አክብሮት የፍቅር ተፈጥሮ እንደምን ሊሆን ቻለ?

 

አክብሮት የፍቅር ተፈጥሮ እንደምን ሊሆን ቻለ?
#በርግጥም አክብሮት የፍቅር ተፈጥሮ አካል ነው።
#ስትወደው ታከብረዋለህ።
#ስትወደው ትንከባከበዋለህ ያከበርከውን ሰብዕና፤ ማህበረሰብ፤ ተቋም አመክንዮም።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ"
 

 
** መነሻ በር።
አቨይ አባቴ መምህር እና የቤተ መፃህፍት ሰው ነበር። የዝምታ ንጉሥ ነበር። የአበይን የበቃ ሳቅ አይቼ አላውቅም። የበሞቴ ልዕልቴ የእሽታ ንግሥቴ የእቭዬ ሰብዕና ደግሞ ጠሐይ ነው። ሳቂተኛ ናት። እንዲያውም እናቷ ጢጢዬ አፍሽ የሰፋው ከሳቅ ብዛት ነው ትላታለች። እኔም የሁለቱን አጣምሬ ይዣለሁኝ። ያልሳቅኩበት ፎቶ የለም።
ከልቤ ከሆነ ጎረቤቶቼ አብዛኛውን ጊዜ እረፍት ሄዳለች ብለው ስለሚያስቡ ከሩሜ የፀጥታ ግርማ ብዛት፦ ሳቄን ስለቀው ደግሞ ያን ያህል አውዳቸውን አለች ያሰኛቸዋል። ድሮ ድሮ በሩቅ ሰው ሳይ እስቅ ነበር። ዛሬ ዘመኑ አስተማረኝ። ወደ ፍቅር ተፈጥሮም እንዳዘነብል ዬረዳኝ ይኽው ነው። ድሮ ባቡር ውስጥ ሆነ አውቶብስ ውስጥ ባዶ ቦታ ካገኜሁ አስፈቅጄ መቀመጥ ነበር። ዛሬ እንደዛ ዬለም። ሰው የሌለበት ወንበር ፈልጌ እቀመጣለሁኝ። የእኛ ቀለም ያላቸው ሁሉ ዕይታቸው ያስፈራል። አያስጠጋም። ይገፈትራል።
ልጅ እያለን እናታችን "እጃችሁን ዘርጉ" ትለናለች። እንዘረጋለን። ከዛ "ጣታችሁን እዩ" ትለናለች። እናውቀዋለን እንላለን። "አታውቁትም" እዩት ትለናለች። እሺ ብለን መዳፋችን አገላብጠን እናያለን። ከዛ "ምን አያችሁ ብላ ትጠይቀናለች።" ጣት መዳፍ እንላታለን። ሌላስ ሌላ ምንም እንላታለን። ወይ ቀድማ የነገረችን እናስታውሳታለን።
እሷ ጣቶቻችን እያሻሸች ትንሽ እጣ የቀለበት እጣት ጠቋሚ እጣት አውራ እጣ የሚዛን እጣት እያለች ታሰዬን እና። "ትንሽ እጣት በቀለበት እጣት አይቀናም፤ መሃል ሚዛን እጣትም ጠቋሚ እጣትን ልቅደም ለጥቆማ አይልም። ሁሉም የተፈጠሩበት አላቸው። አንዱ አንዱን አክብሮ፤፦አንዱን አንዱን ሳይቀናበት ሥራን ፈጥረው ተባብረው ያኖሩናል። ሁሉም የመዳፍ ውጤት ነው። ጤፋ ቢመረት፤ ቢፈጭ ቢቦካ ቢጋገር ማባያ ቢኖረውም። አሁን እንጀራ የሰው እጅ ውጤት ነው። የሆነው ግን እጣቶቻችን ተከባብረው ሳይቀናኑ የፈጠሩት ስለሆነ ነው። በሰው አትቅኑ፤ ሰውንም ተፈጥሯችሁንም አክብሩ ትላለች።" አያችሁ በዛሬ ውስጥ #ነገን እንደምን እንደመራችው።
