ዐይንም ጠንካራ መልዕክት ይልካል።


ዐይን ቋንቋ አለው። ዐይንም 
ጠንካራ መልዕክት ይልካል። 

ከሥርጉተ - ሥላሴ(Sergute©Sselassie)
 02.04.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።) 

„እግዚአብሄርን አንዲት ነገር ለመንሁት፤ እርስዋንም እሻለሁኝ፤
 በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሄር ቤት እኖር ዘንድ፤ 
እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘውን አይ ዘንድ፤ 
መቅደሱንም እምለከት ዘንድ“ 
(ከልብ አምላክ መዝሙር ፳፮ ቁጥር ፬)


  • ·         ፍታ።

ትንሽ ነገር ማለት ፈለግሁኝ። ቋንቋ የፍቅራዊነት (LoveIsm) ረቂቅ ሚስጢር ነው። ቋንቋ የራሱ ሥርዓተ - ህግጋት አሉት። ቃል በሥርዓቱ ውስጥ ሲተገበር ሥርዓቱን ተከትሎ ቤተሰብ ይመሰርታል። የመጀመሪያ የቋንቋ ቤተሰቡ አረፍት ነገር ነው። አረፍተ ነገር ደግሞ ከፍ ያለውን ዞጉን ሲፈጥር ሐረግን ይመሠርታል። ሐረግ ሙሉ ገጽ ሲኖረው ልክ እንደ ፍጡራን ሐገር ይሆናል ቋንቋ - ለእኔ።
እንሰሳት ቋንቋቸውን የሚገልጹት ወጥ በሆነ ድምጽ ነው፤ በነገራችን ላይ የእንሰሳት ድምጽ በስዋሰው የተቀመረ አይሁን እንጂ ከሰብም በላይ ግሎባል ነው። ደንበጫ ያለው ዶሮ ኒዮርክ አካባቢ ካለው ገጠር ከሚኖረው ዶሮ ጩኽቱ ጋር ተመሳሳይ እና ወጥ ነው። ጋና ያለው ውሻ ሲዊዘርላንድ ካለው ጋር ተመሳሳይ ድምጽ ነው ያለው። አውስትራልያ ላይ ያለው በግ ይሁን ፈረስ፤ ፈረስ ይሁን ወይፈን ብራዚል ውስጥ ካለው ጋር ተመሳሳይ የድምጽ አገላለጥ አለው። እንሰሳትም እንደ ሰው አካላዊ ቋንቋ አላቸው ብዬ አምናለሁ። ፍቅርን ሲፈልጉ፤ ቁልምጫ ሲፈልጉ፤ አትኩሮት ሲፈልጉ፤ ታማኝነታቸውን ሲገልጹ፤ ሲበሳጩ፤ ጸጥታን ሲፈልጉ በአካላዊ ቋንቋ መልእክት ይልካሉ። 
ወደ ቀደመው ስመለስ ከሰብ የቃል አንደበታዊ ልሳን ጋር የአካላት ቋንቋም አለ። ጉልበታም እና ሳቢም ነው። ከአካል ቋንቋዎች ሁሉ ዓይን የሰውነት ቋንቋ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ፖስተኛም ነው - ለእኔ። መልዕክተኛ። እንዲያውም አንዱ መጻሐፌ ላይ በዕርስ ደረጃ ጽፌበታለሁኝ። „ርግብ በር ወይንም የተስፋ በር“ መጸሐፌ ላይ። የዓይን አካላዊ ቋንቋ መልክዕክት ውስጥን ፍንተው አድርጎ ያሳያል። መጋረጃ የለውም ወይንም ግርዶሽ። ለድምጽ አልባ ተውኔትም የዓይን ድምጽ አልባ ጉዞ ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ዐዕምሮም ነው ባይ ነኝ - እኔው።
  • ·         ሁለትዮሽ።

