• ለፓን አፍሪካኒዝም #አጀንዳ መጋቢ ቁም ነገር። ለዓለም የጠይማን ዕንቁወችም አጤ #ተስፋን ዘለግ አድርጎ ይመግባል። "#ምህረትህ ከሰማያት በላይ ታላቅ ናት።" (መዝሙር ፻፰፤፬።)
"#ምህረትህ ከሰማያት በላይ ታላቅ ናት።" (መዝሙር ፻፰፤፬።)
«የአፍሪካ እና የካሪቢያን አገራት በጥቁሮች ላይ ለተፈጸመው የባሪያ ንግድ ይፋዊ ይቅርታ እና ካሳ ጠየቁ» BBC.
ምዕራፍ ፲፱።
#ጠብታ።
እንዴት ነን ቤተ - ሥርጉትሻ? እኮ እንዴትስ አረፈድን? ዛሬ ውሽክ ብሏል። ልዕልቲቱ ነጋ አልነጋ ብላ ስትንቆራጠጥ ቆያይታ ወገግን ስታበስር #ፏ ብላ ነበር። ዝማሬው የወፎቹ ቀልጧል። ፏፏቴ ቢኖር እንዴት ያምራል መሰላችሁ። ጠሐይቱ የተስፋ ስንቅ ናት። ዜናውን መሠረት አድርጌ ተያያዥ ጉዳዮችን ለማንሳት ፈቀድሁኝ።
#ይህ ዜና ጠይም ዕንቁውያንን ቀና ያደርጋል።
ሽልንጓ የጎረባበጠቻቸው ፈረንሳውያን እና እንግሊዞች ደግሞ ቼክ አያስፈልግም ባዮች ናቸው። ያልተሰላ ረቂቅ ጉዳይ ተዜናው አስኳል አየሁበት ጭብጡን ሳዬው።
የመዋለ መንፈስን ልዩ የጠይማን ተሰጥዖን፤ ሥልጡን አቅምን ጠይማዊ ዊዝደም እና የቅኝ ገዢወች ሥልጣኔ ምንጭነት ተብራርቶ አልተነሳም ከጭብጡ እንደተረዳሁት። በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ አለችበት። ዊዝደም በማዋጣት፤ መኖርን በማሰልጠን፤ አብሮነትን ተቋማዊ አድርጎ በመቀደስ። ምንም እንኳን ባርነቱ #ባይነካካትም።
ለነገሩ ባርነት ተቀምሶ ቢሆን ኖሮ የተለጠጠው፤ ልቅ የሆነው፤ #ባሊህ ባይ ያጣው የቀደምትን ዊዝደም የማጣጣል፤ የመንቀል፤ የመቅደድ እና የማቃጠል ዘመቻ በተከታታይ ባልተካሄደ ነበር። የአማራ ህዝብ ሃጢያቱ ይሁን ኩነኔው እኮ ለባርነት እንብይ ባይነቱ ነው። ይህን የሚመሰክሩ የዕውነት አርበኞች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፤ ለካቴና፤ ለመሰወር፤ ለዱላ እና ለስደትም ተዳርገዋል።
እመው እና አቨው ቀደምቶች #በአረንጓዴ፤ #ቢጫ #ቀይ ማኒፌስቷቸው፤ በተፈጥሯዊነት የላቀ ብልህነታቸው፤ #በደልዳላው ልዕልናቸው፤ በሰከነው የብቃት አስተምህሯቸው፤ በኢትዮጵያኒዝም ንጥር ፍልስፍናቸው ያበጇትን አገር ዛሬ በቅናት እና በማንነት የቀውስ መከራ የተሰለሱ እንዲህ እና እንዲያ ሲያደርጉት የሚያመው ለዚህ ነው።
ራህብን ለማያውቀው ራህብ ምንድን ነው ብትሉት፤ መልሶ ይጠይቃችኋል። የአክርማ ዛላን ከዳጉሳ ዛላ ጋር ለዩ ቢባሉም ይሳናቸዋል። አለማወቅ መነሻ አልባ ተንሳፋፊ የሚያደርገውም ከዚህ አንፃር ነው።
