"ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ፀፀት ዬለባትም።"

 

"ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ፀፀት ዬለባትም።"

 
(ብፁዑ አባታችን አቡነ አብርኃም ዬጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አሥኪሄጅ እና የባህርዳር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ።)
EOTC TV | "አቶ ተብሎ ማውገዝ አይቻልም ልዩ ቆይታ ከብፁዕ አቡነ አብርሃም ጋር"
ብፁዑ አባታችን የሰጡትን ዝርዝር መግለጫ EMS ዕለታዊ ዝግጅት በጥሞና ያዳምጠው ዘንድ አሳስባለሁኝ በትህትና።
ሌላ የምትችሉ ብፁዑ አቡነ አብርኃም ከእንግዲህ ጉዟቸው #በመኪና መሆን ፈፅሞ የለበትም። መልዕክቴን፤ ጭንቀቴን እባካችሁ አድርሱልኝ። ለነገም የሚቀጠር ጉዳይ አይደለም። በአንድ ገለፃቸው ላይ በመኪና እንደሚሄዱ ተረድቻለሁኝ። በቀጥታ በደንቢደሎ እንደ ታገተቱት ልጆቻችን ገብሬጉራቻ ወይንም ጎኃ ጽዮን ላይ ሊያሰውሯቸው ይችላሉ። አትጠራጠሩ። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ ስለማያከስር ከእንግዲህ በምንም ታምር ጉዟቸው በመኪና እንዳይሆን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሌሎች ብፁዓን ጳጳሳትም እንዲሁ ጉዟቸው በአውሮፕላን ሊሆን ይገባል።
"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"
"#አዲስ አበባን ስጡን፤ #ቁልቢን ስጡን" በኽረ ጥያቄ ስለመሆኑ ከብፁዑነታቸው ቃለ ምልልስ ተገንዝቤያለሁኝ። ጥያቄ አቅርበን መልስ አላገኘነም ለሚሉትም በዬግለሰቡ ዬቀረበ ዬተናጠል ጥያቄ ሲሆን ጥያቄ አቅራቢወቹ በውል አይታወቁም። ይህም ብቻ ሳይሆን ጥያቄው በወርሃ ህዳር ለብፁ ወቅዱስ ፓትርያርከ ዘኢትዮጵያ ለአባታችን ለአቡነ ማትያስ ቀርቦ፤ ከዛ ብፁዕነታቸው እንደመሩት በህግ ክፍል ተመርምሮ እንዲቀርብ መመራቱን ገልፀዋል። ከህዳር ቀጥሎ ያለው ታህሳስ ነው ይህ የክህደት ተግባር የተፈፀመው በጥር ወር ላይ ነው። ይህን ማንም አስተዳደር ላይ ዬነበረ ማንኛውም ሰው ወስኖ የህሊና ፍርድ ሊሰጥበት ይችላል። ታዕምር ከሰማይ በ30 ቀን ሊወርድ አይችልም። ፈፅሞ። ያውም ግለሰቦች በተናጠል ላቀረቡት ጥያቄ???
