ወርሃ የካቲት ለእኔ የቅኔው ልዑል፤ #ፓን አፍሪካኒስቱ የብላቴው ጸጋዬ ገ/ መንፈስ የሚከብርበት ዓውዴ ነው። ለእኔ ጸጋዬዚም + ኢትዮጵያኒዝም + አፍሪካኒዝም= #የዕውቀት ዘርፍ ነው ብዬ አምናለሁኝ።

 

ወርሃ የካቲት ለእኔ የቅኔው ልዑል፤ #ፓን አፍሪካኒስቱ የብላቴው ጸጋዬ ገ/ መንፈስ የሚከብርበት ዓውዴ ነው።
ለእኔ ጸጋዬዚም + ኢትዮጵያኒዝም + አፍሪካኒዝም= #የዕውቀት ዘርፍ ነው ብዬ አምናለሁኝ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን። 
 
 
 
#ምዕራፍ ፲፰ 
 
ክብሮቼ ማዕረጎቼም ቤተ ሥርጉትሻ ቅኖች ሆይ! ዛሬ የ፲፰ ዓመት መንፈሰ ጸጋዬ ጉዞዬ በምዕራፍ ፲፰ቱ የአጤ ፌስቡክ ማዕዴ ዘለግ ብሎ ይቀመራል። እኔ ወደ ብላቴው አቀናሁ ወይንስ እሱ ወደ እኔ መጣ። ቅኔውን ለባለቅኔወች፤ ዕድምታውን ለዕድምታ ባለሙያ ሊቀ - ሊቃውንታት ልተወው። 
 
ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን በሚመለከት ለሙሉ ፲፰ ዓመታት የተጋሁበት፤ የተከሰስኩበት፤ ብዙ ፈተና ያስተናገድኩበት፤ ብዙም የተንገላታሁበት፤ የተገለልኩበት፤ ባን በሉት ብሎክ በእኔ ላይ ፈርሰስ ብለው ወክ እንዲህ ያሉበት፤ የተንበሸበሹበትም በኽረ ጉዳዬ ነው። በፓልቶክ በሉት፤ በድህረ ገጽ፤ አሁን አዲስ ገብ በሆነው የሚዲያ ዕድል ዩቱብም ሳይቀር #ፋክክሩ ለወረት ይደራል፤ የዘለቀ ግን የለም። ለምን? #በድንግልና የተወጠነ ስለማይሆን። አንድን የዕውቀት ዘርፍ ሊያዘልቅ የሚችለው የውስጥ #ቅንነት እና ንጽህና ብቻ ነው። 
 
የጸጋዬ ድህረ ገጽ ነበረኝ። በቦርድ ነበር የሚመራው። የልጆች ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ የነበረው ድህረ ገጽ ነበር። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተገዢነት፤ ተጠቅላይነትን ይሻ ስለነበር አሻም በማለቴ ቦርዱ ተበተነ። ግን ብቻዬን እኩል የጀመርኩት የጸጋዬ ራዲዮ ስለነበር። ያ ቀጠለ። የመጀመሪያው ፕሮግራም ሲደመጥ ነበር በአክራሪ ኦሮሞነት እና በአክራሪ ኦርቶዶክስነት የተከሰስኩት።
 
ፍልሚያው ደንበር አልነበረውም። እስኪበቃቸው የክፋ ሃሳብ እና የቅናት አክቲቢስቶች በአድማ ታገሉኝ። እኔ እህታችሁም የገብሬ (ገብረመድህን በርጋ) ልጅ ነኝ እና እስኪበቃቸው ታገልኳቸው። የጸጋዬ ራዲዮ እስከ አሁን ድረስ ይሰራል። በየወቅቱ ግን አዳዲስ ፈተናን ያስተናግዳል። በወር ሁለት ጊዜ በዕለተ ሃሙስ የቀን ቅዱስ ከ15.00 -16.00 በአማርኛ ቋንቋ #በ97.5 መካከለኛ ሞገድ በእምዬ ሲዊዘርላንድ፤ ዙሪክ ክፍለ/አገር፤ በዙሪክ ከተማ ይካሄዳል። የልጆች ፕሮግራምም ነበረው። 
 
1. በዘመነ ህወሃት የጸጋዬ ራዲዮ የፖለቲካ የትግል ሚዲያ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የሰው ልጅን የሚፈትነው የክፋ ሃሳብ የችግር መነሻ ምንጭ ምንድን ነው? ምን ስተን - ምን አጣን? ምን ብናደርግ ለትውልድ፤ ለአደራ ብቻ ሳይሆን ለሰብአዊነት እና ተፈጥሯዊነት ጠቃሚ ንጥረ ነገር ዘርተን፤ አብቅለን አጽድቀን ማስበል እንችላለን? በሚል የገዘፈ የእያንዳንዳችን የመፈጠራችን መኖርን ክህሎታዊ አመክንዮ ላይ ያተኩራል።
 