ነፃነት #በጡጦ የምትገጠግጠው ስንቅ አይደለም። ነፃነት በቤቢ ሲተር የሚገኝ ተቀማጭ የህሊና አቅም የሚሰጥ አይደለም። ወይንም ነፃነት እንደ ቦንዳ መትረህ የምትቸረችረው ወይንም የምትሸነሽነው፤ ወይንም ላውንደሪ ከተህ እንደ አገር ልብስ የምትጠረጥረው አይደለም።
ነፃነት በመኖርህ ውስጥ መኖርህን በህሊናህ ልክ ትመራ ዘንድ በአቅምህ የምታመነጨው ረቂቅ #እዮራዊ የገነት ውሃ ነው። የማይደርቅ፤ የማይበወዝ፤ የማይሸጋሸግ፤ የማይታቆር፤ የማይነጥፍ ወይንም የማይፈለጥ እንደ አባሎ፤ እንደ ወይራ እንጨት።
ታሪክ #በቀደመ ህዝብ ብልህነት ይጸነሳል፤ ይተከላል፤ ይበቅላል፤ ያሰብላል፤ ያፈራል። ያን የብልህነት ልቅና በየትኛውም ዘመን አንተ ላገኜኽው የመኖር ዘይቤ ልዕለ፤ ሥህነ - መሠረት ነው። አንተ ነበርክም አልነበርክም። አንተ ተቀበልከው አልተቀበልከው። አንተ ዕውቅና ሰጠኽው አልሰጠኽው። የኢትዮጵያ የነፃነት መረቅ በማርክሲስት ሌኒኒስት ይሁን፤ በፌድራሊዝም የተበጄ አይደለም።
የኢትዮጵያ ፍጥረተ ነገር ኦርጋኒክ ነው የምለውም ለዚህ ነው። እና በተሰራ መሠረት ላይ፤ በተበጄ ጉልላት ላይ ሆነህ የአርቲፊሻል የመንፈስ ነቀላ እና ተከላ አደርጋለሁ ብትል ትከስማለህ። ትሟሽሻለህ። ድስት ካለግጣሙ አይሆን ነገር።
የኢትዮጵያን የነፃነት መቅኖ፤ እርጅና ሽው የማይልበትን አልፋ እና ኦሜጋ አንከራዊ ጸጋ አፈጣጠሩን፤ አሰካከኑን፤ አሰባበሉን አታውቀውማ። ግጭቱ ያለው፤ ጦርነቱ ያለው እዚህ ላይ ነው። ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድቀቷ የአንተ የመንቀል ተፈጥሮ የመቋቋም አቅሙ የተመሰከረለት ነው። ኢትዮጵያኒዝም #የ፲፫ ወራት ብርኃን አሰጣጧ እንደ መዳህኒት የሚታዘዝ ቅዱስ ፈውስ ነው። ያልደከምክበት ስለሆነ አትተዋወቁም እንጂ።
የሆኖ ሆኖ በተሰራ ቤት፤ አፍርሶ የሌለ የትውስት #አሳቻ ተፈጥሮ ከመለጣጠፍ፤ ባርነትን፤ ሎሌነትን፤ አንገት መድፋትን ከመናፈቅ ተመጣጥኖ በተበጄ በራስ የመተማመን አቅምህ ልክ ለመሆን እራስህን አሸንፍ ይህ አገላለፄ ሁላችንም ይመለከታል።
ይህን የይቅርታ እና የካሳ ጥያቄ ጉባኤ ልትመራው የሚገባት ፈላስፊት ኢትዮጵያ ናት። ግን የማንነት ቀውስ በሚንጠው ሰብዕና አይደለም። ግን ኢትዮጵያዊነት ጎላ ባለ ቁጥር #በሚያባትተው ሰብዕና ሊሆን አይገባም። ግን በመታበይ ሰረገላም እላፊ በሚሄድ በተንጠራራ ኮንፊደንስም አይደለም።
ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው። ይህን መሰል ጎርበርባጣ ወጣ ገብ ሁነት ሲገጥማቸው "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ። በራስ የመተማመን አቅም ሲለጠጥም ማበጥን፤ ሲሸበሸብም ዝቅታን ያስታቅፋል። ኢትዮጵያዊነት ከውስጥ ሲዋጥ የሚሰጠው ታላቁ የህይወት ዶግማ ኮንፊደንስህን #ያመጣጥናል። ለምሳሌ #ይሉኝታ። ታላቅ ፍልስፍና ነው። የትምም የማታገኜው።
በየትኛውም አገር የሥነ ጹሁፍ ስልጣኔ፤ የአኗኗር ዘይቤ አይከሰትም። ስለሆነም ብዙ ክስተታዊ ልቅናወች ድርቀት ይጎበኛቸዋል። ይህ ምን ማለት ነው የውበት ወዝ ያጥራቸዋል። ይህ የይሉኝታ ጸጋ #በማርኬቲንግ ህግም የማይተዳደር ነው።
ውስጥህን ክደህ ውስጥነት አይገኝም። ፈጣሪ አምላክ ከውስጥነት #መላጣነት ወይንም ልሙጥነት ያድነን ሁላችንም። በተሰጠን ልክ የመሆን አቅማችን በለቅ እና ሽካራ ስለሆነ። ለዚህም ነው እኔ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችን ነው የምለው።
ከዚህ ዜና መሻት፤ ከዚህ ዜና ምኞት፤ ከዚህ ዜና ተስፋ፤ ከዚህ ዜና ጉልበታም ጥያቄ የምንማረው ቁም ነገር ነፃነት እና ባርነት ዘመንን ቁጭ አድርገው #ሲዳኙት ነው። አንድ አይሉ ሁለት እጅግ ዘመናዊ ሥልጡን የፊደል ገበታ ያላት ዩንቨርሷ ኢትዮጵያ የአማርኛ፤ የግዕዝ ፊደላት በቃና፤ በቅኔ፤ በትርጉም፤ በሚስጥር ህብራዊነት አጊጦ እየጠበቀህ፤ እያለህም አንተ የላቲን #ብድር ያስኬደህን ሁነት እሰበው።
በጥልቀት ተኝተህ እሰበው።
ባርነት ---- ሽው፤ መገዛት----- ንፍቅ፤ መናቅ ---- ውል ብሎህ ስለመሆኑ ሳታቆላምጥ የሃቁን #አሳንጋላ አጣጥመው፤ እንዲሽርልህም "ዶሮ ማታ" በለው እና ግጥም አድርገህ ጨልጠው። ቡርሽ የህሊናም የሆድ ዕቃም ስለሚያስፈልግ።
አንድ በቅብዓ ውስጥ የሚገኝ ነፍስ ቤተ - ተዋህዶ "ደጋግመን ነግረን ነበር። ቤተ እግዚአብሄሩ ከብሄራዊ ሰንደቅ አላማ ጋር ያለውን ቁርኝት እንዲያቆም።" ይላል። ዲያቆን ወይ መምህር ናቸው። አደባባይ ሚዲያ በአርሲ ሰማዕታት ላይ ሲወያዩ ለናሙና ቀርቦ ነው ያያሁት። ቤተ - ተዋህዶው እራሱን #ጥሶ ነው ይህን ያለው። "በማን ላይ ቁመሽ ማንን ታሚያለሽ" ነው ጉዳዩ።
በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልበ - ህሊና ኢትዮጵያ የታተመችው፤ ሰማዕትነቱ፤ ዊዝደሙ፤ ብቃቱ፤ ልቅናው እና ልዕልናው #የደባልነት ሳይሆን የባለቤትነት ማህደሩ ፕላዝማው፤ ነጭ እና ቀይ የደም ሴሉ እሱ በእሱ ስለሆነ ነው።
