ግብዕቱ አይቀሬ!

የበረከት የሸር ሸጎሬ፤ ግብዕቱ አይቀሬ!
ከሥርጉተ - ሥላሴ 14.03.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)
„ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው።“ (ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፰።)
·         ው በሀገሩ ተሰዶ በስደትም ተሰዶ። 
የስደቱ ዘመን 27 ዓመት ሆነው። ስደቱ የቁስ ቢሆን ምን ያህል ሚዛኑ ይቀል ነበር። ስደቱ የመንፈስም ጭምር ነው። ስደቱ የአዕምሮም ጭምር ነው። ይህ „ነፃነት“ የሚባለው ቅብዕ ቅዱስ በሀገሩ፤ በመሬቱ፤ በቀዬው ተሰቃይቶ ተሰዶ ነው የኖረው። ለዚህም ነው ዝልቦ ሃሳብ ተሸካሚው „ኢህአዴግ ባህሉን መልቀቅ የለበትም“ የሚለው የአቶ በረከት ሴራ ልቅልቅ ቅዠት። የአቶ በረከት የሸር ሸጎሬ ግብዕቱ ግን አይቀሬ ነው። አይችለውም ይህን የኦህዴድን „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ገድለ ታምር።
·         የወል አዱኛ  እና ፈተናው።
ኢትዮጵውያን የወል አዱኛችን የምንለው በቅኝ አለመገዛታችን የሰጠን የሥነ - ልቦና ልዩ የመንፈስ መቅኖ ነው። ይሄን የዘመናት ገድለ - ታሪክን የአቶ በረከት ስብዕና የመሸከም አቅሙ ራሱ ዝልብ  ነው። ለኢትዮጵውያን ግን በነፃነት መኖር የሰጠን ረቂቅ መንፈሳዊ ሲሳይ ስላለ ቀን ቢበራከትም እውን መሆኑ ግን አይቀሬ ነው። ይህ መንፈስ የትኛውም መዝገበ ቃላት አይተረጉመውም። ከእኛም አልፎ ተርፎ አፍሪካን በሥነ - ልቦና ሙላት አይዟችሁን የቀለበ የማይነጥፍ ጥገት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጥቁር ህዝብ ነፃነትን በመዳፉ መሥራቱን ዓለምን አስተምሯል። ሐዋርያ ነው፤ ሰባኪ ነው ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት አፍሪካዊንት ብቻ ሳይሆን ብሄራዊነትም ነው። ተፈርያንን ማሰብ ልባምነት ነው። ገድሉ የጥቁር ህዝብ የማድረግን፤ የሥነ - ልቦና ሥልጣኔም ምንጩ ይሄ የተጋድሎ የመስዋዕትነት ዓርማ ነው። ይህ ትርጓሜ እርግጥ ነው ውጪ ሐገርም የሥነ - ልቦና የጥቃት ሰለባነትን ታድጎልናል። አጽናኛችንም ነው። በብርታት ይዳስሰናል።
በሌላ በኩል ሳዬው ግን የውጪ ርዕዮት ዓለም ማርክስዚም ሌኒኒዝም ስታሊንዝም ማኦኢዝም እንዲመራን መፈቀዳችን፤ በዛ ላይ የንቃተ ህሊናችን ደረጃ ከፍ ብሎ የሥነ - ልቦና ለውጥ ማምጣቱ በራሳችን ተጋድሎ በመጣው ነፃነታችን ላይ ወረራ አላካሄደም ማለት አልችልም - እኔ በግሌ። በሥነ - ልቦና ተቋማችን ውስጥ የተሠራ አዲስ የወረቀት ሃውልት አለ። ይህ ሃውልት ዛሬም ድረሰ ባሪያ አድርጎናል። ባርነት የግድ በሌላ ሰው ሥር በጉልበት ሥራ ሥር መውደቅ ማለት አይደለም። ማንነትን እዬሸረሸሩ በሚሄዱ የሰለባ ዕድሮችም አብሮ መከተም ባርነት ነው፤ ለዛውም የመንፈስ ወይንም የአዕምሮ - የህሊና። ስለዚህ ቅድመ አባቶቻችን/ አያቶቻችን ራሳቸውን ገብረው፤ ዋጋ ከፍለው በሰጡን ነፃነት ተጠቃሚነታችን እኔ ሳሰላው አንብዛም ነው። ፈቅድን እራሳችን ያጣንባቸው አምክንያዊ ክስተቶች በርካት ስለሆኑ። የትናንቱን የኢህአዴግን ስብስብ እማዬው ከዚህ አንጻር ነው  - እኔ። አባቶቹ/ እናቶቹ ያጎናጸፉትን ብሄራዊ ነፃነት ፈቅዶ ለባርነት የሰጠ ግንባር ነበር ኢህአዴግ። የዛሬን አይድርገው እና ወያኔ ሃርነት ትግራይ ግንባር ተብዬውን እንዳሻው አንበርክኮ የሚገዛው፤ የሚነዳው፤ ጭቃ በልንቁጦ የሚያስቦካው፤ የሚያስጋግረው፤ ሲያሻውም ጠምዶ እንደ ከብት ቀንበሩን ጭኖ የሚያርሰው ነበር። ዛሬ ኦህዴድ እንደ ድርጅት በለማ አብይ መሪነት፤ የገዱ መንፈስም ቅኖችን አክሎ „ከባርነት የአንድ ቀን ነፃነት“ ብሏል። ማለፊያ! የዘመን ልዩ ጥርጊያ መንገድ። አስደሳቹ ነገር ክህሎቱ ድርጁ መሆኑ፤ መሰናዶው ሙልዑ መሆኑ። ሥነ - ልቦናው፤ በራስ የመተማመን ብቃቱ ከሚስጢሩ የተነሳ በመሆኑ ስጦታ ነው። ሽልማትም።

