ፍቅር እና አስተዳደጓ። "ሰፊነት" በትክክል ይገልፃታል።

 

ፍቅር እና አስተዳደጓ። "ሰፊነት" በትክክል ይገልፃታል።
 
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄርም፤ አካሄዱን ያቃናለታል።" 
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
 
 
 
 
ምዕራፍ ፲፮።
 
ዕለቱን ስለ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ተያያዥ ሃሳቦችን አነሳለሁኝ። የወጀቡ ማየል ጎንደር የቆረጠ ውሳኔ ከወሰነች መልካም ስለማይሆን። ጎንደርን ነጥሎ መጓዝ ለአማራዊ ፖለቲካም አይበጅም። ለኢትዮጵያዊነትም ጠቃሚ አይደለም። የጎንደር ጽኑ መንፈስ ተገሎ የትም አይደረሰም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት ውስጥ በአብዛኞቹ ጎንደርየ ስሩዝ እንደሆነች አውቃለሁኝ። ምንም አትፈይድም ከሆነ ነገርየው አይጠቅምም። አቅም መሰብሰብ እንጂ መበተን #ብልህነት ስላልሆነ። 
 
ይህን እምናገረው ስለ ጎንደሪና ምክንያት እየተፈለገ መጨፍጨፋ ሊያባራ አልቻለምና። በቅንነት መተቸት ቢገባም፤ በበቀል ተነሳስቶ መምተር ግን የተገባ አይደለም። ለኢትዮጵያ ሆነ ለአማራ ጎንደሮች አስፈላጊ ቅመሞች ነን። ጉዞው ጣዕም እንዲኖረው ከታጨ እኛን አግልሎ ከሆነ??? #ጠብቁት
 
የአርቲስት ወ/ሮ ፍቅር አዲስ ነቃ ጥበብ ወላጅ እናቷ የለስላሳው ማሩ ቀመስ ደንቢያ ተወላጅ እንደሆኑ በልጅነት እሰማ ነበር። በአካል አላውቃቸውም። ሁለተኛዋ ለጋስ እና ደግ እናቷን ነው እኔ እማውቀው። ወላጅ አባቷ አባ ነቃጥበብ ግን #የቤተክርስትያን ዕውቀትም ያላቸው፤ ጭምት ሰው ነበሩ። በሙሉ ይሁን በከፊል በእኛ ዘመን ትርጉም ሰጪ ስላልነበረ "ከየት መጣ" የሚለው ነጣይ ቋንቋ ጠንቅቄ መናገር ባልችልም አባ ነቃጥበብ ጎጃሜ እንደሆኑ እስማ ነበር። ይህም ከቤተክርስትያን ጸጋቸው ጋር በተያያዘ ነበር አማዳምጠው። 
 
የጎንደር ሰው ብልህ ነው። ከምትጠብቁት በላይ #ቅኔ ነው። እቴጌ ጎንደር የዕውቀት ማህለቅ፤ የባህል ዓውራ የሆነችውም ከሌላ ክፍለአገር ለትምህርት፤ ለሥራ የሚመጡ ሊቃናትን፤ ሊሂቃንን እራሱ አጭቶ #ልጁን ያጋባል። ልጅ ባይኖረው የቤተ ዘመድ ልጅ ፈልጎ ያጋባል። ይህም ባይሆን ለሚያውቀው ጥሩ ባልጀራ ልጅ እራሱ ሽማግሌ ሆኖ ይድር እና ያን አዋቂና ብልህ ሰው #ጎንደርን ይሰጠዋል። ሊቁ ወይንም ሊሂቁ ሃኪም፤ የአስተዳደር ሰው፤ የቤተ - ክርስትያን ዕውቀት ሊቀስም የመጣ ሊሆን ይችላል። መጠነ ሰፊው የጎንደሮች ብልሃዊ ዕይታ ጎንደርን የጥልቅ ዕውቀታት ማህደር አድርጓታል።
 
ጎንደሬ በተመደበበት ቦታ ብቁ፤ በሰብዕናው የተስተካከለ ከሆነ ታጭቶ ይዳራል። ይወልዳል - ይከብዳል። #ጎንደሬም ይሆናል። የጎንደር ትውፊት ዓዋቂን እና ዕውቀትን አያሰድድም። ፈጽሞ። ያን አጓጊ የህሊና ብቃት የእቴጌ ጎንደር ድርጁ ማዳበሪያ ፈቅዶ እና ወዶ ያስደርገዋል። በባህሬው ለስላሳ የሆነ ሰብዕና ጎንደሬ ከገጠመውም ትውልድ እንደ ቀለም ትምህርት ጠጥቶ እንዲያድግ ያደርገዋል። ይመርቀዋልም። አሳዳጊህን ይባርከው ብሎ። 
 
ይህ ፍጹም የሆነ የአብሮነት፤ የእኛነት፤ የውስጣዊነት #አርቆ አሳቢነት እና ሐዋርያነትም ነው። ይገርመኛል ማይክ ያለው ሰው ሁሉ ጎንደርን ሲዳፈር። መኖርን ጎንደር መንፈሱ የሚያሰለጥንበት እና የሚጠበብት ሁነት ልቅና በልዕልና ነው። ጎንደር መጣችሁብን ሳይሆን #ኦርጋኒካዊ መጣችሁልን ነው ይተባህሉ። 
 
