#የማይነጥፈው #ልሙጡ ህልመ - ግብጽ።

 

#የማይነጥፈው #ልሙጡ ህልመ - ግብጽ።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
 
 
ክብረቶቼ እንዴት አደራችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ በጣም ደህና ነኝ። አቤቶ ግብጽ የራሱ የሆነ ጸጋ እና በረከት አለው። የአባይ ጉዞ ወደ ግብጽ ሲያቀና እራሱን የቻለ እዮራዊ ሚስጢር አለው። የግብጽ ሊሂቃን በዚህ እዮራዊ ሚስጢር ውስጥ ሆነው በቅንነት እና በዲስፕሊን የእግዘአብሄርን፤ የአላህን ስጦታ በማክበር ከክፋ ሃሳብ ጋር ሊፋቱ፤ ከቅናት ጋራ ሃራም ሊባባሉ በተገባ ነበር።
 
እንደ እኔ የግብጽ ሊቃውንት ጸጋቸውን የማንበብ፤ የመተርጎም እና የማመሳጠር አቅም ቢኖራቸው ኖሮ ዘመናቸውን ሙሉ በስውር ሴራ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከሚንቀሳቀሱ የየዘመኑ የክፋ ሃሳብ ባለሟሎች ጋር ባልተባበሩ ነበር። ለግብጾች ኢትዮጵያ #እስትንፋሳቸው፤ የመኖራቸው ልሁቅ ሚስጢር ናት። ይህን ትንግርት በወጉ ዕውቅና ሰጥተው ልጆቻቸው፤ ትውልዶቻቸው ኢትዮጵያን የነፍስ አድን ህይወት መሆኗን በማስተማር፤ ስለ ኢትዮጵያ ሊጸልዩ፤ እሷን ሄዶ ለማየት ሊጓጉ በተገባ ነበር። 
 
ግብጽ እንደ አገር የመቀጠሉ ሚስጢር የአጤ አባይ የግዮን ሚስጢር ነው። የግብጽን መኖርን - ያኖረ፤ ማወቅን - ያተባ፤ ለግብፃውያን ትውልድ #ብራ የፈጠረ፤ የአገር ተስፋን ያለመለመ አጤ አባይ ነው። አጤ አባይ ልጆቹ በጨለማ እየማቀቁ፤ በምግብ እጥረት እየተሰለሰሉ ውሃ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን እዮራዊ ቅን መንፈስ ይዞ እየነጎደ ግብጽን ድሯል፤ ኩሏል፦ ለወግ ለማዕረግም አብቅቷል። አባይ ሲጓጓዝ የኢትዮጵያ ንጹህ #ቅዱስ መንፈስንም ይዞ ነው። ይህ ረቂቅ ጉዳይ ነው።
 
አጤ አባይ፤ ውሃ ብቻ እንጂ የኢትዮጵያን እዮራዊ ሁለመና ይዞ እንደሚጓዝ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናትም ሆነ፤ በግብጽ ሊቃናት አጀንዳ ሆኖ አያውቅም። የኢትዮጵያ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊሂቃን ግን ይህንን ያውቁታል፤ ያነቡታል ይተረጉሙታልም ብየ አስባለሁኝ።
ከአጤ ኃይለስላሴ መራራ ስንብት በኋላ የኢትዮጵያ #ሊሂቃን መኖራቸው ዕውቅና ተሰጥቶት አያውቅም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት። ኢትዮጵያ የተበጀችው በኢትዮጵውያን ብሩኃውያን ሊሂቃን ነበር። የኢትዮጵያ ሊሂቃን የፖለቲካ ውክልናም የላቸውም። ይህ ልሙጥነት ነው፤ ትውልድን ዘመን ከዘመን ግብር ለዛውም የሰው ግብር እንዲከፍል እያደረገው የሚገኘው።
 
#ለምን አቤቱ የግብጽ የፖለቲካ ኢሊት ኢትዮጵን ይከታተላታል? በአባይ ብቻ አይደለም። 
 
1) የአቤቶ ግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት የማይነጥፈው ልሙጡ ህልም የአባይ ውሃ ብቻ የሚመስለው ይኖራል። #እእ። የአቤቶ ግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ኢትዮጵያ በሌላው ዓለም ያላት የበቃ የተቀባይነት፤ የተፈሪነት ግርማ እና ሞገስ ተስጥኦ፤ ለግብጽ የፖለቲካ ኢሊት የእግር እሳት ነው። የሚርመጠመጡበት። ዕንቅልፍ አሳጥቶ የሚያባንናቸው።
 
2) የኢትዮጵያ የልቅና እና የልዕልና አቅም አፍሪካ አንድነት ድርጅት ጠንሳሽነት እና መሥራችም መሪ የመሆን ለግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት የሚያንገበግባቸው አመክንዮ ነው።
 
ለግብጽ ሊቃናት የኢትዮጵያ የተመድ መሥራችነቷም የህሊና ካንሰራቸው ነው። ልዕልት ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟ በታወከ ቁጥር የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት የአፍሪካ ህብረት መረጋጋት ሲሳነው ወደ ግብጽ ወይንም ወደ ሌላ አፍሪካ አገር መዛወር ይገባዋል የሚል አንገብጋቢ ስውር ኢሹ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት የሚታመሱበት ቁልፍ አመክንዮ ነው።
 
