የሰው ልጅ የጀንበር የእጅ ሥራ #ዳንቴል አይደለም። ኢትዮጵያ #የወላጆች #የጥሞና ንቅናቄ ያስፈልጋታል።

 

የሰው ልጅ የጀንበር የእጅ ሥራ #ዳንቴል አይደለም። ኢትዮጵያ #የወላጆች #የጥሞና ንቅናቄ ያስፈልጋታል።
 
"አቤቱ ንጹህ ልቦናን ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
ምዕራፍ ፲፮
 
ዛሬም የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ማገዶ ይሻል፤ ይመኛል፤ ይፈልጋል። ያ ……… ማገዶ የወይራ አይደለም። ያ ……… ማገዶ የአባሎ አይደለም። ያ ……… ማገዶ የዝግባ አይደለም። ያ ………ማገዶ የባህርዛፍ አይደለም። ያ …… ማገዶ የኩበት - የፍግ - የሸለሸል አይደለም። ያ … ማገዶ ዘጠኝ ወር በእናት #ሆድ፤ ሦስት ዓመት በእናት ትክሻ በታላቅ እህት ጀርባ፤ በእሚታ፦ በአክስት እቅፍ፤ ሰባት ዓመታት በቤተሰብ፤ በቤተዘመድ፤ በእኛ ባህል እና በወጋችን #በጎረቤት ልዩ ጥበቃ እና እንክብካቤ ያደጋል። ከዚህም በኋላ መምህራን እና በቅርብም በሩቅም ያሉ ወገኖቻችን ይሳተፋበታል። ሙሉ አቅም ይፈሳል። ረቂቅ ነው። የሃይማኖት አቨውም ይደክማሉ።
 
ከዛ የመኖር፤ የመማር ሁነቶች በቤተሰብ #አንጡራ ላብ እና ወዝ ይከወናል። የቻለው ኮሌጅ፤ ዩንቨርስቲ ዕድሉ ከተገኜ ተስፋን ለማግኜት በተስፋ ይተጋል፤ በመሃል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠላፊ ነው ይጠልፋል። ተስፋ ይጨነግፋል። ተድሮ፤ ተኩሎ ልጅ ወልዶ፤ ተምሮ ተመርቆ ከፍ ያለ ደረጃ የደረሰው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊት ለፖለቲካው ማገዶውን ያልዘራውን፤ ያላበቀለውን፤ ቅንጣት አቅም ያላዋጣበትን ይጠልፍ እና #አንጋቹ ያደርገዋል። እኔ ይህን ጊዜ አስትሮኖመር ነበር እምሆነው። 
 
የሚገርመው ብዙው ትዳሩን አሸሽቶ፤ እራሱም ሸሽቶ ተደላድሎ ተቀምጦ፤ ልጁን ትምህርት እያስተማረ ነው "በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለካበታል" እንደሚባለው የኢትዮጵያ እናቶችን የተስፋ ፍሬ ነጥቆ በተንቀለቀለው ቋያ የሚያርመጠምጣቸው። አንድ ጊዜ ይሁን፦ ይምሰል፦ ዘመን ከዘመን የትውልድ #አጨዳ በአዲስ ማጭድ በአዲስም ሥያሜ መናፈቅ? ወጣቶች ሆይ! እሰቡበት።
 
የአያ እከሌ ልጅ የት ነው ያለው? የአያ እንቶኔ ትዳር የት ነው ያለው??? ጨዋታው ይህ ነው። ለመሆኑ አሁን አደባባይ ላይ ያሉት ኢትዮጵያን ለመምራት ከሚናፍቁ እጩ ሊቃናት ውስጥ ግንባር ላይ ልጃቸው ይገኛልን? ከእነሱ መሃል አንድስ እንኳን ከኮሌጅ ያልተመረቀ፤ ከዩንቨርስቲ ያልወጣ ይኖራልን? ምን አልባት ዋርካው ምሬ ወዳጆ። እሱም የእኔዋን ደሴን ከተማ አውኮ አያውቅም። ብሄራዊ በዓላትን ሰላም ነስቶ አያውቅም። የአባቶቻችን ዊዝደም አይበታለሁኝ። 
 