ዛሬ በኢትዮጵያ ሐገሬ የአዲስ ጠ/ሚር ሽግግር ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተከናውኗል። ስንብቱም በሚደንቅ ሥርዓት፤ መምህር በሆነ አስተምኽሮት ተከናውኗል። ተቋም ነበር ማለት ያስችለኛል። በዚህ ሂደት በርካታ ነገሮችን ተመለክቱኝ። ለዛሬው ያዬሁትን ሁለት ነገር አንዲህም ልገልጥ ፈለግሁኝ።
አዲሱ ጠ/ሚር ዶር አብይ አህመድ ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋዋላ ጓዶቻቸው ለሰጧቸው ፍቅር እና አክብሮት ደስታቸውን ሊገልጹ ከመድረክ ወርደው በቀጥታ ሄደው በዬቦታቸው ሲያቅፏቸው አንድ ረዘም ያሉ፤ ጥቁር መነጸር የለበሱ ደርበብ ያሉ የሐገሬ ሰው በደንበር ዓይነት የፈጸሙትን ተመለከትኩኝ። ፍቅርንም፤ አክብሮትንም፤ ትህትናንም መግፋት።
በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞው ጠ/ሚር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሲመጡ ሆነ በሥልጣን ከቆዩባቸው ዘመን ሁሉ እንደዚህ ከመላ ቤተሰባቸው ጋር ደስታን ቅረበኝ፤ ምራኝ፤ ሁነኝ ሲሉ አይቼ አላውቅም። የፈካ ውስጣዊ ሐሤት ነበራቸው። በፍጹም ሁኔታ ልዩና ተፈጥሯዊ ነበር። የባላቤታቸው የፊተኛዋ ቀዳማይ እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬም እራሳቸው ያሳዩት ትህትና እና ፍቅር ልዩ ሥልጣኔ ነበር። ሽግግሩ የህልም ያህል ረቂቅ መልዕክት ለእኔ ልኮልኛል ነጮቹ Dream like እንደሚሉት። እንኳንስ በሥልጣን ተቆይቶ ፓርቲዎች ተዋህደው ሲለያዩ እንኳን ማህበራዊ መሰረቱ ንገት ነው የሚገጥመው። የተገነባው ሁሉ ነው በጎራ ተክፈሎ ባልጠራ ልቦና ስናስተናግደው የኖርን። መራራ ዘመን። 

በሌላ በኩል በሥርዓቱ የተገኙት ሌሎችም ከአንድ ሰው በስተቀር እክሌ ተከሌ ሳይባል ያሳዩት ሥርዓት እና አክብሮት በእውነት ይህቺን ሐገር ኢትዮጵያን ፈጣሪ አምላክ እና እናቱ ድንግል ማርያም፤ በተጨማሪም ቅዱሳን መላዕክት፤ ጻድቃን ሰምዕታት ሁሉ ይወዷታል። መፈንቅለ መንግሥት ሳይኖር፤ እንዲህ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ፤ በታላቅ አክብሮት እና ኢትዮጵያዊ ሥርዓት ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ሲመተ - በዓሉ ሲከበር ይህ በራሱ ለእርቅ መንፈስ፤ ልቦናን ከፍት አድርጎ ነገን ለመቀበል ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው - ለእኔ። አዲስ ዘመን። በዚህ ክንውን ጥቃቅን ሳቢያን እያነቃቁ የሚበትኑ ሃሳቦች ሊከሰቱ መቻለቸውም የሚጠበቅ ነው። ተኖሮበታል። አጠቃላይ የሚያሰገኘው ተረፈ ዕሴት ሳይሆን፤ ክፍተት የሚፈጥሩ ሰባራ ሰንጣራ ሁነቶች አድምጡኝ፤ አትኩሮት ስጡኝ ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። ሂደቱ የነበረበት ፈተናም ይሄው ነበር። „ሰው“ የሚለው የክብር መጠሪያ ጋር እነዛ መቀንጠቢያ ሃሳቦች ለእኔ እንብዛም ናቸው/ ነበሩም። „ሰው“ የሚከበርባት „ሰውም“ የፈጠራት ሐገር ስለመሆኗ ኢትዮጵያ ሙሉዑ ዕውቅና ማግኘቷ ነው ለእኔ የሚስጢራት ሁሉ ዐዕማዴ። የኢትዮጵያ የቁምነገር ዓላማም ግብም የምለው ይህንኑ ጅማሪ ነው። ኢትዮጵያዊው ሰው እንደ ሰው መታዬት መቻሉ።

የሚቀረው የተቆጣጠሩ ትብትብ ቁርሾወችን አስታግሶ፤ መጪው ጊዜ ተስፋን እንዲጠብቅ ምልክት ሰጥቷል፤ ይህ ዛሬ የተካሄደው ክንውን ለእኛ እንኳን በስንት ማይል እርቀት ናፍቆታችን የተባረከ እንዲሆን ያደረገው መንፈስ ቀጣይ እንዲሆን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው ትውልዱን ከብክነት የሚታደገው። ለዚህም መንፈስን ለንጽህና ማሳ እንዲሆ መፍቀድ ያስፈልጋል። ከሴራ ጋር መፋታት። ከጥላቻ ጋር መለያዬት። ከምቀኝነት ጋር መሰናበት። ኢጎን መቅበር። ለማን ሲባል? የመጀመሪያው ለራሳችን የውስጥ ሰላም እና ጤና ሲባል። ባክነናል። ሁለተኛው ሐገር አለኝ ከማለት በላይ የመኖር ክብረት ስለሌ። በመቀጠል ዓውራው ነቁጥ ደግሞ ምንም ለማያውቁት ለነገ ህጻናት ሲባል። የኢትዮጵያ ልጆች ሐገራቸው ኢትዮጵያን የሚሳቀቁባት፤ የሚፈሯት፤ የሚሳደዱበታ ሐገር ሳትሆን የሚወዷት፤ የሚያፍቅሯት፤ የእኔ ብለው የሚሳሱላት ሐገር እንድትሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ትውልዳዊ ድርሻ ተልዕኮው ይሄው ነው። ፍቅርን ማውረስ። ፍቅርን ርስት ማድረግ። ፍቅርን ትውልድ ማድረግ።

