እጬጌው ሂደት።
እጬጌው ሂደት ስለምን ተፈጥሮው
በጽሞና አይመረመርም?
በጽሞና አይመረመርም?
ከሥርጉት © ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
08.04.2018 (ከመነኩሴያዋ ሲዊዘርላንድ።)
08.04.2018 (ከመነኩሴያዋ ሲዊዘርላንድ።)
„የጥልቁን መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልዕክ ከሰማይ ሲወርድ አዬሁ።“ (የዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ ፳ ቁጥር ፩)
እጅግ የምትናፍቁኝ የሐገሬ ክብረቶች እንኳን ለብርሃና ትንሳኤው አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
ተመስገንን የቀለበ ተንሳኤ ነው የ2010። ትንሳኤ የታደለ ለመሆን የታደለ። የሰው ግብር ውጤት እዮርን በር አንኳኩቷል እስቲ ፈጣሪ
ቀጣዩን ጊዜም ይርዳን፤ የእኛን የዘመናኞችን ትቶ ለነዛ ወጣትነታቸውን ቀቅለው፤ ኑሯቸውን በፈርዖን አስጠብሰው፤ ሥጋቸው አልቆ ከመቃብር
ለወጣውን መንፈሳቸው ሲል እንኳን። እንኳንም ዘሃቸውን አገኘነው። አጽማቸውም ቢሆን ለዓይነ ሥጋ ያበቃን አምላክ የተመሰገነ ይሁን።
አሜን!
- · መቅድም።
በ2013 እጬጌው ሂደትን በሚመለከት „አቶ ሂደት“
በሚል ይባረክ እንጂ „ዘሃበሻ“ ጹሑፉን አትሞልኝ ነበር። ጭብጡ የፖለቲካ ሊሃቅኑ ፓርቲ አደራጀን ሲሉ፤ አብረን ለመስራት ተስማማን
ሲሉ፤ ተዋህድን ሲሉ አብረን እንደሰት እና ሲለያዩ እኛ ማህበራዊ መሠረታችን እናጣለን። እንደገናም ሂደቱ በሚፊጥረው ገጠመኝ ከተለያዮዋቸው
ሊሂቃን ጋር አብረው ለመሥራት ሲስማሙ ደግም መልሰን እንገጥማለን። ሲለያዩም አብረን እንለያያለን። አግለናቸው አንያቸው ብላናቸው
የነበሩ ፓርቲዎች ደግሞ የእኛ ከምንላቸው ፓርቲዎች ጋር አብረው ለመሥራት አህዱ ሲሉ በፊት ያራቅናቸውን ረስተን ቦታ ሰጥተን ከመሪዎቹ
በላይ ደጋፊያዎቻቸው እንሆናለን። ይህ አይጥመኝ የሚል ከመጣ ውግዘ ከአርዮስ ነው። „ወያኔ“ መባል አይቀሬ ነው። ወያኔም በበኩሉ
“አሸባሪ፤ ትምህክት፤ ነፍጠኛ፤ ጠባብ“ ይላል። የእኛ ነገር እንዲህ ነው … ለራሳችን ነፃነት ለመኖር የማንፈቅድ መሆናችን ሳይሆን
የሚገርመው አልጣመንም የሚሉትን በዘመቻ እና በደቦ እኛን ካልመሰላችሁ ብለን ማሳደዳችን ነው ክፋቱ።
ለነፃነት መታገል እኮ የራስን ነፃነት ለሌላ ሃሳብ
ምቾትና ድሎት ሙሉ ለሙሉ መፍቀድ አይደለም። ነፃነት መስጠት ከራስ መጀመር አለበት ብዬ አምናለሁኝ። የተሰማን ውስጥ አንዳለ እንደ
ወረደ ማቅረብ። የራስ ጌታ ራስ፤ የራስ እምቤትም ራስ። ያ ካልሆነ ስለምን የነፃነት ተጋድሎን መከራ ተቀበልን። ከባድ እኮ ነው
ውጪ ሐገር ሆኖ የነፃነት ተጋድሎ ቤተኛ መሆን። ይህን ስንወስን ያልከበደን ውስጣችን የሚለን ለመናገር እና በዛ ውስጥ ለመኖር ግን
የተፈጥሮ ጸጋችን እናፍነዋለን በጋዛ እጃችን። ምክንያቶቹ ደግሞ የሊሂቃኑ የአመራር ብልህነት ምጣኔ ነው። ተዉ ማለት ደፍረው አይችሉም።
እኛ መሬት ላይ ጦርነት ግንባር ላይ ሆነን ስንደባደብ ለእርቅ የምትሆን አንዲት ብጣቂ ቃል ትንፍሽ አይሉም - ሊሂቃኑ። የሚያሰደስታቸው
ይምስለኛልም። ቀድሞ ነገር አጀንዳቸውም አይደለም። በዚህ ተኖረ …
ገራሚው ነገር ሌላ የህብረት ሂደት ሲከውኑ ደግሞ
አዲስ ግንኙነት ሊሂቃኑ መልሰን ደግመን እንገናኛለን። ኑሯችን ታወከ በእነሱ ምክንያት። ስለምን? ሂደትን መርምሮ በሂደት ላይ ቁርጥ
ውሳኔ ላይ መድረስ አቅም ስለሚያንሰን። ከነፃነት የተፈጥሮ ሚስጢርም ጋር እንብዛም ስለሆን - ይመስለኛል። አሁን ብዙ ሰው „ኢትጵያዊነት
ሱስ ነው“ ውስጡን አስጨፍሮታል። ፍንድቅድቅ አድርጎታል። ግን አይዋ ማንፌስቶ እንዳይከፋው የውስጥን ነፃነትን ቀምቶ ታፍኖ መደሰት
ግድ ብሎታል። አምቆ መጨነቅ - መጠበብ - ምጥ። ትንሽ ቃል በዚህ ዙሪያ ሲጻፍ ማዕበሉ ይመጣል። እንደ የፖለቲካ የአቋም ለውጥ
ተደርጎ ይታያል። „ወዴት ወዴት እዬሄድክ ነው ምን ነካህ / ነካሽ“ አለበት። ምክንያቱም ከዛኛው ማዕቀፍ ውስጥ አቶ ሂደት በሩን
ክርችም አድርጎ እስር ቤት መላ የመወሰን አቅምን ሰለሚቀብረው። ውስጥን መፍራት። የተሻለውን መምረጥ፤ ልብ የወደደውን ማድረግ ራሱ
በሚመሩት ድህረ ገጽ ሚዲያ እንኳን አይቻልም። ሶሻሊዝም ሳይታወቅ ማዕቀቡን የሚጥለው በራስ የተፈጥሮ ስብዕና ላይ ነው። ለአንዲት
ጭብጥ ለማትሞላ የማናፌስቶ የወረቀት ፍሬፈርስኪ ፈጣሪ አምላክ የሰጠንን ታላቁን የመኖራችን ምክንያት የደስታ ሰብዕናን መገበር።
ደስ የሚለው ደስ እንዳይል፤ ተስፋ ሊደረግበት የሚገባው በተስፋ ማጣት እንዲስተናገድ ወደን መፍቀድ። አናሳዝንም? ዱላው፤ ውግዘቱ
ብቻ ሳይሁን ኢትዮጵያዊ ዜግነትን እንደ ዳቦ ተሸንሽና ቁርማጯ ትሰጠላች። የዜግነት ሲሶ እና እርቦ። አንዱ የክት ሌላው የእዳሪ።
አንዱ የላይ ቤት ባለሟል ሌላው የታች ቤት ተጠቅጣቂ። የዓድዋ ተጋድሎን ትውፊት በራስ ስንፍና ማክሰል። መጀመሪያ ሰው ራሱን ነፃ
ያውጣ፤ ገራሚው አንድ ሰው ለነፃነት እታገላለሁ ሲል ብዙ ነገር ነው የሚያጣው፤ ለሌላው ራሱን ገብሮ፤ ኑሮውን ገብሮ ነው የዚህ
ቅዱስ መንፈስ ቤተሰብ የሚሆነው። በዚህ ውስጥ ግን የራሱን ነፃነት አጀንዳ አያደርገውም። ከማንፌስቶ ነፃነት ከመጠበቅ ቀዳሚው ነገር
ማንፌሰቶ ማዕቀብ የሚጥልባቸው ግርዶሾችን ሁሉ ጥሶ መውጣት ይገባል። ያልተመቸ ሲኖር መሂስ፤ ከዬትኛው ቦታ መልካም ነገር ሲመጣ
አቀባበል ማድረግ። የሚታዬው ግን በማይነቃነቅ አቋም ውስጥ የሚልን ለመተንፈስ ይህን መሰል ጫና በራሱ ላይ መበዬን ለነፃነት ተጋይነቱን