የሆነ ሆኖ አጋሰሱ፤ አይጠረቄው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልደከመበትን ሰብል ተጠቃሚ መሆኑ ባልከፋ። ግን ያ ሰብል ባሩድ፤ ካቴና ይበላዋል። በተለይ "#ሁለገብ" ትግል የሚባል ጉድ በሌለነገር በሰላም ሰርተው በሚገቡ ነዋሪወች ላይ የየዘመኑ የኢትዮጵያ ገዢወች ላይ ጥርጣሬ ስለሚፈጥር በገፍ ትውልድ ለካቴና ይዳርጋል። ይህ መቼም አረመኔነት ነው። ቢሆን እንኳን ዝምታ ማንን ገደለ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ዝርግ ነውና አሳልፎ ያልደከመበትን አዝመራ ይሰጣል። የአብራኩ ክፋይ፤ የደሙ ቤተኛ አዬደለምና።
 
ዱር ቤቴ ያሉት ቆርጠው፤ ወስነው ስለሆነ እራሳቸውን የሚከላከሉበት ጉድብ ይኖራቸዋል፤ ሠርቶ አዳሪው ግን በጭንቀት፤ በስጋት እንዲኖር ይደረጋል። እንደወጣም ይቀራል። ይታገታል። ይሰወራል። "#ሁለገብ" ማለት በሰላማዊ ትግል እና በጦርነት ማለት ነው። የሚከብደው በሰላም መኖሩን በሚመራው ዜጋችን ላይ ላይ ነው። አሁን ደግሞ በፋኖ ሥም አማራው፤ በጫካው ኦነግ ሥም ኦሮሞው ለካቴና ይዳረጋል። ሁልጊዜ ድግግሞሽ። ሁልጊዜ የሰኔል፤ የቹቻ፤ የካቴና፤ የቶርች ናፍቆተኛነት።
 
ዕውነቱን ብነግራችሁ በግሎባል ዘመን በእናንተ አያያዝ አልነበረም፤ ህወሃት እራሱ ድምጽ ሰጥቶ መንበረ ሥልጣኑን የለቀቀው። በጦርነቱም ህወሃት መልሶ ማዕከላዊ መንግሥት መሪ የመሆን ምኞቱ ያልተሳካው በብልጽግና ጥንካሬ አልነበረም። ወደፊትም አፍቅሮተ - ህወሃትን እቅፍ ድግፍ አድርጎ ወደ ሥልጣን ለመሸጋገር መታሰቡ የማይሳካ ነገር ነው። ዊዝደም #የእግዜሩ ይለፍ ስለማይሰጠው። ለዚህም ነው በዚህ ዙሪያ አቅም ለማባከን ቅንጣት ጊዜ እኔ ለማቃጠል እማልሻው። 
 
በደርግ - ዘመን፤ በመኢሶን - ዘመን፤ በኢህአፓ - ዘመን፤ በህወሃት - ዘመን፤ በኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር - ዘመን፤ በግንቦት 7 - ዘመን፤ በኦነግ - ዘመን፤ በፋኖ - ዘመን፥ በብልጽግና - ዘመን፤ ምንግዜም ሁሉም የሰው ኃይል ማገዶ ይፈልጋሉ፤ የሰው ማገዶ። አዝርተው ያላበቀሉት፤ ተንከባክበው ያላሰበሉት። ያን የሰው ኃይል የፖለቲካ ድርጅቶቹ እንደ ሸማ አይሸምኑትም። ወይ እንደ ብርጭቆ በፋፍሪካ አያመርቱትም። ምርቱ የሚዛቀው ከእናት እና ከአባት ነው። ከወላጆች ወይንም ከአሳዳጊወች ነው።
 
