ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የፍላጎት #ቅደም ተከተል ያስፈልገዋል። መሻቱ ከዘመኑ ግሎባል የፖለቲካ #ባህሬ ጋር በእጅጉ ሊጣጣም ያስፈልጋል።
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ፍላጎት ገደብ የለውም። የግል ፍላጎት፤ የማህበራዊ ፍላጎት፤ የቡድን ፍላጎት፤ የቤተሰብ ፍላጎት ይኖራል። ተፈጥሯዊም ነው። የፖለቲካ ድርጅት የሰወች የዓላማ እና የግብ ውህድ #ተቋም ነው። ይህ ተቋም ብሄራዊ ብቻ ሳይሆን አህጉራዊ፤ ሉላዊ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ሊኖርበት መቻሉን በፍላጎቶቹ ውስጥ ማካተት ይኖርበታል።
በሌላ በኩል ዘመን ሰጥ አሉታዊም ይሁን አወንታዊም ሁነት በአንድ የዘመን #ማዕቀፍ ውስጥ ይኖራል። የኢራኑን ጦርነት ማዬት እንችላለን። ኮቢድንም እንዲሁ ለናሙና ማቅረብ እንችላለን።
በተለይ እንደኛ ያለ በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ኋላቀር ተርታ የምትገኝ አገር ብሄራዊ፤ አህጉራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ሁነቶች፤ ዘመን ሰጥ አሉታዊ እና አወንታዊ ገጠመኞችን በቅጡ ማስተዳደር እንዲችል የፍላጎት ቅደም ተከተል #ተመጥኖ ሊኖረው ያስፈልጋል።
ይህ የሚያስፈልገው ለገዢው የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የእውነት ለሆኑት ተፎካካሪ ይሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ፍላጎትን መጥኖ በአቅም ልክ መሰናዳት ያስፈልጋል። ለዚህም የፍላጎት ቅደም ተከተልም አውጥቶ በዛ ልክ ለመራመድ አቅዶ መነሳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ዝንቅንቅ ያለ፤ ያልጠራ ሁነት ነው እየተመለከትኩ ያለሁት።
የቱ ይቅደም? ከምን ላይ ይጀመር? ከቀላሉ ነው የሚጀመረው። ከከባዱ ላይ ከመነሳት በፊት። ስኬት ዕድል ቀንቶ መዳረሻው ቢያምርም እንኳን በሳል እና አስተዋይ ብቁ #ማህንዲስ ያስፈልገዋል። አቅጣጫ የለሽ ፍላጎት መርከቧን ሊያሰምጥ ይችላል።
ከሁሉም በዋለለ ፍላጎት፤ በተበተነ ሃሳብ፤ በቅጡ ባልተደራጄ አቅም የተንጠራራ ፍላጎት #ፋንታዚ ነው የሚሆነው። መቼም አንድ ጽንስ በማህጸን ዘጠኝ ወር ወይንም ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሳይቆይ ልጅ አይሆንም። ቢያንስ የሰባት ወይንም የስምንት ወር ዕንቡጥ ሊሆን ይገባል። አንድ ልጅም ከተወለደ በኋላ ሂደቱን ጠብቆ ነው ለኃላፊነት እና ተጠያቂነት የሚበቃው። ይህ በማዬው፤ በማስተውለው ሁነት አላይም። የሁሉም ዒላማ አንድ ቦታ ላይ ያነጣጠረ ነው።
በሌላ በኩል ምኞትን፤ ፍላጎትን፤ ራዕይን፤ ዓላማ እና ግብን ዕውን ለማድረግ ተጨማሪ አስገዳጅ ሁኔታወችንም በማስተዋል መመርመር ያስፈልጋል። ለምሳሌ የዘመኑ የፖለቲካን ባህሬ ማጥናት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በልኩ ለፍላጎት ቅደም ተከተል አቅጣጫ ጠቋሚ ሊሆን ስለሚችል። በዘርፋ ማለቴ በዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ ዕውቅና እና አቅም ላይ ትኩረት የሰጠ የፖለቲካ ድርጅት ግን አላየሁም። የትኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ከዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ ጋር አጣጥሞ መሄድ ያስፈልገዋል። ይህ ግድ ነው።
