ምልክት።
ምልክት። ምስክር። ምድር ቁስ አይደለችም። የመንፈስ ቅዱስ ማረፊያ እንጂ! እምናረክሳትም እምናስቀጣትም
እኛው ራሳችን
ነን።
ይድረስ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ አራማጆች
በሙሉ።
ለመሪዎችም እንዲሁ ይድረስልኝ ብያለሁኝ። አዲስ አበባ ይሁን
መቀሌ፤ መቀሌ ይሁን አዲስ አበባ።
ለመሪዎችም እንዲሁ ይድረስልኝ ብያለሁኝ። አዲስ አበባ ይሁን
መቀሌ፤ መቀሌ ይሁን አዲስ አበባ።
ከሥርጉተ ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
25.03.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ)
25.03.2018 (ከጭምቷ - ሲዊዘርላንድ)
„ይህ ሕዝብ ወይም ነብይ
ካህን የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፣ አንተ ፣ --- „ሸክሙ እናንተ ናችሁ፣ እጥላችሁምአለሁ፣“ ይላል እግዚአብሄር
ትላቸዋለህ፤ „የእግዚአብሔር ሸክም የሚለውን፤ ነብይንና ካህነን ህዝብንም ያነ ሰውና ቤቱን አቃጥለዋለሁ።“
(ትንቢተ - ኤርምያስ ምዕራፍ ፳፫ ቁጥር ፴፫)
·
መነሻ።
ዛሬ ይህን ስጽፍ ወገኖቼ ሥርጉተ ሞኝት ይሉኛል።
„ሞኞች“ በሉን ብሏል ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ሰሞኑን በሰራው አንድ ወርቅ የሆነ ከግል ፍላጎት እና ዝንባሌ ጋር በፍጹም ሁኔታ ንክኪ
የሌለው የትዝብ ዕድምታው። እና ከ„ሞኞቹ“ መሃከል አባል መሆኔን አሳምሬ አውቀዋለሁኝ እንደ ማለት። ከማህበረ ኢህአዴግ ለዛውም
በሳጅን በረከት ስምዖን ፕሮግራምር መሪነት ሳይሆን ጭንቅላትም አዕምሮም ካለው ከኦህዴድ ከ„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ታላቅ ዕጹብ
ድንቅ መንፈስ ውስጥ የተጸነሰ ቅብዕ ያለው፤ ከአዲስ የሃሳብ፤ ከአዲስ ቀለም፤ ከአዲስ ገጽ፤ ከውስጥነት እኛዊነት መፍትሄ ይምጣል
ብዬ ዕምነት መጣሌ በውነቱ ሰውኛ አይደለም። ተስፋ ያለው ከፈጣሪ ዘንድ ነው። ፈጣሪም ለተስፋ „ተስፋ“ ፈጥሯል ብዬ በጽኑ አምናለሁኝ።
የለማ መንፈስ የሰንደቄ ድምጽ ነው። ሰንደቄ ደግሞ የማርያም መቀነት። መቀነቱ ደግሞ የምሥራች መባቻ ነው። „መባቻ“ ብዬ እኮ ጥፌያለሁኝ።
ኦህዴድ የፍቅር ገበታ ነው - ለሥርጉተ ሥላሴ። ስለዚህም በማያወላውል ሁኔታ ሥርጉተ - ሥላሴ ለማውያን ነኝ።
·
የመነሻዬ ዓይነታ።
„Ethiopoa ሰበር ዜና አስደንጋጭ በመቀሌ
የደረሰ
እኔ ሰውነቴ እዬተንቀጠቀጠብኝ ነው ያዳመጥኩተኝ፤
ለቅቤ ጠባሹ ኢቢሲ EBC ደግሞ የዜናው ጭራ ነበር። የምፈራው ነገር እንዳይደርስ አሁንም ስጋትን ሰንቄ ነው ብዕሬን ያነሳሁት።
የትግራይ ምድሪቱ ዛሬ ዛሬማ ታሳዝነኛለች ብዬ ጽፌ ነበር ስለ አቦይ አባይ ጸሐዬ በጻፍኩት የወግ ገበታዬ ላይ።
„የመሬት መንቀጥቀጥ“ ዜናው ቀንድ አልነበረም ለተረበኛው ኢቢሰ EBC። ጅራት ወይንም በጥሩ አማርኛ ሙጣጭ እንጂ። ሙሉውን ስልቹ ሐተታ ማድመጥ
ለማትሹ ወገኖቼ 26.39 ላይ ይጀምራል። የሰማዩ የእዮር የማስጠንቀቂያ ደወል አሳዛኝም /// አሳሳቢም ዜና። ወደ ታች ማገናዘቢያዎቼ
እና እይታዬን አክላለሁ። ሰሚ ቢገኝ። ለእኔ ኢትዮጵያዊዋ ጸሐይ ወደ ጨለማ በቀን የተቀዬረች ያህል ነው የተሰማኝ። የቤተክርስትያን
ደወሎች በራሳቸው ጊዜ ደወል እንዳሰሙ ነው የተሰማኝ። ድንግል እመቤቴ ተገልጣለች ለእኔ። እርህርሂት ውጽፍተ ወርቅ የልጅና የእናትን
ነገር ታውቀዋለች እና። ህሊና ያለው አንድ ዕጣ ነፍስ ማስተዋል ከተገኘ ቢረፍድም መታበይ እና ዝናር ሙሉ ጥይት ለሰማዩ የምህረት
መቅድመ ዓዋጁ እጅ እንዲሰጥ ይታትር ይሆናል። ተስፋ አያልቅም፤ አሁንም ተስፋ ይደረጋል - ከነሞኞች።
·
እንደ ዛሬ።
ቀኑ ፈታ ያለ ይመስላል። ጉሙኑም፤ ብርዱንም፤
ድቀቀኑንም ገፋ አድርጋ እሜቴዋ በመስኮቴ ገብታ እንዴት አደርሽ አለችኝ። ጫጉላዋ የዕውን ስለማለቁም ባትነግረኝም ፈገግታዋ ግን
ብርታትን ለግሶኛል። ዛሬ መጥታለች የኮሽ አይሏ መንደር እመቤት ጠሐይ። ረፍድ ብዬ ነበር የተነሳሁት። አምሽቶ መተኛት ልማድ ስለሆነ።
ብዕር የሚባል ጽኑ ጓደኛ ጎልቶ አውሎ ጎልቶ ያሳድራል። እርግማን ግን አይደለም ፈውስ ነው። ለዛውም የውስጥ። ይህ ሲታገድ መንፈስ
እንዴት ይነድ? ቅባዕ ተስጥቶት አንድ ዲያቆን ከቅድስና የታገደ ያህል ረመጡ ውስጥን ያጋያል። የሐገሬ የብዕር ሱሰኞች የተፈረደባቸው
የውስጥ ቋያ ይሄው ነው - ጎመራ። ከርሸሌውም አለ ይሄው የጸሐፊ አቶ ስዩም ተሾመ ብዕር እኮ ካዬናት ቀናት ተቆጠሩ። ዱላም አለበት።
መገፋቱም አለበት በራስ ሀገር ስደት። መጻፍ ጸጋ ነው። ሲሰጥ ብቻ የሚገኝ። በስልጠናም ካለሥልጠናም የሚከወን። ሥጦታው የልዑል
እግዚአብሄር ስለሆነ የሰርትፍኬት ቅደመ - ድርድር የለውም። ይህን ማገድ የፈጣሪን ሥልጣና እና ልቅና ማገድ ነው።
·
እንዲህ ነው ነው ነገሩ …
ብቻ ጥዋት ስነሳ ከድንግል መወድስ፤ ከምስብከ
ዳዊት ድምጥ በኋዋላ ዩቱብን ስከፍተው እርእሱ የዜናው ውስጤን አራደው። ድንጋጤ በወረረው ስሜት ክው አልኩኝ። ቀጥልልኝ እባክህ
እናቱ ብዬ በትሁት መንፈስ ዩቱብን ስጠይቅ ሰንክሳሩ በዛ የኢቢሲ EBC ዛዛት አቤት ሲሰለች፤ … ግን መታገስ ነበረብኝ። መጨረሻ
ላይ ልቅላቂው ነበር መደቡ የዜናው፤ እንደ ምናምንቴ ታይቷል መሰል። ስልምንም ደፈርክን ዓይነት። „ትግራይ ለዛውም መቀሌ አቅራቢያ“
ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ አንደ ነበረ ያመለክታል - ዜናው። መርዶ ነው። ጥሩ ዜና አልነበረም። መንቀጥቀጡ ኢትዮጵያ ላይ ነው ለእኔ
የሰጠኝ ፍቺ። ኢትዮጵያ ላይም ብቻም አይደለም አፍሪካንም ያካታል። ዘለግ ባለው ደግሞ ግሎባሉንም ይጨምራል። ደግነቱ ምልክት ብቻ
ነው። ስለ ምስክርነት የእዬር አደባባይ ታላቅ ነጎድጓዳማ አስፈሪ ድምጽ ነው። ኢቢሲ EBC ግን ያዬው …. ድምጹን እንደ ተራ አልባሌ
ነበር። ለእኔ ግን አልነበርም። ተሳስቼ ይሆን ብዬ ደግሞ በድጋሚ አዳመጥኩት። ጆሮዬን ማመን አቅቶት - አቃቅቶትም። በዚህ የግፍ
ብዛት ጣሪያውን ባለፈ መታበይ የሰማይ እሳት አንድ ቀን አይደለም መሰሉ ሰማያዊ ገርፍታው ምቹ ተዘውትሮ ሊመጣ ይችላል - ተምችም
ሊኖር ይችላል። ትግሉ ፈጣሪ ከፈጠረው ከፍጡሩ ጋር ነው እና። ጥፋቱ በዬዕለቱ ሳያባራ ዕንባው ወር ይዞ እስከ ወር … ዓመት ይዞ
