ጥያቄው የብትን አፈር የነፍስ ጉዳይ ነው!

ኢትዮጵያ የቁጥር
ተማሪ አይደለችም።
ከሥርጉተ©ሥላሴ
05.09.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


እንደምን አላችሁልኝ የኔዎቹ? ደህና ናችሁ ወይ። በነገረ ጣይቱ ላይ ዛሬ ጥዋት እጅግ ከማከብረው ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት በላይ በግሉ ስለ ኢትዮጵያኒዝም የተጋ እና ያታገለ የአክቲቢስት አቶ መስፍን ፈይሳን ምልከታ አዳመጥኩኝ። ባለፈው ሳምንትም የርዕዮት ሚዲያን ምልከታ ተከታትያለሁኝ። 

የወዳጄን የመስፍኔን ከቅንነት ስለሆነም በትርጉም ባቃናው፤ ትንሽ ዘለግ አድርጌ እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት ምልከታየን በሚል ነው እንዲህ ማለት ፈልግሁኝ። 

እሱ ቅን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ በሃሳብ ልዩነቱ ልናዝንበት የሚገባ አይሆንም። ምንግዜም በአንደኛው ሃሳብ ባንግባባ በሌላው ደግሞ እንስማማለን ወይንም በድምጽ ተዕቅቦ እንለያለን። ይህ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ፈላጊው እውነት ነው። ግራው ዘመም መንፈስ ያደረበት ብቻ ነው ሞጋች ሃሳቦችን ወይንም ፈንጋጣ ሃሳቦችን የሚፈራው። ያው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አምላኩ ስለሆነ። 
  • ·       የሆድ የሆድን።  

ኢትዮጵያ የክት እና የዘወትር ልጅ የላትም። ኢትዮጵያ ስለ ልጆቿ ክፍልፋይ አሰናድታ አታውቅም። ኢትዮጵያ የቁጥር ተማሪ አይደለችም። ኢትዮጵያ ላይ ያለው ንጹህ አዬር ኦክስጅን አንተ / አንቺ የእኔ አይደለህም /ሽም ብሎ ገድቦ አይዋቅም፤ ለይቶም አያውቅም። አንድ ተራራ ላይ ያለው ነፋሻ አየር እኩል ነው ለሁሉ ፍቅሩን የሚያዳርሰው፤ ዝናቡም ሲመጣ እንዲሁም መቻቻልን በእግሩ አንዲሄድ ያደርገዋል፤ የኢትዮጵያ ጸሐይም ስትመጣ ለሁሉም ብርሃነኗን በሐሤት ትለግሳለች። ስታኮርፍም ስትስቅም እኩል ነው። 

ኢትዮጵያዊ ወቅታት ሲመጡ ጸደይ በጋ በልግ ክረምት ሲመጡም እንዲሁ ሁሉ ለሁሉ ተደራሽ ይሆናሉ - በፈግግታ። ወራትም ቀናትም  ሰዓታትም ደቂቃትም ሰኮንዳትም ሁሎችም ሲመጡም ሲሄዱም አኩል ተደራሽ ናቸው። እስረኛ የሚያደርጓቸው የዬዘመኑ ሥርዓቶች ናቸው። 

ለምሳሌ ካቴና ላይ ያለ እስረኛ ጸሐይ እንዳያገኝ ይገደባል። ዝናብን እንዳያይ ይደረጋል። እንደ አማራው የነፃት ታጋይ ልጅ እናዳይወልድ የዘር ፍሬው ይገደላል። አድዮን እንዳያይ ይደረጋል። ይህ ሥርዓታትን የሚመሩ የባለጊዜዎች እንጂ ኢትዮጵያ ወንጀለኛ ሆና አታውቅም። ኢትዮጵያ ያለው የተፈጥሮ ጸጋ ለሁሉ እኩል ነፃነት ነው የሚያድለው፤ ትእግስቱም የተሰጠው ነው።

የሰው ልጅ ኢትዮጵያዊው ሰው የራሱ የሆነ ነፍስ አለው። ነፍሱ የምትፈቅደው ማዕዶት አለው። ያቺ ነፍሱ የምትፈቅደው ማዕዶት የእድሜ ዘመኑ ማህለቁ ናት። የዕድሜ ዘመኑ ልጓሙ ወይንም መሪው ናት። አሁን ባለው የተስፋ አገር ዜማ ወደ አገር ከገቡት ለጥበብ ዘርፍ እናቱ አርቲስት ወ/ሮ አለምጸሐይ ወዳጆ ናት። 

መቼም እሷን የሚተካ ባለሙያ ኢትዮጵያ አለችኝ አትልም። እራሷ ኢትዮጵያ ናት ብላት እችላለሁኝ። እኔ እዚህ መጥታ በነበረበት ጊዜ የዛሬ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ላገኘት ሄጄ ነበር። በዘመኑ ጉልበተኞች ሳላገኝት ነው የተመለስኩት። 

