ይህቺ ናት ኢትዮጵያ - ከፈለግናት።

                    ይህቺ ናት ኢትዮጵያ - ከፈለግናት። 
                      ትግል ማለት የማያሰራውን
                     አመክንዮ ማሰራት እንዲችል
                     መታገል ማለት ነው - ለእኔ።

„በውኑ ደንገል ረግረግ መሬት በሌለበት መሬት ይበቅላልን?“

(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፲፩)
 ከሥርጉተ © ሥላሴ 19.04.2018 (Sergute©Sselassie)
(ከጭምቷ  - ሲዊዘርላንድ)


  • ·         መነሻ።

ግርም ሲለኝ ነው ይህን ጹሑፍ የጻፍኩት። በቃ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕለታዊ ተግባር በኢህአዴግ ዕለታዊ ክንውኖች ቃለ አቀባይ ሆነው ነው ያረፉት። ሚደያዎችም አጀንዳ አጡ መሰል ጸጥ ረጭ ስል አልወድም አይነት በዬአይነቱ ተንታኝ አስናድተው ያው በተመሳሳዩ አቋም „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ሲሰለቅ አድማጭ ምን ይሰለቸን አይሉም። አደከሙን። ፖለቲከኛ ያልነበረው ሁሉ ዛሬ በሚገርም ሁኔታ እዬታዘብነም ነው። ግን ግን እንዴት አላችሁልኝ ውዶቼ - የኔዎቹ እማ እና አባ ቅንዬ፤
አንድ ነገር ተዚህ ላይ በቅድሚያ የማከብራችሁ ይህን ቢሮ ከራስ እግሩ እስከ ጥፈሩ ትክ ብላችሁ እዩት። ሥሩን ሁሉ ፍቅርን በገፍ ሰጥታችሁ ፈትሹት፤ ተዚያማ የኔዎቹ ወደ ሥርጉተ ጠብታ መሄድ ነው። ማዬት ጥሩ ነው። ማዬት እኮ ነው ዓለምን የፈጠራት። ማዬት ነው ዓለምን ዘመናይ ያደረጋት። እኛስ ፈጣሪ ውረድና ቤት ጥረግ እያልነው አይደለምን? ቅልጣኑ ያቅለሸልሻል። ቃር!
  • ·         ምም።

ምስኪንዬ! አንድ የሚያስማማን ብሄራዊ ቀን የሌለን። አንድ የሚያስማማን የድል ቀን የሌለን። ለቀን ያደረሰ፤ በጥቁሮች ዘንድ የክብር ዘውድ የደፋልን፤ ውስጣችን እንደ ውስጣችን የፈወሰን ባለውለታ ሰንደቅ እያለን ግን ወጥ ብሄራዊ ሰንድቅዓላማችን ማለት አለመቻሉ፤ በዓዋጅ መታሰሩ፤ በተጨማሪ መመሪያ መጣበቁ እና መንገላታቱ የውስጥ ደስታ ፈጣሪ ፈውሳችን ነበር - ለተወሰነው። ግን ብሄራዊ ነፃነት ፈላጊዎች? ምስኪን።

ዓይነ - ገብ፤ ተግባር - ገብ ታሪክ አለን፤ ግን አንድ የሚያስማማ ታሪክ የለንም። የተባ ደማቅ ትውፊት አለን፤ ግን አንድ ወጥ የሆነ የሁላችን የምንለው፤ አክብሮታችንንም በፍቅር የምንለግሰው በወል የምንስቅበት የሚያስማማ ትውፊት የለንም። ዝቀሽ የሆነ ትሩፋት አለን፤ ግን ለዝቀሽነቱ የምንሰጠው ዕውቅና ላይ ስምምነት የለንም። ሐገሮች የዘለቀ ቋሚ፤ ከውርስ ወደ ውርስ የሚሸጋገር ብሄራዊ መዝሙር አላቸው፤ እኛ ግን አንድ የሚያስማማ ብሄራዊ መዝሙር የለንም። ሥርዓቱ ሲፈርስ አብሮ ብሄራዊ መዝሙሩም በጠላትንት ተፈርጆ ይፍርሳል። ኢትዮጵያ የቀደመ የህግ ጥበባት ውበት የሰረጣት ሐገር ናት፤ ግን በዋናው የህግ አምክንዮ ጭንቅላት ላይ ስምምነት እንዲኖር ሆኖ የተደራጀ ለሁሉም ፍቅርና ደስታ የሚሰጥ ህገ መንግሥት የለንም። ይልቁንም አንድነታችን የሚፈታተነውን በእቅፍ እንደ አንቁላል ተይዟል - በክብካቤ።

ጀግኖቻችን እኛን ሰጥተውናልን፤ ዛሬን ሰጥተውናል፤ ሐገር ሰጥተውናል ግን አንድ የሚያስማማ ብሄራዊ ጀግና የለንም- በትውስት ጀግኖች ለመኖር ስለመንፈቅድ የኛዎቹን ቃለ ምህዳን ሳይሆን የትውስቱን የእኛ ብለን የምንኮራ፤ በዬንግግራችን ሥነ - ውበት በውጮች አምልኮ የምንማረክ፤ በራሳችን ላይ ሰንፈን አባት/ እናቶቻችን በደም ግብር የሰጡን ነፃነት ፈቃደን ቀንጣጥብን እራሳችን ለውራጅ የሰጠን የመንፈስ ምርኮኞች …  የሌሎችን ለአብንት መጠቀሙ ባይከፋም፤ ግን እያለን ሙሉውን ተዋሽ መሆን ግን ያስገምታል። ለዚህ „ስኬት“ መጸሐፍ ለአብነት መውሰድ ይቻላል።

ለዚህች ቅጽበት ያደረሱን የውጭ ወራሪን መክተው፤ ህዝባቸውን በፍጹም ልቅና መርተው እና አደራጅተው፤ በዬግንባሩ ኳትነው ዛሬን የሰጡን ብሄራዊ መሪዎቻችን ንቀን፤ የሰው ሐገር መሬዎችን እንደ አብነት መውሰድ ደግ ነው፤ ግን ለኛ መንፈስ አንድ የሚያስማማ ከቀደምቶች የራሳችን ብሄራዊ መሪ የሌለን፤ ከአሁኖቹም ደፋ ቀና የሚሉ እያሉን እንሱንም በስምምነት፤ በወጥነት፤ በቋሚነት የእኛ ለማለት የማንደፍር። የእኔ፤ ወይንም የሁላችንም የሚባልለት ትውልድን ሊያበረክት የቻለ የቅንነት አዋራ የሌለን፤ እንዲኖረንም የማንፈቅድ፤ አንድ የሚያስማማ ማጣሪያ፤ ማንዘርዘሪያ ቸርነት የሌለን - ቅን ሆኖ ነገሮች፤ በስክነት ወቅትን ለማዬትም የማንፈቀድ ነን እኛም እንዲህ ነን፤ ሐገረ ኢትዮጵያም እንደሚታዬው ፎቶ ናት …