አሁን ከሆነ የማያቸው ጉልህ ግድፈቶች አሉ። ያ ለሺ ዘመናት ጎንደር ድንቅነቷን ያስቀጠለችበትን ሥነ - ምግባሮች የሚጫን ነው። በጎሼ የፖለቲካ ዕሳቤ ለጥምቀት በዓል ለማክበር የመጣን መንፈስ መመለስ አንዲት ቅንጣት ስለጎንደር አስቦ ከማያውቅ ሰብዕና ፈልቆ ለስኬት መብቃቱ በጥሞና ለምንኖር የእቴጌ ጎንደር ልጆች ከውስጣችን ያሳዝነናል። የእቴጌ ጎንደርን በቁሙ የጸደቀ ትውፊትን፤ ባህል እና ወግን ጸንቶ ለማይዘልቅ #ጤዛ የፖለቲካ ፍላጎት ማዋል ርግማን ነው። ልዕልት ጎንደር በጀንበር ለብለብ ብላ የተበጀች በአት አይደለችም። 
 
የሆነ ሆኖ ዛሬም ቢሆን ዓራት ዓይናማ ሰብዕና ስናይ፤ ስናገኝ ትውፊታችን ሆኖ አጭተን እናጋባለን። ለዚህም ነው ጎንደር ላይ አዲስ ሰው ሲመጣ ከየት ነህ? ኃይማኖትህ ምንድን ነው? ተብሎ ተጠይቆ የማያውቀው። ጎንደር ላይ አዲስ ገብ ሆኖ አያውቅም። አቀባበሉ ድባቡ ለማዳነትን ያጎናጽፋል። ቀደምቶቹ አቨው እና እመው ጎንደሬወች አጤ በካፋን፤ እና ክብርት እናታቸውን እቴጌ ማርያማዊትን ጎጃም ድረስ ሄደው የአባታቸውን ዙፋን እንዲወርሱ ጠይቆ፤ አምጥቶ #አንግሶ የነበረው። ጎንደርን አትዳፈሩ።
 
የእቴጌ ምንትዋብ በኋላም የንግሥት ምንትዋብ ታሪክ የሚቀዳው ከዚህ ነው። ልዕልቷ ጎንደርዬ በሰውሰራሽ ኩርኩድ ወጪት የተቀረጸች የታጠረች አይደለችም። መጠኗም ይዘቷም ዲካየለሽ ናት። ጎንደር በብዙ አገራዊ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሊቃናት እንደምትገለል በየዘመኑ አስተውላለሁኝ። ምኞቱ ቋት አይገፋም። ዝምታችን እጅግ #አስፈሪ ነው። ስኬታችንም በምርቃት የተዋበ ነው። ድንገተኛ ስኬቶች የእነሱ የክንውን ዓውደምህረቶች ናቸው። ስለምን? ቂም - በቀልን፤ ምቀኝነት እና ጥላቻን እንድንጸየፍ አድርገው ወላጆቻችን በፈርኃ እግዚአብሄር እና በፈርኃ አላህ ስለሚያሳድጉን። ፍቅርም ከዚህ ውጭ አይደለችም። አደባባይ ሚዲያ ልጅ ተክሌ ያነሳው ነጥብ ነበር።
 
ምንም እንኳን ልጅ ተክሌ ነገረ ጎንደር ግጥሙ ባይሆንም። እኛ አክብረን ዕይታውን እናዳምጣለን። ካነሳው ዘንድ የፍቅር አስተዳደጓ ፍልሰቲት ከረጢት አንገታችን ተደርጎልን፤ መክለፍት ተደርጎበት ፍልሰቲትን ቁመን አስቀድሰን፤ ቆርበን ሱባኤውን ስናጠናቅ፤ ስቅለትን አብረን ሆሆ ምሻምሾ ብለን፤ ደብረብርሃን ሥላሴ ሂደን ለወላጅ፤ ለአክስቶቻችን፤ ለጎረቤቶቻችን የተሰጠውን የስግደት ጥብጠባ እኛ ተቀብለን ስግደን፤ ብርሃነ ትንሳኤን፤ ብርሃነ ልደት አብረን አይተን አብረን አድገናል። ፍቅር እንደ ሥሟ ፍቅር ናት በልጅነት ጥዑም ጊዜያችንም። ተኮራርፈንም አናውቅ። ንጥር ያለች የቅድስት ተዋህዶ ልጅ ናት።
 
#የዘገዬ ሰላምታ ቅጣት ከኖረ ዝቅ ብየ እቀበላለሁኝ።
 
እንዴት አደራችሁ ማህበረ ቅንነት? ደህና ናችሁ ወይ? ሰሞኑን ሙሉ ሚዲያው በአርቲስት ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ አዲስ ሥራ ላይ ያተኮረ ነበረ። እኔ የሙዚቃ ሰው አይደለሁም። አንድ ጊዜ የራዲዮ ፕሮጋርም ከባልደረባየ ጋር እየሠራሁ ይህ ደግሞ የማን ነው ብየ እጠይቀዋለሁኝ። "የማንን ታውቂና የማን ልበልሽ" የሚል መልስ ሰጠኝ።
 
ሚዲያወቼ በተፈጥሮ የውሃ ፏፏቴ፥ የወፎች ድምጽ ነበር የሚሠሩት። በጣም በቅርብ ጊዜ ነው ባህሌን እንዳስተዋውቅ ሲያሳስቡኝ ጸጋየ ራዲዮ እና ከበቡሽ ሚዲያ ላይ ኢትዮጵያዊውን ባቲ፤ ትዝታ፤ አንቺሆዬ፤ አንባሰልን ቤተኛ ያደረኳቸው። የፍቅርንም፤ የአርቲስት አሰፋንም አሁን ወጣቶች ሲወዳደሩበት ነው እያዳመጥኩ ያለሁት።
 
የሆነ ሆኖ አደባባይ ሚዲያን ጨምሮ የአብዛኞቹን በጸጥታ ሆኜ ሙግቶችን ተከታትያለሁኝ። የምረቃ ሥርዓቱ የድምጽ ጥራት ስለነበረበት ጀምሬ ነው ያቋረጥኩት። ሚዲያ የድምጽ ጥራት ከጎደለው አላዳምጥም። መግቢያው ላይ አንድ የፍቅር የሙያዋ አጋር ሲናገሩ "#ሰፊ ናት" ሲሉ አዳምጫለሁኝ። ይገልፃታል። ልኳም ነው። 
 
