሆኑ ዛሬም በምናያቸው አካሄዶች መገንዘብ ይቻላል።
 
ኢህአፓ በሦስት እንደ ተከፈለ ይገለፃል። ለኢህአፓ ዓላማ የተሰዉ፤ የታሠሩ፤ የተሰወሩ፤ አካላቸውን ያጡ ብዙ ናቸው። ኢህአፓ ትግሉን በከተማ ጀምሮ በኋላ ላይ ግን ወደ ጫካ ገብቶ ታግሏል። ጫካም እያለ እንዲሁ አንጃ ተፈጥሯል። የአሁኑ #የአማራ #ክልል #ብልጽግና የኢህአፓ ሽራፊ ነው።
 
#የዶር አብይ፤ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ የአቶ ደመቀ መኮነን፤ የአቶ ለማ መገርሳ፤ የተገዳዩ ዬዶር አንባቸው መኮነን ኢህአዲግን ሪፎርም የማድረግ ዓላማ ከኢህአፓ ውስጥ የተወሰኑት አገር ገብተው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው፤ በህወሃት እና በኦነግ የበላይነት በተረቀቀው ህገ - መንግሥት ሥር ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እዬታገሉ ይገኛሉ።
 
ነገር ግን በኢህአፓ ምክንያት የታሠሩት እነኝህ የኢህአፓ አባላት #ከ22 ዓመት በላይ እስር ላይ ይገኛሉ። የሚገርመው #ሴትም አለች። ሴቶች ሲታሠሩ ብዙ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ ትጋት አለ። ለዚህች የኢህአፓ ሴት ታጋይ ግን ምንም ትጋት የለም። ተባዕቶቹም ቢሆኑ ሙሉ ዕድሜያቸው እንሆ ካቴና ላይ ሆነ። በጥገናዊ ለውጡ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ። የኢህአፓወች ግን #አስታዋሽ አላገኙም።
 
የታሠሩት እነኝህ የኢህአፓ አባላት በዜግነት ፖለቲካ ነው። ህወሃት በኢትዮጵያ የገነባው ሶሻሊዝማዊ የዞግ ሥርዓትን ነበር። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ከረንት ፖለቲካ ኢትዮጵንይዝም ወይንም የዜጋ ፖለቲካ ባለቤት የለው። 
 
ማህበራዊ መሠረቱም ለጥቃት ስለሚጋለጥ ስውር ነው። እርግጥ ነው ውህድ ማንነት ያላቸው፤ ሳይለንት ማጆሪቲ ውስጥ ያሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ጽኑ ዕምነት እንዳላቸው አምናለሁ። ነገር ግን አደባባዩ እጅግ ያስፈራል። ቋያ እሳት ነው። ላርባ። 
 
ለዚህ ነው ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ሰው ከዜግነት ፖለቲካ ወደ ዞግ ፖለቲካ እዬተመመ የሚገኘው። በተለይ በኢትዮጵንያዝም ላይ ጽኑ አቋም የነበራቸው የአማራ ሊቃናት፤ ሊሂቃንም ወደ ዞግ ፖለቲካ የሱናሜ ያህል እዬጎረፋ ይገኛሉ።
 
በዚህ መሃል ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያዊነት በሉዓላዊነት ተጋድሎ ህይወታቸውን ያጡ ጀግኖችም ታሪክ እንዲሁ እዬተዘለለ ያለ ይመስለኛል። እስር ላይ ያሉ በዜግነት ፖለቲካ ምክንያት ዬታሠሩትም ባለቤት ያጡት ከዚህ አመክንዮ አንፃር ይመስለኛል።
 
ከሁሉም ከባዱ ፖለቲካ የአማራ ፖለቲካ #መንፈሱ ይመስለኛል። በቅጡ አትኩሮት፤ ዕውቅና ተሰጥቶት ሃንድል ማድረግ ካልተቻለ ከግፋ፤ ከመከራው፤ ከመፈጀቱ፤ ከፖለቲካ በስልት ከመገለሉ አንፃር ቆርጦ ስለተነሳ ለመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካም ዳይናሚክ የሆነ ለውጥ የማምጣት አቅሙ ጠንካራ ሊሆን ይችላል።
 
አማራነት እንደ ምግብ እንደ ውሃ በትውልዱ ላይ በጽናት የገነባው የወል ፍጅቱ እና ስልታዊ በሆነ ሁኔት በፖለቲካ መገለሉ ነው የሚል ዕምነት አለኝ። የአማራ ልጅ ኢትዮጵኒዝምን ቢያራምድም፤ አማራ ነኝ ቢልም እኩል ነው ለአማራ መከራ። ፋሱም // መዶሻውም በአማራ ልጅ ላይ መቁረጣቸው አይቀሬ ነው። አማራ ሆኖ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ከሆነ ደግሞ ያው ቀራንዮ ነው።
 
ተሰዶም አማራ የሚምረው የለም። ይኽው እኔን ዕድሜዬን ሙሉ ያሳድዱኛል። አንድ ነፍሴን ብቻዬን ነው የምሠራው። ፓርቲ የለኝ ምን። ግን ይህችን ብዕሬን፤ ለ16 ዓመት እዬሠራሁበት ያለው የፀጋዬ ራዲዮ፤ ሰባት ለትውልድ የሚጠቅሙ መጸሐፎቶቼ እገዳ ላይ ነው ያሉት። እራሴንም ጠብቄ ነው እምኖረው።
 