መርሁን ይታገለዋል። እራስን ያላሸነፈ አምክንዮ ይዞ ለሌላው ራስን መገበር … ደስታን ተስፋን ያህል የነፍስ ቁምነገር ጋር ላለመገናኘት
ራስን ማቀብ።
ስለዚህም ኑሯችን የሚፈቅዳቸው ሙያዊ፤ ተስጥዖዊ፤
ማህበራዊ፤ ወጋዊ፤ ልማዳዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊ፤ ኪናዊ ጉዳዮች ሁሉ በፖለቲካው ትርምስ ውስጥ ገብተው ለአንዱም ሳይሆኑ ባክነው
ይቀራሉ። ዙሪያ ገባው ብክነት። በእጅ ያለ የሚቻል ነፃነትም ብክነት። ስለዚህም ነበር ያን ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን እነሱ
ሲጋቡ እና ሲፋቱ እኛም አብረን አንጋባ // አንፋታ በማለት „አቶ ሂደትን“ የኮለምኩት። እነሱ ይገቡ // ይፋቱ ላለቀ ሥም መወደስ ይሁኑበት፤ እኛ ግን ከዛ ውጪ
መሆን አለብን በማለት መጻፍ ብቻ ሳይሆን እኔም ከዚህ መሰል የጀምላ ጉዞ ራሴን ደስ ብሎኝ በሐሤት አወጣሁ። መደገፍ ያለብኝ ነገር
ሲኖር እደግፋለሁኝ። መሟገት ሲኖርብኝ ተጠቃ ለምለው እሟገታለሁኝ። እርምጃዬ ውስጤን አዳነው። ሰላሜ ተመለሰ። ነፃነት አገኘሁ።
በቂ ጊዜም ኖረኝ። የሐገሬን ሐዘንም ለመጋራት በደንበር እከሌ ይከፋዋል እከሌ ደስ ይለዋል ሳይሆን የራሴ መንፈሴ የተቀበለውን ብቻ
መደገፍ፤ መቃወም፤ መሞገት ቻልኩኝ። ስለምን? የሂደትን ጫና በራሴ ፈነቃቅዬ ከሥልጠኑ ስላባረርኩት። ዐጤዎች፤ እቴጌዎች ቀደምት
ደሞቼ የሰጡኝን አደራ የነፃነት ቃና እና ቅኔ ልሆንበት ቆረጥኩኝ። ፈጸምኩትም። በሂደት ትርምስ ሥር - ነቀል አብዮት አካሄድኩኝ።
ፍጹም የሆነ ሰላሜንም ተጎናጸፍኩኝ። ጸጥ ላለው ተፈጥሮዬም ሰላሙን መንበር ላይ አዋልኩለት።
·
ሳይጀመር የተጨረሰ አምክንዮ አልተፈጠረም።
የማዕከላዊ መዘጋት ከሰሞናቱ ተደምጧል። ቃለ ምልልሱን
ሳዳምጥ የማዕከላዊ መዘጋት ለውጥ ብቻውን ግብ አይደለም የሚል የወል ግንዛቤ አዳመጥኩኝ። የመጀመሪያው እርምጃ የመጨረሻውን ያመጣል
ብሎ ለማሰብ በቀደመው የአንባሳደር ስዩም መስፍን እና የአቶ አርከበ እቁባ የጠ/ ሚኒስትርነትር የዕዝ ሥር የወደቀ የአቶ ሽፈራው
ሽጉጤ ካቢኔ ቢሆን የተደረሰበት መደምደሚያ ትክክል ነው። አሁን ግን በዛ ሁኔታ ላይ አይደለንም። ተመስገን። አያችሁት አይደል የጅጅጋው
ጉባኤ ላይ ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ ስለቀደመት የኢትዮጵያ ሱማሌ ጀግኖች ሲገልጹ አቶ ሽፈራው ሽጉጤም፤ አቶ ደመቀ መኮነንም
ክው ብለው የተተኮሰባት ሚዳቆ በመሆን የውስጡ ሽሙጣቸውን ካሜራው አጋለጠው። በሌላ በኩል ዶር ነገሬ ሌንጮ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር
የራሳሁዋትን ኢትዮጵያ አገኘኋዋት ብለው ማጣፈጫ አድርገዋታል አትዮጵያዊነትን። በ10 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ውስጥ ኢትዮጵያ ሥንት
ጊዜ ከእስር ተለቃች 22 ጊዜ ያው የቁጥር ተማሪ ስላልሆንኩኝ ግድፈት ቢኖር ይቅርታ እጠይቃለሁኝ። የሆነ ሆኖ ትክክለኛውን ስሜታችን
ለመግለጽ አዲስ ቀናችነ ነው። ትክክለኛውን ስሜታችን ለማናገር በራስ የመተማመን ስሜት ፈጣሮብናል ቀስቅሶናል ነው ዕድምታው። ሌላ
ሰው እስኪመስሉኝ ድረስ ነበር በጽሞና ያዳመጥኳቸው „አባይን“ የገለጹበት መንገድ ደግሞ ሌላ ፍልስፍና ነው። ይህ እንግዲህ ግምሽ
ሰዓት የፈጀው የበዕለ ሹመት ቃል ምን ያህል የውስጥ አድማጭም እንደ አገኘ ያመላክታል። ከ„ኢትጵያዊነት ሱስ ነው“ ወዲህም አንድ ቃለ ምልልስ አደማጬ ነበር ከዶሩ
ግን እንዲህ አልነበረም።
„Ethiopia:
የረሳነውን ኢትዮጵያዊነት ዶ/ር አብይ አስታወሱን“
ዓይኔ ነው ጆሮዬ ነው እስክል ድረስ ኢትዮጵያ
የመተንፈሻ ቧንቧቸው ነበረች። ድንቅ ነገር። ሌላ ሌላ ሰው እስኪመስሉኝ ድረስ። አሁን ያለውን የሂደት መንፈስ በጽሞና በአደብ መመርመር
ያስፈልጋል እምንለውም ለዚህ ነው። በዶር. ነገሬ ሌንጮ ሥር የሚታዳደሩ መንፈሶች ሁሉ አስተዳደራቸው ቀጣዩ መንገድ ይሄን ይመስላል።
ምን አልባትም ስሜታቸውን በትክክል ለመግለጽ በሥራቸው ያሉትን ሠራተኞች በሰፊ አዳራሽ ሰብስበው ይህን መሥመር መስቀጠል ከቻሉ መልካም
ነው። እንቅፋቱ በዬጓዳው ስለሆነ። አድሎው በዬስርቻው ስለሆነ። እጬጌው ሂደት እራስን ለመለወጥም በቅጡ መሰናዳትን እዬዘከረ ነው።
አሁን ኢትዮጵያ በአዲስ የተስፋ መቅድም መቅደስም ውስጥ ናት። ቀጣይ እርምጃዎች በመንግሥት አሁን ከ27 ዓመት በኋዋላ መንግሥት
ልበል እና ሊኖሩ እንደሚችሉ አሁን ያለንበት ወቅት አቅም እና አቋም የሚልክልን በጎ መልዕክት በዬአቅጣጫው አለው።
በሌላ በኩል ደግሞ የመጀመሪያውን በር ማለፍ ካልተቻለ
ሁለተኛውን በር ማግኘት አይቻለም። „ሀ“ ሳይባል አንደኛ ክፍል መቼስ አይገባም። መጀመሪያ የጤፍ ዘር ያስፍልገዋል እንጀራ ለመሆን።
የጤፍ ፍሬ ጥሬውም ተቆልቶ አይበላም። ተቆልቶ ይበላ ቢባል እንኳን ለመቁላትም ሂደትን ይጠይቃል። ቤተሰብ ወደ ማዕከላዊ ሊጠይቅ
ሲሄድ ህንፃውን አለማዬቱ በራሱ እረፍት ነው። ጨካኞች በማህበር ተደራጅተው ናዚያዊ ተግባራቸውን የሚፈጽሙበት ሲኦል በዛ አካባቢ
ለሚኖር ሰው ሁሉ የሰቀቀኑ ጩኸት ጋር መኖር አይበለው ነው። ህፃናትም አሉ። ጠረኑ የአካባቢው የስቃይ እና የጣር የደም ጎርፍ ቤተኛ
ነው …
ስለሆነም እራሱ ህንፃውን መልቀቁ በራሱ ለእኔ
ትልቅ ነገር ነው። ለአካባቢው ለኗሪም። የጩኸቱ ቀልብ እኮ አዬሩን አውኮታል። በሌላ በኩል እርምጃው አዲሱ ጠ/ ሚር ዶር አብይ
