#ሲቃ ስለ ህክምና ዋርካው፤ ፍቱኑ፤ ርትሁም ክቡር ፕሮፌሰር ዶር፤ ማለደ ማሩ።

 

#ሲቃ ስለ ህክምና ዋርካው፤ ፍቱኑ፤ ርትሁም ክቡር ፕሮፌሰር ዶር፤ ማለደ ማሩ።
 
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።"
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
 
 
ክቡርም፤ ልዑልም፤ ንጉስም ብለው የተገባ ነው። ተማሪ እያለሁኝ የኬሚስትሪ እና የባይወሎጂ ባለ100% ተማሪ ስለነበርኩኝ የህሊናዬ #ጽንስ የዚህ ታላቅ ሰው ጥረት እና ህይወት ነበር። 
 
ያን ጊዜ በዛች ትንሽዬ ወጣት ህልም የነበረው በዘርፋ ገፍቶ #ሳይንቲስት የመሆን የተልዕኮ ስንቅ ነበር። ግን የእቴጌ ጎንደር የአቀማመጧ ሁነት የከፋኝ ቤተኞችን ጋበዘ እና ባዕቴ የጦርነት ቀጠና ሆነች። ቤተሰብ ተሰደደ። ኃላፊነት በዛ ለጋ ዕድሜ ላይ ተጫነ። ህልሙም ተረሳሳ።
ታናሽ እህቴን ተክቼ ትምህርቴን ለመቀጠል ሳስብ #ህወሃት ሥልጣን ያዘ። በቃ የትምህርት ናፍቆት ጋር መራራ ስንብት ሆነ። በስደቱም ታለመ ግን ፍጹም የማይቻል ሆነ።
 
ጋሼን ተማሪ ሆኜ የህይወቴ #ሞዴል እንዳደረኩት አልቀረሁም። የሥራ ትጋቴ፤ ቅልጥፍናዬ፤ ሥራን ባዕቴ ማድረጌ፤ በዛ የወጣትነት ዕድሜዬ ወጣትነቴን ተላልፌ እራሴን ከርክሜ፤ ከብዙ ነገር ቆጥቤ መባተሌ እድገቴን ፈጣን አደረገው።
 
ሥራዬ ከዚህ ታላቅ፤ ቅን፤ ጨዋ፤ ትሁት፤ ሰው አክባሪ፤ የጥረት #አብርኃም ጋር አገናኜኝ። በአካል ተገናኜን። የዕውነት የመማርን ልቅና በልዕልና ያዬሁበት ታላቅ የተግባር ዓራት ዓይናማ፤ ቅኔም ሰው ሆኖ አገኜሁት።
 
ለዛች በዕድሜ፤ በተመክሮ፤ በዕውቀት፤ በሥራ ልምድ አናሳ ለሆነች ለግላጋ፤ ቁመቷ ዘለግ ያለች ወጣት የአገር ጉልላቱ ታላቅ ሰው ይሰጥ የነበረው አክብሮት #ዩንቨርስቲ ነበር። ከህሊና በላይ ነበር።
 
ታናሽነቴን ስለማውቅ ከተቋሙ ጋር በሚያገናኙን የወጣት ማህበራት፤ እና የህክምና ባለሙያወች የአደረጃጀት ሁነት ጉዳይ ሲኖረኝ እራሴ ቢሮው ድረስ እሄዳለሁ እንጂ ወደ ቢሮ ና አልልም። #ድፍረት ስለሆነ። የጎንደር ይተብኃል "ልክን ማወቅ ከልክ" ያደርሳልን መተላለፍን ከልጅነት ጀምሮ አልፈቅደውምና። 
 
ወደ ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ቀጠሮ አስይዤ ስሄድ የሚገርም የሰብዕና ልኩን አገኛለሁኝ። የሄድኩበትን ዓላማ ለማስፈጸምም የሚቻሉ እና የማይቻሉ ጉዳዮችን ለይቶ ያስረዳኝ ነበር ከምል ያስተምረኝ ነበር።
 
የጎንደር ክፍለአገር የህክምና ባለሙያወች ማህበር ሊቀመንበር የነበሩ ረዳት ፕሮፌሰር በግማሽ የመናዊ የነበሩ ሌላ ታላቅ ሰውም ነበሩ። በሥሜ አይጠሩኝም ነበር "#ታቸር" ይሉኝ ነበር።
 