 ምክንያቱም አማራነት ለመላ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ወንጀል የሚታይ ክስተት ነው። ይህም ሆኖ ቂምም በቀለም የለብኝም። እኔ የለብኝም ማለት መሬት ላይ አገር ውስጥ ያለው ሚሊዮን አማራ ምን እንደሚያስብ መገመት አይቻልም። እሚያስፈራኝም እሱ ነው።
 
የእነኝህ የቀደምት የኢህአፓ አባላት ለድርጅታቸው የከፈሉት መስዋዕትነት በፍትህ አደባባይ የሚለካው ከመጡበት በዕት፤ ከዞጋቸው አንፃርም ሊሆን ይችላል እንዲህ የእስር ቤት ቤተኛ፦ እርስተኛ ሆነው እንዲቀሩ የሆነው።
 
ሁለት ትውልድ ባልሰከነ ኢሰባዕዊ ርዕዮት እና ፍልስፍና ተገብሮ ዛሬ ሦስተኛው ትውልድም መከራውን ጀምሮታል። ፖለቲካ የማሰብ ውጤት ነው። ማሰብ ደግሞ ነፃነት ይጠይቃል። በኢትዮጵያ ሥር - ነቀል የሆነ የሥርዓት ለውጥ ካልመጣ፦ የማሰብ ነፃነት ባለአደገ አገር የተመሰጠረ የሶሻሊስት ርዕዮት ሥራ ላይ እያለ ዕውን ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።
 
የኢትዮጵያ ችግር ከአንድ ሰው፤ ከአንድ ቡድን ህሊና በላይ ነው። ጥልቅ ጥናት፦ የተረጋጋ ማስተዋል ይጠይቃል። እንደ እኔ ኢትዮጵያ በአንድ ጠቅላይ ሚር // ወይንም በአንድ ፕሬዚዳንት ሳይሆን በቲም ብትመራ እንደ ሲዊዘርላንድ ምኞቴ ነው። ቲሙ ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል፤ ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አካል፤ ደጋፊ ያልሆነ ሰውኛ እና ተፈጥሯዊ የሆነ አጽናኝ ቲም ቢሆን የሚል ዕሳቤ አለኝ።
 
በስተቀር እዛው ሲቧከስ የኖረው መልሶ መንበሩን ቢወስድ አድብቶ ቆይቶ በቀል መፈፀሙ አይቀሬ ነው። ቂመኛ ፖለቲከኛ መበቀሉ ዕድሉን ሲያገኝ ፋክት ነው። ዛሬ ግሎባላይዜሽን ነው። በግሎባላይዜሽን ዘመን አውሮፓውያን፤ ምዕራባውያን፤ የአፍሪካ አንድነትም ድርሻ አላቸው። የኢትዮጵያ ጉዳይ በግልብልብ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ዳንቴል የሚሆን አይደለም።
 
 ወይንም የተወሰኑ ግለሰቦችን በማቅረብ እና ለእነሱ ሃሳብ ብቻዕውቅና በመስጠት አይሆንም። ብዙ በጣም ብዙ የቆሰለ መንፈስ አለ። ፈውስ የሚሻ። ፍትህ ርትህ የሚሻ።
ጥልቅ ጥናት፤ ጽሞናዊ ምርምር የሚጠይቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በደራሽ ፌስቲባሎች ብቻ ሊፈታ አይችልም። ኢትዮጵያ መንፈሷ አንከር ነው ለአፍሪካ። 
 
አንከርነትን ለመወጣት ከቅጽበታዊ ውሳኔ ምዕራባውያንም፤ አውሮፓውያንም፤ የአፍሪካ አንድነትም መታቀብ ይኖርባቸዋል። የ25 ዓመት የፖለቲካ እስረኛ ያለባት አገር ናት ኢትዮጵያ፤ ሚሊዮኖች ስደት ናፍቀው ሺወች በመንገድ ሲሰው ኖረዋል።፤ የተሰወሩት ሳይገለፅ። ሙሉ 40 ዓመት የተሠወሩም፦ የታገቱም ይኖራሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት።
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እና የፌስ ቡኬ ታዳሚወች እንዴት አደራችሁ ሳልል ነው አህዱ ያልኩት ዛሬ። እንዴት አላችሁልኝ? የእነኝህ ወገኖቻችን ጉዳይ ቋያ ሆኖብኝ ነው የሰነበተው። እንሰብበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም የፖለቲካ እስረኛ ሊኖር አይገባም። አሁንም ይህን ዕውን እናደርጋለን የሚሉ ፊት ለፊት ቢወጡ ሊታመኑ አይገባም። መቼ ለእነኝህ ምንዱባን ፍትህ ሰጡ እና ሥልጣን ላይ እያሉ? ሥልጣኑ ባይኖርም ለእነኝህ ምንዱባን ማን ጮኽ????
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/06/024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።