በሌብነት ርክስና የከተሙ፤ በዝማዊነት የበከቱ፤ ንጹሑን ህዝብ ሰው በመግደል የተዘፈቁ፤ በማረድ የጨቀዩ፤ በጭካኔ የዘለቡ፤ ከቀዬ በማፈናቀል፤ በማሳደድ ዝክረ ዘመናቸውን በክፋት እና በሴራ የተሞሸሩ የወያኔ ሃርነት አውራሪሶች ደግሞ ይህ ዘመን ብርክ አስይዞ ይሄው የእንብርክክ እያስኬዳቸው ነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው፤ የእኔ ሲሉት፤ ውስጤ ግርማዬ ሲሉት፤ ንጉሤ ማዕረጌ ሲሉት፤ በሁለመናዬ ተንፈራሰስ ተብሎ ከልብ ሲቀረብ ማንም የማይደፍረው መንፈስ ነው … ነበልባል፤ ቋያ፤ ሞገድ! ካለ ብርጌድ፤ ካለ ክ/ጦር/፤ ካለ አዬር መቃወሚያ፤ ካለ ምድር ጦር እና አዬር ሃይል ወያኔ በእያንዳንዷ ደቂቃ የብርክ ቤተኛ ሆነ እሰከ ማህበረተኞቹ። ምን ይዟል የለማ መንፈስ? ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ብቻ ነው በመዳፉ ያለው። ቀለሃ የለው - ወገብ ሙሉ ባሩድ አልታጠቀ - ሳንጃ ዝምት አላለ። ግን ምድር ቀውጢ ሆነ። እነምርኩዝ ደፋ ቀና ይላሉ … ያለቀባቸው ዕብኖች።  
  • ·         ልቦ።

