ይድረስ ለEthiopian National Dialogue Commission/የኢትዮጵያ ... EthioNDC ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን/ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ይድረስ ለEthiopian National Dialogue Commission/የኢትዮጵያ ...
EthioNDC ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን/
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።
የተከበርከው ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን ሆይ!
#ዕፍታ።
ዘለግ ያለ አቤቱታም፤ ሙግት ነክ ጉዳይ ነው። የማክበር ሰላምታዬን በቅንነት አቀርባለሁኝ። እንዴት ናችሁ? ዬተነሳችሁበት የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ፕሮጀክት ይሳካላችሁ ዘንድ ምኞቴ ነው። ዕውነት እና ፋክት ሸንጋይ ዬሚሹ ባይሆንም፤ ዕውነት እና ፋክት አጃቢ ሠራዊት የለላቸው ቢሆኑም ዕውነት አለን፤ ፋክት አለን ለዛም እንተጋለን ማለት መብት ነውና፦ ይህን ተቀብሎ ግን ሊሳኩ የማይችሉ ሎጅኮችን አቅርቦ መሞገት ደግሞ አስፈላጊ እና መሠረታዊ ጉዳይ ይሆናል።
በወፍ በረር እማዳምጣቸው ጉዳዮች አሉ። የአማራን ችግር በተለይ አሁን ያለውን የሞት የሽረት የፋኖ ዕፁብ ድንቅ ተጋድሎ እንዳኛለን፤ እናስማማለን ብላችሁ መነሳታችሁን አዳምጣለሁ። ለመሆኑ ልትታገሉበት ከተሰናዳው ሰነድ አንቀጽ ውስጥ "ፋኖ" የሚል ኃይለ ቃል አለን? የዚህን መልስ መስጠት ስትችሉ፤ እራሱ መልሱ የስኬታችሁ ወቄት መሆን ይችላል።
ብዙ ተቋማት የሚወድቁት መሠረታዊ ምክንያት በማኒፌስቷቸው የፖለቲካ ድርጅት ከሆኑ፤ ማህበራት ከሆኑም አታጋይ ሰነዶቻቸው ላይ የሌሉ አቅም እና ጉልበት ሲመጣ ዘለው እንዋኝ ሲሉ አላዋቂ ሳሚ ይሆኑና ሰብዕናቸውም ተቋማቸውም አብሮ ይተናል። የትኛውም ተቋም፤ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት #ከሞረሽ በስተቀር አማራ የሚል ኃይለ ቃል በሌለበት የሐምሌ 5ቱ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ አብዮት በጎንደር ከተማ ፈነዳ፤ ቅኔው ጎጃም ሳያወላውል በአድዮ ዋዜማ ፈቅዶ እና ወዶ ተዋህደው። ተቀላቀለው አላልኩም። #አካልተአምሳል #ሆኖ ከደሙለደሙ ተዋህደው። ለዚህም ነው በዝልቀት የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ጎጃም ላይ ዓዕማደ መድህን ሆኖ የቀጠለው። ዲስፕሊኑን የመሸከም አቅሙ፤ ምንጩ ይኽው ተዋህዶ የመፈጠር ሥህናዊ አምክንዮ ስላለበት።
ያንጊዜ አቶ አሥራት አብርኃ የተባሉ የተጋሩ ሊሂቅ የገብያ ውሎ ነው የአማራ ሊቃናት ይጠዬፋታል ሲሉም ማንነት በገብያ ህግ አይተዳደርም በሚል ሞጋች ጹሁፍ በደጉ ሳተናው ድህረ ገጽ ሞገትኳቸው። ያዩታል ዓለም ዓቀፍ ይሆናል ትግሉ ብዬም ነበር። ያን ጊዜ እሳቸው አንድነት ፓርቲ ውስጥ ነበሩ። ዛሬድምፃቸውንም ሰምቼ አላውቀውም። ነገረ አማራ በዘውታ መዛለያ ሊሆን የሚችል አይደለም። አደብ፤ ጥሞና እና ስክነትን ይጠይቃል።
ከሁሉም የትግል መሥመሮች እንደ አማራ ፖለቲካ ከባድ የለም። በጣም ጥልቅ ተመስጦ እና መጨመትን ይጠይቃል። የአማራ ፖለቲካ ጉርምስና ሳይሆን አዛውንትነትን ይጠይቃል። ቢያንስ ጉልምስናን። ለዚህም ነው በዘመነ ተጋድሎው መባቻ ያልነበሩ ተጨማሪ ኃይሎች እና ሰብዕናወች ደርሰው ሲስረገርጉት በዝምታ ዝም ብዬ እማዬው። ከቀደምቶች እኔ እማውቃቸው ዬኔታ አቻምዬለህ ታምሩ እና አቶ ሙሉነህ የኋንስ ብቻ ናቸው። ከመሠረቱ ተዋህደው ስለመጡ ሰክነው ዘልቀዋል። በአንድም በሌላም ስከታተላቸው። ሌሎች የሞረሽ ለወገኔ ልጆች ናቸው።