ልጅ እያለንም ታዳጊ ወጣትነት ላይ ስንደርስ፤ ወጣት ሆነንም፤ በወጣትነታችን አፍላ ወቅት ዕድል በሰጠችን የሥራ መስክ ሆነንም፤ እኔ በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ሆኜ በሥርዓቶች መፈራረቅ ምክንያት አገር ውስጥ ሆኜ ባልከታተላትም፤ በዘመነ ደርግ በኮነሬል መንግሥቱ አስተዳደር በሠራዊቱ የሙዚቃ ባንድ ለሳስሩድም እሄድ ነበር፤ የሳንሱርዱ ትኩረት ፕረዘንቴሽን እና ቴክስቱ ላይ የሚያተኩር ነበር። ያንግዜም ጨዋ፤ የረጋች ዲስፕሊንድ ነበረች። 
 
በዘመነ ህወሃት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ ወቅትም ውግዘት ነበረባት፤ እሳቸው በሥጋ ሲለዩም በቀድሞ ጠቅላይ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ የሥልጣን ዘመንም፤ አሁን ደግሞ በዘመነ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ዘመን በጥሪዋ ልክ አገር ውስጥ ሆና እናት አገራችን በገጠማት ወጀብ፤ ማዕበል፤ አንዳንድ ጊዜ በግሏ በሚጋረፍ ቋያ ትችት እና ውግዘት ሳትበረግግ፤ በችግር ውስጥም ሆና ፍቅር በሆደ "ሰፊነት" የእናት ኢትዮጵያን ጠረን ተመግባ፤ የጥሪዋ ቋት ሳይተጓጎል // ሳይጓጉልም አስቀጥለዋለች። ይህ መቼም ከመታደል በላይ የመኖር ዘይቤ ስኩን #ፍልስፍናም ነው። ዕድል መርጧትም በትዳሯም ውስጧን የተቀበለ ታላቅ የጥበብ የትዳር አጋር ሰጥቷት ስኬቷ ቀጥሏል። ይህም ሌላው ፍቅር የተመረቀችበት ዓውደ ምህረት ነው።
 
የእኔ የግሌ ፍልስፍና አለኝ። መጸሐፍቶቼ ላይም ይገኛል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል ፖስተኛም ነው እላለሁኝ። ለፍቅር ያደላቸው ሦስቱንም በጥምረት ያሟሉ የምርቃት ዕድል ነው። እነኝህን እዮራዊ ጸጋወች አላፈሰሰችም። አሰበለቻቸው።
 
በፍቅር የመኖር ዘይቤ ኩርፊያ ቦታ እንደሌለው አስተውያለሁኝ። የጥበብ ሰው ከአገሩ ከወጣ ፀጋው፤ ጥሪው ጥግ ያጣል። ጨዋው፤ አስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱ ጥበብ ነው። የጥበብ ልጆቹን በኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ልክ ያከብራል፤ ይወዳል፤ ያልቃል፤ ያደምጣል፤ ሞገስም ይሆናል። ይህ የሚገኘው እንደ ፍቅር ሰፊ ልቦና የሰጣቸው ባለ ጥሪወች ሲገኙ ብቻ ነው። በተለይ ወጀቡን አገራቸው ውስጥ ሆነው የሚቀበሉ የጥበብ ሰወች ልዩ ተስጥኦ ነው። 
 
#ሙግት ያጠነክራል፤ ያጠራልም፤ 
 
ፍቅር ተሞገተች ብለው የከፋቸው ወገኖች አሉ። ለጥበብ ሥራ ሙግት፤ የሃያስያኑ ምልከታ ጥገቱ ነው። ለትችት ዝግ የሆነ ማንኛውም የጥበብ ሥራ የታቆረ ውሃ ነው የሚሆነው። የታቆረ ውሃ ሲቆይ ጠረኑ ይለወጣል። ከተፈጥሮ ይወጣል። ስሜቱም #ዳ እና #ቃ ይላል። የጥበብ ተግባር ካልተተቼ ዱካ ሆኖ ነው የሚቀረው። ስለሆነም የጥበብ ሰው የአድማጭን፤ የአንባቢን የሰላ፤ እንደ ቋያ የሚጋረፍ የእርምት ዕይታ አስመችቶ ማስተናገድ ይገባዋል። ይህ መብት ሳይሆን ግዴታችንም ነው። ለዚህም የፍቅር ሰብዕና ሙሉዑ ነው። 
 
ከዚህ ቀደም በአንድ ሥራዋ ላይ የቀረበ ሞገደኛ ሙግት ነበር፤ በጠቅላይ ሚር መለስ ዜናዊ ዘመንም ሰፊ ውግዘት እንደደረሰባት አውቃለሁኝ። በደርግ ዘመን መሥራቷንም ተወቃሽ አድርገው የሚያቀርቡ አሉ። ምን ምርጫ ነበረን በዘመኑ ለነበርን ወጣቶች በዛን ጊዜ ተሎ ሥራ ይዘን ቤተሰቦቻችን ለመርዳት። እንደ ኢህአፓ ጫካ ካልወጣን በስተቀር ከተማርን፤ ከጨረስን፤ ኮሌጅ ለመግባት የምናስቀድመው በኽረ ጉዳይ ከኖረብን የግድ ነው ዕድል የሰጠንን አጋጣሚ አስመችተን ማስቀጠል። 
 