አጠቃላይ በመርህ ደረጃ እንደ ዜጋ የሶሻሊዝምን ንድፈ ሃሳብ መቀበሉ ላይበቃ፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ራሱ ጣር ላይ መሆኑ ነበር አደጋው። ያልበረከተው የአቶ በረከት የሸር ዝልቦ „የኢህአዴግ ባህልን ማስጠበቅ“ የሚሉት ይሄን ነው። ምን ማለት ነው ይሄ? ቀደም ባሉት ጊዜያቶች የጦርነቱ ቀጠና የትግራዊነትን የሥነ - ልቦናዊ አብዮት በኢትዮጵያዊነት ሥነ - ልቦና ላይ የመተካት ሂደት ነው በማለት በተከታታይ ጽፌያለሁኝ። ይሄ የአቶ በረከት የሸር ዝልቦ ሸጎሬ ሃሳብ በኢትዮጵያ ላይ፤ በሁለመናዋ ወረራ አካሂዶ የትግራዊነትን ሥነ - ልቦናዊ አቅም የሚያንጠራራ የ27 ዓመት መርግ ነበር። ከቶውንም የማይደፈር፤ የማይከሰስ፤ የማይወቀስ፤ የመይነቀስ፤ ከበትረ የሥነ - ልቦና አቅሙ የሚነቀንቀው የሌለ አለት ተደርጎ ተመልኮ ነበር። ዛሬም ይህን ማስቀጠል ነው የሸር ዝልቦው የውጪ ግቢ ነፍስ ጣር። በቀጥታ ኢትዮጵያ በቅኝ ባትገዛም ግን በተዘዋዋሪ ምርኮኛ አዕምሮ መፍጠር የሴራው ቸረቸራ  የአቶ በረከት ስምዖን የማያንቀላፋ ትልም ነው። የ3 ሺህ ከዛም ያለፈ የኢትዮጵያ ታሪክ ባለቤትነት ህመማቸው ነው። ቢችሉ ኢትዮጵያ ከዓለም ካርታ ብትሰረዝላቸው ይወዳሉ። ይሄ በህሊናቸው መስጥረው የያዙት በበታችነት ስሜት ወገሚቱ እንዳለዬለት እርጎ ሲንጣቸው የኖረ የጭንቅላት ካንሰራቸው ነው። ከቶ ከእንግዲህ ምን ያህል ዘመን ይኖሩ ይሆን? መቼቱ ተንባይ ቢገኝ እንዴት ጣዕሜ በሆነ ነበር። 
ኢትየጵያ እንመራለን ብሎ የተሰባሰበው ግንባር ኢህአዴግ „ባህል አለው“ የሚባለው ይሄን ነው። በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳሳስብኩት ያልታዬው የጦርነት ቀጠና በትግራዊነት እና በኢትዮጵያዊነት መካከል ያለው የተቃርኖ ሴል መስረታዊ አመክንዮ ነው። ይህ የናዚዝም ፍልስፍና አንድን ጎሳ ለዛውም አናሳውን አጎልብቶ፤ አቅም ፈጥሮ በመዋጣት ሌሎች ነፃነታቸውን ገብረው የህሊና ባሪያ አድርጎ አጉብጦ የመግዛት የተጋድሎ እንብርት ነው። ዋናው አንኳር ጉዳይ ይሄ ነው።
እጅግ በጣም  ብዙ ኢትዮጵያዊ ተቋማት በይፋ ፈርሰዋል፤ የምድር ጦር፤ የአዬር ሃይል፤ የባህር ሃይል፤ የሰንደቅዓላማችን መርህ የነበሩ የአርበኝነት ምልክቶች ሁሉ ወድመዋል - ተደምስሰዋል። ተዘርፈዋልም። በይፋ ያልፈረሱት ደግሞ በትግራዊነት ተተክተዋል ወይ ደግሞ የሌላ ሐገር ስሜት ጥገኛ ሆነዋል። ያን የመሰለ የሆለታ ገንትን የመኮንኖች ማስልጠኛ ቀደምት ታላቅ አፍሪካዊ ተቋምን፤ የደህንነቱ ማስለጠኛ የተሰዬመበትን ሥያሜ፤ የፖሊስ ሹመኞች የማእረግ ሥም አሰጣጥን ስንመከልተ ሃይሎም፤ ክንፈ፤ መለስ አካዳሚ ወዘተ ሳጅን፤ ኢንስፔክተር፤ ክፍለ ከተማ …. ወዘተ … ይህ ሁሉ ሸር ጉድ ኢትዮጵያን ትውፊት አልቦ በማድረግ አንድን ጎሳ ትግራዊነትን ከልክ በላይ አሳብጦ፤ ለጥጦ እና ወጥሮ ጉልላት ማድርግ ነበር ተልዕኮው የአቶ በረከት የቅይጥ ተልዕኮ ዘመን።
የኢትዮጵያ አዬር መንገድ እና ኢትዮ - ቴሌ ኮምም ዛላቸው ብቻ የሚታይ ግን የሆድ ዕቃቸው ለትግራዊነት የሥነ - ልቦና የበላይነት አቅም ሰጊድ - ለከ የሚሉ ናቸው። አዬሩ እራሱ ብክለቱ ኢትዮጵያዊነትን የተጸዬፈ ነው። ከትግራዊነት ጋር አዳቅሎ ቃላት በመፍጠር አዲስ ሥያሜ ማብቀልም ሌላው ያልታዬ፤ ያልተዳሰሰ የመንፈስ ወረራ ነው። ለምሳሌ … የፊልም ተዋናይ ሥምን በሚመለከት ያልተመጣጠነ እጅግ በጣም ብዙ መሬት ያያዙ ተግባሮች ተሰርተውበታል። ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የሚመደቡት ምርጥ ዘሮች የመጀመሪያ ተልዕኳቸው የኢትዮጵያዊነትን ንጹህ አዬር በትግራዊነት መተካት ነው። ልዩ ግዳጅም ይሰጣል። ከሀገራዊ ቋንቋ ይልቅ በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ የሚፈጠሩ አካላትም እጅግ የተመሰጠረ ወረራ አለ። „ኮሚሽን፤ ኮማንድ ፖስት፤ ፌዲራሊዝም“ ወዘተ … እነኝህ በአማርኛ አቻ አላቸው። ግን በአማርኛ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት ያመነጫል ተብሎ ይፈራል። የጥገኛ ቋንቋ በማያስፈልጋቸው ቦታዎች ሁሉ የሌላ ባዕድ ሥያሜዎች መዘውተር ማለት „ኢትዮጵያ ማለት ነፃ ህዝብ የሚኖርበት መሬት“ የሚለውን ይለፍ እንዳይሰጠው ታስቦ የተከወነ የሴራ ክምር ነው። „ኢትዮጵያዊነትን“ ከሚያነሱት ይልቅ ክልላዊ፤ ጎጣዊ፤ መንደራዊ ሥያሜዎች አቅም እንዲያገኙ በበቂ ሁኔታ በከፍተኝ የትምህርት ተቋማት ሁሉ በመደበኛ በተከታታይ ተስርቶበታል። የዚህ ማህንዲሱ ደግሞ የሴራው ቋንጣ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው።
  • ·         ታ አልቦሽ የመንፈስ ወረራ ለባርነት።

