የለውጥ ሃሳብ።

                   የለውጥ ሃሳብ ሂደትን 
                ማዕቀብ በመጣል ማስቆም
                  ወይንም የታቆረ ማድረግ 
                   አይቻልም። በፍጹም። 
                      ተፈጥሯዊ ነውና!
ከሥርጉተ©ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
 13.03.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ)

                  „በታካች ሰው እርሻ፤ አዕምሮ በጎደለው ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ። እነሆም፣ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፤
                    ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል። የድጋዩም ቅጥር ፈርሷል።“ (መጸሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፬ ቁጥር ፴፩)
  • ·         ር።

ለእኔ በማሰብ ልቅና የአስተሳሰብ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ። የነቃው የህሊና ክፍል አዲስ ሃሳብ ሲያፈልቅ ሃሳቡን የሚቀበል ህሊና፤ አዕምሮ ሊኖረው ይገባል። ይህ አዕምሮ ያፈለቀውን አዲስ ሃሳብ የሚመጥን የሰብዕና አቅም የሚኖረው ከአቅሙ ከራሱ በመመንጨቱ ነው። አዲሱ ልቅና ያለው አስተሳሰብ/ ሃሳብ የትውስት ወይንም የብድር አይደለም። ስለምን? አዲሱ አስተሳሰብ ልቅና ካለው ከራሱ ህሊና፤ የአዕምሮ የአቅም ፏፏቴ የመነጨ ስለሆነ የመሸከም ብቻ ሳይሆን በቅጡ አደራጅቶ የመምራት፤ የማስተዳደር አቅሙ ተመጣጠኝ ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊነቱ በራሱ የአዕምሮ የውሃ ልክን የሚያስጠብቅ ተጠባባቂ የሃሳብ ማህበር ዘብም ይኖረዋል። ኦህዲድን እኔ የማዬው ከዚህ አንጻር ነው።
  • ·         ጥነት።

የወገቡ ስፋት 35 ሴንቲሜትር የሆነ ልብስ የ52 ሴንቲሜትር ስፋት ያለው ልብስ ቢጠለቅለት መዋኛ ገንዳ ነው የሚሆነው። ወይንም 35 ሴንቲሜትር የወገብ ስፋት ላለው 10 ሴንቲሜትር ስፋት ያለው ልበስ ቢባል ይሄም በጅ የሚል አይሆንም። አሁን የወያኔ ሃርነት እና የምርኩዞቹ የእነ አቶ በረከት/ አዲሱ ችግርም ይሄው ነው። ቢደረደሩ፤ ቢከመሩ፤ እንደ ተራራ ቢቆለሉ፤ አንደ አነባበሮ ቢነበባሩ ለጥ ብሎ በተኛው የዛገ ሃሳብ ውስጥ ከመዝገጥ በስተቀር ዘለግ ብለው የመታዬት አቅምም ወርድም የላቸውም። አዲሱን ሃሳብ የአዕምሮ ደረጃ የሚመጥን አዕምሮ የላቸውም። አንድ ሰው ቁመቱ የሚያድገው