በኽረ ጥያቄው በኮታ ይሰጠን ቦታ ነው። ዬፓርላማ ውሎ፤ የኮሮጆ ሂደት አድርገውታል። ይህም ቢሆን ዬአጥቢያ አድባራት ብዛት፤ ዬሰንበት ትምህርት ቤት ብዛት የአገልግሎቱን መጠን ይወስነዋል እንጂ የቆዳ ስፋት ሊሆን አይችልም። ቅድስት ኦርቶዶክስ በአማንያኗ ቁጥር ልክ ነው ድልድሉን ልታደርግ ዬሚገባት።
ሌላው ያነሱን የምደባ ሥርጭትን ነው ከቋንቋ ጋር በተያያዘ። ይህም ቢሆን እንደ ብፁዑነታቸው ገለፃ በስሜን ካለው መሥፈርት ለላ ባለ ሁኔታ ዲቁናውንም፤ የመማር ዕድሉንም ቅድስቷ ብታመቻችም #ከተመረቁ በኋላ #ከአዲስ አበባ ወጥተው ወደ መነሻ ቦታቸው ለአገልግሎት ስምሪትን ለመቀበል ፈቃድ እንደሌለ አባታችን ገልፀዋል።
ይህም ጉልበታም አሳማኝ አመክንዮ ነው። ሁሉም ጥያቄወች ቀደም ሲል የቤተክርስትያኗ አገልጋይ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከሆኑት በተደራጀ ሁኔታ እንዳልቀረበ ብፁዑነታቸው ገልፀዋል። እኔ እንደማስበው በድርጅታዊ ሥራ "የብልጽግና" ሰወች ዬሌላ ዕምነት ተከታይም ሊሆኑ ይችላሉ ጥያቄውን እንዳቀረቡት በተለያዬ ሥም እንደሚሆን አስባለሁ። በአንድ መኖሪያ ቤት 200 የመኖሪያ መታወቂያ ካርድ ያወጡ 500000 ሺህ( ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በአሉታዊ ዴሞግራፊ ከሱማሌ ክልል ወደ አዲስ አበባ እና ዙሪያው ያሰፈሩ ) ናቸው። የዬቀኑ ሲሰላ ዬትዬሌሌ ነው።
የመቱ ማሰልጠኛን በሚመለከት አንድ ትልቅ ግዙፍ ፕሮጀክት በባለሙያ ተጠንቶ ነው የሚቀርበው። ሰፊ ጊዜ ተወስዶ በባለሙያ። ነገር ግን ዬቀረበው በሌጣ ወረቀት ብቻ ነው። ፕሮጀክት በዘፈቀደ አይታቀድም፤ በዘፈቀደም አይወሰንም። በአንድ ሁለት ገጽ ምኞት ብቻ ነው ዬሚሆነው። ይህም ቢሆን ይሁንታ ተሰጥቶበታል። እንዲህ ፈተና እያበራከቱ፤ ሰላም እዬነሱ አስተዳደራዊ ሥራን መከወን ይቸግራል። በዛ ላይ አቅሙ ኢኮኖሚያዊ፤ ዬሰው ኃይል ስምሪቱ። በተጨማሪም ቢሠራም ነገረ #ኦሮምያ ቃጠሎ ነው። ኢንቬስተር እንኳን በጅ ብሎ ዬሚሄድ አይኖርም። አልፎ ተርፎ አማራ ክልል አጣዬን ዘጠኝ ጊዜ አውድመዋት ዬለም። ዝዋይ፤ ሻሸመኔ፤ አርሲ ነገሌ ወዘተ ……
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምርጫን በሚመለከት ብፁዑ አባታችን አቡነ አብርኃም ሁለት ጊዜ ቀርበው አንድ ጊዜ በ4 ድምጽ፤ ሌላ ጊዜ በ12 ድምጽ አላለፋም። በሦስተኛውም አሻም ብለው ዘግይተው እንደደረሱ እና ሲመረጡም ሁለተኛ ለወጡት ስጡ ብለው ነበር። እንዲያውም እኔ በግሌ ብዙ ጳጳሳት ዬብዙ አገረ ስብከትን ደርበው ይሠራሉ። ብፁዑ አቡነ አብርኃም ግን ዬባህርዳር እና ዬአካባቢው ብቻ ናቸው። ቢፈልጉ አጥተውት አይመስለኝም። በጣም ቁጥብ ናቸው። አድምተውም የሚሠሩ፤ ዬተረጋጋም መንፈስ ያላቸው።