#ሂደት እና ፍጥጫ የችግር ሰንሰለቶች።
1) ዘግይተውም ጠልፈው ሥሙን አትበስብሰው ወይንም አፍተልትለው አቅሙን ለመንጠቅ አቃላው ዬተነሱት፤
2) ሳቢያ ነው እያሉ ለደሰኮሩት፤ ሁሉ በወቅቱ አንቀጽ 17 የውጫሌ ውል ሳቢያ ወይንስ ምክንያት ስል በዘመኑ በደጉ ሳታናው ድህረ ገጽ ሞግቻለሁኝ። አረጋግጬም የገለጽኩት የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ የህወሃትን ዘመን ሊነቅል ስለመቻሉም አበክሬ በወቅቱ ጽፌያለሁኝ። ምክንያቱም የትግሉ ሥረ - ነገር ሳቢያ ሳይሆን መሠረታዊ ስለሆነ በመሰረታዊ ለውጥ ብቻም ሊዳኝ ስለመቻሉ እኔ ሳልሆን የአብዮታዊ ፍልስፍና ቀመሮች ያስገድዳሉና። ለምሳሌ የግንጫው የኦሮሞ ንቅናቄ ሳቢያ ተኮር ብቻ ነበር።
ይህን ያነሳሁት አገራዊ ምክክሩ ከጅራቱ፤ ከታፋው፤ ከቁርጭምጭሚቱ ላይ ተነስታችሁ መፍትሄ እናመጣለን ብላችሁ ስትነሱ ገርሞኛል። ለምን? ጥያቄው ከእናንተ ከተቋቋማችሁበት አቅም በላይ ስለሆነ። በአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ውስጥ የመዶል ያህል ካልሆነ ውስጠ ዘለቅ ተሳቴፍም አሻራም የላችሁም። መኖር ግድ አይደለም ቢያንስ አመክንዮውን የማድመጥ፤ ከራስ ጋር አስማምቶ አላምዶ ስለማቆዬትም፤
#ዬሆኖ ሆኖ።
አይደለም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፦ መሥራቹ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድም የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎን ጥያቄ የመመለስ፤ መፍትሄ የመሆን አቅም የላቸውም። በጠቅላላ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች የአማራን የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ችግር የመፍታት አቅም አላቸው ብዬ እኔ በግሌ አላምን። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ሥልጣን በጨበጡ በሳምንቱ ለዛ ሥልጣን ያበቃቸውን የአማራ ዬማንነት እና የህልውና ተጋድሎ፦ የአማራ ብሄርተኝነት አስወግዱሉኝ በማለት ቲም ገዱ በዚህ ዙሪያ እንዲዳክር ያደረጉት። ተዳፍኖ እንዲቀር የኳተኑት። አመራሩንም የጨፈጨፋት በባዕቱ ተገኝተው ነበር። አቅል አደብ የሚነሳቸው ጉዳይነገረ አማራ፤ ሚስጢረ አማራ፤ ዓዕማደ አማራ ነው።
ብቅ እንዳይል ጫን ተደል ዘመቻ እና ምንጠራ ያካሄዳሉ። የሌት ተቀን ትጋታቸው ይህው ነው። ያን ጊዜ ገዳይ እና አስገዳዩ ተቀምጦ እርስ በርስ ተገዳደሉ፤ መፈንቅል ሊደረግብኝ ነበር ሲሉ ደጋፊወቻቸው እና አንጋቾቻቸው ሁሉ አሰልፈው ዕውነትን ተፈታተኑት። ዛሬ ስንሰማ አማራ መቼውንም ሥልጣን ላይ አይወጣም የሚል አቤቱ አብንም አኮፋዳውን ተሸክሞ ቀፎነቱን አስረግጠው እንደነገሩት የምናዳምጠው። ጊዜ ወፍ ሲያወጣው እንዲህ ነው።
#የአማራ ተጋድሎ ሁለት የገዘፋ የተጋድሎ ዘርፎች አሉት ብዬ አምናለሁኝ። አህቲም መንትያም ናቸው። ይህ ዕሳቤ ግንእስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ የእኔ የሥርጉተ ሥላሴ ንብረት ነው።
1) የአማራ የማንነት ተጋድሎ።
2) ዬአማራ የህልውና ተጋድሎ።
