መድረሻን ለማወቅ መነሻን ማወቅ ዓዕምሮውን ለወጣው ዘመን ያስፈልገናል።

 

መድረሻን ለማወቅ መነሻን ማወቅ
ዓዕምሮውን ለወጣው ዘመን ያስፈልገናል።
ለነፃነት የሚደረግ ትግል #መኖር ነው። የህይወት ቅጥል ሳይሆን እራሱ #ህይወት፣ እራሱም ትርታ ነው። በጎጃም ቅኔ አማራ ህዝብ ተጋድሎ ፀሐይ ይወጣል ብዬ አምናለሁ። ከውስጣቸው ገብቷቸዋል።
"በታካች ሰው እርሻ አዕምሮ
በጎደለው ሰው ወይን አለፍኩ።"
(ምሳሌ ፳፬ ቁጥር) 

 
ትግል ወረት አይደለም። ለነፃነት የሚደረግ ትግል መኖር ነው። ሲሞላ እና ሲጎድል፣ ሲሳቅለት እና ሲፈነጥዝ ብቻ ልቅዳህ አትለውም። እንዲያውም ሲስቅ ዞር ብሎ አቅምን ከመሳቅ ጋር ላልተገናኙት ምንዱባን ማዋል ይገባል።
ለዚህ ነው እኔ በብዙ ደክሜ ወገኖቼ ከእስር ሲለቀቁ በሰሞናቱ ወይ አልኖርም ብኖርም መደበኛ ተግባሬን ሳላስተጓጉል እምቀጥለው።
ምንም ዓይነት ግንኙነትም አልፈጥርም። ተልዕኮዬን ስጨርስ ዞር ነው። ለዛ የሚሆኑ ሰብዕናወች አሉ እና ጅራት ላይ ቆይተው ቀንድ ልሁን ብለው የሚገማሸሩ። ቦታ መልቀቅ፣ አለመጋፋት፣ ወረፋን አለመጠበቅ የአቅም አስተዳዳሪነት ነው።
#የሆነ ሆኖ።
ያልገባን ዕውነት አለ። #ትግሉ #ለነፃነት መሆኑ። እዚህም ሆኜ ነፃነት አይሰማኝም። እስከ አፓርታማዬ ችግሩ ገብቷል። በዘመነ ህወሃት እንዲህ አልነበረም። በብዙ ሁኔታ ህይወትን የሚፈትኑ ገጠመኞች አሉ።
እኔን በነፃነት አገር እንዲህ ሰላሜን ያሳጡኝ፣ መውጫዬ መግቢያዬ ሰላይ አስቀምጠው ቁጥጥር የሚደረገው ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ አገር ሆነው የሚሠሩት፣ የሚታገሉት ምን ሊገጥማቸው ይችላል ብላችሁ እሰቡት። በብዙ ጥንቃቄ ነው እኔ እምኖረው።
በዘመናት መካከል እንዲህ ዓይነት #አረንዛ#ጃርት የሆነ መከራ ኢትዮጵያ ገጥሟት አያውቅም። ሰላይ መሪ አገር ሲኖራት ዘመኗ #የስቅለት ነው። በተለይ ሊበቀላት የሚሻ ከሆነ። ጥንታዊነቷ #የሚናደው#የሚያበሳጨው ከሆነ።
ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት የእሷ መቅደም የእሱን የፖለቲካ መሠረት ስለሚንደው ያን ያስቀደመ #ውርዝ ሲገጥም በልኩ መሆን ይጠይቅ ነበር።
ግን የማዬው ውሽልሽል ነገር ነው። #ፀረ #ስሜን ፖለቲካ ማህበርተኛውን እዬው። የሚገርመው እራሱን ለማጥፋት የተሰለፈው ስሜነኛ ደግሞ አብሮ ሲንቀዋለል ታዬዋለህ።
የሚገኘው የውጭ አገር ብድር የሚውለው ለዚህ ለጥፋት ስለላ ለተሰማሩት ነው። ስንቱ ሰው #እንደረከሰ እያዬሁ ነው። ይህን እምለው በእኔ በኩል ብዙ ማስቆሚያ መንገዶች እንዳሉ እዚህ አውቃለሁ።
እኔ ነገር አልወድም። መካሰስም አልወድም። ከሰው ጋር ተጣልቼ ክፋ ተናግሬ አላውቅም። ሰው ካስከፋኝ በዝምታ ምንም ሳልናገር ግንኙነቱን እንደተከባበርን ማቋረጥ ነው። ሹልክ እላለሁ።
