አይ No“ ልዩ አቅም ነው።
„አይ No“ ልዩ አቅም ነው።
ከሥርጉተ© ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
04.03.2018
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ።)
04.03.2018
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ።)
„ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሄር ምህረት የተናሳ ነው። ርህራሄው አያልቅምና።“
ሰቆቃው ኤርምያስ (ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፳፪)
ሁልጊዜ የሰው ልጅ ሃሳቡ ተቀባይነት ሲያገኝ እጅግ ደስተኛ እና ሳቂተኛ ይሆናል። „እሺ“ ከሁሉም በላይ የመልካም ነገር ማህጸን ነው እና። እንደ እኔ ዕይታ ደግሞ „አይ“ ማለትም ተወዳጅ ሰብዕና ነው። ብልጽግናው „በማዬት“ አድማጭነት ስለሚለካ። እንደዚህ ዓይነት ሰብዕና ፊት ለፊት ሲሞግተን ደስ ሊለን ይገባል። „እሺን“ ሆነ „ይሁንን“ ስንቀበል ደስ እንደሚለን ሁሉ „አይ“ „አይቻልም“ „አልተቀበልኩትም“ ስንባልም ከውስጣችን ደስ ሊለን ይገባል። ምክንያቱም „በአይሆንም“ ውስጥም ሌላ የአቅም ቅምጥ ሃብት አለና። አንደኛ የሰው ልጅ እንደ ፈጣሪ እራሱን ከሚያይበት ወንበር ዝቅ ብሎ ተፈጣሪ መሆኑን ያውቅበታል። የሰው ልጅ የአቅሙን፤ የመብቱን ጣሪያና ግድግዳ ማወቅ በቻለ ቁጥር የሰውነቱን የማስተዋል ፍሬ ነገር ያያል። በሌላ በኩል የ„አይ“
ቤተሰቦች መንፈስ „ከእሺ“ የበለጡና የተሻሉ ሲሆኑ፤ መሬት ላይ ሙሉ የሆነ ስብዕናን የተላበሱ መንፈሶች ጥሪታቸው እንዲሆን የማድረግ
ባለ ልዩ አቅም ናቸው። ሰው ከቁሳዊ ነገሮች አምልኮት ጋር ባበደበት በዚህ ዘመን „አይን“ የሚደፍሩ የህሊና ዓይን ያላቸው ብቻ
ናቸው። ምከንያቱም ጥልቅ የተፈጠሮ ሚስጢራት መገለጫዎች „ከማዬት“ ማዬት የተገኙ ናቸው እና። ምንም ነገር በምድር ላይ ግኝቱ „በማዬት“
ውስጥ የተፈጠረ ነው።
„ማዬት“ ትልቅ ጸጋ ነው። „ማዬት“ ትልቅ ጸጋ የሚሆነው ከውስጥ በአትኩሮት ከተቀመመ ብቻ ነው። ከዚህም ባለፈ በጥልቀትና በማስተዋል ከተቃኘ ነው „ማዬት“ መክሊት የሚሆነው። ከመደበኛው አማተራዊ „ማዬት“ ጸጋዊ ማዬት የሚለዬው ጉዳዩን የእኔ ብሎ በውስጥነት ለመርመር መፍቀድ ሲቻል ብቻ ነው። ውስጥነት ሲሰጥ ስውር ክስተቶች ራሳቸውን ይገልጣሉ። በመገላለጥ ውስጥ መገናኘት ይፈጠራል። በመገናኘት ውስጥ መተያዬት፤ መነጋገር ይገኛል። በመነጋገር ውስጥ መደማመጥና መቀባበልም ይመሰጣል። ትርፍ ማለት ይሄ ነው።