ልጆችን ብሄራዊነትን እንዲያገኙት ማድረግ የሚቻለው በመሆን ውስጥ ነው። በውኑ ከእኔ የቀጠለው ትውልድ ብሄራዊ ስሜቱ እንዳይበቅል ብዙ ተሰርቶበታል። ለዚህም ነው ወጣቶች ውስጣቸውን ፈቅደው እያጡት የሄዱት። ወደው ግን አይደለም፤ ተገደው ነው። ይህ ፍሬ ነገር ከግቡ እንዲደርስ ህጻናት ሐገራቸውን ፈርተው ማደግ የለባቸውም። ተሳቀው ማደግ የለባቸውም። ደስታ የራቀው ትውልድ ነው ያለው። ስለሆነም ከፎቅ ድርደራው አጅግም በላይ በዐዕምሮው ላይ የተጋ የተግባር መስክ ታቅዶ መከወን ይኖርበታል። እርግጥ ነው ዛሬ ዕለተ ሰኞ መጸሐፍ ሊጻፍበት የሚገባ ተቋም ሲገነባ ልጆችም በዬበታቸው ሆነው ይመለከታሉ። ይህ በጎነት ግን በዬት/ቤቱ መሰራት አለበት። ቤተሰብም ውስጥ አነስተኛ የውይይት መድረክ ፈጥሮ በሐገር ባለቤትነት ላይ ተከታታይ ተግባር ሊከወን ይገባል። ግን ቤተሰቡ በቀልሃ፤ በካቴና ስንቅ የሚሆንበት ዘመን ማክተም መቻል አለበት። ልጆች ጠበንጃ እያዬ ማደግ የለባቸውም። ጠበንጃ ዳር ድንበር ይጠብቅ። ካለ የውስጥ ሰላም አዕምሮ መልካምነትን ለመቀበል አይችልም፤ አንጥሮ ይመልሰዋል። አባቱ፤ እናቱ፤ አክስቱ፤ እህቱ ወንድሙ የታሰረበት፤ የሚገደልበት፤ የሚፈናቀልበት ልጅ እንዴት ነገን በተስፋ ሊጠብቅ ይችላል? ስለሆነም „ሰላም“ ቃሉን ራሱ መተግበር ካላስቻለው ጥረቱ የእንቧይ ካብ ነው።
  • ·         ሰነፉ „የሰላም ምኞት“ …

„ሰላም“ ራሱ ሰነፍ ከሆነ የልጆች አዕምሮ ይጸዬፈዋል ራሱን „ሰላም“ የሚለውን ቃል። ስለምን? ዐዕምሮ የእኔ የሚለው የደስታ መሬት ስሌለው። ውስጥ ስላልተረጋጋ። የደስታው መሬት ሸማም ብሄራዊ ሰንደቅዓለማው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ የሚወደው፤ የሚሳሳለት ያው እስረኛ ስለሆነ። ቤተሰቡም በስጋት እና በቆፈን ነው የሚኖረው። በነፍስ ወከፍ የእያንዳንዱ ቤት የውስጥ ሰላሙ ታውኳል። ልጆችም የስጋት ቤተኞች ናቸው። የኢትዮጵያ ልጆች በሥነ - ልቦናቸው በእጅጉ ተጎድተዋል። ተጎሳቁለዋል። ጠበንጃ ልጆች ከሚኖሩበት ከተማ ውጪ በርቀት መኖር አለበት። የተፈጠረው ለሐገር ዳር ድንበርን ለመጠበቅ ብቻ እንጂ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸውን ልጆቿን „በኩራት¡“ ለመፍጀት አይደለም። ሞት ካለምንም ቅደመ ሁኔታ መቆም አለበት! የታሠሩት ይፈቱ ብቻ ሳይሆን መታሰረም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም አለበት! እራሱ ፋቲኩ የሞት ምልክት ማልያ ነው። መደበኛ ሥራውም ተወዳጅ መሆኑ ቀርቶ እንደ ጎለጎታ እና ቀራንዮ ነው የሚታዬው። ልብሱ የወታደሩ ማለቴ ነው ማስፈራሪያ እና የጭካኔ ምልክት ሆኗል። ስጋት እንዲቆም ማድረግ ሰው በራሱ ውስጥ እንዲኖር ፈቃድ ያገኛል። ይህ ደግሞ ሥነ - ልቦናው የተሟላ ትውልድን ይቀርጻል። ኢትዮጵያዊው ሰው የዓድዋ ድል የሰጠውን ነፃነት ተቀምቷል። ነፃነቱ ሳይሸራረፍ በክብር ሊመለስለት ይገባል።  
  • ·         ንበትም ሐሤታዊነትን ሲያበለጽግ።

