የሰማይ ቤት ሸንጎ አፈ ጉባኤያዊት።
አሽካካች።
ከሥርጉተ ሥላሴ 14.06.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዝዬ)
„አቤቱ በመከራቸው ጊዜ ፈለግሁ፣ በገሰጽሠጽሃቸው ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ
አፈሰሱ።
(ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፳፮ ቁጥር ፲፮“)
ጨረሯ ብቻ ደረሰኝ። ምን ደረሰኝ ብቻ አዳረሰኝ። እሷ ግን አትታይም። ስብሰባ ትሆንን? ወይንስ ሰማያዊ አልጋዋ ላይ ተኝታ … ወይንስ ጫጉላ ጊዜ ላይ ትሆን ወይንስ ከባዘቶማዋ ፍራሽ ተኮፍሳ? ክብር ሲወድላት -- ደግሞም ሲያምርባትም የለችም። ብቻ የለችም። ግን አለች ትንፋሿ አገር ያዳርሳል። መንፈሷ ይሆን የሌለው?
ይሆናል። ምን ይሆናል ነው እንጂ። ግን ለምን? … እእ … ለምን …. እ … ለምን …?
ጠብቅኳት አልመጣችም። ለእኔ ለእራሱ የላከችው ለብ ያለ ጉድ ነው። ልም ነገር። ስትገርም። ለእናንተስ ይሄው የእኔ ዕጣ ፈንታ ደረሳችሁ ይሆን? … አላውቅም። ቀና ብዬ ፈራ ተባ እያልኩ ተመለከትኳት …
„ነገ ሌላ ቀን ነው“ አሃ! ብላ ጽፋለች።
ቀና ብዬ ስመለከት ደግ „ይህም ያልፋል“ ብላ ጽፋለች? ጎሽ! አልኩና ተረጋጋሁ።
ግን ለምን? አላውቅም። ለመሆኑ ያነብበኩትን እርግጠኛ ነውን? „ ነገ ሌላ ቀን ነው „ ብላ ስለመጻፏ እንደ ገና አዎን እንደ ገና አሻቅቤና ሻቅዬ
ሳዬው ተለውጦ …
„የማይቻለውንም መከራ ቢሆን በትእግስት ቻይው“ ብላ ጽፋልኛለች። ወይ ጉዴ ግን … ለምን? አላውቅም።ዝቅ ብዬ እንደ ገና … አዎና እንደ ገና ተመለከትኩኝ።
„ከመከራው በስተጀርባ ክብር አለ“ በማለት ደግማ ጽፋለች። ምን ማለት ነው ይሄ ደግሞ?
እሷን ብሎ ትንቢተኛ፤ እሷን ብሎ ስለነገ ራዕይ ተንታኝ - በታኝ … ከደንቀራው ጋር ስትደልቅ ከርማ ባጅታ፤ ብዬ ላኮራፋት ዳዴ ስልላችሁ በአንድ አቅጣጫ የላከችው ጨረር ተባዛ …ሳቀይንስ ተደመረ …
ተዳምሮ ተባዛና ተነሰራፋ … ሞቅ አንደ ማለት ዳዳኝ። በጨረሮቿ ልክ የተደረደሩ ትዕይንታዊ ስንኞች ኪነን አንግበው ይታዬኛል። ጠጋ ብዬ ልዳስሳቸው ስል በቅጽበት - ቅጽበት ሆነው እርፍ። … ግን እንደ ገና ተፃፈ። መነጠሬን ከኮሮጆዬ አወጣሁና በጥደፊያ ተያያዝኩት …
አንዱ ምን ይል መሰላችሁ … ወይ ጉድድድድድ …! „የጨለማ ፀሐይ“ ይላል። እ! አልኩኝ … ምን ማለት ይሆን ይሄ? ---------------ብዬ ሳመናታ እራሱን ቀዬር አድርጎ ፈታልኝ ፈገግ ብሎ
„ህልም“ ሲል … እህህ! ብዬ ልቤን አዳመጥኩት። አሁን ወደ ቀጣዩ መልዕክት መሄድ እንደለብኝ ህሊናዬ ማስታወሻ ቢጤ ጫር … ጫር አድርጎ ላከልኝ። ቀጣዩ …
„የሰማይ ቤት ሸንጎ“ የሚል መጣልኝ። ሃሃ! አልኩኝ።
ይህ ደግሞ ምን ይሆን? ብዬ ሳመናታ ሌላ አንድ - በአንድ ዘርዘር እያለ በጠብታ ከች
አለ … ሳገጣጥመው … „የሞት አደባባይ“ ብሎ ቁጭ። ውይ? ይሄም ደግሞ አለ? በጣም ፈራሁ። ጨነቀኝ። ተዘንፈዘፍኩ - ስላችሁ። አይጣል?
