#የህይዋን መፈጠር ይሁን #የኖኽ መርከብ እናትነትን የማስቀጠል ሰማያዊ #ሚስጢር ነው ለእኔ ለሥርጉተ©ሥላሴ። እናት #አልቦሹ ነገ በእጅጉ ያስፈራኛል። አናት አልቦው ማግሥትን ሳስበው የውስጥ ሰላሜን ያውከዋል።

 

#የህይዋን መፈጠር ይሁን #የኖኽ መርከብ እናትነትን የማስቀጠል ሰማያዊ #ሚስጢር ነው ለእኔ ለሥርጉተ©ሥላሴ።
እናት #አልቦሹ ነገ በእጅጉ ያስፈራኛል። አናት አልቦው ማግሥትን ሳስበው የውስጥ ሰላሜን ያውከዋል።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#የዕይታዬ ምንጭ የBBC ዘገባ ነው።
 
ጠበቃ አስረስ ዳምጤ የፋኖ መሪ ከመሆኑ በፊት የሚያደርጋቸውን ቃለ ምልልሶች በአትኩሮት አዳምጥ ነበር። የህግ ባለሙያወች ሰብዕናቸው ቁጥብ እና መምህር ስለሆነ ተስፋዬ የዘለቀ እንዲሆን አድርጎታል። ጠበቃ አስረስ ማረ ታስሮም ነበር። ይፈታ ዘንድ በትጋት ከሰሩት አንዷ ነበርኩ። የእስር ቤት ቆይታውም አጭር ነበር።
 
ይህን ዜና በአንድም በሌላም አዳመጥኩት። ውስጤ በእጅጉ አዘነ። ውስጤ ተረባበሼ። ስሜታዊ እንዳልሆን በመስጋት ዕይታዬን አዘገየሁት። 
 
እናት ስለምን #ትገደል?
እናት ስለምን #ትሙት?
እናት ስለምን የባሩድ #ስንቅ ትሁን?
እናት እንደምን #ቀባሪ ትጣ?
እናት እንደምን #ይጨከንባት?
#እናት የሆነ፤ #እናት ያለው ሁሉ ማንንም ሳይወግን፤ ማንንም ሳያገል ብቻውን ሆኖ ከራሱ ጋር ይምከር።
 
 ሴት የተፈጠረችው ለእናትነት ጸጋ ነው። እግዚአብሄር ፈቅዶላት እናት ትሁን፤ መሃን ያ የእዮር የእናትነት ተፈጥሮዋ ምንጊዜም፤ በየትኛውም ሁኔታ ይኖራል። ይህ ጸጋ በባሩድ ሲቀማ እጅግ ያሳዝናል። ትውልዱ ለዛውም በንጉሦች ንጉሥ በአጤ ቴወድሮሥ ሥም የተደራጄ አካል፤ ለሥሙ ክብር ሲል እንኳን እርምጃው ሥሙን በሚያስነቅስ ማንኛውም ተግባር ላይ ቁጥብ፤ የተረጋጋ እና ከስሜት የጸዳ ሊሆን ይገባል።
ሁሉም እናት አለው። ፍጥረት እናት አልቦሽ አይፈጠርም። የነገ እናትነት፤ የማግሥት እማዊነት በዚህ ፈተና ውስጥ አልፎ እንደምን ትውልድን ለአደራ ሊያበቃ እንደሚችል አላውቅም። ተባቶች ሆይ! ትዳር የመሥረት ተፈጥሯዊ መብታችሁን የሚገድብ ሁነትን ብታስቡበት ጥሩ ነው።
ወጣት አንስት ድርጊቱን ፈጸሙት /// አልፈጸሙት ዕውነት ይዳኜው። ግን ሴትነት፤ እናትነትን የትኛውም የታጠቀ የመንግሥት ይሁን ከፋኝ ያለ ኃይል ዕይታውን ከእናትነት እሱ ከተፈጠረበት #የመሐጸን ክብር ጋር ሊያመሳጥረው ይገባል። 
 