አሁንም ነፃነት እያሰገበረችን ነው። ህይወትን። ትውልድን። ግን የሁላችን ብለን የምንቀበለው፤ በጋራ እንደ ማዲባ ወይንም እንደ ማማ ዊኒ በሁላችንም ድምጽ የጸደቀለት የሚያስማማ ብሄራዊ የነፃነት አርበኛ የሌለን፤ … አንድ ለሁላችን የሳቅ በረከት የሚሆን የሚያስማማ ብሄራዊ ራዕይ የሌለን፤ … አንድ የሚያስማማ የምንቆረቆርለት ደግነት የሌለን፤ ለመስማማትም የምንፈቅደው ብሄራዊ አጀንዳ የሌለን፤ … ልንድርሰበት ከምንችለው ጋራ የሚያሳይ ብርሃናማ የሆነ የሚያስማማ ብሄራዊ ተስፋ የሌለን፤ … በወሳኝ የነፍስ ጉዳዮች ከማተኮር ይልቅ ለዋንኛ መሠረታዊ ጉዳዮች ተጫኝ - ቀጫጫ - ተነጫናጭ አጀንዳዎችን በማንሳት ግርዶሽ ለመስራት የምንታክት፤ ሁሉንም በፖለቲካ ማንፌስቶ ምልከታ አውሎ ስንብጠለጥል ውለን የምናድር እኛ እንዲህ ነን… ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …

ምስኪኔታ! ባገኘው ጊዜ በወጀብ ቅጣት በጎርፉ ማዕት ሲለጋ የሚኖር እንጂ አንድ ከውስጣችን የበቀለ፤ ከመንፈሳችን የጸደቀ በቋሚነት የከተመ የሚያስማማን ፍላጎት የሌለን፤ አንድ የሚያስማማ ብሄራዊ የምናመሰግነው፤ የእኛዊነት ዜጋ አንድስም እንኳን የሌለን የምንስማማበት። አንድ የሚያስማማ ብሄራዊ የሁላችን መለያችን የምንለው የመለያ ማንነት እያለን እንዳይኖረን የፈቀድን፤  የሀገር ናፍቆት ራህብ ጥብስ አድርጎን ለአፍ መሻሪያ የሚሆን በአንድ ላይ መስሪያ ቢፈቀድልን የጎሪጥ ሳንተያይ አብረን ለመቅረብ የማንችል ወጥ የፍቅር ማዕዶት የሌለን ደግመን እንዳንገናኝ ሁነን የተወጋገዘን፤ ፈጣሪ በማይመረመር ጥበቡ እና ክህሎቱ የሰጠን እኛ የማናውቀው ግን እሱ የመረቀልን በህሊና ብስለት፤ ምጥቀት በፈጣሪ መክሊት ባርኮት የሚገኝ ሰማያዊ ኢትዮጵያዊ ርቁቅ ጸጋ እያለን ግን አንድ የሚያስማማ እሱን በማወደስ የከበረ፤ የተሠራ የኪነ ጥብብ ሥራን አብቅሎት ማዬትን፤ ማድመጥን የምንነፍግ፤ አንድ የሚያስማማ የበጎ ምግባር አርበኛ የሌለን እኛ እንዲህ ነን፤ ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …
  • ·         አሉታ አርበኝነት።

ምስኪናዊነት! ወዘተረፈ ችግር ተሸክምን፤ ችግሩ አጉብጦ አፈር አስግጦ እዬገዛን፤ በ ዕንባ ጎርፍ እያጥለቀለቀን፤ ግን አንድ የሚያስማማ ቋሚ ብሄራዊ ጥያቄ የሌለን፤ ለመልካም ቀን በር ከፋች ዋዜማዬ የምንለው አንድ የሚያስማማ የምስጋና ቀን የሌለን፤ ፈጣሪን ለማመስግን እንኳን በበዛ ሁኔታ ስስታሞች፤ ግን የልዩነት ግድግዳ ስናንጽ፤ የርግማን ናዳ ስንዘክር፤ የወቀሳ ሸጎሬ ስንምስ፤ የዋይታ ጩኽት ስንሞሽር፤ የሟርት ጥልፍ ስንነቅስ፤ በጎ ያልሆኑ ነገሮችን ቅርሻ ስናሞግስ፤ ለልዩነታችን ሙቀት ስንጨምር፤ የመርዶ ነጋሪት ስንጎስም፤ የስህትት ግሬድር ስንሸምት፤ ለተሻለ ነገር የማቅ ብርድ ልብስ ቦንዳ ስንገዛ፤ ጥሩ ነገርን እንዳይበቅል ጥላሸት ስንደረብ የምንገኝ እኛ እንዲህ ነን፤ ኢትዮጵያም እንደሚታዬው ፎቶ
… ጥሩ ያልሆነውን፤ የሚያስከፋውን ከመልካሙ ጋር በአንድ አስኪደን፤ አደባልቀን በዝንቅ የውስጥን ቁስል የሚያመግለውን፤ ለበሽታ የሚዳርገውን የቱ ነው ለማለት እንኳን በማያሳችል ሁኔታ በድብልቅልቅ የስሜት ሁካታ ጎል አግቢነት ለአውሬ ስንቅ በማቀበል የሻንፕዮን ባለሜዳሊያነት የምንታትር እኛ እንዲህ ነን፤ ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ … 
  • ·         ብክነት ስክነት ምኞተኝነት።

ምስኪንዬ! በብክነት ላይ ብክነት፤ በብሶት ላይ ብሶት፤ በንቀት ላይ ንቀት፤ በጥላቻ ላይ ጥላቻ፤ በመቃቃር ላይ መቃቃር፤ በመሰንጠቅ ላይ መሰንጠቅ፤ በመተርተር ላይ መተርትር፤ በማብጠልጠል ላይ ማብጠልጠል፤ በመቀንስ ላይ መቀንስ። በማካፈል ላይ ማካፈል፤ በመቦጨቅ ላይ መቦጨቅ ሰፊ የሚዲያ እንደስትሪ በወበራ ከፍተን የተስፋ ስቅላት ብርንዶ ቤተኛ ለማሰባሰብ ስንማስን፤ ስንኳትን ትውልዱ ከእኛ ምን ይማራል የሚለውን ለአፍታ አስበነው የማናውቅ በራሳችን ተተኪ ባላደራ ህሊና ላይ ብክነትን ፈቅደን የምንተውን እኛ እንዲህ ነን፤ ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …

በመሰረታዊ ምክንያታዊ ፖለቲካ ጉዳዮች በማተኮር የፍላጎታችን ስኬታዊ መንገድ መተለም፤ ህሊናን በቅጡ ማደራጀት፤ በቅቶ ሐገር በቀሉን ናዚያዊ የደራጎን አውሬን ክፉ መንፈስ ለመመከት ስለሚቻልበት ሁኔታ ከማጥናት፤ ከመመርመር፤ በራስ ተኮር ተግባር ልቆ ከመገኘት ይልቅ የቃላት አቃቂር በማንሳት በመጣል፤ ወሳኝ ጉዳዮች ተድበስብሰው እንዲቀሩ ማገዶ አቅራቢዎች በመሆን ሊቀ ትጉኽን¡ … እኛ እንዲህ ነን… ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …

አለመታደል! ብሩክ አጀንዳዎች ለዛሬ እርሾ እንዳይሆኑ፤ ቀድመው እንዳይወጡ ከትክተን፣ ከትክተን በተለዋጭ ሥም አርሰን አፍርሰን ዓመቱ ሲቀዬር ስንጥር ፈለግን ቁርሾ ላይ ተከዝነን ውስጣችን ጎሽን ከልሶ ግን ላልነበርንበት ዕውነት ዋቢ ጠበቃ ሆነን እንደገና ደግሞ ከሳሽም ፈራጅም፤ ቀያሽም ሆነን ብቅ ማለት እኛስ የለመድነው ነው፤ ወጣቱ ምን ይታዘበን? አንዲት ስንኝ „የአማራ ተጋድሎ“ ለማለት ያልደፈርን፤ ይህ ብክነት እርግማን ሆኖበት ፍዳውን ለሚከፍለው አዲስ አፍላ ወጣት አብነታችን እያፈረሱ ለመገንባት፤ ገንብቶ በማፍረስ ሥነ - ልቦናዊ አቋም አልባ ህይወትን እንዳይመራ፤ ስንችል በመንቀል፤ ሳንችል በማነቃነቅ ስናወዛውዘው፤ ስለነገ ተተኪነት ሚዛናዊነት እና የሃላፊነት ስሜት አጀንዳችን አድርገን ለመስራት የማንደፍር „ለማብቃትም“ የማንፈቅድ፤ ዘመናችን በወርክብ ስንታመስ አሰላኢፈን፤ ያገኘውን ዕድል በክህሎት ዕድል የትሜና በትነን፤ ዛሬ ትውልዱን የሚያዳምጡ ትንግርት ቅኖች ሲጀመሩትም በውጥን በርብርቦሽ አምክኖ ምድረበዳ ለማድረግ በሽታሽቶሽ ሙቀጫ ስንሰልቅ ውለን የምናድር አድረን የምንውል እኛ እንዲህ ነን ኢትዮጵያም እንደሚታዬው ፎቶ ….

ምን ያህል የህሊና? ምን ያህል የመንፈስ እልቂት እያሰናዳን በዬዘመኑ የሰው ብርንዶ እንድምናቀርብ ማስተዋላችን የተቀማን እኛው ነን፤ ወቀሳን ገፋ አድርጎ ለሌላው ማሸከም የማይከብደን እኛ ስለምናጠፋው ደግሞ ድፍረትን በድፍረት የምንጥስ … እኛ እንዲህ ነን ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …
  • ·         ዳ።

ርግማን! በድርጅት ብዛት፤ በትችት ብዛት፤ በወቀሳ ብዛት፤ በስድብ ናዳ፤ በሽሽጎሽ ቧልት፤ በማሳነስ ግርሻ፤ በማመስ ጠበሳ፤ በመሆን አቅበት፤ በማድረግ ዳገት፤ በመገኘት ስንጥቅ ሰንተረትር፤ ዳጥ በመዋታት ስንታመስ፤ ግን አንድስም እንኳን ስለመልካም ነገር አጉልተን ለመናገር፤ አጉልተን ለመመስከር አንደበታችን የተቆለፈብን። እኛ እንዲህ ነን ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …
ሌላው ይቅርታ እንዲያደርግ ትእዛዙ ሲዥጎደጎድ፤ በአሉታዊ ወረርሽኝን ለማቃናት እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ስለባከነው ጊዜ፤ ስለፈሰሰው የሰው ጉልበት፤ ስለጠፋው የመንፈስ ሃብት፤ ስለተበተነው አቅም፤ ስለደማው ሥነ - ልቦናዊ ጉዳት ያነን ሚዛናዊ ለማድረግ ስለተሰዋው ማናቸውም ሁነት፤ ስለባከነው ትውልዳዊ ድርሻ ከራሳችን መጀመር የተሳነን፤ በሌላው ላይ ግን ለመጫን የደፋሮች ጳጳስ እኛ እንዲህ ነን፤ ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ …

·         እጅግ የምትናፍቁኝ የሐገሬ ልጆች ቅኖቹ … የትውልዱ ብከነት ውስጣችሁ ለሆነው ናፍቆቶቼ፤
በእጬጌው ሂደት ውስጥ ሁልጊዜም ክፍት ቦታ መተው ያስፈልጋል። አጋጠመኝ ብሎ ደስ ደስ የሚለውን ብቻ መሙላት አያስፈልግም። ለሚጎድሉ ነገሮችም ግማሽ ክፍት ቦታውን መተው ያስፈልጋል። 50/50። ይህ ከሆነ ስክነትን በመሪነት እንዲረዳ ያደርጋል። ሰው ኑሮው በደስታ እና በሃዘን፤ በመከፋት እና በሳቅ፤ በመበሳጨት እና በመርካት፤ በሙሙላት እና በመጉደል ባሉ ስሜቶች መኖሩ ግድ ነው። ተፈጥሯዊም ሰዋዊም ነው። ደስታ ሲበዛ ፈጣሪን ተንጠራርትን እናስቀይመዋለን። ሲከፋንም ደግሞ ማጣዋርን ሰንቀን እንሰበራለን። ይህም በልክ እንኖር ዘንድ፤ በልክ እንራመድ ዘንድ ግን እንጠነክር - እንጸና ዘንድ ተቋማችን ነው ሁለት የተቃርኖ ስሜቶች፤ ክስተቶች፤ አመክንዮዎች መኖራቸው ተፈጥሯዊ ነው። ጨለማ መኖሩ የሚታወቀው ብርሃን ስለመኖሩ ነው። ይህ የተፈጥሮ ጥብብ ጨለማው እንዳይሰለች - ሩህችን፤ በርሃኑም ግትር እንዳይሆን ንፍሳችን ይረዳል። ወደ ላይም እንዳንወጣ፤ ወደ ታችም እንዳንወርድ ሚዛን ይጠብቃል።

ዴሞክራሲም የሚባለውም የሚመች ነገር ብቻ ሳይሆን የማይመችንም እንደ ተመቼ አድርጎ መቀበል ማለት ነው። የማይመቸውን እንዲመች ለማድረግ፤ ባለመመቸት እንዳይዘልቅ ለማድረግ ደግም ትግል ይጠይቃል። ትግል ማለት የማያሰራውን አመክንዮ ማሰራት እንዲችል መታገል ማለት ነው - ለእኔ። ግልፍተኛ ስሜት የፖለቲካ ትርፍ አቅም አይደለም። ችኩል ትንፋሽም የሩጫ እርገት ነው። እጬጌውን ሂደቱን ለማስተናገድ ደግሞ ማዕከላዊ የተፈጥሮ ሐብት አለ „መቻቻል“ የሚባል። መቻቻሉን ሰንቁ በሥርዓት፤ በጭብጥ፤ በፋክት፤ በምክንያት፤ በጊዜ በቦታ፤ በሁኔታ በታሪክ መስካሪነት መሞገት የትርፍ ማርዳ ናርዶስ ነው።
ግን የሰጡትን አክብሮት፤ የሰጡትን ንዑድ ፍቅር አፋፍቶ መሆን አለበት። የሳሱለትን ተስፋ አቆርፍዶ ወይንም ከእሳት እንደገባ ፕላስቲክ አጨማትሮ አላውቅህም ብሎ አይደለም። „ለአይም“ „ለአዎ“ የምንሰጠውን ክብር እና ዕወቅና እኩል በመስጠት። „አይ“ በሚመለከት ባለፈው እንድ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። „አይ“ ልዩ አቅም ነው። ስለሆነም „አይ“ አቅም ኑሮት „አዎን“ አሸናፊ ሆኖ ይወጣ ዘንድ ቅንነት ያስፈልጋዋል፤ ትህትና ያስፈልገዋል። ተከታታይነት ያለው ጥረትም አጥሚቱ ነው። ከቅንነት በላይ ህይወትን የሚሰጥ መልካም ተፈጥሮ የለም። ሰው ቅን ከሆነ መኖር አይደክመውም።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በእኔ ዕድሜ አንድ ጠቅላይ ሚነስተር እንዲህ ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት ራሱን ዝቅ አድርጎ በኖረበት ሰብዕና ሳይለወጥ፤ በነረበት የድምጽ ቃና ሳይቀዬር፤ በኖረበት ሞራል ሳያዛባ ልክ እንደ እኔ ከሁለት ዓመት በፊት እንደምናወቀው በዛ ጽዑም አንደበት በነበረው ሰብዕና ላይ ከግርማው ጋር ሰክኖ ህዝብን ሲወያይ ሲያነገጋር ሳይ ይህ የመጀመሪያ ነው። ያዘው፤ አስረው፤ አሳደው፤ አጣብቀው፤ ጠርንፈው፤ ግጨው በዚህ ሞረድ የሰብዕና አዙሪት ፍዳውን ሲከፍል ለኖረ ህዝብ እንዲህ ባለ ቅዱስ መንፈስ ሲፈትሽ፤ ሲደባባብስ፤ አይዞህ ሲባል ትንግርት ነው - ለእኔ መሰል ቅኖች። እኛ የምናውቀው ሰብዕናችን ሲሸማቀቅ እና ሲሸበሸብ ነበር። ዛሬ ግን ተካስን። እንድሜ ለሚሊዮኖች ዕንባ።