የሚያሳዝነኝ የኢትዮጵያ ገዢ የሆኑ የየዘመኑ መሪወች፤ ወይንም ገዢ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን የቆየ፤ የማይነጥፍ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ምኞታቸውን ልሙጥ ማድረግ ይችሉ ነበር። ከፋኝ የሚሉ በየዘመኑ ለሚነሱ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሃይሎች ሙሉ ነፃነት ሰጥቶ እኩል በፖለቲካው ዓውድ ይሳተፋ ዘንድ ሁነትን ማመቻቸት ይገባቸው ነበር። ከሴራ ጋር ሳይለካለኩ። ይህም ብቻ ሳይሆን በዕውቀት የተባ አቅም ያላቸውን የኢትዮጵያ ሊቃናት በተለያዬ ስበብ ከአገር እንዲሰደዱ፤ ወይንም መሬት ውስጥ እንዲያረጁ የሚደረገው ሂደትንም ማቆም ገዢወች ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባ ነበር። እንኳን ሊቃውንቱ፤ ሊቃናቱም ከእዮር የተሰጣቸው መልዕክት አብሮ እንደሚሰደድ፤ አብሮ መቃብር እንደሚላክ ለራሳቸው እራሳቸው ፈቅደው ቢመግቡ የኢትዮጵያ አቅማዊ አመራር በአንድም በሌላም ጠቃሚ ይሆን ነበር።
 
የኢትዮጵያ መላ ሊቃናት፤ የቀለም ትምህርት የተማሩት መናናቁ፤ መመቀኛኜቱን፤ መበቃቀሉን ተግ አድርገው ትውልድ እና አገርን ከጩኽት ይልቅ ከስክነት በሚገኝ የህሊና የተግባር ትምህርት ቤት ይፈውሱት ነበር። በዚህ እርምጃ ብቻ በኢትዮጵያ ጸጋ የሚንገበገቡ ሳንኮችን ሴራ መቋቋም በተቻለ ነበር። "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል። የሰው ልጅ አያስተውለውም።" ይላል አካል የሌለው የእግዚአብሄር አገልጋይ።
 
ይህን ቢያደርጉ የኢትዮጵያ የየዘመኑ ገዢወች የግብጽ የፖለቲካ ሊቃውንት #አከርካሪ አልባ ሊሆኑ በቻሉ ነበር። ምኞታቸውን፤ ህልማቸውን አመንምኖ፤ አልፈስፍሶ እንዲመክን ማድረግ ይቻል ነበር። ግን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት የቀደመው ምርቃታችን ተነስቶ፤ #ጥበብ ተሰደደ። 
 
የሚገርመኝ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት መንፈስን የጨለጡ፤ ፍላጎታቸውን የዋጡ የኢትዮጵያ የተፎካካሪ፤ የተቃዋሚ የፖለቲካ ሊቃናት በሽታቸውን ስትመረምሩት ጠረኑ የሚቀዳው ከግብጽ የቅናት፤ የምቀኝነት፤ የተቀናቃኝነት እና የበታችነት ድዌ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃውንት ጸረ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ነው። የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት #ሎጋቸው ጸረ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ጸረ የኢትዮጵያችን ሥልጣኔ፤ ጸረ የኢትዮጵያ ልቅና እና ልዕልና ነው። 
 
3) የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት የአቤቶ ግብጽ ፖለቲከኞች የህልማቸው መቋጫ ነው። አቤቱ ህወሃት ይህን አደላድሎ ፈጽሞላቸዋል። ኦነግም የዚህ ማህበር አባልነት አለበት፤ ሻብያም እንዲሁ። ግን ሻብያ ሁለት የገዘፋ ምጽዋ እና አሰብ የባህር በር እና ወደብ ኖሮት ከኢትዮጵያ ቅዱስ መንፈስ ተነጥሎ ያተረፈው #አንዳችም ነገር አልታየም። ስደት ብቻ።
 
ሌላው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስትራቴጂክ አቀማመጥ ይቀየር ዘንድ አቤቶ የግብጽ ፖለቲከኞች የተጉበት ጉዳይ ነው። ተሳክቶላቸውም። ይህ ጸጋ ኤርትራ ሲገነጠል ቀርቷል። የኤርትራ ጂኦግራፊያዊ እስትራቴጅክ አቀማመጥ በራሱ ልዩ የሆነ የሰማይ ስጦታ ነው። ይህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ሲገነጠል በባለቤትነት የያዘው የሻብያ ፖለቲካ ከመላ ዓለም ምርጥ ሊያደርገው ፈጽሞ አልቻለም። ተፈላጊነቱንም አላከለለትም። በሌላ በኩል አበረታቹ ጉዳይ የኢትዮጵያን የቅብዓ ደረጃም ፈጽሞ #አልቀነሰውም። ይህ ሚስጢር ማንም ደፍሮ ሊተረጉመው፤ ሊያመሳጥረው ቀርቶ በቁሙ ማንበብ የተቻለ አይመስለኝም። ኤርትራ ሉዓላዊ አገር ሁና ያተረፈችው የመንፈስ ፀጋ እና በረከት አደባባይ ይተርጉመው፤ ይለካውም።
 
