የፋክት #ፍልሰት #በፍድሰት።
መጥኒ ላንች ማህፀንሽ ማገዶነቱ አባርቶ ለማያውቀው ገራገሯ የአማራ እናት።
ከዬት እንደምጀምር አላውቅም። ሰሞኑን ዶር ዳኛቸው አሰፋ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በሚመለከት የራሳቸውን ዕይታ አቅርበዋል። በህዝቡ መንፈስ ውስጥ እራፊ መሬት ካገኙ ጊዜ ይዳኜው። እንደ እኔ ግን ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ የተመሰጡበት ዴሞክራሲያዊ አቋም የፋክት ፍልሰት እና ፍድሰት ሆኖ ነው ያገኜሁት። ይህን ያህል ከገዢው ድርጅት " ከብልጽግና" መንግሥት ጋር መተማመኑ ካለ ስለምን ባጀት አይለቀቅላችሁም????
ዶር ዳኛቸው አሰፋ በንግግራቸው ውስጥ ብዙ የማያውቁትን ማብራሪያ ሲሰጡ ሰምቻለሁኝ። ከዚህ ቀደምም። እሳቸው ያልፈፁምትን፤ ወይንም ያላስፈፀሙትን ጉዳይ እንደ ፍልስፍና ሙሁርነታቸው እንደዛ ደፍረው ሲናገሩ ገረመኝ። "አወዛጋቢ ቦታወች" የደቡብ አፍሪካ ስምምነት ያመነጨው ነው።
" ምዕራብ ትግራይ" የሚለው ግን ጥቅምት 2022 ስምምነቱ ተከናውኖ፤ እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ከተከበሩ አንባሳደር ማይ ሃመር ኤክስ ገፃቸው ላይ ሄደው ይፈትሹ። ይህም ብቻ አይደለም የኤርትራ መንግሥት እንደ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መንግሥት፤ ህወሃት እንደ ክልል ባልተጠዬቁበት ሦስት ወንጀል የአማራ ልዩ፤ ኃይል፤ ፋኖ፤ እና የአማራ ሚሊሻ በሦስት ጣምራ ወንጀል ነበር ሲከሰስ እማዳምጠው። ከቦታው ስላልነበርኩ ዕውነቱን ማወቅ አልችልም።
በሰው ልጅ ላይ ግፍ የፈፀመ መጠዬቅ ግድ ነው። ማንም ይሁን ማን። ተጣርቶ ብዬን ከተሰጠበት። ግን ሁለቱም መንግሥታት እና ህወሃት በጦር ወንጀል ብቻ ሲከሰሱ ዬአማራ ፀጥታ ኃይል ግን #በሦስት ወንጀል ተከሳሽ ነበር። ይህስ እንደምን ቆመ? ጥያቄው ለፈላስፋው ዶር ዳኛቸው አሰፋ የቀረበ ጥያቄ ነው። የሽግግር ፍትህ የሚባለው ጠፍቶኝ አይደለም፦ የሰለጠኑት አገሮች #ተስፋ እንደሚያደርጉበት አውቃለሁኝ።
የሆነ ሆኖ ብዙ ክስተቶች እንደምን መልክ እንደሚይዙ ፈጣሪ ያውቀዋል። ስኬትም ከሆነ ዕድሉን ለእግዚአብሄር መስጠት ይገባል። ከዚህ በላይ በሳቸው ጉዳይ እምለው አይኖረኝም።
የፍልስፍና ሊቁ ዶር አንባቸው መኮነን እሳቸው የገለፁት ዕውነት ከሆነ #አማራነትም ሆነ #ጎንደሬነትን ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ በገብያ ህግ እንዲተዳደር እንደሚፈቅዱ ተገልፆል። #መራራ ነበር። #ከርቤ ነበር። #ሬትም ነበር ለእኔ? ያንገሸግሻል፤ ያአንገፈግፋልም። ከቶ የአልባንያን ዴሞክራሲ እንጠብቅ ይሆን?
