አሸባሪው ማን ነው? አቶ አባይ ወልዱ ወይንስ ዬአማራ ተጋድሎ አክቲቢስት ወጣት ንግስት ይርጋ? ከሥርጉተ ሥላሴ 21.01.2017 (ዙሪክ - ሲዊዘርላንድ)

 

• ዬአማራ ተጋድሎ ሲነሳ ዬፃፍኩት ነው። ዛሬ 09.04.2023 አመት ድገም እያለን ነው።
• አሸባሪው ማን ነው? አቶ አባይ ወልዱ ወይንስ ዬአማራ ተጋድሎ አክቲቢስት ወጣት ንግስት ይርጋ? ከሥርጉተ ሥላሴ 21.01.2017 (ዙሪክ - ሲዊዘርላንድ)
 

 
„እንደ ጠቢብ ዬሆነ ሰው ማነው? ነገርንስ ዬሚያውቀው ማነው?"
(መጸሐፈ መክብብ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፩)
ይድረስ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች።
ትግራይና አዲስ አበባ።
• እፍታ።
ያለለት ሃቅ - ትነጥራለች። ያለለትም ውንብድና - ይቆማል። ያለለት ዬምድር ዕንባ ለፍሬ - ይበቃል። ያለለት ዬአፓርታይድ ግዛት መቃብር - ይበላዋል። ያለለት ጥጋበኞች ዬማዕት አውሎ - ይውጣቸዋል። ያለለት ዬዕንባ ቤተኞች መከራቸው መከውኑን ምክንያት አድርገው አምላካቸው ስላደረገላቸው መልካም ነገር ሁሉ በተመስጦና በቀስታ ያመሰግናሉ።
ይህ ከምድራውያን ዬሚጠበቅ ዬራፊ ጸጋ ሳይሆን ዬዕንባ አድማጭ ከሆነው ከፈጣሪ ደጅ ብቻ ዬሚታፈስ፤ በውለታና በጉቦ ዬማይደፈር ሰማያዊ በረከት ነው። በሰው እጅ በመቁንን ተለክቶ በአድሎ - ዬማይደለደል። መክሊት።
እራሷን ለበላህሰቦች ዬማገደች ወጣት ናት። አዎን በአማረነቷ ዬሚደርሰው በደል ልኩን ስላለፈ - ፊት - ለፊት ወጥታ ዬወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌስቶ አንጎል ዬሞገተች ድንቅ ፍሬ ናት። ዬአማራ ጉዳት ዬማይሰማው አካል በግማሽ ግድግዳ ቤትን እንደ መገንባት ስለማሰብ በመሆኑ፤ ሙሉ አቋም ላይ ዬሚገኝ ዬጋራ ቤት እንዲኖረን ዬራሷን ዬቤትሥራ ዬተገበረች ዕንቁ ናት። ዬአማራ መከራ እንደ አልባሌ ማበሻ ጨርቅ ካልተወረወረ … ብሄራዊ ጀግናችን ናት። እንደ ህዝባዊና ሙያ ማህበራት አደራጅነቴ ደግሞ ዓይኔ ናት! ብርቄ ናት! ናፍቆቴ ናት! መሪዬ ናት!
• ምልክት።
ለወያኔ ሃርነት መሳፍንት ሦስት ምልክቶችን መስጠት እሻለሁ። እንድጽፍ ያነሳሳኝም ይሄው ነው።
• ምልክት አንድ
ታስታውሱ ከሆነ ተሰናባቹ ዬአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮዽያ ለጉብኝት ከመግባታቸው በፊት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ወጣት ሴት ጋዜጠኞችን እና ሌሎችንም በድንገት ከእስር - ለቃችኋል። ስለምን? እንዴት? ዬሚለውን ሆድ ዕቃችሁ - ያውቀዋል።
• ምልክት ሁለት።
ዬጀርመኗ መራሂተ መንግሥት ዶር አንጅላ ሜርክል ኢትዮዽያ ከመግባታቸው በፊት - ዬኢትዮዽውያንን ሰላማዊ ሰልፍ ከእነካቢናቸው በጀርመን ርዕሰ መዲና በርሊን ላይ በክብር ወጥተው - ተመልክተዋል። ከዛ በፊት ጀርመን ላይ መሬት አንቀጥቅጥ በጣም በርካታ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጉ ነበር።