እናት ከቁጣ፤ እናት - ከብስጭት፤ እናት - ከንዴት፤ እናት - ከስሜታዊ እርምጃ በላይ ልትሆን ይገባታል። ለምድራዊቷ እናት የሚሰጠው ክብር ከሰማያዊቷ እናት ጋር ለተዋህዶ ልጆች ከእመ አምላክ፤ ከወላዲተ አምላክ ጋራ #በአስተውሎት ሊመሳጠር ይገባታል። በዚህ እርምጃ መስቀልን በማተቡ መለያ ላደረገ አንድ የፋኖ አካል እና አባል ሊከብደው አይገባም። 
 
ሴቶች ተጠርጥረው ይሁን፤ በተቀናቃኝ ሃሳብ ውስጥ ተጠልፈው ቢገኙ እንደ አንድ የጦር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ሰብ ሊታዩ አይገባም። እናትነት ለሰማይም /// ለምድርም የከበደ የሚስጥሮች ሁሉ ልዕለ #መሰጠት ነውና።
 
አንድ ሰው መኖሩ #የሚከዳው እናቱን በሥጋ ከአጣበት ዕለት ጀምሮ ነው። እናት አልባ መኖር አንገት አልቦሽ አካልነት ነው። ስለ እናት፤ ስለእናታዊነት፤ እራሱን የቻለ የጨመተ የሥነ- ምግባር፤ የሞራል ተከታታይ ትምህርት ያስፈልጋል።
 
ኢትዮጵያም እናት ናት። እና እናት አገር #ልትረሽን ይገባታልን? እናት አገር #ስሜታዊነት ሊደፍራት ይገባልን? ከእናት የተፈጠረ ሁሉ በእናቱ ላይ ምላጭ ሲያነሳ እርግማን ይሆናል። መርገምት ይሆናል። "ልጅ አይውጣላችሁ" እርግማንን ፈቅዶ ለመቀበል ስለምን ይህ ሁሉ ክልትም ፋኖ አስፈለገው?
 
"ጠላት" "ባንዳ" "ባዳ" የተለመዱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባንድ የተሠራባቸው ድምፆች ናቸው። ከነዚህ ድምፆች የሚነሱ ንቅናቄወች ሁሉ የሚቀናቸው ጭካኔ ነው። ጭካኔን - ማጨት፤ ጭካኔን እንደ - ጀብዱ ማዬት፤ ጭካኔን - የተስፋ መዳረሻ አድርጎ ማዬት፤ ጭካኔን - የሠርግ #ጥሎሽ አድርጎ መመልከት ለነገ ለትውልዱ የአደራ ቅብብሎሽ ጠባሳማ ወይንም የበለቀ ባህልን ያስረክባል።
 
ሌላው ቀርቶ ከእርምጃ በኋላ እና በፊት ሴቶች "በአጥፊነት" ተጠርጥረው ሲያዙ እናትን በጥልቀት፤ በጥሞና በተመስጦ ማሰብ በእጅጉ ያስፈልጋል። ልጅን ማሰብ። የትዳር አጋርን ማሰብ። አገርን ማሰብ። የተነሱበትን ዓላማ እና ግብ አጀንዳ ማድረግ ይገባል። ከእናት ጋር በዚህ ልክ ጠብ እዮርን ያስደስታል ብሎ ማሰብ ጸሐይን ጨረቃን እንደመተካት ይሆናል። እዮር ከእኛ በላይ ያዝናል። ከእናት ነው የአገር መሪ፤ የሃይማኖት መሪ፤ ዕውቅ ፈላስፋ እና ሳይንቲስት የሚገኘው። እናት እኮ ሥልጣኔን #አዋላጅም ናት። ይህ ደግሞ ከዕንቁም፤ ከአልማዝም በላይ ነው ለአንድ ትውልድ።
 
ሌላው ታጣቂ ከሰው ስለተፈጠረ ሰብአዊነትን አላይህም፤ አልሰማህም ሊል አይገባም። ሰው ሆኖ የመፈጠሩ አንኳር ፍሬ ነገሩ #ሰብአዊነት ነው። ሰው የሚለው ሥያሜ ሰብአዊነትን ያነበበ፤ የተረጎመ ያመሳጠረ እዮራዊ ጸጋ ነው። የኖህ መርከብ እኮ የሰብአዊነት አዳራሽ ነው። መቅድመ ኖህ ተፈጥሯዊነት እና ሰብአዊነትን ከጥፋት ውሃ ሲድኑ የእናትነት ሚናን #ያስቀጠለ የተደራጄ እዮራዊ ሥጦታ ነው።
 
