ጓድ ገዛህኝ ወርቄ እና ማስተዋለቸው ጎንደርን ዳግም ወለደ። #ህወሃታውያን ከጓድ ገዛህኝ ወርቄ ተማሩ። እባካችሁ???

 

ጓድ ገዛህኝ ወርቄ እና ማስተዋለቸው ጎንደርን ዳግም ወለደ።
#ህወሃታውያን ከጓድ ገዛህኝ ወርቄ ተማሩ። እባካችሁ???




 
በዚያ ከቆሙት ውስጥ የዐፄ ቴወድሮስን ጃንሆይ እንግዲህ መሞታችን ካልቀረ የዚህ ጦርነት ምክንያት የሆኑትን፣ እነዚህን ዬታሠሩትን፣ እንግሊዞች መጀመሪያ ገድለን፣ እኛም ሄደን እንሙት ብሎ አማከራቸው፣ ንጉሡ ግን ያገሬን ሕዝብ አንድ ለማድረግ እኔ ያጉላላሁት አንሶ ደግሞ እነዚህን ገድዬ ሕዝቤን በውጪ አገር ሕዝብ እንዲሰቃይ አላደርግም"
(ከሊቁ ብላቴ ጌታ ፀሐፊ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ ከዐፄ ቴወድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መጽሐፍ ዬተወሰደ ገጽ 38)
"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"
ዬተከበሩ የጓድ ገዛህኝ ወርቄን ፎቷቸውን ለማግኜት ብዙ ደክሜያለሁ። ላገኜው አልቻልኩም። ጓድ ገዛህኝ ወርቄ የደርግ አባል ነበሩ። የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሜቴ አባል ነበሩ። የባሌም የጎንደር ክፍለ አገርም የኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ ነበሩ።
ጎንደር መመደባቸው እንደ ልዩ መታደል ያዩት ነበር። ጎንደር የጦርነት ቀጠና ነበር። ወገራ አውራጃ፣ ስሜን አውራጃ ሁልጊዜ ጉድብ ውስጥ ነበር አዳሩ።
ወደ ጋይንት መስመርም በለሳ አርባያ መሰሉ ችግር ነበር። የጎንደር ርዕሰ መዲናነት የተመረጠው በቀደመው ጊዜ እስትራቴጂካል ጠቀሜታው ተሰልቶ ነበር።
የህወኃት የዘለቀ ህልሙ ጎንደርን መጠቅለል ነበር። ምክንያቱም መንፈሳዊውም፣ ተፈጥሯዊውም ሙሉዑ ስለሆነ።
ይህም በመሆኑ ያለው ሥርዓት አልተመቸኝም የሚለው ሁሉ የሚተመው ወደ ጎንደር ተዋጊ እና አዋጊ መልክዕ ምድራዊ ቦታ ነበር።
ከሁሉ በላይ ለምለም መሆኑ ለአማጽያኑ መኖር ምቹም ነው። ዬህዝቡ እርህርህና መለኪያ ዬለውም። ስለዚህ ጎንደር የውጥረት ማዕከል መሆኗ ተፈጥሮ ለእርግማን ይሁን ለጽድቅ የሰጣት ነው።
ወቀሳው፣ ነቀሳው፣ በረዱ፣ ከፍ ዝቅ መደረጉ፣ ዬስላቅ ማሟያ መሆን፣ የደጋፊ ጎርፍ ሲያል ዬተቀናጣው መዝለፋም ምንጩ ጎንደር ካላት ጠቀሜታ እና ህዝቡ ካለው የተፈጥሮ፣ የተመክሮ ዬስክነት አመክንዮ ሁነት ጋር የተያያዘ ነው።
በዚህ ውስጥ ይህንን አካባቢ እና ህዝብ እንዲመሩ ጓድ ገዛህኝ ሲመጡ ፈተና ዬበረከተበት፣ ውጥረት ያዬለበት፣ ጭንቀት ዬበዛበት ግን የውስጥ የሆነ ንጥረ ነገሩ ዝልቅ ስለሆነ እንደ መታደል ቆጥረውት አንድም ቀን ሳይከፋ፣ ፊታቸው እንደ በራ ማትራሰ ላይ ቢሮው ውስጥ መሬት ላይ እዬተኙ ኢትዮጵያን ከህወሃት ለማዳን ተጉ።
ሠርተው አይደክሙም። አይቀጥፋም። ተናግረው አይጠገቡም። አደባቸው፣ የንግግር እርጋታ እና የክሎት ስክነት ልዩ ማህሌት ነበር። አይክለፈለፋም። ከቤታቸው ቢሮ፣ ከቢሯቸው ቤታቸው ብቻ።
