የፖለቲካል ፓርቲን የመረጠ ሰብዕ #የእኔ የሚለው የፖለቲካ ዕይታ ሊኖረው አይችልም።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ፎቶው የፖለቲካ ድርጅት ቋሚ ሠራተኛ ሳለሁ የነበረ የሥራ መታወቂያ ካርዴ ላይ ያለ፤ እንደ ልጄ የማዬው፤ አብሮኝም የተሰደደ፤ እጅግ እምሳሳለት የፓርቲዬ የኢሰፓ ቅርሴ ነው። ፓርቲዬን ኢሠፓ እወደዋለሁኝ። በህይወቴ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ፓርቲዬ ኢሠፓ ነው።
ከኢሠፓ ጋር እስከ መጨረሻው ታግያለሁኝ። እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ለፓርቲዬ ደንብ፤ ፕሮግራም #በድንግል ነው ያለሁት። ከፓርቲዬ ኢሠፓ መራራ ስንብት በኋላ አይደለም የፖለቲካ ድርጅት፤ ማህበር እንኳን በአባልነት ተመዝግቤ፤ ተሳታፊ ሆኜ፤ መዋጮ አዋጥቼ አላውቅም። ወደፊትም ፈጽሞ አይታሰብም። ይበቃል።
እንደ ዕድል ሆኖ እኔ አገር ለመምራት ሙሉ ልቅና፤ ሙሉዑ ልዕልና፤ ሙሉ ብቃት በነበራቸው ታላላቅ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊቀ - ሊቃውንት ነበር የመለመሉኝ። #የሠሩኝ ልበል። እነ ጓድ ገብረመድህን በርጋ፤ እነ ጓድ ወንድወሰን ኃይሉ ወዘተ…
የማይናወጽ ጽናት፤ #የማይበረግግ ሰብዕና፤ እጥፍ ዘርጋ የማይል ዕይታ፤ ገባ ወጣ የማይል የፖለቲካ አቋም ብቻ ሳይሆን አጥርቶ የመስራት ሚስጢር፤ የፖለቲካ ፓርቲ ጽንሰ ሃሳብ፤ ዲስፕሊን ተልዕኮ በተለያዩ የኮርስ፤ የሰሚናር፤ የጉባኤ ዕድሎች እንድሳተፍ በማድረግ ብቻም ሳይሆን ህይወቱ እኖረው ዘንድ በቅርብ እየተከታተሉ አዕምሮዬን አነጹት።
የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ቢመጣ - ቢሄድ፤ ሚሊዮኖች የእኛ ቢሉት፤ ስልጣን ቢይዝ ቢለቅ ከቶውንም #አይናፍቀኝም እስከ ህይወቴ ፍፃሜ። በዛ በተደራጄ፤ ምራቁን በዋጠ፤ ባስተዋለ ብቁ አድማጭ አለቃ የበቀለችው ዕንቡጥ ሌላ አምሮት አጀንዳዋ አይደለም።
እርግጥ ነው ፓርቲዬ ኢሠፓ እንደገና ተመልሶ ቢመጣ፤ ሥልጣን ቢይዝ ፈቅጄ አባሉም፤ አካሉም ልሆን በፍጹም #አልችልም። ለምን? የሕይወት ስታይሌ አንድ ጊዜ ውስጤ የተቀበለው ሰብዕ ይሁን ተቋም ባሰብኩት ልክ መሆን ከተሳነው ደግሜ ዕድል አልሰጥም።
ፓርቲዬ ኢሠፓ ድክመት ባይኖርበት ኖሮ ልጆቹን ለበላህሰብ አስረክቦ እንደ #ተበተን አንቀርም ነበር። አንድ ሰው አልተረፈም። ከወር ደሞዛችን በስተቀር አንዳችንም በባንክ ተቀማጭ ገንዘብ አልነበረንም። አላዘጋጁንም።
እኛ እናስተዳድራቸው የነበሩ ቤተሰቦቻችን የሁለት ወር የሚሆን #ስንቅ እንኳን አልነበራቸውም። ህይወታችን፤ መኖራችን፤ ተስፋችን፤ ራዕያችን ከስሎ ቀረ። ስለዚህም በምንም ታዕምር ኢሠፓን ደግሜ ለማዬት የሚያጓጓኝ አንዳችም ነገር የለም።
ያስተማረኝ፤ እኔን የመራበት፤ እኔን ያበቃበት ስታይሉ ግን በየትኛውም ዩንቨርስቲ እማላገኜው ነውና እንሆ #በድንግልናዬ ያስቀጠለኝ ያ ውለታው ነው ማለት እችላለሁኝ።
በዛን ጊዜ መሪነት የተለዬ ስልጠና በአገር ውስጥ እና በውጭ ይሰጣል። በተጨማሪም የቅርብ አለቆቻችን፤ የመምሪያ ኃላፊወች በሚያገኙን ደቂቃ ሁሉ #ያስተምሩናል። ይመክሩናል። ተግሳጽ ሲኖርም በፓርቲያችን ደንብ መሠረት ደስ ብሎን ቅጣቱን እናስተናግዳለን።