አስከ ተፈቀደለት ድረስ ነው። ያማ ባይሆን ሰማይ ጠቀስ ይሆን ነበር የሁላችንም ቁመት። አሁን የእነሱ ማኦይዝም በጎሳዊ ቀመር ፍልስፍና ዕድገቱ ተቀጭቷል። የነርብ ሲስተሙ ከዚህ በላይ መሄድ አይችልም። አቅም የለውም። ዘመኑን መሸከም አይችልም። ወይ ይፈነዳል ወይ እንደ ለመደበት ለሽ ብሎ ይተኛል። ይሄ ስለተባለ ሳይሆን የዕድገት ሂደት ነባራዊ ሁኔታዎችና ተፈጥሯዊነት የሚያስገደዱት ረቂቅ ህግ አለ። ይህን የእድገት ህግ በሰው እጅ አንቦልቡሎ ወይንም ጠፍጥፎ ማስኬድ አይቻልም። አዲስ ሃሳብ በራሱ አዕምሮ እድገት የሚፈጠር ብቻ ነው።
እነ ማበህረ ደራጎን የወያኔ አንቀልባ አቶ በረከት ስምዖን በታቆረ ጥብቆ ህሊና ሊመጥነው በማይችል ቅዠት ውስጥ ናቸው። ቅዠታቸውን ለማስቀጠል ያላቸው የአዕምሮ ብቃት አቅሙ አልተመጣጠነም። ያልገባቸው ጉዳይ ይሄ ነው። ስለዚህ ባነሰ ግምት ስድስት ዓይነት ጦርነቶች ተከፍቶባቸዋል። አንደኛው፣ … የሻገተው አስተሳብን ለመሳቀጠል ያለ ከራሳቸውም ጋር ራሳቸው ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። ሁለተኛው፣ …  በራሳቸው ማህበርተኛ ወስጥ የተፈጠረ አዲስ ሃሳብ አቅም አስምጧቸዋል። ሦስተኛው፣…  በኦሮሞ እና በአማራ ማህረሰብ ያለው ጉልበታም ማዕብል ያለማቋረጥ  በሥነ - ልቦና ብቃት አኃቲነት ልዕልና በልጦ እዬናጣቸው ነው። አራተኛው፣ … በራሱ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ አዲሱ አመራር ጨፍልቆ የያዘው ክብርና ልዕልና የተፈጠረ ስውር፤ የተከደነ የጦርነት ቀጠና አለ። አምስተኛው፣ … ከሁሉም ያልሆነ ግን የመንፈስ አቅሙ ሙሉዑ የሆነ፤ ልኩ ያልታወቀ አቅም ልዩ ኃይል አለ፤ ይሄ „ጸጥተኛ ድምጽ silent majority“ የሚባለው። ስድስተኛው፣ … የድሮ ዓለምዓቀፍ ወዳጆቻቸው ሂደቱን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም በቅርበት እዬተከታተሉት ነው።
ለዚህ ሁሉ ፈተና የ100 ዓመት ህልማቸውን የሚሸከም የአስተሳብ/ የሃሳብ፤ የሰብዕና፤ የአዕምሮ ደረጃው ነገቲብ ላይ ነው። የዛገ ብርት ዝግን እዬጨመረ በሄደ ቁጥር ቀለሙ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት የመስጠት አቅሙም ያኑ ያህል እዬተፈረፈረ ይሄዳል። በሂደቱ ራሱን መሸከም እያቃተው ለበለጠ ክስመቱ ሆነ ዕድሜ ማጠሩ እራሱን በራሱ ያጣፋል። በዚህ ማህል በተነደለ ቁጥር መወተፊያ የሆነው የለበጣ ግርዶሽ ገመናው የአደባባይ ሲሳይ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል። የስበሰባው የሚጀመርበት ቀን ሆነ የሂደቱ መለጠጥም ከዚህ የመነጨ የውልቅልቅ ምርተት ነው።
