የተከለከለ ~~--- ፍቅር።

የተከለከለ ~~--- ፍቅር። ሲፈቀር - ይገርም … እኮ! ምንልበል ታዲያ ….


ከሥርጉተ ሥላሴ(Sergute©Sselassie)
 03.10.2013 ከኮሽ አይሏ ሲዊዘርላንድ

„በውኑ ሰው እግዚአብሄርን ይጠቅመዋልን?“ 
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፳፪ ቁጥር ፪)

ፍቅር የትውልድ ዋዜማ ነው።

ፍቅር ምንድን ነው? ማድመጥ ነው። ፍቅር ዜማ ነው - ጹዑም! ፍቅር የመንፈስ ጥንግ ሽብሻባ ነው። ፍቅር የስሜት ቃናዊ መዝሙር ነው። ፍቅር የአኃቲነት ብርቅ ወረብ ነው። ፍቅር የመስጠት ለጋስ ፏፏቴ ነው። ፍቅር የታሪክ ማውጫ ፍትኃ - ነገሥት ነው። ፍቅር የውስጥነት ፍውሰት ነው - ድህነት! ፍቅር ጣዕም ነው ንጥር - መረቅ! ፍቅር ብጡል* ነው ክብረት። ፍቅር ኃብታም ነው ዲታ። ፍቅር ምህረት ነው ዘንባባ! ፍቅር ወድ ነው ስጦታ። ፍቅር ሩህሩህ ነው ርግብ። ፍቅር ጻድቅ ነው የመስቀል ወተት። ፍቅር መስዋዕትነት ነው ጤና አዳም። ፍቅርን ሲሰጡ ሊፈቀሩ የሚችሉ ፍጡራን ፍቅርን ሲከለከሉ ደግሞ ማመጻቸው አይቀሬ ነው!  ይፈነዳል። ዋ!

እናት ከሁሉም በላይ ትውደዳለች። እናት የመጀመሪያዋ የህይወት ትምህርት ቤት ናት። እናት መቅድመ የቤተሰብ አሰተዳደሪ፤ የተፈጥሮ ሙሁራ ሊቀ-ሊቃውንት ናት። እናት የርህርህና መግቢያም ናት።  እናት ደግሞ ሴት ናት። እኔ በዓለም ደረጃ የፍቅር ምልክት ዓርማ ሊሆን የሚጋባው ልብ ሳይሆን እናት ነው መሆን ያለበት። ስለምን? እናት የምትሰጠው ፍቅር የማያብል ነውና። እውነተኛ የፍቅር ተፈጥሮ የሚገኘው ከስፖርት ማልያና ከእናት ብቻ ነው። እናት የሥነ ፍጥረት ሙሉዑ አጀንዳ ናት! እናት የመንፈስ ቋንቋ ናት!

እስኪ እንገስግስ አብረን … ወደ ተለምኩት፤ ጉዞ በጋራ መልካም ነው። ኑሮም በወል ጣዕሜ ነው። … ሴት እህት ስትሆን ትፈቀራለች። ሴት አክት ስትሆን ትጠጋላች። ሴት ሚስት ስትሆን እንደ ነፍስ ትታያለች። ሴት ጓደኛ ስትሆን ትታመናለች። ሴት እናት ስትሆን የጸጋ ስግደት ይሰገድላታል። ሴት ይሁን ይሁን … አሜን አሜን … ስትል ….. ሰጥ ለበጥ ብላ ስትገዛና ስትረገጥ …. ስትመች ትመረቃለች ….

እኔ እንደማስበው በእምነቴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አምስቱ  አዕማደ ሚስጢራት ላይ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልዑቅ ነገረ ሳይመር መቅረቱ በጣም ይጎረብጠኛል። እንደሚገባኝ ግን የተዋህዶ ልጆች ለቅድስት እናታችን ባለን ፍጹም ልዩ ፍቅርና ስስት የአምልኮ ስግደት ይገባታል ብለን እንዳንሟገት ብልሆቹ አቨው አስበውበት፤ ምንአልባትም መንፈስ ቅዱስም አቀብሏቸው ወይንም ሚስጢር ገልጦላቸው ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም ከመንፈሳዊ ዓለም ወጥተን ወደ ጋህዱ ዓለም ስንመጣ … በፖለቲካ አስተሳሰብ ሴት ላቅ ስትል ግን „ጉልበታምንት“ ይለጠፍላታል። በጠራ ቋንቋ „ጉልበታም“ ትባላለች። የተከለከለ ፍቅር ይሏችኋል ይህ ነው። ቁስለት!