ከዚህ ላይ በጣም የሚገርመኝ እና በማስተዋል የማስተውለው ቁምነገር በኤርትራ ሥም የሚገኙ ሚዲያወች፤ ብዙም የሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የማይታሙት የኤርትራ ፕሬዚዳንት፤ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሚዲያ ላይ ከቀረቡ በዓለም ፖለቲካ እና፤ አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያተኮረ ነው። ይህን እኔ በአወንታዊ ነው የምመለከተው። ከውስጥህ የቀረ ነገር ሲኖር ነው፤ በአንድም በሌላ ፍቅረኛ አመክንዮን በበጎም በክፋም እያነሳሳህ፤ እራስህን በራስህ እምታጽናናው። 
 
ሃራም አልያት፤ አልስማት የተባለች አገረ ኢትዮጵያ በግብጽ ብቻ ሳይሆን፤ ትናንት የእኛነት ማዕደኛ በነበረችው የኤርትራ ፖለቲከኞችም መደበኛ፤ በኽረ አጀንዳ ኢትዮጵያ ባልሆነች ነበር። አፍቅሮተ - ኤርትራ ያለባቸው ኢትዮጵያዊ ሊቃውንታትም የዚህ ሃሳብ ጽኑ ተጋሪ ናቸው። ብሎኑን ፈታታችሁ ስትመረምሩት የኢትዮጵያዊነት ሚስጢር የሁልጊዜ የልብ ትርታ ስለመሆኑ ትገነዘባላችሁ። 
 
በሌላ በኩል።ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የአፍሪካ ቁንጮ ቀንድነቷ፤ የወደብ እና የባህር በር አልባነቷ ችግር ቢፈጥርባትም የታላቅ አገርነት፤ የቀደምትነት ቅቡል የሆነው መንፈሷ ግን #የነቀነቀው አንዳችም ሁነት የለም። ረቂቅ ነው። ለእኔ ኢትዮጵያ አገር ብቻ ሳትሆን መንፈሷን እንደ አህጉር ነው የማየው። ሁልጊዜ እኔ ፈንገጥ ያለ ዕይታ ነው ያለኝና። ይህ ፍጹም ረቂቅ ጸጋዋ እና ከፍ ያለው የተፈላጊነት ደረጃዋ ቢቀናባት የሚደንቅ አይደለም። ቅናቱ በራሱ ፈጣን ህሊና፤ ብቁ አስተዳዳሪ ቢያገኝ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሸፕ የማስያዝ፤ ይዘቱን ቀጥ አድርጎ የመቅረጽ አቅም በነበረው። 
 
የሆነ ሆኖ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት በኽረ አጀንዳ፤ የካቢኔው የዕለት ተዕለት ተግባር ቅድስት አገር ኢትዮጵያን በመንፈስም፤ በሁለመናም ማጥቃት ነው።
 
በእሷ ጥቃት ግብጽ የአፍሪካ ኃያል አገር ሆኖ እንዲወጣ ማስቻል ነው። ግን ተሳካላቸውን? ወደፊትስ ይህ ልሙጥ ህልማቸው ይሳካላቸው ይሆን? ፈጽሞ አይሳካላቸውም።
 
ኢትዮጵያ *አስተዋይ፤ *በተመክሮ የዳበረ እና *የተደላደለ ሳይለንት ማጆሪቲ የሚባል ልዩ አቅም አላት። የኢትዮጵያ ሳይለንት ማጆሪቲ *ዝርግም *ዝርግፍግፍ አይደለም። *ክውን፤ *ሽክፍ ያለ፤ *የጨመተ *ቁጥብ ነው። የእናቱ ነገር አይሆንለትም። ስስቱም ሁነቱም መኖሩም ናት እቴጌ ኢትዮጵያ *ለአስተዋዩ ኢትዮጵያዊው ሳይለንት ማጆሪቲው።
 
ኢትዮጵያ ገና ከመፈጠሯ በፊት #ፈተናን #አሸንፋ የተፈጠረች አገር ስለሆነች፥ ማንኛውንም የህውከት ወጀብን እዮር ይቋቋምላታል። አቤቶ ግብጽ አምላክ የለውም እያልኩ አይደለም። ፈጣሪ አላህ #መደቡ ቅንነት ንጽህና ድንግልና እና ቅድስና መሠረቱ ስለሆነ ወደዛ ሚዛኑ ያደላል።
 
ስለሆነም እዮራዊ ጥበቃ ለኢትዮጵያ ስላልተለያት ፈተናወቿን ሁሉ በመቋቋም ልዕልናዋን፤ #ተፈላጊነቷ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ይሄዳል። ወደፊትም። የእኛ ተግባር ትውልዳችን በዕውነት፤ በመርህ እና በኦርጋኒኳ ኢትዮጵያ የውስጥ ውስጥነት እንዲሆን ተግተን፤ በብርታት፤ በሆደ ሰፊነት መትጋት ነው። ትውልዱን ቅን እና ቀና የማድረግ ተግባር፤ የንግግር አዋቂወች፤ የጸሐፍት፤ የጥበብ ሰወች የዕለት ተለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል። ይህ ተልዕኮን ለማስፈጸም የጸዳ ህሊና፤ ከቂም፤ ከበቀል፤ ከቂም የጸዳ ህሊናን በራስ ላይ መፍጠር ይገባል። አገር እና ትውልድን አሟልተው ያስረከቡን የቀደምት አበው እና እመውን ሌጋሲ ለማስቀጠል ሌላ አቋራጭ የለንም።
 
