አማራጭ የለም… ስለምን?

እንኳን ደህና መጡልኝ
              አማራጭ 
     የለም…
             ስለምን?
„ዮሴፍም እርስ በርሳቸው የደኅንነትና የፍቅር 
አሳብ እንዳላቸው የጠብም አሳብ እንዳላቸው
 አሳባቸውን በሚያውቅ ገንዘብ አሳብን አሰበ።“
መፅሐፈ ኩፋሌ ፴ ቊጥር ፩ 
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
11.04.2019
ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ።

ይህ ተጋድሎም ለኦነግ እንዳወጣ ተቸብችቧል።

ጤና ይስጥልኝ የኔዎቹ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? ውይ ዛሬ ከፍቶታል። ዛሬ ካፌዋን ጨለጥ አላደረገም መሰል። ጭፍግግ ብሎ ነበር መስኮቴን ስከፍተው የጠበቀኝ። ተዚህ እንዲህ ከሆነ አላዛሯስ ኢትዮጵያ ማለቴ አልቀረም… ያው  በአለችየለችም እዬተናጠች ነው … ይመስለኛል።

እኔ ፈሪ ከሆንኩኝ ሰነባብቻለሁኝ። መፍራት ሲያንስ ነው?  አቅጣጫ የለሹ ጦሮ እያስነካን ነው በጅዋጅዊት … መጥኒ እኛን ለፈጠረች እትብት። በዬዘመኑ አምልኮተ ነገራችን የጣዖታችን መበረከቱ … አይጣል ነው።

አንድን ድርጅት ወይንም አንድን ግለሰብ መውደድ፤ ማክበር፤ ማድነቅ፤ መደገፍ መብት ነው። መንቀፍም ሰብዕናን እስካልተዳፈረ ድርስ እሴታዊ ትሩፋቶችን እስከ አለገነጣጠልነው ድረስ የተገባ ነው። ይህ በግለሰብ ደረጃ ነው።

እስከ አሁን በኖርንበት ዘመን በማከብር፤ በማድነቅ እና በመቃወም፤ እንዲሁም በመውቀስ ጉዳይ ላይ መብት መሆኑ ቀርቶ የጦርነት ቀጠና ሆኗ ነው የኖረው 50 ዓመት ሙሉ። በቃ ሰብሰብ ማለት አውሊያችን አይወድለትም። ጥሎብን መካሳስ እና መገፈታተር ነው ስክነታችን … „አያጣልን ያቀላል ሰው“ አለች እሚታ ጽግሽ ... 

… አሁን ከዚያ ሸጎሪያም ቅርቃር ዘመን ወጥተን ተፈጥሯዊና ሰዋዊ መንፈስ ይሰፍናል የሚል ተስፋ ነበር። አብሶ እኔ ኢትዮጵያ አዲስ ዕድል አግኝታለች ብየ አምን ስለነበር ላመንኩበት እውነት ተግቻለሁኝ።

ያ ያመንኩበት እውነት አማራጭ በማጣት አልነበረም። የጥገናዊ ለውጡ መሪዎች የአገር ተስፋ የመሆን አቅማቸው ብቃቱን እና ሥነ - ምግባራቸው በወቅቱ  በአቀረቡት የሃሳብ ልቅና እምነት በመጣል፤ አብሶ ደፍሬ የመሰከርኩላቸው ጠ/ሚር አብይ አህመድ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚ/ር በነበሩበት ወቅት የነበራቸው አገራዊ ራዕይ፤ ትውልድን በቅን ሃሳብ ለመገንባት የነበራቸው ተነሳሽነት እጅግ የምማረክበት ስለነበር ዕድሉን ቢያገኙ ከኖርንበት ረግረግ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግሩናል የሚል ጽኑ ዕምነት ነበረኝ። ጠቅላላ የፍልስፋና ለውጥም የኖራል ብዬ አስብ ነበር። ሶሻሊዝምን የተጠዬፈ ሰዋዊ እና ተፈጥሯዊነት 
መንበር ላይ የማወል እድሉ ይኖር የሚል ሙሉ ተስፋም ነበረኝ። 

እኔ የደገፍኩት ቅን ሃሳባቸውን ብቻ ነበር። የትኛውንም ወገን ቅን ሃሳብ አለው ብዬ ሳስብ ቅን ሃሳቡን ደግፌ እሟገታለሁኝ። ቅን ነው ብዬ የማስበውን ሃሳብ ሞግተው የሚነሱትም ፊት ለፊት ወጥቼ እሞግታቸዋለሁኝ። እኔ ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ይሁን ግለሰብ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ወይንም ግንኙነት የለኝም። እምኖረው ገዳማዊ ህይወት ነው።

የእኔ የሙግት አስኳል ቅንነት እውነት እና ታማኝነት አለበት ላልኩት መንፈስ አቅም መመገብ ነው። ይህ እንግዲህ በማንፌስቶ አምላኪዎች የሚወደድ አቋም አይደለም።