አህመድ በተመረጡ የመጀመሪያ የሥራ ቀናት ማግሥት መሆኑ በራሱ ትልቅ የእፎይታ ቀጣይ ተልዕኮ እንዳለው ይነግረኛል … ለእኔ ለሥርጉተ
ሥላሴ። ለቀጣዩም እርምጃ የጽኑ ዕምነቴ ተስፈኛ ነኝ እና። ሲቀጥልም በፖለቲካ አስተሳብ ኢትዮጵያዊው ሰው የሚታሰርበት እስር ቤት ሁሉ አለመኖሩ ደግሞ ሌላው ህልሜ ነው።
ስለምን? እስር ቤቱ ካለ ሰው በነፃነት ሃሳቡን ለመግለጽ በተዘዋዋሪም ቢሆን ይቸግረዋል፤ ተጽዕኖ ይፈጣርበታል በዛ ላይ እኛ ይሉኝተኛ
ነን። 43 ዓመት ሙሉ የተገነባው ትውልድ „እታሰር ይሆን በሚል ፍራቻ ነው“ የተለዬ ሃሳብ ሲገልጸ የተለዬ ፖለቲካ ሲያራምድ የጭካኔ
መከዘኛ ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም መባል በራሱ የሚፈጥረው ግሎባል የሥነ ልቦና አቅም፤ እና ግሎባል ዕድምታም ብርቅ ይሆናል። መደብደቢያ
ብቻ ሳይሆን መታሰሪያም መኖር የለበትም። ስንት ዘመን ታስረን ኖርን አይበቃም? አንድ አባት ከኦሮምያ ሲፈቱ በዐጤ ሃይለ ሥላሴም፤
በደርግም በወያኔም ዘመን እንደ ታሰሩ ገልጠዋል። መኖር፤ መፈጠር የታሠረባት ሐገር - ኢትዮጵያ! እርግጥ በደረቅ ወንጀል ደረጃውን
የጠበቀ ፍትሃዊ የሆነ የማስተማሪያ ተቋም ያስፈልገናል። የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ አስቸጋሪ አይደለም። በአንድ ቃል እኮ ነው ይሄ ሁሉ
መንፈስ ሆ! ብሎ በአንድ መስመር የታደመ።
- · የተስፋ ስንኛት ዜማዊነት።
„ማዕካላዊ አልተዘጋም“ የተስፋ ስንኛት ዜማዊነት
የሹመት በዕሉን መሪ ንግግር በጥሞና ቢደመጥ እኮ ለሚነሱ ማናቸውም ነገሮች መልስ ሰጪ ተስፋዎች አሉት። በዛ ቃል ውስጥ ከተስፋ
ጋር ላለመግባባት የወሰኑ ተስፋ አስቆራጭ ግንዛቤዎች መልሳቸው እዛ ውስጥ በተገኘ - ከፈቀዱ። በሌላ በኩል ማዕከላዊ ውስጥ የሚታሠሩት
በፍጹም ጠላትነት የተፈረጁት የነፃነት፤ የዴሞክራሲ፤ የሰብዐዊነት፤ የተፈጥሮ አርበኞች ናቸው - ሊታዩ ሊደመጡ የማይፈለጉ። እነሱ
በኢትዮጵያ መሪ ንግግር ደግሞ አካሌ፤ ወገኔ፤ የእኔ የነፃነት መንፈስ ተብለዋል። ከዚህ ቀደምም በኦህዴድ አንድ ስብሰባ ላይ የጽ/
ቤት ሐላፊ በነበሩበት ጊዜ „„ኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ባይኖራት ኖሮ 60/ 70 የፖለቲካ
ፓርቲ ባላስፈለገ ነበር። መደማመጥ ስሌለ፤ መስማማት ስሌለ ነው እንጂ 60 ፓርቲ አያስፈልገንም ነበር። ይሄ ችግር ደግሞ የሚፈታው
በማኩረፍ አይደለም። የእኔ ሃሳብ ካልተደመጠ ብቻ በማለት አይደለም። በመቀራረብ ነው።“ ብለው ነበር። ይህ የውስጥ እምነታቸው እንጂ ዛሬ
መሪ ስለሆኖ የተለጠፈባቸው አይደለም። ሙሉውን „ህሊና“ በሚል
ርዕስ በስሜ ጉግል ብታደርጉት ታገኙታላችሁ። አሁንም እኮ አለመደማመጥ ነው በጣት በሚቆጠሩ ቀኖች ነው ሲዊዲንን እዬተመኘን ያለነው። „40 ዓመት የኖረች እውር አንድ
ቀን እደሪ ቢሏት እንደምን ብዬ“ እንዳለችው …. ጸሐፊ ዶር. ዘላለም እሸቴ እኮ „ዘብ እቆምለታለሁኝ“ ያሉትም የሚስጢሩን ሚስጢር
ስላመሳጠሩት ነው። ፈጣሪም ሚስጢር ስለገለጠላቸው። ሊሂቁ ማድመጥን ወደዱ፤ የወደዱት ቅንነት የአብይ መንፈስ ጋር አዋሃዳቸው።
መደማማጥ ጠፍቶ ነው እንጂ መሬት ያልያዙ፤ በእጅም
የለሉን አዬር ላይ የተንሳፈፉ ምኞቶችን ከማምለክ ይልቅ፤ በወል ሆኖ የንግግሩን እያንዳንዱ ጭብጥ መመርመር፤ ማጥናት ያስፈልጋል፤
በዛም ላይ እንደ ነፃነት ፈላጊ በቅንነት በጋራ በቡድን በቡድን ሆኖ በንግግሩ ዙሪያ መወያዬት ያሰፈልጋል፤ እም ይቅርታ ለካንስ
አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ላይ ነው ህዝባችን።
ነጻነት ከራበን፤ የትውልዱ ብክነት ከውስጥ ከሆነ
ንግግሩን ስንኝ በስንኝ መመርመር ያስፈልጋል። ምን አልባት ንግግሩ ካልገባነም ወይንም ጠጥሮብናል ወይንም አላስጠገናውም። ለዚህ
ነው ወጣ ገብ የሆኑ ሁኔታዎች እዬታዩ ያሉት። ሃሳቡን አለመደገፍ ቢሆን እንዴት መልካም በሆነ። የሚወጣለት ሳንክ ሲጠፋ ታምሰን
እናምሳለን።
እርግጥ ነው በራስ ማንፌሰቶ ላይ ያለለፈም ከሆነ
ሌላ ፈተና ነው። ተሰውሮ ያለ እኛ የማናውቀው የሴራ ጥምልምል ከኖረም፤ የማናውቀው የማንፌስቶ ህልም ካለም ሌላው ዳገት ነው። ያው
መቼስ ከበጎ ዕሳቤ ጋር አትገናኙ፤ አትረፉ ያለን ፍጡሮች ስለሆን። ትውልዱም ደምህን በብክነት አወራርድ ተብሏል። ያ ፍደኛ ህዝብ
በሰው ልኳንዳ ቤት በጥምር ከፍተህ ደግሞ እንደለመደብህ እርዱን ለአውሬ ላቅርብ ካልሆነ ከዚህ መንፈስ ጋር ትእግስት አሳጥቶ የሚያበጣብጥን
ነገር ባልኖረ።
የህዝብ ድጋሚ ስቃይ እንዴት ይናፍቃል? በውነቱ
ሰው መሆን ተጠዬቅ ያሰኛል። ስንቱን ታዘብነው አዬ እጬጌው ሂደት ማንዘርዘሪያህ ሰማያዊ … ቀድሞ ነገር የሚሆን፤ የሚመስል ነገር
አለውን ከኖርንበት ረግረግ ጋራ? የሩቁን ትቶ ከ10 ዓመት ወዲህ የፖለቲካ መግለጫዎችን በሙሉ፤ የስብሰባ ዕድምታዎችን የራሳችን
የነፃነት አስከባሪ ድርጅቶችን ሁለመና እስኪ መርምሩት ማጠጋጋት እንኳን አይቻልም። በፍጹም! እኔን ይመስላል የሚል ደፋር ፓርቲ መቼም ሊኖር እንደማይችል ይሰማኛል። ስለምንተዋወቅ፤ በሚገባም ስለተፈታተሽን።
የነበረው ፍላጎቶ ምኞቱ ከኢትጵያዊነት አቅም ጋር የሚመጣጠን አይደለም - አልነበረምም። ከአድዋ ድል ለመነሳት ስለመፍቀዱ እራሱ
አጠያያቂ ነበር። አዲስ ዕሳቤ የማፍለቅ አቅሙም የኖርንበት ነው … እኛ አለን ከምንለው አቅም ክህሎት በላይ ዘመኑን የዋጀ ብቃት