የወያኔ ሃርነት ትግራይ በወረራ በያዘባቸው ቦታዎች ጌታ የለበትም። ኢትዮጵያዊ ዜግነት አይታሰብም። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ልሙጡ ብሄራዊ ሰንድቅዓላማም ህልም ነው። አማራነትም ከእነ ሙሉ አካሉ በሁሉም መስክ አቧራ አንዲለብስ ተድርጓል። ይህ ቀና እንዳይል ደግሞ ለባርነት ዘመቻ የተሰዬሙት የሴራው ቋንጣ አቶ በረከት ስምዖን አማራ መሬትን በዙፋን ገዢነት ስጥ ለጥ አድርገው 27 ዓመት ሙሉ ቀጥቅጠው - ሰንጥቀው - ፈላልጠው - ገዝተውታል። በወልቃይት፤ በጠገዴ፤ በራያ ያለው ዜግነት ትግራዊነት ብቻ ነው፤ ያለው ማንነትም ትግራዊነት ብቻ ነው። አውራው ማንነት ኢትዮጵያዊነት ሆነ ቤተሰባዊ ማንነትም ሁለቱም እንዲጠፉ ተደርገዋል። ተጋድሎው በሞትና በመራራ ደም ተወራርዷል። ባዶ ስድስት ለዚህ የተፈጠረ የናዚ ኦሾትዝ ነው።

ይገርምኛል አሁን „አድዋ“ የሚባል የጥቁሮች ማዕክል ለመፍጠር ትግራይ ላይ ያለው ሸር ጉድ ነገር። በዚህ ቦታ ፓን አፍሪካኒዝምን ለመመስረት የህሊናው ሜዳ ኢትዮጵያዊነት ነው። ይሄ በሌለበት እንዴት እንደ ታሰበ እራሱ ይገርመኛል። አድዋ ላይ እኮ ተዘርዝረው የማያልቁ የማንነት ህብረ ቀለማት ያሉበት ርቅቅናው እንኳንስ ይሄ ትውልድ መጪው ትውልድ ራሱ ባለ በሌለ አቅሙ ላጥናው፤ ልስራው፤ ልመራመርበት ቢል ዲካውን ማግኘት አይቻልም። እጅግ በጣም ሩቅ ነው - ምጥቅ። በአንድ ጎሳዊ ዕብጠት የሚመራ አፍሪካኒዝም ሊኖር አይችልም። መጀመሪያ ያ ሚስጢር ምን ስለመሆኑ ቢታወቅ ዛሬ ለአንድ ሰው አንድ ቀልሃ ባልጠፋ ነበር። ቀድሞ ነገር ሌላም የትውስት ፖለቲካዊ ማንፌስቶ ባለስፈለገን ነበር። 

ለኢትዮጵውያን ቀርቶ ለጥቁር ህዝቦች የወል ማንፌስቶ ነበር „አድዋ እና ትንግርቱ።“ ዘመናት፤ ወቅታት፤ የተፈጥሮ ውበቶች ሁሉ አብረው ታድመውበታል። ፍጥርት ለአንድ ዓላማ እና ግብ በዬችሎታው እንደዬአቅሙ፤ በተደራጀ ብልህና ብስል አመራር ያታደሙበት የድል አዲስ ቡኒ ፕላኔት ነው አድዋ። የእኛ ፖለቲካ „ከሰው“ መነሳት ተስኖታል አድዋ ግን „ዱላ፤ ባርኔጣ“ ሳይቀር ታድሞበታል። የምንተራመስበት የፖለቲካ ውጣ ውረድ ሁሉ ከዚህ የሚስጢር ነፍስ መነሳት ባለመቻላችን ነው። የፖለቲካ ቀውሱ መሰረት ይህ ሚስጢር በመዘለሉ ነው። እስከ አሁን የተደከመበት ድካም ሁሉ በከንቱነት መክኖ የቀረው ወረቀቱ ማለትም የሚዘጋጀው የፖለቲካ ማንፌስቶ እና ህሊናችን ውስጥ ቀብረን ከያዝነው መርዝ ጋር ባለመታረቃቸው ነው። ለዚህም ነው ቀዳዳችን ብዛቱ፤ መከራችን ስፋቱ ልክ የለሽ የሆነው። አፍሰን ስንለቅም፤ ለቅመን ስናፋስ …
ስለሆነም ኢትዮጵያ በጠላት በቅኛም፤ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝም ተግዝታ አታውቅም። ማራኪ ታሪክ ነው። በግልጽ የራስ ማንነት ወልቆ በትግራዊነት በግዳጅ እንዲሆን መደረጉ በጥልቅት ሲታይ የአድዋ ትሩፋት ነፃነት ተሽጧል፤ ተለወጧል። ይሄ የአድዋ ታሪክ  ለሽር ዝልቦው ለአቶ በረከት ስምኦን እና ለተልኮአቸው የውስጥ ቃጠሎው ነው። የነደዱበት። የተቃጠሉበት። ያረሩበት። የተኮማተሩበት። ኩፍትርትር ያሉበት። ስለዚህ ይህን ከፍ የሚያደርግ ያልታሰበ ትንግርት ግዮን ላይ ሲገለጥ ውጥረቱ ፈናዳ። ቦንቡ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ ነው። ለዛውም አማራ መሬት ላይ። ተመስገን!
  • የጦርነቱን ቀጣና፤ አቅጣጫ ሁሉ በስክነት ቢመዘን ኢትዮጵውያን በጠላት ተገዝተን አናውቅም፤ ነፃነታችን ጠብቀን ኑረናል፤ የአዕምሮ ነፃነት ያለን ህዝቦችን ነን የምንለው ነገር መነሻው ሥህነ - ልቦና እያጣ መሄዱን የካሰ ነበር የግዮን ድምጽ። ይህን ጥሶ ትግራዊነትን ለማስቀጠል ነው „ኢህአዴግ ባህሉን መልቀቅ“ የለበትም የሚለው የኤርትራዊው የአቶ በረከት ስምዖን እና የግብር ግድሞቹ የአሁኑ የክተት ዘመቻ።

