የህወሃት #የቀውስ ተስፋ የመከነበት #ሐዋርያ የሱማሌ ክልል።

 

የህወሃት #የቀውስ ተስፋ የመከነበት #ሐዋርያ የሱማሌ ክልል።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 No photo description available.
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
በአቶ አብዲ ዒሌ ዘመን እንደ ጋንቤላ ክልል፤ የህወሃት ሙሉ መፈንጫ የነበረው የሱማሌ ክልል አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የክልሉ መስተዳድር ፕሬዚዳንት ከሆኑበት ወቅት ጀምሮ የህወሃት የተደራጄ የቀውስ በቀል፤ የህወሃት ህልም አይሆኑ ሆኖ ከመከነበት ክልል ሐዋርያው የሆነው የሱማሌ ክልል ሲሆን። ሁለተኛው #ሲዳማ እራሱን ችሎ ክልል ከሆነበት ጊዜ ጀምሮም የህወሃት ተስፋ ወደ መቃብር ተልኳል።
 
አብሶ የሱማሌ ክልል የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ቅድስት ተዋህዶም አሳሯን ያዬበት ጊዜ ነበረ። ገና በሽግግሩ ወቅት መቀጣጫ የሆነችው ቅኒት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ነበረች የነደደችው፤ የከሰለችውም። ከህወሃት መንበር ለቀቃ በፊትም ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪወች ሰፊ የሆነ #የፖለቲካ መፈናቀል ደርሶባቸዋል። 
 
በአሁኑ ጊዜ የሱማሌ ክልል መሪ አካላት በወጣት ሊቃናት የተመራ በመሆኑ፤ የክልሉ ቲም ወርክም #ጤነኛ ነው። ህወሃት የአማራ ክልልን፤ ቤንሻንጉል ጉምዝን፤ ሌሎች ቦታወች ላይ የቀውስ መፈተኛ ማሳ የማድረግ አቅሟ በአይበገሬው የሱማሌ ክልል ብቁ፤ ንቁ ትንታግ አመራር መክሸፍ ችሏል።
 
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ 100% የተሳካላቸው ምደባ ይህ ነው። ይህን በጥዋቱም ጽፌበታለሁኝ። ታላቅ ስኬት ነው። የሱማሌ ክልል ከጎረቤት አገራት ጋርም ደንበረኛ በመሆኑ ብዙ አውሎችን፤ የወጀብ ቡፌወችን የተቋቋመ ጠንካራ ክልል ነው።
 
የህወሃት የታቀደ ቀውስ ድል በድል የሆነው #አማራ ክልል ላይ ነው። እርግጥ ነው የጠገዴ ወልቃይት የጠለምት የሰቲት ሁመራ ዞን እስከ አሁን አይደፈሬነቱን አጽንቶ ቀጥሏል። ያ በዓት የህወሃትን መንፈስ በአጽህኖት የሚጠየፍ በመሆኑ አላስጠጋም። በአማራ ክልል ብቸኛው የሰላም ቀጠና ይኽው ነው። ብዙ በጣም ብዙ የሴራ ድፍድፎች ሸውርረው፤ ሻግተው ተደፍተዋል። 
 
በሌላ በኩልም የሱማሌ ክልል በተረጋጋ ፍጹም ሰላም በመሆኑ ጊዜያችን፤ ጉልበታችን፤ መዋለ መንፈሳችን እረፍት የሰጠ ምስጉን ክልል ነው። የሲዳማ ክልልም እንዲሁ።
 
የፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ስልጣን ከያዙባት ዕለት ጀምሮ የቅድስት ተዋህዶ አገራዊ ስደት እና ዕንባ + የአማራ ህዝብ ሰቆቃ እና ግለትን ሰላማቸው ተጠብቆላቸዋል። ህወሃት ክልሉ ላይ የለመደውን ቀውስ ቢያቅድም ያልተሳካለት፤ የከሸፈ ፕሮጀክት የሆነው የሱማሌ ክልል መሪ እና ተመሪው ዓላማ እና ግቡን ያወቁ #ጥበበኞች በመሆናቸው ነው።
 
ስለሆነም እዛ የሚወለዱ ህፃናት፤ ነፍሰጡር ሴቶች፤ አዛውንታት፤ የአካል እክል ያለባቸው ህሙማን፤ የዕድሜ ባለጸጎች ሁሉ ስክን ያለ ሰላማዊ ኑሮ መኖራቸው ባለቸው ኢኮኖሚያዊ አቅም ልክ በሰላም እየኖሩ ነው።
 
