ለወጣቶች ቀን ይሰጣል የእናትነት ፖለቲካ።

 

ለወጣቶች ቀን ይሰጣል የእናትነት ፖለቲካ።
"ቤት በጥበብ ይሠራል
በማስተዋል ይፀናል፥"
(ምዕራፍ ፳፬ ቁጥር ፫)
በቅድሚያ ውጤቱን ለላካችሁልኝ ቅኖች አመሰግናለሁኝ። እኔ ብዙም የመንግሥት ሚዲያ ተጠቃሚ ስላልሆንኩኝ ውስን ነገሮችን ነው እምከታተለው። ለዛውም አሁን ከሆነ።
የትውልድ የሆኑ ነገሮች ሊበረታቱ ይገባል። የጀርመንን ሙሉውን እከታተላለሁ። በተለይ ከሦስት ዓመት በፊት። ለእኛ ብቻ የሚመስሉን የአስተዳደግ ችግሮች ውጪ አገርም መኖሩን አይቻለሁ።
ለዚህም ነው። ሁለት የምክር መፃህፍትን የፃፍኩት። ማግሥት እራቃኑን እንዳይቀር ዛሬ ሊሰራበት ስለሚገባ። ግን ደስታ ታግቶ ሊሆን አይገባም። በደስታው ዕለት ወላጆች፣ አድናቂወች ውጭ ነበሩ። ይህ ደግሞ አንዱ ማዕቀብ ነው። ያልተገባም ውሳኔ ነው። ሊስተካከል ይገባልም።
ቢያንስ ቤተሰብ ይህችን ዕድል እንኳን ለምን ይነፈጋል? ከጎንደር ድረስ የመጣች እናት ውጭ ሆና ደስታን መጠበቅ? ግፍ ነው። ለዛውም ዛሬ ሰው ወጥቶ ስለመመለሱ እርግጠኝነት በሌለበት ዘመን።
ጎኃ ጽዮን፣ ገብሬ ጉራቻ፣ አባይ በርኃ ላይ ሊገጥም የሚችለው ችግር አይታወቅም። ለዛውም አማራ፣ ለዛውም ተዋህዶ? አሁንማ ከኦነግ አልፎ ኦህዲድ እራሱም እያገተ እኮ ነው ያለው በይፋ።
የሆነ ሆኖ የድምፃውያን ውድድር ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። በውነቱ አልተከታተልኩትም። ቅኖች ስትልኩልኝ ግን አክብሬ ተከታዬዋለሁኝ።
በምልሰት ያለፋኝን ለማዬት ሞከርኩኝ። ጥሩ ፋክክር ነበር። በሙዚቃ ዘርፍ ዜሮ ብሆንም። የወጣት ዳኞች እርጋታ መስጦኛል። ቁጥብነታቸውን አክብሬዋለሁኝ።
ሌላው የደነቀኝ ቲም ወርኩ ላይ የተደራጀ እንደነበር አስተውያለሁ። የማይክ አያያዝ ይሁን ጥራቱ አላውቅም ስንኛትን ለመስማት አይቻልም። ማይክ እንዴት መጠቀም እንደሚገባም ማስተማሩ ጥሩ ነው።
የወደድኩት ተወዳዳሪወች የነበራቸው መረዳዳት፣ መተሳሰብ፣ አብሮነት በብዙ ውድድሮች ውጭ አገር ያላዬሁት ጤናማ ሥነ - ምግባር መሆኑን አስተውያለሁኝ።
ቅናት ተሸንፎ አንድነት በርቶለት ተመልክቻለሁ። በተለይ ቃለ ምልልሱን በጋራ የሰጡትን ሳዳምጥ። ሁሎችም አሸናፊወች ናቸው ለእኔ። ዘመኑን የሚፈትነው ልዩነት ማሸነፍ በራሱ አሸናፊነት ነውና። አብሮነትን በተክሊል አንቆጥቁጠውታል።
ፕሮግራም አስተዋዋቂወችንም በጨረፍታ አይቻቸዋለሁ ቲሙ በጠቅላላ ጤናማ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ዩቱብ ቻናል ላይ የኦዴንሱን ዕይታም የቻልኩትን ያህል አንብቤያለሁ። ዕፁብ ነበር። አወንታዊ ነበር። የተስተካከለ ኢትዮጵያዊነትን በግልጽ ቋንቋ ያስተማረ ትዕይንት ነው የተመለከትኩት። የፖለቲካ መሪወችም ቢማሩበት መልካም ነው። ዕውነቱ የት ላይ እንደ ሆነ ግብረ ምልሱ ስለሚናገር።
ይህን በብፁዑ አባታችን አቡነ ኤርምያስ ግብረ ምላሽ አስተውያለሁኝ። ያለብን መሪ የማጣት ችግር ብቻ ነው። እርሾው አለን።
አሸናፊዋ ደርባባዋ፣ እርጋታዋ የሚያስደምመው ወ/ት ያለመወርቅ ጀንበሩ ከልቤ የገባ ነገር ተናግራለች "ጎንደር ላደገ ካሜራ ከባድ ነው። ባህሉ ከባድ ነው። ወጣ ወጣ ማለት አይፈቀድም። ካለ መሞከር መሞከር አስተማሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ" ብላለች። ስንት ዕድላችን ታጥፎ የሚቀረውም በአስተዳደጋችን ተፅዕኖነትም ነው። አንደፍርም።
እራሱ ያለምዬ ባቀረበቻቸው ዝግጅቶች ሙሉ ፐርፎርማንሱ ብቁ ነው። ፕሬዘንቴሽኗም በቂ ነበር። ግን ኦድዬንሱን ለማዬት ዓይኗ አልደፈረም። ጎንደሬነት እንዲህ ነው።
ብዙ የማንደፍራቸው ጉዳዮች አሉ። አሁን ልዕልት ንግሥት ይርጋን ያህል የጨመተ #ዓውራ አብዮት ያደራጀ የመራ፣ ፈጣን ህሊና ያለው የለም። ሌላ ቦታ ብትወለድ እና ብታድግ በዕድሉ ተጠቅማ የት በደረሰች ነበር? ለአንገቷ ማስገቢያ ጎጆ እንኳን ያላት አይመስለኝም። አይደለም ሌላ።
እኔ እራሴ ስንት ዕድል ሚስ አድርጌ ነው እዚህ ተቀብሬ የምኖረው። የዕድል ዓይነት በዓይነት ነበረኝ። መርከቡን ፈጣሪዬ አሰናድቶ ይጠብቀኛል። ግን ባህሉ ጥብቅ እጅግም የማያወላዳ ነው። ፋና ላምሮት ጠልፎ አለምዬን ግን ትልቅ አደረጋት። ተመስገን!