ዕውነት ለመናገር በስደት አገር የተደፋው #ትጋቴ አገሬ ላይ ብሆን ስንት ህዝበ - ጠቀም ተግባር በዛ ጸጋ እከውንበት ነበር? ፈሶ ቀረ። የሆነ ሆኖ ዛሬ የጋሼን ሁነት ሳይ ዕንባዬ ፈቃዴን አልጠየቀም። እኔም አልነፈግኩትም። ያ ትሁት አንደበቱ፤ ያ ሰውኛ አቀራረቡ ይናፍቀኛልና።
ሃኪም የሚባል ዩቱብ ቻናል ላይ በስንት ዘመን ቃለ ምልልሱን ሳገኝ የተሻለ ፎቶ ፍለጋ ጉግል ስገባ #ምንም ፎቶ የለውም። አዘንኩኝ። ከውስጤ ነው ያዘንኩት። በትንሽዬ ቤት የተጀመረ ተቋም አህዱ ብሎ ጀምሮ ከዚህ ያደረሰ የጽሞና፤ የተመክሮ፤ የመሆን፤ የጽናት ጀግናን ፎቶ፤ ታሪክ ይህን ያህል ተራቁቶ ማግኜት ውስጥን እንደ ዳቦ ይቆርሳል።
 
ገራሚው ነገር ሃዘኔን ቋጥሬ አርቲስት ወ/ ሮ አምለሰት ሙጬ ፕሮግራም ብትሰራበት ብዬም እዛው ፔጇ ላይ አመለከትኩ። መልስ የለም። ብዙውን አዘጋጆች አያነቡትም። ይህን አውቃለሁ። ግን አስተያዬቱ ተደጋጋሚ ሲሆን መልስ ለመስጠት #ንፍገት ጥሩ አይመስለኝም። ታሪክን ጊዜ ይሠራል። ጊዜን መሻማት ደግሞ ብልህነት ነው። 
 
ጋሼ #አንድ ሰው አይደለም። ፈውስ ነው። ፍቱን ነው። አብነት ነው። ዩንቨርስቲ ነው። ነገ ነው። ከነገ ወዲያም ነው። ትውልድ ነው። ታሪክ ነው። ትሩፋት ነው። አደራ ነው። ትውልድም ነው። የትውልድም ነው። እርጋታው ይመጣብኛል። ስክን ያለ ነው። አድማጭነቱ ኮሌጅ ነው።
 
አያችሁ የስደት ማዕቀቡ ይህ እንጂ እኔ የራሴ ቋሚ የራዲዮ ፕሮግራም አለኝ፤ ብዙም አማራጮች ነበሩኝ። ግን ስደት በልኩ ያልተሰፋ ሽብሽቦ ስለሆነ የምፈልገውን በምፈልገው ጊዜ ማድረግ አላስቻለኝም። 
 
በተደጋጋሚ ለጋሼ የምስጋና ፕሮግራም #ጎንደሮች እንዲያዘጋጁ ወትውቻለሁኝ። ጋሼ በህይወት እያለ በሥሙ ትምህርት ቤት፤ ኮሌጅ፤ መንገድ፤ ተቋም እንዲሰየምም አቤት ብያለሁኝ።
 
በዚህ አጋጣሚ የሃኪም ፔጅን አመሰግናለሁኝ። እራሱ የፊልም ሁለገብ ባለሙያው አቶ ሰውመሆን ይስማው ጭምር ቢያስብበት መልካም ነው። የዕውነተኛ ታሪክ ዶክመንቴሽን መሥራት ይችላል።
 
በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር የሚተዳደሩ ሚዲያወች እንደዚህ ዓይነት አገር የሆኑ ልዑቃንን ታሪክ ፈልጎ መዘገብ። ተከታታይ ፕሮግራሞችን መሥራት። ለትውልዱ ትምህርት እንዲሰጡ መድረክ መሥራት ይገባል። #ዕንቁ ጉዳይ ነውና።
 
የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የጤና ቢሮ የተከበረው፤ የህክምና ዋርካውን ፕሮፌሰር ዶክተር ማለደ ማሩን #ዕውቅና ሰጥቶ፤ ቢሸልመው ያስከብረዋል እንጂ የሚያጎድልበት አንዳች ነገር የለም።
 
የሆነ ሆኖ ዛሬ ያገኜሁት መረጃ ቢያበረታታም ቀጣይ ተጨባጭ ተግባራት ግን የጎንደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የህክምና ተቋሙ በዚህ ጉዳይ ቋሚ መጠሪያ ተግባርን መፈጸም ይገባዋልል። 
 