ይህን ያዬው፤ የተመለከተው ካለ ህውከት መሽቶ የማይነጋለት፤ የቀውስ አባቱ #ህወሃት ይቁነጠነጣል፤ ለእሱ በገበሩ አንደበቶች የተስፋ ማጣቱን፤ የተስፋ መቁረጡን አታሞ ትራጀዲ ሰርቶ ሲተውንም ሰነባብቷል።
 
በወጣት ሊቃናት የተገነባው የሱማሌ ክልል ደግሞ አፍንጫህን ላስ ህወሃት፤ አንተ ልትመራን አንፈቅድም፤ ጭካኔህ አይናፍቀንም፤ አግላይነትህ ሽው አይለንም፤ ለልዩነት ትራጀዲህ #ሰለባ መሆን አንፈቅድም በማለት ልኩን በልኩ ልክ እንዲሆን በተግባር አስተምረውታል።
የሱማሌ ክልል ቢቀናባት አይደንቅም። ከሰላም በላይ ምን የሚያስቀና ግሎባል ክስተት አለና። ህሊና አስቦ፤ ያቀደውን መፈጸም የሚችለው እኮ ሰላም ሲኖር ነው።
 
በድህነት ለመኖር ሰላም ያስፈልጋል።
ለመሳቅ ሰላም ያስፈልጋል።
ከፈጣሪ ጋር ለመነጋገር ሰላም ያስፈልጋል።
ለመማር ሰላም ያስፈልጋል።
ለመጋባት፤ ለመዳር ለመኳል፤ ልጅ ወልዶ ለማሳደግ ሰላም እስትንፋስ ነው።
 
የሱማሌ ክልል ለህዝቡ የሰላምን ቃና በቅኔ #የመገበ የተሰጠው ክልል ነው። በዘመነ ህወሃት እንደ ሌላ አገር ህዝብ ተገሎ የኖረው በአብይዝም ዘመን የተሻለ የፖለቲካ ውክልና፤ ተደማጭነት እና ተቀባይነት አግኝቷል።
 
የኢትዮጵያ ምክትል #ጠቅላይ ሚኒስተርነት እና የብልጽግና ምክትል ፕሬዚዳንትነት በጣምራ ኃላፊነት፤ ገንዘብ ሚር በቋሚነት እና በቅርብነት፤ በፌድራል ደረጃ ተሰጥቶታል። ይህ በዘመነ ህወሃት በህልምም የማይገኝ አመክንዮ ነው። በ27 ዓመቱ የህወሃት አራጦ በገዛበት ዘመን ሱማሌ ክልል እንደ እዳሪ ልጅ ነበር የሚታዬው።
 
ስለሆነም ሁልጊዜ እኔ እንደምለው ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ ባለመኖሩ የሱማሌ ክልል ለዕድሉ ጥበቃ በተለየ ሁኔታ ቢያደርግ አይደንቅም። 
 
በአንድ ወቅትም የፌድሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሱማሌ ክልል ነበር። ይህ በዘመነ ህወሃት ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር። ዛሬ ግን በዘመነ አብይዝም የሱማሌ ክልል የመሪነት የዕድል በር ተከፍቶለታል። ከሁሉ ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊነት ተቋም የመጡት አቶ ሙስጠፌ የሱማሌ ክልል እናቶች #ዕንባ ያለአግባብ እንዳይፈስ አግዘውናል። ይህ ሁነት እኔ በእጅጉ የምመሰጥበት አንቱ ተግባር ነው። ሰዋዊነት፤ ተፈጥሯዊነት በመሪነት ደረጃ ሲገናኝ ይህን መሰል እርካታ ይሰጣል። 
 
የጎረቤት አገሮች ግንኙነት ሲያስፈልግም ሱማሌ ክልል አስተናጋጅ መናህሪያ ሆኗል እኩል ከአዲስ አበባ ጋር። በለውጡ ተጠቀመ ሊባል የሚችለው የሱማሌ ክልል ነው። አንድ የፌስቡክ ወዳጄ ሲያጫውተኝ ከሱማሌ ክልል እየመጣ ያለው የወጣት የአመራር አቅም የሚገርም ስለመሆኑ አጫውቶኛል።
 
በቅርቡ እንደሰማሁትም በክልሉ ቢሮወች አቅም ያላቸውን የክልሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን የሌላ ዞግ አባላትን የማሳተፍ ጅማሪ እንደ አለ አዳምጫለሁኝ። ድንቅ ብሎኛል። ህወሃት በቀበረው የመርዝ ፈንጅ ምክንያት ይህ ከአማራ ክልል በስተቀር ያልተለመደ ስለሆነ ደንቆኛል። ይበል የሚሰኝም ነው። ሙሉ 33 ዓመት የአማራ ልጅ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ አያውቅም። 
 