እንደ እኔ የመጀመሪያውን ድርጅት ፈጣሪ አምላካችን #ህይዋንን ፈጥሮ ቤተሰብን አደራጄ፤ ሁለተኛው ከክፋ ተግባር ብዛት ትውልድ ከቅጣት፤ ከቁጣ ይርቅ ዘንድ ሁለተኛው ድርጅት የኖህ መርከብ ነው። የኖህ መርከብ ታላቁ ተልዕኮው እናትነትን ማስቀጠል ነው። የህይዋን መፈጠርም እናትነትን ለማስቀጠል ነው። 
 
ይህን እዮራዊ፤ አምላካዊ ሚስጢር አክብሮ መራመድ ትውልድን ያበረክታል።
 
1) ከግድያ ውጪ የጥፋት መቅጫ መንገድ የለንም?
2) ማስተማር ወይስ መቅበር የትኛው ይቀል ይሆን?
3) የትኛውንም በአስተሳሰብ የተለየን ወገን፤ አስተምሮ የራስ ማድረግ ወይንስ የባሩድ ስንቅ ማድረግ የትኛው ሞራላዊ ነው?
 
 
እነኝህ ሦስት ወጣቶች መኖራቸው ሲጎሳቆል የትኛውንም እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። "ለራበው ማጭድ አታውሰው" ብሂልም ሊደፋ አይገባም። ዛሬ ያለው የገዘፈ ችግር ከዚህም የባሰውን ውሳኔ ሊያስወስን ይችላል። መኖር እራሱን ችሎ መቆም ተስኖታል። ነፃነት እና ሰላም አፋፍ ላይ ናቸው። እስኪ ግዜ ሰጥታችሁ የግንባር ሥጋ መሆን የፈቀዱ ወገኖች የሚሰጡትን አስተያዬት አዳምጡ። የአማራ ህዝብ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኜው። ያ አይበገሬ፤ ጽኑ፤ ገራገር፤ ለጋስ፤ ዓራት ዓይናማ ህዝብ ያለበት ሁኔታ አፋፍ ላይ ነው። አጽናኝ ይፈልጋል። አይዞህ የሚለው ቅንነትን ይፈልጋል። 
 
ነገ የአማራ እናትነት ከነጠፈ። ነገ በዕውቀት ለመመራትም ይሁን፤ ለመምራት ዕድሉ ከተገፋ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ህልውናው፤ ተስፋው፤ ምኞቱ እንደምን ይቀጥል? ይህም ገደል አፋፍ ላይ ያለ ገጠመኝ ነው። ማዳንን ለማስቻል፤ ማዳን ከተረሸነ #ማዳን ከወዴት ይገኛል። 
 
#የአማራ ቀጣይ ተስፋ የት ይጠጋ? 
 
ግራ ቀኙ ቋያ ነው። በቋያው ግርፊያ የሚተርፍ ትውልድ ቢኖር ሥነ - ልቦናው ከተጎዳ ሙሉዑነት ያንሰዋል። ህመም - ይኖራል። የፍርሃት፤ የስጋት ህመም። በኢትዮጵያ ስንት የሥነ ልቦና ባለሙያወች እንዳሉም አላውቅም። በዘመነ ቅንጅት 10 ብቻ እንደነበሩ መረጃው ነበረኝ። በሌላ በኩል የእኛነታችን አንጡራ መግለጫ ቅዱሱ ቦታ ደብረ ኤልያስም ተሰቃዬ። የስቃዩ ማሳረጊያ ምን ሊሆን እንደሚችል እዮር ያውቀዋል። ያን የእዮር ቁጣ ለማስተናገድ የሰው ልጅ አቅሙ ያን ያህል ነው።
 