መነጠሬን ለማውለቅ ስታገል … እሱ ደግሞ ለካስ ከዓይኔ ላይ ስበት ተፈጥሮለት አሻም እንዳለ ተሰክቶ ቅርት። ሲያናድድ። ተናደዱ እባካችሁ ከእኔው ጋር። ማስቲካ! ….ቀጥይ ማለቱ እንደሆነም ገባኝ። በምልክት ቋንቋ … በቃ አሸከረከረኝ እንደ ዛቢያ ስላችሁ። ገና እኮ ነኝ ወደ ሁለተኛው ጨረር አልሄድኩም። መዳህ ታውቃላችሁ ዝም ብሎ ታቱ …ዥግራ … ከወፌ ቆመች ያልተደረሰ … ብልጭ ድርግም በሐመራዊነት … አንተ ደግሞ ምን ልትል ይሆን ብዬ ዳጥም - ላጥም ይዞ ሊፈጠርቀኝ ግብግብ ስገጥምላችሁ …. አምላካችሁ አለ ሰውነቴ የማለውቀው ሆነብኝ። ዖዬ! እኔ ወይንስ ሌላ .. ህም …
„ተስፋ ይለመልማል“ አይልም መሰላችሁ። ዎህ! ተመስገን። ወይኔ እኔና ተስፋ
ከፊደል „ተ“ ከቃል „ተስፋ“ ስፈጠር ነው በፍቅር ድብን ብዬ እምወዳቸው። ፍንክንክ ፍልቅልልቅ ቧ ብራ ፏ አልኩኝ። ዋው! ደስ
ሲል አልኩኝ። ይሄስ ምን ትርጉም ያስፈልገዋል ብዬላችሁ ወደ ሶስተኛው ጨረር ላዘግም ስሰናዳ ውልብልቢቴን ጨምድዶ ያዝ አደረገና … „ተስፋ ይጎድላል“
ይቺ ናት እና ሥርጉተ … አለኛ! እቴ የምን ጭንጫ ነገር ነው የኳረተ …
መጀመር እንጂ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት … የራስህ ጉዳይ ነው። ፈንግጠው! ብዬ ቀጨር መጨሬን ሰባስቤ ስሰናዳ … ያለዬለት የነበረው ቀለም እዬነጠረ እዬነጠረ መውጣት ጀመረ … አረንጓዴ ~ ቢጫ ~ ቀይ! ዋው፡~! እንኳንም ለሀገሬ አፈር አበቃህኝ ብዬ ጠላታችሁ ድፍት ይበልና ፍግም ብዬ፤ ክንብል ብዬላችሁ መሬቱን ልስም ስል
„ አትቸኩይ! የሀገርሽ ጉድ ገና ነው።“ የሚል መልእክት በስተጀርባዬ …. ደለቀ።
ቁጣም ግልምጫም ድንፋታም ተዘልለው - ተዝልዝለው ምጥት፤ ህም!
… አንኳኩብኝ …. እህ! አልኩኝና ደግሞ ምን ቀረ? ከማርያም መቀነት ወዲያ ስል አራተኛው ጨረር ፊት ለፊቴ በራልኝ … „ሰንደቁ በእግር ብረት ታስሯል“ የሚል መልዕክት ፃፈ …
ደሜ ሲንተከተክ ተሰማኝና … እኮ እንዴት?! ስል በድፍረት ያነን የተላከልኝን አራተኛ ጨረር አፋጠጥኩት … አሻቅቤ እያዬሁ በድፈርትና - በወመኔ ቁጣ፤ ፈንግጪው እንዳይለኝ ግን ስሜቴ ተክ --- ተክ ---- ትር ----- ትር ---- ብን ---- ብን --- ትን - ትን እያለ ነጋሪቱን ይጎስማል …
„እንቅልፋም!“ አሃ! ህም!
ተብሎ ተጻፍልኝ። ይህችን ትወዳለች ሥርጉትሻ፤ ኧረ እኔ ሆንኩኝ እንጉልቻም? ብዬ ያንኑ አራተኛ ጨረር ----- ላጥድፈው ፈራ ተባ ስል …. እኔ ትልቁ ችግሬ እንቅልፍ ማጣት ነው። መቼ ተኝቼ የማውቀውን ነው። ስጭር እኮ አኮ ነው
ጉልት ብዬ እማድረው። … ይህቺ ብዕር የሚሏት ቀለማም አድብታ ብክፉ ቀን አጠመዳኝ ሳለች ነጋ ጠባ ከእርሷ ጋር ነኝ … እያልኩ ስብተከተክ አምሰተኛው ጨረር ከች አለላችሁ። ጉድ!