እስከ ዓመት … እረፍት ጠፋ፤ ሞት - - እስራት - ድብደባ - አካል መጉደል - ንቅለት - ስደት … ምርር ምርምር ያደርጋል።
ዘመነ አሳንጋላ።
እስቲ ወደ ቀደመው እንመለስ … የግፉ ዱላ ዕንባ
ሌላ ዕንባን እንዳይወልድ ከሊቅ እሰከ ደቂቅ ተጩኋዋል። የዘርፉ ሊሂቅ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጆኦ ስፔስ ሳይንስ አስትሮኖሚ
ኢንስቲቲዩት ዳይሪክተር የሆኑት ዶር. አታላይ አዬለ ሙሁራዊ ትንተናቸውን በ ኢቢሲ EBC መስኮት ኮራ ደልድል ብለው እም! በግምት
አወራርደው ነግረውናል። „ቅድመ፣ ድህረ፣ ዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ“
በማለት ይህ „ዋናው ነው የምንለው ነው // የምንገምተው ከዚህ በኋዋላ
የሚመጡት አነስ ያሉ … ቅድመ ከሆነ ግን ሌላ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል“
… በማለት ባልጠራ ጭብጥ ማህል ላይ ገትረውናል።
ሆነም ቀረ የባለሙያው ትንበያ ሆነ ትንተና ለእኔ
ሰዋዊ ሥጋዊ ነው። እጅግ አነሰብኝ - ይቅርታ። መጪውን ጎምዛዛነቱ የሚከፋውን፤ የሚቀለውንም በፈርጅ በፈርጁ ለማሳዬት ያደረጉት
ጥረትም እንብዛም ነው - ለእኔ። ቅድመ ጥንቃቄ በሰውኛ የፈጣሪን ቁጣ ማስቆም ቢቻል ዛሬ በዓለም ሰለጠኑ በሚባሉት ሐገሮች ባልታሰቡ
ቅጽበቶች የሚደርሱ የተፈጥሮ ምስቅልቅሎች መልክ አስይዘው ዓለም ራሷ ነፃ ሆና ወህ ባለች ነበር።
የሙያው ሊሂቅ ዶር አታላይ አየለ ማለቴ ነው ያላዩት፤
ያላስተዋሉት፤ ያልደሰሱት አንኳር አዕማደ ሚስጢር ግን አለ። ለምን ይህን ቀን ተመረጠ? እዮር ይህን ቀን ስለምን ወሰነው? ስለምንስ
አሁን ይህ የቀስተደመና ደወል በዚህች ወቅት ተደወለ? ሌትና ቀን ምድራዊ ሰው በዬትኛው የሃሳብ አዳራሽ ውስጥ በወል ከትሟል። የ4ኪሎ
ስብሰባ ውጤት እና ዝባንዝንኬው ግምገማ ቅብጥርሶ ምንትሶ ላይ? ሚሊዮኖች ደግሞ ከቀያቸው ተነቅለው ስድት ላይ ናቸው። ህዝብ በከተመበት
አዳራሽ ውስጥ ያለውን ውሳኔ አልባ መታመስ ምጥ አይሉት ማጥ፤ ማጥ አይሉት ንጥ፤ ንጥ አይሉት እንኮሮ፤ እንኮሮ አይሉት ምንትሶ
አቅጣጫ አልቦሽ ሃሳብ በራሱ አዟሪት ሲሽከረከር ይስተዋላል። ከሰው ሸክም በላይ ነው አሁን ሁሉም ነገር።
አዲሱ ዕሳቤ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ን ብዙም
ሊቃናቱ በገሃዳዊ ትርጓሜ እንኳን ሊያስጠጉት አልቻሉም - አልደፈሩም። የኮሰኮሰው የወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ማህበርተኛ ብቻ ነው፤
ነገሬ ብሎ እዬሞገተው ያለው። ድንጋይ ውርዋሮም ያሰኘው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውን“ የውስጥ ሰላሙን በሳት እዬለኮሰ ፈተና ውስጥ
አጥምዶ ይዞታል። መደበኛ ፕሮግራም ሆኗል። የሰው እርድ መቀጠል ስላለበት። ይህ „የመሬት መንቀጥቀጥ“ ሰው ከሚያስበው በላይ ነው
- ለእኔ የሰጠኝ ትርጉም። አዲሱ የለውጥ ማዕበል ደግሞ ከሁለቱም ወገን ያልሆነ ከእሱ ትይዩም ያልሆነ፤ በፍጹም ሁኔታ በምንም እና
በማንም የቅርብ ትንበያ ጋር የማይቀራረብ ወገናዊነቱ „ሰዋዊ እና ተፈጥሯዊ“ ብቻ ነውና። ይህ „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ መንፈሱ
በራሱ ንጥረ ነገሩ ውስጥን የመዳሰስ አቅሙ ልክ የለውም - ለቅኖች። ድምጸቱ ገናና እና ሃይለኛ ማግኔት አለው።
·
ያላለቀላት።
ዛሬ ሐገር መሪ አልባ፤ ዛሬ መከራ ተጠሪ አልባ፤
ዛሬ ኑሮ እረኛ አልባ፤ ዛሬ ህይወት ሙሴ አልባ ወና ላይ የወለሌ
ገበታ ሆኗል በምድረ ኢትዮጵያ። ገና መከራዋ ያላለቀላት ናት እናት ምድር - ኢትዮጵያ። ይህን እልባት ሊሰጥ ወይንም ሰብስቦ በአንድ
ማህለቅ ሥር ማስተዳደር ከሚችል መቋጫ መድረስ አልተቻለም - ፈጽሞ። ትርምሱ የገሃዱ ዓለም ስለሆነ። ስለዚህ የንጉሦች ንጉሥ አማኑኤል
እዮር አደባባይ ላይ ሠራዊተ መላዕክትን ሰብስበቦ መከረ፤ ዘከረ፤ አስተዋለ፤ ዘንበል ብሎም ዕንባን አዳምጦ በረቂቁ ውሳኔ ሰጠ።
እንሆ … ውሳኔውን እዮር ሰጥቷል። ተስፋን ማዳን ከተስፋ ጮራ ላይ ይሁን ብሏል … ቀኑ፤ ሰዓቱ ደቂቃው ሰኮንዱ ሁሉ በፈጠሪ በማይመረመር
ጥበቡ እና ኪናዊ ክህሎቱ ፍርዱ በማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ሰሞናቱ እራሱ የተኖረ ተኑሮ፤ የተባጀ ተባጅቱ
„ፈቃዱ“ የሚል ሥም በምድረ ኢትዮጵያ ከገጠር እስከ ከተማ ገኖ ነግሦ ወጥቷል። „መተዳደሪዬን ጥማዴን እሸጥልሃለሁ“ ከእንግዲህ
እኔ ምን ያህል ልቆይ „ሁለቱንም ኩላሊቴን ውሰድ“ ከመነኮሳት ይደመጣል። ትህትና፤ ርህርህና። አብሮነት በኢትዮጵያዊነት። „ፈቃዱ“ ስለምን ሥሙ ከወትሮው ተለይቶ ነግሦ ለዛሬው ወጣ? ለዛውም ዛሬ
ምድር ቁና ሆና ሰው ወጥቶ ለመግባት እራሱንም ማመን በተሰነው ሰዓት እንደ ተለመደው ኢትዮጵያ ከፍ ብላ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ማግሥት
ሌላ የሃሳብ መሰባበስ፤ ሌላ የማዳን የወልዮሽ ርብርባዊ ተግባር፤ ሌላ የምህረት ጥሪ፤ ሌላ የአይዞህ ደውል በዓራቱ ማዕዛነት ተደመጠ።
መንግሥት ተብዬው ሲዝረክርክ ሲያራዘም ወሎ ሲያድር አንድ ቅን ስብሰብ ግን ዓለምን በደግነት ድባቡ አሰለፈ። አጀንዳ „ፈቃዱ“ ሆነ።
„ፈቃዱ“ „ሐብታም ነኝ የሰው አለ።“ ለሌላም እንቡጥ አባትነት እጁንም፤ ልቡንም ህይወቱንም ለመሰጠት በዬነ። እሰቡት „ሐብታም ነኝ የሰው።“ ማነው የሰው ድሃ? የሰው ድሃስ ምን ማድረግ ይገባዋል? ፈጣሪ አምላክ ምን
ሊያስተምር አስቦ ነው „ፈቃዱ ከማርያም በጸደቀ ወይንም በተተከለ ሥያሜ“
ዛሬ ጎልቶ ከብሮ፤ ነግሦ የሰሞኒት አጀንዳ የሆነው? በአንድ ፕሮቶኮል አልቦሽ ብሄራዊ ጥሪ። ፈጣሪ አምላክ „የፈቀደው ፈቃድ“ አለ።
„ እግዚአብሄር በአንድም በሌላም መንገድ ይናገራል። ሰው ግን አያስተውለውም“ ይላል የአማኑኤል አንደበት። የታመመው „ ከበደ“
አይደለም። ታዋቂው ተዋናይ ሥሙ „ ናደው“ አይደለም። „ፈቃዱ“ ነው።
ይህን ስንተላለፍ፤ አልፈን ተርፍን በገበርዲን
ድንጋይ መወራወር ሲጀመር እንግዲህስ በቃ አለ እዮር። ቀጣዩ መከራን ገላጭ እዮር ምልክትም ጉልበታም ደጎስ ያለ መልዕክት እንሆ
በማይከከሰ ሥልጣኑ ላከ፤ አሁን ማን በካቴና ይታሠር? አሁንስ ማን መሬቱን አንቀጠቀጥክ ተብሎ ይከሰስ? በማዕከላዊስ ማን ይደብደብ?