ከእኛ ቤት ሰው መጥቶ እንግዳ ለሽኝት ስንወጣ ሁላችን አስፓልቱን ሞልተን ነው። አንዳንድ ጊዜ እንግዳችነን ከቤቱ ድረስ እናደርሰዋለን። ጎንደር የባህል አውራ ነው። ሽሮ፤ ድልህ፤ አዋዜ፤፦በሶ፤ ጠላ ተዘጋጅቶ ለጎረቤት ለወዳጅ ቅመሱ አይቀሬ ነው። ሰሞኑን ከህማማት በፊት የዓመት ድልህ ይዘጋጃል። እናም ለሠፈር ይታደላል።
ይህን ጊዜ እሽቅድድም ነው እኔ ላድርስ እኔ ላድርስ። ሌላ ጋብቻ የሚፈልግ ከኖረም ይታጫል። ለዛም እሽቅድድም ነው። ደስታ ያገኜ ካለም የታጨም ለደስታ እንሳላለን። ከባለደስታው በላይ እኛ እንሆናለን። ለምን? ቤት ውስጥ በዛሬ ውስጥ ነገን የመምራት ጥበብ በቅንነት በህሊናችን ሰሌዳ ስለተሰነደ ስለታነፀ። ለዚህ እኮ ነው ያለ ደንበር እኔ ለማንኛውም ሰው በገፍ ስመሰክር ስማገድ የኖርኩት።
#መሬት ትከበር የቤተሰቤ ትውፊት ነው።
አባዬ መላዕከ ብርሃን ነበር። ከእኛ ቤት ሦስት መላከ ብርሃናት አራት መናኩሳት፤ ሁለት ደናግል ገዳማውያን ነበሩ። እና አባዬ በሥጋ ሲለይ ሰኔሉን፤ መገነዣውን እራሱን አዘጋጅቶ ልጆቹን እና የልጅ ልጆቹን ጠርቶ መርቆ ነበር ወደ መኝታው ሄዶ በሥጋ ዬተለዬው። እና አባዬ ለልጆቹ ለልጅ ልጆቹ ያወረሰው "መሬትን አትደብድቡ፤ ተጠንቅቃችሁ ተራመዱ" እያለ ነበር። እኔ አልደረስኩበትም ግን እናቴ ልዩ የልጅልጁ ሥለነበረች ውርሱን በእኛ ህይወት አስቀጥላለች።
በህይወቴ በርም መስኮትም ስዘጋም ስከፍትም በዝግታ ነው። መሬትን ስረግጣትም። መሬትን ስታከብር ለመሬት መኖር፦ መኖርን የተቀበወው የአዳም እና የህይዋን ፀጋ እንዳይተንብህ አስበህ ሊሆን ይገባል። መሬት ስትከበር ፍጥረታት ሁሉ ሰላም ያገኙበታል። ለመሬት ንጉሦዋ የፈጠራት አስተዳዳሪዋ ሰው፦ #እረኛዋ የአገር መሪ ነው።
ዬአስተዳደግ መበደል ነው መሬት እና ተፈጥሯዋን አክባሪዋን እና አለልጣኟን ዬሰው ልጅ በስቃይ፤ በሰቆቃ ውስጥ የሚማስኑት። አሁን በዓለማችን የምናዬው ምስቅልቅል፤ በመሬታችን ላይ ያለው የአማራ ዬምፃዕት ቀናት፤ ዘመናት …… ወራታት……… ሁሉ በዛሬ ውስጥ #ነገን የመምራት አቅም ክሳት ያመጣው ነው።
መሬት እሳት ይነድባታል። ደም ይጎርፍባታል። የተረሱት ዬ40 ዬሻሸመኔ ሰማዕታት የደም ጎርፍ ልከውልኝ አይቸዋለሁኝ። ለቆሙባት መሬት ለተፈጠሩላት መሬት አክብሮት ዬለላቸው ግብዞች ናቸው በዛሬ ውስጥ ነገን መምራት ተስኗቸው ዋይታ አምራች ሆነው ተስፋን ሲነቅሉ የምናዬው። ለምን? ያደጉበት ቤት ስለሚወስነው። የት ያምጡት? ዬአስተዳደግ መበደል አብዝቶ በህወሃት እና በኦነግ ሊቃናት አሉ።