ይህን ደምስሰህ፤ ይህን ደርመሰህ፤ ይህን አልይህ // አልስማህ ብለህ የምታደራጀው ፓርላማም፤ የምታዋቅረው ካቢኔም፤ የምትደምረው ስልጣኔም፤ የምታስገነባው የዴንማርክ የንፋስ የኃይል ማመንጫምይሁን የምትፈጥረው ዘመናዊ ሜጋ ፕሮጀክት የለም። በአንተ ውስጥ አለ የሚባል ቅርጥምጣሚ ጥበብ ካለ የኔታ ቤት ሀ ግዕዝ፤ ሁካዬ፤ ሃራብ እያልክ ስትቆጥር የወሰድከው የበረከት #ጣዝማ መሆኑን ልብ ብለህ አስተውለው።
የትኛውም የሰብዕናህ መገለጫህ በኢትዮጵያኒዝም የተቋማት ብቃት ቤተ መፃህፍት የተቀዳ ነው። ይህ አሊ የማይባል ሃቅ ነው። ዛሬ ጧፋም፤ ማጣፋቱም፤ ከበሮውም መዘረፋ አልበቃ ብሎ ታላቁ የሁዳዴ ፆም እና ትንሳኤው ለማን እየተሸለመ እንደ ሆነ እናያለን። ካለልኩ የተሰፋ ጥብቆ ወይንም ሽብሽቦ ነው። የሁዳዴው እናቱ ዓናቱ ቅኒት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተቀምጣ ………???? ከብሎት ጋር የባጄን ሰብዕና ዕልፍኝ ከአዳራሽ ስታዘናክት የላይኛውን ቁጣ ቢያንስ ፍራ ………
ማንም ይሁን ማንም ከኢትዮጵያኒዝም ማንነት #በላይ አይደለም። ልሁን ቢልም ይንሳፈፋል፤ ወይንም ይሸበሸባል። ዕውነት በዓቱን ለቆ ስለማያውቅ። ቤተ - ተዋህዶ ሆነህ፤ በተሠራች አገር ተቀምጠህ ትንፋሿን፤ ማኒፌስቶዋን ብሄራዊ ሰንደቋን የፍጅት፤ የጭካኔ ምንጭ ነው ስትል ያለ ጥሪህ፤ ያለቦታህ ነው ያለኽው ማለት ነው። ቅባህንም አጨልመኽዋል። ጨለማ - ጨለማን በውስጥ ሲያሰክን። ውጤቱ ክስለት ይሆናል። ምርቃቱ ስለሚነሳ።
የነፃነት አገር በትረ አምድነቷ ባርነትን ስለማታውቀው ፈጣሪ ይመስገን። ባርነትን ለሚናፍቅ ሥነ ልቦናም ወደ ህሊናው ይመልሰው። ምህረት እና ማስተዋል አማኑኤል ይስጠው።
ክብረቶቼ ቤተ ሥርጉትሻ ኑሩልኝ። አሜን። ቅንነታችሁ ሁልጊዜም፤ ምንጊዜም ቁሞ ያስተምረኛል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
20/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
«የአፍሪካ እና የካሪቢያን አገራት አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ ከተካሄደው የባሪያ ንግድ የተጠቀሙ አገራት በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲሁም ካሳ እንዲከፍሉ ጠየቁ። " BBC.