በዛገ እና በማረተ ሃሳብ ውስጥ አዲስ የሚፈጠር በውስጥ የሚበቅል ነገር አይኖርም። ባትሪው አልቋል ወይንም ተቃጥሏል፤ እድገቱ ቁሟል። ከዜሮ በታች ነው። ይህ ማለት ቀዝቅዟል - ዝቅ ባለው ዕሳቤ፤ ከፍ ሲል ደግሞ ግግር በረዶ ሆኗል። እንዲህ እንዲሆን ያደረገው የታሰረበት ንድፈ ሃሳባዊ የአደረጃት መርህ የቀደመ ዕድገትን እየፈራ ራሱን የካሮት ሥር አድርጎታል።
ዘመን ጥሎት ያለፈው ጎሳዊ የሶሻሊዝም ቅሪተ አካል ሲፈርስ ከበላይ ነው። ፍልስፍናው አንጡራ ጠላቱ የህሊና የአዕምሮ እድገት ነው። ህሊና አዕምሮ ሲያድግ የሚበልጥ ሃሳብ ስለሚያፈልቅ ሞቱ ስለመሆኑ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ስለሆነም ከሞቱ በፊት አሟሟቱን የሚያበጅ ሳይሆን አሟሟቱን የሚያፋጥን ከይሲ ተግባራትን ከመፈጸም አይቆጠብም - የዛገው። የአስተሳሰብ ድህንት አለበታ። ስለሆነም የአስተሳስብ ድህነቱን ለመሸፈን ጭካኔው ሆነ አፈፃጸሙ የሚራው በደመንፈስ አዕምሮ ነው። ስለምን? መረጋጋት የሚያስችል እርሾ፣ ብጣቂ የሃሳብ አቅም ፍርፋሪ ስሌለለው። ፍርፋሪ አለ ከተባለ፤ ፍቅረ ንዋይ፤ ዝሙት፤ ጠበንጃ፤ የኢ-ሰብዕዊነት እርምጃ። አስከዛሬም ባለቀ ባትሪ እዬተገፋ ነው የተኖረው - ሪሞርኬ።
  • ·         መጠበቅ። 

ዝገት ካለበት ከታቆረው ውስጥ ስለሆነ፤ እራሱን እያጠፋ ስለመሆኑ አይታዬውም። እርምጃው ውስጡን እያደሰ ወደ ፊት  በአሸናፊነት የሚያስገሰገስው ይመስለዋል። ስለዚህ በህልም ሰረገላ ራሱን ኮፍሶ እያሰመጠው ነው የሚሄደው። በቆየበት ዘመን ሁሉ እዛው ላይ ሲዳክር ስለኖረ የሃሳብ ልቅና የፈለቀበትን አካባቢ ሊይ አያስችለውም። ግርዶሽ አለበት። ግርዶሹ ራሱን እያታለለ መኖር እንደሚችል ግብረ ምላሽ ይሰጣዋል። የተነፋ ህልም።
የፕሮፖጋንዳ መሳሪያዎቹ፤ የጸጥታ ማስከባሪ ስልቶቹ፤ የደህንነት መዋቅሮቹ እነሱን እንዳሻቸው እንዲፏልሉ የሚያስችለው የኤኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩለት መዋቅራዊ ሰንሰለቱ ቀን ሲያጡ እንደሚክዱት ወይንም ከአገልግሎት ውጪ እንደሚያደርጉት አያሰተውለውም። አያድኑትም! አንድ አደጋ ያለበት አካባቢ ለማዬትም የሃሳብ አቅም ወይንም ድርጁ አዕምሮ ያስፈልገዋል። ሽሁራር በበላው ቸረቸራ አዲስ ጥንስስ አይጠነሰሰም። 
አሁን ግብ ግቡ „ዘመን“ „ታሪክ“ „ሁኔታን“ ያደመጠ አዲስ ሃሳብ ጎልቶ፤ ደርጅቶ፤ ጎልብቶ ወጥቷል። የዛገው ሃሳብ ይህን አዲስ ሃሳብ ይዞ የወጣውን መንፈስ ጥሶ ለመውጣት አያስችለውም። ስለምን? መቀበልም እኮ አዕምሮ ሲኖር ነው። የተሟላ ሰብዕና ሲኖር ነው። አንጎል ብቻውን መኖሩ የአስተሳሰብ ድህነትን ሊከላ አይችልም። በፍጹም! አንጎልማ እንሰሳትም እኮ አላቸው አይደል?