ያለው ነው አዲሱ የመንፈስ ጸጋ። የፈጣሪ ጠበለ ጻዲቅ። የሰው የእጅ የዳንቴል ሥራ ሳይሆን የፈጣሪ ነው - ጥበቡ።
- · የመጋቢት 24 ቀን 2010 „ቃለ ምህዳን“ ሥልጡን ጥበባዊ መልስ አለው።
„ቃሉ“ ሥልጡን መልስ ይሰጣል። „ቃለ ምህዳን“
ስለሆነ። ዕምነት ካለን። ሃይማኖት ከኖረን፤ በእግዚአብሄር የምናምን ከሆነ። ስለነገ የአደረጃጀት ሆነ የአመራር ሂደት መታገስ ከተገኘ።
በታቆረ የኩሬ ውሃ ላይ ሙጥኝ ያለ ሃሳብ አይደለም አዲሱ የለውጥ ዕሳቤ። ተስፋ ማድረግ የሚቻለው ተስፋ ለማድረግ መፍቀድ ሲቻል
ብቻ ነው። ይህም ተቀንቶበት እኮ ነው አሁንም መንፈሳችን የሚተረትሩ የሟርት ሰላቢ ማሳሰቢያዎች፤ የተስፋ ቆራጭነት ዜማዎች አድምጡ፤
አንብቡ ተብለን እዬተገደድን ያለነው። እንግዲህ የቀድሞ ምርኩዞች ጡረታ የሚወጡበት ጭምጭምታ ወይንም ግምምግምታ ካለም … ከንቱ ውዳሴ መለቃቀም። ለዛውም በትንሳኤ ዋዜማ በተስፋ ስንቅ ላይ መርዶ
ይመራችሁ እንባላለን፤ ስጋት ይጎብኛችሁ እንባላለን፤ ጥርጣሬ ይርበባችሁ እንባላለን። ዛሬ እኮ ብርሃነ ትንሳኤ ነው። ምን አለ ዕውህዳችን
እንኳን ሻማችን አብርተን በቅን ተስፋ ብንጠብቀው - ምንዱባኖች። ይህም ተቀናበት … አለመታደል።
ወደ ቀደመው ስመለስ „ማዕከላዊ ሊዘጋ“ ነው ሲባል
ቃሉ ራሱ ትንፋሻችን ሰብስቦልናል። አሁን ደግሞ ተዘጋ ሲባል ትንፋሻችን እንዲሰበስብ መፍቀድ ያስፈልጋል። ደስታን ለመቀበል መፍቀድ
ያስፈልጋል። በስተቀር ተስፋ እዬራቀን፤ ውስጣችን እዬተራቆተ ማግስትን መፈቀድ ለመቻላችን፤ ችግራችን ብቻ ሳይሆን የሥነ - ልቦናም
ተጠቂ እንሆናለን። በራስ ፈቃድ በሽታ መግዛት። እኔ እህታችሁ ከወሰንኩኝ ቆዬሁኝ። መልካሟን ብቻ እርእሷን ፈልጌ አነባለሁኝ። መልካሟን ብቻ እርእሷን ብቻ ፈልጌ አዳምጣለሁኝ። በቃ። ደከመኝ። የፈለገ የነፃነት አርበኛ ቢሆን፤ ልሰማው የፈቀድኩለት ቢሆን አሁን ተስፋዬን ካገኘሁበት
ላይ ብቻ ነው አቅሜን፤ መንፈሴንም፤ መዋለ ጊዜዬንም እማፈሰው። ይሄ እርምጃ ጊዜ ይቆጥባል፤ የውስጥን ሰላም ይሰጣል።
- · ይታይሽ።
ይታይሽ የጎንደር የተለመደ ሥም ነው። እና ፈጣሪ
አምላኬ ፈቅዶ 2013 ላይ „አቶ ሂደትን“ ስጽፍ ይታይሽ ብሎ ሥም አቀበለኝ። አዲሱን ሥምም አበቀለልኝ - አዶናይ። እናም ዛሬ
የሚታዬኝ የሟርት ጨለማ ሳይሆን ከብርሃንም ብሩህ ብርሃን ነው!
ከጭብጦ ተስፋም መጠነ ሰፊ እቅፍ ነው። ከመንፈስ ራፊ ማረፊያም
እጅግ ውቅያኖስ የሆነ ቦታ ነው። ግን … ግን ሁልጊዜም እዮባዊነትን
ምራኝ አይቀሬ ነው። ጊዜ የሂደት፤ ሂደት የጊዜ ውጤት ነው። ማደራጀት የበቆሎ ጥብስ አይደለም። ወይንም የፈረስ ግልቢያ። መምራትም
የወንዝ ዳር ሽርሽር አይደለም። ጸጋ፤ መክሊት ይጠይቃል። ከታች ጀምሮ በህዝብ አግልግሎት ተሳትፎ ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል። ተመክሮ።
የህዝብን ኑሮ ታች ላይ ጀምሮ መኖርን ይጠይቃል። ከህዝብ የእለት ዕለት የመኖር ኩህነት ጋር መሰልጠንን ይጠይቃል። መሬት ረግጦ
ከመሬት ከታች ከሥር መነሳትን ይጠይቃል። መሪነትን ለማጎልበት አጋጣሚ የሚሰጠውን ማናቸውም ሂደት በአዎንታዊነት መጠቀም ያስፈልጋል።
ክህሎት የዛፍ ፍሬ ሳይሆን የጥረት ዕንቁ ነው። ይታይሽ ይህን መረመር አድርጋ ስለሄደች ከቅኖች ጋር ተስፋን ሰንቃ ተስፋን በእዮባዊነት
ትጠብቃለች። ተስፋዋን የሰጣት አምላክም ተግባሩን በተሟላ ሰብዕና ያኮመኩማታል። ሌት እና ቀን አምላኳን በሻማ ታመሰግናለች።
- · ሰው ሆኖ መፈጠር ደስታ ነው።
ደስታን ለመቀበል መፍቀድ በራሱ ጤና ነው። የሰው
ልጅ እንደ ሰው መፈጠሩ በራሱ ደስታ ነው። ሰው መሆኑ ራሱ ደስታ ነው።ስለዚህም የደስታ ዋዜማ የሆኑ መልካም የምሥራች ዜናዎቸን
የእኔ ብሎ ማድመጥ ካልተቻለ በጠቆረ ጉሽ ለመኖር ራሱ ባለቤቱ ፈቅዷል። ሲለዚህ ጨለማ የሸለመን አቤቶ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ
ስለምን እንኮንነዋለን? ክፉ ነገር ሲታሰብ ውስጥ ይጠቁራል ደስታ ይርቃል። መልካም ነገር ሲመኙት ግን ደስታ ይሰጣል ውስጥም ይፈካል፤
ዕድሜም ይጨምራል። ደስታ የሚሸመት ሳይሆን ስሜትን በመልካም ነገር
በማትጋት የሚገኝ እርካታ ነው። በጎ ነገሮች ለሚፈቅድ ስሜት ምላሹ ደስታ ነው። ቸርነትን ለተቀበለ ስሜት ምላሹ ደስታ ነው።
ደስታ የፍቅር ልዩ ስጦታ ነው። ስጦታም አንዱ የፍቅር ተፈጥሮ ረቅቅ ሚስጢር ነው። እናቱ እጬጌው ሂደት ለጥ ብዬ የጸጋ ስግደት
ሰገድኩልህ። የተባረከው እጬጌው ሂደት ብሩክ ነህ። መንግሥታዊ የሆነ ዜና ከዛ ቅቤ ጠባሹ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሚዲያ ሁሉ ይገኛል
ብዬ እራሱ አስባለሁኝ - ዛሬ። እናንተዬ አንድ ነገር ረስቼ፤ ለካንስ ኢትዮ ሱማሌ ሚዲያ አላቸው። ይህን በውነቱ አላውቀውም ነበር
…
- · ሃሳብን ሊያሳካሉት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከመጀመር ነው የሚጀምረው።
የሰው ልጅ የኑሮ ጳጳሱ ተስፋ ነው። ተስፋን ሲያውቁት
ተስፋን ይቀልባል። ተስፋን ሲያውቁት መኖርን ይሰጣል። ተስፋን ሲቀበሉት መብራትን ያቀብላል። ተስፋን ሲያቀርቡት መንገድን ይመራል።
ስለሆነም የተስፋ ቅርጥምጣሚ፤ ፍርፋሪ፤ እንጥፍጣፊ፤ ጠብታዎች ሁሉ
የተገባ አክብሮት እና የተገባው ክብር ሊሰጣቸው ይገባል። ተስፋን የሚሰጥ እኮ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው። ፈጣሪ እራሱ ተስፋ ነው።
እና ስለምን ተስፋ ይጋፋል? ፍቀት!