የአፍሪካ እና ካሪቢያን አገራት መሪዎች በጋና ለሦስት ቀናት ያካሄዱትን ጉባዔ ሲያጠናቅቁ በባሪያ ንግድ ለተጎዱ አገራት ፍትሕ እንዲሰፍን ጠይቀዋል።
ያለፈው መጋቢት ላይ የተባበሩት መንግሥታት ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የባሪያ ንግድ "በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች የከፋው" መሆኑን ግልጿል። የተመድ አባል አገራት የካሳ ገንዘብ እንዲያዋጡም አሳስቧል።
ከ15ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ወደ አሜሪካ ግዛቶች በባርነት ተወስደዋል።
በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለውን በተመለከተ በጋና መዲና አክራ በተካሄደው ጉባዔ ላይ 19 ነጥቦች ያሉት ዕቅድ ይፋ ተደርጓል።
ሁሉን አቀፍ የዕዳ ቅነሳ እንዲደረግ፣ የተዘረፉ ባህላዊ ንብረቶች እንዲመለሱ እና ዓለም አቀፍ የካሳ ማዕቀፍ እንዲዘረጋ ተጠይቋል።
ለዓለም አቀፍ የካሳ ማዕቀፉ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጥ አልተጠቀሰም።
ቅኝ ግዛት በአፍሪካውያን ሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ተለይቶ እንዲታይም ተጠይቋል። ቀድሞ በባሪያ ንግድ ውስጥ የተሳተፉ አገራት "ሙሉ፣ ይፋዊ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው ይቅርታ" መጠየቅ እንዳለባቸው የጉባዔው ተሳታፊዎች ተስማምተዋል።
የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሀማ "ታሪክ ጥፋተኛነትን እንድንወርስ አይጠይቀንም፤ ኃላፊነት መውሰድ ግን አለብን" ሲሉ ለአፍሪካውያን እና የካሪቢያን መሪዎች ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት የቅኝ ግዛት ሰለባዎች "ከሰው በታች፣ እንደ እቃ ተቆጥረዋል" ብለዋል።
ሆኖም ግን ካሳን ወደ ገንዘብ ብቻ ማውረድ እንደማይገባ ተናግረዋል። "ቼክ መጻፍ ብቻውን የታሪኩን ምዕራፍ አይዘጋም" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የውሳኔ ሐሳብ ያሳለፈው በ123 ድጋፍ፣ በ52 ድምጸ ተአቅቦ እና በሦስት ተቃውሞ ነው። የተቃወሙት አሜሪካ፣ እስራኤል እና አርጀንቲና ናቸው።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አብዛኞቹ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል። የተመድ የጠቅላላው ጉባዔ የውሳኔ ሐሳቦች እንደ ፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች በሕግ አሳሪ አይደሉም።
ዩናይትድ ኪንደግም (ዩኬ) ካሳን ከሚቃወሙ አገራት አንዷ ናት። ለቀድሞ ጥፋት አሁን ላይ ዋጋ መክፈል ተገቢ አይደለም ብላ ትከራከራለች።
በተመድ የዩኬ አምባሳደር ጄምስ ካሪውኪ "የትኛውም ሰብአዊ ቀውስ ከሌሎቹ በተለየ ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ተደርጎ መወሰድ የለበትም" ብለዋል።
የአሜሪካ አምባሳደር በበኩላቸው አገራቸው "ቀድሞ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ሕገ ወጥ ላልነበረ ክስተት አሁን ላይ ካሳ በመክፈል" እንደማታምን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ካሳው ለእነማን እንሆነ በግልጽ እንዳላስቀመጠም ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ በቅኝ ግዛት ለተወሰዱ አፍሪካውያን ቤተሰቦች ወይም ጉዳት ለደረሰባቸው አፍሪካውያን ካሳ የከፈለ አገር የለም።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎችን በባርነት ይዘው ለነበሩ ግለሰቦች በመንግሥታት አማካኝነት ካሳ ቢሰጥም ለተጎጂዎች ገንዘብ አልተከፈለም።
ቅኝ ግዛት ሕገ ወጥ ሲደረግ በአውሮፓውያኑ በ1830ዎቹ የዩኬ መንግሥት ሰዎችን በባርነት ለያዙ ዜጎቹ ከ21 ቢሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ ሰጥቷል።»

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