የሰው ልጅ ሲፈጠር ጸድቆ ነው። ጸድቆ የተፈጠረውን ንጽህና ማስቀጠል ዓለማችን ስለምን አልቻለችም? እኛም ኢትዮጵውያን የዓለማችን ክፍለ አካል ነን እና። ዓለማችን ጸድቀን የተፈጠርንበትን አመክንዮ ማስቀጠል ያልቻለችበት ምክንያት ወደ ዓለም ስንመጣ ንጽህናችን የሚያስቀጥል ተቋም #ስሌላት ነው የሚል ሃሳብ እኔ አራምዳለሁኝ። እራሱን የቻለም የአዌርነስ የፖስተር ቁጥር ፩ ዩቱብ ቻናልም አለኝ። የፈለገ ሰው፤ የፈለገ ተቋም በእኔ ላይ ያሳድም፤ ይታገል፤ ይፈትነኝ። ምንጩን አውቀዋለሁኝ። 
 
ችግሩ ከእያንዳንዳችን የሚመነጭ ሳይሆን ከግሎባሉ ዓለም የሥርዓት አደረጃጀት ጋር አያይዤ ነው እኔ እማዬው። ማንኛውንም ሁነት በዚህ ዕሳቤ መረብ ውስጥ አድርጌ ነው እምገመግመው። ስለሆነም በማንም፤ በምንም ነገር ላይ ቂም አይታሰብም። የቂም ልጆች፤ የልጅ ልጆችም ትውር እንዲሉብኝ አይፈቀድም። እኔ ሳልድን ሃሳቤን ማዳን አልችልም እና።
 
ክፋ ሃሳብ ለእኛ ብቻ የተሰጠ አይደለም። ደግነትም ቢሆን የእኛ ብቻ አይደለም። መፍትሄውንም ብቻችን ታግለን ከሥሩ መንቀል አንችልም። ግሎባል ንቅናቄ፤ ግሎባል ጥረት፤ ግሎባል ፈቃድ ያስፈልጋል። በመልካም ሃሳብ ዙሪያ ጥረቶች ቀደም ብለው ተጀምረዋል። ግን የግል ጥረቶች ወጥ መፍትሄ ሊያመነጩ አይችሉም። አዌርነስ ግን ሊፈጥሩ ይችላሉ። 
 
የእኔ የመፍትሄ ጎዳና ሃሳቤ ክፋ ሃሳብን የሚመክተው የፍቅር ተፈጥሮ ካሪክለም ተነድፎለት በመደበኛ ትምህርት በተከታታይ እና በትጋት ሲሰጥ ብቻ ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁኝ። ስለሆነም ክፋ ሃሳብን የሚመክት የፍቅር ተፈጥሮ ከሆነ የፍቅር ተፈጥሮን ልክ እንደማህበራዊ ሳይንስ እና የተፈጥሮ ሳይንስ፤ እንደ ሃይማኖታት አስተምህሮም ዕውቅና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አግኝቶ መደበኛ የትምህርት ዘርፍ ሊሆን ይገባል ነው ሙግቴ።
 
ይህን ሃሳቤን የዛሬ ፲፭ ዓመት ለተመድ እና ለአውሮፓ ህብረት ፃፍኩኝ። እነሱም መልስ ልከውልኛል። እግዚአብሄር ያክብርልኝ እና። ግን ዓለማችን የፍቅር ተፈጥሮ አጀንዳ ሆኖ አይቼ አላውቅም። እንደ እኔ ሃሳብ በትሪሊዮን የሚፈሰው ገንዘብ ለጦር መሳሪያ ምርት ነው። እሱን ቀነስ አድርጎ የፍቅር ተፈጥሮ ትምህርት ቤት፤ ዩንቨርስቲ፤ ኮሌጅ፤ የምርምር ማዕከል፤ ሚዲያ ሊኖር ይገባል ባይ ነኝ። 
 
ይህንንን እና ተያያዥ ንድፎችን በቁጥር ፪ Sergute Selassie የሥርጉተ ሥላሴ ዩቱብ በከበቡሽ ልሳንወርቅ ሚዲያ ላይ ለአገላለጽ እንዲያመች በግራፊክ መልክ፤ በድምጽም ሠርቼ አስቀምጫለሁኝ። ተስፋዬ ይህን ፕሮጀክት የሚያስቀጥል ትውልድ ይመጣል ብዬ አምናለሁኝ። የውስጥ አረምን ለማጥራት ቋሚ ተግባር፤ ትጉህ ትውልድ ይጠይቃልና። 
 
2. #ሁለተኛው ሃሳቤ ደግሞ ወንጀል ለምን በረከተ የሚል ነው።
 
ምክንያቱም ህግ የጥቂት ባለሙያወች ብቻ ስለሆነ መብትና ግዴታውን የዓለም ህዝብ ስለማያውቅ ይሆናል ወንጀል የተበራከተው ብዬ አስባለሁኝ። ይህን ለማመጣጠንም ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ ልጆች ስለ ህግ ጽንሰ ሃሳብ ሊማሩ ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ። በሁሉም አገር ህግ አንድ የሙያ ዘርፍ ነው። ስለሆነም የህግ ሊቃናት አሉ። ይህ ለእኔ በቂ ነው ብዬ አላምንም።
 