አንድ የግጥም መጸሐፌ ላይ ስለ እሷ የተገጠመ ስለነበር ይዤላት ነበር የሄድኩት፤ አንድም ፈቃዷን የሚመለከት አንድ ብልሃትም ይዤ ነበር። ነገር ግን ያው ሲዊዝ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለቲያትርም ግዞተኛ ስለሆነ ሳላገኛት መጸሐፉንም እንደ ተለመደው ይዤው ተመለስኩኝ። ያጠፋሁት በርሊን መሄድ ስችል ያን አለማድርጌ ነበር። 

የሆነ ሆኖ የአለምዬ የነፍስ አጀንዳ አንድ ነው። የጥቁር ሴቶችን ታሪክ ያበለጸገችውን የእቴጌ ጣይቱን ሌጋሲ ማስቀጠል። ነፍሷ የተፈጠረው ለዚህ ነው። እናታችን ቅድስ ክርስቶስ ሰምራ በዲያቢሎስ ስህተት ምክንያት ለሚያጠፉት ሰዎች ጥብቅና እንደ ቆመችው ለዛም እንደ ተፈጠረችው ሁሉ ለእሷም ይኸው ነው አጀንዳዋ።

ወደ አገር የመግባቷ ሚስጢርም ይህው ነው። ከዘብርሃናተ ኢትዮጵያ ከእቴጌ ጣይቱ ውጪ አለምዬ ህይወት የላትም። ህይወቷ ይህው ነው። ነፍሷ ይህችው ናት ጣይቱ፤ ትንፋሿ ጣይቱ ናት ራዕዮዋ ጣይቱ ናት በቃ …. ጻድቅ እናት ሙተርትሬዛ ለደግነት ተጋድሎ የተፈጠሩ ቅዱስ ነበሩ። ማዲባ ለምህረት ተጋድሎ የተፈጠሩ ነበሩ። ዶር አንጌላ ሜርክል ለመቻቻል ተጋድሎ የተፈጠሩ ናቸው፤ ኪንግ ማርቲን ሉተር ለቀለም እኩልነት ተጋድሎ የተፈጠሩ ነበሩ። ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ለኢትዮ አፍሪካኒዝም ቅኔ የተፈጠረ ነበር። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለኢትዮ - አፍርካኒዝም አግር ኳስ የተፈጠሩ ነበሩ። 

አሁን ፕ/ ማሞ ሙጬ ለኢትዮ አፍርካኒዝም ለአድዋ ድል የተፈጠሩ ናቸው። እኔም የሎሬቱን ሌጋሲ ማስቀጠል፤ የድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ ሴቶችን ዕንባ እንዲቆም መትጋት ነው … አገር ብሄድ እምታገልላቸው በኽረ አጀንዳዎች እነዚህ ናቸው። ሦስተኛ ልከል ብል የልጆችን ሰብዕና በፍቅራዊነት መርህ በመገንባት እረገድ ለናሙና ሥራ እጀምራለሁኝ ብዬ አስባለሁኝ።  

አለምዬ ኢትዮጵያ ስትሄድ ነፍሷን ይዛ ነው የሄደችው። የአለምዬ ነፍስ ደግሞ ጣይቱ ናት። በማይቻልበት የስደት ኑሮ ጥበብን በሁለት እግሩ አቁማ እንዲሄድ ያደረገች አስምህሮተ ጥበብ ናት። አሁን ኢትዮጵያ መሪ አገኘች። መሪዋ የምህረት እና የይቅርታ ተምሳሌት ናቸው ዶር አብይ አህመድ። ተምሳሌቱን በተግባር መፈትን የሚቻለው እንዲህ ዓይነት ፈተናዎችን ማለፍ ሲቻል ነው። እርዱን ሲባል እንዲህ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መድረክ የመክፈት አቅም ሲኖር ብቻ ነው። 

ለጥያቄ ወቅት አያስፈልገውም። ለመልሱ ነው ወቅት የሚያስፍልገው። በምህረት የገቡት እኮ ከነትጥቃቸው ገብተው በአሰቃቂ ሁኔታ ወገኖቻችን ገድለዋል ወለጋ አካባቢ፤ ወገኖቻችን አሰቀይተዋል። በይቅርታ የገቡትም አፋቸውን ሞልተው አንደበታቸውን አብራርተው ብንፍልግ ዛሬም ማፈረስ እንችላልን እያሉ ነው። እና የዓለም ሴቶች የኮፐንሀገን የድል ጮራ የሆነችውን የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት ማቆም ጥያቄ ማቅረብ የቱ ላይ ነው ስህተቱ?! 