እናታግላለን፤ እንመራለን የሚሉት እንኳን ከዚህ ሁለት አመክንዮ ሲነሱ አላይም። አንዱን ከአንዱ ነጥለው ወይ የህልውና፤ ወይ የማንነት ብለው ነው የሚነሱት። በሌላ በኩል በደራሽ ሞቅታወች የሚጀመሩ ሚዲያወች፤ የሚቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶችም ከችግሩ ምክንያታዊ አመክንዮ ይልቅ ከወቅታዊ የአቅም ሙቀት ብቻም ሲነሳሱ አያለሁኝ። ለዚህም ነው ብቅ ብለው ሳያቆጠቁጡ ችግኝ ላይ እንዳሉ አሟሟታቸው ከፍቶ የሚከስሙት። አንድም የአማራ ሚዲያ ሁል አቀፍ ሆኖ ሰፊው የአማራ ህዝብ ክህሎት እና አቅም ሲያሰባስብ፤ ሲያደራጅ፤ ሲመራ አቅጣጫ ሲቀይስ አይቼ አላውቅም።
ሁሉም በዬጎጄው ጎጆውን ቀልሶ አምሳያውን ብቻ ዕውቅና አሰጥቶ ሲከበክብ እና ሲንከባከብ ይታያል። ለዚህ የገዘፈ የመንትዮሽ ትግል አይደለም የአማራ ልጅ የአማራ ወዳጆች ሁሉ አቅም ፈጥረው አቅም ይሆኑ ዘንድ መስመር ሲቀዬስ አይቼ አላውቅም። ከእስረኛ እስረኛ ሲለይ፤ ከሞት ሞትሲለይእንጂ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የአማራን አቅም የሚፈሩ ኃይሎች ዘመቻ እና ወጀብ ይመስለኛል። ለዚህም ነውየተበተነው የአማራ አቅም እና ክህሎትከሳይለንትማጆሪቲው ጋር ጋብቻ ፈጽሞዝምታን ማንገሱ የአማራጉዳይቀሊል ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል። አማራ ገና አልተነሳም።
ከሁሉ በላይ አስቸጋሪው ጉዳይ የአማራን ችግር ብቸኛ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው ሳይገባው የተፈጠረው #ዬአብን የጉሮሮ አጥንትነት፤ በሌላ በኩል ማህበራዊ መሠረቱን ያጣ ሰብዕና ወደ ተጋድሎው በገፍ መትመሙ፤ እንዲሁም አስፈሪውን አመክንዮ አቀጭጨው መቅብር የሚሽቱ አሸኖች ወይንም #ምርቆች ታክለው የተጋድሎው መንፈስ ልቅና መስዋዕትነቱን አበራክቶበታል። ጉዞውም በስርክራኪ ሳንኮች እንዲጠይም ሆኗል። ግን የፈጄ ጊዜ ይፈጃል እንጂ ንጥር እና መረቅ ሆኖ መውጣቱ አይቀሬ ነው። ቢደምንም ያበራል፤ ቢጠይምም ያፈካል።
#የመሰላል ሂደቶች ……
1) "ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ"
2) ጣና እና ላሊበላ አትኩሮት
3)የልጆቻችን ይመለሱ ጥያቄ እና ዕድምታው፦
4) "ከጎዳና ወደ ፓርላማ" ገልባጭ ሂደት ሁነትን ያበቀለው የበቃን ትንግርታዊንቅናቄ
5) የአማራ ልዩ ኃይል፤ የአማራ ሚሊሻ እና የአማራ ፋኖ ፍካት፦
6) አማራ በደረጄ ቀለም የሚዲያወች፤ የስቢክስ ተቋማት፤ የመፃህፍት፤ የኪናዊ ውሎ አዳር
7) የዘኔ፦ ማስሬ እና አስረሱ፤ የፋኖ ስልጠና ፕሮጀክት እና የሌላው መጎምጀት ያመጣው ሁነት፦
8)የፋኖ ዬትጥቅ ንቅናቄ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና፦
ሌላ በግለሰቦች የሚቀነቀኑ፤ ቀን የሚጠብቁ ባለ ፈርጄ ብዙ የትግል መቀዬሻ አመክንዮወች ሁሉ በአንድ የግለሰብ ፈቃድ በተመሰረተ ኮሚሽን፤ በአንድ አስገብራለሁ ብሎ በፋንታዚ በሚፈነጥዝ ድርጅት ኦነጋዊው ኦህዴድ መሪነት፤ ወይንም በፀረ አማራነት ዕድሜያቸውን በቆጠሩ ዕድሜ ጠገብ የጎሳ እና የዜግነት የፖለቲካ ድርጅቶች መልካም ፈቃድ አይፈታም። ፈፅሞ።
#ሀ፦) 7 መፃህፍቶቿ ስለምን የስቶር ሲሳይ ሆነው እንዲቀሩ ተደረገ?
#ለ፦ ) ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቅ ፓን አፍሪካኒስት ሥም እና ማስታወሻ በብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን ሥም የተከፈተ የፀጋዬ ራዲዮ እንዲዘጋ ለምን ታደመባት????
#ሐ፦ ) የሚደግፋ፤ ቀና ዕሳቤ ያላቸው ሁሉለምንበስውር ይሳደዳሉ?