አይለያዩም፣ ከፍ ዝቅ አድርገው አይናገሩም። ምንጊዜም ፊት ለፊት ሲያገኙ ቁመው ጠይቀው፣ አበረታተው፣ ዬቤተሰብን ጤንነት ጠይቀው፣ በሥራ አጋጣሚም ግንኙነት ሲኖር አመስግነው፣ አበረታተው መሪነትን ሕይወቱን ኑረውበት ነበር።
ሁልጊዜም ከስልክ ንግግር በኋላ አመሰግንኃለሁ፣ አመሰግንሻለሁ አይቀርም። ለትጉኃን ሠራተኞች ያላቸው ስስት፣ ለንብረት ብክነት ያላቸው አትኩሮት ልዩ ፍፁም ልዩ ሰው ነበሩ። ከአባትም አባት።
ህወሃት ከጓድ ገዛህኝ ወርቄ ሊማረው የሚገባ የገዘፈ የዕውነት ጓል ስላለ ነው ዛሬ እሳቸውን የፃፍኩት። እርግጥ ነው መጸሐፍ ብጽፍላቸውም በወደድኩኝ።
እኔ ኢትዮጵያ ብሄድ፣ ቢፈቀድልኝ የጓድ ገዛህኝ ወርቄን ሐውልት ጎንደር ከተማ ማሠራት መደበኛ አጀንዳዬ በሆነ ነበር። ብትችሉ ጎንደሬወች ይህን ብታደርጉ።
ዛሬ ህወሃት ቀንቶት ጎንደርን በበቀል እንዲቀጠቅጥ ዕድሉ ይሰጠው ዘንድ ተግተው ከሚሠሩት ጋር ግብግብ ከመግጠም፣ የጎንደርን ሞት ላተረፋት ለተከበሩት ለጓድ ገዛህኝ ወርቄ ሐውልት ብታሰሩ በፀደቃችሁ።
እንደ ገናማ በፀረ ጎንደር ሚዲያ ከፍተው ቡድን በማደራጀት በጎንደር ላይ ቁዝቃዛ ጦርነት የከፈቱትን ቅስም በሰበራችሁ ነበር። ጥቃት ማውጣት ማለት ይህ ነው። ጦርነት ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ያለችው ጎንደር በተፈጥሮዋ ልክ አትገኝም ነበር። ብዙ በጣም ብዙ ነገር አትርፈውልናል።
በተለይ የ18 ቀኑ ውጊያ ጭንቅ ነበር። ምህላ ነበር። ጉም ነበር። ጨለማ ነበር። ጨጎጎት ነበር። ቀኑም ምሽቱም አይለይም ነበር። በርቀት ዬከባድ መሳሪያ ጩኽት ነበር። ጢስ ነበር። ከተማው ሁሉ ታጥቋል። ወህኒቤት የደረቅ ወንጀል እስረኛ ነበር።
ኮማንድ ፖስቱ ተለዋዋጭ ቦታ ነበረው። ወገራ፣ ስሜን አውራጃ ተለቋል። ጋይንት ደብረታቦር ሊቦ በከባድ የውጊያ ወራት ተለቋል። ጎንደር በህወሃት እና በዛሬው ግርባው ብአዴን መሥራቾች መንገድ መሪነት ቀለበት ሥር ሆነች።
አስተዋዩ፣ ጭምቱ፣ በሳሉ፣ ታታሪው፣ ትጉሁ፣ ዲስፕሊኑ፣ ከፋቲካቸው ወይንም ከካኪያቸው ውጪ ቤሳ ቤስቲ ያልነበራቸው፣ እንደ እኛ እንደ ተራው ህዝብ በቀበሌ ሥኳር በሰልፍ፣ በኪወስክ ዘይት እና ቡና ኑሯቸውን የገፋት መሪ በሕይወት እያለሁ ጎንደር ከተማ ውስጥ ውጊያ ከፍቼ ታሪካዊ ቅርሴን እና የሚ ህዝብ አላስጨፈጭፍም፣ እልቂት ውስጥ አላስገባም ብለው ለቀው ወጡ። ወደ ታች አርማጭሆ ሄዱ።
ይህ መግቢዬ ላይ የፃፍኩትን የአጤ ቴወድሮስን ጎዳና የተከተለ ብልህነት ነበር።
ይህ ፈጽሞ የማይገኝ ዕድል ነበር። ጎንደር ከተማ አንድም ሰው ሳይሞት፣ ቅርስ፣ ታሪክ ሳይወድም። ቤተሰቦቻችን ሳይጎዱ። ዬአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሳይነዱ ከእነዓይን ጥርሳቸው እንደ ተከበሩ አዲሱን የኢህአዴግ መራሽ መንግሥት ተረከበው።
መሸነፍ መስዋዕትነትን፣ ድቀትን፣ ጭንቀትን፣ ፍርኃትን መጨመር ነው። ይህን ለመቀነስ ዬሚደረግ ማንኛውም እርምጃ ለእኔ የፖለቲካ ብልህነት ነው ማሸነፍም ነው። ህዝብንም መካድ አይደለም። ፈጽሞ።