#እናታዊነት እና እኛ።
ሌላ በኢትዮጵውያን ብዙም ያልሰራንበት ከእናት ጋር ያለን ቀረቤታ ግርማ ሞገሱ ዕፁብ ድንቅ መሆኑን ነው። ሁሉም ሲያሸንፍ ወደ እናቱ ያዘነብላል። ይህ ዕንቁ ነገር ነው። እያለች እናት ተገቢውን ዕውቅና መስጠት #የሰለጠነ ሃሳብ ነው።
ስትታጣ አዲሱ ማንነት መኖርን ስለሚፈነግለው ቀድሞ በዕድሉ ዕድል መስጠት የእናት ፖለቲካን ዘውድ ይደፋል። መሳናዶው እራሱ እናትነት ነው የፋና ላምሮች። ቀንበጦችን ገርቶ ከአዲስ ተስፋ ጋር አገናኝቷል።
ለዚህ የበቁት አራት አሸናፊወች ወደ ኋላ ሄደው ጭምት ወጣት፣ ስኩን ዳኞቻቸው የሰጡትን መርኃዊ ምክር ሊያጠኑት፣ የሙያው ፍኖተ ካርታቸው አድርገው ሊጠቀሙበት ይገባል።
"እራሳችሁን ሁኑ፣ በቀለማችሁ ውስጥ ለመኖር ወስኑ፣ እራሳችሁን ለማጣት አትጣደፋ። ሙገሳ ፀጋችሁን እንዳያስቀማችሁ ተጠንቀቁ።" ኃያል ምክር ነው። ወርቅ የህይወት መመሪያ ነው።
አዳዲስ ድንቅ የትውልድ የግንባት ስልት ተከትለዋል ዳኞች። አያስበረግጉም። ትርፍ አይናገሩም። ኩምትርትር አያደርጉም። አዋዝተው ብልህነትን በጥበብ ያስትማራሉ።
ዳኝነታቸው አጭር፣ ግልፅ፣ በውስጥ የሚቀመጥ፣ ዕውነት የሆነ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። ተምሬበታለሁኝ። እኔ ከውድድሩ የዳኞች ዕይታ ነው የሚስበኝ። እዚህም። ያላያችሁት እዩት። ስለትውልድ የሚጨንቃችሁ።
መኖር ብዙ ዓይነት ነው። አትኮድኩዱት። ሁሉንም ዓይነት የኑሮ ሰናይ ህዝባችን እንዲያገኝ ነው ትጋታችን ሊሆን የሚገባው። ሃዘን ላይ ተለያይተን፣ ደስታ ላይ ተለያይተን ስንቱ ይዘለቅ? ሁሉንም በፈርጁ፣ በመልኩ መያዝ ይገባል።
ሌላው ቤተሰብ አልባ ደስታ ልሙጥ ነው። ቤተሰብ ውጪ መጉላላት አይኖርበትም። ቤተሰብ የልጆቹን ደስታ እንዲይ ሊፈቀድ ይገባል። ከዚህ ከሌላ አገር ወጪውን ችለው አዘጋጆች ቤተሰብ አምጥተው ሰርፕራይዝድ ያደርጋሉ።
ጥሩ ነገር አይቻለሁ። በርቱ። ለወጣቶች እንኳን ደስ አላችሁ። ለቤተሰብ። ለዳኞች፣ ለባንዱ፣ ጠቅላላ ለቲሙም ለስኬት መብቃት የታሪክ ምዕራፍ ነው።
አርቲስት ፀሐዬ የኋንስን የመሰለ ታናሽ ወንድምም አይቻለሁ። ኢትዮጵያን ያዜመው።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
13/06/2022
ጥበብ ትርታዬ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።