ቀደም ብለው ለማያውቁት የሃይማኖት አቮ፤ ቀደም ብለው ይህን ምሩቅ መንፈስ ላላስተዋሉት ወገኖች እርግጥ ነው ቃል ብቻ ሊመስል ይችላል። ይህ መንፈስ ታላላቆቹን፤ ሊሂቆችን እክብሮ ያሰናደውን ሽልማት ሲሰጥ እንኳን ተነስታችሁ ኑና ከእጄ ውሰዱ አላለም። በዬቦታው እዬሄደ ነበር የክብር ሽልማታቸውን ወርዶ የሰጠው። በዚህ ውስጥ ብዙ ነገር ድርጊቱ ያናግራል። የአብይ መንፈስ የማለት ሳይሆን ከማለትም፤ ከመሆንም የላቀ የምርቃን ጸጋ ነው። ከዴሞክራሲም በላይ ሰዋዊ ነው። ተፈጥሯዊም ነው። 
ዶር አብይ አህመድ ህንፃውን አፍርሰው ስለሰሩት መግቢያው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሊቃውኑቱ አንባ እንዴት እንደሚመሰልም አስኪ በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ይዩት አበቮወ፤ ምድራውያንማ ሁልጊዜም አምላክ ስለሰጠን አመስግነነው አናውቅም።
·        
ጠቅላይ ሚንስትር / አብይ አህመድ በቀድሞ የስራ ባልደረቦች አንደበት ሲገለጹ

Ethiopia - የመወድስ ግጥም ለዶ/ አብይ አህመድ

Ethiopia - Dr Abiy ከላይ ስትሆኑ በዛ መነጽር ብቻ ታች አትመልከቱ

"ዶ/ አብይ አህመድ (ዲራአዝ) በሚል በዕር ስማቸው ስለ ቴዲ አፈሮ የፃፉት ቴዎድሮስ ተሾመ ምን አለ? ከደራው ጨዋታ"

 

የትእግስቱም፤ የትህትናውም፤ የሁለመናው ልስላሴ የፈጣሪ ጥበብ በሰው ልጅ አድሮ ሲሰራው ለማለት ይቻላል። ዕውን እዬሆነ ያለው በእኔ ዘመን ስለመሆኑ እያዬሁ ማመን ይቸግረኛል። የተጨነቁ አሉ። የህዝብ ፍቅር አንዳይዳብር፤ የጸላዬ ሰናይ ባልደራሶች ተቁነጥንጠዋል። ዕወቅቱ ሊኖር ይችላል ግን፤ ሰዋዊ ጸጋው ግን? ስለሆነም አጀንዳ አልቦሽነታቸው ያባትታቸዋል። ማጣፊያው አጥሯቸዋል። የንግግር ጥበብ ስለምን እንደ ተፈጠረ፤ መሪ ማለት ህዝብን ሳያገኝ ተንሳፎ፤ ሳያነጋግር መኖር ማለት መስሏቸው ሲያነሱ፤ ሲጥሉ ውለው ያድራሉ። አቅል ያላቸው ቅኖች ግን ይህ ሰብዕና በወረቀት ተነድፎ በዬማንፌሰቶው ሰሌዳ ላይ አምሮ በፍሬም ግድግዳ ላይ ከተንጠለጠለው የቃላት ድርድር በላይ የሰማይ መንገድ ስለመሆኑ ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ ሲጠና የቆዬ ነው። ለዛውም ተቆጥባ ወጥታ ነው እንጂ በሰፊው ቢሠራበት ስንት የመልካም ነገር ስንቅ አለ በዚህ ቅን ንጹህ መንፈስ ውስጥ።
የማይደፈር አቅም በዬዕለቱ በቀለማም ጸጋው ፍቅርን - መተሳሰብን - መረዳዳትን - ትብሺ ትብስን ለማፋፋት ተግቷል። የህዝብን ስሜት ያለበትን ደረጃ ሙቀቱን ለክቶ አቅምን ለማቀድ፤ ለምምራት እና ለማስታዳደር ሰብሉን እዬሰበሰበ ነው። ምርቱ ዝቀሽነቱ አይበገሬ ነው። ፈጣሪም አብሮ አለ። ቅኖች አዲስ ቀናችን ስለሆነ በሁሉም መስክ የአዎንታዊ ማሳዎች ሰፍተው እንዲፋፉ ጥረታችን ይቀጥላል። ዲቢሎሳዊ መንፈስም መንገዱ ሰባራ ነውና ቁልቁል ይወርዳል። የሟርት ጎሳሚ ጸላዬ ሰናይ የሚደያ መንፈሶችም በፈጣሪ ረቅቅ ጥበብ እዬኮሰሱ እዬከሱ ይሄዳሉ። አድማጭ አይጡ ሲሄዱ ፍቅር ባቀደው መንገድ የልዩነቱን ግድግዳ እዬደረመሰ ማዕዶቱን ያለማል። 
·         ኖርን ለማኖር።
መኖር አለ፤ መኖርን ለማኖር በመኖር ውስጥ ቀጣይ እና ተቋራጭ አምክንዮችን በስልት፤ በጥበብ፤ በፍቅር፤ በቅንነት፤ በማስቻል ለማዬት ስክንት አብዝቶ ያስፈልጋል። በልብ አልቦሽ የተደረደረ ድንጋይ ይናዳል። በህሊና የታናጸ ሞራላዊ ጽናት ግን ትውልድን ይገነባል። ትውልድ ለመገንባት ትውልድን በጸርነት ፈርጀው ለማምክን የተሰለፉ ተባይ ተውሳክ ርዕዮቶች መነቀል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ከሶሻሊዝም ቁሳዊነት ወደ ሰዋዊነት፤ ወደ ተፈጥሯዊነት ሽግግር የማድረግ የህሊና አቅም ይጠይቃል። ይህ ደግሞ የጀንበር ተግባር አይደለም። ጥልቅ ነው። የህዝብን ሥነ - ልቦናዊ አንድነት ወደ ቦታው ለለመለስ የጥረት ውጤት ነው። የ27 ዓመት ፍቺ ወደ አንድ መንፈስ ለማምጣት ስክነትን ይጠይቃል። እርጋታን ይሻል። ሰው በችኮላ የተሰራ የማሳሮ ጆሮ አይደለም።
  • ·         ልቦሾች።