እርግጥ „ማዬት“ ብዙ ያልተባለለት ግን ዓለምን ምቹ እንድትሆን ያደረገ፤ የመኖር ሸክም እንዲቃለል የሆነው „በማዬት“ ውስጥ መገኘት ስለታዬ ነው። ሳይንቲስት፤ ፈላስፋ፤ ተማራማሪ የምንላቸው „ማዬት“ ልዩ የሃይል ልቅና ያለው መሆኑን መጀመሪያ በመቀበላቸው ነው። ስትመሰጥበት የተተበተቡ ነገሮች ይፍታታሉ። የከበዱ ነገሮች ያናግራሉ። የከበዱ ነገሮች መናገር ሲጀምሩ መዳኛቸውም ፍንትው
ብሎ ይታያል። ችግር መኖሩ መፍትሄ እንድንሻለት ያነሳሳናል። መፍትሄ ለማግኘት በማዬት ውስጥ „ማዬትን“ ማግኘት ይቻላል። የታመመውን ቦታ ማዬት ከቻልክ ታክመዋለህ። ከታከመ ደግሞ ይድናል። ከዳነ ህይወትን ይታደጋል። ህይወት መኖር ሆነ ማለት ነው። መኖር ሥርዓትን ከተከተለ ትውልድን ያጸድቅል - ያንፃል። ግን „ማዬት“ እንዲመራን ሲፈቀድለት ብቻ ነው። የሚያዩ ሰዎች ደግሞ በዓለማችን እጅግ በጣም ጥቂቶች
ናቸው። ለዚህም ነው „ማዬት“ የማይችሉት ስለበረከቱ ዓለማችን የጭንቀት፤ የስጋት፤ የመከራ አትክልተኛ የሆነችው።
ሌላው ሁለተኛው ተመሳጮች ባለመክሊት አይዎች አቅሙን ተጠቅመው „ማዬትን“ ሃይል ፈጣሪ ማድረግ በማቻላቸው ነው። ማዬትን ከውስጣቸው ተቀብለውታል። ስለሆነም „አይሆንም“ የሚሉ ሰዎች ባለቤቱ ያልታዬውን ጉድፍ ሆነ ግድፈት እነሱ አይተውታል ማለት ነው። ስለሆነም „አይሆንም“ ሲሉ የማዬት ልቅናቸውን ከማክበር፤ ከመቀበል ተነስተን „አይ“ ያሉበትን ነገር በፍጹም ንጽህና እና ቅድስና በትህትና መመርመር ይገባል። ጊዜ ወስደን ያልተመቻቸውን አካባቢ ወይንም ክስተት ማጥናት ያስፈልጋል። እውቅና ሰጥቶ፤ አጀንዳ አደርጎ፤ የእኔ ብሎ መውሰድም ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ያለፈውም ሃሳብ ውድቀት ሊገጥመው ይችላል። መውደቁን እያወቁ በ ማይረባው መንገድ መሄድ የማይጠገኑ
ጥቋቁር ዕድሎች ሊወልድ ይችላል። የተወሰነ ነገር ሁሉ ጠቃሚ ላይሆን ይችላል። ታሪክም አለ የሚታዘብ። አብሶ „ማዬት“ በተሳነን
ቁጥር ጠቡ ከታላቁ የተፈጥሮ መፈጠር ምክንያታዊ ከሆነው ሰው ጋር ይሆናል። ሰው የአንድ ቀን ምርት አይደለም። ማዬታችን አማተራዊ
ስለሆነ ሰው የፈጠረው ቀለሃ „ሰውን“ ያህል ፍጡር ስንቁ የሚደረገውም ለዚህ ነው።