ተሰናባቹ ጠ/ ሚር አቶ ሐይለማርያም ደስአለኝ እንዲህ ከውስጣቸው ተደስተው ሳይ የመጀመሪያዬ ነው። ሁለመናቸው ይስቃል። ፊታቸው በርቷል። ደስ ብሏቸዋል። ስጋት አይታይባቸውም። መረጋጋት አለቸው። የውስጥ ሐሴት አላቸው። ቀሪ ዘመናቸውም የደስታ ይሆናል ብዬ አምናለሁኝ። የተካቸው መንፈስ የሚያስቆጭ ስላልሆነ። ቀረብኝ ያሉት፤ የሚሉት አንዳች ነገር እንደሌለ ዓይናቸው ብቻ ልዩ መልዕክት ለእኔ ልኮልኛል። ትርጉሙ ፈቃዳቸውን ዕውቅና የሰጡት ከልባቸው ስለመሆኑ አመላክቶልኛል። ማለፊያ ነው። ብሩክ ምሳሌያዊነት።
„PM Dr Abiy Ahmed farewell to the former primister Hailemariam Desalegn አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በክብር ተሸኙ
የጀግና ሳሙኤል አወቀ ህልፈት ተዘንግቶ ወይንም ተሰርዞ ሥልጣን ላይ ያልወጣው ጮርቃው ሰማያዊ ፓርቲ እንኳን ሥልጣን ቀረ ነው ሁለተኛ ፓርቲ ያስመሰረተው። በሰማያዊ ፓርቲ ምክንያት ድቅቅ ያለው መዋለ መንፈስ ከግምት በላይ ነው። እርግጥ ነው ይሆናል ብለው የደከሙ ወገኖች ነበሩ። እኔ እንኳን ሲጀመርም ብዙም አድማቂ አልነበርኩኝም። እኔ የክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ብርቱ መንፈስ ነበር ይስበኝም፤ ይማርከኝም፤ ያጓጓኝም የነበረው። አንስት በመሆኗ ብቻ ሳይሆን የሰላም መልዕክተኛ ናት ብዬ በጽኑ አምን ስለነበር። ወጣትነቷም ሌላው የአቅም መቅኖ ነበር። ከዚህ በተጫማሪ የህግ የበላይነት ኢትዮጵያዊ ውስጥ ለማምጣት ምዕራፍ ከፋች ፍላጎት አይባትም ስለነበር ክስ እስከሚሰርትብኝ ድረስ ተግቸላት ነበር። ዛሬም ጸጋዬ ራዲዮ ላይ ከእስር ተፈታ እንኳን የፍርዱን ጭብጥ የያዘው ሥሟን ላነሳው ፈቃደኛ አይደለሁኝም። አለ። ወደፊትም እስከ ህልፈቴ ድረስ ይኖራል ሥሟ በጸጋዬ ራዲዮ። ሥሟ ይኑርልኝ። በሥነ ግጥም መጸሐፍቶቼ ላይም የቋጠርኩላት ሥንኞቹ አሉ በክብር። አንድ ቀን መጋዝን ከማሞቅ ወጥተው ከእስር መጸሐፍቶቼ ሲለቀቁ ቅን መንፈሱ ከህዝብ ጋር ይገናኛል ብዬ አስባለሁኝ። መቼም ተስፋን ማሰብ አይከፈልበት … ደጅ አያስጠናም እና …
  • ·         „ቄሮ“ የእኛም ከእኛም ነው!