እርግጥ ነው በወጣትነት የፖለቲካ ድርጅት ጋር ለመቀጠል መወሰን፤ በተለይ ለሴት ልጅ #ጋራ የሚያክል ፈተና አለው። ግን ከብቁ መሪወች ጋር መሥራት፤ በእነሱ ሥር ሆኖ መማር የትም የማይገኝ #ምርቃት ነው።
አንድ ዕውነተኛ የፖለቲካ ድርጅት መሠረታዊ ሰነዶች ይኖሩታል። ደንብ፤ ፕሮግራም፤ መሪ ዕቅድ የሚባሉ። እነኝህ ለአባሉ ይሁን ለአካሉ ህይወቱ #የሚመራበት ሰነዱ ነው።
በፓርቲ ህይወት ውስጥ የግሌ ዕይታ፤ የእኔ አቋም፤ ፐርሰናል ምልከታዬ አይባልም ፈጽሞ! ፈጽሞ። እንደ ፓርቲዬ ወይንስ እንደ ግሌ ነው እምጠዬቀውም አይባልም። የግል የሚባል ፖላቲካ ዕሳቤ የፖለቲካ ድርጅት ቁልፍ መሪ ተሁኖ የለም።
ለአንድ የፓርቲ አካል ቀርቶ አባል የፖለቲካ ዕሳቤው፤ አቋሙ፤ ዕይታው፤ ርዕዮቱ አንዲት #ስንዝር ከፓርቲው ፍላጎት፤ ራዕይና ግብ ውጭ መሆን ፈጽሞ አይችልም። ይህ ተጭኖ ሳይሆን ረቂቅ ደንቡ፤ ረቂቅ ፕሮግራሙ፤ ረቂቅ መሪ ዕቅዱ በጉባኤ ከመጽደቁ በፊት ከታች ወደ ላይ ተመርምሮ፤ ሃሳብ ቀርቦበት በጉባኤ የሚጸድቅ ስለሚሆን። ስለዚህም ለተግባራዊነቱ የጋራ ድርሻ ይኖርበታል አካሉም አባሉም።
ሌላው ቀርቶ አንድ ሃሳብ ቀርቦ እኔ #ባልስማማበት እና በብዙሃን ድምጽ ቢጸድቅ፤ እኔ ለተሸነፍኩበት ሃሳብ ግንባር ቀድም ፈፃሚ እና አስፈፃሚ እሆናለሁ እንጂ የሃሳብ #አንጃ ፈጥሬ የፖለቲካ ፓርቲዬ ዲስፕሊን ፈተና ውስጥ እንዲገባ ፈጽሞ አላደርግም። ፈጽሞ።
ወጣቶችን በዕድሜ የበሰሉ፤ የገዘፋ የፖለቲካ ሊቃናትን በቅርብ ሊያግዟቸው ይገባል። የፓርቲ አባልነት፤ የፓርቲ አካልነት #በሩም ቤተኝነት አይደለም ህይወቱን የሚኖርት ተ - ዋ - ህ - ደ - ው - ነው።
በአባልነት እና አካልነት ውስጥ ስንጥር፤ ጭላንጭል #ስንጥቅ የለም። ሊኖርም አይገባም። አንድ ሰው የፖለቲካ ድርጅት አባልም አካልም ሲሆን እራሱን ሰጥቶ ነው። ሁለት ሦስት መንፈስን እያስተናገደ አይደለም።
በቅድሚያ የፖለቲካ ድርጅት አባልነት በቀጥታ አባል የሚሆኑ ጥቂት ናቸው። 90% መጀመሪያ #እጩ አባል ነው የሚኮነው። የእጩ አባልነት ቆይታው አንድ አመት ነው።
እጩው ወደ ሙሉ አባልነት ሲሸጋገርም ዝም ብሎ አይደለም። ሰብዕናው በጋራ በበላይ አካል ይገመገማል። እጩ ሲሆን እና ሙሉ አባል ሲሆን የአባልነት ካርዱ ቀለሙ እራሱ የተለዬ ነው።
በቀጥታ እጩም ሳይኮን፤ አባልም ሳይኮን #የመሪነት አካልነት አይታሰብም። ኃላፊነትም እንዲሁ በአቦሰጥ አይታደልም። መደበኛ ኮርሶች አሉ። ለአካልነት የሚታጩ 6 ወር የፖለቲካ ትምህርት ተከታታይ ኮርስ ይሰጣል። የትምህርት ቤቱ ሪኮማንዴሽን ነው በመዋቅር ውስጥ የኃላፊነት ድልድል የሚደረገው።
ሌላው ቀርቶ የንግግር ጥበብ ለ40 ሰዓታት ለ20 ፔሬድ ይሰጣል። ዕድለኛ ነኝ ተምሬዋለሁኝ። ከዚህም በራዲዮ ጋዜጠኝነት ኮርስ ፕረዘንቴሽን እና ቃለ - ምልልስ ፎርማቱን ተምሬያለሁኝ። ንግግር ጥበብ ነው። መክሊትም ነው። ክህሎቱ ግን #በስልጠና ይዳብራል።
በተፈጥሮው ሞናትነስ የሆነ ተናጋሪ ፖለቲከኛ ሊገጥ ይችላል። ንግግር #መሰጠትን ይጠይቃል። የሆነ ሆኖ ለህትምት ካልበቃው 8ኛ መጸሐፌ ወጋ ወግ ስለሆነ ከዛ ላይ ስለ ንግግር ጥበብ በጥቂቱ አንዳንድ ሃሳቦችን ጽፌዋለሁኝ።