„አይ“ መባል እንደ አሉታዊ መወሰድ በፍጹም የለበትም። „ሰውን“ ሊያተርፍ የሚተጋ „አይ“ ሊደመጥ ይገባዋል። አንድ መኪና መንጃ
የሚያወጣ ተፈታኝ አንዲት ስህተት ከተገኘበት አያልፍም። ለምን? ጨወታው ሰው ገብያ ተሂዶ የሚሸመት ባለመሆኑ ነው። „ሰውን“ የሰው
ልጅም በእጁ ጠፍጥፎ፤ አንቦልቡሉ ሊሠራው የማይችል በመሆኑ። ስለሆነም ሌላው ቀርቶ ጤነኛ መንፈስ በሌላቸው ሰብዕናዎች ውስጥ እንኳን „አይሆንም“ ከመጣ „የአይም“ ተቀባዩ፤ አቀባበሉ በቅንነት ከሆነ የውስጥ ሰላሙን ይሰንቅበታል። የውስጥ ሰላም የሚታወከው የትኛውንም „የአይሆንም“ ሂደት „በአሉታዊ“ ምልከታ ከተቃኘ ብቻ ነው። „አይ“ ጆሮ ለሌላቸው ፍጡራን ስለመፈጠሩ ላያውቁት ይችላሉ። ግን በግራ በቀኝ ጆሮ ግንድ ላይ ተተክሏል - ለምስል።
እርግጥ ነው ህሊና ከሚጸዬፍባቸው ነገሮች ዋንኛው የማሰብ ነፃነት እስርኝነትን ነው። ግን ከነፍስ እስረኝነትን መፍታት የሚቻለው „አሉታዊ“ ነገሮችን በማራቅ እና ቅንነትን በማቅረብ እንዲሁም በማስጠጋት ብቻ ነው። „አሉታዊ“ ምልከታ ብዙ ነገርን ክው አድርቆ ያደርቃል። „አሉታዊነት አሰተሳሰብ“ የመልካም ነገሮችን መራባት አጸደ ተክሎችን ሁሉ ያፈልሳል። አሉታዊ ግንዛቤ አለቅት እና መሃን ነው። ምክንያቱም ባዶን አምላኪ ስለሆነ። የአሉታዊ ወታደሮች
ውስጣቸው እሾኽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የእሾኹ ውጋቱ ዕለታዊ ህይወታቸው መሪ በመሆኑ በቁስል ዘመናቸው ይጠናቀቃል። በመዋዕለ ዕድሜ
የጸጸት ድንኳነኛም ይኮናል።
በዬትኛውም አቅጣጫ ይምጣ በደጋፊም ይሁን በተቃዋሚ „አይሆንም“ „ከእሺታ“ ጋር እኩል አክብሮት፤ እኩል ዕወቅና፤ የበዛ እና መጠነ ሰፊ ትእግስት ሊሰጠው ይገባል። ስለምን? „አይም“ „ከእሺታ“ በላይ አዳኝ ስለሆነ። በዛ ውስጥም መንገድና ህይወትም አለና። በዛ
ውስጥም ጥሩ ንፈስ አለና። ፍሬ ያለው ማዬት የተመስጦው ዓይነት ንጥር ወርቅ ማለት የጥቂቱ ጥልቃዊ የማስተዋል ልቅና ነው። በጅምላ
ከመነዳት ማስተዋልን በውስጥ ዳኛ ከማድረግ የሚመነጭ ስለሆነ የጥቂቶች „አይ“ ጠቃሚ ፍልስፍና ነው። ትውልድም ነው። የኑሮ ፈላስፎች
እኮ ህዝብ አይደሉም። ከህዝብ የተገኙ „የማዬት“ ጥቂት አርበኞች እንጂ።
የጠራ - የተበጠረ - የታሸ - የበሰለ ግንዛቤ ውጤት ነው የጥቂቶች „አይ“።
ስለመልካም ነገር „አይ No“ የሚሉ ሰዎች ከገሃዱ ዓለም ራቅ ያሉ፤ በመንፈሳዊ ህይወት የከተሙ በውሳጣቸው የበቀሉ፤ ትውስትን ወይንም