በዕለቱ ዬነበሩት ሰልፈኞች 1/30 እንኳን አይሆንም። ኢትዮዽያ ከገቡ በኋላ አንዲቷ ዘለላን ለምልክት ብቻ ላንሳ - ዬገጠማችሁን ቻሌንጅ ለእናንተው - ልተዎው። „ለቀባሪው አረዱት“ እንዳይሆንብኝ። ተቃዋሚ ሃይሎችን ለማነጋገር ሲወስኑ ሴት ተወካዮችን በዓውራ አጀንዳ ይዘው ነው። ያ … ዬንግስት ይርጋ በህይወቷ ላይ ሊደርስ ይችላል ተብሎ በተገመተ መከራና ሥጋት ዬፈጠረው ጫና ያስገኘው ፍሬ ምልክት ይሁናችሁ። ብቻዋን አይደለችም። ይህን ዕወቁ። ዬእሷ መታሰር ያሳደረው እልህ ዬማይታዩ ረቂቅ ዬነፃነት ሀገራዊ ትርፋቶች ሆነ ዕሴቶችን አስገኝቷል።
በዝግታ መራመድ ስለሚያስፈልግ ብቻ ነው፤ ለሚዲያ ፍጆታ - ያልዋለው። ስለሆነም በህይወቷ ላይ፤ በሥነ - ልቧናዋ ላይ ልዩ ጥበቃ ማድረጉ ዬሚበጅ - ይመስለኛል። ከዚህ በላይ መሄድ አልፈልግም። ይበቃል። ከንፍሮ ጥሬ ያወጣው አንድ ቅን መንፈስ ከመሃላችሁ ከተገኜ - ከጥፋት ሊታገዳችሁ ይችላል። በአደብ - እሰቡበት።
ሰው ዬሚላችሁን ዕብድ ዬዘራው አዝመራ - አታድርጉት። አድምጡት። ለእናንተ ሳይሆን ለነገ ደህንነት - ለትግራይ ህፃናት። ለነገሩ ለእናንተ እነሱ አጀንዳችሁ አይደሉ። ጦሳችሁን ትከማምሩላቸው አላችሁ። ምን ዓይነት መዳህኒት ልዘዝላችሁ ይሆን። እስኪ ህፃናት መዋያ እዬሄዳችሁ ዬህፃናትን ቅድስናና ንፅህና ተመገቡ። ብትድኑ።
• ምልክት ሦስት።
ከእሬቻ ዬኦሾቲዝም ዬኦሮሞ ማህበረሰብ ሆነ፤ ዬባዕሉ ታዳሚው ዬወገን ዕልቂትና ከአስቸኳይ ህጋችሁ ማግስት፤ ዬዓለሙ ዬሰብዕዊ መብት አስጠባቂ አባት አቶ ኪም ሙን ዬሶሊዳሪት ምልክት በማሳዬት ከድምጽ አልባዎቹ ዬኢትዮዽያ እናቶች ዕንባ ጎን በአደባባይ ቆመዋል። መቼም ደፋሮች አይደላችሁ፤ በአስቸኳይ ጊዜ ዓውጁ አንቀፃትን ዘርዝራችሁ ክስ መስርቱ። ይህ ዬሚያበላ ይመስለኛል። ዕንባ አድማጭ አለው። ዕንባ ጥግ አለው። ዬወገን ሰቆቃ ዬእኔ ባይ አለው።
• ዬወግ ገበታ።
ዬእኔ ብልህ ወጣት ንግስት ይርጋ ዬተከሰሰችበትን ቻርጅ በሚገባ መርምሬዋለሁ። እሷ ዓላማዬ ብላ ከተነሳችበት መንፈስ ጋር ዬማይገናኝ ነው። „ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ“ እንዲሉ።
አ/ግንቦት ሰባት አቅም ቢኖረው ከሩቁ ሳይሄድ እኔ ለምን ነካችሁት ብዬ አደባባይ ወጥቼ እምሟገትለትን አባል አድርጎ መዳፋ ውስጥ ባስገባኝ ነበር። ዛሬ አ/ግንቦት አለኝ ዬሚላቸው ብዙዎቹ ከመምጣታቸው በፊት ሥርጉተ ቅንነቷንና ድንግላዊ መንፈሷን አልሳሳችለትም ነበር። ግን ማኒፌስቶውን ግዛኝ … ንዳኝ ብላ ፈቀደችለትን? እሱስ ቻለ? አልቻለም።
እንኳንስ በመንፈስ ወጣት ንግስት ይርጋን አዬር ላይ መልምሎ ዬአማራን ህዝብ ሞቢላይዝድ ማድረግ ይቅርና። ይሄን እንደማይችል እናንተም ታውቁታላችሁ፤ አ/ግንቦት ሰባትም አራሱ ያውቀዋል። አዬር ላይ ሞትን ዬሚጋፈጥ ትውልድ መፍጠር - አይቻልም።