አሁን ያለው የፍልሚያ ሜዳ የቅኝ ግዛት ወረራን መቀበል ወይንም እሱን አፍንጫህን ላስ ብሎ ወደ ሚስጢር መመለስ። ለረጅም ጊዜ ተመስጥሮ ተይዞ የነበረው ገመና ከእነ ቅል ቋንቁራው መውደቁ አይቀሬ መሆኑ፤ እንደገና መወለድ ነው ለኢትዮ - አፍሪካኒዝም ዓርማዋ ለኢትዮጵያ - ለሎሬቱ ታቦት - ለይድነቃቸው ቅድስና - ለአፍወርቅ ጽድቅና።
እርግጥ ነው በታወቀ ሁኔታ የበታችነት መንፈስ የሚንጠው ለአናሳው ቡድን ይህ ጥልቅ የሆነ አስፈሪ ነገር ነው። ጎምዛዛም ነው። ማቄን ጨርቄን እያለ መዝረክረኩ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው በመታበይ ውስጥ ላለ ድውይ መንፈስ ውስጥን ይለበልባል፤ ያቃጣላል፤ ረምጥ ነው ያርመጠምጣል። ምርቅ ብስጭት ነው ጎልቶ ልናዬው እኛ የማንችለው። የሚዲያ ስንቅ ሆኖ የቆዬው የማንፌስቶ ትርምስ ሁሉ ጥሬ ዕቃ ያጣል። ለዚህም ነው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“ በሚለው መንፈስ አቅም ከማዋጣት „ኢትዮጵያ ካልፈራረሰች ኦሮምያ ነፃ አትወጣም“ የሚለውን ሃሳብ ጋር ሙግት ጣዕማችን እንዲሆን የምንፈቅደው። አላስፈላጊ ብክነት የመንፈስም፤ የሥነ - ልቦናም።

ለስላሳው፤ ቀናው ጥዑሙ መንገድ እያለ ዳገት በዳጥ ያሰኛል። በዚህ ጉግስ ስንት የኢትዮጵያ እናቶች አምጠው የወለዱትን ልጅ እንደ ገበሩበት አስታውሰነው አናውቅም። ዛሬም ይሄው እንዲቀጥል እንመኛለን። እንመራዋልን የምንለው ህዝብ በአንድ ሃሳብ በመሰባሰቡ አቀባባሉን ውብ ማደረጉ „ተደባልቋል“ ማለት አንድነቱን ለፖለቲካ ትርምስ ታዘዝ እንደማለት ነው - ለ እኔ። አንድነት ይፈራል። ልብ ተክፍሎ ያቺ መከረኛ አሁንም የልጅ ልኳንዳ ቤት እንዲከፈትላት እናልማለን። አንድነቱ መንፈሱ በሥራ የመጣ እንጂ በተራ ፕሮፖጋንዳ የተወለደ አይደለም። አንድነቱ ደግሞ በብዙ ቅናዊ ክሮች መጠለፉ የተስተዋለ አይመስለኝም - አንዳንድ ቃለ ምልልሶችን፤ ምኞቶችን ሳዳምጥ - ውስጤ ያዝናል።

ወደ ብሄራዊነት ስንመጣ ቅንጅት ያገኘውን የመንፈስ ሃይል ያህል ማንም አለገኘውም። ግን መሪ አልነበረውም - ሴራን አሸንፎ ልቆ የሚወጣ ሙሴ አልታደለም። ሃሳብ ብቻውን የኖኽ መርከብ አይሆንም። ሃሳብን የሚመራ፤ አቅጣጫን የሚቀይስ ማሃንዲስ ወይንም ዲዛይነር ያስፍልገዋል - ለብሄራዊ ራዕይ። ያን ያህል መስዋዕትነት የከፈለው ህዝብ „እንመሰግናለን“ እንኳን ሳይባል ተበትኖ ቀረ። የፖለቲካ ሊሂቁ ዶር መራራ ጉዲና አንደሚነግሩን ከሆነ እሰከ አሁን ድረስ በእስር አካል ጉዳተኝነት እንዳሉ ነው። በክ/ ሀገር እማ አብሶ ወሎ ቤቱ ይቁጠረው። ማን አስተውሷቸው። ስበስብ ይፈጠራል፤ ሰው ይገበርበታል፤ ይፈርሳል፤ አዲስ ደግሞ በአዲስ ሥያሜ ቤት ለእንግዳ ይባላል፤ ምን ችግር አለ? የፈረደባት የኢትጵያ እናት የሰው ልጅ ፋፍሪካ አይደለች? ለአዲሱ የሰው ልኳንዳ ቤት ወገቧን ጠበቅ አድርጋ አምራች ናት። ምን ሲገዳት ጥቁር ልብስ ለምግዛቱ። አሁንም የሚፈለገውም ይሄው ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“  „ከቅንጅት መንፈስ ነው“ በላይ በላይ ነው በላይ ነው። መንፈሱ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት የህብርት ማንፌሰቶ ብቻ አይደለም። አፍሪካን ነፃ ያወጣ የጥቁር ልዩ ቀለም፤ የዘመናት ትንግርት ነው።