ኢትዮጵያ የወላጆች እና አሳዳጊወች #የጥሞና ንቅናቄ ያስፈልጋቸዋል። ልጆቻቸው ዘመን - ከዘመን በፖለቲካው አለመርጋት ምክንያት በስደት እምንከራተትበትን፤ ልጆቻቸው ጫካ ለጫካ አሳር የምናይበት፦ ጫካውንም ስለማውቀው፤ ልጆቻቸው የባሩድ እራት የሚሆኑበትን፤ ልጆቻቸው የካቴና መከራ ተሸካሜ የምንሆንበትን ካቴናውን ቀዮዋን በርም ስለማውቃት፤ ልጆቻቸው በጭንቀት እና በስጋት የምንኖርበትን ሁነት የሚቀይር የፖለቲካ ስክነት፤ #የፖለቲካ የእርጋታ ጊዜ እንዲመጣ፤ መግባባት #በመከባበር በኢትዮጵያ እንዲሰፍን የሚያደርግ ንጹህ ልብ ፈጣሪ ለሁላችን ይሰጠን ዘንድ አምላካችን፤ አላሃችን በሱባኤ ልጠንይቀው ይገባል። እስላም ክርስትያኑ፤ የሚያምነውም የማያምነውም ይህችን የ2017 #ጳጉሜ በሱባኤ ልናሳልፍ ይገባል ባይ ነኝ። ውስጣችን አሽዋ ነው። ውስጣችን ኮረኮንች ነው። ቡርሽ ያስፈልገዋል።
 
እኔ የበሞቴ ልዕልቴ እናቴ ድምጼ እንደናፈቃት፤ ዓይኔ እንደራባት፤ እህቴ ታላቄ እትየ እንደተመኜችኝ - ሳታየኝ፤ ድምጼን ሳትሰማ መራራ ስንብት ሆነ። እንግዲያውስ እኔ ከብላቴ ሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን አሻራ ከማስቀጠል፤ ከየትኛውም ወገን ተጎዳ ከምለው ከዕንባ ጎን ከመቆውም ውጪ አይደለም ከፖለቲካ ድርጅት፤ ከሰበካ ጉባኤ አካልነት ያልፈቀድኩ በንጽህና እና በፖለቲካ #ድንግልና ነው የኖርኩት።
የሚታገሉኝም መዳፋቸው ሥር ሊያስቀምጡኝ ስላልቻሉ ብቻ ነው። እኔ ደግሞ እራሴን #አፍርሼ ዛሬ ተጠንስሶ ነገ በሚናድ ሰው ሰራሽ ካብ ጋር የምዳበል ሴት አይደለሁም። እንዲህም ጠንቃቃ ሆኜ የቤተሰቤ ሰላም በእኔ ምክንያት እንዳይታወክ ለቤተሰብ አልደውልም። እኔ ተወልጄ ባደኩበት በዕት ተከባሪ፤ ተወዳጅ የነበርኩ ወጣት ነበርኩኝ።
 
በትምህርቴ ጎበዝ ተሸላሚ ሃርድ ወርከር ነበርኩኝ። መቼም ጎንደር አይሰለቸው አንጋችነት ከፋኝ ያለውን እያስጠጋ ልጆቹን አጫጬቶ ዘለቀ። በወጣትነቴ፤ በሥራ ዓለምም #እሙሃይ እየተባልኩ ነው ያደኩት። ይህን ማህበረሰብ በህይወት ያለውን ማየት ቢቀርብኝ ደውየ ባገኝ መልካም ነበር። ግን እጠነቀቃለሁኝ። 
 
ውጭ የሚኖሩት እንኳን በነፃነት እንዲኖሩ ስልክ አልፈቅድላቸውም። እነሱ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያ ሰወች አይደሉም። ከምኑም የሌለሁ ብሆንም ሰብዕና በገዢወች ሲበደል እሞግታለሁኝ። #ጦርነትን በፍጹም ልቤ የምጸየፍ፤ ከአንድም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰብዕና ጋር የማልገናኝ - የማልደዋወል፤ ከየትኛውም ሚዲያ ጋር #ንክኪ የለለኝ የራሴን አሻራ ለማስቀጠል የምተጋ ግን ለቤተሰቦቼ፤ ለሚያውቁኝ ሁሉ የምጠነቀቅ ነኝ። 
 