መሬት ላይ ወርዶ መከራን መጋራትን ይጠይቃል። ለዛውም ህዝብ ውስጡን ከሰጠ ብቻ። ህዝብ ንጹህ መንፈሱን ሲለግስ ሲወስን ደግሞ ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። ዬፈቀደው ሽልም መንፈሱ እንዳያችሁት ዬአማራን ልጅ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ እንዲህ ዬእኔ ጉዳይ ብሎ እንዲወጣ ያስችለዋል። ሞገድም ነው ምቱ። መሬት ያያዘ ሁነኛ ተግባር ለምለም ነው፤ በፈቃድ መስኖ ዬሚያፈራ። እሽት ነው ዬነገ ሰብል ልብ።
ሌላው መዳፋችሁ ላይ ያለው ዕውነት ያው ፖለቲካና ዕውነት እንትንና እንትን ካልሆኑ፤ እናንተ ሚዲያው፤ ገንዘቡ፣ ስልጣኑ - ጠበንጃው ያላችሁ ዬቻላችሁት ምን ያህል ኪሎ ነው? ዬህዝብን ንጹህ መንፈስ ባለጸጋነታችሁ ዬባለቤትነት ቁመናው ከዜሮ በታች ነው።
ብዙ ዬላቁ ዕውነቶች ድርጅታችሁን ከጨዋታ ውጭ ማድረጉን አሳምራችሁ - ታውቁታላችሁ። ልቡ ዬሸፈተ ህዝብ በጠበንጃ - በጥይት እዬቆላችሁ፤ ረግጣችሁ እንጂ - ፈቅዶላችሁ አይደለም እዬገዛችሁት ያለው። ብታውቁት መንፈሱ ከፈረሰ ባዶ ሥልጣን ላይ ነው ዬተቀመጣችሁት። ተንሳፋፊ ጀልባ። አሁን ደግሞ መርዙም አልበቃችሁ አለና ፈንጅና ቦንብ ጠምዳችሁ ትጨሩስትአላችሁ። ምን ዬእናንተ ነገር … ጉድጓድ።
ዬኢትዮዽያ ህዝብ ጭምት ነው። ከሌላው ለዬት ያለው ተፈጥሮውም ይሄው ነው። በቅዱሳን አባቶቹ ዬድንግልናና ዬቅድስና አቅም ነው ጀንበር ወጥታ ዬምትገባው። እንደ እናንተ ደንታ ቢስነት ቢሆንማ ከባድ ነበር። ኃላፊነት በፍጹም ሁኔታ ዬማይሰማችሁ። ከግድፈት ለመታቀብ ያልፈቀዳችሁ። ስህተት ዬማያሸማቅቃችሁ ሰው መግደል፣ ማሰቃዬት፣ ማሰር ዬማይሰለቻችሁ። ዬህዝብን ሰቀቀንና ጭንቅ ዬምትናፍቁ ዬሰው ጉዶች።
ዬኢትዮዽያ ህዝብ ግን ብሩክ ቅዱስ ነው። ዬዬትኛውም ዓለም ምድር ያልፈጠረው። ጠባቂውም - ፈጣሪው። መሪውም - ፈጣሪ። እንደናንተ ዬጨበራ ተዝካር - ዬጭካኔ እንቢልታ ቢሆንማ ገና ድሮ ድሮ ተባራችሁ ነበር። ዬኢትዮዽያ ህዝብ ትእግስቱ ግን ከአውሬነት ወደ ሰውነት፤ ከጫካ ህይወት ወደ ሰዋዊ ህይወት ሊመልሳችሁ አልቻለም።
እንዲያውም - ባሰባችሁ። ከጉድጓድ ተቀብሮ ዬኖረ አውሬ - አደረጋችሁ። ከሰው ተፈጥራችሁ ዬሰው ስቃይ በልታችሁ፤ ዬፍደኛን ዕንባን ጠጥታችሁ፤ ለብሳችሁ ትኖራላችሁ። በእናንተ ተፈጥሮ ላይ ሥንት ዬሥነ - ልቦና ቀውስ አጥኚዎች ሣይንቲስት በተባሉ ነበር። ሙሁሮቹ - ቢሰሩበት።
ይህን ያነሳሁላችሁ ዬሚሆነው ብቻ እንጂ ዬማይሆነው እንደማይሆን ከልባችሁ እንዲገባ ነው። ዬአማራ ተጋድሎ አክቲቢስቷ ንግስት ይርጋ ዬአርበኞች ግንቦት ሰባት ብትሆንማ አገር ምድሩ ዬእሷ አድናቂ በሆነ ነበር። አላያችሁ ይሆናል እንጂ ዬኢትዮዽያ አርበኞች ግንባርና ግንቦት ሰባት ሲዋህዱ ዬኢትዮዽያ አርበኞች ግንባር ኮትኩቶ ያሳደጋት ዬምንቴ ልጅ ዬሚዲያ ደንበኛ እንደነበረች። በእነ አጅሬ ቤት ቀልድ ዬለም።
ካለሂሳብ ዕውቅና መጎናጸፍ። ዬአማራ ተጋድሎ አክቲቢስቷ ንግስት ይርጋ ፎቶዋ እንኳን ያለው፤ ዜናውን ዬሚዘግቡት ዘሃበሻና ሳተናው ብቻ ናቸው። ለሌሎች ዬእሷ ተጋድሎ ባዕድ ነው። ምንአልባት ከእንግዲህ ወዲያ እንደ ኮነሬል ደመቀ ዘውዴ ፍቶዋ ለጭረታ ልንጠብቅ እንችል ይሆናል።