ሴት ገረድ ስትሆን ትወደዳላች። ሴት ሎሌ ስትሆን ትደነቃለች። ሴት የቤት ውስጥ ሰራተኛ ስትሆን ስንዱ ትባላለች። ሴት ስታጎርስ የራህብ ደራሽ ትባላለች። ሴት ጓዳ ጉድ … ጉድ ስትል ዓይን አብሮ ይዞራል። መንፈስም አብሮ ይንከራተታል። ልብም ዳንኪራውን ያስነካዋል። ስሜትም አብሮ ይከትማል። ሴት እንግዳ ስታስተናግድ ትመሰገናለች። ሴት ልጅ ስትሰጥ በዓይኔ ላይ ፍሰሺ ትባላላች። ሴት ስልጣን ልትጋራ ብቅ ስትል ግን „ኃይለኛ“ ተብላ ትኮረኮማለች ወይንም ትባረራለች። ሌላ ድልዝ ይፈልግላታል። ሌላ የሰብዕናዋ ድክምት ቁፋሮ ይጀመራል።  የተከለከለ ፍቅር … ጎባጣ

ሴት ገንዘብ ያዥ ስትሆን ትመረጣለች። ሴት ገንዘብ ስትሰበስብ ታማኝነቷ ይሰበክላታል። ሴት አዳራሽ ስታሰናዳ ትሞካሻለች። ሴት ስነጥፍ ወይንም ስነጠፍ እንደ ብርቅ ትታያለች። ሴት ቅራኔ ውስጥ ገብታ ስተቀረቀር ይጨበጨብላታል። ሴት መድረክ ላይ ወጥታ አቅም ባላው ብቃት እኩል ስትመጥን ግን በግሳፄ ትባረራለች ….. ድገም ሳትል ከቢጫው ቀዩ ካርድ ቀድሞ ያለ ማስጠንቀቂያ ከጨዋታ ውጪ ትሆናለች። ነዳላ ገጠመኝ።

ሴት ስትለብስ ትፈቀራለች። ሴት ስተሸቀረቀር እንጉርጉሮው ላቅ - መጠቅ ይላላታል። ሴት የተፈጥሮን ፍቅር ስትመግብ ንቢት ተብላ ትሞገሳለች - ትመገባለች - ትጎረሳለችም። ሴት ሽክ ብላ ከጎን ስትጓዝና ግብዣ ላይ እኩል ስትቀመጥ አጃችን* ይሞላል። ሴት ገብያ ወጥታ ቀጨር መጨሬውን ስትሸማምት አበጀሽ ትባላለች። ሴት ኮስሜቲክ ስተገዛዛ ውዳሴ ይነጠፍላታል።  ሴት ወንበርን ልትጋራ ጥንካሬዋን ስታስመከር ግን ትገፈተራለች …. ቆመጥ ይዘጋጅላታል ….. የተከለከለ ፍቅር … ነቀዝ!

ሴት ቤት ስትውል፤ እንደ እመቤት ትታያለች፤ ጫዋ የተረጋጋ መንፈስ የረበባት እዬተባለ ይሰበክላታል። - ደስታ ነዋ ስታፎከፉክ። ሴት አንገቷን ደፍታ መከራን ስትቀበል ቅኔ ይዘረፍላታል። ሴት የልጆች አሳዳጊ ብቻ ስተሆን ትበረታታላች - ትሸለማለች። ሴት በማይታዩ ሩትን /ጥቃቅን/ ተግባራት ስትሰማራ ማን እንዳንቺ ትባላለች። ሴት አንደበቷ ታስሮ የሳሎን ጌጥ ስትሆን ማለፊያ ይባልላታል። ሴት ግን ኃላፊነትን እኩል ለመጋራት ብቅ ስትል ጦር ይሰበቅባታል። የተከለከለ ፍቅር …. ምግለት!

ሴት ስትጋግር … ስትሰራ …. ስታጥብ … ልብስ ስትተኩስ፤ ስታረግዝ …. ስታጠባ …. ከሚፈለገው ቦታ ላይ ተገኝታለችና ይዘፈንላታል። ከዚህ አለፍ ብላ የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ስታነሳ ግን ትወረወራላች …. እውነት ለመናገር በዘመናችን ያሉ ሴቶች እንኳን ጥቃና እንክብካቤ ሊያገኙ ቀርቶ ገፍተው የሚወጡት እንኳን ለምነው ለመታገል እንኳን ፈቃድ አያገኙም በወንድ ትምክህተኞች …. ዛሬም ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ካላው ኮረብታ ላይ እንዳሉ አሉ እነ ተባዕት ….