ግራ ቀኙ የከፋኝ ዱርቤቴ አባላት ይሁን ሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና አካል ከነገ ጋር ያለው ትስስር ፈተና ላይ ስለመሆኑ አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል። የጎጃም የቀለም ተማሪወች፤ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪወች የላቀ ሰማያዊ ጸጋ እየተስተጓጎለ ነው። የዛሬ ሹልከት የሚገባን የዛሬ 15/20 ዓመት ይሆናል። የአማራ ተስፋ #ኢመርጀንሲ ውስጥ ነው። ለዚህ ነው እኔ ብሄራዊ የምህረት #ዓዋጅ ይደረግ ዘንድ የጠየቅኩት። እስር ቤት ላሉትም፤ ዱርቤቴ ላሉትም፤ ሥልጣን ላሉትም፤ ለአማራ ክልል ነዋሪም። 
 
በውይይቱ ውስጣቸውን ሳየው ግብረ መልሱ ሁሉም፤ ሁሉንም ሊያድን የሚችል ብልህነትን ይጠይቃል። ስክነትን ይጠይቃል። በስፋት ተቀባይነት ያለው ሚዲያ በራሱ በዕት አይደለም ግፋ በለው እያለ ያለው። የ130 ሚሊዮን ህዝብ ጉዳይ የአማራ ህዝብ ማገዶ እንዲሆን መሻት አረመኔነት ነው። ሁሉም ክልል ጫካ አለው። ሁሉም ክልል ወጣት አለው። ግን ይህቺ አትነሳም። ሌላው ይማራል። አማራ ግን ይማገዳል። ትናንትም ዛሬም። 
 
"ጠላት" የሰው ጠላት አለው ብዬ እኔ አላምንም። የሰው ልጅ ጸድቀን የተፈጠርንበትን ሰብዕና የሚያስቀጥል ተቋም ዓለማችን ትሁን አገራችን ስሌላቸው ክፋ ሃሳብ ነገሠ። በክፋ ሃሳብ እና በተፈጥሮ ጸጋችን ሰብአዊነት፤ ተፈጥሯዊነት ያለው ግጭት ነው፤ የወንጀል፤ የጥላቻ፤ የጦርነት፤ የቂም እና የበቀል ሂደት አና እንዲል ያደረገው። 
 
የልጆቹ አገዳደል ጭንቅላታቸው ላይ መሆኑ "መበቀል፤ ቂምን" ያሳያል። አለመቀበራቸውም የሰውነትን ደረጃ ይፈትናል። ይህን ለማዳን ቅድስት ኤልዳና ባዬ፤ የኔዓለም አዳሙ እንደገለጸችው በዶንኪ ቱዩብ በነበራት ቆይታ "ጦርነቱን ለማማቆም ምን እናድርግ? " ብሎ እንደ ትልቅ ሰው ይጠይቃታል ኮመዲያን አቶ እሸቱ መለሰ መልሷ "#ማቆም" አለችው።
 
"ትጸልያለሽ" ብሎ ይጠይቃታል። "አወን" አለች። "ምን ብለሽ" አላት "ጌታ ሆይ! ጸጋ እና ምህረትን በእኛ ላይ አሳድር ነው እንጂ ሌላ ምን እላለሁ" አለችው። ጠቅላላ በዚህ ዙሪያ መልስ ስትሰጥ የሰውነት ቋንቋዋ ተአምር ነው።
 
ከዚህች ቅድስት ህፃን የማስተዋል አቅም ጋር መመጣጠን እንዴት አልተቻለም። ስኬቱ በዘገዬ ቁጥር የተስፋ ሁኔታም እየሳሳ፤ የመደራደሪያ አቅሙም እየላላ ይመጣል። "ተመልሶ ካልመጣ ሰሞኑን ተኩስ የለም ነው ያለችው" የ፭ዓመቷ ህፃን። አሁንም ስጋት አለባት።
 
በሆነው ሁሉ እጅግ አዝኛለሁ። ከፍቶኛልም። እስከ መቼ ለሚለውም ይከብዳል። ይህን የሰሙ ወጣት ሴቶች እና ማግሥት አሳሳቢ ነው። ፍርሃት ያነጸው ትውል አይደለም ለአገር፤ ለአህጉር ራስንም ለመምራት ጋዳ ነው። 
 
የኔወቹ እንዴት ናችሁ። በውነቱ እንዲህ በደራሽ ጉዳዮች ብቅ እምለው ዜናወቹ ዕድሜ እንዳይበላቸው ነው፤ እንጂ ወደ መደበኛ ተግባሬ አልተመለስኩም። 
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
የBBC ዘገባው ከሥር አለ። 
 
#የፊደል እርማቱን ቆየት ብዬ እከውናለሁኝ።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
05/01/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ሰውነታችን እናክብረው!
 