ይህ ትውልድ መሪውም፣ ዬፖለቲካ ድርጅቱም፣ ማኒፌስቶውም ልክም፣ ገደብ፣ ደንበርም ያልሰራችሁለት ዬአፓርታይዳዊ ጭካኔያችሁ ግፍ ዬፈጠረው ዬራሱ ዬበቃኝ አቅም ብቻ ነው። ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊና አቅሙ ከላይ ወደታቻ ሳይሆን፤ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ በሃዘን ዬታቆረው ዕንባ ዬፈጠረው ዬበቃኝ ዬችሎት አደባባይ ነው።
አሁን ማን ይሙት ነገረ አማራ ለአ/ግንቦት ሰባት ዬትግሉ ፒላር ሆኖ በማኒፌስቶ ደረጃ ክብር ያገኛል ብሎ መገመት ህልውናችሁ ደመነፍስ መሆኑን ያመለክታል። ዬተፎካካሪያችሁ ዬብቃት ብልት ዬትላይ ስለመሆኑ ገና አልተጸነሳችሁም፤ ተጸንሰናል ብትሉም እጭ ላይ ናችሁ ያላችሁት። ሌላው አውሮፖ ኮሚሽን ፓርላሜንት ላይ አጀንዳ በሆነች ነበር እሷ ሆነች ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ። ዬአማራ ተጋድሎ ቀለማም ዕውቅናም በላቀ ሁኔታ በተሰጠው።
… ይልቅ ንፋስ በነፈሰ ቁጥር ዬፕሬዚዳንት ኢሳያስን ሌጋሲ ካለአቅሙ - አታንጠራሩት። በጸረ አማራነት ደግሞ ፅዋችሁ አንድ ነው። „አድጊ¡“ ነው እምንባለው አይደል? ቻዮች ስለሆን ነው ዬተገፋትን - እናንተ ዬመታገያ መተንፈሻ ዬሀገረ ኢትዮዽያን ብትን አፈር ዬነሳችኋቸው - ዬራሳችን ወገኖች „ዬመፍትሄ መድህናችን ብለው ለሚመርጧት ኤርትራ“ ለፍላጎት ማረፈያ መሆኗ ሊያስመሰግናት እንጂ ሊያስወቅሳት አይገባም በማለት ስንሟገት ዬኖርው እንጂ፤ ለአማራ ህዝብ ዬሁለታችሁ ዕቁብ ዕዳ ከፋይ መሆን ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም።
በማንኛውም ሁኔታ ጥቃታችን ዬሚታለምልን ስለመሆናችን ጠንቅቀን እናውቃለን። ዬክህሎት ክሳትም ዬለብንም። ዬተመክሮ ድርቀትም ዬለብንም። እንደ እናንተ ጣሪያ ባያስነካንም ውስጣችን ያለውን ተቀማጭ ብልህ ጥሪት አሳምረን እናውቃለን። ሰላላ መላላ፤ ወይንም ስውር ፍላጎትም ዬለንም። መሪያችን ግልጽነትና ቀጥተኝነት ብቻ ነው። ተሰውሮ ጓሮለጓሮ ዬሚሄድ ስብዕና አልፈጠረልንም። „አማራነት ይከበር ነው!“ መሪያችን።
ስለሆነም አብሶ ተግባራችን ሆነ ሙያችን - ኑሯችን ፖለቲካ ሆኖ ላሰደገን ህሊና ከተገባው በላይ በቂ ዕውቀት አለን። በነገረ ኤርትራ ይሁን፤ በነገረ ህውሃት - ትምህርት ቤት ገብተን ዬሰለጥንበትም ነው። ዬኢትዮዽያ ታሪክና ፈተናዎቹን። ኑረንበታል። ይልቅ ዛፋም፣ ቅጠሉም፤ ወንዙም፤ ነጎድጓዱም ሆነ መብረቁ ባንፏጩ ቁጥር ከሽብር ጋር - አታለካልኩት። ንዝረታችሁን ለማስታገስ ደም ጠማኝም አትሁኑ። ጽድቅና ኩነኔ መኖሩን ስለማወቃችሁ ባላውቅም፤ በሥራችሁ ዬታህሳስ 10,1948ቱን ዬዓለም-ዓቀፋን ድንጋጌ ፈተና ላይ ጥላችሁታል። ልብ ግዢ ቢኖረው መግዛት ዬነበረባቸው ፀረ ሰዎች በሆኑ ነበር።
• በበደሉ ልክ ሊቀጣ ዬሚገባው - ትዕቢት።