ጥያቄው ይህ ነው። የፀጋዬ ራዲዮ ቢከሰስም፤ ሰርክ ቢታገሉትም በሲዊዘርላንድ ዙሪክ ክፍለ አገር በ97.5 መካከለኛ ሞገድ በዕለተ ሃሙስ በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎቱቀጥሏል። ታግሎ ሙሉ 15 ዓመቱን አጠናቆ 16ኛው ይዟል። ሌላ ሴት ይህን ብታደርገው #የዘውድ አክሊል ይደፋላት ነበር። ይህ ቀርቶ መሳደዱ በቀረ።
ሥርጉተ ሴት ስለሆነች አይደለም። እእ።
ሥርጉተ ሰው ስለሆነች አይደለም። እእ።
ሥርጉተ አማራ እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ስለሆነች ሳይለንት ዲስክርምኔሽን ይደረግባታል። ጎንደሬነቷምይታከላል። ልክ እንደኛ ከሁሉምክፍለ አገር ባዕትበጥርስ ከተያዘው ከሚቀናበትምከባዕተ ጎንደርም ስለተገኜች። ልክ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ቅኔው ጎጃምን በጥርሳቸው እንደያዙት። የጎጃምን ስይት የሚበሉ እኮ አይመስሉም። አንድ ጊዜ ሙጃ ብሉ፤ አንድጊዜ አቦካዶ የሚሉትምከፀረ እንጀራጋር ባላቸውተውሳክም ነው። የሆነ ሆኖ መሳደዱ ዘርፈ ብዙ ነው። ጥልቅም ነው።
የሚገርማችሁ በዋናው ሥሟ በሰብለ ሥም ምንም አስተያዬት እንዳትጽፍ ሁሉ ገደብ ተጥሎባታል፤ ለምን? ዓለምዓቀፋ ማህበረሰብ ደግሞ ያውቃታል ተብሎ። ገድሜ እዬኖርክ አንድ ቀንጣ ነፍስ ስደት ላይ መቆሚያ መቀመጫ ሲያጣበባዕቱማ??? ይህ ብቻ አይደለም ስለ እኔ መልካም የሚናገር ሁሉ አይደግመውም። አሳደው በስውር ያከስሙታል። የአማራነት ችግር እጅግ #ጥልቅ ነው። ውስብስብ ነው። የአማራ ፖለቲከኛ ነኝ የሚለውም በችግሩ ልክ የገባው አይመስለኝም። የገባቸውማ የኔታ አቻም የለህ ታምሩ ነገረ ወልቃይትን? የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ሃብታሙ ተገኜ በራራ ቀዳሚት አዲስ አበባን የትውልድ እርስት በዕውቀት ገንብተውታል። ልክ እንደ አጤ ፋሴል፤ እንደ ቅዱስ ላሊበላ፤ እንደ ደጋጎቹ።
የአማራ ነገር እራሱ ፈተናው፤ ሚስጢር ነው። ሚስጢርን የሚፈታ የተሰጠው ነው። ያ ደግሞ መፍቻው በእግዚአብሄር፤ በአላህ እጅ ነው።
1) የአማራነት ችግር የባህል አይደለም። በፍፁም።
2) የአማራነት ችግር የኢኮኖሚ አይደለም። በፍፁም።
3) የአማራነት ችግር የታሪክ ጉዳይም አይደለም። በፍፁም።
4) የአማራነት ችግር ሃይማኖታዊም አይደለም። በፍፁም።
የአማራነት ችግር #የፖለቲካ ችግር ነው። ይህ የፖለቲካ ችግር ደግሞ ዓለማችን ዕውቅና ስትሰጠው ብቻ መፍትሄ ያገኛል።
#የችግሩ ሰቆች።
1) አማራ የለም የሚሉ የፕሮፌሰር መስፍን ተከታዮች አሉ፤
2) አማራ መጤ ነው ብለው የሚያምኑ የሌንጮወዲማ ተከታዮች አሉ፤
3) አማራ ገዝቷል፤ ጨቁኗል ብለው የሚያምኑ የአቶ መለስ ዜናዊ ተከታዮች አሉ።
4)አማራ ሽዋ አንዲት ጠባብ ጉሮኖ ብቻ ያለው ነው ብለው የሚያምኑም ከሰሞናቱም እያዳመጥኩ ነው።
5) አማራ ነኝ ማለት ማነስ ነው የሚሉም የእኛው የገመናጀበናወችም አሉን።
1) አማራ ኢትዮ አፍሪካዊ ነውን?
2)አማራ አገር አለውን?
3) አማራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አበርክቶ ነበረውን?
4) አማራ ወጥ ኃይማኖት አለውን?
5) አማራ ከሌላው ማህበረሰብ ብሄራዊ፤ አህጉራዊ፤ ሉላዊ ማህበረሰብ ጋር የዘር ትስስር፤ ውህድነት አለውን? ብዙ በጣም ተያያዥ ጥያቄወችን ማንሳት ይጠይቃል።
ይህን በሚመለከት ባለፋት አራት ዓመታት የተለያዩ ሃሳቦችን ሳነሳ ነበር።
ከላይ ያነሳኋቸውን ጥያቄወች ምላሽ ለመስጠት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ህጋዊ ዕውቅና ያለው አካል ተፈጥሮ የአማራ ፍጥረተ ነገር ሊፈተሽ ይገባል፤ ለኢትዮጵያ #መጤነቱንም አክሎ በዓለም አቀፍ ህግ ፍርድ ቤት ሊዳኝ የሚችል መስመር መዘርጋት ግድ ነው እያልኩ በብዙ ጽፌያለሁኝ። ለዚህም አንድም የአማራ ተቋማት ሥርዓት ዘርግቶ አመስግኗቸው የማያውቁትን ፀሐፍት የኔታ አቻምዬለህ ታምሩ እና የኔታ ፕሮፌሰር ዶክተር ሃብታሙ ተገኜን አያውቅም። ትውልዱን ያበጁ የህሊና የኔታወች ናቸው። መነሻ መድረሻውን የቀዬሱ ማህንዲሶች። ስለ አማራ ሲነሳኢትዮጵያ ልታመሰግናቸው እንደሚገባላዘክር እሻለሁኝ። መረጃ በጥናት በጥረት በጥራት ካለ የስኬት መጥምቀ ትንሳኤ ይሆናልና።