ጋሼ ቅንነቱ፤ አዛኝነቱ፤ ሰዋዊነቱ ተማሪ እያለሁ ታምሜ ሁሉ ሆስፒታል ተኝቼ በታዳጊ ወጣትነቴ በዕውን #ርህርህናውን አይቻለሁኝ። አቨይ ምግብ ይዞ ሲገባ ከአጠገቤ ያሉ ሰው አለፋ፤ አቨይ ሰውነቱ እየተንዘፈዘፈ ሄዶ አመለከተ። አቨይ አባቴ "ልጄን ስጡኝ ወይንም ክፍል ቀይሩላት" ብሎ ነበር ወደ ጋሼ ቢሮ የሄደው። ከዛ በፊት አይተዋወቁም። 
 
ለእርዳታ ፈጣን ብቻ ሳይሆን እጁም #ፈዋሽ ነበር። አባቴን አቨይም በሌላ ገጠመኝ በመዳህኒት ግጭት ምክንያትሁሉም ኦርጋኑ ተጎድቶ፤ ከሞት አትርፎልኛል። 
 
ወደ ቀደመው ስመለስ አቨይ መምህር እና የቤተ መጸሐፍት ኃላፊ ነበር። አቨይ ከቢሮው ሄዶ ሲያመለክት ግን ጋሼ አክብሮ ወዲያው አብረው ከአባቴ ጋር መጥተው ክፍል ተቀየረልኝ። ትንሽ አባበለኝ። እኔም ደንግጬ ነበር። ሞትን በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዬሁበት አጋጣሚ ነበር። ፈርቼ ነበር።
 
ህወሃት ጎንደርን ሊቆጣጠር ዋዜማ ላይ እያለም ታናሽ ወንድሜን ህፃን እንዳልክን እያስታመምኩ ከእጄ ላይ ነበር ያረፈው። ሁለቱ ኩላሊቶቹ ፌል አድርጎ ኮሌጁ የሚችለውን ያህል ጣረ፤ ግን አለፈ። በህይወቴ የሞትን ጎምዛዛ ስንብት ለሁለት ጊዜ በዓይኔ አይቻለሁኝ። በዚህ ጊዜም ቅኑ የህክምና #ጉልላት እረድቶኛል። 
 
ይህ ምን ልላችሁ ነው የሰብዕናው ጥሪው በማናቸውም ጊዜ፤ በሁሉም የሁኔታ ዓይነት ስለመሆኑ ላጠይቅላችሁ ነው።
አገር የተበጀችው፤ አገር የጠነከረችው፤ አገር ነገ የምትሆነው በዚህ መሰል ቅን የቀና፤ ትጉህ የተባ፤ ብርቱ ጠንካራ፤ ሌት ተቀን የባተለ ንብ፤ ልቅና እና ልዕልና። ታጋሽ እና ለፈተና አይበገሬነት የብቃት የውሃ ልክ ነው።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
30/03/926
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
 
"የፕሮፌሰር ማለደ ማሩ ‹‹የቸቸላው አባታችን›› የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ምረቃ በዓል ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን ያደረጉት ቁልፍ መልዕክት
*************************************
"የምንወድዎና የምናደንቅዎ አባታችን ወይም በአዲሱ መጽሐፍዎ አጠራር "የቸቸላው አባታችን" ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ፣
ክቡራን የዚህ ታሪካዊ መጽሐፍ ዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት፣
የታላቁ አገር ባለውለታ ታሪክ ጸሀፊ ዶ/ር ሰሎሞን በርሔ፣
ክቡር ፕ/ር መንገሻ አድማሱ የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣
ክቡር ፕ/ር ይግዛው ከበደ የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣
 
በዚህ ታሪካዊ መጽሐፍ ምረቃ ላይ የተገኛችሁ ክቡራን የፕ/ር ማለደ ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ የቀለም ልጆች፣ ታላላቅ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ምሁራን እና በዚህ ምረቃ ሥነ ሥርዓት በአካልና በበይነ መረብ ለታደማችሁ ክቡራን እንግዶች፣ ክቡራትና ክቡራን፤ ከሁሉ አስቀድሜ ታላቁ ምሁር፣ የተቋም ግንባታ ፋና ወጊ እና የሀገር ባለውለታው ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ፤ እንኳን ለዚች ታሪካዊት ቀን አደረሰዎ፣ አደረሰን እላለሁ።
 