ይገባኛል የአክቲቢስት መስፍን ፈይሳ ስጋት። ህሊናዊ ተግባር ቀድሞ ይሠራ ነው።  የኤርትራና የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት አሁን በተሄደበት መንገድ ባይኬድ ኖሮ የዛሬ 50 ዓመትም አይፈታም ነበር። ዛሬ የመጀመሪያዊቷ ኢትዮጵያዊቷ መርከብ ምጽዋ ወደብ ተነስታ ወደ ቻይና ትጓዛለች። ጠ/ ሚር አብይም አህመድም ከደልዳላዋ እምቤት ከወ/ሮ ዝናሽ ታዬቸው ጋር አሰብም ምጽዋንም ጉብኝት ላይ እንደሆኑ አሁን አዳምጫለሁኝ። 

ይህ ማለት የአልጀርሱ ስምምነት አፈጻጻም ላይ ደንበር ላይ እንቸክል ቢባል፤  አዕምሮ አጠባ እንሂድ ቢባል እናውቀዋለን ያው ኔገቲቡ ዘልቆ አዎንታዊው አፈርድሜ እንደሚግጥ። 

ገና ከጅምሩ ስንት ውርክብ እንደተነሳ ታስታውሳላችሁ። የባድመ ዕድምታ በሥርጉተ ዕይታ የተጋተውም በዚኸው መንገድ ነው። አጀንዳ ያለቀባቸው ሰዎች ሁልጊዜም አጀንዳ ይሻሉ። ነገር ግን ከክፈታው ተጀመረ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ተደረስ። ልክ እንደዚህ ነው የነገረ ጣይቱ ጉዳይም። "ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው" ላስገኘው ነፃነት የእቴጌ ጣይቱ መንፈስ ስለምን ካቴና ውስጥ ይከዘን?

ሌላም አንድ ምሳሌ ላንስ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ዞጋዊ ዕሳቤ ተው፤ በቀይ ምንጣፍ አንድነትን ተቀላቀሉ ተብሎ ጉሮ ወሻባይ ሲባል ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ህዝብ ይዞ ወጣ ብለው ህገ መንግሥቱ ተናድ ነው የሚሉት። ነፃነት ላሳቸው፤ ዴሞክራሲ ለሳቸው ምን ማለት እንደሆነ በዚህ ዕድሚያቸው እንኳን ሊያሳዩን አልቻሉም። እሳቸውን እራሱ ከእስር ነፃ ያወጣው የብአዴን 45 ድምጽ ነው። ወደፊትም በአሁኑ አያያዝ ከሆነ ጋዳ ይሆናል።  

የጎንደር የአማራ ማንነት አብዮት ነው የድሉ ገፊ ሃይል። በዚህ ዘመን እነሱ ከሸጎሪያቸው ሊወጡ አይፈቅዱም። ይህ ከሊቅ አስከ ደቂቅ የሚታመሱበት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ምንም የማስተማር ፕሮጀክት አያስፈልም፤ ልክ እንደ ኤርትራው እና ኢትዮጵያው ግንኙነት ሥራ ላይ መግባት ነው በቃ። እውን ኢህዴግ ኢትዮጵያኒዝም መርሄ ነው ካለ፤ ከቆረጠ፤ ከወሰነ። ጡጦ የሚጠባ ልጅ የለም … የተሟገትንለትን ያህል ሆኖ መገኘት ግድ ይላልዋል። ስንት ፈተና ነው እኔ ራሴ የገጠመኝ "ለማዋያን" ነኝ በማለቴ እና ገና ከመቅድሙ በመደገፌ። አሁን ያለው ድጋፍ እኮ ከመቼ ጀምሮ ቢባል ጉግል ይጎለጉለዋል። 

ጥበቢት ወ/ሮ አለምጸሐይ ወዳጆ ነገረ ጣይቱ ለእሷ ነፍሷ ነው። አጀንዳዋን አቅርባለች ፈተናውን ማለፍ አለማለፍ ደግሞ „ የኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ጉዳይ ነው። እንግዲህ "ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው" ለቧልት ካልሆነ። ስንቱ ጥያቄ ይሸሽ? የዚህ አብዮት ገድሉ የሚዘከረው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው። ስለተፈለገ ብቻ ሳይሆን ምዕራብውያኑ የመፍትሄ አንኳር አድርገው ለኢህዴግ አስረግጠው የነገሩት ብልሃት ያለው ከዚህ ሚስጢር ላይ ነው።

ለዚህ ነው የነፍጠኛ ሲል የነበረው ህብረ ብሄር ፓርቲ ሁሉ አሁን ሠራዊቱን ተከታዩን ያን የነፍጠኛ ያለውን ብሄራዊ ሰንደቅዓላማ፤ እና ክልል የሙጥኝ ያለው። ሰንደቁንም ደጋፊው ይዞ እንዲወጣ የሚደረገውም በዚህው ስሌት ነው።  