 ለምሳሌ የግንቦት 7 ደጋፊዎች የኤኮኖሚ ሳይንቲስቱን ፕ/ ብርሃኑ ነጋ እንጂ የሚያራምዱትን ፖሊሲ አልቦሽ ጉዞ አይደለም የሚያከብሩት፤ የሚወዱት፤ የሚታገለሉለት።

ስለዚህ እርምጃቸው ቀነሰም ወደቀም ዘገጠም ሁልጊዜም መደገፍ አላባቸው ፕሮፌሰሩን። ማንም ዜጋ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አካሉ ወገኑ ደሙ እንደሆኑ ያምናል። እሳቸው በሚቀጠቀጡበት ጊዜም እኔ በቅንነት እርምጃቸውን ደግፌ ቆሜያለሁኝ። ሳንክ 
ሲገጥመው ቅንነቴ ደግሞ መታመን አልተጠበቀም ብዬ ሞግቻለሁኝ።

አንድ ደጋፊ አንድ የአንድ ሃሳብ አቀንቃኝ ግለሰቡን እንደ ሰው ማክበር መብቱ ነው። ሃሳቡ ከወደቀ ግን አብሮ ለመውደቅ መወሰን የተሰጠን ህሊና ለሌላ በጸጋ የማውረስ ፈሊጥ ነው።
ይህ ደግሞ አይደለም አገርን እራስንም አያድንም። 

አሁን የግንቦት 7 አባላት አማራጭ ሃሳብ የሌለውን ድርጅት ደግፈው ስለነበር በዚህ ኢትዮጵያ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት በምትፈልገበት ጊዜ አማራጭ የለም ከአብይወለማ ሌጋሲን ከመደገፍ ውጪ ነው የሚሉት።

ስለምን? ሲባል ፕ/ ብርሃኑ በእጃቸው ምንም የሃሳብ ልዕልና ብሎ ነገር ስሌላቸው አገር ውስጥ የነበረውን ሰማያዊን እራሱ አይሆኑ አድርገው ስለበተኑት የግድ ለደጋፊዎቻቸው መንፈስ መጠጊያ የአብይወለማወተከለ መንፈስ አዋጭ አድርገው አቅርበዋል። እሳቸው ማጣፊያው ስላጠራቸው ነው፤ ሌላው ግን ይህን መመርምር ይገባዋል። ሬሳ ሃሳብ ሰኔል እና ቹቻ እንጂ ሜዲቴሽን ስለማያስፈልገው። 

የጎንደር ጎጃም አማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ውርስነት ሲመጣም የሞገትነው ለዚህ ነበር። አንድ ደርጅት ባልተፈጠረበት ተፈጥሮ ውስጥ ጎልቶ የወጣን አዲስ አቅም ልወርስ ሲል ወራጅ አለ ማለት የተገባ ስለነበር። ቀድሞ ቢያቀነቅነው፤ ቢሟገትለት ምንም አይደለም ግን ደርሶ ዱብ ሲል ግን በህግ አምላክ ማለት ይገባ ስለነበር። ለነገሩ ሰማያዊ ፓርቲም ደርሶት ዋጥ አድርጎት ቁጭ ብሏል። 

እርግጥ ነው በሳቸው አይፈረደም። ምርጫ የላቸውም፤ መዳፋቸው ላይ አቅም የለም። እኔ አገር አትግቡ ብዬ በተናገርኩበት ወቅት ብደመጥ ኖሮ ቢያንስ አብይወለማወታከለወጃዋር ወንጉሡ መንፈስ ይህን ያክል አይፏልልም ነበር። "እርጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት" ይላሉ ጎንደሮች...  

የነፃነት ተጋድሎ ሸብልሎ ጠቅልሎ ያያዘው አውራው ፓርቲ ግንቦት 7 ነበር። አሁን እጁን ለእንሱ ሲሰጥ ተስፋኛው ሁሉ ማህል ቤት ቀረ። ልክ ቅንጅት ሲፈርስ እንደነበረው ነው አሁን ግንቦት 7 መራራ ስንብት ያደረገው። ታሪክ ራሱን ደገመ። ትናትም እሱው ዛሬም እሱው እራሱ በማንም አይመካኝ፤ በማንም ማለከክ አይቻልም። 

ሌላው ቀርቶ ሰማያዊ ቢኖር እንኳን ትንሽ መወላዳት ይቻልም ነበር። ግን ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ የተጠጉት ሁሉ እንደ ዕድል ሆኖ መፍረስ ነው። ይህ ስለምን ብሎ መጠዬቅ የለም። ከልጅነት እስከ እወቅት በርክቶ፤ አድጎ፤ አስብሎ፤ አቅም ሆኖ አሸንፎ የማይታይበትን ሁኔታ ማጥናት ይገባል። ስለምን? እዮር ይጠዬቅ። እኔ በምን አቅሜ?