ማንኛውም የዓለም ልጅ ሁሉ የአገሩን ብሄራዊ ህገ - መንግሥት እና ዓለም ዓቀፍ ህግጋትን እንደ ዕድሜው ደረጃ ሊማረው ይገባል ባይ ነኝ። በኢትዮጵያ የሙያ ምርጫ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሲጠናቀቅ እና ውጤት ሲመጣ ነው። ይህ መንገድ ብቻውን የወንጀለኛ ተግባራትን መቋቋም አይችልም ባይ ነኝ። ማን? እኔው። 
 
2.1 " ወንጀለኛ" የሚለው ቃል ለእኔ ቀጥተኛ ትርጉሙ ጋር ስለማይመጣጠን፤ ሙግት አለኝ። ግዴታውን ያላወቀ አንድ የአለም ዜጋ ቢያጠፋ ወንጀለኛ ሊባል ይቻላል ወይ? 
 
22. የህግን ድንጋጌ Zአንቀጽ ባንቀጽ ማንበብ ብንችል እንኳን በምን አቅማችን #ልንተረጉመው እንችላለን???? ጥያቄዬ ይህ ነው። እርግጥ ባልተፃፈ ህግ የሚተዳደሩ አገሮች አሉ።
 
#እዚች ላይ።
 
የህግ ባለሙያወች ላይስማሙበት ይችላሉ። እኔ ግን ኢትዮጵያ ባልተፃፈ ህግ እና በተፃፈ ህግ ትተዳደራለች የሚልም ሃሳብ አለኝ። የሆነ ሆኖ እያንዳንዱ የዓለም ልጅ የአገሩን ብሄራዊ ህገ - መንግሥት ብቻ ሳይሆን #የተመድን የታህሳስ 10/1948 ድንጋጌም ሊማረው ይገባል ባይ ነኝ።
 
ስለሆነም ህግ ለጥቂት የዩንቨርስቲ ተማሪወች ብቻ የሚተው ሳይሆን፤ ሁሉም እንዲማረው ዕድሉ ሊሰጥ ይገባል ነው ጉዳዬ፤ ቢሆንልኝ ብዬ እምመኜውም። በኮሚኒቲም፤ በሚዲያም እንደ እኔ ያለ ሙሉ ዕድሜ ላለንም ዕውቀቱ ጋር እንገናኝ ዘንድ ሁኔታወች በግሎባል ደረጃ ይመቻች ነው እኔ የምለው። የህግ ድንጋጌወች ለእኔ ቅኔወች ናቸው። የጸጋዬ ራዲዮ፤ ቲክቶኬ ቁጥር ሁለት ዩቱብ ቻናሌ የከበቡሽ ልሳንወርቅ ሚዲያ አትኩሮቱ ይህ ብቻ ይሆን ዘንድ ወስኜ እዬሠራሁበት ነው። 
 
//// ጭካኔ የተለዬ ባዕት የለውም። ይልቁንም ድንበር አልቦሽ ነው።
////// ጥላቻ የተለዬ አገር የለውም። ይልቁንም ደንበር አልቦሽ ነው።
//////// ቂም የተለዬ ባድም የለውም። ይልቁንም ደንበር አልቦሽ ነው።
///////// በቀል የተለዬ አህጉር የለውም። ይልቁንም ደንበር አልቦሽ ነው።
////////// ወንጀል የተለዬ ፕላኔት የለውም። ይልቁንም ደንበር አልቦሽ ነው።
 
ችግሩ የወል ነው። መፍቴሄውም ዓለም ዓቀፍ የፖሊሲ ለውጥን ይጠይቃል። እኔ ቀደም ብዬ የዛሬ ፬ ዓመት ተመደ ዘመኑን በሚመጥን ሁኔታ እንደገና ይደራጅ፤ ይዋቀር ብዬ ነበር። ሰሞኑን ቁልፍ የዓለማችን ሊቃናት ሲያነሱት አዳምጫለሁኝ። ስለሆነም በማናቸውም ጊዜ የማነሳቸው ትውልድን አዳኝ ዕይታዬን ለቀኑ ቀን ሲሰጠው ዕውቅና ያገኛል። የተከበሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራንፕ ከተመረጡበት ዕለት ጀምሮ ዘመነ ትራንፒዝም እያልኩ እጽፋለሁኝ። አሁን ሁለት ሚዲያ ላይ ትራንፒዝም ዕርስ ሆኖ አዬዋለሁ።
 
የእኔን ሥም ሚዲያ ላይ ማንሳት #ከጋዜጠኛ ሥሜነህ ባይፈርስ በስተቀር ድፍረት ባይኖርም በእንድም በሌላም እኔ እማቀርባቸው ሃሳቦች ህይወት ያገኛሉ። ወር አይሞላውም የኢትዮጵያ መንግሥት ብሄራዊ የምህረት ዓዋጅ እና እራስን የመግለጥ ሁኔታ ያመቻች ብዬ የፃፍኩት። አቤቱ ፋኖ የራሱ አድርግ ተጠቅሞበታል። ይህ ማለት ማን ይሁን ማን ሃሳቤ አድማጭ ማግኜት ብቻ ሳይሆን ገዢ አግኝቷል ማለት ነው። በአጤ ፌስቡክም ብዙ ነገሮችን ቀርጫለሁኝ። እያዬኋቸውም ነው። ምኞቴ ያ ነው። 
 