„ከዚህስ ወዲያ! … እ¡¡¡“ የሚል በሥነ - ስላቅ፣ በትዝበት የቆዛዘመ ስንኝ ብቅ ጥልቅ እያለ አቅሌን መፈናፈኛ - ነሳት። ወይ አይጸድቅ ወይ አይነቀል። ወቼ ጉድ አልኩኝ። ማለት ነበረብኝ። ኧረ ባበቃልኝና ግልግል በሆነ ስል ተተካ ተረኛው፤ „ትራስሽ ምን ግዴ ነው“ ተባለኩኝ። ህም! „እሺ ምን ልሁን?
ምንስ ላድርግ? ይነገረኝ … እያልኩ ወኔዬ ገፍትሮኝ እዬተለማመጥኩኝ ስንተባተብላችሁ ስድስተኛው ጨረር …„አደብ - በሆደ ሰፊነት- ይመስጠር።“ ሲል ውሽክ ብሎ ሽክ አድርጎ ፈታልኝ። ህም!
በተፈጥሮዬ ጮኽ ብሎ መነገር አይሆንልኝ። ግጥሜም - አይደለም። አልኳችሁ ፊታውራሪ በር እንኳን ከልጅነት እስከ እውቀት አንድ ቀን ሰለቀችኝ - ቡጢዋን እልቻልኩትም ብሎ ችሎት ገትሮኝ አያውቅም፤ እንደተመሰጋገን ይሄው አለን። ግን ነገር ግን የአሁን አቤቱታ ቁሮ እንጂ የእኔ ማንነት አይደለም፤ እያልኩ ብቻዬን እያወጋሁ እጄን ከግራ ወደ ቀኝ … ከቀኝ ወደ ግራ ሳወራጭ --- ላችሁ … መንፈሴ መሳሪያውን ሲያቀባብል - ሊተኩስ --- ተሰማኝ … „ዛሬ! ዛሬ! ዛሬ! ቁረጭ - ምረጭ! ለህዝብ ጠቀም ተግባር ሰባራ ሰንጣራን ከባህር ከገደል ጠቅልለሽ ከነዲሪቶው ጣይ … በይ! በይ!“ በማለት ወጥሮ ሰንጎ ለምን አይዘኝም መሰላችሁ።
„እሺ ምን ልሁን ? ፈወስ … ምንድን ላድርግ?“ እያልኩ እጅግ በሚያባብል በቁልምጫ፣ ህሊናን ዘና አድርጎ የጫጉላ ሽርሽር በሠረገላ ፈሰስ - ፈርሰስ በሚያደርግ ድምጽ ትህትናን አጋብቼ ድምፄን ለቀቅ … ሰብሰብ … ቀዳ … ወዛ … ሰበቅ
እያደረኩኝ በክብር አሽሞንሙኜ ቀና አልኩ። አዎን በተጠንቀቅም ጸጥ ረጭ ብዬ ቆምኩኝ። እንደባንዴራው። ከዛ አዎን ከዛማ ሰባተኛውን ጨረር ተላከ። እንዲህም ይላል፤ በጉልህም ኮቢውም ብራናውም ፈቅደውለት ተጥፏል።
ይበል … „የተግባር ስንቅና ትጥቅ ይኑርሽ“ በማለት የጉዳዩን አናት በዕለተ ሰንበት ጸበሉን ትእዛዝ አሳወቀችኝ። ይሁን! እሺ! ብዬ ልሰግድ ጎንበስ ስል … እርገት ውረድ … ሰባቱም በአኃቲ ድምጽ …
„ቁረጪ! ትውልዳዊ ድርሻሽን ለመወጣት“ ብለው ሲናገሩ … በእነሱ ቅኔዊ - ቃናዊ ድምጽ መጉላት ጉልበታምነት መሰለኝ … ከዙፋኗ ብቅ አለችና ብርኃኗን በመቁንን ሰደድ - አደረገችልኝ። „እንዴት ነው ነገሩ ለብም አለደረገኝ። ከአንጀቴም አልደረሰም የብርኃን እናት ክብርት ልዕልተይ --- ሆይ! ስላት …“
„በተስተካከለ ሙላት ለመኖር ሆኖ መገኘት + እዮባዊነት“
በማለት ከልቧ አዎን ክልቧ ☞ ከትከት ብላ አሽካካች …
ብሄራዊ ሰንደቅዓላማችን የሚፈታበት ንፍቅ አለኝ …. አብይ ሆይ እባክህን
በቃህ በለው?
የኔዎቹ ቅኖቹ ክብሮቼ መሸቢያ ጊዜ!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