ይህ ዛሬ መዳፍ ላይ ያለው የተስፋ ጮርቃ ከብት
ታርዶ፤ በግ ታርዶ ሳይሆን እነ ሰማዕቱ የእኔ ሰው ገብሬ እንደ በግ ሥጋ ተጠብሶ፤ እና ሺብሬ እና ህጻን ነብዩ ተሰውተውበት፤ እነ
ሰምዕቱ አሳፋ ማሩ በአደባባይ ተረሽነውበት፤ ሻ/ አጣናው ዋሴ እሰር ቤት ውስጥ ህዬወታቸውን ገብረውበት፤ እነ ፕ/ አስራት ወልደዬስ
ራሳቸውን አቅልጠውበት ስንቱ ይጠቀስ? እነ አርበኛ አበባ ካሴ ታርደውበት በሰው ግብር የተገኘ ነው …
አንድ ፈላስፋ እኮ ትልቁን ተልዕኮውን ለመከወን
የሚነሳው „ከሐሳብ“ ነው። ሐሳቡ በራሱ ለፈላስፋው የግኝት ግቡን አያሳካለትም። ሃሳቡን ሊያሳካለት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከመጀመር
ነው የሚጀምረው። የንድፉ ሂደት የዕድሜ ልክ ሊሆን ይችላል። የብዙ መልካም ነገሮች ፈጣሪዎች ምኞታቸውን፤ ህልማቸውን ሳያዩ ያልፉ
እና የፈጠሩት መፍትሄ ግን ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ እዬዳበረ፤ እንደዘመኑ እያደገ ሲሄድ ይታያል። አንድ ጊዜ የተፈጠረ ነገር
በዛው ላይ አይቆምም። ያድጋል። አሁን አውሮፕላን እንይ፤ ከንድፉ ጀምሮ በዬዘመኑ በቅርጽም በይዘትም በሁኔታም፤ በአግልግሎት ሰጪነትም
ከንድፉ በላይ ሥልጣኔው በተወራራሽነት አንድ ቦታ ሳይቆም ቀጥሏል። ምን አልባት የዛሬ 50 ዓመት ዛሬ ካለው የአውሮፕላን ቅርጽ
እና ይዘት፤ የአገልግሎት መጠንም ሊለይ ይችል ይሆናል፤ ምን አልባትም አብራሪዎች ላይፈለጉ ይችሉ ይሆናል። መሬት ላይ ተቀምጦ በሪሞት
ኮንትሮል ሊሆን ይችላል በረራው የሚመራው። ስለሆነም በቅድሚያ የሃሳቡ ጤናማነት ነው መፈተሽ ያለበት። ቀጥሎ ሐሳቡን ለመፈጸም የሚችል
ሙሴ አለ ወይ ነው? ማሳውስ? እርግጥ ነው ማሳው ወጣ ገባ፤ ኮረኮንች የበዛበት፤ አሽዋ የጠናበት ነው። ነገር ግን ለፈጣሪ የሚሳነው
የለም። በእርግጠኝነት ረቂቅ ዕድል አለን ይህን የሚደለድል መሃንዲስ ፈጣሪ ሰጥቶናል።
- · ተስፋ በተፈጥሮው አዎንታዊ ነው።
- ተስፋ ማደረግ መልካም ነገር ነው። ተስፋ አዎንታዊ ነው። ተስፋ ሲመጣ በአውንታዊነት እና በቅንነት መመልከቱ የሚበጀው ለራስ ነው። በዛ ላይ ተስፋ ማድረግ ባይኖር ለነፃነት ተጋድሎ ከዘመን ወደ ዘመን የተሻጋገር የሰው፤ የንብረት፤ የመዋዕለ መንፍስ ግብር በግፍ ባልቀረበበት ነበር። ለነፃነት ተስፋ ስለተሰነቀ የተፈጥሮ ግብር ቀረበበት። ዴሞክራሲ ሰፍኖባቸዋል በሚባሉት ሐገሮችም እኮ የሰው ልጅ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ተሟልቷል ማለት አይቻልም። በሰለጠኑ ሐገሮች ድሆችም አሉ። ተሸናፊ አሸናፊ ሃሰብ አለ። ተሜንታዊነት በእጅጉ አጠቃን። የሚገኙ የሚታዩ ተስፋዎችን ባቀለልናቸው ቁጥር ቀጣይ ተስፋዎችን ለማዬት ይቸግረናል። ተስፋችን ዳፍንት እንዳይዘው ባይታሚን ኤ ያስፈልገው ይመስለኛል። ቢታሚን ኤ ራዕይን ለመግለጥም ይረዳል። ነገር ግን የተስፋ ልቅና ሰብዕና የማዬት እቅሙ እዬደከመ ሲሄድ መኖራችን እራሱ ወደ አለመፈለግ ያሸጋግረናል። የስሜቱ ፍሰት በዚህ መልክ ከሆነ በትውልድ የተስፋ ግንባታ ላይም ጨለምተኝነትን ውርስ፤ ቅርስ እንዲሆን እንፈቅዳለን። ይህ ከሆነ ስለምን በወጣትነት የመኖር ኑሮ ብቃትስ አቅምስ ተገበረ? ይህ ሁሉ ዘመን ስለምን ትውልዱ ባከነ? አሁን እኮ የተወለደው ልጅ ጽንስ ሁን ወደ እናትህ ማህጸን ተመለስ እኮ ነው ግብግቡ?
- · የእስር ቤት ልማታዊነት።
ሃሳብን አስሮ ልማታዊነት እንዴት? መፍጠርን አስረህ
ዕድገት እንዴት? ግኝትን ቀፍድደህ ብልጽግና እንዴት? ስንቱ የተፈጥሮ ዓይነት ይሆን ከሥር ነፃ የሆነው? ለእኔ ማዕከላዊ ብቻ አይደለም
ማሰቃያ ቤት፤ ኮተቤ ያለው የክንፈ የደህንነት ማዕከልስ? ትግራይ ላይ ያለው ባዶ ስድስትስ የወልቃይት ጠገዴ የትግራይን ወጣት አዛውንታት
የበላው ዋጮስ ያ ገሃነም? በዬቤቱ ያለው ወዘተረፈ እስር ቤትስ? ገበሬ መንደር ውስጥ ያሉ በቀድሞው ጊዜ የአገልግሎት መስጫ የነበሩ
ሁሉ እስር ቤቶች ናቸው 27 ዓመት ሙሉ። የአማራ የህልውና ተጋድሎ ሲነሳ እኮ ት/ ቤቶች ሁሉ ወደ እስር ቤት ተዛውሯል። ያተሰሩት
በሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች የተጋድሎ አርበኞቸስ ጉዳይስ፤ ኢትዮጰያዊነት እራሱ እስረኛ ነው። የምንፈቅደው ብሄራዊ ሰንደቃችን ልሙጡ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አዳኝ መርሃችንም እስረኛ ነው። ኢትጵያ ውስጥ ያለው አዬርም እስረኛ ነው። ሁሉ ነገር እስረኛ ነው። የእኔ የምንለው
ብሄራዊ መዝሙር ራሱ የለንም። ልማታዊነት?
… ነገር ግን በዛ የአብይ መንፈስ መሪ ቃል ውስጥ
ለእስር የሚዳርጉ የአምክንዮ ጭንቅላቶች ሁሉ ትህትና፤ ተፈጥሯዊነት፤ ህጋዊነት፤ ሰዋዊነት፤ አክብሮት፤ ምህረት፤ ይቅርታ፤ ተስፋ፤
መቻቻል፤ ራዕይ፤ መደማመጥ፤ ሰጥቶ መቀበል ሊመራቸው እንደሚገባ ዕውቅና ተሰጥቶ አዳምጠናል። ይህ ደግሞ በማለት ብቻ ሳይሆን በመሆን
ስለመረጋገጡ ተስፋ ማድረግ ይገባል። ተስፋ ማድረግ ለማይፈቅድ ሰብዕንም ቢሆን መብት ነው … ተስፋዬ በሚለው መስመር አቅሙ ካለው
መቀጠል ነው። ካለው ማን ይከለክለዋል?! ሜዳውም ፈረሱም መጭ ይባልበት … ግራም መብት ነው ቀኝም መብት ነው። ወደ ፊትም መራመድም
መብት ነው ወደ ኋዋላም መብት ነው። መሰለጠንም መብት ነው አለመሰልጠንም መብት ነው፤ ባለበት መታቆርም መብት ነው ተራማጅነትም
መብት ነው፤ መራመድም መብት ነው ባሉበት መቆዘምም መብት ነው። መቆምም - መነሳትም - መነቃነቅም - መጋደምም - መተኛትም ሁሎችም
መብቶች ናቸው። መፍቀድም አለመፍቀድም መብት ነው። ምርጫው የባለቤቱ ነው። እኔ እምጽፈው እራሴ መሆን የምፈልገውን እና መሆን የቻልኩትን
ብቻ ነው … የሚከተለኝ ቅን ካለ እሰዬው ነው፤ … ደስ ይለኛል። ሐሤትም አገኝበታለሁ። የጸጋዬ ድህረ ገጽን ስመሰርት መሪ መፈክሬ
„ትውልዳዊ ድርሻችን እንወጣ፤ እልፍ ነን እና ዕልፍነታችን እልፍ እናድርገው“ ነበር ስለሆነም የድርሻዬን ካልኩኝ እረፍቴ ነው
- የህሊና። ሰብል ለቅንነት ከተገኘ ደግሞ አዕምሮ ነው።
- · የህይወት ፈተና።
የህይወት ትልቁ ፈተና ሥነ - ልቦናን ጤናማ አድርጎ
መቅረጽ፤ ማደራጅት መምራት ነው። ውስጥን በቅንነት መሥራት። ለዛውም ሶሻሊዝምን የፈጠሩት የትውስት ንድፈ ሃሳብ የፈጠሩት ተውት
አድርገውት፤ እኛ የሙጥኝ ብለን 43 ዓመት ይዘነዋል የሸር ፖለቲካን።