ወደ ዋናው እርዕሴ ገመግባቴ በፊት ትንሽ በምልሰት ዬደረስኩበትን ዘመን ገፅታ ልነግራችሁ - እፈልጋለሁ። ስለምን? ከዛሬው ዬትዕቢት ጋሬ ጋር ስለሚመሳሰል። በደርግ ጊዜ ሻለቃ ገ /ህይወት ዬሚባሉ ዬደርግ አባል ነበሩ። በብሄረሰባቸው ትግሬ ነበሩ።
ዬስሜን አውራጃ ዋና አስተዳዳሪ ነበሩ። ሻለቃ መላኩ ተፈራ ለትግራዊው ሻለቃ ገብርህይወት ዬወገራና ዬጭልጋ አውራጃዎችን ዬበላይ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው። ጭልጋም ሆነ ወገራ ዬዬራሳቸው አስተዳዳሪዎች ነበሯቸው። ሁለቱም ጎንደሬዎች - አማራዎች ነበሩ። ከስሜን ጎንደር ዬቀረው ጉንደር ዙሪያ አውራጃ ብቻ ነበር።
ከዛማ ምኑ ይነገራል ዬአማራ ገበሬ ልጅ ዬሴት ቀሚስ እዬለበሰ በዬገብያው ይሰቀል ነበር። በገጠር ከተሞች ምክትል ወረዳ ይባሉ በነበሩት ማለት ነው። ቅዳሜ ብቻ አልነበረም ዬገብያው ቀን ሰኞ ገብያ፣ ማክሰኞ ገብያ፣ እሮቡ ገብያ፣ ሃሙሱ ገብያ፣ አርብ ደግሞ ዬመንገድ ገብያ ዬሚባል ዬጎንደር ባህላዊ ገብያ አለ። መንገድ ላይ ገበሬው በሚመጣበት በር ላይ ጠብቆ መንገድ ላይ መገበያዬት። ሻጩም ሸማቹም ድርድሩም - በቁም።
በዚህ ሁሉ ቀናት ሳምንት ይዞ እስ ከሳምንት ገበሬ ዬሴት ቀሚስ እዬለበሰ በገመድ ዬአማራ ገበሬ ይንጠለጠላል። በሦስቱ አውራጃዎች በስሜን፣ በወገራና በጭልጋ አውራጃ። ይህን ግፍ ለማስቆም ከእኔ በተምክሮም በዕድሜም ዬበሰሉ ሁለት ወንድ ጓዶቼ ጋር ትግል ጀመርን። ከታዳጊ ወጣትነቴ ጀምሮ ጉሩፖቼ ወንዶች ነበሩ።
እናላችሁ መጨረሻቸው በወገራ አውራጃ ሥር ከነበረው ከሰቲት ሁመራ ተነስተው ወደ ጎንደር በረራ ሲያደርጉ አዬር ላይ አመድ ሆኑ። ዬወገራ አውራጃ ባይጨመርላቸው ሰቲት ግዛታቸው ስላልሆነ አይሄዱም ነበር። ለዚህ ዓይነት ዬሰማይ ቅጣትም አይዳረጉም ነበር።
ቅምጦቻቸው ወደ ሃያ ይሆኑ ነበር፤ ጎንደር ከተማ ብቻ ስንት ድንኳን ተጥሎ ነበር መሰላችሁ። በዛን ጊዜ ዲታነታቸው ዬዛሬው ሽህ አላሙዲን ምስጋን ይንሳው። በደም ዬጨቀዬ ብር በሽ ነበር። አውሬነታታቸው ልክ ስላልነበረው እርምጃቸው ሰቅጣጭ ነበር። እሳቸው ወደ ጭልጋ ሲንቀሳቀሱ ዬፖለቲካ ፖርቲው መሪዎች ደውለው ያስጠነቅቁናል። ቤት እንዳናድር።
ከከተማ ዞር ብለን እንድንሰነብት። ሻለቃ መላኩ ላጭር ጊዜ ውጪ ሀገር ሲሄዱ ብልሆቹ ሁለታችን ዬካቲት 66 ፖለቲካ ትምህርት ቤት፣ አንዱን ጀርመን ሀገር ለትምህርት ላኩን። - በተለይ ጀርመን ሀገር ዬተላከው ወንድሜ እና እኔ ዬተሳለብን ያውቁ ዬነበሩ ሊቆች እሱ ከትምህርት ሲመለስ ሽዋ፣ እኔ ከዬካቲት 66 ፖለቲካ ትምህርት ቤት ስወጣ ወደ አርሲ ዬተመደብኩበት ምክንያትም በዚህ ነበር።
ስለምን ሻለቃ መላኩ ተፈራ ይህን ያህል ስልጣን እንደ ሰጧቸው ዛሬ ድረስ አይገባኝም። ዬሚገርመው ጋይንት ላይ መቶ አለቃ አክሊሉ ዬሚባሉ ቁጡ ዬደርግ አባል አስተዳዳሪ ነበሩ። እሳቸው አማራ ናቸው - ወሎዬ። ለሳቸው ግን ሻለቃ መላኩ ተፈራ ሊቦ አውራጃንና ደብረታቦር አውራጃን አልደረቡላቸውም። ለምን? አላውቅም።