ሌላው ላተኩርበት የምሻው ቁምነገር ብዙ የኦሮሞ አክቲቢስቶች የሰሞናቱ ምዕራፋዊ ዕለት „የቄሮ“ ውጤት ብቻ ነው እያሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁኝ። በዚህ ስሌት አንድ የነፃነት ድምጽ ብቻ ያስገኘው ውጤት ተደርጎ ተወስዷል። ዘመናት የፈጀ የተጋድሎ ውጤት ነው ይህን ሙሉዕ ሰብዕን ያመጣው። ድክመቶች እኮ በራሳቸው ተቋም ናቸው። ሃያስያን የሚሰነዝሩት ትችት ሰብዕናን አሳምሮ ይጠርባል። የባከነው ትውልድ መከራም በራሱ ውስጥን ፈትሾ ወደ ተፈጥሯዊነትም ይመልሳል ልቦና ላለው። ሁሉም ሥጋውን አጥንቱን ገብሯል።
ለዚህም እክሌ ተከሌ ሳይባል ሁላችንም መስዋዕትነት ከፍለንበታል። ሁላችንም ህይወትም፤ እንግልትም፤ ኑሮንም፤ ወጣትነታችን ከፍለንበታል። ቤተሰብም ተበትኗል። መስዋዕትነታችን አንዱ በሌላው ላይ መከራውን ተጋርቷል። የዛሬው ኦህዴድ እኮ ነፍሱ እዚህ የደረሰቸው የጎንደር እና የወሎ ገበሬወች በከፈሉት የደም ዋጋ ነው። ለዛውም ምንም ላላገኙበት የነጻነት ተጋድሎ። አሁንም አፈር እንደለበሱ ብቻ ሳይሆን በኢሊኮፍተር የተደገፈ ጭፍጨፋን እያስተናገዱ ነው። እስከ ቀያቸው ድረስ ተሂዶ ከእርሻ ስራ እንዲተጓጎሉ እዬተደረገ ነው። ሌላው ይቅር ተብሎ …
በሌላ በኩል ደግሞ ኢሠፓ በመሰረተው ህዝባዊ መሰረት ላይ ነው አቶ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሥልጣን እርካብ ባለቤት የሆነው። ብዙ የመንፈስ ሐብታት እና መዋለ ዕድሜ ተከፍሎበታል። ሌሎችም ያልተማቻቸው ወገኖች በዬጊዜው ዛሬም የሚችሉትን ተዋፆ አበርክተዋል። እንደ ዘመኑ የተነሱ ንቅናቄዎች ካለ እርሾ ከሰማይ ዱብ ያሉ አይደሉም። የፖለቲካ ፍልስፍና ድህንት ከሌለ በስተቀር።
በሌላ በኩል „ቄሮም“ የእኛ አካል ነው። „ቄሮም“ የእኛም የልብ ነው። „የአማራ ተጋድሎም“ ገናና ተግባርም አለ። ይሁን ቢባል ካለ ገዱ መንፈስ ኦህዴድ ብቻውን ቢገባ በድምጽ ያሸንፍ ነበርን? ወደፊትም አትሰቡት። አይሆንም። በሌላ በኩል ዘሩን የገበረ ሰፊ ማህበረሰብ አለ አማራ የሚባል እንደ አኟኩ። የመሃንነት ሂደት በዬትኛውም ማህበረሰብ አልተሞከረም ከአማራ በስተቀር። አሁን ደግሞ ኦሮሞ በቀናት መካከል ዘሩ መጥፋት ብቻ ሳይሆን ከቀዬውም እዬተነቀለ ነው ልክ እንደ አማራው እና እንደ ጋንቤላው በዘመቻ እዬተሠራበት ነው። ሬቻ ላይ አኮ 600 ወገኖቻችን እንደወጡ አቧራ ለብሰው አልፈዋል። ከሞቱ አማሟታቸው እጅግ አሰቃቂ ነበር። በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊ ሱማሌም የጥቃቱ ተጋሪ ነው። የሁሉንም ቁስል ከውስጥ እንቀበል ዘንድ ነው ይህ ሁሉ ማዕት የፈሰሰብን። መማር አለብን። ገንጥለን ዘንጥለን ማዬቱ አልበጀንም ወደፊትም አይረዳንም። ልብ ይስጠን።
  • ·         አብሥራ። 

ከሁሉ በላይ ይህ ቀን ሰው ሰራሽ አልነበረም - ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ። የፈጣሪ ሥራ ነው። የፈጣሪ ጥበብ ነው። ፈጣሪ እርስቴ ባለባት ሐገር 43 ዓመት ሙሉ ክብር እና ልዕልና በበዓለ ሲመት በህግ ተከልክሎ ኗሯል። ዛሬ የሰማይ እና የምድር ንጉሥ ራሱ የራሱን ንግሥና ልዕልና ክብር በክብር ሐገሩ ያሰከበረበት የሰማይ ታምር ታይቷል። ለዚህ ነው ሂደቱን ከሰውኛ እና ከገሃዱ ዓለም ወጣ አድርገን እንመልከተው እያልኩኝ ስኮልም የከረምኩት። እያንዳንዱ የዛሬ ዕለት „የዕለተ ሰኞ“ መጸሐፍ ጽላት ያሰቀርጻል - ለእለቱ። ዛሬ እኮ የህማማት መባቻ ላይ ነን ለተዋህዶ ልጆች። ኢትዮጵያን የፈጠራት፤ ያኖራት፤ የሚያኖራትም የእምነቷ ጽናቷ ብቻ እና ብቻ ነው። ኢትዮጵያ አምላክ ፈጣሪ አለኝ ብላ ማመኗ ነው መንግሥት በሌለበት ሐገር የሚኖር ህዝብ ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ባለበት ሐገር እንኳን የማይታይ ረቂቅ የሆነ የመኖር ምስባክ በጨዋነት የሚታዬው።
እናት ሐገር ተገላ፤ ተጥልታ እና ታስራ፤ ሸማዋ ታሥሮ እና ተጠልቶ፤ እሷን የፈጣራት፤ የባረካት እና የቀደሳት ልዑል እግዚአብሄር ክብሩ ተገስሶ ቀልሃ ነግሶ ኗሯል። ስጋት የተፈሪነት ማዕረግ ነበረው። ፈጣሪ ለዚህ ነበር ሰንበት ላይ ለዛ ለሃይማኖቱ ቀናይ ለሆነው የትግራይ ህዝብ የመሬት መራድን ምልክት የሰጠው። ሊመሰገን ሊከበር የሚገባው የፈጣሪ የአማኑኤል የአባታችን ታምራቱ ነው። ሰው ምን አለው? „ሲይዙት ጭብጥ፤ ሲለቁት ሜዳ ሙሉ“ … ፈጣሪ ቀኑን ባያበራው ቀኑ ጨለማ እና የዋይታ፤ የስጋት፤ የሰቀቀን፤ የጭንቅ ይሆናል። ስለዚህ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን ማለት ቢቀድም መልካም ነው። „ቄሮ“ ብቻ ለምትሉ ወገኖቼ እስኪ ይሁንላችሁ እና „ለቄሮም“ ፈጣሪ ነው አቅም የሰጠው፤ ሃይሉ እግዚአብሄር ነው ብላችሁ ማመኑን ዋጋ ስጡት
ስለነገም የጠቅላይ ሚኒስተር ዶር አብይ ዘመን የሽግግር ጊዜው ሲጠናቀቅ ሥልጣኑ በዛው ያበቃል የሚል ቀን ተቆርጦ የተሰጠ  ቃለ - ምልልስ አዳምጫለሁኝ። ይህም የፈጣሪ ሥራ ነው። የእኔ ወይንም የእርስዎ ወይንም የሁላችን አይደለም። የልዑል እግዚአብሄር የባለቤቱ ነው። ቅብዕ ሰውኛ አይደለም። የእዮር ምርቃት ነው። በመጀመሪያ እኛ የራሳችን የቤት ሥራ እንስራ። ስለ አደረክልን መልካም ነገር ሁሉ እናመሰግንሃለን እንበለው - ቢያንስ። እኛ የተፈጠርነው እኮ ለምስጋና ብቻ ነው። ሌላማ የሰማይና የምድር ንጉሥ፤ የሰማይ እና የምድር ልዑል፤ የሰማይ እና የምድርል ጌታ ሥልጣነ - ክህሎቶ አልፋ እና ኦሜጋ ነው። ሁሉ ይቻለዋል። ሁሉም አለው። እንደ ሰው ቢያንስ ስሜትን ከፈጠረው ከራሱ ከልዑል እግዚአብሄር ጋር ድንቅን ለማያያዝ ዝቅም ትንሽ ማለት የሚገባ ይመስለኛል - በትህትና። መደገፍም መቃወምም መብት ቢሆንም የፈጣሪ ስራውም መዘንጋት አይገባም።