የሱማሌ ክልል አብነታዊ ጉዞ የህወሃት ማኒፌስቶ ህልም ወደ መቃብር ስለሚልክ ህወሃት #ቢወራጭ አይደንቅም። የፈለገውን የቀውስ፤ የጦርነት ሴራ ፈጥሮ ሱማሌ ክልል ላይ ህወሃት መራሽ የሰው ህይወት ሊጠፋ አልቻለም። ተቋማት አልወደሙም። ይህ ለህወሃት እና ህውሃትን ለሚያፈቅሩ ሁሉ የህሊና ካንሰር መሆኑ ልብ ልክ ነው።
 
ህወሃት ያለአንዳች ሃግ ባይ አማራ ክልል ላይ ሥልጣን ላይ በነበረው ጊዜ አቅም ልክ ፊት ተሰጥቶት የአማራ ሊቃናት አልቀዋል። የአብነት ትምህርት ቤቶች፤ ገዳማት፤ አገልጋዮች፤ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፤ ከተሞች ወድመዋል። ይህ ለህወሃት ትልቅ #የባዛር ድግሱ ነው። ይህ ግን በሱማሌ ክልል የማይሞከር ሆነ። ያዙን ልቀቁን የመጣበት አመክንዮ ይህ ነው። አማራ ክልልን የሚመራው የጨካኙ የህወሃት የነቀዘ መንፈስ ነው። እግዚኦ! ያሰኛል። 
 
ከሁሉም ከማዕከላዊ ጎንደር 80 ሺህ ነዋሪ ከተፈናቀሉበት ዕለት ጀምሮ የትምህርት ነገር በአማራ ክልል የዕውቀት የዕድል በር ተከርችሞበታል። ይህ ለህወሃት ከሞት የተነሳበት #ተንስዑ ያለበት ልዩ ስጦታው ነው።
 
ትምህርት ውጤቱ ዛሬ አይታይም። የዛሬ 15/20 ዓመት ነው የዛሬው ጨቀጨቅ የሚታዬው። የተማሩ የፖለቲካ ሊቃናት የአማራ ታጭደዋል፤ ተተኪያቸው ደግሞ እንዳይማር ሆኗል፤ ቁጥሩ እኮ ይሰቀጥጣል። ከ5 - 7 ሚሊዮን። የነገ ተስፋም #ክስል ብሎ አሯልም። ሱማሌ ክልል ላይ ይህን የመሰለ የደባ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ፤ የበቀል በትውልድ ዕጣ ፋንታ ጢባጢቦሽ መጫወት አልተቻለም።
 
ተወደደም ተጠላም ዛሬ ብቻ ሳይሆን የዛሬ 10/20 ዓመታት ውስጥ በተለያዬ የኃላፊነት ደረጃ ኢትዮጵያን የመምራት ዕድሉ ለሱማሌ ክልል #ብሩህ ዘመን ይሆናል። በትጋት እና በተከታታይነት እዬሰሩ ነው። ይህ ነው ህወሃትን የእንክርዳድ ጠላ እንደጠጣ ሰብ መላ ቅጥ ያሳጣው።
 
በጦርነት ውስጥ የአዝርት፤ የቤት እና የዱር እንሰሳት ስደትም ይኖራል። ስደቱ መነቀሉ የሰው ልጅ ብቻ እንደማለት። ይህ ለቀጣይ ትውልድ #ጠንቅ ነው። ሱማሌ ከዚህ ድኗል። ሱማሌ ክልል በሰብአዊነት ላይ ለምንተጋው ለእኔ መሰል ባተሌም ዋጋ ፈጽሞ ሊወጣለት የማይችል ስጦታ አበርክቶልናል። አይዟችሁ የአገሬ ልጆች ብሎም አጽናንቶናል። 
 
ስለሆነም ነው ዛሬ ከህሊናዬ፤ ከውስጤ የሱማሌ ክልልን መስተዳድር ላመሰግን የፈቀድኩት። ለሰው ልጅ የሰውን ልጅ ማህበራዊ ሰላም ከመጠበቅ፤ ከመስጠት በላይ ምን ልዩ የሆነ ዘመን ሰጥ ገጠመኝ ሊኖር ይችላል?
 
የተከበሩ የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ እና ቲሙን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። በእርሰወ ላይ ከመቅድሙ ጀምሮ ያለኝ መታመን ተፈጥሯዊ ነው። ይኑሩልን ለእኛም ለእናት ኢትዮጵያም። አሜን።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ ቤተ ቅንነት። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie.
30/03/026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።