እጅግ የምትናፍቁኝ ቅኖች ወገኖቼ … ይህን ከላይ የለጠፍኩትን ፎቶ ስታዩት ከሥር ያሉትን የወዳደቁትንም በተደሞ እባካችሁ እዩት እስኪ - በአክብሮት። ባለቤት የሌላቸው፤ ያልነበራቸው፤ ባሊህ ባይ ተፈጥሮላቸው የማያውቁ የእኛው ዜጎች ናቸው። ህሙማንን በዚህ ውስጥ ማዬት ትችላላችሁ። አልጋ ላይ የዋሉ፤ ህዝቡ ህይወቱን ኖሮበት። ሲብስበት ባለቤት የለኝም ብሎ ቁርጡን ሲያውቅ ያነሳቸው እጬጌ ጥያቄዎች አጀንዳዎቹ  ናቸው። ትናንት መሬት ላይ ወዳድቀው ቢታዩም፤ አቧራ ለብሰው እንደ አልባሌ ሆነው የትም ቢጣሉም። ለዛ እኔ ነኝ ያለ፤ የሽግግር በሉት፤ የአደራ መንግሥት፤ የአስታራቂ ይሁን ማንኛቸውም አካል የሚደፍሩት አይሆኑም። ለብዙዎቹ ሹመት እና ሽልማት እንጂ የፍቅራዊነት መንገድ ያልበረ ስለመሆኑ ከዚህች ሰሞናት ወዲያ መስታውት የለም።
አሁን ተመስገን የሚያሰኘው ዝቅ ብሎ ነገሮችን ሊያጠና የፈቀደ ልስሉስ መንፈስ ፈጣሪ በፈቀደው ሰዓትና ጊዜ ሰጠን። ጭንቁ እንዲህ እንደተበተን የቁርሾ ማወራረጃ ሆነን የአፍሪካ መሳቂያ እንዳንሆን ነበር። በዬቤቱ ዕምቅ ቁርሾ፤ ጥል ያሰኘው ቂም፤ በቀልን ያቀደ ወይንም ያረገዙ ብስጭቶች አሉ። እንዚህን በስልትና በጥበብ ለማድመጥ መፍቀድ ትልቅነት ነው። ይህ ድንቡልቡል ሚስጢር ገና የህሊና ማጠቢያ ማሽን ያስፈልገዋል።

… እናም የራስን ስራ ጠንክሮ ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ መትጋት። ሌላው ያለመመረጥ ጨዋታ ከቅንጅት ሌላ ማን በምርጫ መጣ? አዲስ ማንፌስቶ ይዘጋጃል የማንፌስቶው ፈጣሪው መሪ ራሱን ይሾማል፤ የሚቀርቡትን ለይቶ ያቀርባል፤ በስንት ጣር ጉባኤ ሲሆንም በዛው ይቀጥላል። መውረድ የለም እንደተንጠለጠሉ ዘመን መቁጠር። … ስለዚህ ወቃሹም ተወቃሽ፤ ተወቃሹም ወቃሽ መሆን አይችሉም። ታዛቢ በቅርብ ጌታው ህሊና በርቀት ዳኛው ህዝብ አለና።

አሁን ኢትዮጵያ ያለው መንፈስ … የወያኔ ሃርነት ትግራይ በመርፊ የከተበው፤ ወይንም በስሪንጅ ያስገባለት አይደለም።  ቀደም ባለው ጊዜ „አገሪቱ“ ነበር። አሁን ደግሞ „ህዳሴ“ ሆኗል። „ትግራይ“ ቢሉ አገር እንደሚናድ ያውቃሉ። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ለጠፍ ስላልሆነው  የእናት እና የልጅ የልብ ተልብ የቀደመ ቅኔ በጥቂቱ … … የእኔ አይደለም ቅኔው ዝልቅ ነው፤ የቅኔው ዘረፋም ምጥቅ ነው፤ የአዳዲስ አማርኛ ቃላት አፈጣጣጠሩም ሩቅ ነው … ለመተርጎም ትንሽ እንደ አቅሚቲ ጀምሬዋለሁኝ አልጨረስኩትም … ለትውና ሥራ ባሌቤቶች በላሙያዎች መንገዱን እንዲያዩት ለማመላከት … በተለይ ቅኖቹ። ስችል ቀን ያው ለሳተናው ይላካል። ለዛሬ ግን ለቅምሻ እንደ አለ እንዲህ …  የባለቅኔው ወጣት የጠ/ ሚር አብይ አህመድ መንፈስ …. ከላይ በሚያምር ድምጽ ቀርቧል በጹሑፍ ሲሆን የበለጠ ስሜትን አስክኖ ውስጥን በጸጋው ያሳዬናል … 

„ዛሬ ሳይሆን ትናንት አሁን ሳይሆን ድሮ
ያኔ ምንም ሳልሆን ምኔም ተቀይሮ፤
ከርመን ልንገናኝ ኑረን ልንሰናኝ አልቦነት ተሽሮ፤
እኔ እና አንቺ እኮ ነበረን ቀጠሮ።
ቀጠሮ ክቡር ነው ካገርም ቢሰፋ
ቀጠሮ ክቡር ነው የእንገናኝ ተስፋ፤
ለዚያ ነው ያለሁት በቀጠሮሽ ቦታ፤
በቀጠርሽኝ ቦታ ሙሽራዬን አንችን ሰርግ ላገለግል ህልምሽን ልፈታ።
ለዚያ ነው ያለሁት የእኔን ነገር ጥዬ ለቀጠሮሽ ብዬ፤
ካዋልሽኝ እዬዋልኩ ካኖርሽኝ እዬኖርኩ ስትጥይኝ ተጥዬ
አንችኑ ቀዳሽ ነው፤ አንቺን ባይ መንፈሴ
ለእኔ እኮ ባዳናት መከረኛ ነፍሴ“

v  „ልነሰናኝ“ አዲስ የቃል አገባብ ነው። „አልቦነት“ ዞግ ዘለል መንፈስ ነው።
v  ውዲቷ ኢትዮጵያ የተሰጠ የነፍስ ስጦታ ነው - የወጣቱ ባለቅኔ።
  • ·         ሳዊነት።

ያልደረሰንበት ጣሪያ! ቅድሚያ መንፈስ ይደራጅ። ገበሬም ሰው ነው። ሴትም ሰው ናት። ወጣትም ሰው ነው። ኪነጥበብ ቤተኛም ሰው ነው። መምህሩም ሰው ነው። ሠራተኛውም ሰው ነው። መንገድ ላይ የወደቁትም ሰዎች ናቸው። አዛውንቱም ሰው ነው። ደሃዋም/ ደሃውም ሰው ነው፤ የጎዳና አዳሪውም ሰው ነው፤ ሰው ናት። የኢትዮጵያ ችግር ቢዘረጋ 7 አህጉራት ያነጥፋል። ሌላው ቀርቶ ችግሩን እንደ ዓይነቱ በሰንጠረዥ ዘርዝሮ የማስቀመጥ አቅሙም የለንም። እንኳንስ በፋይል ለማድረግ፤ እንኳንስ ፋይሉን በማቀፊያ ለማድረግ፤ እንኳንስ በማቀፊያ ያደረግነው መደርደሪያ ላይ አድርገን እንደ ቅደምተከተላቸው ለሥራ በሚያመች ሁኔታ መዋለ መንፈሳችን፤ መዋለ ንዋያችን፤ መዋለ ማሳችን አደራጅተን በፍጥነት በዬፈርጃቸው ለይተን ለመንቀሳቀስ ቀርቶ፤ ገና መሆናችን አለማዋቀችን ነው ከፍላጎታችን ጋር ሊያገናኘን ያልቻለው። ይህ አለመቻል እኮ ነው መድፍ እዬረገጠ ህዝብ ሲረመጥ የከረመው … ድርጁ መሪ ስለአጣ። እሲክ ዓይነ ገብ የቢሮ አመራር እና አደረጃጀት ይኑረን። በምስቅልቅል ቢሮ እንግዳን ቁጭ አድርጎ ሐገራዊ ጉዳዮች ጋር ለማወያዬት የማይደረፍ ሐቅ ነው። ለዛውም ኢትዮጵን ያህል ገናና ሐገር የወዘተረፈ ችግር መናህሪያ።
  • ·         ርሾ።