በነገረ አማራ ጉዳይ ሁለት አውራ የጥቃት ዓውታሮችአሉ።
1) ቀጥታ ተጠቂ
1.1አማራ እንደ ህዝብ
1.2የአማራ ትውፊት፤ ባህል፤ ወግ ልማድ፤
1.3አማርኛ ቋንቋ፦
1.4የአማራ ህዝብ ክርስትና፤ ይሁዲ፤ እስልምና ተከታይ ስለሆነ
የአማራ አገልግሎት መስጫ ተቋማት
1.5የአማራ የኢኮኖሚ አውታራት
1.6የአማራ የዕውቀት ማደራጃ ትውፊት እና ስኬቶች
1.7የአማራ የአኗኗር ዘይቤወች እና ቃናወች
1.8የአማራ የህሊና ውጤት የሆኑ ዕሳቤወች፤ ዕይታወች፤ ሎጅኮች፤ ፋክት እና ዕውነቶች፤
1.9የአማራ ኪናዊ ጥበቦች፤ አርኪቴክቸሮች ከሌሎችም ማህበረሰቦች ፈጠራዋች ጋር በውህደት፤ በተወራራሽነት ያደጉ፤ የተደራጁ፤ ነፍስ ዘርተው ነፍስ የሆኑ የአቅም ምክለቶች፤ ደርብ እና ምድሮች፤ ጉልላቶች፤
1,10የአማራ ቃና ያላቸው የአገላለጽ፤ የአባባል ተረት እና ምሳሌወች፤ ግጥሞች፤ ሥነ ውበቶች ወዘተ
2. በተደራቢ ተጠቂ
2.1) አፍቅሮተ አማራ ያላቸው ሰብዕናወችዕውቁ ጋዜጠኛ አቶ ታዲዮስ ታንቱን ለናሙና ማንሳት ይቻላል፤
2.2) ከአማራ ጋር የተጋቡ፤ የተዋለዱ ኢትዮጵውያን እና የውጭ ዜጋ ሰብዕናወች
2.3) የአማራን ውስጥነት የተቀበሉ እንደ ጉራጌ፤ አፋር፤ ወላይታ፤ አማሮ፤ ጉራጌ ወዘተ ያሉ
2.4) ከአማራነት ጋር የተዋህዱ እንደ አርጎባ፤ ራያ፤ አገው፤፦ቅማንት፤ ሽናሻ፤ ወይጦ መሰል ማህበረሰቦች
2.5) አማራ ያደራጃቸው፤ የመሠረታቸው ከተሞች፤
2.6) ከላይም እንደጠቀስኩት ከቅን የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረው የጎለበቱ ቀደምት፤ ዘመናዊ ኩነቶች ጠረነ ዝንባሌያቸው ወደ አማራነት ወሰድ የሚያደርጋቸው፤
2.7) በአማራ ልጆች ሁለንትናዊ የእድገት ግስጋሴወች የከበሩ ማንነቶች፤ የተገነቡ ዘላቂ ሉላዊ ፍሬ ዘሮች፤
2. በአማራ ልጆች አበርክቶ የተገኙ የአገር አወቃቀር፤ አደረጃጀት ሥነ - ህግጋተ ድንጋጌወች፤ ይሉኝታወች ከሌሎች የማህበረሰብ አካላት ጋር ከደማቸው ጋር ተዋህደው ስምም ሆነው የሚገኙ ማንኛውም የአኗኗር ሥነ - ሕይወታዊ ትንፋሾች፤
#የማከብራችሁ የአገሬ አንጋፋ የክህሎት ባለቤት የሆናችሁ የብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን አካላት ሆይ!
ሰርክ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ "ከውስጥ ሆነን ለውጥ አመጣን። በዛ መንገድ አትሞክሩት" ሲሉ አዳምጣለሁ። ከዕውነት ጋር መፋለም ሃፍረታቸው ስላልሆነ እንጂ ዓለማችን ይሁንታ ስትሰጥ አብይ የሚባል ሰው ከነመፈጠሩም አታውቅም ነበር። አንድ አገር ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። የሉላዊው ልዑላን ይሁንታ ያስፈልግ ነበር። ያም በሎጂክ ነው። ሎጂኩን የሠሩት ደግሞ የአማራ ልጆች ናቸው።
1) የሬቻ ጭፍጨፋን የተመድ የቀድሞው ፀሐፊ ሩህሩሁ አቶ ኪም ሙን ወጥተው አውግዘው ሶልዳሪቲ ያሳዩት በኢትዮ አማራዋ ሥርጉተ ሥላሴ ብዕር አቤቱታ አማካኝነት እንጂ በጃዋሪዝም፤ ሌንጮይዝም፤ መራራይዝም፤ ለማይዚም አልነበረም። በህይወት አሉ ጠይቋቸው። ይነግሯችኋል። ያን ላደረገ የአማራ ልጅ ግን በፋስ መቀላት ነው የተረፈው። ከእንግዲህግን የሚቀመስ ቅንጣት አቅም የለም። በተሸነገለው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ድክረት የለም።
2) ሌላ ዕውነትም ማቅረብ ይቻላል በግርሻ የሚያምሱት የብአዴን አካላት ሙሉ 45 ድምጽ ባይሰጥ ኦህዴድ ከነመኖሩም ብዕራችን ነክቶት አያውቅም ነበር። አሁንም ከዬት እንደሚሰበስቸው ባላውቅም የብአዴን ስርክራኪ አሰሮችን ማዘዝ፤ ማስረገድ ስለቻሉ እኛን የገዙ፤ ያስተዳደሩ፤ የመሩ ይመስላቸዋል። እሳቸውም አይሞክሩት። እኛም አንገኝም። ቅንነታችን፤ ድካማችን ምስክራችን ወላሂ ከእንግዲህ አማራ አልሆንም ያለችውን ቀንበጥ አላተረፈልንም። እግዚአብሄር ለአንድ ቅን ሲል ብዙ ነፍስን ምህረት ይሰጣል። ትግል ከጀመርኩበት ዕለት ጀምሮ እንደ ኦነግ በቃኝን የማያውቅ ድርጅት በታሪክም አንብቤ አላውቅም። ይሉኝታ የነጠፈበት፤ ሰባዕዊነት የተነበት።በእሱ አመራር ምህረት ሰላም ይቅርታ አይታሰብም።
#በባዶ ባዶነት። ከቻላችሁ ሰርክ የሚወርፋትን የአማራ ህዝብ ንቀታቸውን እንዲያስታግሱ አድርጉልን።