አዲሱ ሃሳብ አዳጊ ተራማጅ እና ስልጡን ነው። ይህ የሚሆነው በራሱ ህሊና የበቀለ ስለሆነ የራሱ ስልት እና ታክቲክ እየፈጠረ፤ ወቅቱን እያደመጠ በሄደ ቁጥር የፈለቀው አዲስ ሃሳብ እዬዳበረ፤ እያደገ፤ እዬጠነከረ የመሄድ ተስፋው የፋፋ ይሆናል። ይህ የፋፋ አዲስ ዕሳቤ ህሊናዊ ሂደት በራሱ የሚሰጠው፤ የሚፈጥረው ሌላ የሙቀት ስበት gravity አለው። ለዚህ አዲስ ሃሳብ ከማረተው አስተሳሰብ አፈንግጠው የሚወጡ አዳዲስ ቡቃያዎች / ችግኞች በራሳቸው ጊዜ ይኖራሉ። እነዚህ ድርብ ግፊት እና ግጭት ሲፈጥሩ የማረተው ሃሳብ ቀስ እያለ አቅሙ እዬተሸበሸበ፤ ግርማው እዬሟሟ፤ ተስፋው እዬሸሸው ይሄዳል። ትግሉ የአልሞትም ባይ ተጋዳይነትን ስለሚጨምር የሚያስከፍለው መስዋዕትነት የከፋ ይሆናል። ግን አዲሱ ሃሳብ በአዲስ አቅማዊ ስልትና ስትራቴጂ በጥበብ ስለሚመራ አሸናፊ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት „ጸጥተኛ ድምጽ silent majority“ አባልተኞችም የቀና ቀን ጠባቂዎች ናቸው። ስብጥራቸው ሁሉንም  የአቅም አይነት ያሟላ ነው። እነኝህ ከሁሉም ጋር ያልነበሩ ድርጁ መንፈሶች የበቃ የአቅም መቅኖ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። የዛገው ሃሳብ የእኔ ሳይላቸው ረስቷቸው ወይንም ባሊህ ሳይላቸው የቆዩ በመሆኑ ባለቤት መሆን የሚችል አዲስ ሃሳብን ለመቀበል ንጹህ ሰሌዳ ናቸው ማለት ይቻላል። የዚህ መንፈስ ቅን እና ንጽህና ያለው ስለሚሆን ወደ አዲሱ ሃሳብ የመጠቃለል ዝንባሌያቸው ሰፊ ነው። እኔ እንደማስበው እነዚህ መንፈሶች ያልተነካ የአዕምሮ አዱኛ ያላቸው፤ በስብዕናቸውም አንቱ የሆኑ፤ አደብ የገዙ፤ ጭምቶች፤የማይቸኩሉ፤ በቁጥርም ብዙሃን በመሆናቸው እጅግ ጠቃሚ ሃይሎች ናቸው።
በተለይ እነሱ መስጥረው የያዙትን ምኞት ጋር አዲሱ ሃሳብ ካፈለቀው „ከአዲሱ ሃሳብ“ ማህጸን ጋር ተመሳሳይ ወይንም ተቀራራቢ ከሆነ ለመጠቃለል ጊዜ አይፈጅባቸውም። ምክንያቱም ጊዜና ወቅት ጠበቂዎች በመሆናቸው የተስፋ ዘበኞች ለመሆን ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በቀጥታ አቅማቸውን ለአዲሱ አስተሳሰብ ይሰጣሉ። ህሊናቸውን፤ ውስጣቸውን ብቻ ሳይሆን ሰብዕናቸውን ፈቅደው ይሸልማሉ። ከዚህ ላይ አዲሱ ሃሳብ ለእነዚህ ንጹህ መንፈሶች የተለዬ ጥንቃቄ እና አያያዝ ለማድረግ በህሊናው ቃል ማሰር አለበት። ድምፃቸውን ሲያሰሙ የሚያደምጥበት ድርብ ጆሮ፤ ሰፊ ልቦና ሊኖረው ይገባል። ስለምን? ዝምታን ሰንቆ የተቀመጠ አዕምሮ የአቅሙን ልክ፤ የባህሬውን ሁኔታ፤ የሚወስደውን የእርምጃ ዓይነት፤ የማስታዋሉን ልኬታ ኮቴ ማወቅ አይቻልም። የተከደነ ሲሳይ ነው። ናድ ብለው ከሄዱ አዳጋው ሰፊ ነው የሚሆነው። ፍቅር ሲያልቅ ትዕግስት ይሰደዳል እኔ የምለውም ለዚህ ነው። …
