#ተግባር ትጥቁ ተግባር - ተግባር ስንቁ ተግባር - ተግባር ትንፋሹ - ተግባር ነው! ከሥርጉተ ሥላሴ 19.07.2015 /ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ/
እንደገና ሥራ ስላስጀመሩን "ሀ" ብለን ለመታገል ፋይል፤ ፎቶ ቪዲዮ ሳስስ ያገኜሁት ነው። ለዛሬም ይጠቅማል። መሪም አቅጣጫ ቀያሽም ለሌለው ትግል ዬተደከመበት ማሳ። በ2015 እንደ አውሮፓውያን የተፃፈ ነው።
#ተግባር የነጠረ ንጡህና ፃድቅና ፀዲቅም ነው።
#ንጡህና ጻድቅ ደግሞ ልክስክስ የሆኑ ጉድፎች ክፍሉ አይደሉም - አይሆንም።
#ስለሆነም ተግባር፣ ተግባርን ጸንሶ ተግባርን ይገላገላል እንጂ ተግባር ክፋትን - ቂም በቀልን ጸንሶ ዬእንግዲህ ልጅን - አይገላገልም።
#የተግባር ሩኹ ብሩኽ - ራዕይ ነው።
#ብሩኽ ራዕዩን ለማግኘት በሠርግና ምላሽ አለመሆኑን ጠንቅቆ - ይገነዘባል።
#ተግባር መከራን ለመቀበል፤ ፍዳን - ለመሸከም፤ አሳርን ለማስተናገድ የተዘጋጀን ጀግና - ይደግፋል፤ ይመራል - ያስተዳድራል።
#የተግባር ድፍረቱ የሚመነጨው ከተነሳበት እውነተኛ ህዝባዊ ዓላማና ካስገኘው ውጤት - ይነሳል።
#አዎን! የተግባር መነሻው ተግባር ነው።
#የተግባር መድረሻው ተግባር ነው።
#ተግባር ሁልጊዜም አሸናፊ ነው።
#ተግባር ሁልጊዜም ድል ላይ ነው።
#ተግባር እንኳንስ እሱ ሊሸነፍ ተሸናፊዎችን ሳይቀር በነጠረ ጭብጥ በመሆኑ - ነፃ ያወጣቸዋል።
የተግባር መሳሪያው ተግባር ብቻ ነው። የተግባር ጠበቃው ተግባር ብቻ ነው። የተግባር መከላከያው ተግባር ብቻ ነው። ዳኛው ተግባር መከረኛውን አሁንም በተግባሩ - ይክሰዋል። በጥርስ የተያዘው ሌት ተቀን የሚከተከተውን፣ ደመ -መራሩን - መከራውን እንደ ጌጥ ቆጥሮ ቀልጦ ሻማ እንዲሆን - ይረዳዋል። የተግባር ታቦቱ -ድርጊተኛው ነው። የተግባር ሽልማቱ የተሰጠው መክሊቱ ነው።
አሁንስ? እኮ አሁንስ? ምን ይባል ይሆን። ክርችም ዝግት ይሆን - ይሆን? ፀጥ ረጭ ይሆን? ወና ይሆን ዕጣ ፈንታው የአታሞው፤ ወይንስ ደግሞ ያው እንደተለመደው የለወጥ ንፋስን እንዘውር ተብሎ አካኪ ዘራፍ ይባል ይሆን? ዬዕንባ ወታደር አይተኛም - አያንቀላፋም። ይልቁንም ዕንባን የረገጠውን በተግባር አብነት በማስተማር፤ በማደራጀት ቀንዲልነቱን በተግባሩ - ያረጋግጣል።
ተስፋ ተግባር ነው ወታደሩ፤ ለተስፋ ድርጊት ነው - መጽናኛው፤ ለተስፋ መሆን - ሁነኛው። እነሆ ሁነ። እነሆ ተስፋ አዎ ሆነ። ተስፋ ነው ሆነ። ተስፋ በድርና ማግ ራዕይን ዕውን ለማድረግ የበዛውን መከራ ለመቀበል - እውነትን ፈቀደ። ተመስገን!
ይህ ታሪካዊ ጉዞ ይህ አደራን የተቀበለ ጉዞ ዛሬን ለማሳደር ነገን አብቅሎ ያሰብል ዘንድ ትውልዳዊ ኃላፊነትን ወዶ በመቀበል የግዙፉ ትውፊት ተልዕኮ አስኳል ነው። ሞትን ፈቅዶ - ለተቀበለ፤ ሞትን ወዶ - ላከበረ፤ ሞትን ናልኝ ብሎ ለመገናኘት ለገሰሰ ወገን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን፤ እንዲሁም መስኪዶቻችን ማናቸውም ቤተ አምልኮች ሁሉ በዚህ ነፍሰጡር ሴቶች ተረግጠው ጽንስ ሞት በተፈረደበት ዘመን ያሉ ሁሉ ይህን ጊዜ የሱባኤ ወቅት በማድረግ ማህበረ ምዕመኑን ወደ አንድ የጸሎት አቅጣጫ በመምራት ሰፊ የሆነ የተደራጀ የጸሎት ተግባር በግልና በጋራ እንዲከወንብት በማደረጉ በኩል ሰፊውን ድርሻ በመውሰድ በይፋ ዕወጃ ከጎን መሰለፍ ያለባቸው - ይመስለኛል። አባቶቻችን ለድል የበቁት ባለ ሀገር፣ ባለ ሰንድቅ ዓላማ፣ ባለ ማንነት፤ በለ ዕምነት እንድንሆን ያደረጉን በዚህ መንገድ - ነው።
„በቃኝ“ እንዲህ ነው። „በቃኝ“ ለቁርጥ ቀን „የቁርጥ ልጅ ነው“ የአሻም ምላሹ „የአሻም ጉልላት“ ነው። የቁጭ በሉ ዳንኪራ አሁን አድራሻውን መፈለግ አለበት። የሚያዘናጉ ሆነ ትጥቅን የሚያስፈቱ ዘመቻዎች ሁሉ እዩኝ እዩኝ እንዳሉ ሁሉ ደብቁኝ ደብቁኝ ማለት - አለባቸው። አጀንዳቸው እነሆ እንዲህ - አከተም።
ሊቀጠል፣ ሊሰፋ ወይንም ሊጣፍ የማይችል አጀንዳ ግብዕቱን የሚፈጸመው እንዲህ በተግባር አሸናፊነት ነው። አዎን ተግባር ሻንፕዮን ነው። የተግባር መዳሊያው መሆን ብቻ ነው። ሆኖ መገኘት!
ያመነ - የተቀበለ - የቆረጠ - ለድል ይበቃል። ድሉ የዕንባ ነው። ድሉ የህዝብ ነው፤ ድሉ የነገ ነው። ድሉ የትውልድ ነው። ድሉ የተስፋ ነው። ድሉ - ለተገፉት ነው። ድሉ ለመከረኞች ነው። ድሉ የኢትዮጵያ ነው። እርግጥ ነው ድሉ ለቀለጤዎችና ለድሎተኞች ግን አይሆንም፤ እንዲያውም ዛሬ ትቅማጥ በትቅማጥ እንደሚሆኑ - አስባለሁ።
ቅድስት እናቴ እመቤቴ፤ የሰማይና የምድር ንግሥት፤ የሰማይና የምድር እምቤት፤ የሰማይና የምድር ልዕለት እናት ናትና፤ ሩህሩህ ናትና፤ ስደቱንም ታውቀዋለችና መክሊትን ጠብቂ። ጥላ ከላላ ትሁናችሁ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