ማንስ ይንኮላሽ? ማንስ ጥፍሩ ይውለቅ? ማንስ ዕውነቱን ገለጥክ ተብሎ ልክ እንደ አቶ ታዬ ድንዳዓ ይታሠር? ድንጋጤ በመላ ኢትዮጵያ
ነግሶባት በኖረበት ዘመነ ኮሶ ከትግራይ በስተቀር 27 ዓመት ሙሉ ይህ የሰማይ ምልክት አይታሰብም ነበር። ዛሬ ግን በሰው እጅ ያልተሠራ
መልዕክት ተሰማዬ ሰማዬት ቀጥ ብሎ ወረደ … እጅግም አስደንጋጭ ነው።
„የአማኑኤል ቁጣ፤ ማዕብል ሊሆን ይችላል፤ በሽታ ሊሆን ይችላል፤ ወጀብ ሊሆን ኢችላል፤ ተባይ ሊሆን ይችላል፤ ጦሮ ሊሆን ይቻላል፤ የመሬት
መታወክ ሊሆን ይችላል፤ ሌትና ቀን በረድ ወይንም ዝናብ ሊሆን ይችላል፤ የሚወለዱ ህጻነት ጤና መጓደል ላይ ሊሆን ይችላል“ አይታወቅም … ማስቀረት
የሚቻለው መሬት ላይ ተደፍቶ ትቢያ ነስንሶ፣ እግዚኦታን በመታደም ብቻ ነው። ከተራራ ወርዶ አቧራ ላይ ከተነጠፈው ህዝብ ድምጽ ጋር
መገናኘት ሲቻል ብቻ ነው - ቅንነት። … በቃኝን ማወቅ። በቃችሁን ማድመጥ። አሁንም እኔ የሚጨንቀኝ ለትግራይ ህፃነት ነው። እነሱ
ቅዱስ ናቸው። ዛሬን አያውቁትም። እኛ በምን እንደምንተራመስ አይገባቸውም። ግን ዕዳ ከፋዮች እነሱ ናቸው። ለነገሩ መቼ የኢትዮጵያ
ህፃነት ሁነኛ ሃሳባችን ሆነው ሲውቁ ነው? ነገ እኮ ታስቦም አያውቅም። … ነገን ፎቅ አያድነውም። የመልካም ተግባር ውርስ እንጂ።
·
ሳስባችሁ።
የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ አምላኬዎች ሳስባችሁ
ለእናንተ ቁብ የሚሰጣችሁ የሰው ልጅ ተፈጥሮ አይደለም። ሰለሌላው ሌላለው ያሳስበው ግድዬለም ተውቱ - ለእኛ ለገራገሮች። ግን ስለራሳችሁ
ተተኪዎቻችሁ ስለማግስትም የትግራይ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ይሄ ነው የሚባል ጭንቀት አይታይባችሁ። ሥለ ማግስቱ የትግራይ ህፃነት በቅርበት
እና በባለቤትነት ልትታትሩ ሲገባቸሁ የሥልጣን፤ በመንግሥት የመዝለቅ ጉዳይ ነው አንኳሩ ጉዳያችሁ። „ሰው እና እንጨት ተሰባሪ“ የነበረው በቅጽበት እንዳልነበረ ስለመሆኑ አስባችሁትም፤ አስታውሳችሁትም አታውቁም።
የብዕሩም፤ የብራናውም፤ የመግለጫውም፤ የቃለ ምልልሱም፤ ቃለ ምልልስ የሚያደርጉላችሁ ጋዜጠኞች፤ ሆነ የሪፖርተሮች ግንዛቤ እጅግ
የሰዋዊነት፤ የተፈጣሯዊነት ጠረን የተነፈገው፤ አብዝቶ ቁሳዊነት የዳበረበት እና የጎለመሰበት ነው። ኢትዮጵያዊነት እራሱ ትርፍ ነው።
ካተረፈ ብቻ ይፈለጋል። ለውድድር ሲባል … ሥሙን በመጠዬፍ ትጠቀሙበታላችሁ፤
ሲያስፈልግ ብቻ እንጂ እንደ ዜግነት፤ እንደ መተንፈሻ ቧንቧነት ከዚህ ጣሪያ ላይ ያደረስ ባለውለታ ስለመሆኑ ጭራሽ ከልባችሁ ሆናችሁ
ልታገናዝቡት አልተቻላችሁም - አብዛኞቻችሁ። አንጡራ የቅንጥ ድሎት
የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ወዝ ስለመሆኑም ትዝ ብሏችሁ አታውቁም።
የተጋዳይ በረከት ስምዖን ሳጥናኤላዊ ምክር ብቻ
ነው በህሊናችሁ የታቦት ያህል ነግሦ የሚገኘው። የሰይጣን ሰበጠራ ነው የአቶ በረከት ስምዖን ሶፍት ዌር። መልካሙ ነገር ሁሉ በእናንተ
ሰዎች ጥረት እና ጥራት በታታሪነት የተገኘ ረድኤት እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስለ እናንተ ያደረገው ምድርበዳ ነው። ለማዬት
አልታደላችሁም። ሁለም ድሉም፤ ክብሩም፤ ዝናውም የጠበንጃ ሥጦታ ነው - ለእናንተ። ከማከብራቸው ቅዱስ አባት ከአቶ ገ/ መድህን
አርያና እና ከእውቁ የህግ ምሁር ዶ/ር ያእቆብ ኃ/ማርያምን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው የባዶ ስድስት ሰለባ ከሆኑባቸው በስቀር። የፈጣሪን ቁጣ እና ነዲድማ ትዝም ብሏችሁም አያውቅም። ፈጣሪ ሲቆጣ ሊመጣ ስለሚችለው
ነገር ከሃሳብ ውጪ ነው። መሪዎቻችሁ ከፈጣሪ በላይ ተመላኪ ናቸው እና።
እንደ ተዋህዶ ልጅነትም የሃይማኖት አባቶች እንኳ
ስለሚከፍሉት አሳር በካቴና ታስረው ስታዩ ምናችሁ አልነበረም። የእናንተ ጉዳይ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ቁስ ላይ ነው። ይህ ቋሚ
ደህንነት ጠበቂ እና ህይወትን አስቀጣይ ሆኖ የመንፈስ ሃብት ሆኖ ሲያስቀጥል የሚታይ ይሆናል … እንዴት ለልጅ ልጆቻችሁ ቢያንስ
ማሰብ ይሳናችሁ? ሰው መሆን ማለትስ ምን ማለት ይሆን በእናንተ ቤት? የመሬት መንቀጥቀጡም ከዕቁብ እንደማትቆጥሩት አውቃለሁኝ።
ለዚህ ነው ዛሬ በተለዬ ሁኔታ ጆሯችሁን ከፍታችሁ ታደምጡት ዘንድ በአድራሻችሁ የጻፍኩት። ተራ ዜና አድርጋችሁ እንደምታዩት ነው።
… ሞት ደጅ ላይ፤ ጥፋት ደጅ ላይ ነው ያለው። የሌላውን ቤት ሲፈርስ የራስ ቤት ደግሞ ሰማይ ቤት ፍርድ ሊሰጥበት መሰናዳቱን ላስተውሳችሁ
ውድጄ ነው ይህን መልክት የምልክላችሁ። የአቲካራ ጊዜ አይደለም። የእንካ ሥላንትያ በመንትያ የውርርድም ጊዜም አይደለም። መኖር
መትረፍ አለበት። ለዛ ደግሞ ባለጉዳዮች ሐዋርያው፣ ድንግሉ፣ ቅዱሱ ሰባኪው ቅዱስ ጰውሎስ „የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬበታለሁና“ እንዳለው ሁሉ ይህን ቃል ለማስተናገድ ተሰናዱ። ድምጹን የእዮርን
ምልክታዊ ደውልን ብታዳምጡት ይጠቅማል እንጂ አይከፋም፤ ያበረክታል እንጂ ምንም አያሳጣም።
·
ደወል።
ብትክትኩ ኢቢሲ EBC ሰሞኑን እያለፈ … እያለፈ
ጢባ ጢቦ ሲጫወት ከራረመ። ቃለ ምልልስ ያደርጋል። አንደበት በተዘጋባት ሐገር ራሳቸውን ለመግለጥ እንኳን ለሚቸገሩ ወገኖቼ በፍርሃት
ቆፈን ውስጥ ሆነው እዬተንዘፈዘፉ ትናጋቸው ሲቆራረጡ ይታያል። ሐገር በጭቃ ተቦክታ የምትሠራ፤ ህዝብም ሰው ጠፍጥፎ የሚሠራው ነው
ለከንቱው ኢቢሲ EBC። ኢቢሲ ሐገርን ያህል፤ ህዝብን ያህል የፈጣሪ ሥራ እቃ እቃ ጨዋታ አድርጎ ሲብተከተክ ይደመጣል …. „ቀጣዩ ጠ/ሚር ምን ቢሆን ይሻላል? ማን ቢሆን ይሻላል?“ እያለ