ለምን? የሰው ልጅ የአንድ ጀንበር የእጅ ሥራ አይደለም እና። ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኢዴፓ በስተቀር በተለያዬ ጊዜ ጠይቀውኛል። እንኳንስ አባልነት #በደጋፊነትም ተነካክቼ አላውቅም። ምክንያቴ ልቤ አንድ ነው። ያ ንጹህ ልብ በልጅነቴ ለኢሠፓ ተሰጠ። እነሱም ያገኙኝ በትጋቴ ነበር። እኔም ፖለቲካ ነው ብየ አውቄ አልነበረም። 
 
ትምህርት ስለምወድ በዛ ነው የተጠለፍኩት። ተግባሬም #ማደራጀት ብቻ ነበር። አለቆቼ የዘመን ልዩ ስጦታወች ነበሩ። መደበኛ ሥራቸው እኔን በብቃት ማነጽ ነበረ። ፈጸመቱ። ግን ኢሠፓ መራራ ስንብት አደረገ። ከዛች ቀን ጀምሮ በድንግልናየ ቀጠልኩኝ። መልሶ ኢሠፓ ስልጣን ቢይዝ #አልቀላቀለውም። ጠንካራ ቢሆን አይወድቅም ነበርና። ወድቆ እኔንም ህይወቴን አስመሰቃቅሎ ዕድሜየ በከንቱ ከባከነ፤ በስደት ከተንከራተትኩ በኋላ መልሶ ላገኜውም፤ ላየውም፤ መንፈሱ እንዲጠጋኝም አልፈቅድም። እናቴ በእኔ ምክንያት መነኮሰች፤ በሥጋም ተለየችኝ። 
 
የእሽታ ንግሥቴ እናቴ፤ የህይወቴ #ካርኪለም እትየ ታላቅ እህቴ ድምጼን እንደ #ሳሱ አለፋ። ቤተሰባችን የተባረከ በመሆኑ ሁለት ሌሎች እናቶቼ የታላቄ እና የታናናሾቼ እናቶች አሁንም ይጠብቃሉ። ግን ለደህንነታቸው ስል ድምጼን ነፈግኳቸው። አቤቱ ብልጽግና ሆይ! እዚህ ቪንተርቱር ከተማ እና ዙሪክ ያሉ የደህንነት ሰወችህን ሃግ እባክህ በልልኝ። በመኖሪያ አፓርትመንቴ ሳይቀር ሰላሜን ነስተውታል። በቤት ስልክ አልደውልም። እሱንም ጠልፈውታል። ወንጀል ስለሆነ መክሰስ ይቻላል። ወገኔን በስደት ከስሼ ምን የውስጥ ሰላም ላገኜ። አላደረኩትም። 
 
የሆነ ሆኖ አባባ አድባሬ፤ የሰው ቅዱስ አርጅተው የልጄን ድምጽ ይላሉ። ለሰላማቸው ስል አላገኛቸውም። የእኛ አገር ፖለቲካ ማስተዋል የነሳው የተርገበገበ ቂመኛ ጨካኝ ነው። የፖለቲካ ሞጋቾች እጅግ በጣም ጠቃሚወች ናቸው። እነሱን ተቃዋሚ ይሁን ገዢ፤ ተለጣፊ ይሁን ተጠማኝ፥ ሊንከባከብ ሲገባ ለጥቃት ይራወጣል። ተቀናቃኝ ይጨምራል። የአቤቱ ግንቦት 7 ወኪሎች እስከ አሁን ያሳዱኛል። ብልጽግናወችም በአዲስ ጉልበት ያሳዱኛል። ለምን? ህሊና ቢሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳሻው ልብ ላልገጠመላቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ሁልጊዜ ሰላማቸውን ያውካል። ይህ የተገባ አይደለም።
 