የትኛው ችግር ከዬትኛው ይቅደም ለማለት ችግሮችን ለይቶ አበጥሮ አንተርትሮ መለዬትን ይጠይቃል። ለዚህ ነው ትናንት የተከፈለውን መስዋዕትነት እዬረሳን በአዲሱ ላይ ሃይልና አቅማችን በማባከን ላይ የምንገኘው። ከትናንት መነሳት ስለሚሳነን እርሾ አልቦሽ ስንባዘን የምንታዬውም በዚኸው ነው - ብክነት። ሦስት አራት የምንደረድራቸው ችግሮች ብቻ አይደሉም። ተዘርዝሮም፤ ተጽፎም፤ ተነግሮም የማያልቅ ችግር ነው ያለው። ወገኖቼ ቅኖቹ …. ልክ እንደምታዩት ፎቶ ….
ጥቂት ምሳሌ … አንድ የቅርስ ጥበቃን ብንወስድ ችግሩን ለይቶ በፈርጅ ፈርጁ ለማቅረብ የዓመታት ተግባር ነው። እስረኛ በሚመለከት የአጋዚው ቤት፤ የአጋዚው የሚራመድበት መንገድ፤ አጋዚው ዕቃ ለመግዛት ዘው የሚልበት ሱቅ በደረቴ፤ አጋዚው የሚኖርበት ሰፈር ሁሉ እስረኛ ነው፤ ያሰፈራል፤ ፋቲኩ ያስፈራል … የወያኔ ሃርነት ትግራይ አባላት በያሉበት ቦታ ሁሉ ዓፄዎች ናቸው፤ ያስፈራሉ … ያርዳሉ … ሰው በቤቱ ነፃነት የለውም። ሰው በነፍሱ ነፃነት የለውም። ሰው በአካሉ ነፃነት የለውም። ሌላው ቀርቶ ከዚህ ዓለም የተሰናበቱ አጽመ ርስቶች ሰላማቸው የታወከ ነው። ከሰው ይልቅ ቀልሃ፤ ካቴና ሙሉ ነፃነት የታወጀላቸው ናቸው … ይህ የአንድ ጀንበር ሥራ አይደለም።

ጭካኔን በዓዋጅ ማስቆም አይቻልም። ጭካኔ እኮ ስሜት ነው። ስሜት ልታስረው፤ ልትደበድበው አትችልም። ስሜትን ለመግራት አንተ ከጭካኔያዊ ዕሳቤ ራስንህን መጀመሪያ ማዳን ያስፈልጋሃል። ዕዱሉን ብታገኝ ይህን ሲጨክን የባጀን ስሜት ትቀጠቅጠዋለኽ ወይንስ ሰው እንዲሆን ጥረት ትጀምርለህ? ፈታኙ ጥያቄ ይሄው ነው። ሰው ለመሆን የሰው ፊቱ ሰው ይመሰላል ብሎ መነሳትን ይጠይቃል።

  • ·         መሪነት እና ጠባቂ።

ይሄ ከልጅነቴ ጀምሮ እምመኘው ምኞቴ ነበር። ካለ ወታደር፤ ካለ ጠባቂ የሚሄድ መሪ። ቀድሞ ነገር ካለጠባቂ የሚሄድ መሪ አለን? የትኛው መሪ ነው ውጪ ሐገር የሚኖረው አሁን አፍሪካ ስብሰባ ቢኖረው ብድግ ብሎ የሚሄደው? ይችላልን ወይንስ ይጠለፋል? የትኛውን መሪ ነው በፈቀድነው ጊዜ አግኝተን ለአደባባይ ሳናበቃ የልባችን ቁስል ዱለንበት ወህ የምንለው? አለን? በቀጥታ አግኝተን ያሻንን የፈቀድነውን የምናነጋግረው መሪ በሃሳብስ አለን? የውጮች ሐገሮችን ታላላቅ የሐገር መሪዎችን ሳይቀር የመጨረሻ ደረጃ ያላቸውን ማግኘት እንችላለን። አክብረውም መልስ ይልኩልናል በአድራሻችን። ፖስታ ቤት ሂደው ራሳቸው ያስጋባሉ፤ በእጅ ጹሑፋቸው አድራሻችን ይጽፋሉ። እኛና መሬዎቻችን የት ላይ ነው የምንገናኛው? መከራችን ብዙ ነው። ፍዳችን ውቅያኖስ ነው። ዛሬ ያ ሁሉ የተሰማ ፍላሎት 27 ዓመት ታምቆ የፈላ የመከራ ሞገድ ነበር። መታፈን ለነፃነት የስቃይ ዕዳው ነው። 
  • ·         ደወል።

ከዚህ ላይ መቀሌ አቅራቢያ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥን ይሁነኝ ብሎ ማድመጥ ይገባል … እዮር በፈቀደው ሰዓት የፈቀደውን የመከወን ባለድርሻ ነውና … ይህ የፈጣሪ መልዕክት ለሁሉም ነው። ልብ ያለው ግን ከስንት አንድ እንኳን የለም። ፈጣሪ የሰጠን የበቃችሁ መሪ ቃል ነበር፤ ብናውቅበት። ፍቅር እዬመጣልን ጠብ ያምረናል። ትህትና እዬተጋበዝን ሳንጃ ሸው ይለናል። አክብሮት እየመጣልን ርግጫን እንሻለን ኧረ የኛውስ የጉድ ነው። ቅልጣን አይሉት ቅልጣን፤ ቅብጠት አይሉት ቅብጠት፤ ዘመናይነት አይሉት ዘመናይነት … ለዛውም በመዳፍ የእኔ የምንለው እኛ የደከምንበት፤ የወጣን የወረድንበት፤ አቀበት ቁልቁለት የወጣንበት፤ የወረድንበት፤ ፍቅር ለግስን በፍቅር የከበከብነው የመንፈስ ጥሪት ሳይኖር ነው ይህ ሁሉ ጉድ እዬታዬ ያለው።
  • ·         ነዲድ ላናቃ።