የሚገረመው የተሻለ ሆኖ ለመውጣት በሚታተረው አብን ላይ የግንቦት ደጋፊዎች የሚለቁት ናዳ ደግሞ የሚገርም ራስን የመናድ ተግባር ነው። ምንም በሌለበት አውላላ ሜዳ ላይ ተሆኖ እንዴት የሚታትረው ድርጅት ላይ ተኩስ ይከፈታል። 

ኦነግ ስለምን አብን ጠመደው ብሎ ማሰብ ይገባል? ኦዴፓ ስለምን ባሌ ላይ ለዚህ ቀንበጥ ድርጅት ሰለማዊ ሰልፍ እስከማደረጃት ደረሰ ብሎ ማሰብ ይገባል?ማስተዋል አነሰን። 

ሁሉን አፍርሰን የቱ ላይ ተስፋ ይደረግ? በርጋታ ማሰብ ይገባል። ተጨማሪ የዞግ ድርጅት የጉራጌ እና የጋሞ ግንቦት 7 አገር ከገባ በ ኋዋላ የተቋቋሙ ናቸው። እነሱ አቅማቸው ገና ነው። ቢሆንም ነኪም፤ ከሳሽም፤ ወቃሽም፤ አሳዳጅም የለባቸውም። ህሊና ላለው ሰው ስለምን አብን ላይ ኦነጋውያን ሰፈሩ ብሎ ማሰብ ይገባል? አሁን ልጅ ፋሲል አንድ ጹሑፍ ጽፎ አንብቤያለሁኝ  ... ተሰሞናቱ ... 

መንግስት በኦነግ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ሊዋጥልኝ አልቻለም * (ፋሲል የኔዓለም)

አብን ከሳጅን በረከት መወደቅ ጋር አዋዶ ጽፎ ሞግቸዋለሁኝ። እና እናማ አቶ ወንድም ልጅ ፋሲል የእኔ አለም ጉራጌውን፤ የጋሞውን አዲሶችን ድርጅቶች ከማን ጋር ሊያዋደው ይሆን ብያለሁኝ ኮሽ ያላች ነገር አልተጠመደችም።

ፕ/ብርሃኑ ነጋ አብይወለማወተካለ ያሻግሩናል፤ አብይን አመንዋለሁኝ ብለው ባልደራስን ሲወነጅሉ ያልጻፈው ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ፤ እኒያ የግንቦት 7 አውራ የነበሩ አቶ ነአምን ዘለቀ ከድርጅቱ በፈቃዳቸው ሲለቁ አጀንዳው ያልነበረው ብዕር አሁን ስለ አነግ ይጽፍልናል።

ገፅ ገፅ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር / ብርሃኑ ነጋ ጋር የተደረገ ውይይት፡፡OBN መጋቢት 202011

ገፅ ገፅ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር / ብርሃኑ ነጋ ጋር የተደረገ ውይይት OBN 19 07 2011


አገራዊ ንቅናቄ ኦነግን ተሸክሞ ግንቦት 7 የኦነግን ሬሳዊ መንፈስን ከሞት አስነስቶ ለወግ ለማዕረግ ሲያበቃ ያልታቸ ነፍስ አሁን ሞጋች ሃሳብ አቅርቧል … እውነት የት ትጠጋ … ነው የእኔ ጉዳይ? ቅንነትን ታማኝነት የት ይደረሱ? እውነትን ወይንስ አዬር ላይ ያለን ተንሳፋፊ ባለ አንከሊስ ተስፋ ገር መወደቅን መቀበል የትኛው ይሆን ምርጫችን?

ቢመርም ለይቶ መደገፍ፤ አምርሮ መታገል የግድ ይገባል … ጦሩ ለሁሉም መሆን አለበት። ዛሬ ባለው መራራ ቀን ነገ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ማሰብ የሚገባው ድርጅቴ የሚሉት ግንቦት 7 ሁለመናው ለኦነግ መንፈስ ሲያስረክብ ከመደገፍ ፊት ለፊት ወጥቶ መሞገት ይገባ ነበር። 

መልካም ነገሮችን ከነወዛቸው እውቅና መስጠት ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፤ ነገር ግን „አብይን አምነዋለሁ“  ለአንድ ዕድሜ ልኩን በፖለቲካ ለቆዬ ሊሂቅ የሚመጥን አይደለም። 

ሌላው ቀርቶ ህግ ተጥሶ የመጣን ከንቲባ መርህ ተጣሰ ማለት ያባት ነው፤ ኑሮን ጥሎ ጫካ የገባ መንፈስ ነፃ ያወጣችሁን መንፈስ መታገል ብሎ ሲያቀርብ የ ኦዴፓ ጋዜጠኛ ፊት ለፊት አንተን ነፃ ያወጣህ የእኔ ተጋድሎ ነው ማለት ሲገባ በቸልታ ነው የታለፈው … ስንቱ ይነሳ …?