=========////===========
«የፋኖ ኃይሎች "ሰላይ ናቸው" ያሏቸውን ሦስት ሴቶች መግደላቸውን የታጣቂዎቹ አመራር አረጋገጡ»
«በታጣቂዎቹ ሰላይ ናቸው በሚል የተገደሉት ሦስቱ ሴቶች» BBC.
3 ጥር 2026
 
«በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ በሚገኘው ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሦስት ወጣት ሴቶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ተገድለው ተገኙ።»
 
«ድርጊቱ መፈጸሙን ለቢቢሲ ያረጋገጡት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ ኮማንድ አባል አስረስ ማረ ዳምጤ፤ ሦስቱ ሴቶች "ለጠላት ሲሰልሉ በመገኘታቸው እርምጃ መወሰዱን" በመጥቀስ እርምጃውን ተከላክለዋል።»
 
«የደብረ ኤልያስ ወረዳ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ግድያው የተፈጸመው "የቀን ሥራ ላይ" ተሰማርተው በነበሩ ሴቶች ላይ እንደሆነ እና ከመካከላቸው አንዷ "የመስማት ችግር ያለባት" እንደሆነች በመግለጽ ታጣቂዎችን ከስሰዋል።»
 
«ከ17 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሦስት ሴቶች ከደብረ ኤልያስ ከተማ ወጣ ብሎ ባለ "ጥጃ ጎጠር መገንጠያ" የተባለ አካባቢ ተገድለው የተገኙት ማክሰኞ ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም. እንደሆነ የወረዳው የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደምስ አለኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።»
 
«የወረዳው የፀጥታ ኃይሎች ሦስቱን የሴቶች አስከሬን ያገኙ ከነዋሪዎች በደረሳቸው ጥቆማ እንደሆነ የወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሙላት ሙንዬ ገልጸዋል። ሙላት እንደሚናገሩት አስከሬኖቹ የተገኙበት ቦታ "በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያለ" ነው።»
"[አካባቢው] ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ነው። ታጣቂዎች የያዙት አካባቢ ነው። [...] እዚያ የሚተላለፍ ሰው 'ሦስት ልጆች ተመትተው ወድቀዋል፤ ጭንቅላታቸውን ነው የተመቱት' የሚል ጥቆማ ሲደርስ የፀጥታ ኃይል ሄዶ፣ አስከሬናቸውን አምጥቶ፣ ለቤተሰቦቻቸው አስረክቦ እንዲቀበሩ ተደርገዋል" ብለዋል።»
 
«ይህንኑ የሚያጠናክሩት የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊው ደምስ በበኩላቸው፤ ሦስቱ ሴቶች "በጥይት ተደብድበው" እንደተገደሉ አስረድተዋል። "የተለያየ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች ፈጽመውባቸዋል" ሲሉም ወንጅለዋል።»
 
«ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙ እንዴት እንደተረጋገጠ ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው፤ "ሐኪሞችን ይዘን ሄደን ነበር። ከዚያ በኋላ የተፈጸመ ድርጊት ካለ በሚል ነበር አስቀድመን ይዘናቸው የሄድነው። ይዘናቸው ከሄድን በኋላ ያለውን ናሙና ወሰዱ፣ ልጆቹን ከፋፍነው አነሱ። ከዚያ በኋላ ሲታይ እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደፈጸሙባቸው ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት" ብለዋል።»
 
«የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሙላት እንደሚናገሩት የሟቾቹ ማንነት የታወቀው "በመታወቂያቸው" አማካኝነት ነው።»
 
«ከሟቾቹ አንዷ የሆነችው ሙያነሽ ተሾመ "የ17 ዓመት" ታዳጊ እንደነበረች የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊው ደምስ ተናግረዋል። ትህትና (ቃልኪዳን) አለኸኝ እና መልካም ታዴ የተባሉት ሁለቱ ሟቾች ደግሞ "18 እና 19" ዓመታቸው እንደነበር ገልጸዋል።»
 