ህብረ ብሄር የሚባለው ከጎንደር አብዮት በፊት እንተዋቀቃለን፤ ይህ እንደ አንድ የትግል ስልት የተያዘው በዚህ እንጂ ትርፍ ስለተገኘበት እንጂ በዬአደባባዩ ተይዞ ሲዞር የነበረው እድሜ ለዘመነ ግሎባል ሁሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው። ስለዚህም ይህ አጀንዳ አትራፊ ከሆነ እና ለሥልጣን ካበቃው ኦህዴድን ኢትዮጵያዊነትን ላቆዬች ንግስት ልዕልት ብትን አፈር እንዴት ትነፈጋለች? አሁን አኮ የብትን አፈር ነው ጥያቄው? 

ምህረት ይቅርታ ፍቅር ሲባል እኮ ውጪ አገር አጽማቸው ያረፉት ወገኖቻችን ሁሉ አጽማቸው ፈልሶ ወደ ርስት አገራቸው መመለስንም ይጠይቃል። እንዲያውም በስሚ ስሚ እንደ ሰማሁት ጠ/ ሚር ዶር አብይ አህመድ የሊቢያን ሰማዕታት የማምጣት ዓላማ እንዳለቸው ሁሉ አዳምጫለሁኝ። ሐውልትም እንዲሁ እንደታሰበ ዜና ተከታትያለሁኝ። እና ለእቴጋችንስ? 

በ2006 እ.ኢ.አ እኔ የለንደኑ ይሁን የአትላንታው ጉባኤ የኦሮሞ ወገኖቻችን ሲያካሂዱ፤ የስያትሉ የአማራ ወገኖቻችን ጉባኤ ሲካሄድ ዛሬ እንዲህ ለማ አብይ  ሊያንቆለባብሱት„በባዶ ሜዳ“ ብለው ፕ/ መስፍን ወልደማርያም ሲጽፉ እኒያን ታላቅ የአገር አድባር ተዳፍሬ አምቄ ያቆዬሁት ቁስለቴን ነገር ሁሉ ዘርግፌ ፊት ለፊት የሞገትኩት ሃሳቦች መውጣት የትውልድ አድን መዳህኒት በመሆኑም ጭምር ነው። 

አሁን ብዙ ሰው የዲሲው እና የሎሳንጅለሱ ይበቃ ነበር ይላሉ። ኖ! እንኳንም ሚኒያ ላይም ተካሄደ። የሰው ልጅ አዬር ያስፈልገዋል። የሚሳማውን ስሜቱ ካልታወቀ መዳህኒት አይገኝለትምና። እኛንም ሚዛናው ያደርገናል። 

የታፈነ ነገር ነው አደጋ የሚያስከትለው እንጂ የወጣ ነገር፤ የተነገረ ነገር፤ የተወያዬንበት ነገር፤ መፍትሄ ቢያመነጭ እንጂ ችግር ሊገጥም አይችልም። ቢያንስ የችግር አያያዝ ቅደም ተከተል ስልት ለመንደፍ ይቻላል። ህሊናም ይሳናዳል። ከሁሉ በላይ አቅም እንዳይባክን ያደርጋል። አሁን እኔ መርጬ ነው የማዳምጠው። 

አንድ ጊዜ ካወቅኩት በኋዋላ ስለምን ሌላ ጊዜ አቃጥላለሁኝ። ሳውቀው ግን ላድንቀው ወይንም ላገለው እችላለሁኝ። ከተናገረው፤ ከተነፈሰው በኋዋላ ግን የራሴን አቋም እዬዛለሁኝ። እስከ ተወሰነ ደረጃ የተደገፈ ሃሳብም ቢሆን እዬተደመጠ ሲሄድ እዬጠራ ይሄዳል ወይ ለአይ ወይ ደግሞ ለይሆናል ይወሰንለታል። ለዚህ ነው እኔ ለመጠዬቅ ቀነ ቀጠሮ ሊያዝለት አይገባም የምለው። የሆደ የሆድን መጫወት ይገባል። መዳን ከፈለግን። 

ስለሆነም መስፍኔ ከሰማህኝ ነፍሷ እቴጌ ጣይቱ ለሆነች አንዲት የጥብብ ሊሂቅ አገር የምትገባበት ሌላ አጀንዳ የላትም። አሁን OBN አገር የገባባት ጉዳይ አለው። ይህን ጉዳዩን አሁን እያስፈጸመ ነው። መሬት ላይ የሚሠሩ ነገሮች ሁሉ እዬታዩ ነው። ትልቁ ፕሮጀክቱ ኦህዴድን በጥርጣሬ እንድናዬው ነበር፤ ተሳክቶለታል። እነሱም ከብልህነታቸው ርቀው በመገኘታቸው መንፈሳችን እንዲሰረቅ በር ከፍተዋል።  