  • ·         በጥበብ መከራን ስለመሻገር።

በዚህ ሂደት የቀደመው የዛገው ሃሳብ ከራሱም እያመለጡ በሚሄዱት፤ እንደገናም ባሊህ ብሏቸው የማያውቃቸው፤ ባለቤት ያልነበራቸው ህሊናዎች አብዛኛውን ቁጥር የያዙቱ በመሆናቸው ወደ አዲሱ አስተሳስብ ሲጠቃለሉ ከባህር የወጣ አሳ ይሆናል። ግማቱ ከአናቱ ይሆናል። የማረተው ወይንም የዛገው ሃሳብ ማህል ሜዳ ላይ አውላላ ሜዳ ላይ ተንገዋሎ ይቀራል።
በዚህ ወቅት የዛገው መንፈስ ስለሚወራጭ፤ ገርጭራጫም፤ ብስጩም ስለሚሆን የሚጠፉ ነፍሶች ስለሚኖሩ ሽግግሩን በቀላል መስዋዕትነት ለማድረግ „አደብ“ „ጭምትነት“ እንደ ፍልስፍና ሊወሰድ ይገባዋል። እያንዳንዱ መሬት ላይ ያለ ግለሰብ ሆነ ድርጅት ለራሱ ራሱ ዘበኛ / ተቆጣጣሪ/ ጠበቂ መሆን ይኖርበታል። ማስተዋልን የህሊና መሪ ማድረግ ይገባል። ብልህነትን የሰብዕና አዕምሮ ማድረግ ያስፈልጋል። እልህን/ ቁጣን ዋጥ አድርጎ መያዝ ያስፈልጋል። ባሩድን የተማመነ አውሬ በተፈለገው ጊዜ፤ የፈለገውን የማድረግ ሃይል አለው፤ በተለይ ሐገር ቤት ያሉት የሚናፍቁኝ ወገኖቼ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በምግብ ብክለት፤ በመኪና አደጋ፤ በቤት ቃጠሎ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በተደራጀ ሁኔታ እርምጃ ሊኖር ይችላል። ስለሆነም በሁሉም ዘርፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ትግሉ መጨረሻው ከማይታወቅ የክፋት ጉድጓድ ጋር ነውና … ከሲኦል ጋር … 
በዚህ ሂደት መጻፍ የሚፈልግ፤ ቃለ-ምልልስ ማድርግ የሚሻ ካለ የዓውደ ዓመት ዶሮ እንዳይሆን በትዕግስት የሚያልፋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል። አሁን ሰሞኑን አባ ትርጉም ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ ጎንደርም ጎጃም ነበር። ከቤተሰባዊ አቀባበል የዘለለ የሆነ ነገር የለም። እጅግ ያደገ፤ የበሰለ ብልህነት ነው ያዬሁት። ይህም ሆኖ የዛገው መንፈስ ጠብ አጫሪ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል። በገፍ የመጨፍጨፍ፤ የማሰር፤ የማሳደድ፤ ቤት እዬገባ የመደብደብ፤ በለፈም የመድፈር  ወዘተ … አቅም የለውም ብሎ መዘናጋት በፍጹም አይገባም። አቅም የአዕምሮ የሥነ - ልቦና ነው የሌለው፤ የጭካኔ እና የመሳሪያ መዋቅሩ የተለመደው በመዳፉ ነው።