„ተለጠጠም“ ሌላ ያዳመጥኩት ነገር ነው። አሜሪካኖች እኮ ለወራት ነው የሚደክሙበት። የሐገርና የህዝብ ጉዳይ ስለሆነ። ፈጣሪ የሚሠራው ተግባር ይጠበቅ ስለነበረ ከሁሉ በተለዬ ጉዳዩ ትኩረትን ስቧል። ያልተወለዱን፤ ጭንቃችን ሲጋሩ የኖሩት ሁሉ ደፍረው አላውጡትም እንጂ ከእኛ ጋር ጭንቅ ውስጥ ነበሩ። ስለ ሰው ልጅ የሚያጋባቸው የዓለም ዜጎች ሁሉ በመከራችን አብረው እንደኖሩት ሁሉ ይህን የምጥ ቀንም አብረውን አምጠዋል። እንዲህ በቀላል ሂሳብ ለጨዋታ ማሟያ የነበረ ወቅት አልነበረም። ዕንቅልፍ አልነበረም። በሰዓቱ መመገብ አልነበረም። ምክንያቱም ግብረ ምላሹ በታሰበው መልክ ባይሆን፤ እልቂቱ ሲታሰብ የከፋ ነበር። በዛ ላይ በአፍሪካ ቀንድ ወሰን ላይ ስለመገኘታችን ሌላም አህጉራዊ ጉዳይም አለበት። እርግጥ ነው ደስታ ቀላል ነው። ምንም ላይመስል ይችላል። ይህ ባይሆን ግን አንድ የተበሳጨ ሰው ብዙ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል። የታመቀ ቋያ ነበር። የሆነ ሆኖ ሃይል የፈጣሪ ነው እና በማይመረመር ክህሎቶ አድኖናል። ተመስገን!
  • ·         የመቀሌው ዓውራ ዘመንን ሊጋራ።