 ሰው በሰውነቱ ክቡር ፍጥረት ነው፤ ሊወቀስ ሊነቀስ ሊሞገስ የሚገባው ግን ከስብዕናው ለዬት አድርጎ አስተሳቡን ነጥሎ አውጥቶ መሆን ይገባው ነበር። የደገፈከው ሃሳብ መቃብር እዬቆፈረ እንዴት ትደገፈዋለህ? ስለምንስ አቅምህን ታፈስለታልህ? ቢያንስ ጉዞህ ትክክል አይደለም ማለት እንዴት ይሰናል …? ስንት ተስፋ ነው አሮ አፈር ትቢያ የላሰው … ? "ወይ ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽ?" እኮ ነው የሆነው። 

አካል አካልህን ሲያጎድለው እንዴት ዝም? ነገ ደግሞ በአዲስ ካባ ሌላ ትዕይንት ስለሚጠብቅ አቅም ለመበተን … መንፈስን አውላላ ሜዳ ላይ ለማትነን ሌላ ድራማ ይጠበቅ። መንገድ ላይ ለመተው … ለሞተልህ እንኳን ቆመህ ለመመሰከር ከተሰናህ አንተ ማነህ? እኔስ ማን ነኝ ማለት ይገባል …  

·       ብይወለማ ሌጋሲ …

አሁን ወደ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እና ወደ ጠ/ሚር ለማ መገርሳ ጉዳይ እንመጣ። እኔ ስደግፋቸው፤ ስሟገትላቸው ታማኝነታቸውን፤ ቅንነታቸውን፤ አውነታዊነታቸውን እንጂ እነሱን እንደ ሰብ ወገኔ አሉኝ አላሉኝ ብቻ ለእኔ ወገኖቼ ስለሆኑ ትናንትን፤ ዛሬም ወደፊትም እንደራሴ ሰው እቀበላቸዋለሁኝ። ጠማዳ መንግዳቸውን ግን እሞገትዋለሁኝ። 

ስለሆነም የመሰከርኩለት ቅንነት ታማኝነት እውነት ራሱን ችሎ መቆም ካልቻለ ግን ገና አማራጭ የለም ብዬ አቅም የማዋጣበት ከንቱ ህሊና የለኝም።

እሱቡት ወገኖቼ ከልብ ሆናችሁ፤ ከህሊናችሁ ሆናችሁ ሰው ሆነን ከተፈጠርንበት አምላካዊ ቃል ውስጥ ሆናችሁ ያ ሁሉ በግል በጋራ የተሰዋንለት የነፃነት ተጋድሎ፤ ያፈሰሰነው የመንፈስ ሃብት፤ ያዋጣናው ማዋለ ንዋይ ሁሉ ለኦነግ ስለመሸለሙ አይጎረብጣችሁምን? አያንገበግባችሁንም? ድልድይ አሻጋሪ ሆነው የቀረቡት እኛን መስለው ነው አብይወለማ መሬት ላይ ያለው እውነት ግን መግል ነው።  

ይሄ ግብር መዋለ መንፈስ፤ መዋለ ሃብት፤ መዋለ ሥነ - ልቦናዊ ብቻ አይደለም አገራችን ፈቅደን እያስረከብን ነው። አገር እንስረክብ ነው የፕ/ ብርሃኑ ነጋ አምላኪዎች የተሰለፉበት ረድፍ። አልገባቸውም። 

ፕ/ብርሃኑ ነጋ ሊደገፉ ሊከበሩ በሰብዕናቸው ቢገባም በሚፈልጉት ራዕይ ውድቀት ግን አብሮ ለመወደቅ አብሮ መሰለፍ ሰውኛ አይመሰለኝም።

አብይወለማታከለወጃዋር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የሚፈልጉበት ምክንያት ሌላ ምንም ሳይሆን የአማራን አቅም ወደ ኦነግ ባርነት እንዲያዘውሮላቸው ብቻ ነው። ማዬት እኮ ሩቅ ሳይኬድ ዶር ወርቅነህ ገበዬሁን እንዴት እንደ አሮጌ እንስራ ቂጥ አውልቀው እንደጣሏቸው ተመልከተናል። የፈለጉትን እስኪያሳኩ ድረስ እያባበሉ፤ እያሞጋገሱ ውደዱልኝ እያሉ አቅረበው ሲጋልቡ ባጅተው አሁን የሆነውን እያዬን ነው። 

እነሱ አቅደው በሚከውኑት ተውኔት ውስጥ እኛ ሳናቅድ ዘው ብለን አገር አልባነትን እያሟሟቅን ነው። እነሱ ከተነሱበት ዓላማ ቅስቅስ አይሉም። በፍጹም።  