የእኔ ለ17 ዓመታት የዘለቀው የጸጋዬ ራዲዮ፤ የከበቡሽ ብሎግ፤ የከበቡሽ ዩቲውብ ቻናል፤ የሥርጉትሻ ፌስቡክ እና ቲክቶክ የተሳትፎ አቅጣጫ ይህ ብቻ ነው። ይህን በርጋታ መፈጸም ከጀመርኩ እንሆ ሙሉ ሁለት ዓመት ሆነኝ። አቅም የወንዝ ዳር አሽዋ አይደለም። ሁሉም ነገር አንጡራ አቅም ይጠይቃል። የእኔ አንጡራ አቅም ዕንቁየ ነው ለእኔ በፍጹም ልቤ እማከብረው። ዕንቁየን ማባከን አይገባም። አገር እና መንግሥት ኢትዮጵያ ኖሯት "ኢትዮጵያዊ" የሚለው ገናና መጠሪያ እንዲቀጥል እሻለሁኝ። 
 
አናርኪዝም ለአገሬ ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለአንድ ግለሰብ የትዳር ህይወትም አልመኜውም። ስለሆነም ሰብሳቢያችን፤ አሰባሳቢያችን አጤ ኢትዮጵያዊነት አሽቶ ይቀጥል ዘንድ ተግቼ ሥሰራ ኖሪያለሁኝ፤ ወደፊትም እሰራለሁኝ። የገዢውን የብልጽግና መንግሥትን ስሞግት፤ ግድፈቶቹን እንዲያርም በትህትና ስጠይቀው ኢትዮጵያ የዓለም የሰባዕዊነት ሮል ሞዴል ትሆን ዘንድ በቅንነት በማሰብ ነው።
 
ቅንነቴን ፈቅዶ ለሰጠኝ ለእዬሱስ ክርስቶስ፤ ቅንነቴን ተንከባክበው ላሳደጉት ወላጆቼ፤ የቤተክርስትያን ሊሂቃን ቤተሰቦቼ፤ እንዲሁም ሰዋዊነት ማዕከሉ የሆነው ያሳደገኘኜ የጎንደር ህዝብንም በማክበር አመሰግናለሁኝ። ለሰከንድ ቅናት፤ ለሰከንድ ምቀኝነት፤ ለሰከንድ በቀል ፈጽሞ እኔን መርቶኝ አያውቅም። ከእኔ በላይ ስለ ሊቃውንት ሰብዕና በበዛ ቅንነቴ የገነባ አንዳችም ጸሐፍት አይቼ አላውቅም። ምርቃቴሜ የተፈጠርኩበት ሚስጢርም ይኽው ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በቅንነት ዘለግ አድርጎ ለመመስከር ደፋር የለም። ሁሉም ፈሪ ነው። 
 
ወደ ቀደመው የመነሻ ሃሳቤ ስመለስ የኢትዮጵያ #ኦርጋኒካዊ ተፈጥሯዋ ሰው ሰራሽ ችግሮችን የመቋቋም አቅሟ ምንጩ #ምርቃቷ ነው። መሪወቿ፤ እንዲሁም ለወደፊት እራሳቸውን ለመሪነት ያጩትም ይህ ሚስጢር ገና አልተገለጠላቸውም። እሷን የከዳ፤ #የካደ መንፈስ ሁሉ መጨረሻው ፈጽሞ አያምርም። እንደባከነ ክትመት ይሆናል።
 
4) ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ራሷን መቻል ለግብጽ ፖለቲከኞች እና እነሱ ላፈሏቸው ችግኞች *ካንሰራቸው ነው። *ምንም አድርጎ ወደ መቃብር የሚልካቸው። በዚህ ዘርፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚደክም እስትራታጂ በነደፋ ቁጥር የግብጽ የፖለቲካ ኢሊትን አጀንዳ እያስፈጸሙ ስለመሆኑ አይገባቸውም። 
 
የኢትዮጵያ *መንግሥት ይሁን፥ *ከፋኝ የሚሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች #ጦርነትን፤ ህውከትን፤ ሽብርን፤ ስጋትን ባጩ ቁጥር ጨዋታው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድቀት፤ የሥልጣኔ መታመም እና መጎሳቆል፤ የትውልድ የሳይንስ እና ምርምር ፍልስፍናዊ ሂደት መስተጓጎል፤ የትምህርት ሂደቱ ማጎፈር ስለመሆኑ በማስተዋል አይመረምሩትም። 
 
ከግብጽ ሥር የተኮለኮለ ማንኛውም ተቋም፤ ማንኛውም ሰብዕና የማግሥት ራዕይ የሌለው #አልቦሽ ነው። የአቤቱ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናትን ፍላጎት ያዘለ ማንኛውም አካል እየሠራ፤ እየተገበረ ያለው ኢትዮጵያኒዝምን የሚያልቅ ሳይሆን የሚቀብር፤ የሚነቅል፤ ባድማ እንዲሆን ነው። እራስን በራስ ማጥፋት ማለትም ይኽው ነው። 
 
5) የኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛት ለግብጽ የፖለቲካ ኢሊት *አልዛይመር ነው። የሚገርመው በነፃነት ተወልዶ ያደገ ኢትዮጵያዊ ቅኝ ተገዥነት ሲናፍቀው ማየት የእርግማን ነው።
 