ለምሳሌ በእኔ ሁነት አባባ ሸፈቱ በደርግ ላይ። ልጆቹን ማን ይረከብ??? ኮሌጅ፤ የረጅም ጊዜ የትምህርት ዕድል ወይንስ የትውልድ ኃላፊነት መረከብ? ለዛውም ዘመን ከዘመን ጎንደር የከፋኝ አንጋች ስለሆነች በስጋት እና በጭንቀት ነው ያደግነው። አሁንም ይህ መቀጠሉ ማህጸኔን እንደ ዱባ የሚቀረድድ ገጠመኝ ነው። ይህ አዟሪት አንድ ቦታ ላይ ሃራም ሊባል ይገባዋል ባይም ነኝ።
 
የሆነ ሆኖ እርግጥ ነው ወቃሾች መብታቸው ቢሆንም ባለሙያቸው ጥሪያቸው፤ ጉሮራቸው፤ ቅባቸው ነውና በመብታቸው ልክ መጓዛቸው የተገባ ነው። ስንቱ ይሰደድ? ስንቱስ ፖለቲከኛ ይሁን? 
 
ሌላው በዚህ ሙግት ያዬሁት ጉልህ አመክንዮ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአለን ውስጣዊ ፍቅር በቅንነት የተቀመረ ነው። "#ሰላም ለኪ" ቃሉ የግዕዝ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወድስ ብቻ ሊሆን የሚገባው ለኮንሰርት ሊሆን አይገባም ነው። እነሱ ያነሱት ነጥብም ይረዳኛል። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር ከእኛ ይበልጣል። ዝም ብየ ሳስበው አባቶቻችን ከአዕማደ ሚስጢራት ውስጥ ነገረ - ማርያምን ስለምን አላስገቡትም ብየ በጥልቀት አስባለሁኝ። ለእኛ አስተዳደግ እኔ ከቤተሰብ የወረስኩት የፍልሰታ ሱባኤ ሙሉ ቤተሰብ መሬት ላይ ጀንዴ ይነጠፍለታል።
 
ከዛ "የኦ ማርያም ዝማሬ ምህላ" ይጀመራል። ረጅም ነው። መውጣትም ሆነ መነጋገር አይፈቀድም። ስንጨርስ በተቀመጥንበት እንተኛለን። ውጭ መውጣት አይፈቀድም። እመቤታችን ቁማ ስለምታደምጥ በዛ ክብር ልክ ቤተሰቡ ተገርቶ ያድጋል። ቀን ላይ "ኦ ማርያም" አይዘመርም። ምክንያት እመቤታችን ትቆማለች እና እሷን ማስተጓጎል ነው ተብሎ ይታመናል። ይህን ያህል ጥልቅ ፍቅር፤ ጥልቅ አፍቅሮታችን ለእመቤታችን ከጸጋ ስግደት ፍቅሩ ወደ አምልኮ ስግደት እንዳይወስደን ለመጠንቀቅ ይመስለኛል አቨው አዕማደ ሚስጢራት ላይ ነገረ - ማርያምን ያላስገቡት ብየ አስባለሁኝ። ከዚህ አንፃር ለእመቤታችን ከመሳሳት የቅድስት ኦርቶዶክስ ልጆች ያነሷቸው ነጥቦች ይረዱኛል። 
 
#ግዕዝ ቋንቋ ነውን???
 
ለእኔ መልሱ አወን ነው። ግዕዝ ቋንቋ ከሆነ ለቋንቋ የሚሰጠው መብት እና ግዴታም ይኖርበታል ማለት ነው። እርግጥ ነው ላቲንም ለአውሮፓውያኑ የቤተ- እግዚአብሄር ቋንቋ ነው። የህወሃት መንግሥት ግዕዝም አማርኛ ቋንቋም አያስፈልግም ብሎ ከደቡብ እና ከአማራ ክልል ውጪ ያሉት ክልሎች ላቲንን እንዲጠቀሙ እንዳስደረገ አዳምጫለሁኝ። ኦሮምኛ በላቲን ቋንቋ ነው የሚሠራው። መኖር በኦሮምኛ በላቲን ቋንቋ የሚሰለጥን ከሆነ፤ ለዓለማዊ ተግባር የአውሮፓውያኑ የቤተክርስትያን ቋንቋ ዋለ ማለት ነው።
 
በሌላ በኩል ብልሆቹ ጀርመኖች አማርኛ ቋንቋን፤ ግዕዝ ቋንቋን፤ በሃንቩርግ፤ በበርሊን ፍሪ ዩንቨርስቲ፤ በሃይድልቨርግ ዩንቨርስቲ ይሰጣሉ ትምህርቱን። ግዕዝ ሙያ ነው። ግዕዝ ቋንቋም ነው። ሙሁራኑ አንድ ቋንቋ ሊያደርገው በሚገባው ልክ ይጠቀሙባታል። ይህን መጠነ ሰፊ ግሎባል ሁነት ልምራ ማለት ይቻል ይሆን? አቅሙስ አለን? ፈቃዱንስ ተጠቃሚወች ሊሰጡ ይችላሉን? እኛ የናቅነውን፤ ወርውረን የጣልነውን ሚስጢር ፈልፍለው የፍልስፍና፤ የምርምር ያደረጉት አገሮች እኛ እንምራችሁ ቢባሉ ይሁን ሊሉ ይችላሉን? በሆደ ሰፊነት እንመርምረው። መምህር ዘበነ ጥያቄው ተነስቶላቸው መልስ ሰጥተውበታል። 
 