ቀድሞ ነገር ግንቦት 7 ያህል በመንፈስ ልዕልና የነበረው ድርጅት ኢህአዴግ ባቋቋመው ኮሚሸን በመደበኛ ሠራተኛነት ለመሾም ማሰብ በራሱ እኮ ውደቀት እኮ ነው። ያን ጊዜ እኔ ጥሞና ላይ ስለነበርኩኝ አላዬሁትም። ስመጣ ድብልቅልቅ ብሏል።

ሥራ የሌላቸው ያድርጉት ለምሳሌ ዶር አረጋይ በርሄ ስድስት ሰው ማቀረብ የማይችሉት። ግንቦት 7 ግን እንዴት ይህን የኮሚሽን ሃላፊነት እሽ ብሎ ይቀበላል? እንዴት? እራሱን ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ አድርጎ ያፈረሰው ያን ዕለት ነበር።

ለምሳሌ ፕ/ብርሃኑ ነጋ የአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ የቦርድ አባል ቢሆኑ ለአካዳሚ ነፃነት የሚፈይዱት ፋይዳ ይኖራል የለት ዕለት ክትትልም አይጠይቅም። የራሱ የእኔ የሚለው ድርጅት ላለው ግን ራስን አፈርሶ ለኢህአዴግ ብርቱ ተወዳዳሪነት እና ቀጣይነት ውስጥን ከማራቆት ውጭ ምንም የሚፈይደው አይኖርም።

እነሱ የሚሠሩትን ስልት ቀድሞ መረዳት ይገባ ነበር እንደዛ ጠቅልሎ ገባሪ ከመሆን። ትልቁን ሚዲያ ኢሣትንም ያደረጉት እንደዛው ነው። ቆዩ በስልት የብሮድ ካስት 
ተንበርካኪ ይሆናል። ዕድሜውን ይስጣችሁ።

እኔ ከውጥኑም ስላለማረኝ የቆሞስ ኢንጂነር ሰመኜውን ሞት ሳዬው ያን ቀን በቃ ሁለመናው መልኩ ቀለሙ ድምጸቱ ምቱ እንደተቀዬረ ተረዳሁኝ። እናም ግንቦት 7
 ኢሳትም አገር ለመግባት አትጣደፉ ብዬ ጻፍኩኝ።

የሚያሳዝነው ነገር አቅም ሁሉ ተንጣፍጦ ካለ ቅድመ ሁኔታ ነው የገበረው። የሌላው 
ጥረት ሁሉ ተጠቃሎ እጅ እንዲሰጥ የተደረገው በግንቦት 7 ነው። አገራዊ ንቅናቄም 
ዕድሉን ቢያገኝ ኖሮ ከኦሮሞ ሊሂቃን ጋር አንዲት ስንዝር መራምድ አይቻልም … ነበር። 

ተመጣጣኝ አድርጎ መንፈስን፤ ድርጅትን አለማደራጀት ጉዳቱ ይኸው ነው። ቅንጅት ከተሰበረ በኋዋላ አብረው የነበሩት ሁሉ አይሆኑ ሆነው ነኩተው ቀሩ። አሁንም ግንቦት 7 ያመለከ መንፈስ ሁሉ መራራ ስንብት ነው ያደረገው።

ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያን በበላይነት እዬመራ ያለው የኦነግ መንፈስ ነው። 
መንፈሱ ደግሞ እዬተጋ ያለው ለኦሮሞ ሪፕብሊክ ነው። ለዚህ አቅም ማዋጣት እብደት ይመስለኛል። በ2030 ከሚወድቁት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አለችበት። ለዛ 
እዬተሠራ ነው። ቢያንስ ጠረኑን መርምሮ አቅጣጫ ለማስያዝ አለመጣር 
የሚያርመጠምጥ ጉዳይ ነው … የተሳሰተ መንገድ ላይ ሆኖ ተስፋን መጠበቅ የሞት
 መንገድ ነው ለእኔ ... 

የሚገርመው ለዚህ ግርባው ብአዴን፤ ቀዝቃው ደህዴን አብረው ቆማዋል። ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አገራቸውን በህጋዊ እውቅና ለሌላ አገራዊ ምስረታ እያስረከቡ ስለመሆኑ ልብ ሊሉት አልደፈሩትም። ህውሃት ኤርትራን አገር አድርጎ እንዳወጣው ሁሉ አብረው ተግተው እዬሠሩ ነው እነሱም ውስጣቸውን ለማስረከብ። ሻብያስ ደሙን ጠብ አድርጎ ታግሎ ነው ... ኦዴፓ ከሌላው የተለዬ ምን አድርጎ ነው? አብሶ ከብአዴን የተለዬ ምን ስላደረገ?

 ለመሆኑ አሁን አዬር ሃይሉስ? መከላከያውስ? ደህንነቱስ የማን ነው? ማነው የሚያዘው? በማን ሥር ነው? በዚህ ውስጥ የኤርትራ ድርሻ እስከምን ድረስ ነው? 
የራሷ ችግርም ቢኖርባትም እትጌ ኤርትራ? የመካከለኛው አፍሪካ ነገርስ፤ የአፍሪካ
 ቀንድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? የክርስትና ሃይማኖትስ ተስፋስ?

