#በአማራነት #ቃሉ ኢትዮጵያዊነት ነው።
የአቅሙ ጣዝማም ኢትዮጵያዊነት ነው። ጉዞው የመስቀል የሆነውም ለዚህ ነው። መስቀል ስል የእስልምና ዕምነት ተከታይ ወገኖቼ አይክፋችሁ። ጉዞው መከራን መሸከም ነው ለማለት ነው።
ኢትዮጵያዊነትን ያዋህደ ተፈጥሮ #ለአናርኪዝም ቦታ አይኖረውም። ፈጽሞ። የዓለም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አዩ፣ አዩ አንድም ቦታ በአማራ ተጋድሎ አናርኪዝም፣ ጭካኔ፣ አረማዊነት አጡ። እናም #በባዶ #ከሰሱ።
የአማራ ህዝብ በሚበደለው ልክ አፀፋ ልመልስ ቢል አይደለም ኢትዮጵያ መካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ህውከት ይሆን ነበር። የአማራ ህዝብ የመቻል አቅም ኢትዮጵያን አፅንቷል ትናንትም ዛሬም።
የአማራ ህዝብ 50 ዓመት ሙሉ በደሉን ችሎ #ችሎቱን #በአልማዝ አፅፏል። ይህ ህሊና ላለው ሁሉ ዩንቨርስቲ ነው። ዓለምን በሚመለከት ድርጅቶች አሉ ተብሎ እንጂ ተናጠላዊ ተጋድሎ በማድረግ ዝበቱን ማረቅ ይቻላል።
ህወሃት እኮ ቅራቅር ድረስ መጥቶ ሲዋጋ ጥሶ ጎንደር እገባለሁ፣ ባህርዳርን አጋያለሁ ሲል ከዕለተ ማክሰኞ እስከ ቅዳሜ የተፋለመው ህዝብ ነው። ዛሬ እነ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚበጠረቁበት ገመና ይህ ነው። ሠራዊቱ የደረሰው ቅዳሜ ነው።
ይህን የሚያስረዳ፣ ዕውነቱን የሚናገር የአማራ ተቋም የለም። የተማረውም ያልተማረውም በኦነግ ሠበር ዜና ሲቧከስ፣ የራሱን የቤት ሥራ ትቶ የሰው ቤት ሲያበጅ እንሆ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ሆነ።
ቀድሞ ነገር የዶር አብይ አህመድ ሥርዓት የአማራን በደል ዕውቅና እንዲያገኝ አይሹም። ሌላው መከራ ይሄ ነው። ለዚህ ነው ሲኦል ተቀምጦ ፃድቅ የተኮነንው። እኔ በአምንስቲ ተስፋ ከቆረጥኩ ቆዬሁ። ስለታገቱ ተማሪወች ከ6ወር በኋላ ነበር ዕውቅና የሰጡት። አምንስቲ አለ ለማለት አልችልም።
ሰባዕዊነት ገንዘብ ሆኗል። ሰባዕዊነት የባለፀጋ አገሮችን ፍላጎት ማስፈፀም ሆኗል። ለዚህ ነው ከዩክሬን እና ራሽያ ጦርነት በፊት ዓለም እንደገና መደራጀት አለባት ስል የባጀሁት። በጀርመንኛም ጽፌዋለሁኝ።
ግርም ያለኝ የተመድ የወቅቱ ፀሐፊ የዩክሬኑ የቡቻ ጉዳይ ከልባቸው እንደገባ ሲነግሩን፣ የማይካድራ፣ የአጋምሳ፣ የጊሊምሶ፣ የኮንበልቻ፣ የደሴ፣ የወርቄ፣ የአፋር 117 ህፃናት ወዘተ የህዝብ ጭፍጨፋ ግን ሠርጋቸው ነበር ማለት ነው። ዓለማችን አብዳለች ወይ ሰክራለች።
ኢትዮጵያ ትድን ዘንድ የኢትዮጵያዊነትን ቀለም ማገዝ፣ መርዳት፣ ጥግ መሆን ይጠይቃል። ያ ካልሆነ ሁሉም ንፋስ፣ አውሎ ይሆናል። ኢትዮጵያ አምላክ አላት እና።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/04/2022
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