ለምሳሌ የኢትዮጵያ የፊደል ገበታ እያለ ትውስትን በቋሚነት መጠቀም። ለነገሩ የግብጽ ኢሊትን ባይረስ የተሸከመ ሁሉ ድዌውን የወረሰው ከቀናተኛው እና በቀለኛው ከግብጽ የፖለቲካ ኢሊት ስለሆነ መዳኛ የለውም። 
 
በዚህ እንኩቶ መንፈስ ውስጥ ለሚዋዥቅ ማንኛውም አካል ወይንም ተቋም አቅም ማዋጣት ክው ብሎ ቃ ማለት እና ***መድረቅ ነው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊት አማራጭ አጥተው ከኢትዮጵያ ሁነኛ ጠላቶች ጋር ሊተባበሩ ለሚፈቅዱትም መፍትሄ አለው።
አጀንዳውን ሽባ የማድረግ ፖሊሲ የትናንቱ ኢሠፓ፤ የዛሬው ገዢው ብልጽግና ቅንነትን ቅደመኝ ቢባል መፍትሄው መዳፍ ላይ ይሆናል። ቅንነት አይከፈልበትም። ቅንነት የቀና ብሩህ ጎዳና ጠራጊ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን አብነቱ በአወንታዊነት የላቀው የትውልድ አዲስ ቀረፃ ነውም።
 
ቅንነት መለኪያ የለውም። ቅንነት አይመተርም፤ ቅንነት አይሰፈርም። መጠኑንም፤ ክብደቱንም መለካት አይቻልም - የቅንነት። ቅንነት ቀና ሃሳብን የመቀበል፤ ትሁታዊ፤ አወንታዊ ሥነ - ምግባር ነው። የህሊና ልዕልና ልቅናም ነው - ቅንነት።
 
#የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ህመማቸው …… 
 
1) የኢትዮጵያ ተፈሪነት፤
2) የኢትዮጵያን ብቁ ግሎባል ተቀባይነት፤
3) የኢትዮጵያን ጽኑ የአፍሪካ አንከርነት ያማቸዋል።
 
የግብጽ ሊቃናት ትናንት የነበሩ ብልሃናት የኢትዮጵያ አቨው እና እመው በዊዝደም የፈቱት፤ ዛሬም መንፈሳቸው እንዲቀጥል የሚያግዘው ብልህነት ምራኝ ቢባል የግብጽ የፖለቲካ ኢሊት ቋሚ ህልም ማምከን ይቻላል። የግብጽ ፖለቲካንም ቁሞ ቀር ማድረግ በተቻለ ነበር። የውስጥን ችግር አዳምጦ፤ ዕውቅና ከልብ ሰጥቶ፤ በማስተዋል ምቹ ድልዳል እንዲያገኝ ቢደረግ ማን እንደኛ ጌታ።
 
ከአጠራር ጀምሮ ይሰቀጥጣል። ማሸነፍ በመርህ እና በዕውነት አመክንዮ እንጂ አንጠልጥሎ በመጥራት፤ አንተ እና አንቺ በሚል ዘለፋ እና ሽሙጥ፤ ማቃለል እና ማጣጣል አይደለም። ይህን የሚያዘወትሩ የሚዲያ ባለቤቶች እኔ አላዳምጣቸውም። የአክብሮት ትውፊታችን እየተነቃቀለ እነሱን ቁጭ ብየ ለማድመጥ አቅምም፤ አቅልም የለኝም። የኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ቀለሙ ፈጽሞ ይህ አይደለም። 
 
ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ከሊቅ እስከ ደቂቅ እራሱን በግሪደር እያፈረሰ ሌላውን በአመክንዮ ቢሞግት እኔን ሊያሳምን ፈጽሞ አይችልም።
ስለሆነም አገር የሚያስፈልገን ከሆነ፤ ትውልድን በሞራል ማነጽን የምንደክምበት በኽረ አጀንዳችን ከሆነ ለራሳችን በቅድሚያ ላፒስ፤ ለውስጣችን ቡርሽ እንግዛለት። በቤታችን ውስጥ ያሉ ልጆች፤ አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶች ምን አረም በህሊናቸው እያበቀልን ስለመሆኑ በማስተዋል ልናስብበት ይገባል።
 
የተበከለች አንዲት ቅንጣት ነገር ከምንጠጣው ውኃ ላይ ቢጨመር የውስጥ ኦርጋን ትርምስ ይፈጥራል። መጨረሻውም ስንብት ይሆናል። ለዛውም - መራራ። ስንብቱ *የሰው ብቻ አይደለም። ስንብቱ *የመልካምነትም ብቻ አይደለም። ስንብቱ ብትን አፈር የማጣት ነው፤ እንደ ኩርድሽ ህዝብ። አገር አልባ ማንነት እኔን ሥርጉተ©ሥላሴ ሰብለ©ሕይወትን አይናፍቀኝም። 
 
ከማንኛውም ትርምስ እራሴን ያላላከኩበት ሚስጢርም ይኽው ነው። ኩርዲሽ የራዲዮ ጋዜጠኛ ባልደረባወቼ ምን ያህል እያሉ የሌሉ ስለመሆናቸው የማውቀው ሃቅ ነው። የኩርድሽ ልጆች ውስጣቸው በእጅጉ የተጎዳ ነው። ይህ ልሙጥ ዕጣ ፈንታ የእኔ እንዲሆን ፈጽሞ አልፈቅድም። ፈጽሞ። አገር የመንፈስ ገዢ ታላቅ ሰማያዊ ስጦታ ነው። የአገር ባለቤትነት ቁምነገር በብር፤ በሽልንግ የማይገዛ፤ በገብያ ህግም የማይተዳደር ነው።
 
ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊት የኢትዮጵያዊነት ኦርጋኒክ አቅምን በቅጡ ከውስጥ ተቀብሎ ለማስተዳደር የክህሎት እጥረት፤ በሌላ በኩል የመቻል፤ የመቻቻል፤ የመደማመጥ ሁነት #ስስነት ንጉሥ ዳዊት፤ ልብ አምላክ ዳዊት "የቤትህ ቅናት በላኝ" ያለውን ዶግማዊ አስተምኽሮ ከውስጥ ለማድመጥ አለመፍቀድ ትናንት ጁቡቲን፤ ኤርትራን አሳጥቷል፤ ዛሬ እቴጌ ትግራይ መንገድ ጀምራለች። ወደፊት ማን ሊከተል እንደሚችል አንድየ ያውቀዋል። 
 
የብልጽግናው መንግሥት ለድርጅቱ የሚመግበው አቅም ከኖረው፤ ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ልዕልና እና ልቅና ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊነትን ማስቀጠል ካልተቻለ የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት እና የችግኞቿ ትንሳኤ ይሆናል። 
 
የግብጽ ኢሊት በኽረ ህልም ኢትዮጵያ እንደ አገር *እንዳትቀጥል በትጋት መሥራት ነው። እኔ እንደማስበው ሰፊው የግብጽ አመታዊ በጀት የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ የሚመደብ ይመስለኛል። በሺህ የግብጽ የሚቆጠር ሚዲያወቻቸው፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በበቃ ሁኔታ የተማሩ በግሎባል ተቋማት የሚሠሩ ብቁ ኢሊቶቻቸው ሁሉ በአኃቲ ልቦና በአንድ አቅጣጫ ተዋህደው፤ የማያስማማቸውን አመክንዮ ጠብቀኝ ብለው ጎልተው፤ ከኢትዮጵያ በላይ ቁንጮ የአፍሪካ ኃያል አገርነትን፤ ገናናትን ለማግኘት ሰርክ ይተጋሉ። በአንድ ወቅት ከአንድ የግብጽ ሰደተኛ ጋር አንድ ኮርስ ጋር ተገናኜን። በፍቅር አወጋጋን።
 
በቀጣይ ምን ለመሆን ነው የምታስበው ስለው፤ "ከአገሬ ከግብጽ ህግ ተማርኩኝ። ከዚህ ሲዊዝ የሚዲያ ህግን ማስተር ማድረግ እፈልጋለሁኝ" አለኝ። ሲጀምር እራሱ ከአገሬ ከግብጽ ብሎ ነው። ትውልድ እንዲህ በብሄራዊ መንፈስ ሲታነጽ መንፈሱ የአገሩ ዘብ አደር ይሆናል። 
 
የዛ ኮርሰኛ ወዳጄ የፕሮጀክቱ መቋጠሪያ #የውሃ ፖለቲካ ስኬትን በዓለም ዓቀፍ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጎ ማውጣት እንደሆነም ገባኝ። ለብልኽ የክሯን ጫፍ መስጠት ብቻ ነው። በሌላ ጊዜ የፊደላት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር እኔ ለኢትዮጵያዊው አማርኛ ቋንቋ ተመረጥኩኝ። ለአረብኛ ቋንቋ ለፕረዘንቴሽን የተመረጠው አረብኛ አስተርጓሚ ነበር። በሻይ እረፍት ሲያወጋኝ "ሁልጊዜ የግብጽ ድምጽ ይጠራኛል" ነበር ያለው። እኛስ ነው ቁም ነገሩ። የኢትዮጵያዊነት ድምጽ ሁልጊዜ እንዲጠራን እንፈቅዳለን ወይ? 
 
እኔ በኢትዮጵያኒዝም ላይ ክሳት እንዲኖርብኝ ፈቀድኩ ካልኩኝ፤ ከላይ የጠቀስኩትን የግብጽ ሊቃናት የዘመናት ህልም እንዲሳካ አቅም በገፍ በነፃ አቀረብኩ ማለት እንደሆነ አውቃለሁኝ። ይህ ከጅላጅልነት በላይ *ቀፎነትም ነው። የአገረ ግብጽ ማዕከላዊው የፖለቲካ አውታራቸው የውሃ ፖለቲካ ነው። የእኛስ?
 
የግብጽ ሊቃናት ፋክክር ካለ ቅባቸው ሙሉ አቅማቸው በመዳከር ነው የሚያሳልፋት መዋዕለ ዕድሚያቸውን። ኢትዮጵያን አብዝተው #ይቀኑባታል። ርቁቅ መንፈስ ያላት ድንቅ አገር ናትና ኢትዮጵያ፤ ቢቀኑባት አይደንቅም። ይህን ማሳካት የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት የካቢኔ፤ የፓርላማቸው ህሊና ነው። 
 