ሚዲያወች ይረሱ። ብዙ ይላሉ። ቃናውም መርገምት ነው። የሚያድን የሚፈውስ አይደለም። እልህ የሚያጋባ ነው። እልህ እራሱ ጊዜ አለው። ጀግንነትም ቀን ሲሰጥ ነው።
ህዝብን፣ ከተማን ማዳን ትልቅ የፖለቲካ ትርፍ ነው። የአሁኑ የዶር አብይ መንግሥት ኦፕሬሽን ሙሉ አደብ የገዛ ነው። ብዙ የሚዲያ ኳኳቴ፣ የመግለጫ ብልጭልጭ አላዬሁበትም።
ዬትግራይ ዋና ዋና ከተሞች ተይዘዋል። ብዙም የከፋ ዜና አልሰማሁም። ድልቂያም የለም። ብዙ ትምክህትም አላይም። የዝምታ ኦፕሬሽን ነው ያዬሁት። ይህ ለህዝብ የሰከነ ህይወት ይጠቅማል። ያረጋጋል።
እኔ ገና በልጅነት ዬጦርነት ቀጠና ውስጥ ስለአደኩኙ ገና ሲጀመር አይበጀነም ያልኩት ለዚህ ነበር።
አድጌ የጦርነት አስከፊነትን አይቸዋለሁኝ። ባይሆን መልካም ነበር። ቂም፣ በቀል፣ ጥላቻ አመድ ነው የታፈሰው። በአሜሪካ የሚሊተሪ አውሮፕላን ተጉዞ ደቡብ አፍሪካ መግባት አፈር ለሆነው ህዝብ የሚጠቅመው ነገር ዬለም።
የጠፋው ጠፎቶ ቢያንስ አሁን ስለ መቀሌ ሰላም ህወሃታውያን ይጭነቃችሁ - ይጥበባችሁ።
በዚህች ቅጽበት #ምጥ ላይ ያለች እናት ትኖራለች። ጎንደር የጋሼ እያዩ አብደላ ባለቤት የአዘዞዋ ሙሉዬ የቅድስት ሳራ አምሳያ ምጥ ላይ እያለች ያለፈችው የጎንደር ጭንቅ ቀን ነበር።
ቅርጥምጣሚ ሰውነት ህወሃታውያን ተበደሩ። እልሁ፣ ጀብዱን አኑሩት። ሥልጣን ላይ እያላችሁም 1.5 ሚሊዮን ህዝብ በዕለት ደራሽ እርዳታ ነው ዬኖረው።
ወልቃይት ጠገዴን ራያን ለምለማውያንን ጠቅልላችሁ። አሁንም ሁለት ዓመት ሙሉ በልመና እህል። ሙሉ ጥገኝነት??? በጭንቅ። #መርዶ የለሽ ጥቁር ቀን።
እንደ ሥርጉተ ሥላሴ እንደምትቀጥሉትን እገምታለሁ። ፈንጅ እያጠመዱ ማሰቃዬት። ጫካ ገብቶ ሽምቅ ውጊያ መጀመር።
በጥላቻ ጥላቻን እዬጡጡ መኖር።
ለትግራይ ትውልድ ግን አይበጀውም። ለነገሩ በህወሃት መንደር ግራጫ ዘው ብሎ አያውቅም። በ80 ዓመትም እንደ 16 ዓመት ታዳጊ ወይንም እንደ 18 ዓመት ጎረምሳ ማሰብ።
ስትነሱም፣ ስትጓዙም መናኽሪያችሁም ብክል ዕሳቤ ነው። ይህ በቲፎዞ ፖለቲካ አታስሉት። መሬት ላይ ያለውን ዕውነት ተቀበሉ። ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ጆኖሳይድ ሊጠቃ ነው ብሎ አስቦ ያውቃልን?
ታላላቆቻችሁን እንዴት እንደፈጃችሁ፣ ዛሬም የልጅ ልጆቻቸውን እንዴት እንደምትማግዱት ታውቃላችሁ። አማራ እና አፋር ክልልን እንዴት እንደተበቃላችሁ ታውቁታላችሁ። አመድ እያፈሱ ከረባት እና ገበርዲን??? ሚሊዮን ዘመን ከዘመን ቹቻ እና ሰኔል???
በቀል አገር አይሠራም።
ጥላቻ ትውልድ አያበቅልም።
ዕብለት ለነገ ቀጠሮ የለውም።
ተኝታችሁ እሰቡት። ለመቀሌ ጭንቀት ስልታዊ ሁኑ። ለቀጣዩ ትውልድም እሰቡለት። በቃችሁ። #በቃንም በሉ።
እያንዳንዱ የሰከንድ ክፍልፋይ ስጋት ያውጃል። ዛሬም መቀሌ ያለችበት ሁኔታ አስበዋለሁ። ኑሬበታለሁ እና።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
 

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30/10/2022
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።