ለዚህ ምስቅልቅል አቅም ያለው መንፈሰ ጽኑ አቅም ከባልዳራስ ንቅናቄ ውጭ ማን አለ? እሱስ ማን ደጀን አለው ከፈጣሪ በስተቀር?

አብን ቀጣዩ የኦነግ ኢላማ ነው። ኦዴፓ ራሱ በስልት ያስከስማዋል። ግንቦት 7 ቢሆን ለመሰንጠቅ ዓይኑን አያሽም። ለዚህ የተሰጠው ነውና። ስለምን ቢባል ኢትዮጵያዊ 
መንፈሱ ሃይል ነውና። ያ መንፈስ ኦዴፓን ያብረከርከዋል። 

ምክንያቱም አገራዊ ምስረታውን ስለሚያደናቅፍበት። ለዚህም ነው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ቤተ- መንግሥት ሳይቀር በእስክንድር ንቅናቄ የተንዘፈዘፈው … በአንድ ወር ውስጥ ስንት ስብሰባ፤ ስንት ንግግር፤ ስንት ፓናል ዲስከሽን … ስንት መግለጫ ወጣ? በዚህ ውስጥ ዴሞክራሲ እና ቹቻው፤ ዴሞክራሲ እና ሰኔሉን እኔ አስተውላለሁኝ። ምርጫ እና እርግጫውንም። ዜግነትህ እየተበወዘ "አምነዋለሁ ያሻግረኛል?" 

ኦዴፓ ሦስት ቀጠና ላይ ዘመቻ ከፍቷል። አንደኛው ተረግጦ ብአዴንን የመግዛት ስለ ህወሃት ማንፌስቶ እንደ ተጋኸው ተረኛው እኔ ነኝ ስለ ኦሮማማም ትጋ ነው፤ ሁለተኛው ፊት ለፊት ተጋፍጦ የባልደራስን ንቅናቄ ሽባ ማስደረግ ነው፤ ሦስተኛው አብን ተርትሮ አቅሙን መበተን።

ይህ የቅድሚያ ኢላማው ሲሆን ጎን ለጎን ተረስታችሁ ነበር የሚባሉትን ክልሎችም በትህትና በአክብሮት በማማለል ማቅርብ። ከእነዚህ ውስጥ በዓይነ ቁራኛ የሚታዩት መንፈሳቸው ሰውኛ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ኡመር ይሆናሉ።

እስከ አገለገሉ በድርሳነ አለስልሴ ሞድ አበረው እሰከ ተፈለጉበት ቀን መጓዝ ይችላሉ፤ አፈነግጣለሁ ካሉ ደግሞ እንደ ቆሞስ ተስፋዬ ጌታቸው አይነት ይሆና ዕጣ ፈንታቸው። የሳቸው ለዬት ያለ ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና እና ሰብዕዊነት አምክንዮዋ ምልከታ ለአብይወለማ መንፈስ ምቹ አይደለም። ተወዳዳሪነታቸውም አይፈለገም። 

ቀደም ባለው ጊዜ እኔ "የጃኬታችን እናውልቅ" ፍልስፋና መንፈስ ተገዢ ስለነበርኩን ጠ/ሚር አብይ አህመድ የተለዬ ምልከታ ነው የነበረኝ። አሁን ግን እንደዛ አለመሆናቸውን እያዬሁ ነው። ሥልጣናቸውን ይወዱታል፤ ለመልቀቅም ዝግጁ አይደሉም። 

ለመተቸትም አይፈለጉም። የሚበልጣቸው ሊሂቅም አይፈልጉም። ወይ እኔ ተሳስቻለሁኝ በቀደመው ዕይታዬ ወይንም ደግሞ እሳቸው አዲስ ሰብዕና ጠ/ሚር ከሆኑ በዋኋላ ተላብሳዋል። የማውቃቸው አይነት አይደሉም አሁን። በቃ አዲስ ሰው ነው የሆኑት ...ያ ሳጠፋ ቆንጥጡኝ፤ ገስጽኙ ዛሬ ወንጀል ነው። ለዛውም ጦር የሚያሰብቅ ... ዕድለኞች አይደለንም እኛ ... ዕጣ ፈንታችን ጥቁር ነው። አንድ ጥቁር ጥበብ የጠቆረ...  

·       ተስፋ በማን እናድርግ?