ከዛ እንኳን በአካል ድምፄም እንደተናፈቀ ይቀራል። በግሌ ጉዳይ ማለት ነው። ስለዚህ መፍትሄውን ለመዳህኒዓለም ሰጥቼ በጥንቃቄ እዬኖርኩ ነው።
#ዛሬ ሲዘረዘር።
የነፃነት ትግሉ ከኖርንበት በጣም ይለያል። እራስን ከመጠበቅ፣ ቤተሰብን ከመጠበቅ፣ ክብርን ከመጠበቅ፣ በምግብ ብክለት ከሚመጡ ማናቸውም ጥቃቶች ከመጠበቅ ሁሉም ነገር ይቅርብኝ ከማለት፣ ከመወሰን፣ ከመቁረጥ ጋር በፅኑ የተዋደደ ነው። ለብልሆች።
በተለይ እንደ እኔ ሙሉ ዕድሜውን የከባበዱ አምክንዮችን እዬደፈረ ወደ ፊት ለሚገሰግስ ማገዶነት ለማይታክተው ሰብዕና።
ይህን እንደ ህዝብ አማራን፣ እንደ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ስታስቡት ሁለቱም ገና ለብ አላሉም የችግሩን ሆድ ዕቃ ለማወቅ። ትብትብ ያለ ዘመን ነው። እራሱ መነሻቸውን ያወቁ በሰብ ደረጃ እንጂ እጅግ በጣም ጥቂት አሉ። በተቋም የለም።
ካለ ተቋማዊ ተጋድሎ ደግሞ ይህ ስውር አረንዛ ነፃነት ገፋፊ ሥርዓትን መነቅነቅ አንችልም። እንኳንስ አቻዊ ትግል አድርገን ልንፎካከር ቀርቶ።
እኔ አሁን ብቅ ብቅ ያሉ የአማራ፣ የተዋህዶ ልጆች መታሰራቸው ብርቄ ነው። ከባሰው ክፋ ነገር የተሻለው ክፋ ነገርን ስለምመርጥ።
ዕውቅና ካገኙት ያላገኙት ስለሚበረክቱ። 20 አይሞሉም ዕውቅና ያገኙ ታሳሪወች። እስሩ ቀጥሏል። ሙጃው ብአዴን ባለው እንኳን 4500 ነው። የሚገመተው ግን ወደ 8000 ነው። ይህም ጭፍጫፊ ነው። ገና ይቀጥላል። በሰሌዳ ማን መቼ ይረሸናል የታቀደ ትራጀዲ ነውና።
ዕድሜ ልካቸውን በቀል ያበቀሉ ሰው ናቸው አገር እዬመሩ የሚገኙት። እሳቸው በሚገባ በሰነድ ተዘጋጅተዋል። ደራሽ የሚሆነው ለእኛ ነው።
እዩት ከዛ የቀደሙ ጉዝጓዝ ንግግሮች፣ ሽፋኖችን በቅደም ተከተል ውስጣችሁ አድርጉት።
የብፁዑ አባታችን የአቡነ አብርሃም የክብር ቀን። በማግሥቱ #ቱርኪ #ባህርዳር ገባ። ባሳልስቱ ጄኒራል ባጫ ደበሌ #ቱርክ ኢስታንቡል ገቡ። በአርባቱ ጠቅላዩ መቃድሾ እና ጁቡቲ ነበሩ።
ዝም ብላችሁ በስክነት ሳትነጣጥሉ የዕለታዊ ሁኔታወችን በዬአቅጣጫው የሚለቀቀውን ፕሮፖጋንዳ ቸል ብላችሁ ተከታተሉት። ጨምታችሁ። ሳትበሳጩ።
በአሉታዊነቱ የሚገርም፣ በአሉታዊነቱ የሚደንቅ፣ በስልት የተያዘ ሁለመናን እያሳቀቁ የማራገፍ፣ ስጋት እዬመገቡ የመንቀል ፕሮጀክት ተመችቶት እዬተከወነ ነው።
ሁለመና በሰበር ዜና ታግቶ እያለቀ፣ እዬፈረሰ፣ እዬተናደ፣ ከሥሩ ደግሞ አዲስ የሆነ #በባዕድ መንፈስ የተኳኳለ አሉታዊ ድርጁ ተግባር እዬተከወነ ነው። ድርጁነቱ ለእነሱ ነው ለገዳኦዳውያን። ለዬቦታው አስፈፃሚወች አራት ዓመት ሙሉ ተከውኗል።
ከላይ ቅብ የኮታ ነገር ታያላችሁ። ወሳኙ ቦታ ግን የአጥፊው ፕሮጀክት ባለድርሻ አካላት ተሰክተዋል። ይህን ሸንጎ አፈ ጉባኤና ምክትል፣ የሰላም ሚር እና ምክትል ሁሉን ቦታ እዩት።