ከቀን አንድ ጀምሮ ድካሜን አውቀዋለሁኝ እኔ በግሌ። መላ የጎንደር እና #የጎጃም ህዝብ ውሃ ሳይሆን #ደም ገብሮበታል። #መኖሩን ሰጥቶበታል። #ነፍሱን ሳይሳሳ ለግሦበታል። ያ " #ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ " የባሩድ ስንቅ ላደረገው ለሰማዕቱ አቤ እና መሰል ሰማዕታትን ከፈጣሪ ጋር በዲሞክራሲ አግባብ ተነጋግረው እስኪ ያስመልሱልን ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ። የኮነሬል ደመቀ ዘውዱ ዴሞክራሲ ከዬትኛው ፖለቲካዊ ርስተ ጉልት ተነሳ? ይህ ብልጠት ወይንስ ሽንገላ? አልቦሽ ስልጣኔ ነው የሆነብኝ።
አይደለም #ዴሞክራሲ ፌድራሊዝም ከአማራ ክልል ውጪ የት ላይ ይሆን ያለው? ኢትዮጵያ ውስጥ በህልምስ ቢሆን ዴሞክራሲ አለን? ዕንኳንስ በውን? ብዙ ነገር አደምጣለሁኝ። ግን የኮነሬሉ ስክነት፤ የከፈሉትን መስዋዕትነት አስቤ ዝም ብዬ ነው የኖርኩትኝ። የተረጋጋ መንፈሳቸውን አዳምጣለሁኝ። ይህ ደግሞ ለትውልድ መልካም አብነት ነው ብዬ አስባለሁ። አቅል የለሽ ሰብዕና የብዙ ግድፈት እና ኪሳራ መሰረት ስለመሆኑ ጠንቅቄ አውቃለሁኝ።
የዛ ሁሉ አማራ ስቃይ #ካሳውን ማን ያወራርደው???? በቃ ሰማዕትነት ፍስስ?
"እኛጎንደሬ ነን። አማራ ነን ብለናል።" "ይህን ከዚህ ውጪ ሃሳብ ያለውንም እናስተናግዳለን?።" ምን ማለት ይሆን ይህ #ዝርግ ድንቡልቡል አዲስ ቅኝታዊ ሃሳብ???። እሳቸው ታሥረው ለሳቸው ሲል አፈር የሆኑ ነበሩ። ከፊታቸው ላይ የተሰው።
እንደ ክርስቶስ። ከጎጃም ከሽዋ ሳይቀር እስር ቤት እዬሄዱ ይጠይቋቸው የነበሩ የአማራ ልጆች ነበሩ። ከእስር ሲለቀቁም የወል ደስታው ግሎባል ነበር። ለዛ የተበቃው በዊዝደም ነበር። በስልት እና በጥበብ በጨመተ እዮራዊ፥ ፈጣሪ የሰራው ታምርም - ትንግርትም ነበር። እራሱ ህወሃትም የደነገጠበት፤፦ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም ዱብ ዕዳ ነበር።
#ከሀምሌ 5ቱ የጎንደር ሆነ ከቄሮ የግንጫ ተጋድሎ በፊት 500 የጎንደር ወጣቶች ተመሳሳይ ቲ ሸርት አሰርተው "#የፈራ ይመለስ" በሚል ንቅናቄ ጀምረው ነበር። እነኛ ወጣቶች ብዙ ፈፈተናን ነበር ያስተናገዱት። ያ ቀዬ ብዙ እጅግ በደል የደረሰበት ነው በዬዘመኑ። የእኔ ትውልድም። ከፋኝ የሚለው ሁሉ ወደ ዛ እናት ሆዱ ባድማ ይተማል።
በርደኑን የጎንደር ትውልድ ይሸከማል። ይህም ሆኖ አንድም ፖለቲከኛ ቀን የሚወጣውን ህዝብ እግዚአብሄር ይስጥልኝ ብሎ አያውቅም። አሁንም እነ ኮነሬል ደመቀ ያን ውርስ ያደረጉት ይመስለኛል። ምን ሲባል ይህን መሰል #ስንጥር ሃሳብ በህሊና ይፈጠራል?????