„በር ዘግቶ ግቡ … ዳር ለዳር ማህሉን ሳትነካኩ፤ ጠርዝ ለጠርዝ ኳትኑ
አናት እንዳትደርሱ እያለ ባባዶ ሜዳ ይቧርቃል“ ቃለ ምልልስ
አድራጊው እንኳን ራሱን ደፍሮ ማሳዬት አይችልም። ከንቱነት። የሆነ ሆኖ ፈጣሪን የጠዬቀው የዋልድባ መነኮሳት የካቴና ዕንባ መልሱን
በደወል ሰጥቷል፤ በውሳኔም አጽንቷል። ዘለግ ያለውን ጥልቅ ትርጉም ደግሞ ለአቮው ለዕድምታ ተርጓሚዎች … ልተወው። ከቀስት እንድን
ዘንድ የተሰጠ የቃል አሰሳ ነው … መቀሌ አካባቢ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ።
·
ዘመን ጠሪ ጉልላታዊ ጉልበታም ምልክት - ምልከታ።
መቀሌ አጠገብ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ምልክት
ሁላችንም ይመለከታል። ይህ ምልክት የሁላችን ጉዳይ ነው። ይህ ምልክት የሁላችን የእኛዊነት መግለጫ መፈታተሻ ነው። ይህ ምልክት
ነገን ያመተረ ነጋሪተ - ምልክት ነው። ይህ ምልክት አቅጣጫ የጠቆመ የሰማይ መለከት ምልክት ነው። ይህ ምልክት የሳትነውን ነገር
በፍጥነት እናስተካከል ዘንድ በጽሞና የመከረ ሐዋርያም ነው። ይህ ምልክት ልቦናችን እንመረምር ዘንድ በተደሞ ብሄራዊ ህብራዊ ጥሪ
አስተላልፏል።
ይህ ምልክት ለውጥ ፈልገን ለውጥ ለምንፈራ ሁሉ
የተላለፈ የእግዚአብሄር ድምጽ ነው፤ መቀሌ አቅራቢያ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ። ተስፋ የሰነቁ፣ አድገው ያልጨረሱ እኮ ህዝቡንም
አስተዳደሩንም አምነው ሄደው ታዳጊ የዩንቨርስቲ ቀንበጦች በመቀሌ፤ በአክሱም፤ በአዲግራት ዩንቨርስቲዎች በፎቅ ተውርውረዋል። ሽንት
በኮዳ ፈልቶ ሰፊው የወልድያ ህዝብ በድፍረት እና በማናአለበኝነት በቀዩ እበላዩ ላይ ተደፍቶበታል። አስተሮዮ በጭስ ቦንብ ፈተና
ድርሶበታል። በኤሊኮፈትር የተደገፈ የህዝብ ፍጅትም ተካሄዷል። ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ ከምራዕብ አስከ ደቡብ፤ ከደቡብ እስከ ስሜን
ዋይታ ተበራክቷል። ዋይታው ታቅዶ የህዝብን የውስጥ ሰላም በማናወጽ ላይ ያተኮረ ነው። ይህም የስጋት እና የሰቀቀን የዱላ ዘመን
ተቀንቶበት። ይህ ምልክት የመቀሌው አቅራቢያ የመሬት መንቀጠቀጥ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ነው፤ ወቅቱ የሁዳዴ ፆም መሆኑ እንደ ተጠበቀ
ሆኖ።
ግፍ በዛ፤ ዕንባ በረከተ፤ መከራ ጠና፤ ፍዳ አና
አለ። ሃይማኖት ተጣሰ። ሱባኤ ተረገጠ። ክህንት ተደፈረ። ጠኔ የነፃነት ቤቱን ሁሉን ቃኘው። ድምጽ ተዘጋ። ውሸት እና ማዳዳጥ የመንግሥት
መኩሪያ ፖሊሲ ሆነ። ጥዋት የተነገረው በዛው ፍጥነት ተደምስሶ ወይ ተደመርምሶ ይደመጣል። ዝግጠት። ዝገት። ብላሽነት። ቃልአባይነት
ነገሠ።
ተፈጥሯዊ ሰዋዊነት መተንፈስ ታገደ። መንቀሳቃስ
ተከተረ። ሰው ለሰው ይገናኝ ዘንድ እንደ ወንጀል ተቆጠረ። ሁሉም ተከረቸመ። ቀደም ባለው ጊዜ እኮ ሊኳንዳ ቤቶች ሁሉ በሁዳዴ ዝግ
እንደ ነበሩ፤ እንደ ገናም በገና ድርደራ እንጂ ሞቅ ያለ ዜና እንኳን እንደ አልነበረ፤ ጭፈራ ሳይኖር በተመሰጠ ልባዊነት ብቻ ሃይማኖት
የከበረባት ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ነበረች ነው ድርሳናቱ የሚገልጹት። ዛሬ ከዛም አልፎ በመትረዬስ መንገድ ላይ የተገኘ ሁሉ በፆመ
ሁዳዴ ይታጨዳል። ሚሊዮን ተፈናቅሎ ለስደት ይዳረጋል። የተገኘው ሁሉ ይታሠራል። መሬት ያፈራው የታዬው ሁሉ ይወረራል፤ ይጋፈፋል
በቃኝ፤ ጠግቤያለሁ የለም። ህዝብን በጅምላ የጨፈጨፈ የላቀ ሹመት እና ሽልማት ይሰጠዋል። ህዝብን የደበደበ፤ ወንድን ያንካላሸች
ሴት ሁሉ ስለመፈጠሯ እዬሰማን ነው። ዘመነ ጉዲት። ከዛ አልፎ ዕንባ ለጠናባቸው ወኪሎች በኮዳ ውሃ ተሞልቶ በሃዘንተኛ ቤተሰቦች
ላይ በጥጋብ እና በማንህሎኝነት ይወረወራል። አቤት! ልክ ታጣ …
·
ዕዳችን።
መታበይ ነገሠ፤ ንቀት ጣሪያ ነካ፤ ጥጋብ ዙሪያ
ገባውን ትጥቁን አሳምሮ በተፈጥሮ ላይ ዘመተ። መተማመን - መደማማጥ - መከባባር - መቻቻል -
መፈቃቀድ ሁሎችም ጠወለጉ፤ ፊትም ተነሱ። ጠበንጃ ንጉሥ ሆነ። ጠበንጃ ተመለከ። ጠበንጃ ገዢ ሆነ። ጠበንጃ የሥልጣኔ
መለኪያ ሆነ። ጠበንጃ የትምህክት - የትዕቢት - የጥጋብ ደጀን ሆነ። ጠበንጃ መፎከሪያ የሰው ልጅ ረቂቅ ተፈጥሮ ማሸነፊያ ሆነ።
ሰው ረከሰ ከእንሰሳም በታች ታዬ። የሰው ልጅ እንደ ምናምንቴ ታዬ … ተወረውረም … ፈጣሪ ተጨንቆ ተጠቦ የሠራት ምድር ክብር አጣች
ተደበደበች።
የሰው ልጅ መስፈሪያው ሰብዕናው መሆኑ ቀር። „በመጀመሪያ ቃል ነበር፤ ቃልም በእግዚአብሄር ዘንድ ነበረ። ቃልም እግዚአብሄር
ነበር። ይህ በመጀመሪያ በእግዚአብሄርም ዘንድ ነበር“ ይላል አካል የሌለው የኢግዚአብሄር አገልጋይ ቃለ ወንጌል። ሰውን የፈጠረው
እኮ የእግዚአብሄር ቃል ነው። ያ በድፍረት በማንአለብኝነት ተጠሰ - ተበጠሰ። በምድሪቱ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ጨምሮ እንደሌለ ተቆጠረ።
መኖር ተሰበረ። የነበረው ኢትዮጵያዊው ዜጋ እንዳልበረ ታዬ። ሁሉም በተለያዬ ሁኔታ ከፈጣሪ ቃል ወጥቶ ሰዋዊነቱ በደቦ ሰረዘ። ሰው
እያለ የለህም፤ ማህበረሰብ አይደለህም ተባለ። ሰው አልተፈጠረም እስከ ማለት መንጠራራቱ አንቱ ሆነ።
መለኪያው፤ መሥፈርቱ፤ ልቅናው፤ ዕውቅናው ሌላ
እና ሌላ ሆነ። መለኪያው ሰው ከተፈጠረ በኋዋላ በሚገኙ ሰብዕና ተኮር ተሆነ። ሰውነት ከተፈጥሮ በታች ቀርቶ ሰውነት ስለመፈጠሩ
የሚገድቡ ድንጋጌዎች ሁሉም በእጁ ሥራ እንደ ዳንቴል ተፈበረኩ። ድንጋጌው በድንጋጌ ላይ ዘመኖ ሰው ሆይ! በኢትዮጵያ ምድር በመንፈሱ
ተሰቃይቶ ጥርኙን ይለቅ ዘንድ፤ ታፍኖ ይፈናቀል ዘንድ ተገመደለበት።
ኢትዮጵያዊው ሰው በፆታው፤ በሙያው፤ በዕውቀቱ፤