ንቀታቸው ዲካ የለውም። የሳቸው ቅጥል የአማራን ችግር ሊፈታ መስመር ተሰርቶለታል። ኢትዮጵያዊነት የሚወሩለትን ሳይሆን የሚኖሩለትን ብቻ ይሻል። በኢትዮጵያዊነት መኖር ያልቻሉ ሰብዕናወች በህወሃት ማኒፌስት በተደራጀ መዋቅር ህይወት እና መንገድ ብለው ዛሬን ሲቀበሉ፤ ትናንት ግን ህወሃትን ቁም ስቅሉን ሲያሳዩት ነበሩ። የዕውነት ቀራንዮ፤ የዕውነት ጎለጎታበ እነኝህ ሰብዕናወች ውስጥ አያለሁ፤ አስተውላለሁም። ህወሃት ከተነቀፈ ኦህዴድ የህወሃት ልጅ ስለሆነ መሰል አቋም ሊኖር ይገባል።
በሌላ በኩል መፍትሄ ኮሚሽኑ ያመጣል ብላችሁ መድከማችሁ ይገርመኛል። ለኢትዮጵያ የሶሻሊዝም ርዕዮት ልኳ አይደለም። ኢትዮጵያ መሠረቷ ላዕላይ እና ታህታይ አወቃቀሯም የራሷ የእኔ የምትለው ተፈጥሮ ያላት አገር ስለሆነች፦ ሌላ ውራጅ የትውስት ማኒፌስቶ አያስፈልጋትም። ኢትዮጵያዊነት ውራጅ ማንነት አይደለም እና። ከዚህ ረግረግ የተገባውም በዚህ ነው።
ብዙ ሰው የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ማኒፌስቶ፤ በዘመንኛው አገላለጽ ፍኖተ ካርታ የለውም ሲል አዳምጣለሁኝ። ለአማራ አያስፈልገውም። እደግመዋለሁ ለአማራ ውራጅ ማኒፌስቶ አያስፈልገውም። ለምን?
ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ኢትዮጵያዊነት ነው ማኒፌስቶው። አራት ነጥብ።
@ኢትዮጵያዊነት ሚስጢር ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ዩንቨርስ ነው። ኮከብ ሳይቀር የተሰዬመለት።
@ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ህግ ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ይሉኝታም ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ሉላዊነትም ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ጠይማዊ ዳማነትም ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ህብራዊነት በመስተፃምር ሳይሆን መስተዋድዳዊ ነው።
@ኢትዮጵያዊነት የመኖር ጠበብትም ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ሰዋሰዋዊ ክስተት ነው።
@ኢትዮጵያዊነት አናባቢም ተነባቢም ድንቅነት ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ፊደላዊነት ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ግዕዛዊነትም ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ፈርኃ አላህ፤ ፈራእግዚአብሄርነት ነው። በህግ አምላክነት ነው።
@ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሯዊነት፤ ሰዋዊነት፤ አዛኝነት ርህርህናም ነው። እና አማራ ምን ፈልጎስ፤ ምንስ ሊያገኝ ከዚህ ማዕቀፍ ወጥቶ ሌላ ውራጅ ጋራጅ ያሰኜዋል??? ለዚህ ሃቃችን፤ ላሂያችን ነው እምንታገለው።
#ንቀት
ጎንደሬወች ባለ ቅኔ ናቸው "የናቁት ይወርሳል" ይላሉ። የተከበረው የምክክር ኮሚሽኑ ከቻለ ለመሪው ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ብትነግሯቸው ይበጃል። አሁን ይፋዊ ጦርነት በአማራ ህዝብ ላይ ከፍተው በቀዩ፤ በባዕቱ ህወሃት ቆርምሞ በሰጠው ባድማ እንኳን እንዳይኖር እያደረጉት ነው።
ወንድ ልጅ የተባለ በአስፓልት፤ በአውራ ጎዳና ላይ እዬረሸኑ ነው። ከሆስፒታል የገባን ገመምተኛ ሳይቀር አውጥተው በግፍ እዬፈጁ ነው። የሚገርመኝ ስለ ሰው ልጅ እልቂት አስከፊነት የሳቸው ልሳኖች NBC እና ፋና በሃማስ እና በእስራኤል ጦርነት ተቆርቋሪ ሆነው ሲዘግቡ አዳምጣለሁ። የአማራ ልጅ በተገኜበት እዬታደነ፤ እዬተረሸነ፤ እዬታገት፤ እዬታሰረ አንዲትም ቃል አያወጡም። "እራስ ተከናኒቦ ቂጥ ገሊቦ" የሆነ ጉድ። "የሚሉሽን ብትሰሚ ገብያ …… " እንዲሉም። ኮሚሽናችሁ ይህን ሰዋዊነት መልክ ማስያዝ አልቻለም።
የአማራ ልጅ በአገሩም ተሰዶም ፈተናውን እስከ ዛሬ ድረስ ለጠቅላዩ አጀንዳ አይደለም። የውሽማ ሞት ሆኖ እንዲቀር ይፈለጋል። አንድ ቀን እራሳቸው የሚዘምቱበት ቀን ይመጣል። ጦር አዝማች ሆነው ስንቅ ቆጥሩልኝም እዬጠበቅ ነው። ከአቅምም፤ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ። አማራነትን ኢምንት አድርገው ያዩታል ግን ውስጣቸውን ሸረካክቶታል። ንዶታልም። በፈለገ ዓይነት ቀመር በሽርፍራፊ ጥረት፤ በሽንገላ እጀላ የአማራን ህዝብ ፖለቲካዊ ጥያቄ ተትበስብሶ ሊቀር አይችልም።