ገፍቶ ከመጣ የማይቀረው ነገር ሊቀር እንዳማይችል የተፈጥሮ ግዴታ ቢሆንም፤ ግን በስልት፤ በጥበብ፤ በልበ ሰፊነት መያዙ መስዋዕትነቱን ይቀንሰዋል። ምክንያቱም አሁን የግጭቱ ዓውድ አዲስ ሃሳብ ይዞ የተነሳ መንፈስ አለ ኦህዲድ እንደ ድርጅት፤ ብአዴን በገዱ መንፈስ ሥር ያሉ ነፍሶች። ስለዚህም የዛገው ሃሳብ የጦርነቱ መስክ መሰረት ከሆነው ሁለቱ ማህበረሰቦችን በተጠናከረ ሁኔታ ጥቃት በመሰንዘር የአቅጣጫ ለውጥ በጫና ማምጣት ግቡ ይሆናል። ሂደቱ እጅግ የታመመ በመሆኑ ጥንቃቄ የሁሉም ዜጋ ሊሆን ይገባል። የልተገባ እልህ አስፈላጊ አይደለም። መንግሥት በሌለበት ሐገር የሚኖረው የኢትዮጵያ  ህዝብ ጥጉ ፈጣሪው በመሆኑ ሁሉም እንደ ዕምነቱ በጸሎት ከፈጣሪው ጋር መተሳስር ያስፍልገዋል። የተደሞ ጊዜ ነው። የወል የመከራ ጊዜ ነው። የዕንባ ወቅት ነው።
የዛገው የወያኔ ሃርነት ትግራይና የማረቱ ምርኩዞቹ የዚህን የአዲስ ዘመን መንፈስ ሰላሙን በማወክ ትንፋሹን ማባከን ቀዳሚው መስኩ ነው። የማያዋቀው ነገር ግን የአዲስ ሃሳብን ሂደት ማስቆም ቀርቶ መገደብ አለመቻሉ ነው። አንድ ጊዜ ተፈጥሯል። እንደ ጉርሻ ዋጥ ተደርጎ ጸጥ የሚባልበት አይሆንም። አዲስ ሃሳብ ምጡ እስኪ ወለድ ድረስ ነው። ከተወለደ በኋዋላ ግን በራሱ ጊዜ እድገቱን መቀጠሉ የተፈጥሮ ህጉ ነው። አንድ በህክምና ዶር. የተመረቀ ሰው በዕወቀቱ ላይ የተለዬ ስልጠና እዬወሰደ ያዳብረዋል እንጂ እንደገና ወርዶ 7ኛ ክፍል ላይ ስለተፈጥሮ ሳይንስ ልማር አይልም። ምክንያቱም አቅም ፈጣሪው አዕምሮ ወደላይ ከመዝለቅ በስተቀር ወደ ታጅ መውረድን ስለማይፈቅድለት።
አሁን ያለውን ቡቃያ የለማ አብይ የገዱ መንፈስን በዛገ የምርኩዝ ጋጋታ፤ በፈለገው ዓይነት መጠራቅቅ መቋቋም አይችልም የትግራይ ሥርዕዎ መንግሥት። ይህ የለውጥ መንፈስ ከብሄራዊ አልፎ፤ አህጉራዊና ዓለምዓቀፋዊ ጫናም ፈጥሯል። የፈጠረው ጫና በፍጹም ሁኔታ ወያኔ በሚያስበው መልክ በግርድፍ የሚሾከሾክ የገብስ ቆሎ አይደለም። በፍጹም።
  • ·         መታዬት።

የዛገው ባለሃሳብ አዲሱ የለውጥ መንፈስን መቀበል ብቻ ሳይሆን ከአዲሱ መንፈስ ጋር ለመቀጠል እንኳን በግትርነት የሚሆን አይሆንም። የሚመጥን የአዕምሮ ብቃት፤ የሰብዕና ንጽህና፤ የሥነ - ምግባር ሞራል፤ የሥርዓት መዋቅራዊ ደርጁነት የለውም። ያስፈራውም ይሄው ነው። አሁን ኢትጵያ ከዬትኛውም ፍልስፍና ያፈነገጠ እና የወጣ ተፈጥሯዊነትን አቤት! ወዴት! ያለ አዲስ የሃሳብ ልቅና ላይ ትገኛለች። ስለሆነም ከአራዊት መንጋ፤ ከዝሙት ከተማ፤ ከዘረፋ ጅረት፤ ከደም ማፈሰስ ሱስ፤ ከመስፋፋት ትዕቢት፤ የምትላቀቅበት አዲስ የሃሳብ ዓዕማደ ተስፋ ላይ ናት። ይህን የሃሳብ ቡቃያ የመሸከም አቅም የለውም እንኩቶው የዛገው  የአቶ በረከት/ አዲሱ መንፈስ።