ግንቦት 7 መሪው ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስተር ሆነው ከብልጽግና ጋር እየሰሩ፦ ተከታዮቻቸው በግፍ የሚያሳዱን ወገኖቻቸውን አይገስጹም። ተው እረፋ አይሉም። የግንቦት 7 ቅሪት አካል አዲስ ስብስብ ላይ ነው። በስውር ነበር የባጀው። ይህን አሳምሬ አውቃለሁኝ። መብታቸው ነው። ምን ያገባኛል እኔ።
 
ቁምነገሩ እነሱም አሁን አብረን ከፍ እና ዝቅ ለማለት ለማንፈቅድ ባተሌወች ሌላ #ወጥመድ ያዘጋጃሉ። ለእኔ አንዲት ፔና ገዝቶ ያላስተማረ፤ ለእኔ መሃያ ቆርጦ ያላስተዳደረ እኔን ለመንዳት ማን ይፈቅድለታል? እኮ ማን? እነሱ ብልጽግናን ሲያጅቡ አብሬ ማጃብ፤ ሲኮንኑት አብሬ መኮነን? አይሰቡት።
 
እኔ ሥርጉተ©ሥላሴ፤ እኔ ሰብለ©ሕይወት የራሴ ህሊና አለኝ። የራሴ መንገድ አለኝ። የራሴ ቋሚ አሻራ ከየትኛውም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት በላይ ቋሚ አሻራ በእምየ ሲዊዘርላንድ አለኝ። በዛ ውስጥ ልዕልተ - ኢትዮጵያ አለች። ህንፃው ተጠናቋል። እድሳት አያስፈልገውም። ከሁሉ በላይ እኔ አይደለም ለኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም የምታገል ሰው ነኝ። ዓለማችን፤ ኢትዮጵያችን ጦርነት በቃቸው። አኔ አንድም የኢንተርኔት ጉባኤ፤ አንድም የዙም ውይይት፤ በዚህ ተግባር የተሰማሩ ሚዲያወችን አዳምጬ አላውቅም። ሚዲያወቹ የባለሙያ ትንተና ሲያዘጋጁ ብቻ መርጬ አዳምጣለሁኝ። 
 
ትውልዱ ሞናትነስ በሆነ የፖለቲካ ግብግብ መኖሩ፥ ዕድሜው ሊዘረፍ አይገባም ባይ ነኝ። ከማን ምን ልማር ቁጭ ብየ ጊዜ ላቃጥል? ጊዜው ከኖረኝ መዝሙረ ዳዊትን ባነብ ወደ አባቶቼ ዊዝደም መንገድ ይመራኛል። ጸጋየ ራዲዮ፤ ቲክቶካ፤ ከበቡሽ ሚዲያዬ በሙሉ አቅጣጫው የመፍትሄ ጎዳናው ትውልድን በተሟላ የጥበብ ብልህነት፥ የፍቅር ተፈጥሮ እንዴት ማነጽ ይቻላል ላይ ያተኮረ ነው። ፌስቡኬ ሰብዓዊ መብትና የሃሳብ ሙግት ከገጠመኝ በዛ ዙሪያ ይሰራበታል። ከእንግዲህ ሼር የሌላ መንፈስ አላደርግም። 
 
የእኔ ንጹህ መንፈስ ብቻ በሁሉም ሚዲያዬወቼ፤ ብሎጌን ጨምሮ ይተላለፋል። ጤነኛ የምትሉት ቆይቶ ታሞ፤ ወይ ወፈፍ አድርጎት ታገኙታላችሁ። የመሰከራችሁለት፤ የተማገዳችሁለት የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የቅርስ የውርስ አውዳሚ ሆኖ በገሃድ ይወጣል። ትውልዱ ተቸገረ። መፍትሄው -------- በጠራ ጎዳና በራስ አቋም ብቻ መጽናት ነው። 
 