#ሥነ - ግጥም እና ቋንቋ ቅኔ እና ቋንቋ።
 
ቅኔ ዝንባሌው ለግዕዝ ቋንቋ ነው። የተፈጠረበትም። ግን አማርኛ ቋንቋንም ለቅኔ ሥነ - ግጥም፤ ለቅኔ ስድ ንባብ እጠቀማለሁ እኔ በግሌ። የሆነ ሆኖ ኮርስ የወሰድኩበትን አመክንዮ ልንገራችሁ። ሥነ - ግጥም አገር ቤት ኮርስ ወስጃለሁኝ። መምህሮቼ አቶ አበበ ኬሪ እና አቶ ደረጄ ይባሉ ነበር። አቶ ደረጄ አሁን ሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር የደረሰው ነው። ይቀየራል ተብሎ የቃላቱ፤ የስንኙ፤ የፊደላቱ፤ የሐረጋት መጠን ተሰጥቶ እኔም ተወዳድሬ ነበር። ስክሪፕቱም በእጅ እንደተፃፈ አለ በእጄ።
 
ኮርሱን የወሰድኩት ለሰባት ወር ነበር። ኮርሱን የሚሰጠው የአዲስ አበባ ባህል እና ስፖርት ቢሮ ነበር። ኮርሱ ፕለይ፤ ሥነ - ጹሁፍ፤ ሥነ - ግጥም እና ፕረዘንቴሽን ነበር። የአብየ ለማ የግጥም መርኽን በእጄ ጽፌው ከእኔው ዘንድ ይገኛል። እጅግ ከባድ ነው። በደርግ ዘመን የንግግር ጥበብም ተምሬያለሁኝ ለ20 ፔሬድ ለ40 ሰዓታት።
 
ሲዊዘርላንድ ውስጥም የራዲዮ ጋዜጠኝነት ኮርስ ላይ ፕረዘንቴሽን፤ ቃለ - ምልልስ፤ የዘገባ ቅመራ ተምሬያለሁኝ። በZAU የስደተኛ መጋዝን ዝግጅት ለሦስት ዓመት ተምሬያለሁ፤ ሥነ - ግጥም ZAU መጋዚን የጀመረው በእኔ ሥራ ነበር። ስለ ራህብ ነበር የመጀመሪያ ግጥሜ። እኔ ዕድል ቀንቶኝ በተማርኩባቸው የትምህርት ክፈለ ጊዜ ውስጥ አንድ ገጣሚ በአንድ ግጥም ውስጥ #የፈለገውን ቋንቋ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳለው ነው የተማርኩት። ይህም ብቻ አይደለም። አንድ የሥነ - ግጥም ባለተስጥኦ እርዕስ አልቦሽ ግጥም መፃፍ እንደሚችልም መብት ተሰጥቶታል። የሥነ - ግጥም ጸሐፊ ሙሉ ነፃነት እንዳለው ሙሉ ኮርስ ይሰጣል። ምክንያቱም ለሦስት ወር የሚቆይ ትወና ገጣሚ በግማሽ ገጽ ሊጽፈው ይችላልና። 
 
ስለዚህም ነው ሦስቱ የዓዋቂወች የግጥም መጻህፍቶቼ ተስፋ - መክሊት እና ውል። አንዱ የልጆች የግጥም መጸሐፌ #ፊደል፤ በተጨማሪም ርግብ በር የአዋቂወች 7ኛው የምክር መጸሐፌ ሥነ - ግጥምም ስላለው ግጥሞቼ በዲዛይን የተሠሩ ናቸው። እርዕሳቸው ጠርዝ ላይ፤ መሃል ላይ፤ ወይንም ታዛ ላይ ይሆናል። ጭብጡን እኔ ጸሐፊዋ ስጠራው አቤት ከሚለኝ ላይ ዕርዕሱ አለ። የኮፒ ራይት ጉዳይ ስላለበት በዓለም የመጀመሪያ መቅድም ስለሆነም የሥነ - ግጥም ሞድ "Switzers die 193 Nation der Schweuz" ለእኔ በተፈቀደልኝ ፔጅ ላይ "ሀውልት" የሚለው ግጥሜ በጃንጥላ ቅርጽ የተሠራው ለህትምት በቅቷል። ገጽ 217 ተገቢ ደረጃ ተሰጥቶት ለግሎባሉ መጽሐፍ የተበረከተው ባለ ዲዛይን ሥነ ግጥሜ በመቅድምነት ስለ እኔ በየትኛውም ዘመን ሊመሰክር ይችላል። በዓለም ዓቀፍ መጸሐፍ ለህትምት በቅቷልና።
 
በዚህ መጸሐፍ ምድራችን የክፋት እና የክፋነት ባህሬ እየፈተናት ስለሆነም፦ የፍቅር ተፈጥሮ እንደ ሶሻል ሳይንስ እና እንደማህበራዊ ሳይንስ፤ እንደ ሃይማኖታዊ አስተምኽሮ ካሪክለም ሊነደፍለት ይገባል፤ የፍቅር ተፈጥሮ መምህራን፤ ፈላስፋ፤ ኤክስፐርት፤ ኮሌጅ ዩንቨርስቲ ሊኖረው ይገባል የሚለውን ለየት ያለ ዕይታየን ተመድን እና አውሮፓ ህብረትን የሞገትኩበት ጭብጥም በዚኽው ገጽ ይገኛል። መጸሐፋ ግሎባል ነው። 441 ገጽ አለው ኪሎው ከአራት ኪሎ በላይ ነው። ትልቅ ብሄራዊ ፕሮጀክት ነበር። የመጸሐፋ ማጠናቀቂያ ገጹ ላይ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ነው።
 
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ ገጣሚ ያልተገደበ ሙሉ ነፃነት አለው። "Yes" የሚል ዕርዕስ የሰጠ ገጣሚ ጭብጡን ቢፈልግ - በፈረንሳይኛ፤ ቢፈልግ - በአማርኛ፤ ቢፈልግ - በስፓንኛ፥ ቢፈልግ - በአረብኛ አቀላቅሎ ሁሉ መጻፍ ይችላል። እንኳንስ አገር በቀሉ ግዕዝ የግጥም ቤተኛ ሊሆን አይገባም ተብሎ ሊወገዝ ቀርቶ። የቋንቋ ዕድገት መሠረቱ ሥነ - ጹሁፍ ላይ መዋሉ ነው። በስተቀር ይጫጫል። 
 