ጃዋርውያን የኦህዴድን መንፈስ መሻማት ነበር ተሳክቶለታ። የኦህዴድን ምስል አባለሹበት። የጃዋርያን መንፈስ አፍታ አልቆዬም ይህን ሲያደርግ። አሁን ደግሞ ጦርነት ባሰነሳው የም/ ከንቲባው የአቶ ታከለ ኡማ ጉዳይ ነበር የተሰነባባተው፤ ተተኪው ደግሞ በነገረ ጣይቱ ጉዳይም ሌላ ጦርነት ከፍቷል ቡድኑ። 

ይህ ማለት እነሱ ሲሰሩት መልካምነት እና ወቅቱን የጠበቀ ሌላለው ሲሰራው ደግሞ ወቅቱ ያልጠበቀ ሊሆን አይገባም። ነፍስ ተደብድቦ፤ ተገድሎ፤ ተስቅሎ ሲጨፈር አጀንዳ አይደለም፤ አዋራ ዜና አይደለም። ብቻ ብዙ ፈተኝ ነገሮች ተቆልለዋል ለኢዲሱ ለውጥ መንፈሰ፤ ጃዋርውያን ብቻ ሳይሆን መንፈሰ - ኢንተሪገርን ሁሉ እንዴት እንደሚያዝ ሚዛናዊ ሆኖ በማስተዋል ማዬት  ያስፈልጋል። በሌላ በኩል በዬለቱ በመከፋት ከማዕቀፉ የሚወጡ፤ የሚለዩ መንፈሶችም ይኖራሉ። አሁን ባለው ሙቀት ገቢ እንጂ ወጪ አያስፈልግም ነበር ግን አያያዙ እያሰጋኝ ነው ... 

የሆነ ሆኖ እነሱ እንዳሻቸው በሚፈንጩበት ኢትዮጵያ ሌላውም ሊከለከል አይገባም። ኢትዮጵያ እንሱ አገራችን ብለዋት አያውቁም። ወደፊትም አይሏትም። "ሚስጢር" ስትባል እንዴት እንሚያንደፈድፋቸው እንተዋወቃለን። የሆነ ሆኖ አሁን የተገኘው ድል ደግሞ አጀንዳው ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ብቻ መሆኑን አሳምረው ያውቃሉ። ሚሊዮኖች ኦነጋውያንን ወይንም ጃዋርውያን ደግፈው አይደለም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት። የለማ አብይን ኢትዮጵያዊ መንፈስ እንጂ ...  

ይህ መንፈስ ነው አገር ገብተው እንዲያነኩሩ፤ እንዲበጠብጡ ሰው በአደባባይ አሰቅለው እንዲጨፍሩ ያደረጋቸው። መንግሥት የለም እስኪአሰኝ ድረስ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ዓርማ አዲስአባባ ላይ ያ ሁሉ የኢንባሲ ጽ/ ቤት፤ ያ ሁሉ የአፍሪካ ህብረት መንፈስ፤ ያ ሁሉ የዓለም ነፍስ ባለበት አገር የአሸንፈናል ዓርማቸውን በልበሙሉነት ንግግር ነበር ያወጁት። ስለዚህም ሁሉ ሰው አሁን በኦህዴድ ላይ  በተእዕቅቦ ሂደቱን ጥሞና ላይ ነው እዬተከታተለው ያለው።

መታመን በስፋት ርቆታል ኦህዴድን … ኦህዴድ አገራዊ ሃላፊነት የመወጣት ብቃት አለው የተባለለትን ያህል አሁን ሙቀቱ ወርዷል። የፈለገ በፈለገ ሁኔታ ኦህዴድ የታማኝነት ደረጃውን መልሶ ለማግኘት በምን ሁኔታ እንደሚችል ራሱን ይጠይቅ። "የቸኮለ አፍሶ ለቀመ ነው" የሚሆንበት። አይደለም በኢትዮጵውያን በምዕራብውያን ዘንድም። እውነቱን ነው የምናገረው እኔ።

ያለው መንፈስ በዶር ለማ መገርሳ እና በዶር አብይ አህመድ ብቻ እምነት ማሳደር ነው እሱም ቢሆን በነገረ አማራነት ጉዳይ ሌላ እምቅ አመክንዮ አለበት። በሌላ በኩል የኖረው የሴረኛች አብሾ ደግሞ  ሌላውን ስልት ነድፎ ይሆናል። ከእነገመናው ነውና "በመደመር ፓሊሲ" የከተመው። 