ይህም ብቻ አይደለም አደራውን ለመወጣት ተተኪ አቅም ከምንጠብቀው በላይ ተዘጋጅቷል። ተተኪ አቅምን በመስበር ተጥምዶ የነበረው „የኢህድግ ባህል“ አከርካሪውን በጽኑ ድዌ ተመቷል። ወረርሽኝ ገብቷል ከነወያኔ። ከእንግዲህ ለኢህአዴግ የትግራዊነት ባርንት ኦህዴድ ይንበረከካል ተብሎ አይታሰብም። በፍጹም! በፍጹም! በፍጹም!
የትናንት ነፃነት ዛሬ ለባርነት የዳረገውን ሥርዓት ሃሳብ ታግሎ በማሸነፍ የአዲስ ብሩህ ሃሳብ የመንፈስ ባለሟል ነው - ኦህዴድ። በበቃ፤ በጥበብ በሰከነ፤ በብልጹግ ሰብዕና፤ በበቀለ በራስ አቅም፤ በእኛዊነት ተመክሮ ውስጥ በታደመ አዲስ ሰዋዊ፤ ተፈጥሯዊ፤ ልባዊ ፍልስፍና ለድል ያጨው አደአደር ነው - እንደራሴ። ያ የኢህአዴግ ምንትሶ … ቅብጥርሶ … አንቶ ፍንቶ … ምናምንቴ ድሪቶ ቀልቀሎ „ የ ኢህዴግ ባህል“ ቀልድና ቧልት አብቅቷል። „በድሮ በሬ አርሶ የከበረ … „ አንዲሉ። ለዘነዘነው ውዝዋዜ ባንድ ከፍቶ እንደ አቅሙ ለመኖር ማሰቡ የተሻለው መንገድ ነው እንደ እኔ። ሲያልቅ አያምር እንዳይሆን … መመኪያ አንዲት የሥነ - ልቦና አቅም የለም። በሸፈተ ልብ ውስጥ ትግራዊነት እንደ ገና ይንሰራራል ተብሎ አይታሰብም። ተጠልቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንቅሩ ተፍቶታል። እዬሞተ ለመኖር የሚፈቅድ አንድስም ነፍስ አይገኝም። „ሰው የጠላው እግዚአብሄርም የጠላው ነው“ ለነገሩ ዕምነቱ ሲኖር ነው … አወዳደቅን መሳመር ቢያንስ አዘውትሬ እንደምናገረው ላልተፈጠሩት የትግራይ ህጻነት ቀጣይ መከራን ይታደጋል።
  • ·         ዕዶተ መሰናዶ።

ዝልቦው ዝልብ ቅዠቱን ይዞ ወደ መቃብር መውረዱ ዛሬ ሳይሆን ቆይቷል። እያንዳንዱ ኦሮምያ መሬት ላይ የሚሊዮን መንፈስ ሐገራዊ ሐላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ተሰናድቷል። ይሄ ትጥቁን ያሳመረ መሰናዶ እንደ ተለመደው በተኮረኮመ ፍልስፍና ማሸነፍ አይቻልም። የለማ አብይ መንፈስ አቅሙ ከአቅሙ ሚስጢር ስለተነሳ የሠራዊት ጌታም ሚስጢራዊ ዕድምታ አለበት። አሸናፊ የሚያደርገው የእናቱን ይሁንታ፤ ምርቃትን በርከክ ብሎ በትሁት አክብሮታዊ ልስላሴ ምራኝ በማለቱ ነው። በዚህ መንፈስ ውስጥ እኔ፤ እርስዎ፤ እኛ ሁላችንም አለን። ቅንነቱ ካለ ተስፋም አለን። ሁላችንም በመበላለጥ ሳይሆን „በሰዋዊነት ተፈጣሯዊነት“ ቤተኛ ነን በማዕዱ። „ነፍስ ጎሳ የላትም ነው“ የሚሉት። „ኢትዮጵያዊነት የገብያ ሸቀጥ አይደለም። አንድነታች ለደቂቃ ስጋት ሊገባው አይገባም፤ አንዳችን ለአንዳችን የምናስፈራ ሳይሆን፤ አንዳችን ለሌላችን ጋሻ - መከታ - ጥግ መሆን መቻል አለብን፤ ኢትዮጵያዊነት ከጅብ ቆዳ የተሰራ ከበሮ አይደለም። ኦሮሞም ኦሮሞ አማራም ነው፤ አማራም አማራ ኦሮሞም ነው፤ ጉራጌ ጉራጌም ኦሮሞም ነው፤ ትግሬም ትግሬ ኦሮሞም ነው፤ ከንባታም ከንባታ ኦሮሞም ነው ወዘተ … ። ለኢትዮጵያ መዳህኒቷ ህዝቧ ነው፤ ለህዝቧ መዳህኒት የመሆን ታሪካዊ ተልዕኮ አለብን። አመላካከታችን አጥብን ማዬት የለብንም ጎንደር ማን አለው? 80ብሄር ብሄረሶቦች ማን አላቸው? እኛኑ ነው የሚጠብቁት። ጥያቄ  ተሸከመን ከትወልድ ትውልድ መሸጋገር የለብንም፤ ጥያቄ ሳይሆን መልስ ማውረስ አለብን፤ ይልቅስ ሁናችሁም ተሰናዱ“ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከገዳው የአባቶች ተምክሮ እስከ ሃይማኖት መሪው ድረስ እንደ አንድ ቃል ተናገሪ አንድ ልቦና አሳቢ መንፈስን ሰብበሳቢ ነው ያለው። ፍቅር - መቻቻል - መከባበር - መደማመጥ - መተዛዘን - መረዳዳት ለናፈቀው ከቅዱስ ወንጌል በላይ ነው - ለቅኖች።