"#ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን።"
 
ይህ የተለመደ ኢትዮጵያዊ አገላለጽ ነው። "ሰላም ለኪ" ለዚህ ቤት ሰላም ይሁን እንደ ማለት ነው። ምንም ጦር አላስመዘዘም እስከዛሬ ይህ ሥንኝ። ምንም ወጨፎ አልተወናጨፈበትም። በሌላ በኩል ልዕልት ጎንደር የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በሚሠፍሯት፦ ወስደው በሚዘፍቋት ረግረግ ውስጥ አይደለችም። መንፈሷ የነፃ እና የጸዳ ነው። ስትማገድ የኖረችበት ሚስጢር ከመላ ኢትዮጵያ ከፋኝ ያለውን ሁሉ በማህጸኗ እቅፍ ድግፍ አድርጋ ስለምትይዝ ነው። ይህ ደግነቷ ዋጋ አስከፍሏታል። አሁንም እያስከፈላት ነው። 
 
ጎንደሮች ሊመክሩበት የሚገባ ቁምነገር በየዘመኑ የከፋኝ ባዮችን እናትነቷን ማስታገስ እንደሚገባ ነው እኔ እማምነው። ሊቆቿ ከሌላው ተለይተው ሲቀጠቀጡ ውለው ያድራሉ። አሁን ደግሞ የጥበብ ህሊናዋ ላይ ያለው ወጀብ እግዚኦ ያሰኛል። ጎንደርን እባካችሁ ተዋት።
አንድም ሰው፤ አንድም ተቋም ለጎንደር ከተሰጣት ሰማያዊ ክብር ዝቅ ማድረግ አይቻለውም። ጎንደርን በመዳፈር ኢትዮጵያ የምታተርፈው ቅንጣት ሁነት የለም። ጎንደሮችም ባልሰከኑ ወዘተረፈ ሥያሜ በየጊዜው በሚሰረዙ በራሳቸው በመሥራቾች ተቋም ጎንደር ገብታ የምትዳክርበት ሁነት ሊቀይሩት ይገባል።
 
የተተረፈ ቅንጣት ነገር የለምና። ማገዶነቷን ዕውቅና መስጠት ቀርቶ ማዕቱ በበረደላት ባለድል በሆነች ነበር ጎንደርዬ የእኔ እናኑ። በፋኖ ንቅናቄ ማገዶወቹ የእሷ ሊቃናት ናቸው። ልቅም ብለው ነው ያለቁት። የህወሃት መንበረ ሥልጣኑን ፈቅዶ መልቀቁ ጎንደር ለስኬቱ ባለቤት እንጂ ጥገኛ አይደለችም። አንድም ሊቅ በህይወት የለም። ሌሎቹማ የውጭ ድርጅት ተቀጥረው የተደላደለ ኑሮ እየመሩ፤ እየተማሩ ነው የሚገኙት። ለጎንደር መገበር ግን አንድም ዕውቅና ከአንድም ተቋም ከጎኗ የሚቆም አላገኘሁም። ከተራ ሕይወት ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ተዝቆ ጎንደርን ሲዳፈሩ ሁሉ አዳምጫለሁኝ። "በማን ላይ ቁመሽ" የሆነ ነገር።
 
"የአማች በዕት" ቅጥቀጣ ሰርክ ነው። ወይ ከአማች ወይ ከተቃዋሚው ሳትሆን እቴጌ ጎንደር የሁለት አገር ስደተኛ ነው የሆነችው። የሰው ልጅ ለሚሰዋበት፤ ለሚማገድበት ሁነት ቢያንስ ዕውቅና ለማግኘት ይህን ያህል ተንበርክኮ መለመን ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ጽግሽ እንደምትለው "ብልሃት የለለው ቅላት ነው።"
 
አሁን ከፋኝ ብለው ዱር ቤቴ ያሉት ታጋዮች የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና መቋጫው ባይሳካ ጥቅልል ብለው ወደ ጎንደር በርሃ እንደሚሄዱ ልቤ ይነግረኛል። አንዲት ቀን በአንድ የፖለቲካ ሊቅ - ተመስግና የማታውቅ እቴጌ ጎንደር አይታክቴው መከራዋን አስቀጣይ እሷ እራሷ ናት። መወሰን ተስኗት። ለነገ የመንግሥት ምሥረታ ስብስቡ ውስጥ፤ የሚዲያ ተንተኙ ውስጥ አንድም የጎንደር ጠረን አይፈቀድም። 
 
ጎንደር በኢትዮጵያ ፖለቲካ በየዘመኑ ሳይለንት ዲስክርምኔሽን እና ሳይለት ኔግለሽን የሚከተክታት ጭቁን በዓት ናት። ይህን በአደብ፤ በጥሞና መርምሩት የጎንደር ሊቃናት፤ እና የጎንደር ሊሂቃን። የምትማገዱት ለማን? የምትቀቀሉት ስለማን? ምንስ ነገ አገኜ ብላችሁ እንደሆነ ገምግሙት። ቢያንስ እንደ ወንዝ አሽዋ የትም የምታዘሩትን ጉልበታም፤ ጉልህ አቅማችሁን ቆጥባችሁ ለማስተዳደር እሰቡ። ምከሩም።
 