«ሦስቱ ሴቶች ላይ የተፈጸመው ግድያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የፌስቡክ ገጾች ባጋሩት ልጥፍ ነው።»
 
«በአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል "ቴዎድሮስ ዕዝ 206ኛ ኮር የሕዝብ ግንኙነት" ስም ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ጽሁፍ "የጠላትን ተልዕኮ ተቀብለው ለዘጠኝ ወራት መረጃ ሲያቀብሉ በነበሩ ባንዳዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን" ይገልጻል።»
 
"የፋኖ ካምፕ አለበት በተባለበት ሁሉ እየተዘዋወሩ መረጃ ሲያቀብሉ እንደነበር" በማለት የሚከስሰው የፌስቡክ ልጥፍ፤ "በሕዝቡ ለደረሰው የሕይወት፣ የሀብት እና የንብረት ጉዳት ተጠያቂ" ናቸው በማለት ይወነጅላል። በዚህም ምክንያት "'ሌሎችን ያስተምራል' በማለት በተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል" ይላል።»
 
«በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተሠራጨው ይህ መረጃ ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ ኮማንድ አባል አስረስ ማረ ዳምጤ የጉዳዩን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።»
 
«ሦስቱ ሴቶች "ካለፈው የክረምት ወር ጀምሮ ለረጅም ጊዜ የስለላ ሥራ ሲሠሩ ነው የቆዩት" በማለት የሚከስሱት አስረስ፤ ይህንንም ያደረጉት "በቀን ሠራተኛነት ሽፋን" ነው ይላሉ።»
 
"ይህንን የስለላ ሥራቸውን ሪፖርት የሚያደርጉት በአካባቢው ላሉት የሚሊሻ እና የመከላከያ እንዲሁም የአድማ ብተና አመራሮች መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።»
 
«እንደ የፋኖ አመራሩ ገለጻ፤ ሦስቱ ሴቶች የተያዙት "ወታደራዊ ሥልጠና ከሚወስዱ ምልምሎች ጋር በመመሳሰል በሥልጠናው ቦታ ሥልጠና የሚወስዱ መስለው ለምዝገባ በቀረቡበት ወቅት በታየባቸው የሰላይነት ምልክት" የተነሳ ነው።»
 
"ያንን ተከትሎ በተደረገ ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራዎች ተደርገዋል ይጠቀሙባቸው የነበሩ ስልኮችን፣ የነበራቸውን እንቅስቃሴ፣ እነማን ተልዕኮ እንደሰጧቸው ጭምር እነሱም አምነዋል" ብለዋል።»
 
"በተለይ ደግሞ ጅበላሙ ተራ የሚባል ሻለቃ ላይ ጉዳት እንዲደረስ ደምባ፣ አንገታም ጃንተከል እና ሊባኖስ የተባሉ ቀበሌዎች ላይ መረጃ ሲያጣሩ እንደነበር ከራሳቸውም አንደበት ተረጋግጧል፤ ከሌሎች መረጃ ከተቀበሏቸው ሰዎችም ተረጋግጧል፣ ከያዟቸው የግንኙነት መሳሪያዎችም ጭምር ተረጋግጧል" በማለት ተናግረዋል።»
 
«ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደብረ ሊባኖስ ወረዳ አመራሮች ግን ወጣቶቹ ሴቶች የስለላ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር መባሉን አይቀበሉትም።»
«የወረዳው የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች፤ ግድያው የተፈጸመው "ሰሊጥ የመሰብሰብ ሥራ ላይ ተሰማርተው በነበሩ የቀን ሠራተኞች" ላይ እንደሆነ በመግለጽ የታጣቂዎቹን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል።»
 
«ከሟቾቹ አንዷ የሆነችው ትህትና ዘመድ እና የወረዳው ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ዘውዱ ደምስም በተመሳሳይ፤ "እንኳ ተልዕኮ ልትቀበል፤ ከመንግሥት አካል ማን ምን እንደሆነ አታውቅም" ሲሉ ይከራከራሉ። ሌላኛዋ ሟች መልካም ታዴም "የቀን ሠራተኛ እና ሻይ ቤት ነው የምትሠራው" ይላሉ።»
 