ይህ ለማዊ የጥገና መንፈስም አይደለም። ያለው የሰዋዊነት መንፈስ ነው። ሰው መሆን! ለሰውነት ጠበቃ፤ ጋሻ፤ መከታ መሆን! ሰውን እንደ እንሰሳ የሚያታይበት፤ ሰውን እንደ ግዑዝ ከረጢት ነገር የሚታሰርበት - የሚፈታበት፤ ሰውን በጅራፍ ተዘቅዝቆ ታስሮ የሚቀጣበት፤ በራስ ወገን የመርዝ መፈተኛ የሚሆንበት፤ ሰው እንደ በግ የሚሸለትበት ዘመን በማክተም እና ለማስቀጠል በሚባዝኑ የመንፈስ ደሃወች መሃከል ነው ጦርነቱ።
ቀደም ባለው ጊዜ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ይውደቅ እንጂ ከዛ በኋዋላ ችግር የለም የሚሉ አመክንዮዎች በርካታ ስለነበሩ፤ መንፈስን ጥግ ለመስጠት አልተቻለም ነበር። አስፊሪ የሆኑ የጨለማ አምክንዮች ነበሩ። አሁን ነገስ ምን? ለሚለው አስከ ታች ድረስ አቅም እያበቀለ፤ አቅምን በብቃት ኮትኩቶ እያበቃ የመጣ ድርጁ ኢትዮጵያዊ መንፈስ አለ። ይህ የአቅም ተከታታይነት በተጠባባቂ አቅም በሙሉ ስብዕና የተገነባ ነው። አንድ ሰው ቢወድቅ ሌላ ተተኪ አለው። አንድ ሰው አቅም አንዲኖረው እርስ በርሳቸው ረቂቅ በሆኑ፤ ዘመኑ በሚጠይቃቸው መስመራዊ፤ መንፈሳዊ፤ ሞራላዊ፤ ሰዋዊ፤ እኛዊ መሠረት ያዬዘ አቅም አለ።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ፕሮቴስት እና የአማራ የህልውና ተጋድሎ ዕውቅን በመስጠት ረገድ የነበረው ዝበት አሁን ሚዛኑን ጠብቋል። የዚህ ሚዛን መጠበቁ በራሱ የሚፈጠረው የተስፋ አቅም አለው። ለውጡ በራሱ ተጋድሎውን የመሸከም አቅም አምጦ ሊወልድ ግድ ይለው ነበር። በስተቀር በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆነው። ይህ የተመጣጠነ የመንፈስ መግባባት በዛገው ብረትም የፈጠረው ድንጋጤ አለ። የአማራ የህልውና ተጋድሎ መስዋዕትነቱ ዕውቅና እንዳያገኝ ከወያኔ ባለነሰ ውጪ ሐገርም ሰፊ ፈተና ነበር። ዛሬ የአማራ የህልውና ተጋድሎ እጅግ በተሻለ ሁኔታ ግራ ቀኝ እስሩን ጥሶ ወጥቶ እኩል እውቅናውን ማስጠበቅ ችሏል። በአደባባይ ከሚሰሙትም፤ ከሚደመጡትም በላይ ያሉ ረቂቅ የመንፈስ ሃብቶች አሉት ተጋድሎው። ስለምን? አዲሱ ሃሳብ ስለነገ ያለው ዕይታ ያልደፈረሰ፤ ያልተስረከረከ ግልጽና ቁልጭ ያለ በመሆኑ ምክንያት አቅሙን አቅም ለማድረግ በቅርበት ውህድነትን ዘመን በራሱ ጊዜ፤ ፈጣሪ አምላክም በኪነ - ጥበቡ ስለባረከው።
ከዚህ አፈንግጦ የዛገው ብረት በማረተ ሃሳብ ጊዜውን በጅ በለኝ ቢለው ብዙም የሚያወላደው አይሆንም። ጅው ወደ አለው ገደል ራሱን የሚለቀው ራሱ ነው። ቅራኔው እዬተካረረ፤ እዬተወጠረ በሄደ ቁጥር በራሱ ነፍሶች ላይ የዘለዓለም የበቀል ስንቅ ተክሎ ያሸልባል። ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ሁሉ ነገም በራሱ ቀን ስለሚመጣ ዛሬ ሊሆን አይችልም።
  • ·         ፃ የወጣ ኢትዮጵያዊ የአዕምሮ ነፃነት!