ሌላው ዛሬ የሚዘረዘረው ችግር ዬድምጽ ብልጫ አጣን ለሚሉት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቁልፍ ኃላፊነት ተመርጠው አገልግለዋል። ያን ጊዜ ወፋ? ዛፋ ማን ይሆን ድምጽ ዬሰጣቸው? ጥያቄው የእኔ ነው። ይህም ብቻ አይደለም ሃላፊ በነበሩበት ዘመን ዛሬ የሚደረድሩትን ችግር ስለምን ዕልባት አልሰጡትም። በእጃው ይቆረጥ በነበረበት ጊዜ? ቢያንስ ችግሩን ለማሻሻል ያደረጉት ተዋፆስ ምን ነበር? ቢሠራበት ይህ ቁልል ክስ አይፈጠርም ነበር።
ዬተወገዙትን አቅርባችሁ አልጠዬቃችሁም ለተባሉትም። እስከ መጨረሻው ደቂቃ ዬተደረገውን ጥረት ገልፀዋል። ዶር ሃጂ ሙፍትሂ፤ ዬካቶሊኩ ካርዲናል፤ ከፕሮቴስታንትም ያሉ አቨው ምን እንርዳችሁ ብለው ሲመጡም አቅጣጫው በዚህ መስመር እንደነበር ብፁዑ አቡነ አብርኃም ገልፀዋል። እኔ #ሰሃ አላገኜሁበትም በጠቅላላ ሂደቱ። እንዲያውም እንደገባኝ ቲሙ ፓርቲ መመሥረት ዓይነት ጉዞ እንደ ነበረው ነው ዬተረዳኝ።
ዬሆነ ሆኖ ቅድስቷን ውርስ ለማድረግ የተነሱት አካላት ዬተነሱበት ዓላማ #ዬእንቧይ ካብ ብላሽ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ፈጽሞ ቅንጣት ነገር የሚያሳምን አላገኜሁበትም። ችግር ዬአስተዳደር ከዚህም ከዚያም ድምፀ ሕወሃታውያንም በህብረት ያነሳሳሉ። 27 ዓመት አራጦ ገዝቶ፤ አስተዳድሮ እንደ አሻው ፈንጭቶበት ነበር እኮ።
ለዛሬ የኦነግ መንፈስ ድል አድራጊነት እና መታበይ ብፁዑ ወቅዱስ አባታችን የፈንጅ ወረዳን እዬረገጡ ጥሪያቸውን የተወጡ የነፃነት አርበኛም ሐዋርያም ናቸው። በዓለ መስቀል ጎንደር ሲከረቸም፤ ጥምቀትም ሲደበዝዝ ባህርዳር ላይ ግን መጀመሪያ እኔን ግደሉ ብለው ከማህበረ ምዕመናን ጋር በእግራቸው እዬተጓዙ አንዳችም በዓል ሳይስተጓጎል ሰማዕትነትን በቁማቸው ተቀብለዋል።
ህወሃት መራሹን ኢህአዴግም ፊት ለፊት ወጥተው በመሞገት የነፃነት ድምፃችን፤ የተስፋችን አንደበት ነበሩ። ብፁዑነታቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በባህርዳር ሲገኙም ስለ መታመን ጥያቄ አቅርበው ነበር። አሁን ላይ ሳስበው የመንፈስ ቅዱስ ፀጋቸውን ጥልቀት ተረድቸበታለሁኝ። በሌላ በኩል የማስተዋላቸውንም ልቅና። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ዬታጨቀ ቅምጥ ፍላጎት ስለነበራቸው ያን ጊዜ በሰጨኝ ብለው ነበር። ዬባህርዳሩ የህዝብ ጉባኤ ፈትኗቸው ነበር። ቅኔ ህዝብ።
በኋላም ጠቅላይ ሚር አብይ በተሳተፋበት ቅድስታችን አኃቲ ለማድረግ በነበረው የማስታረቅ ሂደት የልዑኩ አባል ሆነው ሐዋርያዊ ተግባራቸውን ተወጥተዋል። ብፁዑ አባታችን ግልጽ፤ ቀጥተኛ የዕውነትም አርበኛ፤ እና ፈርኃ እግዚአብሔር ያላቸው፤ አቅማቸው ለትውልዱ አብነት ነው። በጣም ጥንቁቅ፤ ሊቀ ትጉኃን መሆናቸውን በጥብቅ ስከታተል ቆይቻለሁኝ። እግዚአብሔር በዚህ የምፃዕት ዘመን እኒህን ብርቱ አስተዳዳሪ ለቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስለሰጠ የተመሰገነ ይሁን። አሜን።