ከዚያ በኋላ ሙሉ #ጎጃምም ሳያቅማማ ከጎናቸው ተሰለፈ። "ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ" ብዙ ሰማዕታት ተገበሩበት።
ከጎንደር እና ከጎጃም ብቻ 20 ሺህ የአማራ ወጣቶች ጣና በለስ ታሰሩ። በማታ ማታ ድብደባ ብዙ ወጣቶች እዬተሰው ሌሊት ቀብር እንደሚደረግ በወቅቱ መረጃ ይወጣ ነበር። ቁጥሩ ዝበት ሊኖርበት ቢችልም ጉዳቱ ግን ሰፊ ነበር። ይህም ብቻ አይደለም በዬሰልፋ በአደባባይ ህዝባችን ደሙን ገበረበት። ግልምጫው፤ ከሥራ መባረሩ፤ ስጋቱ ወቅቱ ስላለፈ ተረስቶ ይሆናል። አንዲት መነኩሲት ባህርዳር ላይ የስናይፐር ሰለባ ሆነው ነበር። ፎቷቸው አለኝ ቆስለው ደማቸው ሲያዘራ። ደብረታቦር እና ጎንደር የቅዳሜ ገብያወች ነደዱ።
ይህ ብቻ አይደለም በወልቃይት ጠገዴ የነበረው #መገፋት የገፋቸው ወገኖች ጎንደር በዬቤተሰቡ መኖርን ለማስቀጠል ሲሹ አባ ቅንዬ ጎንደሬ ሁሉንም ሁኖላቸዋል። በዬቤተሰቡ ብዙ በጣም ብዙ የተከደነ ታሪክ አለ። ጎንደር ጥቁር የለበው ህወሃት በገዛበት ዘመን ሁሉ ነበር። ህወሃት መንበሩን ሲለቅም አምስት ሊቃናቱን ጎንደር ገብሯል ኢንጂነር ስመኜውን ጨምሮ።
በግሎባል ደረጃ ሰፊ የሆነ የህሊና፤ የሞራል ተግባር በትጋት በቅንነት፤ በልግሥና ተከውኗል። በተለይ #የጎጃም ህዝብ ጨርቅ፤ ወርቅ አይደለም የገበረው #ልጁን፤ #ትዳሩን፤ ተስፋውን፤ መኖሩን ነው። አንድ ቀን እግዚአብሄር ይስጥልኝ ተብሎ ጎጃም አያውቅም። የሚገርመው ለአማራ ወገኑ ሲል ፈቅዶ እና ወዶ በባሩድ ለነደደ፤ የካቴና ስንቅ ለሆነ ቅን ህዝብ ዛሬ #በዴሞክራሲ¡¡¡¿¿ ወልቃይቴ የፈለገውን ይወስን ዘንድ ለሁሉም እንሰጣለን ኮነሬድ ደመቀ ዘውዱ ማለታቸውን በአንድአፍታ ሚዲያ ዶር ዳኛቸው አሰፋ ነገሩኝ። እሳቸውድንቅ ብለው ተደስተውበታልም። ማህከነ።
#ማንነት በገብያ ህግ አይተዳደርም። ማንነት ሸቀጥ አይደለም።
ይህን የፃፍኩት የዛሬ 10 ዓመት ነው።የሆነ ሆኖ በሃሳቡ እኔ እንደተረዳሁት ህወሃት ጽንሱን ከጀመረበት እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በግልጽም በስውርም የተሰዋው የአማራ ወገን ለኮነሬል ደመቀ የልብስ ጥለት ያህል ዋጋ አልተሰጠውም። ዕውነትን የመሰከሩ የትግራይ ወገኖቻችንም ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል። ኮነሬል ደመቀ ከሱቅ ተሂዶ የሰው ልጅ ነፍስ፤ ትርታ የመገዛት ያህል ነው ያዩት። ምንም አልመሰላቸውም። ከእሬት የመረረ፤ ከከርቤ የጎመዘዘ የፋክት ፍልሰት ነው የሆነው። ፋክት ለእኔ ተሰዷል ማለት ይቻላል። ፍቀትም ነው።
ጎንደሬወች ሲተርቱ "አያ ጅቦ ሳታማህኝ ብላኝ ይላሉ።" እንዲህ ዓይነት ውሎ ጉዞ የለሽ ገጠመኞቻቸውን ጎንደሬወጅ " እንኳን ሲሸጡኝ ሲስማኙ አውቃለሁኝ።" ሲሉም ያክሉበታል። ምን እዬተዶለተ እንደ ሆን ይገባናል። ማጭበርበር በገንዘብ ባይገም እስቲ ይሁን። ወንጀል ቢሆንም።
የሚሊዮኖች መገበር ጊዚያቸውን፤ ጉልበታቸውን፤ መዋዕለ ንዋያቸውን፤ ነፍሳቸውን፤ የመውለድ ተስፋቸውን የገበሩት ይህን ለመሰለ የሽንገላ ትዕይንት ነበርን? እስኪ ቀየ መሬት ተናገሪው። ስንትሰውቅራኔ ውስጥ ተማገደ? ስንቱ በበቀል ተቀቀለ? ስንቱተሰደደበት? ስንቱ ባህር በልቶት ቀረ???