ጅማሮ ነው ግን የብራ ምልክት ነው - ለእኔ። ሌላ ቸር ወሬው የመቀሌው ዓውራ ዜና ነው። የትግራይ ሊሂቃን ያልደፈሩትን የመቀሌ ነዋሪዎች ቅን ዕይታቸው እና መልካም ምኞታቸውን ስርክራኪ በሌለበት ሁኔታ በንጽህና ገልጸዋል። የወገን ተቆርቋሪነታቸውንም ሳዳምጥ እጅግ በተመሰጠ ሁኔታ ነው። በዘንድሮው የግሼ መንፈሳዊ ጉዞ አንድ መንፈሳዊ ወጣት ልቤን የነካ ቃለ - ምልልስ አድርጎ ነበር። „ግሼ ማርያም“ ከሌሎች የንግሥ ባዕላት ትበልጥብኛለች ነበር ያለው። 
„Ethiopia: የመቐለ ነዋሪዎች ስለ / አብይ አህመድ መመረጥ የሰጡት አስተያየት“
የመቀሌ ነዋሪዎቹ ያላቸውን በጎ ነገር ሳዳምጥ ፈጣሪ ሆይ! ይህን የሰጠህን አምላክ ተመስገን ብያለሁኝ። ያሳዘነኝ ግን ይህን ተስፋ የያዘ ተወካይ አንድስ ሊሂቅ እንኳን ለመልክት ከ108 ቅዱሳን ጋር ሳይደመር መቅረቱ ነበር። ታሪኩ አብሮ ተቀምሮ ቢሆን መልካም ነበር። ስለዚህም የወያኔ ሃርነት ትግራይ፤ ሆነ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችስ „ትግራይን“ ይወክላሉን የሚል ሌላ ጉልበታም አምክንዮ ያፋጣል - ዛሬ። ፍጹም ንጹህ የሆነ ቅንነትን የተላበሰ መንፈስ ያለው ሃብት ነው እኔ ያዳመጥኩት - ከኗሪዎቹ። „የተከደነ ሲሳይ“ ልበለው። ኮርቸባችሁአለሁኝ። እኛ ብቻ መጨነቅ የለብንም። ራሳቸውም እንዲህ መትጋት አላባቸው ወደ መልካም ነገር ለመምጣት።   
  • ·         ሆሳዕና መቅድመ ሰኞን ሲዘክረው። 

አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ እስከ ቤተሰባቸው ሐሤታቸው ወስጣዊ ሆኖ በማዬቴ እናፍቀው የነበረውን የሐገሬ ፖለቲካ ተስፋ እጥፍ አሳድጎልኛል። ለነባሩ ጠ/ ሚር ለአቶ ሐይለማርያም ደስአለኝ እስከ መላ ቤተሰባቸው መጪው ጊዜ የደስታ እና የብሥራት አንዲሆንላቸው ከልብና በቅንነት እመኛለሁ። የቀደሙት ቀዳማይ እምቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ያሳዩት ትሁት እና ፍቅራዊ ሥነ ምግባርም በውነቱ አስደስቶኛል። ተተኪው ጠ/ ሚር ዶር. አብይ አህመድም በሙሉ ልብ የሚገልጹት ፍቅራዊነት ለፍሬ ያበቃቸው ዘንድ እንደ ውዳሴ ማርያሜ ሁልጊዜም ደሃዋ እህታቸው ድንግልን መለመኗን አታቋርጥም። ያለኝ አቅሜ ይሄው ብቻ ነው።  „የእናቴ ምትኬ፤ የእናቴን አደራ የተረከበች ያሏቸው“ ባለቤታቸው ቀዳማይ እምቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸውም „ሰብዕዊነት“ ላይ ይተጉ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳቸው። የአደራ ዕዳ ነው ይህ ብሄራዊ ሃላፊነት። 43 ዓመት ሙሉ የኢትዮጵያ እናቶች ሥነ - ልቦና በእጅጉ ተጎድቷል። የስተዛሬው የባለቤታቸው ጥንካሬ መሠረቱ እሳቸው ናቸው እና ወደፊትም ኢትዮጵያ እንድታርፍ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጡ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳቸው። አሜን! ቤተሰቦቻቸውም „በሰባዊነት፤ በተፈጥሯዊነት“ ላይ አቅም ያክሉ፤ ጉልበት ይሆኑ ዘንድ በትህትና ላሳስባቸው እሻለሁኝ። ኢትዮጵያዊዋ መሬት ትረፍ፤ ኢትዮጵያዊ ንፋስም ከስጋት ድኖ ረፍት ይሰጠው፤ ኢትዮጵያ ያለው ነፍሳት ሁሉ እረፈት ሰላም ይሰጣቸው።
  • ·         ራን ቤተሰቡ ላደረገ ቅንነት። 