በመቀጠልም ዛሬ በዚህ ታላቅ የክብር መድረክ ላይ እንድገኝ ስለተጋበዝኩና መልዕክት እንዳስተላልፍ ዕድል ስለተሰጠኝ የተሰማኝን ጥልቅ ደስታና ክብር መግለጽ እፈልጋለሁ። በዚች ዕለት እንድገኝ ስጋበዝ የተሰማኝ ደስታ እና ቀኑ እስኪደርስ የነበረኝ ጉጉት ወደር የለውም፤ ለዚህ ደግሞ ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝ።
 
አንድ ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ በሙያው ሀገርና ወገኑን አገልግሎ፣ ያበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ለትውልድ በሚተላለፍበት ታሪካዊ አጋጣሚ መገኘቴ ብቻ አይደለም፤ እንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንትነቴ፣ የፕሮፌሰር ማለደ ማሩን የአመራር አሻራ እና የዲንነት ኃላፊነት በትውልድ ቅብብሎሽ የተረከብኩ በመሆኑ፣ ይህ ሁነት በግል የሚሰጠኝ ትርጉም በእጅጉ ላቅ ያለ ነው።
 
ክቡራትና ክቡራን፤
 
ሀገራችን በልጆቿ እውቀትና ቁርጠኝነት የተነሳ አዎንታዊ ለውጥ እንዳስተናገደች አንድ ታላቅ ማስረጃ ቢፈለግ፣ ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ ዋነኛው ሆነው መቅረብ ይችላሉ። ፕሮፌሰር ማለደ ሀገራቸው አስተምራ ለቁም ነገር እንዳበቃቻቸው ሁሉ፣ እርሳቸውም ለሀገራቸው የዋሉት ውለታ እጅግ ታላቅ ነው፤ ይኸውም የተቋም ምሥረታና ማስቀጠል ውለታ ነው። ሀገር በተቋም ይጸናል፤ የማይናወጥ ጥልቀትና ቁመና የሚኖረውም ተቋማት ሲጠነክሩ ነው። ይህንን እውነት በአግባቡ የሚያሳየን ደግሞ ከሀገራችን ቀደምት የሕክምና ተቋማት መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ነው።
 
ከማሰልጠኛ ማዕከልነት ወደ ሕክምና ኮሌጅ የተደረገው ተቋማዊ ሽግግር ከእውቀት ባሻገር እንደ ፕሮፌሰር ማለደ አይነት ብርቱ አመራርን ጠይቋል። ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የአሁኑ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ (የዚያን ጊዜው የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ) በፕሮፌሰር ማለደ ብርቱ ክንድና ራዕይ የተነሳ፣ የሀገራችን ዝነኛ የሕክምና ጠበብትና የጤናው መስክ አመራሮች የሚፈጠሩበት የልህቀት ማዕከል መሆን ችሏል። ይህ ደግሞ እጅግ ታላቅ የኩራት ምንጭ ነውና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሕክምና ታሪክ ሲዘከር ይኖራል።
 
ክቡራትና ክቡራን፤
 
ተቋም ግንባታ የከበደ ኃላፊነት መሆኑን አብዛኞቻችሁ ትገነዘባላችሁ። ሀብት ማሰባሰብ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ድጋፍ አግኝቶ ሥራ ማስፈጸም፣ የውስጥና የውጭ አጋር ማበጀት፣ በተለይም ደግሞ በዚያ ፈታኝ ወቅት የነበሩ የፖለቲካ ጫናዎችን ተቋቁሞ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ግዙፍ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ሀገራችን በፖለቲካ ቀውስ በምትናጥበት በዚያ "የእሳት ዘመን"፣ የተቋም ግንባታን ኃላፊነት በብቃት መወጣትና ለተተኪው ትውልድ ጽኑ መሠረት ማስተላለፍ መቻል፣ ብዙዎቻችን ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ የፕሮፌሰር ማለደ ማሩ ታላቅ ታሪካዊ አበርክቶ ነው ብዬ አስባለሁ።
 
ፕሮፌሰር ማለደ ይህንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ግልጸኝነት ያለውና ከግለሰባዊ ፍላጎቶች የተሻገረ ተቋማዊ ዓላማ፣ የአቋም ፅናት እና ሙያዊ ሥነ-ምግባር ነበራቸው። የማሠልጠኛ ኮሌጁ ወደ ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲያድግ ሲወሰን፣ የዝግጅት ማነስ መኖሩንና በችኮላ መከናወኑን በድፍረት ተናግረው አካሄዱ እንዲስተካከል ገስጸዋል።
 