በፍጹም ሁኔታ የነፃነት ትግሉ ሆነ፤ ነገ የሚታሰበው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረቱና እርገቱ ከሴቶች ውጪ ሊታሰብም ሊሳካም እንደማይችል በጣም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የነፃነት ትግሉ የሴቶችን ሙሉ ተዋፆ በአጽህኖት፤ በተደሞና በአርምሞ ይጠይቃል። አኔም የጥቃቱ ማዕደኛ በመሆኔ …. በልበ ሙለነት እጥፋለሁ … እንዲህና እንዲያ … ትርፉ ትራፊና ፍርፋሪ መሆን ነውና ….

ይህቺ ለመላሾ „ እነ ተባዕት ቦታ አካፍለናል“ የሚሏት አለ …. ልጥፍ ሽፋን ለማንም አይበጅም - ነገንም አያበጅ። የዶደመ …. መንገድ ነው። የነፃነት ትግሉ ሙሉዑነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሴቶችን የመጠነ ተሳትፎ በቅንነት ተግባር ላይ ሲያውል ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ካላት ያልተነካ ቅምጥ ኃይል በላይ የሴቶች ሃብት እስከ ዛሬ ድረስ ሥራ ላይ አልዋለም። … ነገም ከፍቶት ይታዬኛል።

እርግጥ ማሳሳቻ አስፓልት አለ። „የሴቶች መምሪያ ከፍተናል … ጉዳያቸውን የሚከታተል መዋቅር ዘርግተናል“ … ይህ ሴቶችን ብቃት የሚያቀጭጭ አፋኝ የማስመሰያ ጅራፍ ነው። በማናቸውም ዘርፈ ብዙ እኔ ነኝ ባለ ኃላፊነት ሁሉ ሴቶች ጉልበታም አቅም አላቸው። ለዛ የሚመጥን ቦታቸውን አትጋፉ ነው መሰረታዊ ትግሉ። እድሉን ያገኙ ሴቶች መቼ ተዝርክርኮ አምሮና ሰምሮ፤ በጥራትና በጥንቃቄ እንዲሁም በስልትና በብልኃት ሁለመናው ያምርበታል። ነሴቶች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚተጉት …. አብሶ በእናትነታቸው ፍጹም የማይታይ ሰማያዊ ጸጋ ስላላቸው ምቹ ሁኔታ  ካገኙ፤ በቂ እንክብካቤና ጥበቃ ለመክሊታቸው ከተደረገ …. ማን ችሏቸው። ያኮራሉ!

አውሮፓ ያላችሁ ሁሉ እንደምትከታተሉት አውሮፓ በኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ተሰቅዞ ሲባትልና ሲብተለተል የመፍትሄው ጭንቅላት የተገኘው ከጀርመን ነበር። የጀርመኗ መሪ ጠ/ሚ አንጅላ ሜርክል ቀጥ አድርገው በማያዝ ማገር ሆነው አውሮፓን ከውርዴት ዘመኑንም ከጥፋት ታድገውታል። ጠ/ሚር ሜርክል ፓን አውሮፓኒስት ናቸው። በተግባር የከበሩ የመጀመሪያዋ የጀርመን ተወዳጅ ሴት መሪ። የእንግሊዟ ታችር፤ ንግስት ኤልሳቢጥም፤ ተፍርተው በአጭሩ ተቀጩ እንጂ ልዕልት ዲያናም አሳይተዋል አስመስክረዋል … ያን ጉልበታም ተዝቆ የማያለቅ ብቃት …. ከብልህነት ጋር። ይህ በኒውዘላንድ፤ በአውስትራልያ፤ በፊላንድና በብራዚልም ተመሳጥሯል። ሲዊዘርላንድ በሰባት ሰዎች ትመራለች አራቱ ሴቶች ናቸው። ያውም ቁልፍ ቁልፍ ቦታ የያዙ … በጀርመን ከምርጫ በኋላ ያለውን ሽግሽግ አልተከታተልኩትም እንጂ ቀደም ባለው ጊዜ በርካታ ሴት ሚ/ራት ነበሩ …. የእውነት አባዛኞቹ ሴቶች በማለት የሰከሩ አይደሉም። እናታዊ ሥነ -ምግባራቸው አይፈቅድላቸውምና!