#በተጫማሪነት የጸጋዬ ራዲዮ የአትኩሮት አቅጣጫ ……… 
 
ብላቴው የሥነ ግጥም ዓውደ ምህረት ነው። ስለሆነም በጸጋዬ ራዲዮ የእኔው ግጥሞች፤ የብላቴው በድምጽ የተሠሩ፤ በእሳት ወይ አበባ መድብሉ ካሉት ውስጥም የሥነ ግጥም ጊዜ አለ፤ እንዲሁም አሁን ከሆነ የባቲ፤ የአንቺ ሆዬ፤ የትዝታ፤ አንባሰል ቅኝቶችም በየሩብ ዓመቱ ሙሉ ፕሮግራም ይኖራል። 
 
በየመሃሉ በመደበኛ መሰናዶየም እንዲሁ፤ በተጨማሪም ራዲዮ ሎራ በባዕላት ዕለት የሙዚቃ ክፍለ ጊዜውም ኤክስትራ የኢትዮጵያ ሙዚቃም ቤተኛ ይሆን ዘንድ እየሰራሁበትም ነው። ቀደም ባለው ጊዜ እኔ ተፈጥሯዊ ድምጽ ላይ ነበር እማተኩረው ፏፏቴ፤ ዝናብ፤ የወፎች፤ የዋልያ ድምፆች ጋር ነበር መሰናዶዬ የሚቀርበው። አሁን ግን ጠረነ ኢትዮጵያ ገዢ ሆኗል። የጸጋዬ ራዲዮ ፓን አፍሪካንስት፤ ፓትሮዬቲዝም አቀንቃኝ ስለሆነ በዚህ ዙሪያ አንጀት አርስ ጉዳይ ሲገጥምም ይስተናገድበታል። 
 
ለዚህም ነው የየትኛውም ተቋም፤ የፖለቲካ ድርጅት፤ ንቅናቄ አቀንቃኝ፤ ጥገኛ የማልሆነው። እራሴን አፍርሼ ከዘመነኛ አዲስ ገብ መንፈስ ጋር ለመዳበል በፍጹም ፈቃደኛ የማልሆነው። ቋሚ አሻራውን እራሱን አስችሎ የገነባ ሰብዕ ሌላ ልጥፍ ጥገኝነት አያስፈልገውም። ለዛውም የሚቸግር ነገር ሳይኖር። እጅግ በጣም ተጠንቅቄ ነው ራዲዮ ፕሮግራሜን እምሠራው።
 
#እኮ ለምን?
 
ምክንያት ሥሙ። "የሚኒሊክ፤ የአሥራት፤ ቴወድሮስ፤ አሉላ፤ በላይ፤ አብርሃም ደቦጭ፤ አዲስ ዓለማዬሁ፤ በዓሉ ግርማ፤ ጣይቱ፤ ምንትዋብ፤ የኋንስ፤ ባልቻ፤ ሞገስ አስገዶም፤ ዘውዲቱ፤ እያሱ፤ ፋሲል፤ ዘራይ ደረስ፤ ገብርዬ፤ ወዘተ" ብለህ ስትጀምር ዬዛን የከበረ ባለሞገሥ የተግባር ጉልላት ሰብዕናን አክብሮ በዛ ልክ መሆንን ይጠይቃል። ማዝለቁም - እንዲሁ። ሥሞቹ አሻራ ናቸው። ሥሞቹ የተጋድሎ ምልክቶች ናቸው። ሥሞቹ የአደራ ምስብሃክ ናቸው። ሥሞቹ የትውልድ መንፈስ ገንቢ ንጥረ ነገር ያለባቸው ናቸው። ሥሞቹ ዓራት ዓይናማን ትንታግ ለማፍራት ሙሉ አቅም፤ ሙሉ አክሰስ፤ ሙሉ ክህሎት ናቸው - በራሳቸው።
 
ዕውነቱን ብነግራችሁ በህይወቴ ሙሉ ሐሴቴ የሚፈልቀው የብላቴውን የራዲዮ ፕሮግራም ሥሰራ ብቻ እና ብቻ ነው። ጥሪዬ ነው ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን። በሙሉ 18 ዓመት ጉዞዬ በብላቴው ዙሪያ የፃፍኩት የወግ ገበታ፤ የፃፍኳቸው ሥነ ግጥሞች፤ የሠራኋቸው ፕሮግራሞች ቢሰበሰቡ ቡዙ መፃህፍት ይወጣቸዋል። ነፍሴ ከዚህ የቅኔ ልዑል ጋር ያስተሳሰረው መምህር እና የቤተ - መጻህፍት ባለሙያው አባቴ #አቨይ ነው። ጥበብ ውስጥ ያስገባኝም አባ ዝምታ እሱ ነው። 
 