በብሄረሰቡ፤ በዲታነቱ፤ በቋንቋው፤ በዝናው ብቻ ተለካ - ተመዘነ - ተሰፈረ። ሰው „ሰው“ ሰውኛ ጠረኑ በድርቅ በወበራ በዘመቻ
ተመታ። ኢትዮጵያዊው ሰው በራሱ ውስጥ ለመኖር አልፈቀድለት ሲል በራሱ ውስጥ ሆኖ እንኳን መሰደጃ አጣ። ክራሞቱ ተንከራተተ። መባጃው
ክልትምትም አለ። ነፍሱ ፍዳ ጠናባት እና መንፈሱ በጠና እንደ ጣና ዘገዮን ታመመ።
·
ፈጣሪና ፍጥረቱ ኢትዮጵያ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ያውቃታል። የሚያውቃት ከመፈጠሯ
በፊት ነው። ስለምን አወቃት ብዬ እኔ የአባቶቼን የሚስጢረ መለኮትን እድምታ አንባቢዎች፤ ተርጓሚዎች ፍች ሰጪዎች እና አመሳጠሪዎችን
አልጋፋም። ጸጋው አልተሰጠኝም እና። ግን አንድ ነገር አውቃለሁ። ኢትዮጵያ የልዑል እግዚአብሄር መንፈስ ያረፈባት ሐገር ስለመሆኗ።
ፈቃዱን ሊሞሉ የሚተጉትን ሁሉ ሊቃነ - መላዕከት፤ ሠራዊተ መላዕክት፤ ቅዱሳን፤ ደናግላን፤ ሐዋርያት ሁሉም ኢትዮጵያ ምልክታቸው
ናት። ማደሪያቸወም ናት። ይሳሱላታል። ይወዷታል። የተቀቡ ሁሉ ዕምነታቸውን ይጥሉባታል። ከነብዩ መሐመድ ጀምሮ ነብያቱ፤ ዘጠኙ ቅዱሳን፤
ተንባያን የተከፉ፤ የተሳደዱ ሁሉ ቤተ መቅደስ እንደሆነች ተናግረዋል። ትንቢትም ጽፈዋል። እሷም በመሆኗ ውስጥ አሳምራና አስመችታ
ትንቢታቸውን ሆናበታለች። ዛሬ ግን እራሷንም ለማኖር፤ ራሷንም ለማስቀጠል ችግሩ ውጧታል። በመከራ ሙጃ ተወራለች። ስለዚህም ነው
የአሁኑ በመቀሌ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ምልክት እዮራዊ ደወል ያስተጋባው። የራሄል ዕንባ ፈሶ አይቀርምና። ይህን
ያደመጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን አብነት ትተውልን ሄደዋል። ያ የትምህርት ተቋማችን ነው። ግን ጭንቅላት ሳይሆን አዕምሮ ሲኖር
ብቻ ነው ማስተዋል የሚቻለው። ህሊና ከሌላ ላይታይ ይቻል። እዮር በጸጥታው - በዝማታው - በእርጋታው - በአርምሞው - በጭምትነቱ ውስጥ ጥሶ የወጣ ጉልህ ድምጽ አሰምቷል።
መታመሱ ይቁም ብሏል። ወዮ! ብሏል። ድምጹን ለመዳን፤ ድምጹን ለምህረት - ድምጹን ለሥርዬት፤ ድምጹን ለፍቅራዊነት ለሚያዳምጡት
ሁሉ መልዕክት ያውም በዐጽዋማት ዓዕማድ በሆነው የክርስትን ዕምነትም ዓላማና ግብ በሆነው በሁዳዴ ልኳል። ተዚህ በፊት የእዮር ድምጽ
እንዴት ተስተናገደ? በቀጣይ የምንታደምበት ይሆናል …
·
ለአብነት ያህል …
1. በውል ተደመጠ የፈጣሪ ውሳኔ በዘመነ ዐጤ ሱስንዮስ መንግሥተ።
ይህ መሰል እዮራዊ ደወል በቀደሙት አባቶቻችን
ዘመንም ታይቷል። ግን እኛ የምናቃልላቸው፤ ስህተታቸውን እዬቆፈርን የምንብጠለጥላቸው፤ አልተማሩም የምንላቸው፤ አልፈን ተርፍን
„ጀብደኞች¡“ ነበሩ ብለን የምንወርፋቸው በዘመናቸው የተፈጸም የተጋድሎ አውራ ነው። እኛማ በዛ ዘመን
ልክ የማድመጥ አስተውሎት የተነፈግን ነን። ባሻን ሰዓት ያሻንን ህግን በመተላለፍ ዛሬ ያሉት ያልከወኑትን፤ የትናንትኖቹ ሐገርን
ያህል መጠለያ ሰርተው ያለፉትን እንኮንናለን። ብልሆች የቀደሙት ግን ፈጣሪያቸውን የተላለፉ ሲመስላቸው ሁልጊዜም አቤት ያንት ያለህ
የእኔ ጌታ፤ ይቅር በለኝ! ብለው ወደ አምላካቸው ይመለሳሉ። ይህን በአጤ ፋሲል አባት በአጤ ሱስንዮስ ከታሪክ ድርሳን አንብበን
ተረድተናል።
ዐጤ ሱስኔዎስ የካቶሊክ ሃይማኖትን ተቀበለው ሲኖሩ
አንድበታቸወ እንደ ተዘጋ፤ ይህም በዕምነታቸው ጽናት ልልነት እንደ ተፈጠረ ተጸጸተው ፈጣሪያቸውን ይቅር በለኝ ለማለት የደፈሩ ነበሩ፤
እንደ ታሪክ ጸሐፊዎች አስተምህሮት። ለዚህም ነው ለመጥመቂያነት ፋሲለደስ የጥምቀት ባህር ሥርዓት ጥምቀት ይፈጸም ዘንድ ጽኑ ቋሚ
ትውፊት ተሠርቶ የጠበቀን። … ይህን ሂደት የታሪክ ሊቀ -ሊቃውነቱ ጸሐፊ ክቡር ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ
ዐፄ ቴውድሮስ በጻፉት መጸሐፍ ምዕራፍ 29 …ከገጽ 138 እስከ
139 እናገኘዋለን …
ሊቁ እንዲህ ይላሉ … „በመጨረሻም በነገሡ በ27ኛው ዓመት ዐፄ ሱስንዮስ ታመው አንደበታቸው ተዘጋ።
በዚህ ጊዜ ታሪክ ነግሥታቸው እንደሚለው ልጃቸው ዐፄ ፋሲል እግዚአብሄር ይህን ማዕት ያመጣባቸው ሃይማኖታቸውን ቢለውጡ ይሆናል ሲሉ
በዬገዳማቱና በዬአድባራቱ በፀሎታችሁ፣ በሃዘናችሁ አባቴን አድኑልኝ እናም ያላችሁኝን አደርጋለሁ፤ እያሉ ብዙ መባእ ላኩ። አባ ዐምደ
ሥላሤን ገዳም አዲሰ ቆርቁረው በበርሓ የሚኖሩ የበቁ መነኩሴ ነበሩ። እራሳቸውም ለቆሮቆርሁት ገዳም 44 ጉልት ልትሰጠኝ ቃል ኪዳን
ግባልኝ፤ አባትህን እኔ አፈውስልሃለሁ ብለው ወደ አቤቱ ፋሲል ላኩ። አቤቶ ፋሲልም እሺ ያሉኝን አደርጋለሁና መጥተው አባቴን ይፈውሱልኝ
ብለው መልሰው ላኩ።“
እንግዲህ በዛን ጊዜ የዐጤ ሱስንዮስ ልጅ ዐጤ
ፋሲልም የካቶሊክ ዕምነት ተከታይ እንደሆኑ ነው ታሪካቸው የሚነግርን …. ግን ምህርትን ለመጠዬቅ የሄዱበት መነገድ ዛሬ በግፍ በሚደበደበው
የገዳማቱ መጠለያ ወደ ሆነው ወደ ቅዱሳኑ ባዕት ነበር መልዕክት የላኩት። በዛ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶችም ብዙዎቹ
ስደት ላይ እንደነበሩም ይገለጻል …
ወደ ቀደመው ስመለስ „ከዚህ በኋዋላ አባ ዐምደ ሥላሴ ከገዳማቸው ተነሥተው መነኮሳትን አስከትለው
ደንቀዝ ሄዱ። በደረሱም ጊዜ አቤቶ ፋሲል በክብር ተቀብለው በመልክት የተነጋገሩትን በቃል አጽድቀው፤ አባ ዐምደ ሥላሴን መነኮሳትን
ጨምረው 3 ሱባኤ ወስነው፤ ቀን በጸሎት ሌሊት በሰዓታት እግዚአብሄርን ለምነው ዐጤ ሱስንዮስን አጥምቀው ስላቆረቧቸው ዐጤ ሲስንዮስ
የተዘጋ አንደበታቸው ተከፈተና „ የእስክንድርያ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ትምለስ የሮም ሃይማኖት ትርከስ ፋሲል ይንገሥ“ ብለህ