በአቶ ለማ መግርሳ እና በዶር አብይ አህመድ ያለው ሃሳብ ነፃ የወጣ ኢትዮጵያዊ ነፃ የአዕምሮ ነፃነት ነው። ነፃ የወጣ ስል የአዕምሮ ነፃነቱ የትውስት ሰብዕናን፤ የትውስት ፍልስፍናን፤ የትውስት አቅምን፤ በትውስት አዕምሮ የተፈጠረ ንድፈ ሃሳባዊ ቀመርን በፍጹም ሁኔታ የተጸዬፈ ነው። በአካልም በመንፈሰም የዬትኛውንም ሐገር ፍልስፍና ወይንም የኤኮኖሚ አቅም፤ ወይንም የዲፕሎማሲ ጫና አልሞ የተነሳ አይደለም። ይህ ራሱን ችሎ በራሱ ጊዜ ነፃነቱን አውጆ የተነሳው ሃሳብ በቀጥታ የ21ኛው ምዕተ ዓመት ወዳጅ የሆነውን ሰዋዊነት፤ ተፈጥሯዊነት ኢትዮጵያዊ ቀለም ሰጥቶ የተነሳ በመሆኑ ስለሰው ግድ የሚላቸው፤ ስለተፈጥሮ ግድ የሚላቸው ባለ አዕምሮችን ቀልብ ሲስብ ፕሮፓጋንዲስት ወይንም ቀስቃሽ ወይንም በፕሬስ ውደሳ አይደለም።
ዛሬ ሁሉንም በጋራ የሚያገናኘው አንድ ተፈጥሯዊ መርህ አለ ሰብዕዊነት። ከኦህዲድ ጋር ከበዙ ቅን መንፈሶች ጋር የተሰራው ሃዲድም በዚህ መስመር ነው። አንደኛ … በራስ ወገን የተሰብ መሆኑ፤ ሁለተኛ … አቅሙ ስፋቱና መጠኑ ባለጥሪት መሆኑ፤ ሦስተኛ … ከማንም እና ከምንም ከዬትኛውም ሐገር የውለታ ጥገኝነት የሌለበት መሆኑ። አራተኛ … ሁሉንም በአኩልነት በእቅፉ ለማድረግ ከልቡ የፈቀደ መሆኑ። አምስተኛ … ተረስተው፤ ተዘንግተው የኖርትን ሁሉ ፍቅርን በገፍ መስጠቱ። ስድስተኛ … ነገስ ለሚለው አደራውን ለመወጣት ያለው የህሊናው መሳናዷዊ አቅሙ ሙሉዑነት፤ ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያን ከነክብሯ፤ ከነግርማ ሞገሷ የእኔ ብሎ ከሚስጢሯ መነሳቱ ለቅኖች ቅደመ ሁኔታ ሳያሰኛቸው በመንፈሱ ተስፋን እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል።  
  • ·         ውጫ።

ጊዜ እና ቦታ፤ ሁኔታ እና ዕድል የሚነሱትም የሚያሳጡትም አለ።  … ያ እንዳለፈው ሁሉ ይህም ያልፋል። ሲሞላም ይፈሳል ሲከርም ይበጣሳል። ሂደትን ጠብቀኝ ማለት አይቻልም፤ አብሮ መጓዝ ብቻ ነው ምርጫው፤ በስተቀር መንጠባጠቡ በመፈጥፈጥ ይሆናል። ሰማይን ንጋት እንዳይሰጥ የሚያደርግ ወይንም ጸሐይ ብርሃን እንዳትሰጥ የሚያደርግ የተፈጥሮ ህግ የለም። ህግ ጣሹ በህግ ጥሰቱ ውስጥ ራሱን ጥሶ ግብዕቱን ይፈጽማል። በዚህ አሰልቺ በሆነ ደንዛዛ አቅም - ጊዜ  - ማቃጠሉ ቅራኔውን ቢያባብሰው እንጂ ሊፈታው አይችልም። ጨው ለራስህ ብትል … ይብቃኝ እነ እንቅልፍ ከተለመደው የበረከት አንቀልባ ጋር አንጎላቹ … ፍዝ ብውዝ። ትንሽ ስለነገ ስላልተፈጠሩት የትግራይ ህፃነት የማታስቡ የግዴለሽ ግንዶች።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
የኔዎቹ ለዘንካታ አድማጭነታቸሁ ፍቅርን፤ አክብሮትን ልሸልም።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።