ብላቴውን ጨምሮ ቀደምት ጸሐፍት የአቨይ የህሊናው ሃይማኖቶቹ ነበሩ። አቨይ በአባቱ ደባርቄ የዋልድባ ሰው ነበር። ልጅ አያድግለትም ነበር። ዋልድባ ድረስ ሄዶ ተስሎ ነው የወለደኝ። ለጥሪዬ አቨይ ካፒቴን ነበር። ገና በጋሜዬ ለጀመርኩት የፖለቲካ ህይወትም ልዩ አማካሪዬ ነበር። ጭምት፤ በጣም ዝምተኛ፤ አንባቢ፤ ቁጥብ ነበር አቨይ። የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን አስተውሎትን በልጅነት ህሊናዬ የቀረጸው #መሐንዲሱ አቨይ ነበር። የኢትዮጵያ ጸሐፍት ለአቨይ ፲፫ኛው ፕላኔቶቹ ነበሩ። ራዲዮ እንዴት እንደሚወድ ቃላት አይችለውም። የራዲዮ ጋዜጠኝነትም ለእሱ ክብረ - በዓሉ ነበሩ። የVOA፤ የDW ጋዜጠኞች የክብር እንግዶቹ ነበሩ። አገር ውስጥም በተመስጦ ለይቶ የሚያደምጣቸው ነበር። 
 
የሚገርመኝ ስለብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ጉዳይ ቤተሰቦቼም ተመሳጮች ናቸው። ተጽዕኖ አሳድሬባቸዋለሁኝ። ምንም ዓይነት አዲስ ነገር በሌላ ሰው ሲዘጋጅም በብላቴው ከኖረበት ቀድመው ነው የሚያደምጡት። ጎንደሬነት መሆን የሚረዳው ከዚህ ላይ ነው። ብቃት፤ ልቅና እንጂ ሌላ መሥፈርት ለጎንደሬ ለማናቸውም ማህበራዊ ግንኙነት የለውም። 
 
አሁን እኔ እዚህ ሲዊዝ ስኖር ጓደኞቼ ጎጄ፤ ሽዌ ናቸው። ቤታቸውም የምሄደው፤ ይመጡም የነበረው ወደ እኔ እነሱ የመረጥኳቸው ናቸው። እኔ በተፈጥሮዬ ግንኙነቴ ሰብሰብ ያለ ነው። ዝርግ ህይወት አልወድም። እጅግ በጣም ቁጥብ ነኝ። ስለሆነም የተመጠነ ግንኙነቴ ለነፍሴ ከቀረቡት ጋር እንጂ ሌላ መሥፈርት አያስፈልገኝም። ወደፊትም።
 
#የጸጋዬ መንፈስ እና የኮሽ አይሏ እምዬ ሲዊዝ መስጋብር።
 
የጸጋዬ ራዲዮ ልዩ በሆኑ ክፍለ አገራዊ መሰናዶወች ይጋበዝ ነበር። ልምዱን ተመክሮውን እንዲያቀና። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውክልናም ሲያስፈልግ ይጋበዛል። ኢንባሲወችም ይጋብዙታል። አሁን አሁን እኔ አቅም እያነሰኝ ሲመጣ ተሳትፎዬን አቆምኩት እንጂ የጸጋዬ ራዲዮ፤ የጸጋዬ ድህረ ገጽ በራሱ ጊዜ ዕውቅና ያገኜ ነው። በተለይ በኢንተግሬሽን ቤተ መጸሐፍቶች። የጸጋዬ መንፈስ የፈተና ይሁን የነፃነት ትግሉን በየፈርጁ የረታ፤ መሰናክሉን ሁሉ አስታግሶ የበረታ፤ ኢትዮጵያም እንዳይጎድልባት ጎደሎዋን ለመሙላት የተጋ፤ የእናቱ ሥሟ አንገቱን እንዳይደፋ የበኩሉን ድርሻ በተሟላ ዲስፕሊን የተወጣ ነው። 
 
እርግጥ ነው አንዲት አርቲክል ጽፈው ጀግና ተብለው፤ ውዳሴም ሲዘንብላቸው፤ ክብርም ሽልማትም እንደሚያገኙት የየጊዜው፤ የየዘመኑ ሰብዕናወች አንፃር ዕድሉ {} ነው። ለምን። #በጎንደሬዋ አንስት ራዲዮ ፕሮግራሙ ተመሥርቶ ስለሚመራ። ጎንደሬነት ከምድር በላይም ይሁን በከርሰ ምድር ብዙ ፍች፤ ትርጉም እና ሚስጢር ያለውን ያህል የልጆቹ ልቅና በልዕልና ግን ተዳፍኖ ይቀር ዘንዴ፤ ፊት ይነሳ ዘንድ መሰናክሉ ወዘተረፈ ነው።
 