ዐዋጅ አናግር ብለው ለልጃቸው ለአቤቱ ፋሲል ተናገሩ ይባላል። ይህም ዐዋጅ ተነግሮ ከተፈጸመ በኋዋላ በዬዋሻው፤ በዬበርሃው የተሰደዱት
ሊቃውንትና መነኮሳት መጻህፍቶቻቸውን ይዘው ወደ የቤታቸው ተመለሱ።“
ከዚህ ላይ የመንረዳው ቀደምቶች እጅግ የቀደሙ ናቸው። ማድመጥ ይችላሉ። ማዬትም ይችላሉ። አስተውሎት የሰጣቸው ስለመሆናቸው
የድርጊቱ ክንዋኔ ያስተመረናል። ከግል ፍላጎት ፈቃድ ህግ ተላላፊነት ይፈሩታል። መሪነት ይሄ ነው።
ነገሩን ካነሳሁት ዘንዳ … የጥምቀት ሥርዓት በፋሲለደስ
ቅርስ ያለው ትውፊት ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሚስጢረ ጋር የተያያዘ እንጂ በሰውኛ በገሃዱ ዓለም ሊተረጎም ከቶውን አይገባም። ለዛ የሚሆን
ዘውር ያለ ቦታ ይኖራል - አለም። ቀደም ባለው ጊዜ ጎንደር የተወለደ ልጅ/ የተወለደች ልጅ በዕለቱ ቀኖቻቸውን ወደ ጥር 12 በማጠጋጋት
የዛሬውን አላወቅም ብጹ ህጻናት ጥምቀታቸው እዛ ይፈጸማል። የእኔ ሟቹ ወንድሜ እዛ ሃይለ ሚኬኤልም ሥርዐተ ጥምቀቱ እንደ ተፈጸመለት
እናቴ ገልጻልኛለች። መሠረቱም ያ ነው „ፋሲል መዋኛ“ የሚለውን ሥያሜ ትክክል አለመሆኑን የታሪክ ሊቀ - ሊቃውነቱ የተከበሩ ረ/
ፕ ዶር. አበባው አያሌው በጽሞና እና በተደሞ ገልጸውታል። ዐጤ ፋሲልን ጨምሮ ብዙው በዬመሪዎቻቸው የካቶሊክ ዕምነቱን የተቀበሉት
በወል የጥምቀት ሥርዓቱን በስፋት ለመፈጸም ታስቦ የተሰራ ገንዳ ነው። እንኳንስ ያን ጊዜ ዛሬም ጎንደሬ አባወራ / እማወራ ለዛውም
ንጉሥ በህዝብ ፊት ልብሱን አውልቆ ይዋኛል ተብሎ አይታሰብም። በፍጹም። እንኳንስ ያን ጊዜ ዛሬም ቢሆን በእኔ ሰብዕና ውስጥ ይሄ
አይታሰብም። ጥልቁ የጎንደር የባህል ገጸ ባህሬ የማይፈቅዱና በፈቃድ በራስ ላይ የተጫኑ ትውፊታዊ ሥነ - ምግባሮች ጥብቅና ከቶውንም
የማይደፈሩ ናቸው። ትውፊቱ በሁላችንም ዘንድ አለ። ሰው ኖረ አልኖረ፤ ውጪ ሐገር ተኖረ // ሐገር ውስጥ ተኖረ ህሊና ይቆጣጠረናል።
አባቶቻችን ካቆዩልን ትውፊት ዝር እንዳንል ይከተለናል ሥርዐተ አስተዳደጋችን።
እግረ መንገዴን „የፋሲል መዋኛ“ የሚለው ሥያሜ
ግድፈት ስለመሆኑ ለማጠዬቅ ነው። „መጥምቀ ፋሲለደስ“ ቢባል እንኳን ያስኬዳል። ወይንም „ጥምቀተ የፋሲለደስ ገንዳ“ … „ሥነ ጥምቀት
በፋሲለደስ“ ብቻ እኔስ እላለሁኝ የተሻለ ሥያሜ ከምግብሩ እና ከትውፊቱ ጋር የሚቀራረብ መሆን አለበት። በተለይ አስተርጓሚዎች ጥንቃቄ
ማድረግ ይኖርባቸዋል። የፈጣሪ የማስጠንቀቂያ ደውል ተደምጦ ምግበሩ የተከወነበት የታምር መክፈቻ ነውና ነገረ ፋሲለደስ መጥምቀ ስክነቱ።
የጥሞና ሚስጢር!
·
የእዮር ደውል ድምጸት ተደማጭነት በዳግማዊ ዐጤ ሚኒልክ
ዘመነ መንግሥት፤
2/ እንደ ታሪክ ጠሐፊዎች ገለጻና ዕድምታ …
በሌላ በኩል በዳግማዊ ዐጤ ሚኒሊክ ዘመን የዐጤ ዮሖንስ የጽናት፤ የማተብ ምልክትን በደሙ ያሰከበሩት የነፃነት አባት ልጅ አልጋው
ለእኔ ይገባኛል ብለው በዳግማዊ ዐጤ ሚኒሊክ ላይ አመጡ። ሽማግሌ ሲላክም አሻም ብለው፤ ጉግስ ለመግጠም ወሰኑ። ነገር ግን ልክ
እንደ ዛሬው ትግራይ ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ። ፈጠሪ
እንደ ዛሬው ምልክት ሰጠ እዮር ደማቅ ድወል በጉልህ ደወለ። አባቶቻችን / እናቶቻችን ብልህነታቸው የሰማይ ነበር። ዕምነታቸውም
ጽኑ እና የማያወላዳ ነበር። ስለሆነም የሰማዩን የቴሌቪዥን ዜና አዳመጡ፤ ምድራዊውን ሳይሆን። እናም ፈቃዱን ፈጸሙ። ሐገርም ህዝብም
አረፈ። ክብር ለቀደሙት አስተዋይ አባቶቻችን / እናቶቻችን።
·
ታሪኩ እንዲህ ይላል …
„ራስ መንገሻ ዮሖንስ ሁለት ጊዜ እጅ ለመንሳት ወደ አዲስ አባባ ተጉዘው ነበር። ሁለቱም
ጉዟቸው በንጉሡና በእቴጌይቱ የተደረገላቸው አቀባባል፤ መስተንግዶም ግሩም ነበር። በተለይ እቴጌ ጣይቱ የለግሷቸው ልዩ ቀበሬታ እና
እንክብካቤ ተገቢውን ቦታ እና ትርጉም ሊያገኝ አልቻለም። በሚዚያ 1899 ራስ መንገሻ ራሳቸውን እንደ ተበደሉና እንደ ተገፋ በመቁጠር
ማፈንገጣቸውን እና የትግራይ ንጉሥ ተብለው ባለመንገሣቸው ቅሬታ ተላብሰው ለማመጽ ከተከታዮቻቸው ጋር ሲመክሩ እንደነበር የሰሙት
እቴጌ ጣይቱ በግላቸው ይሄን የተማህጽኖ ደብዳቤ ፃፉ።“
„ይድረስ ለወዳጄ! ለልጄ! ራስ መንገሻ የላኳቸው ሰዎች መቼም ለጃንሆይ ወደ ሽዋ መቼም
አልመለስም ማለትህን ሲናገሩ ሰምቼ አጥብቆ ገረመኝ! ደነቀኝ! እኛ የአንተን ቤት አንሥራለን ብለን ስንደክም የእኛን ቤት አፈርሳለሁ
ብለህ አሰብክ?! ይህንን ነገር እግዚአብሄር ይወደዋልን?! ይህን ክፉ ሃሳብህን ብትተወውስ የሰይጣናትን ክንፋቸውን ስበረው ከዚህ
ቀደም ወንድማማቾች ራስ አሉላ፤ ራስ ሐጎስ እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ ምን ያህል እንዳዘን ታስታውሳለህን?! በዚህ አሳዛኝ ክስተት
የሚደሰቱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ብቻ ናቸው። ልጄ ወዳጄ! እኔ እናትህ በዚህ በአደረከው ነገር በጣም አዘንኩኝ። አጥብቄ አለቀስኩኝ።
እኔስ ቁሜም ተቀምጬም ባስበው አንተን የሚያስቀይም ነገር የተፈጸመብህ የቱ ጋር እንደሆነ ለማወቅ አልቻልኩም።“
„Ethiopia | ክፍል 2: እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘኢትዮጵያ | Etegue Taitu በመኮንን ወ/አረጋይ Sheger FM,Sinkisar“
ከዚህም በተጨማሪ እቴጌይቱ …
„መምህር ዜና እና መምህር
ፈቃደን፤ መምህር አካለ ወልድን፤ የሐይቁ መምህርን አባ አምደ ሥላሴን፤ የግሸኑን ግራ ጌታ ውበትን፤ አባ ወ/ ገብርኤልን መስቀል
እስይዘው ወደ ትግራይ በመላክ ነገሩ በሰላም እንዲያልቅ መማጸናቸውን ቀጠሉ።““
ዳግማዊ ዐጤ ሚኒሊክም በበኩላቸውም „የትግራይን አድባራት በሙሉ ይዛችሁ እኔ በድዬህ ከሆነ ማረኝ! ይቅር በለኝ!