የማከብራችሁ አገር ውስጥ የምትኖሩ የጎንደር ሊቃናት፤ የጎንደር ሊሂቃን ሁሉ በጨመተ ሁኔታ ይህን በኽረ ጉዳይ አጀንዳችሁ አድርጋችሁ ተወያዩበት። እቴጌ ጎንደር ደሟ መራራ ነው። ልጆቿንም እየተከታተሉ የሚያጠቁን ምክንያቱ ይኽው ነው። መድረክ ላይ እራሳቸውን ለመሪነት ካጩ ውስጥ ጎንደርን #የሚወክል ቀርቶ ጎንደርን በቅንነት የሚመለከት የለም። ምን አልባት ዛሬ እኔ ይህን ከፃፍኩ በኋላ አንድ ፌክ ልጥፍ በአፈላላጊ ተፈልጎ እንደ ቁሮ ከሰል፤ ወይንም እንደ ቁሮ እንጨት ይሰየም ይሆናል። 
 
በዘመነ ኢህአዴግ የተፈጠሩ የጎንደር ሊቃናት ተመጠዋል። በሽታሽቶ ከዋዜማው ጀምሮ አልቀዋል። የጎንደርን ያህል በዚህ ፰ ዓመታት ሊቃናቱን ያጣ አንድም በዕት የለም። ከጥበበኛውም፤ ከፖለቲካ ሊቃናትም፤ ከመኮነኖችም ጎንደሬ ታጭዷል። የአማች ዘመን እንዲህ በሃዘን ድባብ ሥር ወድቆ ጎንደር ባላገኘው ትርፍ ደግሞ ያላባራ ጥላቻ እና የቅጥቀጣ ናዳ ይፈስበታል። 
 
የኮሪደር ልማት ጎንደርን የቀደመ ስበቷን አሰናብቶ #ደመና ነው እንድትለብስ ነው የተደረገው። የቱሪዝም መናኽሪያ በመደዴ ትልም ሊደፈር አይገባውም ነበር። አሁንም ቢታሰብበት መልካም ነው። የፋሲል የቤተ - መንግሥቱ ጀርባ ከአጣጣሚ ሚኬኤል እስከ አደባባይ እየሱስ ያለው መንገድ፥ ከጉምሩክ እስከ ደብረብርኃን ሥላሴ ያለው መንገድ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ነው።
 
ቀዳማይ እመቤትነት ታቅዶ የሚከወን አይደለም ጎንደሮች የሚሆኑበት ሁነት። ህወሃት ሥልጣን ለቆ ቀዳማዊት እመቤት የጎንደር ልጅ ይሆናሉ ተብሎ በህልም አይታሰብም። ድንገቴ ደራሽ ጉዳይ ነው። ይህ አመክንዮ ሲመሳጠርግ #የቅብዓ ጉዳይ ነው። ይህም ሆኖ የቀድሞው ጠቅላይ ሚር የአቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ክብርት ባለቤት፤ ቀዳማዊ እመቤት በነበሩበት ጊዜ ምንም ወጀብ አልነበረም። 
 
አሁን የኢትዮ ፎረም እና የደራሽ ታጋይ ዩቱበሮቼ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀዳማዊት እመቤቷ ሆኗል። የወቅቱ ቀዳማዊት እመቤት ሰብዕናቸው ከአቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ባለቤት ጋር ተመሳሳይ ይመስለኛል። ግን በረዱ ሰርክ ይፈሳል። ለምን? ጎንደሬነት። በፖለቲካ ውስጥ እገባለሁ ቢሉ እኔ ሥርጉትሻ አልምራቸውም። እኔ እበቃቸዋለሁኝ።
 
ጎንደር ላይ የከፈቱት እንደ ፎቶ ፍሬም ተበጅቶለትሊታይ ብቻ የተፈቀደለት ለ30 ደቂቃ የቆየው ዳቦ ቤታቸው፤ ጎንደርን በሌሎች ጸረ ጎንደሬ ኃይሎች ያስቀጠቀጠው ሲያስመርቁት "ዳቦ ብሉ ተብላችኋል" ሲሉ እኔ ሞግቻቸዋለሁኝ። ይተው ፖለቲካውን አይችሉነም። የጀመሩት ግብረ ሰናይ ፕሮግራም አለ፦ በዛ ቢቀጥሉ ይሻላል ብየ ሞግቻቸዋለሁኝ። 
 
ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ ሮ ዝናሽ ታያቸው አድማጭ ናቸው በዛው ሰሞን የጅማውን ሲያስመርቁ ጥንቅቅ፥ ጠፈፍ ያለ ንግግር ነበር ያደረጉት። አክብሬያቸዋለሁም። የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪወች ለዛ አቅም እኛ በነፃ የምንመግበው አቅም ሆኖ ለሰከንድ አድምጠውን አያውቅም። ለዚህ ነው እኔ በትጋት እሠራበት የነበረውን የሰብዕና ግንባታ እርግፍ አድርጌ የተውኩት። 
 
ሌላ ጊዜ ደግሞ ክብርት ወ/ሮ ዘማሪት ዝናሽ ታያቸው በአንድ መዝሙራቸውም እግዚአብሄር አምላክን "ክንፍ እንዳለው መላዕክ" አድርገው የዘመሩትንም የዶግማ መፋለስ ስለነበረበት እኔ ብቻ ነው የሞገትኳቸው። ቤተ - ክርስትያናችን እንኳን ባሊህ አላለችውም ነበር። ከመርኽ፤ ከእውነት አንፃር ከሆነ እኛ እንደሌላው ለበዓታችን ሊቃናት ርህራሄ ፈጽሞ የለንም። በተለይ እኔ።
 