እኔ ተስፋችን ፈጣሪያችን ነው ብዬ ነው እማምነው። ውጭ የሚገኘው ማህበረሰብ ግን ከሽብሸባ ወጥቶ መጪው ጊዜ ከኖርንበትም እጅግ የከፋ ስለሚሆን አንድ ነፍስ ያለው፤ ያረጀውን የፖለቲካ ድሪቷዊ መስመር የተጠዬፈ አንድ አሰባሳቢ የፖለቲካ ንቅናቄ መጀመር ያለበት ይመስለኛል።

ባለቤት አሁን ሁሉም የለውም። ኢህአዴግ ያን ያህል ማዕት እንዋርድበት የነበረው ግንባር እንኳን አሁን በአኃቲ መንፈስ የለም። በተናጠል አሁን ሃሳባቸውን የሚገልጹ ወገኖችም ቢሆንም ጸጥ የሚያደርግ መከራ ከፊት ለፊታቸው ይጠብቃቸዋል …

ስለዚህ እነ በርብሬ ቀንጥሱ ተስፈኞች እኛው አዬር አምላኪዎች ሳንሆን በተለይ ወጣቶች አንድ ነገር መፍጠር ያለባቸው ይመስለኛል። የድሪቶ ፖለቲካን ያለዛለ። ትናንት የህልውና ተጋድሎው የአማራ ነበር አሁን የኢትዮጵያ የህልውና ተጋድሎ እጅግ ድቅድቅ ከሆነ ጨለማ ውስጥ ነው ያለው። ለዚህ ባለቤት ያስፈልገዋል።

ይህ እከሌን አትንኩብኝ ነገር ቆሞ እውነት በሆነው ጉዳይ ላይ አብሮ መቆም ያስፈልጋል። የለንደኑ የአትታላንታው ጉባኤ ነው አሁን ዕውን እዬሆነ ያለው …

መራራ ነው ግን መራራውን ተቀብሎ ቀጣዩን መራራ ነገር መጋፈጥ ግድ ይላል … በወደቀው ላይ አቅም ከማፍሰስ፤ ነፍስ ያላቸውን ነፍሶችን በመደገፍ አቅም አዋጥቶ መደገፍ ይገባል። ቢያንስ መሸነፋችን መቀበል። የእውነት ተሸንፈናልን።

ከእንግዲህ ግንቦት 7 ደግሞ ሊነሳ አይችልም። ደግሞም ይበቃዋል። ስንት መንፈስ አሳልፎ እንደሰጠ፤ ስንት መንፈስ እንዳቃጠለ እሱም ያውቀዋል እኛም አሳምረን እንውቀዋለን። እሱ ይቀጥል በጀመረው የቤተ መንግሥት ቅልቅል እና ግጥግጡን ያስነካው። እኛም ቢያንስ ጤነኝነታችን ላለማስወርስ እንትጋ። 

አምልኮተ ፕ/ብርሃኑ ነጋን የአብረን እንስመጥ አደንዝዜ ፈለግ ትቶ አዲስ መስመር እና አዲስ እሳቤን መከተል ይገባል። ከማንም ከምንም ንክኪ የሌለው። ለነገሩ ግንቦት 7 አመለኛ ድርጅት ስለሆነ ውጭ አገር አንድ አቅም አለው የተባለ ነገር ከተከሰት እዛም ዘው ማለቱ አይቀሬ ነው … ወይ ጸጥ ወይ ሲጥ ወይ ላጥ ለማድረግ። የሆነ አንዳች ነገር አለበትና … እናስተውል፤ 

ከሁሉ በፊት ኢትዮጵያ ነበረች ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት በፊት። የሚበልጥብን እንወቅ። አገር ነው ጌጥ። አገር ነው ህልውና እንጂ ግለሰብ አይደለም። ወይንም ኢጎ አይደለም።

·       ለማጠቃለል።

ቅንነትን፤ ታማኝነት፤ እውነትን ብቻ ደግፎ መቆም ነው አላዛሯን ኢትዮጵያ መታደግ የሚችለው … ኦነግ አገራዊ ሪፕብሊክ ሲመሰረት ዝም እንበል፤ ጊዜ ይሰጠውም ሆነ አቅም እናዋጣ የሞት ታናሽ ወንድም ነው። አታጋይ ሞቶ እንኳን አሁን የለንም። ወና ላይ ነን ያለነው። በር የለሽ ቤት። ነፃነት እኮ የመኖር ማኖር ነው። የሰብ መኖር ነው አገር መኖርን የሚያስገኘው።

ሰውንም ለመውረስ ለተነሳ ድውይ መንፈስ ተኝተህ በለኝ የተገባ አይደለም። ወንበሩ ባዶ ነው። በባዶ ወንበር ላይ ያለው መንፈስ ደግሞ ለአገራዊ ራዕይ አቅሙ ባዶ ነው። እኛ የማናውቀው ብቻ ሳይሆን የግንባሩ ቁልፍ ሰዎች የማያውቁት የውስጥ ድርድር አለ።

ራሱ የም/ጠ/ሚሩ የአቶ ደመቀ መኮነን ድርሻን እሰቡት ወና እኮ ነው … መንፈሱ ተጠልፏል ያልኩት ሐምሌ ላይ ነበር። ያው የፕ/ አለማርያም „አክ ወሬ“ አደበዘዘው እንጂ ሙግቴን።

ከዚህ ቀደም አነሰም በዛም ለነፃነት ተጋድሎ ያደረጉ ወገኖቻችን አክብረን ግን ከአገር በላይ ምንም ነገር ስሌለ ኢትዮጵያን የማስረከቡ ድንዝንነት ግን ወደ ደመ ሞቃትነት ተሻግሮ፤ አማራጮችን ማዬት ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል ….