በዘመነ ክሊንተን ያን ስሜትን የሳበ የፕ/ ቢል ክሊንተን ቅብጠት ብልኋ ባለቤታቸው እመቤት ሄነሪ ክሊንተን የሆነውን እንዳልሆነ አድርገው ትቢያ አልበሰውታል። በወቅቱ አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጠይቋቸው ነበር … „የሚባለውን አልሰማሽንም … አላነበብሽውንም ሲል“ ብልኋ እመቤት ግን „ እናቴ ከልጅነቴ ያስተማረችኝ ሰው የሚለኝን ከሰማሁ የምሰራው የሰወችን እንጂ የእኔን እንዳልሆን ነግራኛለች፤ አስተምራኛለች። መርሄ ይህ ነው። እኔ የኔን ሥራ እሰራለሁ ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ይሰሩ“ ነበር ያሉት። ሰማዬ ሰማዬት የዘለቅ ዕጹብ መልስ ነበር። በዚህም ትዳራቸውን ከነዙፋኑ እስከብረዋል። ማለፊያ ብቃት!

ከዚህም በኋላ በዘመነ ፕ/ባራክ ኦባማ የውጭ ጉዳይ ሚር/ ሆነው እጅግ ውስብሰብና ፈታኝ በሆኑ መሰናክሎች ሁሉ በማለፍ የሴቶችን የመወስን አቅም በተግባር አሳብበውታል። አሁንም የፕ/ ባራክ ኦባማ ባለቤት ቀዳማይ እመቤት ሚሻዬል ኦባማ ሁለገብ ንብ በመሆን ባለቤታቸውን ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጣን ባለቤት አብቅተዋል … ለዚህም ደረጃ ያበቋቸው እርሳቸው ናቸው። ዓይን ካላችሁ ከዚህ ሀቅ ጋር ዓይናችሁ ይታረቅ ዘንድ ብዕሬ በጽሞና ያሳስባችኋል …

በአፍሪካ ታሪክ ጉልበታሙ የፕ/ ማንዴላ ተገዳሎ የምዕተ ዓመቱ ታላቅ መዘክር ነው። በፆታዊ ችግር የተፈጠረውን ነገር ዝለሉትና ወ/ሮ ዊኒ ማንዴላ ባላቤታቸው እስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የነፃነት ትግሉን በግንባር በመምራት፤ ልጆቻቸውን በማሳደግ፤ ለትዳር አጋራቸው አጥር ቅጥር በመሆን የጽናት ወተት ነበሩ። ይህን ከባለቤታቸው ጋር ይጻጻፉ የነበሩትን የነፃነት ትግል ትምህርት ቤት ከነበረው ዝክረ ደብዳቤዎች ማገናዘብ ይቻላል።

በእኛዋ እናት ሀገርም … በቀደመው ዘመን ንግስት ዘውዲቱ የመቻልን ተፈጥሮ፤  ከእቴጌ ምንትዋብ የተግባር ሚስትነትና አርበኝነትን፤  ከከዕቴጌ ጠይቱ የብልህነት - ፖለቲካ መሪነትና አማካሪነት ጠበብትነትን ጠብተን አድገናል። በዘመችንም … ሳራ ግዛው፤ አያልነሽ - አለምዘውድ፤ ሺብሬ ደሳለኝ፤ ብርቱካን ሜዲቄሳ፤ ሰርካለም ፋሲል፤  ርዕዮት ዓለሙ፤ በላይነሽን ስንቶቹን የነፃነት አርበኞች እናት ሀገራችን አፍርታለች። መሬታች መሃን አይደለም። ተሳትፎውን ያነጠፈው የወንድ በላይነት ብቻ  ነው። አሁንም  በአንድነት ወ/ት ወይንሸት የምትሰጠውን ቃለ ምልልስ አኑትና አጣጥሙት …. ያው ታች ስለሆነች ቅጥቀጣው ያልፋታል ብዬም አስባለሁ … ቀና ካላች ግን ቅንጧን ነው … በለመደ እጅ … እህህህህህ!  