ይህን ለመመከት ሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና መንግሥት ብልህነትን ቢሰንቅ የራሱን ተቀናቃኝ የሆነውን የተቃዋሚ የፖለቲካ አካላት፤ ተቋማትን ጥያቄ በስክነት ዕውቅና ሰጥቶ በታማኝነት ሥራ ላይ ለማዋል ፕሮጀክት ሊሠራለት ይገባ ነበር። ኢትዮጵያዊ አቅምን የማሰባሰብ፤ የማደራጀት፤ የመምራት ጉዳይን በውስጥነት ተቀብሎ መላ ቢፈልግለት፡ የግብጽ ፖለቲከኞች እና ችግኞቻቸውን ህልም ማምከን ይቻላል። በቁማቸው ክው አድርጎ ማድረቅ ይቻል ነበር። መንሹ ሥልጣን ላይ ባለው የኢትዮጵያ መንግሥት መዳፍ ላይ ነው ያለው።
1)ለኢትዮጵያ ህዝብ የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
 
2) የመፃፍ የመናገር፤ የመሞገት ነፃነት ገቢር ላይ ማዋል ይገባል።
 
3) ፌክ ኢትዮጵያዊነትን አክ ማለት። በኢትዮጵያዊነት ላይ በስውር ተፃሮ ከመቆም ይልቅ ሁላችንንም የሚበልጥ ስለመሆኑ መቀበል ይገባል። በተከታታዬ ለፕሮፖጋንዳ የማይውል ሰሚናሮች፤ ወርክሾፖች፤ ፓናል ዲስከሽኖች፤ የትምህርት ሥርዓቱ አካልነት፤ ፖስተሮች፤ በራሪ ጽሁፎች፤ መጋዚኖች በነፃነት ይተነፍሱ ዘንድ መፍቀድ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
 
4) በህዝብ መሐል የተዘራውን ጥላቻ የሚመክት ዕውነተኛ ተግባር መፈጸም። በዚህ ዙሪያ ብልጽግና በጣም *ልግመኛ ነው። መንታ ፍላጎት ነው ያለው። ትውልዱንም መንታ መንገድ ላይ ገትሮ እየተወነ ነው የሚገኜው ብልጽግና። ይህ ጉዞ ለራሱም አይበጀውም።
 ያራቁተዋል። ይህ አያዋጣም ለአንድ መንግሥታዊ ሥርዓት። ጥላቻን ከኢትዮጵያ ለመንቀል መንሹ በእጁ ነበር አቤቱ ብልጽግና። ሰባት ዓመት ቀርቶ ሰባት ሰዓትን ቴጉህ አምራች ማድረግ ይቻላል። ግን ለብልጽግና ኢትዮጵያዊነት አጀንዳው አይደለም። በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥቃት ከመፈጸም ቢታቀብ አቤቱ ብልጽግና ምንኛ ዕድለኝነት በሆነ ነበር። 
 
አረንጓዴ ቢጫ ቀለምን የሚያጎሉ ሁነቶች ፊት ተነስተዋል። የግብጽ የልቦች እነ - ማህበረ ኦነግ ኢትዮጵያዊነትን የሚጸየፋበትን ሌጋሲ ማስቀጠል የግብጽ መንግሥት ከአናቴ ላይ ቁብ ብለህ ባልስህን አስነካ እንደማለት ነው። የኢትዮጵያን ክብር፤ ልዕልና፤ ጸጋ እና በረከት አስቀጣዩ መሃንዲስ፤ ሁነኛ ካፒቴኑ #ኢትዮጵያኒዝም ብቻ እና ብቻ ነው። #ፌክነት ለድል አያበቃም። በኢትዮጵያዊነት ላይ ቅናትና ምቀኝነትትን መስጥሮ መጓዝ ዳጥ እና አጣዳፊ ምጥነት ነው። ይህ መስመር ኢትዮጵያን በሉዓላዊነት ለማስቀጠል ጥቁር ግርዶሽ - ሾተላይም ነው።
 
5) የፖለቲካ እስረኞችን "የወንጀል ክስ አለባቸው" የሚላቸው ከኖረም አቤቱ ብልጽግና እነሱን በህግ አግባብ ለይቶ መፍትሄ መስጠት ለይደር ሊቀጠር የማይገባው ጉዳይ ነው።
 
6)የፖለቲካ ሞጋቾች ሳይፈሩ፤ ሳይሸማቀቁ የግል ሕይወታቸው አደጋ ሳያጠልልበት ሃሳባቸውን በሙሉ ነፃነት እንዲሰጡ መፍቀድ ይገባል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፈና፤ የአደበት ቁልፋ ያለመሰልጠን ምልክት ነው። 
 
7) የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በሱዳን በኩል በግራ ቀኝ የተደፈረባቸውን ሁነቶች በዲፕሎማሲያዊ ጥረት መፍትሄ መስጠት ይገባል። አገርኛ ነኝ፤ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ እየተጋሁ ነኝ የሚለው ብልጽግና። ለነገሩ አንደበታቸው እርማትን የማያውቀው ዶር ለገሰ ቱሉ ከኮምኒኬሽን ተነስተው አንባሳደርነት ሲሾሙ ይህ መንግሥት ጤነኛ ነው ወይ ብያለሁኝ። የውጭ ግንኙነቴን እንዳሻህ አዋዥቀው እኮ ነው ጉዳዩ። በሙያቸው በኢኮኖሚስትነት እንደ አቅማቸው እና ጸጋቸው ሊሠሩ በሚገባ ቦታ መመደብ ሲጋባ የሆነው ግን ኮሚክ ነገር ነው። ገርሞኛልም። 
 
ስምንተኛ) የእርስ በእርሱን የጦርነት ፖለቲካ ፖሊሲን ሙሉ ለሙሉ ማቆም። ሌላ ጦርነትም አለመጫር ያስፈልጋል። ምርጫን በጦርነት ባንድ አጅቦ ማጨት ዕውነትን መዳፈር ነው። 
 
9) ኢትዮጵያዊ ጠረንን አለመቀናቀን ቁልፋ ቁምነገር ይመስለኛል። ነውም! 
 