ኢትዮጵያ #ኦርጋኒክ ናት። ኦርጋኒክ የሆነ ትውልድ ይኖረን ዘንድ ለዛ መትጋቱ ነው የሚያዋጣው። ተቃዋሚወች ይሁኑ ብልጽግናን ጨምሮ ለትውልድ ተስፋ፤ ለአገር ክብር እና ልዕልና የሚገድፈው ነገር ከኖረ ተነቅሶ በጥንቃቄ ይሞገታሉ። የኢትዮጵያ እናቶች መሪር ሃዘን፤ መሪር ዕንባ ይቆም ዘንድ ቁጭ ብለው የኢትዮጵያ ሊቃናት፤ ሙሁራን ሊመክሩ ይገባል። 
 
ለጠፋው፤ ለተቃጠለው የትውልድ መንፈስ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ በጸጸት ጅራፍ እራሱን ሊገርፍ ይገባል። በገፍ ትውልድ የሚማገድበት ሁኔታ ሊጠና ይገባል። ኢትዮጵያ ተበድላለች በፖለቲካ ሊቃናት ልጆቿ። ልትካስ፤ ይቅርታ ልትጠየቅ ይገባል። የኢትዮጵያ እናቶች በአጸደ ነፍስ ያሉትን ጨምሮ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊት ልጆቻቸውን እየነጠቀ የእሳት እራት አድርጓቸዋልና ሁሉም ተንበርክኮ የኢትዮጵያ እናቶችን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል። የኢትዮጵያ አባቶችም ይቅርታ ሊጠየቁ ይገባል።
 
ልጅ የጀንበር የእጅ ሥራ ዳንቴል አይደለምና። ትዳርም ብዙ ፈርሷል። በኢትዮጵያ እግዚአብሄር የፈጠረው መኖር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች ምክንያት ጓጉሏል - ተስተጓጉሏል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች አሳካን የሚሉት ፋይዳ ቢኖር የኤርትራ መገንጠል፤ ኢትዮጵያ በጎሳ እና በሰፈር መሸንሸን ብቻ እና ብቻ ነው። 
 
የእነሱን ዘመን በከንቱ የሸኙት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አሁንም የሰው ልጅ መንፈስ እና አካል፤ ራዕይና ተስፋ፤ መኖር እና መተንፈስ ማገዶ ይሻሉ። የኢትዮጵያ ወላጆች #በቃችሁ ሊሏቸው ይገባል። ገዢውን ብልጽግና ይሁን ተቃዋሚውንም። ጎደሎ ሞልቷል። ብዙ አስከፊ ነገሮች በምድሪቱ ይፈጸማሉ። የጭካኔ ፋክክር አለ። ይህ #ረብ ይል ዘንድ ሁሉም ወደ ልቦናው ይመለስ። ወደ አምላኩ፤ ወደ ፈጣሪው፤ ወደ አላህ ተንበርክኮ ይጸልይ። እርግማችን - እንዲነሳ። ምርቃታችን - እንዲበረክት። 
 
ኢትዮጵያ ለሁላችሁም ትበቃለች ሥልጣን ለምትሹት ማለቴ ነው። በመጨረሻ ሥርጉተ ሥላሴ በዝምታዋ ውስጥ የአንበረከከችውን ህወሃት መፍትሄ ያመጣል የሚል ህልም ስለላት ቅንጣት አቅም አታዋጣም። የህወሃት መንበረ ሥልጣን ለምትመኙ ናፍቆተኞች እንደማይሳካ ልንገራችሁ። ቀድሞ ተቋጭቷል። መርዶ ነው። ህወሃት ተፈትኖ የወደቀ ለዛ መከረኛ ማገዶ ለትግራይ ህዝብ መሆን ያልቻለ የሥልጣን ራህብተኛ ድርጅት ነው።
 
ውዶቼ፤ ክብረቶቼ በኢትዮጵያችን ልክ ለመሆን እራሳችን እንሆን ዘንድ እንፍቀድ። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችን ነውና። የማሸነፍ፤ የመከበር፤ የስኬት ሚስጢር ኢትዮጵያዊነት!
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/08/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።