የዛሬ 8/9/10 ዓመት አማራ ማለት ወንጀል ነበር። አማራ መደራጀቱ አስፈላጊ ነው ስንል ማት ይወርድብን ነበር። ዛሬ የሚዲያው ቀንዲል አማራ ሆኗል። በሌላ በኩል አማራ ተረግጦ ግን የአማራ ክልል፤ የአማራ ማስ ሚዲያ አለ። ፌድራሊዝም ያለው አማራ ክልልል ብቻ ነው። የአርጎባ፤ የቅማንት፤ የአገው፤ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳ ያለው፤ ውክልና ያለው አማራ ክልል ብቻ ነው። ዶር ለገሰ ቱሉ በአማራ ክልል የተወከሉ ኦሮሞ ናቸው፤ ሌላም በአማራ ኮታ የቅማንት፤ የአገው ሊቃናት ሙሉ ውክልና አላቸው። ይህን ተሸክሞ አማራ ኖረ። በኬሚሴ የአማራ ልጆች በአማርኛ ቋንቋ አይዳኙም።
በሁሉም ክልሎች አንድም የአማራ ተወላጅ በመንግሥት ሆነ "በብልጽግናቸው" ውክልና የለውም። የአማራ ልጅ ከክልሉ ከሚኖረው ሌላ የበለጠው በሌላ ክልል የሚኖረው። ያን ለመቀነስም ነው። ግማሽ ሚሊዮን ኦሮሞ አዲስ አበባ እና ዙሪያ እንዲሠፍር የተደረገው፤ በኦሮምያ ያለው አማራ ምንጣሮም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። የአዲስ አበባ ጎለጎታነትም እንዲሁ።
የተከደነው ፈንጅ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆችም የሉም። በፖለቲካው ዘርፍ ልሙጥ ነው። አንድ ቀን ይፈነዳል። እዬተብላላ፤ እዬተንተከተከ ያለ ዕውነታዊ ፍላሎት ነው። ይህንስ አስባችሁ ታውቁታላችሁን???
ከሁሉ የሚገርመኝ በሎቢም፤ በአገርም በሙሉ የአማራ ድጋፍ ሥልጣን የያዘው በኦነግ መርህ የሚመራው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሥርዓት የአማራን ህዝብ ክህሎት፤ ፀጋ፤ ታለንት፤ የማድረግ አቅም እና ችሎታ ዕውቅና ለመስጠት ንፍገቱ ነው። ውስጡ ብል የበላው ዬነቀዘ ሳጥን ያደረገውም ይህ ንቀት የፈጠረው ውስጣዊ ዕምቅ ቁጭት እና ረመጥ የፈጠረው እልህ እና የተግባር ትጋት ነው። ይህን ሁለንትናዊ አቅም መተርጎም፤ መተንተን መተንበይም አይቻልም። ለዚህ ነው ከአቅማችሁ በላይ ስለሆነ ባትንጨባረቁ የሚል ትሁታዊ ዕይታዬን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ በአክብሮት ላቀርብላችሁ እምሻው።
በእኔ ውስጥ ያለውን ማግኔታዊ አቅም እንኳን በችሎታችሁ ረትታችሁ ከሥራችሁ ልታስገቡት አትችሉም እንኳንስ የ40/50/ሚሊዮን ህዝብ ወጥ ጥያቄ። ጥያቄያችን ፖለቲካዊ ነው። ምላሽ ሰጪውም ሥር ነቀል፦ የሥነ - ልቦና እና የሥርዓት ሉላዊ ለውጥ ብቻ ይሆናል።
እናንተ ለእርቅ ስትላኩ አለቃችሁ ዕውቅና ሳይሰጡት ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በዕውን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንደዛ ከሚያንገፈግፋቸው የአማራ ታጋዮች ጋር ቁጭ ብለው ሊወያዩ? ሊነጋገሩ? አትድከሙ! አያደርጉትም። ለዚህም ነው በቀላቸው እጅግ መራራ እና ጎምዛዛ የሆነው።
ማዘን ላልፈጠረለት ልብ እርህርህናን እንደ ኮሶ አፍንጫውን ሰንጎ መጋት አይቻልም። ፈጽሞ። አይዟችሁ የሚጎመዝዘው መሪ ለእርቅ እና ለሰላማዊ ጉዞ ይሆናል ብሎ ማሰብ ጨረቃ ፀሐይን ትተካለች እንደማለት የገዘፈ አመክንዮ ነው።
የእሳቸው እርምጃ ከቡቃያም፤ ከግንድም፤ ከቀንበጥም ከአሸተም የአማራ ትውልድን ከመመንጠር ጋር የተያያዘ ነው። በረሃብ፤ በበሽታ፤ በጦርነት ስለሚያልቀው ወገን የትንኝ ያህል ስሜት አይሰጣቸውም። በቅያር፤ በቅያር፤ በቅያር ሰብዕና እዬትዥጎረጎሩ የሚያሳዩት ፍፁም ጭካኔ እና አረመኔያዊነት እርምጃ እንደ አገር መሪነት ለማዬት አይቻልም እሳቸውን። ዘነዘናቸውም ናቸው። የሚገርመኝ ብስጭታቸውን በታይታ ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት እና ይህን መሰል አዘናጊ፤ ትጥቅ አስፈቺ ድልዝ ኮሚሽን በመፈጣጠር በትረ ሥልጣናቸውን ለትንፋሽ ለማብቃት መፍጨርጨራቸው ነው። ከማህበረ ኦነግ የሚጠበቅ ኢትዮጵያዊነት የለም!