«በታጣቂዎች ፌስቡክ ላይ በተለቀቀው ቪዲዩ ላይ ዘመዳቸው የሆነችው ሟች ስማቸውን በመጥቀስ "የፀጥታ ኃይል፣ አስተባባሪ" እንደሆኑ መናገሯን ያነሳሉ።»
 
"እኔ ደግሞ ሥራዬ ከፖለቲካው ጋር የሚያገናኘኝ ሳይሆን የመንገድ ትራንስፖርት ኃላፊ ነኝ" የሚሉት አቶ ዘውዱ፤ በቪዲዮው ላይ ይህንን የተናገረችው በተፈጸመባት "ድብደባ ምክንያት ነው" ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል።»
 
"ድብደባ ደርሶባታል፣ ብዙ መከራ አይታለች፣ ተደብድባለች፣ ተቀጥቅጣለች፣ በወሬ ደረጃ ከአንድ ወር ከሁለት ሳምንት በላይ ታስራለች። [...] የምታውቀኝ እኔ ስለሆንኩ ዘውዱ ብላ 'ተልዕኮ ተሰጥቶኝ ነው፤ እንዲህ ነው' የሚል መልዕክት አስተላልፋለች " ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።»
 
«ሁለቱ የወረዳ አመራሮችም በተመሳሳይ የተወነጀሉበትን ድርጊት ያመኑት "ድብደባ ተፈጽሞባቸው ነው" የሚል መከራከሪያ አንስተዋል።»
 
«የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ማዕከላዊ አመራሩ አስረስ ማረ ዳምጤ በበኩላቸው በሦስቱ ሴቶች ላይ "ድብደባ እና ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሟል" በሚል ቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።»
 
"የፋኖን ስም ለማጥፋት የአገዛዙ ሰዎች የሚናገሩት ነገር ነው እንጂ ሐሰተኛ ነው" የሚሉት አስረስ፤ በአካባቢው ከሚገኘው ሕዝብ "መካከል መርጠን እነዚህ [ሦስት ሴቶች] ላይ እርምጃ ልንወስድ የምንችልበት አንዳችም የተለየ ምክንያት የለም" ሲሉ ተከላክለዋል።»
"የደረሰባቸውም የፆታ ጥቃት የለም። ቃለ ምልልሱንም ሰጡት በነጻነት፤ ያለ ምንም አስገዳጅነት የተሰጠ መረጃ ነው። ሠራዊቱ በተለየ ሁኔታ እነሱ ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚያደርስበት፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ እነሱ ላይ እርምጃ የሚወስድበት ሌላ ምክንያት የለም" በማለት መከራከሪያቸውን አጠናክረዋል።»
 
«አስረስ "ስለላ ላይ ተሰማርተዋል" በማለት የሚከስሷቸውን ሴቶች "እንደ ተዋጊ ኃይል" እንደሚቆጥሯቸው ተናግረዋል።»
"በሕገ ደንባችን መሠረት ለጠላት ስለላ ሥራ ሲሠራ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የሞት ቅጣት እርምጃ እንደምንወስድ፣ ሌላም አካባቢ ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንደምንወስድ ይታወቃል" ብለዋል።»
 
«በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ላይ ግድያን መፈጸም እንደ የጦር ወንጀል ድርጊት ሊቆጠር የሚችል ስለመሆኑ ጥያቄ ቀረበላቸው የፋኖ አመራሩ አስረስ "ምርኮ የተያዘ ሰው፤ በተኩስ ልውውጥ መሃል በፈቃደኝነት እጁን የሰጠ ሰው ሲሆን ነው። ይሄኛው ግን በልዩ ሁኔታ የስለላ ሥራ ሲሠሩ ስለሆነ በቁጥጥር ስር ዋሉት፤ በሕገ ደንባችን መሠረት እንደ ምርኮኛ የሚያዙ አይደሉም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።»
 
"በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት እና ምርኮኛ አያያዝ ሕግ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የሚጥስ ነው ብለን አናምንም" ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።»
የፋኖ ኃይሎች "ሰላይ ናቸው" ያሏቸውን ሦስት ሴቶች መግደላቸውን የታጣቂዎቹ አመራር አረጋገጡ - BBC News አማርኛ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።