ስለሆነም አብሶ ሁለቱም አንድነታቸውን በታማኝነት አጽንተው ፈተናቸውን መቋቋም እስከቻሉ ድረስ ነው የለውጡ ቀጣይነት ተስፋ። ምክንያቱም የሁለቱ ጥምረት የኢትዮጵያዊነት አብራክ ስለሆነ ጸላዬ ሰናይ አይተኛም። ለዚህ ማንም አይርፍም። ከሊቅ አስከ ደቂቅ ለአፍራሽነት የሚተጋበት ነው የሚሆነው።

ይህን በፖለቲካ ዓለም ለቆዬነው ሴራ እና ሸር እንዴት ትውልዱን እያመሰ እንደ ኖረ በመደበኛ ሥራችን ላልነው ሰዎች አይጠፋነም። እከሌ አለኝ ብለው ሊያምኑት የሚችሉት ቅን ሊሂቅ አያገኙም ሁለቱም ራሳቸውን ገርተው አንድነታቸውን ማጠናከር እስክልቻሉ ድረስ በድርጅታቸው ውስጥ። 

ይህን ስል ልክ በመርፌ ቀዳዳ ግመል እንደምታልፍ ያህል እርግጠኛ ሆኜ ነው። ምክንያቱም አልተለመደም ሳያጠቃ ሥልጣኑን ለመሳቀጠል አስቦ የሚያውቅ ሊሂቅ …. ለዚህ እኮ ነው ወንጀለኞች አሁን አደባባይ ወጥተው፤ ሚዲያውን ሁሉ የተቆጣጠሩት እነ ሳጅን በረከት ስምዖን ወንጀላቸውን ተሸከምን ኑሩ መበላቸውን እንኳን አልተቀበሉትም፤ የትግራይ መሳፍንትም እንዲሁ …

የሆነ ሆኖ የጥብብ እናት አርቲስት ወ/ሮ አለመጸሐይ ወዳጆ የሄደችበትን ጥያቄ አቅርባለች፤ አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ከሆነች፤ የአብይ ካቢኔም ኢትዮጵያዊ ከሆን ይለካባታል ይፈተንበታል። 

ለዚህ እንዲያውም ቀዳሚው አስፈጻሚው ኦህዴድ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁኝ። ባለፉት ሰሞናት ከኦህዴድ የማልጠብቃቸው ቁስሎች እኔ በግሌ ስለገጠመኝ ይህን ቢያደርግ ሚዝናኑን በተወሰነ ደረጃ ይጠብቅልኛል። የአማራ ተጋድሎ መሰረታዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን አሁን ግፍን በግፍ እየዛቁ ያሉት የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የቆቦ እና የራያ የአማራ ወጣቶች መከራም አለ። ባሊህ ባይ ያጡ እና እንደ ትርፍ ዜጋ የታዩት። 

አዲስዬ።

አዲስ አባባ አጥብቦ ከልሎ ወስኖ ማዬትም የአስተሳስብ ድህነት ነው - ለእኔ። አገራችን አፍሪካን እንድትመራ የተፈቀደላት የሰው ልጅ መፈጠሪያ ስለመሆኗ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው ማንነት ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት ነፃ አገር መሆኗ ነው። 

ይህቺ አገር እንደ አንድ የትምህርት ሳብጀክት አፍሪካውያን ሊማሯት የሚገባ ሆና ሳለች መዲናዋ ተከልሎ ተገድቦ ድንበር ተሰርቶለት የኦሮሞ ብቻ ናት መባል ምን ያህል ደረጃውን የጠበቀ አምክንዮ ስለመሆኑ አባ ዝምታ ይመልሰው፤ አዲስ አባባ የአፍሪካ መዲና ናት።

ኢትዮጵያ ከዚህም ባለፈ የመካከለኛው ምስራቅም ማዕከል ናት፤ ከዚህም ባለፈ የዓለም የፖለቲካ መንፈስ ማዕከል ናት። ይህ ደግሞ ቢያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም። የኒኮ ሐውልት ያቆመች አገር ስለምን የእቴጌ ጣይቱ ለማቆም ይቸግራታል? አገር የሚባለውን ያቆዬው እኮ የእቴጌይቱም የተጋድሎ ጥበብም ጭርም ነው።

በሴቶች የፖለቲካ ዘመን ለእኔ የተሻለ ዘመን ላይ ያለን ይመስለኛል በአብይ ሌጋሲ። በአስተሳሰብ ደረጃ ብዙ ሥራ ቢጠብቀንም። ልክ እንደ አርንጀንቲናዋ ኢቫ ፔሮ/ ኢቢታ ያለች ሴት እስክትፈጠር ድረስ ማለቴ ነው። የሆነ ሆኖ ይህ ሐውልት የጥቁር አፍሪካ ሴቶችን የፖለቲካ አቅም ማመሳከሪያ ሰነዳችን ነው።  