እንዲህ ዝብርቁ፤ እንዲህ ድብልቅልቁ በወጣ ሁኔታ ላይ የተቀመጠ መሪ ለእኔ እንደ አዛርያ፤ እንደ ሚሳዬል፤ እንደ አናንያ ነው … ጫናው፤ ውጥረቱ፤ ጦርነቱ ፍንዳታው፤ ቀውሱ፤ ወቀሳው፤ ትእዛዙ፤ ትችቱ፤ ሰው ከሚችለው በላይ ነው … ሰው በመሆን ብቻ የተቻለ ነው። እያንዳንዱ ይህን ቀን ቢሰጠው በበነገታው መነሳት አይቻለውም። ይፈነዳል። … ሰባት ቀን እና ሌት መሥራት … ከግምት በላይ ነው … ከብረት ቁርጥራጭ መሰራት። እንግዲህ ይሄ በዘመነ ኢሠፓ የነበረ ልማድ ነው። እኛ እራሱ ማትራሳችን ቢሯችን ነው። ስንቅ እየተመላለሰልን ነው ከቤት የምንሥራው ጊዜ ለመቆጠብ። ክ/ ሐገር ላይ … ሰንበት ዓውደ ዓመት አያውቀንም እኛም አናውቀውም። አውራጃ ላይማ፤ ስሜን አውራጃ፤ ወገራ አውራጃ፤ ሊቦ አውራጃ፤ ሰቲት ወራዳ፤ አርማጭሆ ወረዳ የሚያድሩት ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ጉድብ ነው። አፈር ለብሰው። አካሎቻችን ልብሳቸውም ፋቲክ ነበር። እረፍት ወጥቶ የሚያውቅ ሠራተኛ አልነበረም። ቀድሞ ነገር የ ዓመት እረፍት ስለመኖሩም፤ በህግ ስለመደንገጉም አናውቅም። ይሄ የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ቀርቶ የዘመን መለወጫ ቤታችን ለግማሽ ቀን ባሳለፍን ምንኛ ዕድል በነበር? ልብሳችንም ዩኒፎርም ካኪ ነው የነበረው። ሌቱም ተሎ ነው የሚያልቅብን። ማንም ሰው በፈለገው ሰዓት እና ቀን እና ሌሊት ቢፈልገን ደውሎ ያገኘናል። ቢሯችን ወደ መኖሪያ ቤት ተቀይሮ ነበር። የቅልጣን ጊዜ አልነበረም። ወጣትነታችን ጋር የተላለፍነው በዚህ መልክ ነበር። ለዚህ ነው እኔ በሥራ ደክሞኝ የማያውቀው።  … ዛሬ ይህን መሰል የሥራ ባህልን በፈቃድ የማገልገል ጥበብ ጅምር ኢትዮጵያ ውስጥ እያዳመጥኩኝ ነው። ግን ቅንነት ከዬት ይሸመት፤ በዬትኛው የሰማይ ቤት ጸበል ለሁሉ ይረጭ … ፍላጎቱ ውዲህ መወራጫቱ ወዲያ ያልተገናኝቶ ገብያ … ከተደላደለው አውሮፓ እና ስሜን አሜሪካ ተቀምጦ በሽታሽቶ ቅኑ መንገድ ካለርህራሄ እም! …  

ሌላ አንድ ነገር ልክል። እዚህም ሲዊዘርላንድ መደበኛ ሥራ ማግኘት አይቻልም። በጣም የማይቻል ነገር ነው። የፈለገ ጥረት ቢደርግ ሥራ ማግኘት የመኖር ዳገቱ ነው። ግን በፈቃድ በነፃ መገልገል ይቻላል። መልካሙ ነገር በፈቃድ ሲገለገል የተለያዩ ሙያዎችን የመቅሰም ልምድም ስለሚኖር እያንዳንዱ ሥራ የራሱ ቀለም ስላለው ህብራዊ ቀለም ይገኛል። የፈቃድ አገልግሎቱ ጫና የለበትም፤ ግን ነፃ የሥራ ልምድ ታላቅ የጥበብ ት/ ቤት ነው። ከዛ በላይ በህይወት የማይገኙ ሰዎችን የማግኘት አጋጣሚው ሲታከልበት ትርፉ ብዙ ነው። በነፃ ሲገለገል ከእኔስ የሚለውን ስለሚመልስ ፍጹም የሆነ ውስጣዊ ደስታ ነው የሚሰጠው። ጤና ነው። የእኔ ሁሎችም ጓደኞቼ ከዛ የማገኛቸው ናቸው። የእናቴ ልጅ ያህል ነው የሚሰሙኝ። አሁን ኢትዮጵያም ይህን ቅዱስ መንፈስ እያዳመጥኩኝ ነው። ተመስገን!
  • ·         ንበር።

ሰው የራሱን ነፃነት አንዳይነካበት እንደሚፈቅደው ሁሉ ሌላውም ሰው የግሉ ነፃነት እንዳለው ማወቅ ይገባዋል። የግል ዕይታ፤ የግል ዕምነት፤ የግል አትኩሮት፤ የግል የሥራ ስምሪት የራስ መብት ነው። የራሰም ውበት ነው። የራሰም ቀለም ነው። በዚህ መብት ውስጥ የሰው ልጅ ኮፒ ያልሆነ የራሱ የሆነ የሥራ - አማራር ጥበብ አለው። አመራር ሬድ ሜድ የለውም። እንደ ሰው ሰብዕና ይለያያል። አንዱ ከሥር፤ ሌላው ከማህል፤ ሌላው ከላይ፤ ሌላው ከጠርዝ፤ ሌላው ከቁንጮ ሊጀምር ይችላል። አሁን እኔን በፖለቲካ ሰብዕና የቀረጸኝ ጓድ ገ/ መድህን የመጀመሪያው ጸጋው። ሰውን ማየት ነው። ሁለተኛው ጸጋው ማድመጥ ነው። ሦስተኛ ጸጋው ከብዙ ሰው ለ እሱ የማያት እና የማድመጥ መንፈስ ምቹ የሆነውን መንፈስ መርጦ „ማብቃት“ ነው። በማብቃት ሂደት ውስጥ ያ ምርጥ መንፈስ „ክትትል“ ይደረግለታል ድርቀት እንዳይገጥመው ውሃ ገብ የመስኖ ሃዲድ ይዘረጋለታል። በተወሰነች የጊዜ ማዕቀፍ ወስጥ ዘመን የሚያሻግር ሙሉ ሰብዕና ይገነባል። ተተኪው ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጠርለት እሱም መሰሉን ይከውናል፤ ተከታታይነት የህሊና ቀረፃ በድርጁ መንፈስ ያለማቋረጥ ይከወናል።

የእያንዳንዱ መሪ አፈጣጠር ይለያያል። ኮ/ አሰፋ ሞሲሳ ደግሞ በጥያቄና በመልስ ወስጥ ነው ተመክሮን የሚያቀኑት። ጓድ ዘርጋው አስፈራ እጅግ አንባቢ ነው፤ ከመጸህፍት ያገኘቸውን መልካም ነገሮች ጣል እያደረገ እያዋዛ ያስተምራል። የሥነ ጹሑፍ ውበት ከእሱ የወሰድኩት ነው። በፃፋቸው ንግግሮች ላይም ውይይት እናደርግ ስለነበረ ማረፍ ሲያምረው ቢሮው ውስጥ ይጠራኝ እና እንሟገታለን። ያው የሶሻሊዝም ኢንትሪግ ያን ጊዜ ስለነበር የሆዴን የምነግረው ለእሱ ብቻ ነበር። መምህርም ስለሆነ ከተማሪዎቹ እንደ አንዷ ነበር የሚያዬኝ። ቃላቶቹ የውበታቸው ጥልቅት ምን ይባሉ? ኳካብ ናቸው። በጣም የሚቀለኝ ሰው ነበር። ጓድ አበበ በዳዳ በእዬለቱ ቢሮችን እሰኪጸዳ ነበር እኔ የማገኘው። የቢሯችን ቁልፍ ለጽዳተኞች ስለማይሰጥ። እሱ ደግሞ የህይወት ተመክሮቹን ዘና አድርጎኝ እንደ አለቃ ሳላዬው፤ ሳልፈራው እንደ ታናሽ እህቱ ቅርብ አድርጎኝ ያጫውተኝ ነበር። ከ እሱ ጋር ማህበራዊ ኑሮውን ስለሆነ ያስጠናኝ የነበረው እኔም የገጠሙኝን እንግረዋለሁኝ። ከሁሉ የሚገርመኝ ይሰጡኝ የነበረው ፍጹማዊ ነፃነት ነበር። ሥርጉቴ ደግሞ የመማር ጥማቷ በዚህ መስምር ታለማው ነበር። መማር በዩንቨርስቲ ብቻ አይገኝም። ሰለሆነም እዚህ ሥራ አገኘሁ አላገኘሁ ከገንዘብ ጋር አይደለም ቁርኝቴ ልምድ የማገኝበትን፤ የጤና አቅሜ የሚፈቅደውን የነፃ አገልግሎት መስጠትን አሳድጄ እታደምበታለሁኝ። ሥራ እና ሠራተኛ እንዲገናኙ ዬዬመሪው የጥበብ አያያዝ የተለያዬ ነው። የተቀባይውም እንዲሁ። ስለዚህ እኔ በምቀድለህ መስመር ብቻ ተጓዝ ማለት የተወለደ ልጅም ይህን ገምድልነት አይቀበለውም እንኳንስ የፌስ ቡክ ቀጭን አዛዥነትን። 
·         ሰው ሮቦት አይደለም። 