የጸጋይ ድህረ ገጽን ሆነ የጸጋዬ ራዲዮን ስመሠርት ስደተኛ ካንፕ ሆኜ ነው የጀመርኩት። ኢንተርኔት ያንጊዜ አይታሰብም ነበር። ኮንፒተር ህልም ነበር። መኖር እራሱ ዳጥ እና ማጥ ነበር። ግን ታቀደ። ተከወነ። እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ መፃፊያ ጠረጴዛ ኑሮኝ አያውቅም። ጉልበቴ ነው ጠረጴዛዬ። ይህን ስጽፍም ከጉልበቴ ላይ አስደግፋ ነው። ካንፕ እያለሁ ለምዶብኝ ከጠረጴዛ ላይ ስሆን ሃሳብም ማፊ ነው። የተፈቀደልኝ ይህ ነውና። በተፈቀደልኝ ህይወት የድንግሉ፤ የመምህሩ፤ የሐዋርያውን ቅዱስ ጳውሎስ "ይበቃኛልን" አስፈቅጄ በሐሤት ከብዕሬ ጋር በታቦታችን በጸጋዬ መንፈስ አለን። አይደክመኝም። አልዝልም። 
 
በእኔ የዕድሜ ደረጃ ሊገኙ የማይችሉ ክፍለ አገራዊ፤ ብሄራዊ፤ ሉላዊ ገጠመኞች ነበሩኝ። በኃላፊነትም እንዲሁ። ግን እንደ ራዲዮ ጋዜጠኝነት የሚገዛኝ ሙያ ግን ፈጽሞ የለም። እኔ እንጃ የራዲዮ ጋዜጠኝነት ቀለሙ፤ ህብሩ ሐመራዊ ነው። የመጨረሻው የመውደዴ ደረጃ የሚገለጸው በራዲዮ ፍቅር ነው። እግዚአብሄር ይመስገን ለየትኛውም የራዲዮ ዝግጅት ድምጼንም አማኑኤል አባቴ መርቆልኛል።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።" 
 
3. ………#ከለታት አንድ ቀን የሆነውን ልንገራችሁ።
 
3.1) የፍቅር ተፈጥሮ የመማሪያ ካሪክለም ሊነደፍለት ይገባል ብዬ ተመድንም፤ የአውሮፓ ህብረትንም ከጠየቅሁ በኋላ በፍቅር ዙሪያ ዓለማችን ምን እየሠራች ነው ብዬ ማሰስ ጀመርኩኝ። ሁሉንም አህጉር አዳረስኩት። የእስያ ልጆች በሜድቴሽን ጥበብ የውስጥ ብስጭታቸው ታግሶ አገኜሁት። ስለዚህም ቲም ወርክ ላይ ሰላማዊ እንደሆኑ ተረዳሁኝ። ብዙ ቲም ወርክ ላይ ከቀውስ ነፃ የሆኑ ወጣቶችንም አስተዋልኩኝ።
 
3.2) ከዛ አውሮፓ ላይ አንድ የጀርመን ዩንቨርስቲ የልጆችን የውስጥ ቁጣ ለመግራት ጥረቱን አዳመጥኩኝ። አሜሪካም በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ሜድቴሽን እና ወጣቶችን በሚመለከት መረጃ አገኜሁኝ። እስኪ እኔም ልግባ እና ልማረው ብዬ ዮጋ ተማርኩኝ። ቲሙ እጅግ ሰላማዊ፤ ፍቅር እና ንጹህ ትስስር እንዳለው ተረዳሁኝ። መሰጠኝ የአኗኗር ዲስፕሊኑ።
 
3.3) አፍሪካ ላይስ ምን ተወጥኗል ብዬ መጀመሪያ ኢትዮጵያ አገሬ ላይ አንዳንድ ነገሮችን ገባ እያልኩ ማየት ጀመርኩ። የህወሃት ፕሮፖጋንዳ ያቅለሸልሸኝ ስለነበር የህወሃትን ሚዲያ የማዳመጡ ፍላጎት እንብዛም ነበርኩኝ። የሸገርን ታሪክ ቀመስ መነባንብ፤ እና ቃለ- ምልልስ አዳምጥ ነበር። ሳደምጥ ልዕልት አገሬ ኢትዮጵያ ላይ እንዳለሁም ይሰማኝ ነበር።
 
3.4) በፈላስፊት ኢትዮጵያ የውስጥን ሁነት ለመምራት ያለውን ጥረት በሚመለከት ስጥር ዶር ምህረትን ደበበን አገኜሁ። ሃይማኖታዊ ይዘትም ቢኖረው የመልካም ሃሳብ አቅጣጫ ለትውልድ መፍትሄ ነው ብዬ ስለማምን መከታተል ጀመርኩኝ። በዚህ ውስጥ ነው አቶ አብይ አህመድን ያገኜሁት። የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚር ነበሩ። ያን ጊዜ አቶ ነበሩ።
 