ሴቶች እኩል ዜጋ ከሆን ሌላው መፈተኛ አሁን ነው። እውን ኦህዴድ ሴት ወጣቶችን ለፖለቲካ ስልጣን ሲያበቃ እንዳልሰሰተው ሁሉ በዚህም ላይ ቁልጭ ያለውን ግልጽ አቋሙን ማዬት እሻለሁኝ እኔ። እውን የኦህዴድ የፖለቲካ ሊሂቃን ኢትዮጵያዊነትንም ከፈቀዱት - በድንግልና ከሆነ።  

እኔ እንዲያውም በነገሥታት ታሪክ ሆነ ስለ አዲስ አባባም ጉዳይ በዝምታ ውስጥ ነው የምኖረው ማለት እችላለሁኝ። ጥልቅ ጥልቅ ማለት አልወድም። ዛሬም የግድ ሆኖ ነው መስፍኔ ወቅቱን ያልጠበቀ ስላለው ነው። 

የሌላው ህብረ ብሄር ነን የሚሉት የውጭ አገር የፖለቲካ ድርጅት ዳንኪራ አዲስ አባባን በመሚለከት ያለው አቋም ከኦነግ የተለዬ ስላልሆነ ዘመን ጥሩ ነው እንዲህ እያበጠረ እና እያንተረተረ እያንገዋለለ ያሳዬል ሃቁን። ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያና በሱዳን ደንበርም መሰሉ ወለም ዘለም የተለመደ ነው። 

በሌላ በኩል ግን ይሁንም አይሆነም ሊጠበቅ የሚገባው መልሱን ነው፤ መጠዬቁ ግን የተገባ ነው፤ አለምዬን የሚያስወቅስ አንዳችም ጉዳይ የለም። ሌት እና ቀን አድርግ፤ አታድርግ ስለተባለ ሳይሆን በዛ በጨለማ ዘመን የጎንደር አብዮት ሲፈነዳ ሙሉውን  የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ከእነ አርማው ይዞ ነው የወጣው።  

የቴዲ የባህርዳር ኮንሰርትም እንዲሁ፤ ዓውደ ዓመትም እንዲሁ ዛሬ ባባህርዳር እስተዲዮም ስለ ኢትዮጵያዊነት ቅስቀሳ ይደመጣል። ጊዜ ማቃጠል እና ሥራ ፈትነት ነው - ለእኔ። ይህን አጀንዳ ይዞ ወደ አደማ ብቅ ማለት ነው። ወደ አሶሳ ብቅ ማለት ነው። ወደ መቀሌ ብቅ ማለት … 

አደርኩኝ አልኩኝ ለማለት ሳይሆን ለአማራ ኢትዮጵያዊነት አስተማርኩኝ ማለት አይቻልም። መምህሩ እራሱ የአማራ ህዝብ ስለሆነ፤ የአፋር ህዝብ ስለሆነ፤ የደቡብ ህዝብ ስለሆነ፤ የጉራጌ ህዝብ ስለሆነ፤ የቦንጋ ህዝብ ስለሆነ ወዘተ …

የማክብርህ መስፍኔ ሆይ! ጃዋርውያን እቴጌ ጣይቱ ድርሳን ሳታደርስ ተግባር አህዱ እንደማትል ጠንቅቀው ያውቃሉ። እቴጌይቱ የድንግልዬም ብርቱ ወዳጅ ነበረች። መበጥበጡም አንዱ ይህው ነው። ሚደያውም ሥራው ይህው ነው። ኢትዮጵያ የሁሉም እንጂ የጃዋርውያን ብቻ አይደለችም። 

የሁሉ ከሆነች ደግሞ የሁሉንም ጥያቄ እኩል ማስተናገድ ይገባል። አሁን በተጠባባቂነት ያሉት ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን የነፍስ ሥጋና ደም ናቸው። ማፈንገጣቸውም ሆነ አለማፍንገጣቸው ካዛ ከታቦተ ሎሬቱ መንፈስ ፈተናው ትልቁ ጋራም ይኼው ነው። አጥንቶ ማለፍ ወይንም ሳያጠኑ መውደቅ።

በሌላ በኩል ርዕዮት ሚዲያም የተወያዬበት ምርኩዙ ከሥር አለ። የመስፍኔ በቅድሚያ እናስተምር ነው የሚለው እንደዛማ ቢሆን "ጣና ኬኛን" ሆ! ብለን ባልተቀበልን። ስለምን? አይደለም ትናት ዛሬ ያለውን የነገረ አማራን ተስፋዊ ትዕይንትም ስለምናስተውል። አዎን እሺ ይሁን ብለን በቅንነት የሞገትንለት መርሃዊ ጉዞ አሁንም፤ ነገም ከነገ ወዲያም እንደ ወርቅ ተፈትኖ ማለፍ ወይንም መውደቅ ነው።  