እኔ … በአጽህኖት እናገራለሁ። የፖለቲካ መሪዎቻችን የውስጥ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። በፍጥነት። በንግገራቸው ውስጥ እንኳን ብጣቂ እርስት አልተሰጠነም። እንኳንስ በፍላጎታቸው ልብ። በራዕያቸው አንጎል። ምንአልባት ትዝ የምንላቸው የራባቸው ጊዜ ይሆናል። ለነገሩ ነጭ ሀገር ፋስት ፉድም አለ … እራሰም ይጋገራል … እንዲሁም በዬአጋጣሚው የሚሾሟቸው የበታች ገዢዎቻቸውንም ለውጡ ገፍቶ እንዲያነጥራቸው እንሻለን። አቅም በመበተንም አንቱ ናቸውና! ይደግም። የበታቾቻቸው አቅም በመበተን አንቱ ናቸውና!  የበላዮች የበታቾቸውን የሚከታተሉበት መስመር ቢኖር መልካም ነው።  የጉሮሮ አጥንቶች እነሱ ናቸውና። የፓለቲካ አመራር ልም ነው። ጣጣውን የጨረሰ ለስምሪት ንጥር ቅቤም የተሰናዳ። እኔ የማዬው ዘመንተኛው ፖለቲካ ግን ሽርክትና ግርድፍ ሆኖ ነው። አብሶ አጋርን በመገፍተር እረገድ ከንፍሮ የወጣ አንድም መሪ አልገጠመኝም። ቆሞ ስለ አርበኛ አንስት የሚመሰክር ዓይናችን አላዬም ….  

እርግጥ ነው ሥር ላይ ያለው ተግባርን የሚያደምጡት፤ ከበታቾቻቸው ለዛውም ስታስቲክሱን በሩቁ ነው። ያው ወያኔ ባላው የተዛነፈ ዳታ ይወነጀላል። የኛም እኮ ያው ነው። ከታች ወደ ላይ የሚተላለፈው። የበቃ ፍጽምና ያለው ተሳትፎ …  ለማዬት ወረድ ይበሉ። ሰፊ መድረክ ይክፈቱ። የትችት አንባ ይወጁ። እንዲያድጉ እንዲመነደጉ ከፈለጉ። … የበታቾቻቸው እኮ ስለፓርቲያቸው ማንፌስቶ ክርክር ቢገጥማቸው ከተረት ተረት ያለፈ ከሽምደዳ ተራ ምት የዘለለ የማኒፌስቶውን ጭብጥ ይዞ ጭብጥን በጭብጥ አፋጭቶና አታግሎ የነጠረውን የፓርቲያቸውን አቋም አሸናፊ ለማድረግ እንኳን አቅም የለሾች ናቸው። ማረር!

ያው ቁንጮቹ የሚሉትን በተገኘው አጋጣሚ የጎረሱትን እዬፈቱ ሁሉ ሲደግሙና ሲሰልሱ ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ከዛው ለዛው ሲዳክሩ ነው የሚታዩት። ተመስገን ነው ዛሬ እድሜ ለ ኢሳት ስበሰባ በስብሰባ ነውና ከሊቃኖች አዳዲስ ነገር ስንቅ ስለሚገኝ ተሽሎ ሊሆን ይችላል። ግን የራስ ጌታ ለመሆን ማንበብ መልካም ነገር ነው። የነፃነት ትግሎች ለድል እርከን የደረሱት አጋራቸውን ባሊህ ብለው ነው።  … እርግጥ ላይኞቹ ሴቶች ማለት ሲጀመሩ የታችኞች ቅጂውን እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋቡታልና እባካችሁ ላይኖቹ ጀመሩት …. ግን በተለበጠ መልኩ ሳይሆን ቁምነገር ባለው ዕውነት - ክልብም። ዝም ብሎ ከሆነ ልጥፍ ይሆንና የተላመጠ አገዳ ይሆናል ምኖታችን።
  
ተከታታይ የሆነ አቅም ያለው የመንፈስ ጥሪት ለመገንባት ይሞክሩ ፖለቲከኞቻችን ….፤ ሙሁሮቻችን። የሴቶችንም ነገረ ሚስጢር አክለው …. የሃይማኖት አባቶቻችን ሲያሰተምሩን ነገረ ማርያምን ነጥለው ሳይሆን አስቀድመው በፍቅራ እነሱ ቅጥል እያሉ ነው። የእናታቸው ፍቅር ግብግብ እያደረጋቸው ነው። እኛም እንደነሱ ሆነን እናታችን የማናሰነካው። የድንግል ነገር የሁለመናችን ገዢ የሆነውም በዚህው ነው። ማለት ለተዋህዶ አማንያን። አሳምረው ስለጠረቡን ነው።  

