ሰማዕቱ ደብረ ኤልያስ። ግፍ የተፈፀመበት ፃድቁ እና ሐዋርያው ቅዱስ ባዕት።

 

ሰማዕቱ ደብረ ኤልያስ። ግፍ የተፈፀመበት ፃድቁ እና ሐዋርያው ቅዱስ ባዕት።
 No photo description available.
"ዬቤትህቅናት በላኝ።"
እንዴት ነን? አይዞን። ይህ ክፋ ዘመን ያልፋል።
ከሊቀ ትጉኃን ከአቶ ኪሩቤል ዘላዓለም ዬተገኜ ነው።
"ደብረ ኤልያስ"
"የሐዲስ ዓለማየሁ ፣የዮፍታሔ ንጉሤ፣የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሃገርየነመልካሙ በጎሰው፣የነዶ/ር ኢሳይያስ የትውልድ ከተማ።
ዛሬ በቅዱስ ኤልያስ በዓል ዋዜማ ላይ በሥፍራው ተገኘሁ። አካሄዴ በደብረ ኤልያስ የተሠራውን ሆስፒታል ለደገፉ ምስጋና ለማቅረብ በተደረገው ፕሮግራም ለመሳተፍ ነበር። ይህንን በቀጣይ እመለስበታለሁ። ነገ ታሕሳስ 1 ቀን 2015 የሚከበረውን የቅዱስ ኤልያስን በዓለ ልደት ዋዜማ ለማየት ከታደሉት አንዷ በመሆኔ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ሆነን ወደ ገዳሙ ተጓዝን። ከየገጠሩ መንደሮች ከሩቅም ከቅርብም ለጠበል ጣዲቅ የሚሆን ምግብ የተያዘበት መሶብና ገምቦ እየያዙ ወደ ቤተክርስቲያን የሚጓዙትን እያየን በአቧራማው መንገድ ወደዚያው አቀናን። እነሆ ታላቁ ገዳም ከነሙሉ ግርማው በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቆ በምእመናኑ ደምቆ ጉብ ብሏል። ቅዱስ ኤልያስ በእሳት ሠረገላ በእሳት ፈረሶች ተነጥቆ ወደ ሰማየሰማያት ሲወሰድ የሚያሳየው ውብ ሥዕል በአፀደ ቤተክርስቲያኑ መሐል ጉልህ ሥፍራ ይዟል። "
"በመጽሐፍ ቅዱስ የተፃፈው ገድሉ እንደሚያስረዳው "ከደቀ መዝሙሩ ከኤልሳዕ ጋር እየተነጋገሩ ሲሔዱ የእሳት ሠረገላ፣ የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገቡና ለያዩዋቸው፡፡ ኤልያስም በእሳት ሠረገላ ዐረገ፡፡ ኤልሳዕም የኤልያስን ወደ ሰማይ መወሰድ አይቶ ጮኸ፤ ኤልያስም ልብሱን ከሁለት ከፈለው፡፡ መጠምጠሚያውንም ለኤልሳዕ ጣለለት፡፡ የኤልያስ ጸጋና በረከትም በኤልሳዕ ላይ አደረ" ይላል።
"የቅዱስ ኤልያስ በረከት እንዲደርሳቸውም ይመስላል ሰማያዊና ነጭ የቤተክርስቲያን ልብስ የለበሱ ልጃገረዶች የሚመጣውን ሰው እግር እያጠቡ ለመመረቅ፣ በረከትን ከእናቶች፣ከአባቶች ለማግኘት ይሽቀዳደማሉ።ለኔም ይሄ ክብር ደርሶኛል። እግዚአብሔር ይባርካቸው። "
"ወንዶች አገልጋዮች ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ ካህናት ጥምጥማቸውን ከብሰው ፣ካባቸውን ደርበው ፣ ነጠላ ወይ ጋቢያቸውን ለብሰው የሌሊቱ ማህሌት እስኪጀመር ይጠባበቃሉ። ሴቶች መነኮሳትና ወይዛዝርት ከግቢው መግቢያ ወደ ቀኝ አቅጣጫ መሬት ላይ አንጥፈው ቁጭ ብለዋል። ዳዊት ይደገማል። ፀሎት ይፀለያል። "
"ከመንፈሳዊ ድባቡ የተነሳ በአፀደ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ አምላክ በግርማ የወረደ ፣ መላእክት ክንፋቸውን ዘርግተው የረበቡበት፣ ቅዱሳን የተሰበሰቡበት ይመስላል። በቅርብ ርቀት አባይን ተሻግሮ ያለውን የወለጋውን ሻምቡ ሲያስቡት እዚያስ ሕዝበ - ክርስትያኑ አምላኩን በፀሎት እያስጨነቀ ይሆን ? የሚል ስሜት ይሰማል።"
"ከመግቢያው በስተግራ ሲል ፊታቸው ላይ ፈገግታ እየታየ አንዳንዴም የሚያወኩ ወጣቶች ክብ ሰርተው ከመሐል ያለ አንድ ነገር ትኩረታቸውን ስቦ አየሁ። ጠጋ ስል አንድ ተለቅ ያለ ጠፍጣፋ ድንጋይ አለ ። እሱን በተራ እያነሱ ለመሸከም ይሞክራሉ። ይህንን ድንጋይ የተሸከመች ወይም የተሸከመ ለሚቀጥለው ዓመት የልጅ በረከት ያገኛል የሚል እምነት አለ። ለዚህ ነው በልጅ ፀጋ ለመባረክ የሚፈልጉ ወደዚህ የሚመጡት። ፀሎታቸውን ፈጣሪ ይስማቸው።"
"ይህንን ታላቅ ገዳም ለማየት በመታደሌ ከተሰማኝ ደስታ ጋር የሕዝቡ ትሕትና፣ በአምላኩና በፃድቃን ሰማዕታቱ፣በቅዱሳን መላእክቱ ያለው የማይናወጥ እምነትና ፅናት ልቤን ነክቶታል። ይህ ሕዝብ ብዙ ፈተናን ታግሶ የሚያልፈው ከዐለት በጠነከረ እምነቱና ፀሎቱ ነው። አሁንም ከዓባይ ወዲያ ማዶ የሚመጣለትን ክፉ ዜና፣ በወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን አሰቃቂ ግፍና መከራ ፈጣሪው እንዲያስቆምለት ይማፀናል። "
" በዚህ ሁሉ መሐል ከዚህ ቅዱስ ምድር የበቀሉት ሐዲስ ዓለማየሁ የፈጠሯቸውን የፍቅር እስከ መቃብርን ገፀ ባሕርያት በምናቤ አየኋቸው ልበል? ያውና በዛብህ ነጠላውን አደግድጎ ከጓደኞቹ ዲያቆናት መሐል። እኛስ የቤት ሥር ቀጭን ፈትል ቀሚሳቸውን ለብሰው ከትንሿ ዛፍ ሥር ቆመው የፀሎት መጽሐፋቸውን የሚያነቡት ወይዘሮ? ውድነሽ በጣሙ? ወይዘሮ የሰራሽ ግሩም? እ እ እሳቸውም በዘመቻ ጊዜ ብቻ ነው የሚመጡት...ከዲማ ደብረ ኤልያስ ሊመጡ? ፊታውራሪስ? የትኛው? አበጀ በለው የጎበዙ አለቃ?"
በረከቱ ይድረሰን። አሜን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።