ቅይጥ ነው ነገረ ዓለሙ። እስያን፣ አረብ አገርን ሰረናንቆ አርቲፊሻል ዛሬ የተጀመረች አገር የመፍጠር ሂደት ነው። ለእኛ ውልቀት ነው። ውርዴት ነው። ክሽፈት ነው። አብረው በተባባሪነት ለሚሠሩት ደግሞ መቃብርነት ነው።
ለእኛ ማለቅ ነው። ለእኛ #ኦርጅናላዊነታችን ተፈጥሯዊነታችን ማስማረክ ነው። ልክ ፆታ እንደሚቀዬረው፣ ልክ የአፍንጫ፣ የገፅ ሰርጀሪ እንደሚሠራው ማለት ነው።
ለእኛ የራስ እንደራሴነት አውልቆ የማናውቀው፣ ያልተነገረን፣ ዕውቅና ያልሰጠነው፣ ያልወሰንበት #ውራጅ ማንነት መሸከም ነው። ፈቅደን - ወደን። አሻም ያሉ ሞገደኞች በግል ይኖራሉ። ግን አሰባሳቢ ሞቶ፣ አሰባሳቢ እናት ድርጅት የላቸውም።
በተዋህዶ አንፃር እናት ቤተ ክርስትያን አለችን። ግን አራት ዓመት ሙሉ የተካሄደው ወረራ፣ ጉርጎራ የሚለካ አይደለም። ዊዝደም ይጠይቃል። ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠዬቅም ይጠይቃል።
በአማራ ጉዳይ የተበጣጠሰ ነው። ያገኜ እንደ አሻው የሚደውረው ነው። ባለፈው እንደ ፃፍኩት የአጥር ወይን ወይንም የአጥር ኢንጆሪን። አላፊ አግዳሚው የሚሸመጥጠው።
ተፈሪ የአቅም ዘብአደር መፍጠር አልተቻለነም። ኮማንድ ፖስት የለንም። ቢጋር የለንም። ሲናርዮ የለንም። ቅድመ ሁኔታ አላሰናዳንም። ብቻ ሰንደቅ አላማ ከተለበሰ ችግር የለም። ግባ በለው ነው። ሆታ ነው።
አሳቻው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የሚያመልጡበትን መላሾ በዬሰከንዱ እያመረቱ ውልቅልቅ አድርገው በአዲስ #ቅልጥም እዬገጣጠሙን ነው። ባዕድ እስኬለተን ሳይቀር ነው እዬተገጠመልን ያለው።
ልክ የውስጥ ልብሱ በእግር ሥር እዬወለቀ በላዩ በራስ በኩል እኛን የማይመስል፣ የእኛ ያልሆነ ፍፁም ባዕድ፣ ልንፀዬፈው የሚገባ ሲኦላዊ ማንነት እከክ፣ በለው ቹፌ፣ ቹፌ በለው አንከሊስ፣ አንከሊስ በለው ውርዴ እዬተበጀ እዬተለማመድነው። አንድ አካባባቢ ይሰሙ የነበሩ ጭካኔወች ባህል እዬሆነ ነው።
ዲሞግራፊው እኛነትን አውልቆ የህሊና ነቀላ እና ተከላውንም ይጨምራል። ሃዘን አብሮ ማዘን ያስወቅሳል። በእሳት አሳሮ መግደል ያሸልማል። ፅንስ መብላት ወግ ሆኖ ካባ ያሸልማል።
እዬተሸራረፍን፣ እዬፈራረስን ውኃ እንዳጣ ዋልካ ስንጥቅጥቅ ብለን ሰንበር በሰንበር ሆነናል። ለምን? ለትግል ስንነሳ መነሻችን ሆነ መዳረሻችን ጋር በትልልፍ ስለሆነ። ስለዚህ ስኬት እዬራቀን መረታትን ተቃቀፍን።
ምን እናድርግ?
ስክነት።
ማድመጥ።
ዘመኑን ከውስጥነት ማጥናት።
አቅምን ቆጥቦ ማስተዳደር።
በዕድ ለሆኑ ሁነቶች አቅል መንፈግ።
የራስነገር አጥብቆ መያዝ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
13/06/2022
ሳትጠፋ አጥፊህን ዘመን በልኩ በስልት ታገለው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።