በዚህ ብክለት ነው አቅምም፤ ተፈጥሮም፤ ክህሎትም፤ ሥነ - ልቦናም ሲታጨድ የኖረው። ሶሻሊዝም ጸረ ሰብዕን ነው። የሰው ልጅ እንደ
እጅ እና እንደ የራስ ቅል አሻራው በዛው ልክ የተለያዬ ነው። ሥነ - ባህሪያችን ዥንጉርጉር ነው። ያደግንበት ማህበረሰብ፤ ቤተሰብም
አስተዋፆ አላቸው። ቦታ ጊዜ እና ሁኔታም እንዲሁ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው። ሥነ - ልቦና ገርቶ ወደ መልካም አቅጣጫ መምራት ግዙፉ
የትውልድ ሃላፊነት ነው። ከሁሉም የገዘፈው ፈታኙም፤ አድካሚውም የተግባር ማሳ ነው።
ሁሉ ነገር በአሉታዊ ብቻ የሚዩ ሰዎች ይኖራሉ።
እነኝህ በተፈጥሯቸው በጎ ነገር ፈጽሞ የማይታያቸው ጨለምተኞች
ናቸው። የጠሉት መላዕክ ሆነ ቢመጣ እንኳን አይቀበሉትም። አይጥማቸውም። ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ደግሞ በአሉታዊና በአውንታዊ መሃከል
ሦስተኛ ሰብዕና ተላብሰውም የሚፈጠሩም መኖራቸው ነው። ነጭ እና ጥቁር ቀለም ብታዋህዱት ግራጫ ይሆናል። እነኝህ ሦስተኛ ስብዕና
አላቸው የምላቸው ግራጫማ ሰብዕና ያላቸው ናቸው። እጅግ ጥቂት
ሰዎችም የዚህች ዓለም ቤተኞች ናቸው። አነዚህ ግራጫማ ሰብዕና ያላቸው ሰዎች ደስታ አመጣ ብላችሁ ደስ ሲላችሁ፤ በጥድፊያ ደግሞ
ጨለማውን ሃዘን አምጥተው ይከልሱበት እና ደስታችሁ ቅጽባታዊ ይሆናል። ቆይቶ ደግሞ ተመልሶ ሙቀት መጣልኝ ስትሉት በረዱን ይለቁባችኋዋል።
ለኑሮ ወጥነት ለማነቀናቅ የተፈጠሩ ናቸው። ሰይጣን እስከ ሠራዊቱ አለና እንዲህ ዓይነት ሰዎች መፈጠራቸው ግድ ይላል።
አሉታዊውም ሆነ ግራጫማ ሰብዕና ያላቸውን ፍጥረቶች
ወደ አዎንታዊ ለማምጣት በትግል፤ በዓዋጅ፤ በድንጋጌ፤ እልህ በማጋባት አይደለም። እንደዛ ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ሰው የኢትዮጵያን
ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በእጁ፤ በአንገቱ፤ በማተቡ፤ በራሱ፤ በአልባሳቱ ባልፈቀደው ነበር። የወያኔ ሃርነት
ቀንደኛ ጠላቱ ብሄራዊ ሰንደቃችን ነው። ስለምን? አንድነትን ይፈራው ስለነበረ። ይህ ሁሉ እስር እንግልት የዛ ጦስ ነው። ግን ቻለ?
አልቻለም። አሸንፎ ወጣ። በዬትም ቦታ በተካሄዱ የአማራ ተጋድሎ አብዮታዊ እንቅስቃሴ፤ በጠቢቡ ቴወድሮስ ካሳሁን የባህርዳር ኮንሰርት
የስፖርት ሜዳ እስኪመሰል ድረስ ሞትን ፈቅዶ እስራትን ፈቅዶ እየሆነበት ነው። ራሱ የወያኔ ማንፌሰቶውን ድርቅ የመታው፤ በርሃ ላይ
የበቀለ መርዛም ዕጽ አድርጎ ካለ እርሾ ምድረበዳ ያደረገውም ይሄ አሉታዊ እሳቤው በሰንደቁ ላይ ያስወሰደው እርምጃ ነው።
ቢሆን ኖሮ ሁሉም የፈቀደውን እንዲይዝ ቢፈቅድ
ግን መከራው ይቀንስ ነበር። የሰው ልጅ የተከለከለውን ነገር ሞክሮ ማዬት በዛም መኖርን የበለጠ ይፈቅደዋል። ባትከለክለው ግን ጉዳዩ
የአዘቦት ይሆናል። ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የአዘቦት ነው ማለቴ ግን አይደለም። ከእሱ በላይ እኔ በህይወቴ ደስታም ድምቀትም ነፍሴንም
የሚታዳጋት አንዳችም ነገር የለም። ቁርባኔ ነው። አንድን አምክንዮ ለዛውም ደም የተገበረበትን አቁም፤ አትውደደው፤ አታድርገው ሲባል
ጥላቻ ገዢ ይሆናል።
ስለዚህ የሰው ልጅ በእንቢተኝነት መንፈስ ውስጥ
ሊያቆዬው የሚችለው አቅሙን ለማስተካከል ሂደትን ይጠይቃል። ጠንካራ ተቋምም ይጠይቃል። መፍትሄ አምንጭነትን ይጠይቃል። ጥረትን በተከታታይነት
በቋሚነት መከወንን ይጠይቃል። የህሊና ሥራ ከባዱ የቤት ሥራ ነው።
አዕምሮን መለወጥ በቅንነት ውስጥ መኖርን ይጠይቃል። አትስረቅ ብለህ እምትሰርቅ ከሆነ ማለትህ ይናቃል። ክብርህም ይኮስሳል።
ሁሉ ነገር ያለው አዕምሮ ውስጥ ነው። ስለሆነም
አዕምሮን መግራት የቡፌ ግብዣ አይደለም። ሂደትን ይጠይቃል። ለሂደት፤ ቦታ፤ ጊዜ፤ ከነገሮች በላይ አቅምን ማሳደግን፤ ሁኔታን፤
ጥረትን፤ ያለመታከትን ሌሎች ተባባሪ አምክንዮዎችን ማያያዝን፤ ተቋም መፍጠርን ይጠይቃል። ከሁሉ በላይ ለ43 ዓመት ሶሻሊዝም የሴራ
መከዘኛ፤ እንደ ጥንቸል መመኮሪያ ሆና የኖረች ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ ልክ ወስጧን ከውስጧ በቀለሟ ሃዲድ ለመዘርጋት ጊዜ ያስፈልጋታል።
የነበረን ትልቁ ችግር መሬት ላይ ለመኖር የተፈቀደለት አንድ ሙሴ
ማጣት ነበር፤ ሙሴ መራጩ ፈጣሪ በትንሳዬ ዋዜማ ተግባር ገብ ሙሴ ሰጥቶናል። ተመስገን! አሉታዊነት /ጨለምተኝነት/ ግራጫማዊነት
/ዝንቅ/ በብርሃኑ አዎንታዊነት አንድ ቀን ይረታል። ባይረታም ይቀንሳል … የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው …
- · ተከታታይነት።
የሥነ - ልቦና ጉዳይ ተከታታነትን እና የትጋት ሥራን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ እና ዶር
ምህረት ደበበ አዕምሮን ወደ መልካም እና ወደ ቅን ነገሮች
ለማምጣት እኮ መሰረት ጥለው እዬሠሩበት ነው mindset። ያን ጊዜ ልብ ያለው አልነበረም። አድማጩ በመቶ የሚቆጠር ነበር እኔ
ዶር አብይ አህድን የሚቀናቀን መንፈስ ሲነሳብኝ በዓይኔማ አትምጡ ብዬ ለማመሰከሪያ „ለአብይ ኬኛ“ ስጠቀምበት እንኳን
አንድ ሺህ አይሞላም ነበር። አሁን ከ300 ሺህ በላይ ሆኗል።https://www.youtube.com/watch?v=sokxTcjrpv8&t=542s „ልብ የሚነካ አስገራሚ ንግግር Dr
abiy ahmed # mind set“ ተሳታፊውም ቁጥሩ ራሱ ኢትዮጵውያን የናፈቀን
አዎንታዊነት ቅንነት ስለመሆኑ ምልክታችን ነው። ይህን መርሃዊ የመንግሥት ጉልበታም ጉዳይ አድርጎ ማምጣት ነው የሚጠበቀው።
በቅኖች አስደግፎ ማጠናከር። በዚህ የሚሰራ መደበኛ ፕሮግራም መጀመር። ሚደያዎቻችን እኮ „የመርዶ፤ የሟርት“ ዓዋጅ ነጋሪዎች
ናቸው።
አዎንታዊነትን
በሰው በውስጥ መሥራት በአንድ ጀንበር አይከወንም። እኛም ልናግዘው ይገባል። ሰውን ሰውኛ አድርጎ ማላመድ ቀላል የሆነ የትውልድ የቤት ሥራ አይደለም። ራሱ ሚደያችን በስንት ዓመታችን መልካም ዜናውን ለማስተናገድ እንኳን አቅሙ ስስ ነው። በዬለም የተባዛ። የሚገረመው የምሥራች ዜናው አብሮ እንዳይቆይም ሌላ የዋይታ እና የሟርት ተግባርም ታቅዶ እዬተከወነ እያዬን ነው … በፊት አይሆንም፤ ሲሆን ደግሞ ለምን ሆነ። እራሱ የኢህዴግ ስብሰባ ከተለመደው ውጪ ሌላ ለውጥ አያመጣም የጠ/ ሚር ምርጫ የለውም እያሉ በተከታታይ ተስፋን ሲገድሉ የነበሩ ሃሳቦች ሁሉ ነበሩ። ቢያንስ ስብሰባው እስኪያልቅ ድረስ እንኳን ተስፋን እንዳንጠብቅ ጋሬጣ መረጃ እያቀረቡ ሊያዘናጉን፤ ትጥቃችን እንድንፈታ ሊያደርጉን የነበሩ ፈታኝ ነገሮች ሁሉ ነበር። እክሌ በዚህ ስብሰባ ተገኘ/ አልተገኘም … ወዘተ። ዋናው ቁልፍ ነበር የሚያስፈልገን። ከሰማያ ሰማያት መላዕክ ቁልፍ ይዞ መሬት ላይ ይጠበቀ ነበር። እሱን እራሱ በጠበጡት አወኩት።