አሁን አላውቅም የዬዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ በእኔ ዘመን ኮርስ ላይ እራሱን ችሎ ይሰጥ ነበር። ለምሳሌ በብዛት ከቀኝ ግዛት አገዛዝ አፍሪካዊ አገራት ነፃ ሲሆኑ እንደ አንድ የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ ይታይ ነበር። #የጎራባቾቢዝም መነሳትም ሌላው የዛ ዘመን የዘመኑ መለያ አንድ ባህሪ ነበር የሶሻሊዝሙ ካንፕ የተናደበት ስለነበር። የበሪልን ግንብ የፈረሰበት፤ የአውሮፓ አገሮች ወደ ትናንሽ አገር የተቀየሩበት ወቅት።
#ለምሳሌ የቅርቡን ባጣቅስላችሁ።
1) ህወሃት ጋር የነበረው አህጉራዊ፤ ዓለም ዓቀፋዊ የፖለቲካ አሰላለፍ አሁን የለም።
2) መልካዓ የአውሮፓ ህብረት ከ2024ቱ ጋር ሲታይ በዛ አቅሙ፤ የፖለቲካ አቋሙ ላይ አይደለም።
3) የአሜሪካ ገዢ ፓርቲ ሪፓብሊካኖች ናቸው።
4) የኔቶ አሁናዊ ፖለቲካዊ አቋሙ ከሦስት ዓመት በፊት በነበረው ላይ አይደለም።
5) በ2013 ዓም የኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት የነበረው የዓለም የኃይል አሰላለፍ በ2018 ዓይነቱ የተለዬ ነው።
ትናንት ዲታ አገራት ከራሳቸው አልፈው ለሌላው አገር ፍትህ፤ ዴሞክራሲ፤ ሰብዓዊነት ይታገሉ ነበር። በገፍም የእርዳታ እጃቸውን ይዘረጉ ነበር። በሌላ በኩል ለተከፋ ህዝቦች ዕንባም #ቅርብ ነበሩ። ዛሬ ግን ብለን ልንነሳ ይገባል።
ዓለማችን ትፈተናለች በየዘመኑ። በእኛ ዘመን እኮ እንዳዬነው መጀመሪያ "ሽብርተኝነት" ከዛ በመቀጠል ኮቢድ፤ ከዛ የይኩሬን እና የራሽያ ጦርነት፤ ከዛ የጋዛ እና የእስራኤል ጦርነት፤ አሁን ደግሞ የኢራን ጦርነት ፍም #የጋመ ላይ ያለ ሁነት ነው። ይህ በቀጥታ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አሰላለፍ፤ የኢኮኖሚ ሁነት፤ የዕቅድ አፈፃጸም ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
ስለዚህም ብዙ የዓለምን የኢኮኖሚያዊ፤ የማህበራዊ፤ የህልውናዊ ሁነቶችን የሚወስኑ ፈተናወች እያንዳንዱን አገር #እየፈተኑበት ስለሆነ እነኝህ ግሎባል ሁነቶች፤ ያላደጉ አገሮች ላይ የሚኖራቸው የሃሳብ፤ የሞራል፤ የኢኮኖሚ ተርድዖውን ይቀንሳል። አትኩረትን ይሻማል። የመኖር ተስፋ በመላ ዓለም ጭንቅ ላይ ስለሆነ የድሃ አገሮች ምርጫ፤ ግንባታ፤ ውበት፤ ዴሞክራሲ፤ ጦርነት ላይ የዲታ አገሮች ተሳትፏቸው ቀዝቃዛ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ከዘመኑ የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ጋር አብሮ የሚሄድ ፍላጎት፤ የአቅም ማኔጅመት፤ የፍላጎት ምጣኔ ቅደም ተከተል በእጅጉ በጣም በእጅጉ ያስፈልጋል። ልኩን ያልሆነ ኮንፊደንስ ጣጣው ብዙ ስለሆነ።
የምርጫ ክርክሮችን ሳዳምጥ፤ መሪወቹ ከተለያዬ ሚዲያ ጋር የሚያደርጉትን ቃለ ምልልስ ሳዳምጣ በእጅጉ ይገርመኛል። ቀንጣ ያሉ ፍላጎቶችንም አደምጣለሁኝ። ሌሎችም ሁነቶችን ስከታተል ይደንቀኛል።