3.5) ማን ናቸው እኒህ ሰው ብዬ ማሰስ ጀመርኩኝ። የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚር ሆነው አገኜኋቸው። ቢሯቸውን ሳይ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን #በክብር መንበር ላይ አገኜሁት። ሌሎች ኢትዮጵያዊ ቀደምት ጸሐፍትም በግቢው ውስጥ ርስተኛ ሆነው አገኜኋቸው። ይህም አለ አልኩኝ። አቶ አብይ አህመድ የሚመሯቸውን ስብሰባወችን በመደበኛ መከታተል ጀመርኩኝ። ልቤ ተከፍቶ የመልካም ሃሳብ ፍሰትን ማዳመጥ ጀመርኩኝ። ያን ጊዜ የአሁኑ ዶር አብይ አህመድ አልነበሩም። ይህ ሰው ጠቅላይ ሚር ቢሆን ሁሉ ብዬ ከሥር ጽፌም ነበር። ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን፤ ፓን አፍሪካኒስቱን፤ የቅኔ ልዑሉን መንፈሱን እዛ በክብር ሳገኝ ተስፋ ኖረኝ።
 
በውነቱ ስለብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ቀድሞ መፈጠር አትኩሮቱ እንብዛ በነበረበት ባላሰብኩት ቦታ ክብሩ ጎልቶ ሳገኝ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በተቋሙም፤ በአመራሩም ተመሰጥኩኝ። 
 
3.6.1) ከዛ ደግሞ ዘመኑን ባላስታውሰውም እኔ የጸጋዬ ራዲዮን መግቢያ ያደረኩት "ፈራን ፍቅር ፈራን" መግቢያ አድርጎ ቀንበጡ ቅኔኛ ቴዲ አፍሮ (ዶር) ተቃኜበት፤ ምስርዬ የእኔ ብርሃን ካሴቱን ገዝታ ላከችልኝ።
 
3.6.2) ከዛ ለውጡ መባቻ በዘመነ ኦሮማራ አካባቢ አንድ ሙሁር በቅኔው ልዑል በብላቴ ጸጋዬ መንፈስ መጸሐፍ እንደፃፋም ሰማሁኝ። ጠቅላይ ሚር አብይ ጥረታቸውን ቀጥለው በሥልጣን መባቻቸው የእጅ ሰዓታቸውን ለጨረታ አቅርበው በትውልድ ቀየው ጠንከር ያለ ፕሮጀክት ተጀመረ። ከዛ በኋላ ብዙም አክቲብ ሆነው አላዬኋቸውም። ያ ተነሳሽ መንፈሳቸው ጠቅላይ ሲሆኑ የበለጠ ዕድል ጎልምሶ ሊያገኝ ይችል ነበር። ሁሉ ነገር በእጃቸው ነው። "#አብይም አለ …" ተብሎ ነውና ሁሉ ነገር የሚወጠነው።
 
3.7.3) በሌላ በኩል ቀደም ብሎም የመጀመሪያው የተውኔት የግል ትምህርት ቤት መሥራች፤ ሁለገቡ የጥበብ አባወራ፤ የሚዲያ፤ የፎቶግራፍ፤ የፊልም ባለሙያ አባ ቅንዬ ፍጹም አስፋው በማለዳ ኮከቦች በደንብ የሠራበት ዘርፍ የብላቴው መንፈስ ነበር።
 
3.6.4) የብላቴው መንፈስ "ፍቅር ፈራን" ካሪክለም ነው። እኔ እራሱ ተመድንም፤ የአውሮፓ ህብረትንም የጠየኩበት የፍቅር ተፈጥሮ ራህብ ከውስጤ ጋር ሃዲድ ሰርቷል። ይህ እኔ በማውቀው፤ ታቅዶ የተከወነ አይደለም። አንድም ግለሰብ፤ አንድም ተቋም፤ እንደ ማህበርም፤ አንድም የጥበብ ቤተኝነት፤ እንደ አገርም ኢትዮጵያ #አይዞሽ ብሎኝ የሚያውቅ፤ የሚረዳኝ - የሚያግዘኝ ገጥሞኝ አያውቅም። 
 
ግን ገፊ ኃይሉ ጥሪው ከፍጥረቴ ስለሆነ አቅጣጫውን እያስተካከለ የራዲዮ ፕሮግራሙን እራሱ መንፈሱ መርቶ ቋሚ አቅጣጫ አማኑኤል እንሆ አስያዘው። እራሱ ጋሼ ጸጋዬ ካሪክለም ነበር ብዬ አምናለሁኝ። ለእኔ ልዩ ስጦታዬ ነው። ምንም ነገር አይሰብረኝም። ሲከፋኝ፤ ሆድ ሲብሰኝ እንዴት እረሳኽኝ እላለሁኝ። ልክ እንደ ታቦት ነው የማዬው። እርግጥ ነው በሥራ ዓለምም ጠንካራ ሠራተኛ፤ ደፋር፤ የማልበገር ደግሞ ዲስፕሊን ነበርኩኝ። የሥራ መየዘኛኜ ሁልጊዜ A+ ነው። ከዚህም። ሥራ አገሬ ነው። ሥራ ሥሰራ ደክሞኝ አያውቅም። ዛሬም።
 
4. #ፊትነስ ለፍቅር ተፈጥሮ ያለው ዲስፕሊናዊ ዕሴት ምን ይሆን? ዮጋስ? ቲያትር እና ዳንስስ? ቋንቋ እና ሙዚቃስ? 
 