„የጥልቁን መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልዕክ ከሰማይ ሲወርድ አዬሁ።“ (የዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ ፳ ቁጥር ፩) ቢያንሰ አሁን ተስፋ ያጣ በሥነ - ልቦና የተጎዳ ህዝብ ደስታውን ለመቀማት የሚደረገው ሩጫ፤ ተስፋን ለመቀማት ባይቻል ለማደፍረስ የሚደረገው ግብግብ ተግ ቢል መልካም በሆነ። ግን አይዋ ዲያቢሎስ ምን ሰርቶ ይደር። ማህያው ይሄ ነው ማታኮስ። አሁን ያለው
ሁኔታ መልካሙን ነገር አጉልቶ አውጥቶ በዛም ተስፋን መሰነቅ ሲገባ፤ በጣም ስስ የሆኑ silly ነገሮችን ይዞ በመቅረብ የተገኘውን ደስታ ምድረ በዳ ለማድረግ በትጋት እዬተሠራበት ነው። ኩድኩድ።
·
በርግጥም የአብይ
መንፈስ የትግራይን ህዝብ እጬጌው አዲሱ ሂደት ይታደገዋል።
በቋሚነት
ሰንበት ላይ እምታደምበት
„ኢትዮ ሚደያ“ ነው። ሚዛን ስለሚያስጠብቅልኝ። ስለሆነም ዛሬ አንድ ቀልቤን የሳበው ተጠዬቅ አገኘሁ - ከጸሐፊ አቶ ተስፋሁን ከአትላንታ ነው። „እነ አቦይ ስብሃት ያላደረጉትን የትግራይን ህዝብ ዶ/ር አብይ ያድኑት ይሆን?“http://www.satenaw.com/amharic/archives/54267 „በዶ/ር አብይ አህመድ የጠ/ሚኒስትር ምርጫ ላይ የሕዝብ አስተያየት ከአዲስ አበባና መቀሌ“
በዚህ ሥር አንድ አስተያዬት አንብቤያለሁ። ሌላ
ቦታ ያሉትን ነዋሪዎች ስለምን አይጠዬቅም የሚል። እይታዬን ልግለጽ …
አንደኛ ኢትዮጵያ ሁለት ርዕሰ መዲና ነው ያላት፤
አንዱ አዲስ አባባ ሁለተኛው መቀሌ። ሰለዚህ ሌላ ቦታ የአሜሬካ ድምጽ ዘጋቢ የለም። ያሉት ዘጋቢዎች በሁለቱ ርዕሰ መዲና ነው ድርሻቸው
- ይመስለኛል። አትርሱት „ታላቋ ልዑላዊት ትግራይ“ ሁለተኛው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሴራው ምሽግ ያደረገው ይህን ህዝብ ነው።
የድክመቱ፤ የዝርፊያው፤ የስርቆቱ፤ የሴሰኝቱ፤ የገዢነቱ፤ የወረራው፤ የጭካኔው መሰረቴ የሚለው ይህን ህዝብ ነው። ስለዚህ መደመጥ
ያለበት ዋሻዬ ነው ከሚለው ህዝብ መሆን አለበት። እና ትክክል ነው። ዕንባ ለመጋራት የነበረው ፈቃድ ምንም ስለነበር። ሰዋዊነታችን
ሃዲዱ ተጥሶ ስለነበር። ተለያይተናል እኮ።
መለያዬታችን በፕሮፖጋንዳ እንለብጠው ካላልን በስተቀር። እራሳችን በራሳችን እናታልል
ካላልን በስተቀር ፍቹ በቂምም በጥላቻም የታጠነ ነው። ይልቅ ለአቶ ተስፋዬ ጹሐፍ ስመለስ … አዎን!
በትክክልም ያድኑታል። ከቃለ ምልሱ የሚገርም ተስፋ አላቸው። ራሱን አስችዬ ለመጻፍ ሁሉ ፈልጌ ነበር። መልካሙን ነገር ለመቀበል
እንደ አለመታደል ሆኖ አቅም ስለሚያንስን። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሚዲያው ሁሉም የሚሰራው በአሉታዊ ብቻ ስለሆነ እንጂ የአብይ መንፈስ
ትግራይን ያድናል የሚል ጽኑ ተስፋ አለኝ። የትግራይ ወጣቶችን ለማናገር አስተርጓሚ አያስፈልጋቸውም። በአጠገባቸው የሚደረገውንም ማናቸውንም ንግግርም ራስ እግሩ እነሱ ስለሆኑ
አስተርጓሚ አያስፍልጋቸውም። በአስተርጓሚ አለመሆኑ በራሱ የሚስበው ለቅን የትግረይ ነዋሪዎች የፍቅር ጣዝማ ይኖረዋል።
የነገሩ መገጣጠም እኮ የዕድምታ አባቶችን ተጠዬቁ ያሰኛል። ትግረኛ ቋንቋ ይችላሉ።
ፍቅሩን ባይፈልጉት አይፈቅዱትም። አሁን በዬትኛውም ሁኔታ ሲመዘን የትግራይ ወጣቶቹ እጅግ ብስጩ ሆነዋል። በራስ የመተማመን አቅማቸው
ደግሞ ከመደበኛው በጣም ወደ ላይ የወጣ ነው። የራስ መተማመን ሲያንስም ሲበዛም በራስ መተማማን አደጋ አለው። ማመጣጠን የሚቻልበት
መንገድ ያስፈልጋል። ሰብዕናው የተበደለ ስለሚያደርገው። ከበዛ ማበጥ
ነው ካነሰ ደግሞ የበታችነት ነው። ሁለቱም አደገኛ ናቸው።
ስለዚህ ይህን „ኢትጵያዊነት ሱስ ነው“ ችሎት አለው ለማመጣጠን። ያልተፈቱ፤ የተበተቡ፤ ካለመጠን የሄዱ የተለጠጡ ነገሮችን ሁሉ
ወደ ማዕክል አምጥቶ መሰመር ያስይዘዋል „ኢትጵያዊነት ሱስ ነው“ ግን እዮባውያን ከሆን ብቻ ነው። ዕውነት ደግሞ ምስክር ናት።
የወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ከትግራይ
የሚነሱ ማናቸውም የስብስብ መንፈስ ድብልብል ነው። ድንቡልቡል። በዛው ዙሪያ ነው የሚሽከረከረው። ህዝብ ይህን እንደጠላው እዬታወቀ፤
የአደባባይ ሚስጢሩን ሁሉ ሊሂቃኑ ሲያዳልጣቸው ነው የሚደመጡት። ትንሹ ህጻን ቢጠዬቅ የሚመልሰውን እነሱ አይደፍሩትም። „መጠላት“ እኮ ከባድ ነገር ነው። ልብን እንደ ዱባ ይቀረድዳል።
እነሱ ግን እዛው ላይ ነው የሚረግጡት። ሊሂቃኑ እራሱ መዳን አለባቸው።
ከቅዱሱ አቶ ገ/ መድህን አርያ እና አንድ ሁለት
ከምንቆጥራቸው በስተቀር። የሚገርመው ግን ነዋሪዎች የመቀሌ በሚገርም ሁኔታ ለስላሳ መንፈስ ነው ያላቸው። የሚያስፈራ ነገር አላዬሁበትም።
ለዚህ ደግሞ አሁን ብቻ ሳይሆን በዶር አብይ አህመድ ንግግሮች ሥር የሚጻፉ ዕይታዎች ላይ ቀን ቀን በቀን ስለምከታታለው እኔ ምንም ብስጨት አይታይባቸውም። እጅግ የሰከነ፤ እጅግም የረጋ፤ ተስፋ
የሰነቀ መንፈስ ነው ያለው። ስለዚህ የአብይ መንፈስ አሉ ከሚባሉት የትግራይ ሊሂቃን በላይ በላይ ተሻግሮ ያጣናቸውን ልጆቻችን ወደ
ውስጣችን ይምለሳቸዋል። ህሊናቸው ሊዳኘው በሚገባ የእውነት ፍትህ ላይ እንዲመክሩ፤ እንዲወስኑ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል ከዚህ
ቃለ ምልልስ የተረዳሁት ቁምነገር የአዲስ አባባ ነዋሪዎች ከደስታቸው ብዛት የተነሳ „ኢትዮጵያ“ በዚያ የባዕለ ሲመት ስንት ጊዜ
እንደተነሳች ሁሉ ቆጥረውታል። አስተያዬታቸው እራሱ ሰብዕናቸውን ከገጻቸው፤ ውስጣቸውን ከህሊና አቅማቸው ጋር አዛምደው የንግግር
ጥበቡን ልቅና በሚገባ ገልጸውታል። ፍቅር የሆነ የማይፈራ መሪ ለስላሳ አግባቢ እና ተግባቢ አንጋገር ውበት እንዳዩም ህልም ዕውን ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ተስፋ እንዳደረባቸው፤
ይህን ተስፋም ከዚህ ቀደም አዳምጠው እንደማያወቁ ነው የተናገሩት። ተመስገን!