ከከበረ - ቤተሰብ፤ ከከበረ - ሰብዕና በዛሬ ውስጥ ነገር አሳምሮ ቀጥቶ መምራት ማስተዳደር ይቻላል። ለብዙ ነገር ደብረ ማርቆስ ምርጫዬ ነው። ማዕከላዊ የሰላም ቀጠና ነው። ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎም ጎጃም ንጥር ነው። እና እግዚአብሄር ይስጥልኝ ለማለት ከመተከል ምንም ወላጅ የሌላቸውን #ሦስት ህፃናትን ማርቆስ ላይ ለማሳደግ ፈለግሁኝ። ሁነኛ አገኜሁኝ። ፕሮጀክቱን ላኩኝ። በመሃል ባልና ሚስቱ ታመሙበኝ። እና ቀረ። እንጂ ዘላቂ ዬትውልድ ግንባታ አህዱ ከአጋዥ ፕሮጀክት ጋር አልሜ ነበር። ልጅ እንዴት ትውልድ እንደምን መሠረቱ እንደሚጣል አሳያቸው ነበር።
ለምን? ነገ የሚገኘው በዛሬ የሰከነ ተግባር ነው። የቅርብ አማካሪዬ አሜን የሚል ሥም አውጥቸላታለሁኝ። እሷ ጋር በፍቅር ተፈጥሮ ህግጋት ላይ ብዙ ተወያይተናል። ክሬዚ ሴት ትለኛለች። እና ሥራዋን ትታ የልጆችን ዬጀመረችው በእኔ ተጽዕኖ ነበር። ትውልድ ነገን መርቶ ዬሚችልበት መስመሩ ልጆች ላይ መሥራት ሲገባ ብቻ ይሆናል።
አንድ ጊዜ ለዬት ያለ ነገር አብረን ፈጽመን በሌላ አገር ሥም የተደነቀችበትን አመክንዮ ለህትምትም ለአመታዊ ሪፖርትም አብቅታዋለች። እሷ ስትለቅ በቦታዋ ሰው ተተካ። ነገር ግን የቀደሙ ባልደረባዋ ይህቺን ሴት አውርሽኝ ተብላ እኔም ፈቅጄ አምስት ዓመት አብረን አለን። በወር አንድ ጊዜ እንገናኛለን። አጀንዳችን ኢትዮጵያ ናት።
ሁልጊዜ በወር ውስጥ ያገኘኋቸውን ድንቅ ሰወች እነግራታለሁኝ። "ለንቺ ማን ጎርብጦሽ" ያውቃል። ሁሉም መልካምሽ ሁሉም ክብርሽ ነው ትለኛለች። አሁን በቅርቡ የት አመጣሽው ይህን አወንታዊነት ብላ ጠዬቀችኝ። ስደተኛ ቢሮም፤ አምንስቲም የሠራች ናት። ከወላጅ እናቴ ነው አልኳት። እና ዬማምንበትን ገለጽኩላት። እናት የፊደል ገበታ። እናት የመጀሪያዋ ትምህርት ቤት ናትም አልኳት። ብዙም ጽፌበታለሁኝ። ለዛ ነው ሃዘንሽን በእኔ አቅም ላጽናናሽ ያልቻልኩት አለችኝ። ዕንባዬን የተጋራች ዕንቁዬም ናት።
የሆነ ሆኖ በዛሬ ውስጥ ነገ የሚመራው በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነገን በቅጡ በትክክል ሊመሩ የሚችሉ አወንታዊነት፤ ቅንነት፤ ፍቅራዊነት፤ ተፈጥሯዊነት፦ ሰዋዊነትን አክብሮ ከራስ በላይ መውደድ ሲቻል ብቻ ይሆናል። ይህን ለማስቻል በዬትኛው መስመር ቀና ይሆናል ……ቀጣዩ ፁሁፍ ይመልሰዋል።
አቨይ እና እቭዬ ሆይ! ነፍሳችሁን በአፀደ ገነት ያኑርልኝ። አሜን። እኔን ሰጣችሁኝ። በእኔ ውስጥ እላፊ እንዳልሄድ ቀጣችሁኝ። ተመስገን።
ክብሮቼ ዕለቱን በዚህ እርጋ ልበለው።
መሸቢያ ጊዜ። ደህና ሁኑልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergure©Selaseie
08/04/2023
ዕውነት ሠራዊት የለውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።