ይህ ትግል የሚባለው ጀግና … አርበኛና ሰማዕት …. ጎድሎበታላ ታላቅ ነገር ቅናዊ ዕይታ፤ ሥልጣንን የማጋራት ግልጽነት፤ ኃላፊነትን በቅመም የመመጠን ትርጉም ያለው ተግባርና እርምጃ ሳይፈጠር አሯል። አይታይም። የመከነ ጉድ ነው …. በዬትኛውም ሁኔታ በቦታው የሌለ ነገር ሴቶችን  በአክብሮት እኩል ለማሳተፍ ያለው ፈቃደኝነት ልሙጥ መሆኑ ነው። ድርቅ የተጫወተበት፤ ዝናብ ሲሄድበት የከረመ አለት የመሰለ ለዛ የለሽ ዕሳቤ ነው። በጣም በረቂቅ ሁኔታ በሴቶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ዘመንና ጊዜ ይፈታዋል የሚል ግምት የለኝም። የተሳሳረ ትብትብ ነገር ነው። በሩ ተቀርቀሯል። ጭላንጭል መተንፈሿ ቧንቧው የታነቀ ነው ….  ለዛውም እኮ ቆርጠው የሚወጡት ጥቂት ሆነው እነሱን እንኳን በአግባቡ ለመያዝ ምንም …. ታውቃላችሁ?! ምንም ነው 00000

ህይወት ካለ ሴቶች ኮረኮንች --- አመዳም --- ቡላ ---- የፋደሰ ---- ቀዝቃዛ --- የነፈዘ ----- ነው …. የትግሉም ዕጣ ፈንታው ይህ እንዲሆን ተገምድሎበታል። ይፍታህ በሉት! ነይልኝ --- ነይልኝ --- „የህይወቴ ህይወት“ ለዚህ ብቻ ፍቅር … ይፈለጋል። ትውልድን ለመገንባት፤ ታሪካዊ ድርሻን ለመወጣት ግን ለአጃቢነት ወይንም ጥላ ለመያዝ ወይንም ለዘበኝነት ብቻ። ድንበር ሰበር ለሆነ ለሚመጥን የሥልጣን ክፍፍል ማነቆ - እገዳ - ክልከላ … ሰባራ ጉድ፤ …. ጨምዳዳ ….. ዕጣ። የተሸበሸበ … ራዕይ። ሽራፊ …. ህልም። ያመለ … ። የሻገተ …። ያልተጠረገው መንገድ አዲስ ቅናዊ የቅኔ መኃንዲሶች ያስፈልጉታል … ይመስለኛል። እስኪ ከሰኘኝ እመለሳለሁ በዚህው ዙሪያ … ካልሆነም በሌላ … ለሰጣችሁኝ ዘንካታ ትዕግስት ሞንሟና ምስጋና እንሆ!

እናሳርገው። …..
የምቀኝነት በሽታ ያለባቸው ድውያን በዬአጋጣሚው ያፈኑት ነገር መተንፈሻ ከሌለው አጉል ቦታ ይፈስና ብዙ መስመሮችን ይበርዛል። „ልብ ያለው ሸብ“ ብለናል … ከብሂሉ ጋር እርገት ይሁን።  እኔ ምን እንደሚናፍቀኝ ታውቃላችሁ ዓይነታ የወጣለት መሪ … ደፈር ብሎ ስለ ሴቶች …. ጥበቅና አጋፋሪ የሚሆን ሊጋባ። የነፃነት እልፍኝ አስከልካይ ሀቀኛ። ሴቶች ብዙ አላቸዋ፡፡ ያጡት ያላቸውን የሚያቀኑበት ገብያ ብቻ ነው ….. ግጥም ታውቃላችሁ … እንደ ግጥም የልብን ድርስ የሚያደርጉ ምርጥ ፉጡራን ናቸው አብዛኞቹ ሴቶች። እርዳታቸው - ፈጣን፤ ምክራቸው የልብ አድርስ፤ ጽናታቸው ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ፤ ፍቅራቸው የትውልድ ዋዜማ፤ ሥልታቸው ሥልጡን፤ ብልህነታቸው ተጨባጭን የዋጠ። ጉዟቸው ደፋር። እስኪ ካሰኘኝ እመለሳለሁ በዚህው ዙሪያ … ካልሆነም እንዳላሰለቻችሁ በሌላ … ለሰጣችሁኝ ዘንካታ ትዕግስት ሞንሟና ምስጋና እንሆ!

 
መፍቻ

  • አጃ የልብ መደረስ፤ ከጠበቁት በላይ መርካት።
  • ቅንጧን ቅንድቧን …
  • ብጡል የተለዬ … የተመረጥ …
  • መገምደል … ፍትህን የጣሰ ፍርድ።

 ሴቶች የነፃነት ትግሉ ዓርማ ናቸው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።