ሰውን የሚያዘው የራሱ ህሊና ብቻ ነው። በኤሌትሪክ ገመድ ትብብትብ ደመነፍሱን የሚንቀሳቀስ የሰው ልጅ የለም። ሰው ታላቅ ዕጹብ ድንቅ ፍጡር ነው። ሰው ረቂቅም ነው። ሰው መንፈስም ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክትም፤ መክሊትም ይዞ ነው የሚፈጠረው። እኛ እንደ ራሳችን ለመኖር የምንፈቅደውን ያህል ሌላውም በራሱ ውስጥ ለመኖር በሚያደርገው ሂደት መጋፋት ኢትዮጵያዊነት አይደለም። ስናበራው የሚበራ፤ ስናጠፋው እንደሚጠፋ ቤተ ቆጣሪ ማዬቱ ያስገምታል። የአረብ ሥነ ጹሑፎች የመጠቁ ናቸው። ግን ገረር ያሉ ናቸው። ስለምን „ይሉኝታ“ የሚባል ጸበል ስለሚያነሳቸው - ለእኔ። „ይሉኝታ“ ያልሠራንበት፤ ያልጻፍንብት፤ ምርምር ያላደረግንበት ግን የህሊና ዳኛችን ችሎታችን ነው። ድንበር ጥሶ መሄድ የተገባ አይመስለኝም። ለነፃነት እዬታገሉ የሌላውን ነፃነት እዬተጋፉ ከሆነ ውደቀቱ ከራስ ይጀምራል። በዛ ላይ እንታገለዋለን የምንለው ድርጅት የማናዬው ተመራምረን የማንደርስበት እኮ ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማለት። በፍጹም ሁኔታ ወያኔ ሃርነት ትግራይን አናውቀውም። ሴራውን በመሸረብ የተዋጣለት የሴራ መሃንዲስ ነው … እና ለእሱ ስንቅ ማቀበል ትውልድን ያተርፋልን? ለዚህ ነው የህሊና ቤታችን ፎቶውን ይመስላልያልኩት። የፍላጎታችን መንፈስም እንዲህ እና እንዲያ …

ዜና ልትሰሙ ሲከፈት መርዶ፤ ድህረ ገጽ ልታነቡ ጎራ ስትሉ ሟርት፤ ዩቱብ ስትቡ „አስደንጋጭ ዜና“ ይላል ርእሱ ገና። የውድቅት ስለት? የነፃነት ዋጋው ምን ያህል ይሆን?!!  አንድ ሚደያ እንዲያው ተሳስቶ ስለ መልካምነት፤ ስለደግነት፤ ሰለበለጠው ውጤታም ነገር እንዴት ማንሳት ይሳነዋል። አንዱ ታገደ ሲል ሌለው ተለቀቀ ይላል። ከእንዴት አይነት ቤተሰብ ታደገ ያሰኛል? መጀመሪያ ቅጥ መጠኑ በዚህ ነው፤ ውሉ ይሄኛው ነው፤ ውልብሊቢቱ ይሄ ነው የሚባልበት በሌለበት ድብልቅልቅ ባሉ የፍላጎት፤ የራዕይ፤ የተስፋ ትርምስምስ ተቀምጠን የተያዘ የተረዘዘውን ሁሉ በመተቸት በቃ ተፎካካሪነት ያለ መስሎናል? ወዘተረፈ ችግርን የተሸከመች ሐገርን ለመምራት አንዲትን ቢሮ በሥርዓት ለማደረጃት እስኪ አቅሙን አምጠን እንውለደው …   
  • ·         ክወና።

ትጋት መሆን ያለበት አገር ቤት በመልካም ጉዞዎች ላይ ማበረታት፤ አጃቢ ጃንጥላ ጉዳዮችን ትቶ ወሳኝ ጉዳዮችን አንስቶ በጨዋ ደንብ መሞገት፤ ትውልዱ ሞራላዊ ዕሴቱን ሳይለቅ ሙግትን መማር እንዲችል ያደርገዋል። በእያንዳንዷ ነጥብ ጣቢያ የትውልድ ግንባታ መዘንጋት የለበትም።

የማከብራችሁ የሐገሬ ልጆች ኢትዮጵያም እንደምታዩት ፎቶ ናት። ሁሉም ቢችል እዛው ቢቀመጥ ከዚህ የተሻለ ስዕል ይኖረን ነበርን? ወይንም እንደ ሲዊዞች 7 ወንበር ቢዘጋጅ እንገላገል ይሆን? ግን እኛ እራሳችን በጥበቃና በተደላደ ሁኔታ ሆነን እነሱ ያን ፍዳ እና መከራ ተሸክመው፤ ቀን እና ወቅት ጠብቀው ሐገር ጥለው ሳይሰደዱ፤ እዚህ ድረስ በማደረሳቸው በራሱ ትልቅ ድል ነው። ግን  ለእኛ መላዕክ ቢመጣም አይጥንም። መቼውንም አንረካም። መቼውንም ተመስገን አንልም። መቼውንም የትውልዱ ብክነት እንዲቆም አንሻም። ትግል የምሽት ተግባር አይደለም … ሂደትን ተከተሎ መሄድ ይኖርበታል … ግን እንዲህ በዬፌርማታው ተስፋ  እዬተቆረጠ አይደለም። ማዘዝ የሚቻለው ራስ ባደራጁት፤ በመሩት፤ በመረጡት አካል ብቻ ነው። ለዛ ብቁ ነን? የሚበልጠን ሥም ለማንገሥ መቼ አስበነው አውቀን ነው? 42 ዓመት ከታወቁት መሪ ሥያሜዎች ላይ ነው እኮ አሁንም ቸክለን ያለነው። … ያለችን ሐገር ይህን ፎቶ ትመስላለች … ጠቅላይ ሚኒስተር ዶር አብይ አህመድ እስከ ካቢኒያቸው የተረከቧት ኢትዮጵያ ይህን ፎቶ ባህካል ትምስላለች …. ፍርድ ለራስ ነው - ዳኝነትም የህሊና።   

የኔዎቹ ለነበረን ውብ ሸባላ ጊዜ ኑሩልኝን ዝቅ ብዬ ልሸልም።
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ዓራት ዓይናማው መንገዳችን ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህና ሰንብቱ! መሸቢያ የተዋበ ጊዜ!




አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።