ዛሬ ደግሞ በአቶ አባይ ወልዱ ጥጋብ ወጣት ንግስት ይርጋን ጨምሮ 20,000 ዬአማራ ወጣቶች ለእስር - ቁጥር ያልወጣላቸው በአማራ መሬት ላይ ሞት፤ ታሪካዊው ዬቅዳሜ ገብያ ለቃጠሎ፣ ዬአንባ ጊዮርጊስ ህፃናት በሱዳን ወታደር ለእልቂት ተዳረጉ።
ለእኔ እንደሚገባኝ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጎርማዳ ማሰሮ ናቸው። በስውር ዬትግራዩ አድመኛ አቶ አባይ ወልዱ ዬአማራው መስተዳድር ተብዬውን በመጨመር ዬበላይ ፕሬዚዳንት ናቸው ባይ ነኝ። ልክ ሻለቃ መላኩ ተፈራ ስሜን አውራጃ ላይበቃ ጭልጋና ወገራን ዬዕንባ ቤተኛ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ዛሬም መጋዙ ተስሎ ተሰጥቷል።
በቃ! አማራ ልጆቹም ባለቤት አልሆኑለትም፣ ዬአማራ ልጆች ቦታ ሲያገኙ በዬዘመኑ አማራውን ሲያሳርዱት ኖሩ - ዛሬም ይሄው እዬታዬ ነው። ከአግላዮቹ ጋር ከትመው ፍዳውን ያስከፍሉታል። ኦ! አምላኬ እባክህን አቁርለት ለዛ አሳረኛ - ዬመከራ ቀለብኛ።
ስለሆነም ለሺህ ዬአማራ ልጆች ዬጥቃት ሰለባነት ዬዳረገው ሽፍታ አቶ አባይ ወልዱ ወይንስ „አማራነት አሸባሪ አይደለም“ ብላ በአደባባይ በባዶ እጇ ዬሞገተቻችሁ ንግስት ይርጋ? መቀጣት፣ መታሰር ያለበት አሸባሪው፣ ዬህዝብን ሰላም ዬቀማው፤ ዬህዝብን ሃይማኖታዊ ዕሴት ያስተጓጎለው ወይንስ ክብሪትና ቤንዚን፣ ፈንጅና ቦንብ ዬያዙ ወንበዴ አምላኪዎችን አደራጅቶ ዬህዝብን አብሮነት በግፍ ዬቀቀለው አረመኔያዊ መንፈስ።
የአሸባሪው ዬአቶ አባይ ወልዱ ዬተንጠራራ ትዕቢት ገመናችሁን እንደ ቄጤማ ነው - ዬነሰነሰላችሁ። ዬማንፌስቷቹህ ህልውን ዬምስጥ ማድመቄያ - ሆኖላችኋል። ብታውቁት። በአሸባሪያችሁ በአቶ አባይ ወልዱ ላይ ዬምትወስዱት ቆራጥ እርምጃ ሆነ፤ ዬምታሳዩት ቸለልተኝነት ዬነገን ዬትግራይ ህፃናት ሰላማዊ ህይወት - ይወስናል። እኔ ነኝ ዬሚል ህግ ይሁን ማንፌስቶ ይህንን ዬጥቃት ምጥ ሊገታ ወይንም ሊያስቆም አይችልም።
ማነው ህግ ጣሹ? ማነው ዬሰው ድንበር ጥሶ አመፃ ያስነሳው? ማነው ጥጋቡ ዬፈላበት? ማነው ዬጥላቻ ደራጎን? ማነው ባለ ሥልጣኑ? ማነው ባለ ጊዜው? ማን በፈጠረው ችግር ይሆን ተሸፍናችሁ ዬኖራችሁበት ዬፌክ ዘመን ክንንቡ ከልቶ ባንደበታችሁ ከ100% ፐርሰንት ቁልቁል 51% ላይ ያወረዳችሁ በዚህ እኮ ዬአለምን ሚዲያ ሆነ ዬአለሙን መሪ ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ኦባማን ተማጽናችሁ - አሳስታችኋል። ትልቅ ወንጀል እኮ ነው ይሄ።
ዬዚህ ሁሉ ረግረግ አቡኪና ጋጋሪ ጃርቱ ዬአቶ አባይ ወልዱ ጣሪያ ያልበቃው መታበይና ዬኃላፊነት ብቃት ሽሁራር ውጤት ነው። ልክንም አለማወቅ። ስለዚህ አቅሙ ካላችሁ ጃርታችሁን ፍርድ ቤት ገትሩ። አሸባሪው እሳቸው ናቸው።
አብሮ ተጋብቶና ተዋልዶ ተከባብሮና ተቻችሎ ዬኖረውን ህዝብ ሙሉ ዕሴቱን - ያጋዬ፤ ያነደደ - ዬበቀል፤ ዬቁርሾ - አጋፋሪ። እሳቸውን ጠይቁ ደም ለማድረቅ ካስፈለጋችሁ። ላይ ታች ዬሚዘለውን ኢ - ፍትኃዊ፤ ጫካዊ ህጋችሁንም አደብ አስገዙት። ጥጋቡም ልክ ይኑረው።
• ልብ … ካለ?