ብላችሁ መስቀሉን ተሸክማችሁ ውደቁና አስታርቁን ብለው መነኮሳትን ሽማግሌዎችን ላኩ።“
„ይህ ሁሉ ጥረት ባለመሳከቱ በራስ መኮነን የተማራ ጦር ወደ ትግራይ ዘልቆ መቆጣጠር ጀመረ።
ራስ መንገሻ ራስ ስብሃት „በደገሃሙስ“ ምሽግ እያሉ ግትር አቋማቸውን ለመቀዬር ያስገደደ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተከሰተ።“
የሚኒሊክ ዜና መዋዕለ ጸሐፊ እንደሚሉት „ የመሬት
መንቀጥቀጡ እግዚአብሄር በያዝኩት አቋም ያለመደሰቱን፤ እንዲሁም
ለእሳቸውም አብረዋቸው ካሉት የሰይጣን ሃሳብን ከሚያራምዱት ወገኖች እንዲነጠሉ ምልክት ያሰዬ ነው ብለው እንዲያሰቡ አደረጋቸው።
ከዚህ ክስተት በኋዋላ ራሳቸው ራስ መንገሻ ዮሖንስ ለራስ መኮነን እና ለራስ ሚኬኤል ነገሩን በሽምግልና ጥረት እንዲያልቅ ተማጸኗቸው።
ራስ መኮነን ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ሆነው ሁለቱም ድንጋይ ተሸክመው በእንብርክካቸው ከንጉሡ ዳግማዊ ዐጤ ሚኒልክ እግር ስር በመውደቅ
ለራስ መንገሻ የሖንስ ምህረት ያደርጉላቸው ዘንድ ተማጸኑ ፈቃድም አገኙ።“ አዬችሁ እነ ቤተ - ተጋሩ ራስ መንገሻ የሖንስ
የልባቸውን ጥልቅነት እና ሰፊነት የቻይነት አቅም እና ተስጥኦ - ምስባክ እኮ ነው። አናባቢም ተነባቢም። ዛሬም እዬታመሱ በ4 ኪሎ
ያሉት መሪዎቻችሁ ትክክል አለመሆናቸውን ነው ለማጠዬቅ ነው „ታሪክ
ራሱን ይደግማል“ እዮር አዲስ ልክ እንደ ሚዘያው 1899 በተቀራረቢ ወራት የመሬት መታወክ መቀሌ አቅርቢያ የተደመጠው። በፊትም
ንግሥና ይገባኛል ዛሬም ጠቅልለን እንያዝ ነው። 27 ዓመት አልበቃነም ነው። ፈጣሪ አምላክ ግን በቃ! ብሏል።
·
ማጣቀሻ ለህሊና ዳኝነት።
እቴጌ ጣይቱ ለራስ መንገሻ ዮሖንስ በጻፉት መልዕክት
ላይ እንዲህ የሚል አለበት
„እኛ የአንተን ቤት አንሥራለን ብለን ስንደክም የእኛን ቤት አፈርሳለሁ ብለህ አሰብክ።
ይህንን ነገር እግዚአብሄር ይወደዋልን?!“ ይህን ዛሬ የወያኔ
ሃርነት ትግራይ በድፍረት እና በማን አብኝነት ፈጽሞታል። በኮ/ ደመቀ ዘውዱ ትህትናዊ ሃሳብ ላይ የወሰደው የእብሪት እርምጃ ይሄውን
ነበር። የትግራይን ቤት ሥራ በቅንነት ደሙን ወጣትነቱን ለገበረ፤ ለተገበረ፤ ዛሬ ማዕት ወረደ በመላ የአማራ ህዝብ ላይ። በመላ
ኢትዮጵያ ላይም … አቧራዊ ፍርድ በሞት ቀለም። ማድመጥ፤ ማዬት፤ ማስተዋል ከህሊና ጋር ያላቸው ውል ያልተፈተሹ ስለመሆኑ የጠራ
ግብረ ምላሽ የሚሰጡ ብዙ እጅግ በርካታ አምክንዮችን ማንሳት ይቻላል።
·
መታበይ ፍርዱን ከሰማይ ነው የሚያገኘው።
ዛሬ ዕምነትም፤ ጽናትም፤ ሐገራዊነትም፤ ሃይማኖትም
የጎደለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ በትዕቢት ያን የተፈጠረበትን የትግራይ
መሬት በክፉ ምግባሩ እያስነሳ ነው። ነገም ፍዳውን መለካት አይቻልም። እትዬ ትግራይ ግራጫም ጠፍቶባታል። ባለግራጫዎችማ ቀደም ብለው
ተመንጥረዋል። የባዶ ስድስት ሰላባ ሆነዋል። የሰማዩ ዜና የሚነግርን የዚህ ሁሉ ግፍ ድምር በቅጽበት ሁሉንም ነገር እንዳልነበር
ማድርግ እንደሚቻለው ነው። „በቃህ!“ ነው የሚለው የእዮር አደባባይ
ወያኔ ሃርነት ትግራይን። „ትርምሱን አቁም!“ ነው የሚለው የሠራዊት
ጌታ እግዚአብሄር። „ህዝቤን ልቀቅ!“ እያለ ነው አዶናይ መቻሉ
ጫፍ አድርሶ። „የህዝቤን ሰለሙን አትወክ!“ በማለት ሠራዊተ
መላዕከትን በረድፍ አሰልፎ እዬጠበቀ ነው። „ህዝቤን አትጨርስ የከፈትከውን
ባሩድ ዝጋ!“ እያለው ነው አማኑኤል ለወያኔ ሃርነት ትግራይ እና ሰይጣናዊ መካሪዎቹን ሁሉ እያስጠነቀቀ ነው። „መታበይህን አስታግስ!“ ብሏል የእዮር አዳባባይ። „ የመንፈስ ሃብት አንድስም እንኳን እርሾ የለህም ቁጣዬን የ እኔን የፍርድ መቅሰፍ ሊያስቆም፤ ሊገድብ የሚችል አንዳችም
ሃይል የለህም“ እያለ ነው የሰማዩ ዳኛ። „ቁጣዬ ሲነድ እንኳንስ ሰው ሰራሽ ወንበርህን እኔ የሰጠሁኽን ሰውነትን
ለመሸከም ይሳንሃል፤ የ27 ዓመት የቁንጣን ጊዜህ ሲጠናቀቅ የቅጽበት ናት“ እያለው ነው ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሄር ከእዮር
አደባባይ ሆኖ። ጆሮ ያለው ያድምጥ፤ ልብ ያለው ያስተውል ነው የዛሬው የብራና ቀለም ተደሞ።
·
ቁጣ የሰማይ።
ይፋጃል። ቋያው አያሰቀርብም። የነዲዱ ወላፈን
አያስጠጋም። እሳቱ ከተለመደው የገሃዱ ዓለም ፍብረካ ውጪ ነው። ፈጣሪ ሲቆጣ ነበልባሉ ከሰውኛ በላይ ነው። ሳይንስ ምንትሶ ቅብጥርሶ
ሱናሜውን ማስቆም አይችሉም። ይህንም ዋልድባ ሲደፈር በመቅድሙ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ቁንጮ እስከ ጭንቅላቱ ነበር የተሰናበቱት።
ያ በሰውኛ ብቻ ተተርጉሞ ነው የታለፈው። ነገር ግን ታምሩ፤ ገድሉ የሰማይ ነበር። ዛሬ በካቴና ላይ ታስረው የፈጣሪን የቀራንዮ፤
የጎለጎታ ሰቆቃ በመቀበል ላይ ያሉ የዋልድባ አብርንታት አባቶች ስለምክንያት ነው ያን ያህል ፍዳ የሚከፍሉት። እንኳንም ታሠሩ።
የተከበሩ ፕ/ አስራት ወ/ደዬስ ሲታሠሩ እንኳንም ታሠሩ ብዬ አዕምሮ ጋዜጣ ላይ ጽፌ ጋሼ አብርሃም ጉዝጉዜ „ስለምን ብሎ“ ጠይቆኝ
ነበር። ሐብት የሰው ነው። የሰው ሐብት ደግሞ የፈጣሪ ነው ብዬው ነበር። ትውልድ የማይተካቸው አባት ፕ/ አስራት ወልደዬስ በጤናው
ዘርፍ እጃቸው አዳኝ ነበር። ሲዳስሱ ብቻ ፈውስ ነበረው። ከዚህ በላይ በሰዋዊነት ለተገለለ እና ጥግ ላጣ የአማራ ማህበርሰብ የፈጸሙት
ገድል ደግሞ የቅድስና ብትህትና ነበር። ለዛ ብትን አፈር ላጣ ከርታት ሰፊ ማህበረሰብ አለሁህ፤ እኔን ልገብርልህ ብለው ራሳቸውን
ገበሩ። ያ የበለጠውን ክብር እና ሞገስ በፈጣሪ ዘንድ አስገኘላቸው። ሚሊዮኖች አባታችን አሏቸው። ዛሬም ጊዜ ጥሩ ነው ዳግሚያ ትንሳኤውን
እያዬን ነው።
የዋልድባ አብርነታት ገደም ድርሳነ ታሪክ እንደሚነግርን
ራሱ አማኑኤል የገደመው ነው። የባህተውያን እስርም እንደ ሥጋ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈጣሪ በጥበቡ በሰውኛው ሲዖል ውስጥ ሆነው
አንዷ ቅንጣት ዕንባቸው አዮርን እንዲያስከፍት የተፈቀደላቸው ናቸው። ሰማዕት ናቸው። እነሱ እኮ ገዳምም ቢኖሩ ፈተና ካልኖረው ገዳሙን
አይፈቅዱትም። ምነው ፈተና አዘገዬህ ብለው ሁለት ሦስት ሱባኤ ይገባሉ። ልክ ቅዱስ አባት አበርሃም „እንግዳ እንዴት ነሳህኝ“ እንደሚለው ማለት ነው።
የዋልድባ መነኰሳት ፈጣሪ ዕንባቸውን ቆጥሯል።
ገድለኛ ምልክትም ልኳል። ይህ ምልክት ለሁሉም ነው ለእክሌ ተከሌ አይልም። ኩራታችን፤ ክብራችን ሥማችን ወይንም ማንፌስቷችን፤ ዝናችን፤