የሚደመጠው የዕንባ ድምጽ የኪዳን የምህረት ድምጽ ነው። የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንደ ገና መወለድ Renaissanceይሄ አድነኝ እኮ ድንበር አቋርጦ፤ ውቅያኖስ ጥሶö ስንት ማይል ተጉዞ ጽናትን በማጽናናት፤ አይዞህን/ አይዞሽን በቅንነት እዬመገበን ነው። ቢያንስ የጸሎት አቅም ያነሰናል? ያን ትብትብ በግፍ የዘለበ የኢህአዴግ የበቀል ተርቲም አንኩት ብሎ መቃብር ይወርድ ዘንድ ተንበርክክን ኤሉሄ ማለት ያቅተናል? እንኳስ ስንት አማራጭ እያላል። አሁንም ይቻላል ሁሉም ይቻላል እንደ ቃሉም ይሆናል። 
  • ·         ስለማግሥት።

ይሄ የኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ ለሚያርበደብደው፤ የውስጡ ቁስለት ለመገለበት ኤርታራዊው አቶ በረከት ስምዖን እና ለካቢናያቸው የስለላ መረብ ሴላቸው የቀብር ሥርዐት ነው። ስለዚህ የህሊና ባርነቱን ለማስቀጠል መንደፋደፉ የሚጠበቅ ነው። በግልጽም በስውርም ግን አይቻልም። ነፃ ህዝብ ነፃነቱን የቀማውን አውሬ ለደቂቃም የሚያስጠጋበት የአዕምሮ ግድግዳ የለውም። ጊዜ እንዲህ ይክሳል። ጊዜ እንዲህ ወርቅ ነው መከራን አንጥሮ የመንፈስን ድል ያጎናጽፋል። በሥነ - ልቦና ወያኔ ሃርነት ትግራይ እስከ ሪሞርኬው ከሞተ ቆዬ። ዓመቱን ሁሉ የሥብሰባ ጋጋታ፤ የመግለጫ ኳኳቴ፤ የዓዋጅ ትርምስ ውልቅልቁ የወጣው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ትግራዊነትን በሃይል የመጫን ህልሙ ብትንትኑ ስለወጣ ነው። ተመቷል። ጠበንጃው፤ ባሩዱ፤ መድፉ፤ መትረዬሱ አዬር መቃወሚያው በራሱ በረዶ ነው። ሰው ሊገድል ይችላል። ንብርት ሊያውድም ይችላል። የ„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የጸዳለ ጸደይን መንፈስን ግን ከጫፉ መድረስ አይችልም። ንክች አያደርጋትም። ሚሊዮን ወታደር አለው - ለማንፌስቶ ፍቅር ያላደሩ ቅኖች ሥነ - ልቦናቸውን ፈቅደው ሸልመውታል። ፈተናው ግዙፍ ቢሆንም በሰለጠነ አዕምሮ፤ በታቀደ ጥበብ እና ማስተዋል ይወጣዋል። ዘቦቹ በዬትም ቦታ፤ በዬትም ሁኔታ አለነው። ኦሆዴድ እንኳን ኢትዮጵያን አፍሪካን የመምራት ሙሉ ፓለቲካዊ አቅም አለው። ለዛውም በስብአዊነት። ሰብአዊነት ከዴሞክራሲም በላይ ነው! በፍሬም ተድሮ ተኩሎ 43 ዓመት ግድግዳ ላይ የተንጠለጠለው ፓስተር ለቅርጫት እራት ….