በዚህ ውስጥ ያልበላ አንጀት ተሳትፎው ምን ሊሆን ይችላልም ታስቦ አይቼ አላውቅም። እራሱ እጩ ተወዳዳሪው የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሊሆን ይችላል ወረዳ ላይ ያለ #የጠኔ ቤተኛ ሊሆን ይችላል።
ምርጫ ችለው በሚካሄድባቸው ቦታወች በምርጫ ወቅት ሊኖሩ የሚችሉ የሎጅስቲክ መሰናዶም በማጓጓዝ ወዘተ …… ሰፊ ፈተና ሊኖር ይችላል። ለአስፈፃሚወችም ይሁን ለሰፊው መራጭ ህዝብ ተሳትፎ፤ ለታዛቢወችም ይሁን ለእጩወች አሁን ካለው ዓለም ዓቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ ለመጓዝ የመሻት ወይንም የፍላጎት ቴርሞ ሜትር ምጣኔ #በአቅም ልክ ሊሆን ይገባል።
ቅብጥ ቅልጥ ያሉ፤ ዘመን ዘለግ ያሉ መሻቶችን አደምጣለሁኝ። ሁሉም ለአገር ከሆነ ኃላፊነቱንም ሼር ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ጊዜ ዓለም ጭንቅ ላይ እያማጠች የፍላጎት ቅደም ተከተል መኖር በጣም ያስፈልጋል።
ሌላው ገዢው ፓርቲ ብልጽግና "ግጭት" ቢለውም ድሮን የሚሳተፍበት ጦርነት አማራ ክልል ላይ አለ። ይህ በራሱ ብዙ ነገርን ያሳጣል። ወደፊት ግራ ቀኙ በነባር አቅማቸው ልክ መፋለም ይችላሉ ወይ? ይህም ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ፈታኝ ጉዳይ ይመስለኛል።
የጦርነት ሁነቱ የአማራ ክልልን #የፖለቲካ ውክልናን በብዙ እጅ ይቀንሰዋል። አማራ ክልል ከትግራይ ባላነሰ ሁኔታ የፖለቲካ ውክልና ስስነት ሊገጥመው ይችላል።
ተመርጠው ምን ይሰራሉ? ያዬነው ነገር የለም ልትሉ ትችላላችሁ። #መብትን ፈቅዶ ማጣት በፖለቲካ አረዳድ የዊዝደም ቤተኛ አያደርግም። አንድ ድምጽ ሚሊዮን ነው። ፈጣሪ ከሰውም፤ ከተራራም ይመርጣል። የማናውቀው ሚስጢር አብሰንት በሆነበት ቦታ ሊፈልቅ ይችላል።
ሌላው ኢትዮጵያዊው ብቻውን አይበላም። ቤተሰቡን ይረዳል። የፓርላማ አባል ሲኮን መሃያ ይኖራል። ልምድም አለ። ሌላ የዕድል በርም ሊከፈት ይችላል። ስለዚህ ሊቀድሙ በሚገቡ የፍላጎት እርከኖች ላይ ተግቶ ከመስራት ይልቅ ፍላጎትን የወለሌ ገበታ መሸለም የተገባ አይደለም ባይ ነኝ።
የተደበላለቀ፤ ብዙ ዕምቅ ፍላጎቶች እርስ በርሳቸው የሚሰነቃቀሩበት፤ ቅይጥ የሆነ መንፈስ አያለሁኝ። ወስነው አይወስኑም። ልብ አንጠልጥለው የሃሳብ ሽክርክሪትን ዕድል ያወጣህ ዓይነት ድራማ አይጠቅምም። አንድ ፖለቲከኛ ቅድሚያ የራሱን የፍላጎት አጥር እና ግድግዳ አደራጅቶ የመምራት አቅሙን ሊወስንለት ይገባል።
በአንድ ጊዜ ክህሎት አይገኝም። ክህሎት የሂደት እና የሥልጠና እንዲሁም ዕድል በአግባቡ የመጠቀም #ቡቃያ ነው። ለዛ ደግሞ ዕድል በር ተዘግቶበት ሳይሆን በጭላንጭሏም ቢሆን ተጠቅሞ ዕድልን ማለምለም ሲቻል፤ ግን #ዚግዛግ የሆነ፤ ጥምልምል፤ #ጥምንምንም የሚል የሃሳብ አዟሪት ነገር ነው እኔ የማስተውለው።
የተሻሉ የሚባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ጥቂት ናቸው። ዕድል በተደከምክበት ልክ ነው የሚገኜው። #የገበሬውን ኑሮ ፈቅዶ የተንገላታ፤ ድምጹን ይሁንታውን ለማግኜት አቀበት የወጣ፤ ዳጡን የተፋለመ ማን ይሆን????