ወደ ነገረ ተጋሩ ስመጣ ዛሬ ወያኔ ሃርነት ትግራይ
አለላቸው ነገስ? አላግባብ የሆኑ ነገሮች ላይ ጋዜጠኞቻቸው ሁሉ ያን በደል ግርዶሽ ሰርቶ ከማባበል ዕዝነ ልቦናቸው „ሰው“ እንዲሆን
መፍቀድ ይኖርባቸዋል። እያወያዩ „ት“ ከተነሳች ትዕግስት ይሁን ትህትና ይሁን ትምህርት ይሁን ሳያወቁ ገና „ትግራይ“ ይነሳል በማለት
ሃሳብን በፋስ ሲቆርጡት ሁሉ ታዝቢያለሁኝ። ይህን ዕድል ለመጠቀም አቅልን ከእዮብ መሸመትም ያለባቸው ይመስለኛል። ትልቁ ዕድል ነው
ይህ ዕድል፤ እንዲያውም የበደሉ ክርፋት ረቂቅ ስለሆነ አስማሚ፤ አስታራቂ መንፈሱን የእኔ ማለት ይኖርባቸዋል። ከማንኛችንም በላይ
እኔም አብይ ነኝ ማለት አለባቸው። ከማንም እና ከምንም በላይ …
… የአቦይ ስብሃት፤ የአቶ በረከት መንታ መንገድን
ያሰላ ነው። ተከድኖ ይብሰል። ያልተፈተሸ መርዝ ተከዝኖበታል። … ግራ ቀኝ ትርፍ ሲዝቅ ነው የከረመው፤ እንዴትስ ከእነሱ ማዳን
ይታሰባል? ለዘለአለም ቋሚ የነቀርሳ ተቋም መፍጠር ነበር ህልማቸው። አድርገውታልም። አሁን አኮ ትግራይ ላይ ለተዋህዶ ሃይማኖት
እንኳን መሆን እዬተሳነው ነው። የአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ገዳም መደፈር ከማንም በላይ ሊከፋ የሚገባው የትግራይ ህዝብ ነበር። እንህን
ቅዱስ አባት ክብር የሰጠ፤ ታቦት የቀረጸ ገዳም እኮ ነው አሁንም በደል እዬተፈጸመበት ያለው። እነሱ ስሌታቸው „ቁስ“ ነው። „በሥነ
ልቦና የበላይነትም“ እንዲሁ። ያ ህዝብ ኢትጵያዊ ትውፊቱን ተነጥቋል ኢትዮጵያ የነበረችበት ግን ዛሬ በሃሳብም በግብርም የሌለችበት
የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነው የነበሩት። የአድዋ ድል ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ምኑ ነው?
የሆነ ሆኖ መፍትሄው ይህን ወርቅ ዕድል ወደ ልቦናቸው
ተመልሰው አጥር ቅጥር ሊሆኑለት ይገባል። በመንግሥት መሥሪያ ቤትም
ያሉ በመታበይ ላይ የተንጠለጠሉ መንፈሶችም ወደ ልካቸው መውረድ እና እንደ አቅማቸው ለመኖር መፍቀድን በራሳቸው ጊዜ
መከወን ይኖርባቸዋል። የተንጠራሩ መንፈሶች አሉ። ባለፈው የአማራ
ቴሌቬዥን የጣራ ገዳም አዲስ ዘመን ላይ የነበረውን ውይይት ሳዳምጥ ያቆስላል። በአማራ ክልል በትንሽ ከተሞች እራሱ ያለው ግፍ ከ
- እስከ አይባልም። ለዛውም የመገለውን ሃሳባቸውን የገለጹት ወጣቶች እስከ አሁን እስር ቤት ካልገቡ ነው። ዱላውም አካላቸውን ካላጎደለው
ነው። መታሰራችን፤ መደብደባችን አይቀርለትም እያሉ ነበር ሲናገሩ የነበሩት። ደንበጫ፤ ንፈስ መውጫ ላይም መሰሉን መንፈስ ነው የሰማሁት።
ቢያንስ ሰው በቀዩ ስለምን ስደት ይፈረድበታል? የበይስ ተመልካች ስለምን ይሆናል?
በድለናል ማለት ሲችሉ ተበዳዩም የአባት አደሩን
ባህል ወይንም ይተብሃል ይገዛዋል። ኢትዮጵያ እኮ ባልተጻፈ ህግ ከሚተዳደሩት ሐገሮችም አንዷ ናት። „በህግ አምላክ“ ቃሉ ብቻ ወታደር
በሌለበት ሁሉን ቀጥ ያደርጋል። ወንጀል ሠርቻለሁ ሲል እኮ እራሱ ሄዶ ነው እሰሩኝ የሚለው ኢትጵያዊው ሰው …
የአብይ ፎርማት አዲስ ነው፤ ስለዚህም የትግራይ
ልጅ የሊሂቃኑን ሆነ የእነ ማህበረ ሴራ የአቶ በረከትን ጋንታ ጥምር ሴራ ጥሶ ወጥቶ „እኔም አብይ ነኝ“ ማለት ይኖርበታል። ጥላችን
በፍቅር ማሸነፍ የሚቻለው ራስን ቀድሞ በማሸነፍ ነው። እስከ አሁን ባለው በባዕለ ሹመቱ፤ በሰሞኑ የጅጅጋ ጉብኝት እንዲሁም የመቀሌ
ነዋሪዎች ያደረጉት ውብ ጅምር ነው - ለእኔ። ደስም ብሎኛል። ምክንያቱም እኔ ገና ለመጸነስም ላልታሰቡ የትግራይ ህፃነት ስለሆነ ጭንቀቴ ፍቅር እንዲጠበቃቸው እሻለሁኝ።
- · የኑልን ቃለ - እርካብ …
ሌላም ኑልን ብቻ ሳይሆን ቀረጥን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ
ለሚመጡትም ሆነ ለሚወጡት አዲስ ነገር አለ ይሄው ኮምኩሙ - ቅኖቹ። ሟርተኞች የተፈጠሩበትን ይሥሩ፤ እኛም የተፈጠርንበትንም እንከውን።
በተረፈ መልካም በዓል። ለነበረን ዘንካታ ጊዜ ዝቅ ብዬ ምስጋናን እንሆ አልኩኝ። ይገባችሆዋል የእኔ ክብረቶች ከፈጣሪ በታች እናንተ
ያልተከበራችሁ ማን ይከበር? ኑሩልን!
·
በጣት በሚቆጠሩ ቀናት ምን ተከናወነ። ከግብጹ መሪ ጋር
በስልክ መነጋገራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ።
„ጠ/ሚ አብይ አህመድ ለተመላሾች ከቀረጥ ነፃ እቃዎችን ይፋ አደረጉ Ethiopia Dr Abiy Ahmed“
„ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ተለቇል ማህከላዊ እስር ቤት ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል Ethiopia Dr Abiy
Ahmed“
„[ሰበር ዜና] በዶ/ር አብይ ትዕዛዝ አስክንድር ነጋን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ Ethiopia Dr Abiy
Ahmed“
„WATCH:
Dr Abiy Ahmed, Abdi Iley and Lema Megersa's Speech“
·
በሁሉም አቅጣጫ የአብይ
መንፈስ አይዞህ
ባዮች በጥቂቱ
እንዲህ ይላሉ
…
ይድረስ ለሳዲቅ አህመድ እያየን እንራመድ !! እያስተዋልን እንተንፍስ !!
ከበድሉ በዛብህ አውስትራሊያ ሜልበርን
„ዓቢይ አህመድና የኢትዮጵያ ፖሊቲካ መስፍን ወልደ ማርያም“
„መልካም ጅማሬ
ኦባንግ ይደመጥ“
„ዘብ ቆመናል ክቡር የኢትዮጵያ ልጅ ዶ/ር አብይ አህመድ (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)“
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“
(ከአቦ ለማ መግርሳ የተወሰደ።)
እግዚአብሄር
ይስጥልኝ ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