ይህ እርምጃ የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ገድል የመላ እቴጌዎች አቅም መግለጫ፤ የመላ ልዕልታውያን ክህሎት ማዘከሪያ፤ የመላ ጥቁር ህዝብ ድንቅ ማስታወሻ ነው። ሃሳቡ ቅዱስ ነው መንፈሱም ቅዱስ። የኢትዮጵያ ሴቶች በዘመናት ተጋድሎ ውስጥ አልነበርንም? አሁንስ ተጋድሎ እያደረግን አይደለንም?! ግን ስለኛ አንዲት ማስታወሻ በ3000 ሺህ ዘመን መሥራት ብርቅነቱ ከምኑ ላይ ነው?

ብቻ ሁለቱም በቅንነት ነው ጉዳዩን የተመለከቱት። የአክቲቢስት መስፍኔ ፈይሳ ስጋቱ ይገባኛል። ነገር ግን ሁሉ ነገር ተፈርቶ አይቻልም። አሁን እኔ የአኖሌ ሐውልት ይፍረስ /አይፍረስ በሚለው ሙግት አጀንዳዬ ሆኖ አያውቅም፤ መፍረስ ያለበት የአማራ ጥላቻ ህሊናዊ ሐውልት ነው።  መፍረስ ያለበት አማራን በመንፈስ የማግለል ሐውልት ነው። እሱን ደግሞ ልብ ያለን ሰዎች እያስተዋልን ነው።

የሆነ ሆኖ  የወልቃይት የጠገዴ የራያ የመተከል ጉዳይ ተፈርቶ፤ የአማራ የህልውና ታገድሎ መገለል ተፈርቶ ስንቱ ተፈርቶ ይዘለቃል። ትግል አይቆምም ድልም ሂደት ነው። ሥርዓትን እስከ ጠበቀ ድረስ፤ አዎንታዊ እስከሆነ ድረስ፤ ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ ጥያቄዎችን መፍራት የተገባ አይደለም። ድጋፉ እኮ ጥያቄዎች ዕውቅና ያገኛሉ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ተብሎ ነው ለተሻለ ዘመን። 

ለውጥ ማለት ለውጡ ያመጣውን መንፈስ አስኳል እዬረሱ ከሆነ ለማግስትም ከባድ ይሆናል። እኔ እንደ ሌላው አይደለሁም። በቅንነት ነገሮችን እቀበላለሁኝ። በእዮባዊነትም ብዙ ነገሮችን እከታተላለሁኝ። ለዛ ቅንነት ፊት ለፊት ወጥቼ እሟገታለሁኝ፤ ከተሟገትኩለት በኋዋላ ደግሞ በጥንቃቄ እከታተለዋለሁኝ። አሁን አማራ መሬት ላይ ያለውን ጫና ጥልቅ የፖለቲካ ፍልስፍና ያለበት ነው። በዝም ብሎ፤ በመደዴ የሚታይ አይደለም። በጣም ለዘለቁ ዓመታት ያሉ የተከደኑ የሃሳብ ፍሰቶች አሉበት። 

ምክንያቱም ለውጡ እንዲቀጥል ከተፈለገ ሚዛናዊ የሆኑ አምክንዮች በዬክልሉ መከወን አለበት። ህብረ ብሄር ነኝ የሚል ፓርቲ ትጥቅ የፈታውን ሠራዊቱን ማስቀመጥ ያለበት አገራዊ መናህሪያው አዲስ አባባ ላይ እንጂ አማራ መሬት ላይ መሆን የለበትም። 
ይህ ሎጅክ ነው። 

የአማራ ሠራዊት መቼም የግንቦት 7 ሊሆን አይችልም። ይህን መሰሉ የፖለቲካ ቁማር ወይንም ቁሞቀር ፍልስፍና ነገ ምን ዳመና ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ያስፍልጋል። ገርጭራጫ አዬር ከተፈጠረ ደግሞ አሁን ካቴና የሚጠብቀው ያው ክልል ነው የሚሆነው። ለዚህ ህዝብ ርህርህናው ትኩረቱ ወገናዊነቱ ዕውቅና መስጠቱ 

ይህ ምልክት ይመልሰው ?!።

·       ኔዎቹ ምርኩዞቹ ሊንኮቼ እኒህ ናቸው።

Ethiopian politics - ለአለምፀሀይ ወዳጆ የጣይቱ ሀውልት ከመገንባቱ በፊት ትምህርት ይቅደም

Ethiopia:የእቴጌ ጣይቱ ሀዉልት ጉዳይ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔረተኝነት በሚል ርዕስ የዜና መጽሔት ውይይት


ሴቶች የነፍስ ጥበቦች ናቸው!
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
የኔዎቹ ክብረቶቼ ውዶቼ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።