ይህም ሆኖ 100% ከመናፈቅ ዕድልን በፈቃደ እግዚአብሄር፤ በፈቃደ አላህ ላይ ጥሎ፤ መሻትን በአቅም ልክ መጥኖ፤ ለፍላጎት ጥርት ያለ የቅደም ተከተል የተግባር ሰሌዳ ሰርቶ ዘመን ሰጥ ሁነቶች ጋር መላመድ #ብልህነት ይመስለኛል።
አገር መምራት ለዛውም ኢትዮጵያን፤ ለዛውም የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ በየሰዓቱ ተለዋዋጭ በሆነበት ሁኔታ ብርቱ ማስተዋልን፤ ጥሞናን፤ ዘለግ አድርጎ ማሰብን በእጅጉ ይጠይቃል። አገር የመምራት ተመክሮ #ሱቅ #በደረቴ ላይ ስለማይሸመት ሰክኖ ደግሞ፤ ደጋግሞ ማሰብ በእጅጉ ያስፈልጋል።
አገር የገብያ ሸቀጥ አይደለችም። ወይንም ባዶ ቤት ሆና ገንዘብ ያለው የሚከራያት። አገርን ለመምራት በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የሰከነ የልምድ፤ የተመክሮ ባለቤትነትን ይጠይቃል። ለዛውም ዛሬ ዓለም ጭስ እና ጭንቅ በገፍ እየተቀናባት ባለበት ጊዜ? "#እናስተውል።"
"ጎልጓይ የፊት የፊቱን" ይላል። በቅድሚያ የቅርቡ፤ ዝቅ ያለው፤ የሚቻለው፤ የመሳካት ተስፋም ያለው ይደፈር፤ ከዛ በራሱ ጊዜ ትዕግሥቱ ከኖረ የሩቁን ለማግኜት ይቻላል እንደማለት።
በሌላ በኩል የሳይለንት ማጆሪቲው አቅም ስሌት ውስጥ ይግባ። እሱም ዜጋ ነውና። አቅሙም ከዲስፕሊኑ ጋር #አንቱ ነውና። በጣም የጨመተ ስኩን ማህበረሰብ ሙሉ አቅም፤ ሙሉ የማስተዋል ጸጋም የተሰጠው ነው። የማድረግ አቅሙም ሙሉዑ ነው።
ብዙ ጥግ የለሽ፤ በርካታ ባለቤት አልቦሽ ጉዳዮች በስኬት የሚጠናቀቁት ሙያ በልብን በሰነቁ፤ መድረክን በሚሸሹ ግን የአገር ህሊና በሆኑ ቤተ - ሳይለንት ማጆሪቲ አባላት ነው። ለእነሱ፤ ስለእነሱ ጉዳዬ ባይባሉም የተንጠለጠሉ፤ ተጀምረው የቀሩ ሁነቶች ተከርክመው፤ ጠፈፍ ብለው ለስኬት የሚበቁት በማህበረ ጭምቶች ነው። ፍላጎትን ለማሳካት የእነሱ #ይሁንታ በእጅጉ ያስፈልጋል እንደ ማለት።
ቸር አስበን ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
30/03/026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