ወይንም ጠበንጃችን ነው እኛን የፈጠረን፤ የቀረጸን አድርገን የምናስበው። ግን የፈጣሪ ሃይል ከሁሉም በላይ ነው። ሞት ራሱ የተረሳ
ነው። … በፈጣሪ የክት እና የዘወትር፤ መዳብ እና ነሃሳ የመደብ ምደባም የለውም። በገሃዱ ዓለም እና በመንፈሳዊ ዓለም መንፈስ
መሃከል ትልቅ ገደል አለ። ገደሉን መሻገር የሚችሉት መንፈሱን ያከበሩ፤ የተቀበሉ፤ አለህ ብለው ያመኑት ብቻ ናቸው። ድምጹን የሚሰሙት።
የተፈቀደላቸው ብቻ ናቸው።
ትውልድ መዳን የሚችለው የመጀመሪያው „ሰውን የፈጠረው
ፈጣሪ ነው“ ብሎ አምኖ መቀበል ሲቻል ብቻ ነው። የፈጠረውን ፍጥሩን እንደ ጉልት ገብያ በሸቀጥ መድቦና በሜትር ሽንሽኖ፤ እንደ
ጣቃ በቦንዳ መትሮ ሰብዕናውን ማግለል ወይንም ማቅረብ ወይንም መፈቅፈቅ ጠቡ ከአንድዬ ጋር ብቻ ነው …። ፈጣሪ አምላክ ሰውን ሲፈጥረው
እንዲያመስግነው ነው። አመስጋኙን የሚጻረር፤ የሚያጠፋ ደፋር እስከ ልጅ ልጁ ቅጣቱን ይልክበታል … ለዚህ ነው ቀደም ባሉ ጹሑፎች
ወይኔ ሃርነት ትግራይም እና እትዬ ትግራይም ድንጋይ ተሸክመው የኢትጵያን ህዝብ የፈጠረውን አምላክ ይቅርታ ይጠይቁ እያልኩኝ ስቸከችክ
የከርምኩት። አሁን ከመሻል ወደ ባሰ ረግረግ ላይ ነው። የመጨረሻው የምልክት ደወል ተደውሏል። ከእዮር … ቀሪውን ደግሞ ከኛ የሚለጥቁት
ትውልድ የሚያዩት ይሆናል።
·
የ4 እግር ውርክብክብ።
ቀኑ በፈጣሪ የታቀደ ነው። ቀኑ በፈጣሪ የተቀባ
ነው። ቀኑ በፈጣሪ ለድህነትም ወይንም ለጥፋትም የተጋድሎ ምልክት ነው። ትግራይ መቀሌ አቅራቢያ ታዬ የተባለው የመሬት መንቀጥቀጥ
ይህ ምልክት ዛሬ ያለውን የ4ኪሎ ቤተ መንግሥት ውርክብ ጸጥ ረጭ አድርጎ በአንድ ቃል፤ በሙሉ ድምጽ፤ ያለመከፋፈል መፍትሄው አናት
ላይ እንዲኮን ፈጣሪ እራሱ መወሰኑን ያበሥራል። ቅብዕ የፈጣሪ ነው …. ቅብዕ የተሰጠው አለ። አመጣጡም ሁኔታውም ሂደቱም መሠረቱም
አዲስነቱም ልብ ተብሎ ሲመረመር፤ ተወራራሽ ነገሮች ሲጠኑ ፈጣሪ በእሱ አድሮ ምን ሊሠራ እንደሚችል አማኑኤልን በርከክ ብሎ መጠዬቅ
ነው። መልሱ እዛ ላይ ይገኛል።
ይህ ከተረገጠ ግን ወዬ ነው። ኢትዮጵያን የጠበንጃ
ሃይል አይደለም የሚገዛት፤ ፈርሃ እግዚአብሄር ብቻ ነው። ስንቋም ትጥቋም ፈርሃ እግዚብሄር ነው - ለሐገረ ኢትዮጵያ። የሚያስተዳድርትም
ፈርሃ እግዚአብሄር ብቻ ነው። ራሱ ቤተ መንግሥቱ እኮ ረክሷል ይሄ ያልባለቀች ዕንቡጥን አስገድዶ የደፈሩ ምኖች ነው ያሉበት? በዬደረሱበት
ከሥጋ ፈቃድ ጋር ግብ የሚገጥሙ፤ ገዳዮች የበረከቱበት። ደም- ደም ይሸታል ዓውዱ። ዘማዊነት እንደ ሰዶም እና ገሞራው ዘመን ነግሦል
እኮ። በዘረፋ ነፍስ ሁሉ በሌብነት ጨቅይቷል። በሃጢያት በተነፋ ባሎናዊ ነፍሳት ተውጧል - ቤተ ምክር ቤቱ ቁንጮዎች። ጠረኑ በሰው
ደም እና እንግልት እጅግ ይከረፋል። ይጎፈንናል። ታዳጊ ወጣት የደፈረ ለጠቅላይነት ይቀፋል - ለመስማትም። ይህን አሸኮኮ አድርጎ
መውደቅ መነሳት ከጸያፍነትም በላይ ነው። ምን ገዳዩም አፈናቃዩም ሴረኛውም ገመናውን ተሸክሞ በረድፍ ተኮልኩሎ ሲመክር ሲታመስና
ሲተራመስ ውሎ ማደሩ እዬተደመጠ ነው? እፍረት እኮ ክብር አይደለም - አይደል? ሎቱ ስብሃት። መጥኒ ለአንቺ ለእትዬ ትግራይ …
ቅል ቋንቁራው ይጠቅመኛል ብሎ ለሚያጋብሰው ድውይ መንፈስ …
·
ጥሞና!
የፈጣሪን ጥበብ ተዳፍሮ የሚገኘው የረከሰውና የበከተው
የቤተ መንግሥት ጠረን መታጠብ አለበት - በጥሞና። በአዲስ ቡቃያ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ አዳኝ ሃሳብ በአዲስ ልዕለ ንዑድ መንፈስ
መጽዳት አለበት የገናናው ኢትዮጵያዊነት መወሰኛ ምክር ቤት። ለዛውም እያንዳንዷ ቅንጣት እርምጃ በርከክ ብሎ በጸሎት፤ በሱባኤ፤
በስግደት፤ በድዋ መትጋትን ይጠይቃል - በጥሞና እና በተመስጦ። ሐዋርያት እኮ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሲሰጣቸው በጸሎት ነው የተጉት።
ለክብሩ ያደረጉለት አቀባላል በአርምሞ ነው። ስለሆነም ዘመናይነት ካባውን መሬት፤ ትቢያ ላይ መነጠፍ አለበት - ራስን ዝቅ አድርጎ።
ቅብጠቱ፤ ቅልጣኑ፤ ለዛሬ አይሆንም። ደወሉ ከባድ ነው ‚የመሬት መንቀጥቀጥ‘ ባልታሰበ ቀንና ሰዓት ግን በወሳኝ የነፍስ ጉዳይ ከች
አለ። ድምጹ የእዮር ነው። ቅንጥ እንዲቆም ነው እዮር መልዕክቱን በማስጠንቀቂያ የላከው። ምልክቱን እንዲያሳይ በተፈለገበት ቀንና
ሰዓት ነው ውሳኔው እንሆ የተላከው።
ይህን ልብ ያላችሁ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ
ማህበርተኞች፤ ሌሎችም አጃቢዎች ከልባችሁ በጥሞና ሆናችሁ፤ በተሰበረ ልቦና መመርመር የእናንተው ተግባር ይሆናል - ትእዛዝ ከቶውንም
አይደለም። እንዘምን የሚሉ ለውጥ ፈላጊዎችም ለውጥን መፍራቱ የፈጣሪን ደወል መጋፋት እንዳይሆንባቸው ከሚያመልኩት ዕምነት ጋር በውል
በጥሞና መቀራረብ፤ መነጋገር የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል አሁንም ትእዛዝ ከቶውን አይደለም። ጊዜ ሳያጠፉ ቢሆን ይመረጣል - በትህትና።
በአልባሌ ቀን አይደለም ይህ የመቀሌው የመሬት መነቃነቅ፤ ህውክት የተከሰተው። በትክለኛው ነጥብ ቀን ላይ ነው። የእዮር ድምጽ ርግጠኛ
ድምጽ ነው። ተረገጡን ልካችን እስከ ምን እንደ ሆነ ነግሮናል። „ልብ ያለው ሸብ።“
„እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክየይ ፤ ለሥራሽ ፤ ዋጋ ይሆናልና ፥ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ ፥ ይላል እግዚአብሔር ፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸዎ ይመለሳሉ። »
Ethiopia
- Dr Abiy ኢትዮጵያን ማሸጋገር ይቻላል!
Ethiopia
- ….ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች! ትለወጣለች!
እድልን በታማኝነት መጠቀም ያስፈልጋል!
አቤቱ! ማስተዋልን የፈጠርክልን መዳህኒተ ዓለም ክርስቶስ ሆይ! ማስተዋልን እንጠቀምት ዘንድ ለዕዝነ
አዕምሯችን ብልህነትን ግለጽለት።
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!!!!!“
(ከአቶ ለማ መገርሳ የተወሰደ።)
„ለአንዲትም ሰከንድ የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም!!!!“
(ከዶር አብይ አህመድ የተወሰደ።)
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። በቃችሁ ይበልን ፈጣሪ አምላካችን። አሜን! ሁሉም በሱ ነው። ሁሉም በእሱ እንዲሆን
ግድ ነውና።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