ክብሮቼ ለማህበረ ምዕመኑ ያስተላለፋት ጥሪ አለ በጥሞና አዳምጡት። ቅድስት ኦርቶዶክስ ለማፍረስ እና ለማስረከብ ስለመሆኑም ዘመቻው በአጽህኖት ገልፀዋል። ሂደቱን በውጪ እና በአገር ውስጥ በህግ ባለሙያወች ክትትል እንደሚደረግበትም አስገንዝበዋል። በጣም ፈተና ውስጥ በግልም መባጀታቸውን ከገለፃው ተረድቻለሁኝ። በጥንካሬያቸው፤ በብርታታቸው ደግሞ ልዩ አቅም እና ከደስታ በላይ ሐሴት አግኝቻለሁኝ።
ችግርን በሚመለከት በአንድ ቀን አይተንም፤ አይበንም። አዲሱ አስተዳደር ከጀመረ ጊዜው ልጅ ነው። ለዛውም ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ጋር መሥራት #የቀራንዮ #ውሎ ነው። ውስጣቸው ቀውስ ስለሆነ ሰላም አይሰጡም። ቅድስት እናት ቤተክርስትያናችም በኽረ አጀንዳቸው ፕሮጀክታቸው ናት በአሉታዊ ሁነት። "እንዳያማም ጥራው እንዳይበላም ግፋው" መርኃቸው ስለመሆኑ አውቃለሁኝ። ውስጣቸው እኛን አይፈቅድምና።
በተጨማሪም ችግር እንዳለ እዬሰማን ነው፥ እነሱም ሊደመጡ ይገባል፤ መልስ ቀና ካልተሰጠ ወዮ ለሚሉትም ኢሳት በሙሁራን፤ በሚሊዮን ደጋፊ የሚንበሸበሽ ተቋም ነበር። #ከሥንት #ተሸነሸነ? ወደ ሰባት ይመስለኛል። ተጀምሮ የቆመውን የጋዜጠኛ ምናላቸውን "ሚዛንን" ሳልጨምር። ዬፖለቲካ ድርጅቶችስ የትኛው የፖለቲካ ድርጅት እንደ ተፈጠረ ቀጥሎ የትውልድ ሆነ? በሥንት ዓይነት ሥም ሲዥጎረጎር ውለው ያድራሉ???
ይህን የማነሳው በምክንያት ነው። "ችግር" ዬሚለው ድምጽ ገዝፎ ስላደመጥኩኝ። ከዚህ በላይ ኮረና፤ ጦርነቱ፤ የህዝብ ዬጀምላ ፍጅቱ፤ በብፁዑ ወቅዱስ አባታችን በአቡነ ማትያስ ዬደረሰው ዘርፈ ብዙ መከራ፤ ለቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እናታችን፤ ተፎካካሪ፤ ጠላት ሲመረት እንዴት እንደባጄ፤ ዬአደባባይ ባዕላቷ እንደምን እንደተስተጓጎለ፤ በመንበሯ ላይ ልጆቿ እንደምን ሰማዕት እንደሆኑ፤ ስንት አብያተ ቤተ ክርስትያን እንደነደዱ፤ እንደ ተዘጉ፤ ማህበረ ምዕመኑ ያሳለፋት ሰቆቃ እንዲያውም ጽኑ ናት እናታችን። ዬአንድ አገር መሪ ሰላይ ከሆነም ዝናብ ያዘለ ተራራ መሸከምም ነው።
በጥቅሉ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሰማያዊ ፀጋዋ ችሎት ነው ዬቀጠለችውም። መወቀስ ዬለባትም።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።"
ወስብኃት ለእግዚአብሄር።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/01/2022

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።