ስለሆነም እሳቸው የሚመሯቸው ተቋማት ሁሉ ድዌ የሚዘንብባቸው ይሆናሉ። ስለዚህም መታመንም ይሰደዳል። ትልቁ ፕሮጀክታቸው የቀኑባቸውን ሰብዕናወች ሁሉ ለበብ ብለው ያስጠጉ እና እንኩቶውን ያስታቅፋሉ። አንድ ቀን እንክህ እንክህ የሚባለው የተቋማችሁ ዕጣ ፈንታም ይህው ይሆናል።
ከሳቸው በላይ ዘለግ ብሎ እንዲወጣም፤ እንዲታይም፤ ቀድሞ የበቀለ ፀጋ እና ምህረትን ማዬት አይሹም። ይታመማሉ። በምርጫው አቶ ለማ መገርሳ ቢወዳደሩ በባዕታቸው እንደሚመረጡ ስላወቁ ግዞት መደቡላቸው። መቼም ከኦሮሞ ኦነግ ፖለቲከኞች ጭምቱም የሚመጥኑትም እሳቸው ብቻ ነበሩ። ለእኛ እያልኩ አይደለም። ለኦሮሞ ለኦነግ ፖለቲካ ማለቴ ነው። ለእኛማ ዴሞግራፊን መሠረት ያስያዙ ይቅርታም ያልጠዬቁን ሰው ናቸው።
ማጠቃለያ።
ዶሮ ወጥ በተልባ አይሠራም። የእናንተ ሙከራም ይኽው ነው። ማዛ ቃና የለውም። የኢትዮጵያንም ሆነ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ጋር አልተገናኝቶ ገቢያ ነው። እናንተ ለስካንድቢንያ አገሮች ነው መድህን መሆን የምትችሉት። በማኦይዝም፤ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም፤ ፋሺዝም እና መሰል ርዕዮት ለተቀመረው ፀረ ሰው ርዕዮት እና መንግሥት መንገድ ጠራጊነት የማይሆን ጅማሮ ነው። ቢያንስ የተከበረውን ሰብዕናችሁን በጊዜ ብታድኑ መልካም ይመስለኛል። ያ የዕድሜ ሙሉ ተመክሮ እና አሻራ፤ ክብር እና ክህሎት እንዳይመንን። ዲሞግራፊ ላይ ተቀምጦ ምህረት እና ሰላም፤ እርቅና መቀራረብ አይቻልም። ፈፅሞ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሽግግር ፍትህም ከፋሺዝም ሥርዓት አልጠብቅም። የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ የገዳ ወረራ፤ የገዳ መስፋፋት፤ የገዳ አስምሌሽን እና ዲስክርምኔሽን ነው። ይህን የሚመጥን የፖለቲካ ዕሳቤ ደግሞ ከማህበረ ኦነግ ሳይሆን ከኢትዮጵያኒዝም ብቻ ይፈልቃል። ለዚህ ሥርዓቱ የለም። አልተዘረጋም። ኢትዮጵያ በማህበረ ኦነግ ፖለቲካ ሃይጃክ ተደርጋለች።
ንፁሁ ተፈጥሯችን ትናንት የሚናፍቀን ሰብዕናወች ለዚህ እንተጋለን። ኃይል እና አቅማችን አላህ አምላካችን ብቻ ነው። አንሰበርም። ለድል እንበቃለን። ኢትዮጵያ አገራችን ናት። አማራ የማይሳደድባት፤ የማይጋዝባት፤ የማይጨፈጭፍባት ኢትዮጵያ ትመጣለች። የጎበጠው ቀን ይቃናል። ለቀኑ ቀን ሲሰጠው ስኬት ይሆናል።
"የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ" ይላሉ አበው። የአገራዊ ብሄራዊ የምክክርኮሚሽኑ በብክል ሥርዓት ውስጥ መፍትሄ አመንጭቶ የመዳን ጉዞን ሊመራ አይችልም። አያድግም። ጨንግፎ ይቀራል። ይቅርታ የማልጠይቅበት ምስባክ የኮሚሽኑ ጉዞ የተቃጠለ ካርቦን ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ወይንም ኤክስፓዬርድ ያደረገ ባትሪ።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/10/2023
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