ዬጎንደር ልጅ በስፋት ውጪ ሀገር ወጥቷል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ውጪ ሀገር ቤተሰቡ አለ። ስለዚህ ውጪ ካለው ቤተሰቡ ጋር መገናኘቱም ተፈጥሯዊ ነው። ይህን ቤተሰባዊ መስመር ዬእናንተን አውሪያዊ መንፈስ በመስጋት ይቅርብኝ ብለው ከቤተሰቦቻቸው በስልክ እንኳን ተለይተው ከተፈጠሩት ጥቂት ዬናፍቆት ምንዱባን በስተቀር። ይህ እኮ ብታውቁት „ብዙ … ተባዙ“ ያለው ዬወንጌል ቃል ዶግማ ነበር። ዬፈጣሪ ቃል።
ግን በእናንተ ቤት ለምህረት ድርድር ዬሚቀርብ ዬሰባዕዊነት እንጥፍጣፌ አልተፈጠረም። በምንም ቃልና ቋንቋ ዬአገዛዛችሁ ዬጭካኔ መርህ ሊገለጽ አይችልም። ቢያንስ ሰው ከቤተሰቡ ጋር እንዴት በስልክ መገናኘት ይነፈጋል? ይሄ ራሱ ወንጀል ነው። በዓለም ፍርድ ቤት ዬሚስቀጣ። ሰውን እኮ በስጋት ጭስ መንፈሱን ዬባዶ ስድስት ሰለባ - አድርጋችሁታል። ኧረ! ልክ ይኑረው ጥጋቡ። ማዕት ያወርዳል ለነገ ወዲያ ….
ሌላው ትልቁ ነገር ሀገራዊ ጉዳይ ለቤተሰብ ነግሮ ቤተሰብን አጋር ማድረግ አይቻልም። „አብደኃል? ጤና ዬለሽም“ ነው ዬሚለው - ቤተሰብ። ጎንደር ዬራሱ ዬሆነ ዬመኖር ጥበብ አለው። በራስ መንፈስ ውስጥ መኖር።
ይህ ይመስለኛል ዬጎንደር ሚስጢር። ጎንደሬዎች ዬመሰረቷቸው ሰብዕዊ ድርጅቶች ይሁን ዬፖለቲካ ድርጅቶች ውጪ ሀገር አሉ። እና ሥርጉተ ውጪ ሀገር ነው ዬምትኖር። ከልካይ ዬላትም። ግን በእነሱ መንፈስ ውስጥ ሳይሆን በራሷ መንፈስ ውስጥ ነው ዬምትኖረው።
ዬወንዜ ልጆች ስለመሰረቱት ወይንም አማራ ስለሆኑ ቅሬታዬን ከመፃፍ አጋጅ ዬለኝም። ዬተፈጠሩበትን ዕሴት ውስጣቸውን ስለሚያውቀው በጸጋ ነው ዬሚቀበሉት። እነሱም ቢሆኑ ዬማይመቻቸው ካለ አይምሩኝም። አላነበባችሁም ዬሞረሽ ወገኔ ለአማራው ዬበኽር ልጅ ዬሆነውን፣ አንድ ዓይኑን (ዐድራ) ዐማራ ድምጽ ራዲዮን በወሳኝ ወቅት ስቅጠቅጠው፤ ሳብጠለጥለው።
ስለዚህም ማንም - ዬዬትኛውም ድርጅት አባል ዬሆነ ጎንደር መሬት ላይ አባል ማፍራት ሆነ መመልመል በሞፈር ዘመት በፍጹም አይችልም። ፍላጎቱንም መጫን አይችልም። ዬተከለከለ መንገድ ነው። ዬወልቃይትና ዬጠገዴ ዬአማራ ዬማንነት አስፈጻሚ ኮሚቲዎችን ዬጎንደሩ ከተማ ጉባኤ „ዬዬትኛው ዬፖለቲካ ድርጅት አባል ናችሁ?“ ብሎ ዬጠዬቀው ለዚህ ነበር።
በጎንደሮች ልብ ድንገት ዘው ዬሚል መጤ ማንነት ዬለም። ስንት ጊዜ ይነገራችሁ። ይህንን ዬመፍታት አቅም ይስጣችሁ ፈጣሪ - ለወያኔ ሃርነት ትግራይ መሳፍንታት። እንኳንስ እነሱ ጎንደር መሬቱ ላይ ሆነው፤ ኮሜቲው ዬደረሰበትን አብሶ ዬሰቲቱ ድራማ ሪፖርቱን ሳዳምጥ ልቤን ነው ያጨሰው። ይህ ጥቃት ነው ዬአማራውን ተጋድሎ ሆነ መሪዎችን እንዲሁም አክቲቢስቶችን እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው እንዲነሱ ያደረገው። ይገባቸዋልም።
እንደ ሰደድ እሳት ነው ውስጥን ይበላል። ዬሚቻል አይደለም። ይፈትናል። ቀላል አይደለም ዬቀዬን ጥቃት ሰምቶ ትዕግስትን ስንቅ ለማድረግ።