4.1 በፊትነስ ቋሚ ቲም ባይኖርም፤ ያው ገብያ ማለት ስለሆነ፤ አዕምሮን ለመግራት አቅም እንዳለው ተረድቻለሁኝ። ልብስ ለመቀዬር ስገባ ስወጣ፤ ከሰኞ እስከ እሁድ እሰራ ስለነበርም፤ በተለያዬ ሰዓት የፊትነስ ታዳሚውንም አየኋቸው። ፊትነስ በራሱ ጥሩ የዲስፕሊን ማዕከል መሆኑን ተገነዘብኩኝ።
 
4.2 ከዛ ቲያትር ስልጠና ጀመርኩኝ። የሚደንቅ ልምድ አገኜሁኝ። ከተለያዬ ሙያ፤ ከተለያዬ አገር፤ የተለያዬ የቆዳ ቀለም፤ የተለያዬ የዕድሜ ደረጃ ላዛ ፔሬድ ግን ቋንቋችን የጥበብ ዲስፕሊን ሆኖ አገኜሁት። ቋንቋን መማር በሙዚቃም ሞካከርኩት። ይህም ሌላው ትንፋሽን የሚሰበስብ አዲስ አቅጣጫ ነበር።
 
4.3 ከዚህ በኋላ እስቲ የዳንስን ዲስፕሊን ልዬው ብዬ ሞከርኩት። በትልቅ አዳራሽ ብዙ ሆኖ የሚሠራ አዲስ አርት ከሆላንድ የተገኜ ተብሎ አየሁት። ነፃነት በዕውን ዳንስ ዕውቀት ላይ እንዳለ አረጋገጥኩኝ። በአለባበስ፤ በሥልጠና ሂደት ያለው የነፃነት አቅም ቅኔ ነው። ኮርሱ የአንድ ቀን ብቻ ነበር። በያመቱ ይካሄዳል። ብቻ የእኔ ጥረት የሰው ልጅ ጥላቻን፤ ክፋ ሃሳብን፤ ቂም እና በቀልን፤ ጭካኔና ኢጎን አሸንፎ መውጣት የሚችልበት ዲስፕሊን የት ላይ ይገኛል ነው ጥረቴ? 
 
5. #በዚህ ሂደት ውስጥ … እያንዳንዱ የሠው ልጅ የሚሠማራባቸው መስኮች ሁሉ ያላቸው ዲስፕሊን ፍጹም የሆነ ሌላ የህይወት ተመክሮ ምዕራፍ መሆኑን ተረድቻለሁኝ።
 
እርግጥ ነው እናቴን በሥጋ ከማጣት ጋር ትጋቴ ፈተና ገጥሞታል። በዚህ ፈተና ውስጥ በጥንካሬዬ በቀደመው ልክ ያስቀጠልኩት የጸጋዬ ራዲዮን በሲዊዝ በዙሪክ ክፍለ አገር፤ በዙሪክ ከተማ በራዲዮ ሎራ ነው። ራዲዮ ፕሮግራሙ 24 ሰዓት ይሠራል። ከ20 በላይ ቋንቋወችን ያስተናግዳል። የሚመራው በኮሚሽን ነው። በጀቱ ከአባላቱ በሚሰበሰብ መዋጮ ነው።
 
አትኩሮቱ በሰባዕዊ መብት፤ በሴቶች፤ በፖለቲካ፤ በሙዚቃ፤ ጠንከር ብሎ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር እረገድ እንዲያውም በፊት ሰላማዊ ሰልፍ ነበር።
 
የሥራ ባህሉ ይደንቃል። የየለቱ ሠራተኛ ምግብ በጋራ እዛው ሠርተው ይመገባሉ። የበጋ፤ የበዓላት የወል ፕሮግራም አለ። በፊት እኔም በትጋት እሳተፍ ነበር። አሁን አሁን እየደከመኝ መጣ። ጉዞም አልወድም እኔ። እዚህም እምኖርበት ከተማ አብዛኛውን ጊዜ በእግሬ ነው የምጓዘው።
 
መልካም ፆመ - #ሁዳዴ
መልካም ፆመ #ረመዳን
 
#እርገት ይሁን። 
 
ምን ያህል እንደተጓዝኩ አላውቀውም።
ምን ያህል እንደሚቀረኝም አላውቀውም።
አለማወቄን ስጠይቀው፤ አለማወቁን ገለጸልኝ።
ተስፋን እጠብቃለሁኝ።
ተስፋ የአዋቂወች የግጥም መጸሐፌ ነው። በሽፋኑ ላይ ያለው ነው።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
የከርሞ ሰው ይበለን። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
18/02/2026
 
"ጥበብ ቤቷን ሠራች፤
፯ ምሰሦም አቆመች።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።