ኢትዮጵያዊ ሥነ - ልቦና አንዲኮስስ አንቆ በመያዝ የተለያዩ ጎጆዎች ሠርቶ ግን በዛ በተሰራው ጎጆ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዊ የሥነ - ልቦና አቅሞችን በሂደት እዬሰለቡ በማክሰም ትግራዊነትን የማሰልጠን ተግባር ተሰርቶበታል። ትግራዊነትን የበላይነት ልዕልና አድርጎ ማውጣት ከእንግዲህ ግን ፈጽሞ የሚታለም አይሆንም። ለዚህ ለህብረ - ብሄር እንተጋለን የሚሉት ሁሉ እዬተሸነፉ ያሉበት ጉዳይ ነው። ስለምን? ኢትዮጵያዊነት ሆነ ዴሞክራሲያዊነት በመሆን ውስጥ መታየት ስለተሰናው። ተጠበቀ፤ ተጠበቀ፤ ተጠበቀ ግን፤ ግን ሆኖ ቀረ። ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ተሰደደ … ተመስገን! ተስፋ ግን ቀለቡን ፈጣሪ ሰጠው።
  • ·         ሞክራሲ ለሳር ቅጠል አልተሰዬመም። እንደ መከወኛ …

ዴሞክራሲ ለሳር ቅጠሉ አይደለም። ዴሞክራሲ ለሰው ነው። ታዲያ ታዛ ተሰርቶ፤ እልፍኝ ተነጥፎ፤ ጓዳ ተኮልኩሎ ይሆናል? ሰው መሆን ብቻ ከበቂ በላይ ነው። የሰውን ልጅ ክብር ለማስጠበቅ ሰው ለሆነው ሁሉ እኩል ፍቅር፤ አኩል ቸርነት፤ እኩል ርህርህና፤ እኩል እውቅና፤ እኩል አያያዝ መስጠት። በሰው መሃል የክትና የዘወትር፤ ብረት እና ወርቅ መደብ ተለይቶ ዴሞክራሲ ታይቷል፤ ተስምቷል። ስለሆነም ቃሉ ለሰለቸው የእንባ ቤተኛ ቃር ነው በተለይም ለሥርጉተ - ሥላሴ።
እግዚአብሄር ይመስገን እለፈኝ - ቅደመኝ  - መሪህ ነበርኩ ተመሪህ ለመሆን ዝግጁ ነኝ፤ ስንዱ ነኝ፤ አጋዥ ረዳትህ መከታ ክንድህ ለመሆነም ቀዳሚ ነኝ የሚል ነፍስ በዘመናችን አዬን። ከዚህ በላይ ዴሞክራሲ ምን ሊጠበቅ ይችላል? ይህ በህልም እንኳን ይታሰባለን? 43 ዓመት ሙሉ መሪነት ዳግሚያ ሙጋቤነት ያዬነውም፤ የሰማነውም ይሄው ነበር … አብረን ኖርን አኮ ስንጠበቅ።
ይህ የመሆን አባት ያለው ያ … ጥዑመ መንፈስ፤ ያ … ልስሉስ መንፈስ፤ ያ … ተደምጦ የማይጠገብ መንፈስ እራሱ የዴሞክራሲ መጸሐፍ ሆኖ ሰበከ፤ አስተማረ፤ ሐዋርያ ሆነ ለማ የዘመን አናባቢ ቅዱስ ሰው… እኔ ጨለማ ሳይሆን ብርሃን ይታዬኛል። የሚያጠግብ። ቢያንስ ይህ መንፈስ ኦሮምያ ላይ ያሉት የዕንባ ቤተኞች የውስጥ ሰላማቸውን በመጠበቁ ብቻ ለእኔ ከሐሤት በላይ ነው። ቁስላቸው እንዴት እንዳቆሰለኝ አማውቀው ባለቤቷ እኔ እና የውስጤን ቁስል ያደመጡት ያውቁጣል።
በሌላ በኩል በኢሠፓ የማደራጃ መምሪያ ውስጥ ለሠራ ሰው የኦህዴድን ድርጅታዊ አቋም፤ በተመክሮው ውስጥ ያለው ብስለትና ጥራቱን ለማዬት ቀላሉ የቤት ሥራ ነበር። ለማሟያ፤ አማራጭ ስለጠፋ አይደለም። ብቁ ነው። ኦህዴድ አንጎል ብቻ ሳይሆን  አዕምሮም አለው። ይሄው ነው ከግንባሩ ተልይቶ ልዩ ጸጋው - የተሰጠው። ኢትዮጵያን ለመምራት ከሙሉ ሰብዕና እና ሞራል ጋር የጸደቅ ሙሴ ነው። ዕምነቴ ጽኑ ተስፋዬም ዝልቅ ነው! 
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“

ኦህዴድ አንጎል ብቻ ሳይሆን  አዕምሮም አለው! ፊርማ ገጭ።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
የኔዎቹ እስኪ እነብትክት ምን ይሉ ይሆን? ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ ስለሆነ በድል ተጋድሎውን ይወጣል ብዬ አምናለሁ።

ምን ልሸልማችሁ? ክብርት ወይንስ ኑሩልኝን? ኧረ ምን ገዶኝ ክብረቱንም ኑሩልኝም ተሸለሙ። መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።