በተረፈ አወን በተረፈ የቀዳማዊቷ እመቤት እርጋታቸውን፤ ጭምትነታቸውን፤ ዝግታቸውን ሳስተውል ይህ ሰብዕና የሚበጅ ስለመሆኑም አምንበታለሁኝ። ለቦታውም - ይመጥናል። ሲክለፈለፋ አይቼ አላውቅም። የድሮዋን የህወሃትመራሹን የኢህዴግ ቀዳማዊ እመቤት የቃብቲያዋን ተወላጅ ወሮ አዜብን እኮ እንደ እኔ የሞገታቸው የለም። 
 
ጎንደሮች ባለቅኔወች ናቸውና "ሸማ በየዘርፋ ይለበሳል" ይላሉ። ግድፈት ካለ፤ የመርኽ ጥሰት ከኖረ በእኔ ቤት ምህረት የለም። ማን ይሁን ማን። የራሴን የሃሳብ ተቋም እምመራው እራሴው ነኝና። ሌላ ተለጣፊ ጥገኛ ሃሳብ ከእኔ ቤት ቦታ የለውም። ለዚህም ነው ከጎረፈው ጋር የማልጎርፈው፤ ከአጎፈረው ጋር የማላጎፍረው፤ ከዘለለው ጋርም የማልዛለለው። በራሴ መርህ እና የአሻራ ቅኝት በጸጥታ የጸና ተግባርም እምፈጽመው። 
 
#እና ከተቻለ ……
 
ከተቻለ በሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚኬኤል ሥም፤ በቅዱስ ኡራኤል እና በሌሎች ሰማዕታን ቅዱሳን ሥም ያሉ መጠጥ ቤቶች፦ መሸታ ቤቶች፤ ሥጋ ቤቶች ሥማቸውን እንዲቀይሩ ታገሉ እስቲ። ለሃይማኖቱ ቀናኢ የሆነ ይህንንም መመከት ይገባዋልና። በሌላ በኩል "ማርያማዊት" በሚል ሥያሜ የሚጠሩ የጥበብ ሰወች፤ የሚዲያ ሰወች፤ የፖለቲካ ሰወችም አሉ። ሥማቸውን እንዲቀይሩም ንቅናቄ መጀመር ነው።
 
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም "ከሴቶች የተለየች" ስለሆነች በእሷ ትክክል የሰው ልጅ ሊኖር አይችልም። ቤተሰብ ለድንግል ካለው ፍቅር አንፃር ሥሙን የድንግል ያደርገዋል። ጽዮን፤ ጽላት፤ ውጽህፍተወርቅ፤ ማሪያማዊት፤ ወዘተ የሚባሉ ሥሞች አሉ። ይህ ጉዳይ በዓዋጅ፤ በህግ በደንብ ሃይማኖታችን ባለቤት ሥላለው ቅኒት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እስካልገደበችው ድረስ ቀጣይ ይመስለኛል።
 
"ማርያማዊት " "ውጽፍተወርቅ" የሚል ሥያሜ ያላቸው ልጆች በድንግልና መንኩሰው መቀመጥ ይኖርባቸዋል ማለት ነው አሁን በተነሳው የክርክር መስመር። ውጪ አገርም ኢቫ ህይዋን በጀርመንኛ፤ ኢቪታ በአርጀንቲናም፤ አና በጀርመንኛ ሃና፤ ማርያ፤ ሜሪማ፤ ክድጃ፤ የሚባሉ ሥሞች ተወዳጅ ናቸው። ሰብዕናቸው በቅዱሳን አንስት ልክ ይሁን ተብለው ሲሞገቱ ሰምቼ አላውቅም።
#አስፈሪ ጊዜ ላይ ነው ያለነው።
 
እምሰማው በጣም ታላላቅ ሰወች ቅድስት ኦርቶዶክስን እየተው ወደ ፕሮቴስታንትነት እየጎረፋ መሆኑ ነው። በተለይ ተባዕት በባህሪው ጭንቀት አይወድም፤ ውስብስብ ነገር አይሻም፤ ረዥም ሃተታ አይፈልግም፤ ውጥረትም አይሻም። ነገሩ በከረረ ቁጥር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን የሚሸሸው የተባዕት ቁጥር ይበረክታል። በቅድስት ድንግል ማርያም ስብከት ዓራት ዓይናማ የነበረ ሰባኪ ዛሬ በቦታው እንደሌለ ስሰማ አልቅሻለሁኝ። 
 
በሌላ በኩል ቅድስታችን ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሙሉ የተደራጄ ተቋም ናት። ግድፈት ከኖረ ለእሷ አቤት ማለት ይገባል ።
በተረፈ ፍቅር " ሰፊነትሽ" ስደትን አለመምረጥሽ አዘውትሬ የምደነቅበት የበቃ ብቻ ሳይሆን የተሰጠውም አቅምሽ ነው። መሰጠትሽን እምለካው በዚህ እንደ አገር ሰፊ በሆነው ሰብዕናሽ ነውና። ተባረኪ! 
 
ቅኖቹ ወገኖቼ አገራችን ባለችበት ውስብስብ ወቅት ሆደ ሰፊነት፤ አዙሮ ማየት፤ በጥልቀት የማስተዋል፤ ከውሳኔ በፊት እርጋታን ምራኝ ማለት ለትውልድ ይጠቅማል። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። ሞጋቾችን ሆነ ተሞጋቾችም ዴሞክራሲያዊ መብታችሁን እየተጠቀማችሁ፤ ሥራ ላይ እያዋላችሁ ስለሆነ ለግራ ቀኞች ወገኖቼ የታላቅ እህት ምርቃት እንሆ። ተባረኩልኝ። አሜን።
 
ፖለቲከኞች ሆይ! ጎንደር ደክሟታል። እባካችሁ ተዋት። እባካችሁን? 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ደህና ሁኑልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/09 2025
ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥት ሲያልቅም ፍቅር ይሰደዳል።
መኖራችን ካንፓሳችን፤ ኮንፓሳችንም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?