እንደ እኔ የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ኢትዮጵያ ቢገባ ደስ ይለኛል። ይህን ማለት ከጀመርኩኝ ቆዬሁኝ። መከላከያው የማን፤ ደህንነቱ የማን፤ አዬር ሃይሉ የማን፤ ፖሊሱ የማን ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።

ከኦነግ መንፈስ የሚጠበቅ ብጣቂ የነፃነት ተስፋ የለም …  ዶር ብርሃነመስቀል አበበ እኮ ነግረውናል ‚አብይ የኦነግ ወራሽ ነው ብለው‘ አዚም ስላለብን፤ ስለተደገመብን አናስተውለውም እንጂ።

እኔ እንዲያውም በህልሜ ስለማምን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ስሜን አሜሪካ ሲጓዙ ነበር ወንበሩ ባዶ ሆኖ ያዬሁት፤ ሌላ ጊዜ ወንበሩ ጠርዝ ላይ ሆኖ ደግሞ አዬሁት። እና እሳቸውን በቅደመ ሁኔታ ያገተ መንፈስ አለ የሚል ለረጅም ጊዜ እምነት ነበረኝ።
አሁን አሁን ብስጭታቸውን ሳዬው ግን እሳቸውም የተጠላፊውም የተጠለፈውም መንፈስ ቤተኛ ሆነው ነው ያገኘኋዋቸው።

ይህ የሚወርፉት ነገር እጅግ ይገርመኛል። ድርጀታቸው የሚያወጣው እግር እጅ የለሽ መግለጫ የማስተባበሉ መደራራብ ጉዳይ ሳዬው ዪሚያምኑበትን ነገር እንደሚያደርጉ ነው እኔ እማስበው … እንዳዬሁት ማደመጥም አይወዱም። ራሳቸውን ወይንም ቤተኞቻቸውን ብቻ ነው የሚያደምጡት። ኮከባቸው ንጉሥ ነው። ንጉሥ ኮከቦች ደግሞ እንዲህ ናቸው። 

በፊት እሳቸውን ነፃ የማውጣት አንድ አገራዊ ንቅናቄ ቢኖር እል ነበር፤ አንድ ሰውር መንፈስ አግቶታል መልካሙን ራዕአቸውን ብዬ በጽኑ አምን ስለነበር፤ አሁን ግን ከቶውንም አልልም … ለመታመን በቃል ውስጥ ያለ የሰናፍጭ ታክል ተግባር የሰውን ህሊና የመግዛት አቅም አለውና።

ሌላው በግንቦት 7 እጸዬፈው የነበረው ነገር ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን እያደኑ ቤተኛ የማድረጉም ነገር ሌላው ስውር መከራ ሆኖ አግኝቻዋለሁኝ። እሳቸውም መደበኛ ሥራቸው አድርገውታል። ሚዲያውን ለመቆጣጣር ያላቸው ጥበብ እና ጉዞ ርቀቱንም፤ መጠኑንም መለካት አይቻልም። ስለዚህ ትግሉ ከፍ ያለ ነው ማለት ነው።

 https://www.youtube.com/watch?v=Vu8q4uIViLI&t=32s


አሥራት ስሞታ:- በአዲስ አበባ ለ አንድ ወገን መታወቂያ እየታደለ ነው በሚል 

ለሚዲያ መረጃ ሰጠሃል ተብሎ የተባረረው ወጣት አመራር አየለ ነጋሽ

ብቻ መንፈሴን ለማቀራረብ አሁን ካለው ሂደት ጋር … መቋሚያዊ ቦታ አጥቸአለሁኝ። ስለዚህም እፈራለሁኝ። ስለ አገሬም አንደለመደበኝ ውስጤ ይንገበገባል … ኢትዮጵያ ለእኔ በአሁኑ ሰ ዓት ሁነኛ ሰው አላገኘችም። አዲስ አባባ አግኝታለች የባልደራስ ንቅናቄ ቤተኞችን አላዛሯ ኢትዮጵያ ግን ሱባኤ ላይ ናት … እንደ ቀደመው ሁሉ። ሐሤቴ እና ሰናዬ ደግሞ ትናት ላይ ትኬት ሊቆርጥ እንደሄደ አልተመለሰ ... ሲመለስ እንገራችሁ አለሁኝ ... መልካም የውሳኔ ጊዜ ...



ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።