“ኮሌጁ ለሀገሪቷ የጤናው ዘርፍ ያደረገውን አስተዋፅኦ ከግምት ያላስገባ... የጤና አገልግሎቱን በቀዳሚነት የተገበሩትን ያላገናዘበ” በማለት ተቃውሞ ማሰማት፣ ድፍረት በሚመስልበት በዚያ ዘመን፣ ይህንን መናገር ፕሮፌሰር ማለደ ማሩን መሆንን ይጠይቃል። በአገልግሎት ዘመናቸው በመንግሥት በኩል ቃል ተገብተው ግን ያልተተገበሩ ሥራዎችን በነቂስ በማውጣት፣ ባለሥልጣናት ለሙያውና ለተቋሙ ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ ታግለዋል።
 
ክቡራትና ክቡራን፤
 
ለሀገርና ለተቋም መሥራት ዋጋ የሚያስከፍልበት ሁኔታ እንዳለ በጎንደር ቤተ-መዛግብት የተገኙ ፋይሎች ያስገነዝቡናል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በነበረው የሥርዓት ለውጥ ወቅት፣ ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ ደሞዛቸው ታግዶ ለእንግልት መዳረጋቸው የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስገነዝብና ልብ የሚሰብር ሁኔታ ነው። ይሁንና የሰው ልጅ በጽናትና በእውነት መንገድ ያደረገው አበርክቶ ሁሌም ቢሆን የሚዘከርበት ቀን መምጣቱ አይቀርምና ዛሬም የሆነው ይህ ነው። ጊዜው ቢረፍድም፣ እውነትና ሥራ ግን አይደበቁም።
ውድ ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ፤
 
ክቡራትና ክቡራን፤
 
የእርስዎ አበርክቶ በአንድ መጽሐፍ ተጠናቆ ይቀርባል የሚል ግምት የለኝም። ነገር ግን ይህ መጽሐፍ በመዘጋጀቱ፣ ባለውለታዎቻችን በሕይወት እያሉ "እንኳን ደስ አላችሁ" የማለትና ምርቃታቸውን የመቀበል ዕድል ስለሰጠን ደስታዬ ወደር የለውም።
 
በቅርቡ በሚመረቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70 ዓመትና የማስተማሪያ ሆስፒታላችን 100ኛ ዓመት ጉዞ መጽሐፍ የእርስዎ አስተዋጽኦና ስም በተደጋጋሚ ተወስቷል። ከዚህ በተጨማሪ እርስዎ ስምዎና ሥራዎ እንዲታወስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም የሕክምና ትምህርት ቤታችን በስምዎ የሰየመ ቢሆንም ለእርስዎ ያለንን ክብር ሕንፃ በስምዎ በመሰየም ብቻ የምንገልጸው ሳይሆን፣ በጽኑ መሠረት ላይ ያቆሙትን ተቋም በላቀ ደረጃ በማሳደግና የእርስዎን የሥራ ሥነ-ምግባር በማስቀጠል ለተተኪው ትውልድ በማስተማር ይሆናል።
 
በመጨረሻም የሕክምና ሳይንስ ኮሌጁን ምሥረታና ቀጣይነት በማይናወጥ የተቋም ባህል (Institutional culture) በጽኑ መሠረት ስለገነቡልን፣ በአስቸጋሪው ዘመን ምሁራንን ከምሥራቅ ጀርመን በማስመጣትና እስካሁን ድረስ የዘለቀ ታሪካዊ ዓለም አቀፍ ትብብርን በመፍጠር ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ ስላደረጉልን፣ እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ የማይጠፋ የዕውቀትና ተሞክሮ ሀብትዎን ስላወረሱን፣ በእርስዎ ጥላ ሥር በተቋሙ ተመርቀው በአገር ውስጥና በተለያዩ ዓለማት ለፍሬ በበቁ አእላፍ ምሁራን እና በመላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬንና አክብሮቴን አቀርባለሁ።
 
ለዛሬ መሰባሰብ ምክንያት የሆነውን በታላቁ የአገር ባለውለታ ፕ/ር ማለደ ማሩ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለጻፉልን ዶ/ር ሰሎሞን በርሄና ይህን ያማረ ታሪካዊ የመጽሐፍ ምረቃ መርሀ-ግብር ላዘጋጃችሁ ሁሉ በራሴ፣ በመላ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ እና የቀድሞ ተማሪዎቻቸው ስም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
 
ፈጣሪ ረጅም ዕድሜና ጤና ይስጥልን!"
 
አመሰግናለሁ!"
 
አሥራት ዓፀደወይን (ዶ/ር)
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣
መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም.

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።