ስብሰባ መምራት፤ የስብሰባ የአመራር ሥርዓቱ፤ ቅደም ተከተሉ ሳይቀር ስልጠና አለው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት በሥርዓት ካልተመራ #አናርኪዝም ይፈጠራል። አናርኪዝም አንጃን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ፓርቲውን እራሱ ሊያከስለው ይችላል።
የሆነ ሆኖ የሚመስጡኝ ፖለቲከኞችን አዳምጣለሁኝ። ውሽክ የምልበት ገጠመኞቼ ስለሚሆኑም ነው እማዳምጣቸው። ገና ከመልሱ በፊት "የግሌን ወይንስ የድርጅቴን፤ ወይንም ይህ ፓርቴየን አይወክልም የግሌ ነው" ይላሉ።
ፓርቲ እኮ የፖለቲካ መስመር ምርጫ ነው። ስለዚህ የተመረጠ መሥመር ፖለቲካዊ ህይወትህን፤ ፖለቲካዊ ህይወትሽን ሊመራ ግድ ነው። በስተቀር #ደባል ናችሁ ማለት ነው።
በሌላ በኩል የዲስፕሊንም ግድፈት ነው። በማናቸውም ሁኔታ ፓርቲውን ወክሎ የሚቀርብ ሰብ ሁለመናው፤ ጠረኑ ሳይቀር የፖለቲካ ድርጅቱን መምሰል ሳይሆን #መሆን መቻል መብታዊ ግዴታው ነው።
በፖለቲካ ፓርቲው ውስጥ ማመን፤ መታመን የውስጥ ፈቃድ ሊኖር ይገባል። ምክንያቱም በየትኛውም ሁኔታ የፖለቲካ ድርጅት አባልነት #በፈቃደኝነት ላይ ነው የሚመሰረተው። የደንቡ መጀመሪያ ድንጋጌ "አባልነት በፈቃደኝነት።" ይህ የማይናወጽ መርህ ነው፤ በተለይ በሶሻሊስቱ ርዕዮት።
ከፖለቲካ ድርጅት ጋር አካል ብቻ አይደለም ውህድነቱ የመንፈስም ነው። እኔ ሳሎን ቤት አለሁ፤ ፓርቲዬ ጓዳ ነው። "ማህረሜን ያያችሁ" እንባባል፤ ፈልግቻሁ አግኝቱ ዓይነት የተገባ አይመስለኝም።
ይህ ካልሆነ የፖለቲካ ድርጅት ምሥረታውም፤ ታሪካዊ ገጠመኙም #የገብያ ውሎ ወይንም አንድ የኢቤንት ናሙና ብቻ ይሆናል። የሚገርመኝ ነገር አለ። እኔን "አባል አድርገንሻል።" የሚል ኢሜል ይደርሰኛል።
እኔ እኮ የመንገድ ዳር ውሃ አይደለሁም፦ ያገኜ የሚጨልፈኝ። ፈቃድ ያስፈልጋል። ለዛውም ማኒፌስቶ ሲያረጅ ነው የሚዘጋጅለት ተደራጄ የሚባለው ፓርቲው ሁሉ። ደንብ ብዙወቹ ያላቸው አይመስለኝም። ለዚህም ይመስለኛል ከውልደቱ #ንደቱ የሚቀድመው። የሚያይለው።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት በደንቡ ድንጋጌ ልክ መጓዝ ከተሳነው #መገነዣ አዘጋጅቶ ሊጠበቅ ይገባል። ፒላሩ ደንብ ነው። የአንድ ተቋም አሰራርን ለማወቅ የሂሳብ አያያዝ ሰነዱን ማዬት በቂ ነው። እንደዛ ማለት ነው ደንቡ።
የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሸራረፍ የትውልድ ሆኖ እንዲቀጥል መልካም ዜናው ደንቡ ነው። አሁን ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከተሆነ በቃ ዕንቁነት ሆኗል። የፓርቲ ዲስፕሊን ግን አይፈቅድም።
ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለዛች ለተሰጠችው መክሊት እንጅ ከዛ ላለፈ ዲስፕሊን በልኩ ያልተሰፋ እጀ ጠባብ ወይንም ሽብሽቦ ነው የሚሆነው። ይህን በዘለንስኪዝም በተጨባጭ አይተናል። ያ ሁሉ የሥልጣኔ አቅም በጦርነት ሲፈተን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
31/03/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