ጥቃትን በልቶ፤ ጥቃትን ጠጥቶ፣ ጥቃትን ተጎንጭቶ፣ ጥቃትን አግስቶ፣ ጥቃትን አስመችቶ ዬሚኖር ትውልድን ዬአማራ እናት አትጸንስም። አይታለምም! ከጥቃት ጋር ተስማምቶ ከመኖር ሞት በስንት ጣሙ። በእኔ ውስጥ ያለውን ዬሚንቀለቀል ስሜትንም ነው እዬነገርኳችሁ ያለው። ይህ ዬተፈጥሮ ጸጋ እንጂ አሸባሪነት ከቶውንም ሊሆን አይችልም። ዬሥነ - ተፈጥሮ ፍልስፍናዎችን ለማንበብ - ሞክሩ። ዬምትጭኑት ዬመስቃ ጭነት ምን ያህል ሊያስጉዛችሁ እንደሚችል - ይተረጉምላችኋል። እረብም በሉ!
• እርገት ይሁን።
ወጣትነት ሁለመናነት ነው። ወጣትነት ጀግንነት ነው። ወጣትነት ቀዳሚነት ነው። ወጣትነት ትንታግነት ነው። ወጣትነት ዬአቅም ሙላትነት ነው። ወጣትነት ዬማወቅ ጉጉተኝነት ነው። ወጣትነት ዬለውጥ ሃዋርያዊነት ነው። ወጣትነት ዬፍትኃዊነት አርማ ተሟጋችነት ነው። ወጣትነት ጀግንነት ነው። አዎን! ወጣትነት አፍላነትና ችኩልነትም ነው።
ወጣትነት ድፍረት ነው። ይህቺ ዬምታዮት ወጣት ምናችሁን ፈርታ ይሆን ዬሌላ ማኒፌስቶ ዓርማ ይዛ ያልወጣችው። ወጣትነትና ፍርሃት፤ አይተዋወቁም ወጣት ሁናችሁ ታውቁታላችሁ። ለእናንተ ድሎት፤ ሹሞትና መዳሊያ ወጣትነቱን ላስበላው ለመሪዋ ዓላማ መሰለፏን እዩት። ዬጀግና ኮነሬል ደመቀ ዘውዴን ምስል፣ በራሷ ወጪ፣ በራሷ መንፈስ ውሳኔ „አማራነት አሸባሪ አይደለም!“ በማለት ዘመን አሻጋሪ ትንግርት ነው ዬሠራችው። ጫካውን ብትፈልገው፣ አርበኞች ግንቦትን ብትፈልግ ዬጫካ ጉዞ ህይወታችን እኮ ነው።
ዒላማ መለማመድም። ነፍጠኛ አይደለን! ስለሆነም በአንድ ጀንበር መንገዷን ፋት አድርጋ - ኤርትራ መግባት ትችል ነበር። ከአርባ ምንጭ፣ ከአዲሰ አበባ ተነስተው ዬገቡ አሉ - እኮ እንኳንስ - ከጎንደር። ምን ዬገደዳት ይመስላችኋል?
ስለዚህም ክሳችሁ ዬድቡሽት ቤት ነው። ያልተገባ ዕውቅና መስጠትም ጎጅነቱ እናንተን እንጂ እሷማ ዬቆረጠችበት መንገዷ ነው። ጥያቄዋ „አማራነት ይከበር ነው!“ ጥያቄዋን መልሱ። አታዳድጡ! ዬሚያባንናችሁ መፈንስ ጋር ለመፋታት ዬፍትህ ክታብ እሰሩ። ወይ ደግሞ ከተክልዬ መዋት ሁለት ሰባቷን ….
በመጨረሻ …. አስገድዳችሁ አርበኞች ግንቦት ሰባት ነኝ ዬማሰኘቱንም እንካ ስላንትያ እንጠብቃለን። ቀጣዩ ልፋጭ ትወናችሁ ይሄው ነውና!
„አማራነት አሸባሪነት አይደለም!“
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።





  • 47m 
    Shared with Public
    ዬመሸበት የፍሪንባ ቤተኛ ይህን እያለን ነው። አለማፈራቸው ይገርመኛል እነ ማህበረ የሞጋሳ ተጠማቂ።

    አስተያየቶች

    ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

    ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

    እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

    አብይ ኬኛ መቅድም።