ውራጅነትን የተጸዬፉ የትውልድ ቋሚ አጸደ ተክሎች ናቸው፤ ስለምን? ሙያዊ ማዬቱ የፈጠረላቸው ድፍረት የማግስትን ጉዞ ስለሚያሳያቸው
ከተለመደው የመደዳ ኑሮ ግብግብ ወጥተው „ሃላፊነት“ ስለመፈጠሩ የአዎንታዊ ወታደር መሆን መቻላቸው በራሱ አቅም ይፈጥርላቸዋል።
„ሰው“ መሆናቸውን ያውጅላቸዋል። „ሰው“ ሆኖ መቆም የመጀመሪያው የሰውነት መለኪያ ነው። „የአይ“ አቅሙ ትርፉን „ማዬትን“ በሚናፍቁ መንፈሶች ሁሉ ቤተኛ የመሆን
ዕድላቸውን ሰፊ ያደርግላቸዋል። መቼም ከዬትኛውም የዲታነት ሽልንገኛ የብዙሃን መንፈስ ቤተኝነት መሆን ውስጥን ይፈውሳል። ልብ የተሸለመ
ትውልድ - ማግሥት ነው። ከልብ የራቀ ከሆነ ግን በመፈጠር ግን ባለመፈጠሩ ውስጥ የሚኖር ዕብን ነው።
„በአይ“ ውስጥ „የጥልቅነት ማዬት“ ከተገኘ፤ በመዬት ውስጥ የትልቅነት አትኩሮት ይኖራል። በአትኩሮት ውስጥ ራስን ማግኘት የሚቻለው ሥሩን „ማዬትን“ በመፍቀድ ይሆናል። ክህሎት ማለትም ይህ ነው - ለእኔ።
ቅሪት የሆኑ አዋኪ መንፈሶችን ሁሉ ተለቃልቀው ከተወገዱ ነፍስ በጠራ መስመር ተልዕኮዋን መወጣት ትችላለች። ይህ ንዑድ አጋጣሚ የአዲስ መንፈስ፤ የአዲስ አቅም፤ የአዲስ ሃይል ፍጹም ቤተኞች ያደርጋል። አዲስ አቅም፤ አዲስ መንፈስ፤ አዲስ ሃይል ደግሞ የቀጣይ ህይወት መድህን ነው። ቀና መንገድ ካሰቡት የሚያደርስ ሰጋር በቅሎ ነውና።
ራስን በማግኘት ውስጥ ራሰን መሆን ይገኛል ሲባልም ለመሆን መፍቀድን በማዬት ውስጥ ተደላድሎ ሥፍራ አግኝቷል ማለት ነው። „አይሆንምን“ ስትቀበሉት ከውስጥ ከሆነ የውስጥ ላውንደሪ ቤት ከፍታችኋዋል ማለት ነው። ይህ ማለት „አይሆንም“ ንጽህናችሁን እንዲጠብቅ ፈቅዳችሁለታል ማለት ነው። „አይ“ ያጸደል። መንፈስንም ህሊናንም።
ንጽህናን መፍቀድ ማለት ደግሞ ቆሻሻ የሆነውን፤ ካልተገባው ቦታ የተቀመጠውን ስርክራኪ ሁሉ ታጸዱበታላችሁ ማለት ነው። መጽዳት በመንፈስ የውስጥ ቋሚና ዘላቂ የሰላም ዘበኛ ነው። ጠባቂም ነው። ይህ ሲሆን የጥራት ነፍሱ በረቀቀው በማዬት የሚስጢር ቅምረት ይስክናል ማለት ነው። ነገር ግን ተፈጥሯዊነት ክው ብሎ በደረቀበት ጣውላ ውስጥ ላለ ነፍስ „አይ“
የጦርነት ቀጠና ይሆናል።
አንድ ለስንብት …. ግን „አይ No“ ሲባል ደስ የሚለው ማን ይሆን፤ እኔ፤ እርሰዎ ወይንስ እኛ ሁላችን በጋራ?
ፍቅር ተፈጥሮው ከግዙፋን ነገሮች ብቻ ሳይሆን መነሻው ከቅንጣትም ነው!
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