10) ለጥቃት ከተጋለጠው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጋር ጀርባ ለጀርባ የሆነውን ዕውነት ባሊህ ማለት። ባለውለታ ናትና ቅድስቷ። የፖለቲካ ውክልናም ያስፈልጋት። 
 
11) ከተንደላቀቁ ፕሮጀክቶች ይልቅ ቅድሚያ መጠለያ ላጡ ኢትዮጵያዊ ተፈናቃዮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ በአካል ተገኝቶ ችግራቸውን በዘላቂ መፍታት፤ ወዘተ … ይህ ለአንድ መንግሥት መብቱ አይደለም ግዴታው ነው። ከስድስት ጊዜ በላይ አንድ ከቅላይ ሚኒስተር አገራዊ ፕሮጀክትን በአካል ለመከታተል የፈቀደ አንድ የዓለም የሰላም አባት፤ ሎሬት መንገድ ላይ፤ ድንኳን ውስጥ የተጠለሉ ወገኖችን በአካል ሄዶ ማየቴ፤ ማጽናናት፤ መኖራቸውን የሚያስቀጥል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል። 
 
የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 130 ሚሊዮን ደረሰ ሲባል በቁጥሩ ውስጥ እንኚህን ምንዱባን ስለሚያካትት፦ ጉዳዩን የህሊና ጉዳይ አድርጎ የተደራጀ፤ የተቀናጄ ተግባር መከወን ይገባል። በተለይ ሴት የካቢኔ አባላት ለዚህ ጉዳይ እንደሚያሳዩን የፋሽን ትዕይት እናታዊ ጸጋቸውን ለከፋቸው ወገኖቻቸው ሊያደርጉ ይገባል። ከጎርፍ ጋር የሚታገሉ ድምጽ አልባ ሴት እህቶቻችንም አሉና። ካቢኔ ውስጥ የብልጽግና ገዢነት እንዲቀጥ ከፈለጉ የብልጽግና ሴት ሊቃናት የተበተኑ መንፈሶችን የእኛ ብለው ሊቀበሉ ይገባል። ቢያንስ ዓይንን መፍቀድ። ወንዶች በተፈጥሯቸው ስልቹ ናቸው። ውስብስብ ነገር አይፈቅዱም። የቀላል እና የግልጽ ሁነት ምርኮኞች ናቸው። ሴቶች ደግሞ የእናትነት ጥልቅ ጸጋችን ለቤዙ የማስተዋል ጥሪወች ምቹ ነው። ብንጠቀምበት።
 
12) ስጋት፤ ፍርሃት፤ መሸበር የህዝብ ስንቅ ሆኗል። ሥርዓትአልበኝነትም። ይህን ማስቆም ይገባል። ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ መገናኘት የማይችሉ ስደተኛ ዜጎቹን ነፃነት አለመንፈግ በእጅጉ የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው። ለእኛ እኮ ስደቱ የሙሉ ዕድሚያችን የሱባኤ ጊዜ ነው። ቢያንስ በዘመነ ዲጅታል ዕድሉ ሊነፈገን አይገባም። ይህ ክስተት ባሊህ ሊባል ይገባዋል።
 
13) ስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን መኖራቸውን የሚሰልሉ፤ የውስጥ ሰላማቸውን የሚነሱ የብልጽግና ካድሬወችን ሃግ ማለት ይገባል። መኖራችን ሰቅዘው ይዘውታል።
 
14) ስደተኛ ዜጎች የሚያቀርቡትን ገንቢ ሃሳብ በሚገባ ማድመጥ ይገባል። በየደረጃው መፍትሄ ለመስጠት መትጋት ይገባል።
15) የዜጋው የመንፈስ መሸንሸን አስመልክቶ አዲስ ዕውነታዊ ጉዞ መጀመር በእጅጉ ይገባል። ፌክ ያልሆነ ጉዞ።
 
16) በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንድቅ ዓላማ ላይ ሥልጣን ላይ ያለው ብልጽግናን ጨምሮ ጥላቻውን ማስወገድ። ለምን ሰንደቃቸውን የሚያመልኩ ሳይለንት ማጆሪቲ ውስጥ የሚገኙ፤ እዩኝ እዩኝ የማይሉ ዜጎችን ፍላጎት መጫን ሳይለንት ዲስክርምኔሽን ነውና ይህንን ማቆም ይገባል።
 
ባጠቃላይ ባይተዋር ለሆነው ኢትዮጵያዊው ዜጋ ቅድሚያ ሰጥቶ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ግልጽነትን፤ ዕውነተኝነትን፤ መታመንን ድርጊት ላይ ማዋል ቢቻል አቤቶ የግብጽ የፖለቲካ ኢሊት ቆሞቀር ማድረግ ይቻላል። ዕውን የሚወዳትን፤ የሚያከብራትን አገር እየመራ መሆኑን አቤቱ ብልጽግና ካመነበት። 
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፥ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ውቦቹ የቤተ ሥርጉትሻ ቤተኞች ደህና ዋሉልኝ። በሰላም እደሩልኝም። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/08/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።