የፈተና ዘመን ነው ግን ከ8 ሰዓት በላይ መሥራትን ባህላቸውም መርሃቸውም ላደረጉት አዲሱ ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ በርካታው ነገር የሚገድ አይሆንም ብዬ አምናለሁኝ። ጭንቁ ሥራን ሐገሩ ካደረገ ሰው ጋር ሲሰሩ እስኪለምዱት ድረስ እስፖርት እንደሚሳራበት የመጀመሪያ ሰሞናት ጡንቻ ሊጓጉል ይችላል። „ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለውጥን የሚያመጣ ተራማጅ እድገት“ ህልማቸው ስለሆነ፤ „አብረን እንሩጥ“ ነውና ሞቷቸው። ቅኖች አሁንም ከሳቸው ጋር ይተጋሉ ብዬ አስባለሁኝ። ለነሱም ጥሩ አጋጣሚ ነው። በተጨማሪም „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውም“ የአቅማቸው ዓይነታ ይሆናል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁኝ። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ቅዱስ መንፈስ ነው ለእኔ። በድፍረት እናት ሐገሩን „ኢትዮጵያ ክብሬ“ ያለ መሪ ክብሩ ሙላት ነው። ብልጹግ!
አቀባበሉ፤ ሲመተ - በዓሉ፤ የመኖር ርክክቡ ማለት የጠ/ ሚር ሐይለማርያም ደስአለኝ አሸኛኘት ሁሉም ነገር የቀደመ እና ኢትዮጵያዊነትን ከነሙሉ ተፈጥሮው ያከበረ፤ ያነገሠ ልዩ ቀን ነበር - ለእኔ። ሐሴቴን አግኝቸበታለሁኝ።
አንድ ነገር ተዚህ ላይ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ቀደምት መሪዎችም በሥርዓቱ ላይ የነበራቸው አቀራረብ መልካም ነበር። ውስጣቸውን ለማዬት እዬደጋገምኩኝ ተምልክቸዋለሁኝ። ትውልዱን በተለይ ለትግራይ ህጻናት ያለሰቀቀን መኖር ከራሳቸው የሥልጣን ውክል እና በላይ አጀንዳቸው ይህ ሊሆን ይገባል ባይም ነኝ። ራሳቸውን ማሸነፍ አለባቸው። በውስጣቸው የተቋጠረው ጥላቻ በቀልሃ ሳይሆን በመሆን መርታት አለባቸው። የትውልዱ ብክነት አዙሪት አሁን መቆም አለበት። የባከነ ትውልድ ነው ህይወታችን ሲመራው የኖረው። ፍቅር ሲሆኑት ነው የሚገኘው። ሲገኝም ሐሤት ነው። ሲገኝም የውስጥ ሰላም ነው። ሶሻሊዝም የመርዝ ብልቂያጥ ነው። በዛ ላይ ለኢትዮጵያ ካለልካ የተሰፋ ጥብቆ ነው። አይመጥናትም።

„ገዳ“ ራሱ ስንት ወርቅ ነገር አለው። „በላሃ ልበልሃ፤ ተጠዬቅ፤ አውጫጭኝ“ ስንት ክህሎት አለው። ወደ ራሳችን እንመለስ። አዳኛችን እሱ ብቻ ነው። ከሶሻሊዝም ማኖቆ ይልቅ የአባት አደሩ ይተብሃል ይጠቅመናል። ምህረት አለበት፤ ይቅርታ አለበት፤ ፍትህ አለበት፤ አደረጃጀት አለበት፤ መምራት አለበት፤ ደጀንንነት አለበት። መከባባር አለበት። አብሮ መኖር አለበት። ፍቅር፤ ትህትና፤ ፈርሃ እግዚአብሄር፤ ባህል አለበት፤ መቻቻል ሁሉም አለበት፤ ሃይማኖት አለበት፤ ይሉኝታ አለበት። አንቺ / አንት ትብስ /ትብሺ አለበት። መተዛዝን አለበት። ከሁሉ በላይ በራስ ላይ ተፈቀዶ ስለሚጫን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ወታደር አያስፈልገውም። ተፈጥሯዊ ነው፤ እኛንም በፍጹም ሁኔታ ይመስለናል፤ አምሳያችን ነው። ቁርጥ ደማችን ነው የሚመስለው።  
  • ·         ይከወን።

ጠቅላላ አቀባበሉም ሆነ አሸኛኘቱ ደረጃውን የጠበቀ፤ ሥልጡን፤ ልቅም ያለ ልክ እንደ አሜሪካን ሐገር ባዬነው መልክ ነበር የተከወነው። ራስን ማስከበር የሚቻለው ራስን እክብሮ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው። ኢትዮጵያን ያከበርን ዕለት ሌላውም ያከብራታል። ለዚህ ነው ቀደምቶች „ባለ እዳ ያቀለለውን አሙሌ ባለቤት አይቀበለውም„ የሚሉት። 
ቤቱ ልዑል እግዚአብሄር አምላክ ሆይ! የልቤን መሻት አይተህ „አድርገህልኛልና አመስግንሃለሁ!“ (መዝሙር ፶፩  ቁጥር ፱)
ሐዘን ለባጀበት ጆሯችን፤ ሰቀቀን ለሰበረው ልባችን ቀጣዮችን ጊዜያት ቸር ቸር ወሬዎች ያሰማን ልዑል እግዚአብሄር። አሜን።
የምናፍቃችሁ የሐገሬ ልጆች ጹሑፌን ስለምትታደሙበት ትእግስታችሁ - የኔታዬ ሆኖኛል። ተመስገኑ በኑሩልኝ! 
 ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!“
(ከአቦ ለማ መግርሳ - የተወሰደ)
„ኢትዮጵውያን ስንኖርም ስንሞትም ኢትዮጵውያን ነን!“
(ከጠ/ሚር ዶር አብይ አህመድ - የተወሰደ)
ፈጣሪ ሆይ! እኛን ስለሰጠህን እናመስግንሃለን።


እግዚአብሄር ይስጠልኝ። መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።