እጅግ አከብራቸው የነበሩት ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ በህይወት ቆመው እንዲህ ከ35 ሚሊዮን በላይ የሆነውን የአማራ ህዝብ ክህደት መፈፀማቸውን እንኳንም አዬን። ትንፋሻቸው ቀጥሎ ይካዱን። ይጨክኑብን። ባንማርበትም። የጎንደር ሰው፤ ጅል፤ ጅላጅል፤ ጅል አንፎ ይላል። ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነገር ሲገጥመው።
ጎንደሬውም መላ የአማራ ህዝብን ዲካው በማይለካ ሁኔታ ክህደት ብቻ ሳይሆን ጭካኔም ተፈጽሞበታል ብዬ አስባለሁ። ዱላው በፋስም ነው። መንፈስን ቅጥቅጥ ነው ያደረጉት ኮነሬል ደመቀ ዘውዱ። የቅኔው ጎጃም ውለታ እንዲህ ፍስስስስ። ካለ ጎጃሜ ጥረተም ምኞቱም መና ነበር የሚቀረው። የብረት መዝጊያ የሆነውያ ጥበብህዝብ ነው።
በሌላበኩል ኮነሬሉን ያ ድምቅ፤ እብብ፤ እምር ብሎ አክብሮ ያስከበራቸው፤ ተናግረው እስኪጨርሱ ቀጥ ብሎ ቁሞ የሰንደቅ ዓላማ ጃኖ ዘርግቶ ፍቅሩን በገፍ ላፈሰሰ የጎንደር ህዝብ መጥኔ ለአንተ ልል እሻለሁኝ። አመድ አፋሽ።
ጠሚር አብይ አህመድ አሊ እንዲህ ከአማራ ልብ መውጣታቸውን ኮነሬሉ ሲውቁ አሸኛኘቱን ያሳምሩታል። የተካኑ ናቸው። ኮሽታ፤ ድለቃ በሳቸው ቤት የለም። እለፍ ይላሉ። መመልመሉን ካስተዋሉ እንደሚሆን ያደርጉታል። ፖሊሳቸውም ይመስለኛል። ከአንድ ቀን ውጪ በአካልም የተገናኙ አይመስለኝም። ራቅ አድርገው ነው የሚከታተሏቸው።
እኔ ለኮነሬል ደመቀዘውዱ ለቀጣይ ህይወታቸው በብዙ ሁኔታ ሳስብ ነው የኖርኩት። ብቅ ያለ አቅም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይ በዚህ አሳቻ ዘመን ምን ሊገጥመው እንደሚችል ስለተረዳሁኝ። በተለይ ለተባዕት ፖለቲከኛ።
ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተደከመበት፤ ብዙም ለስኬት የበቁ ህብረ አመክንዮች ባሉበት የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ እንደዚህ በቀንዲሎቹ ልውስውስ፤ ልፍስፍስ ሲል ማዬት ለቀጣዩም የትግል ዘርፍ ማህበረ ቅንነት ማስተዋል እንዳለባቸው በትህትና አሳስባለሁኝ። ጀግና የማይበረክትለት ትውልድ ነው እና። ለነገሩ እኔ ልብሰጥቶኝ በብዙ ጉዳዮች በጥንቃቄ ነውየምሳተፈው በብዕሬ።
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎን ከውስጡ የተቀበለው ቅን እና ቀና የጎጃም ህዝብ ከለውጡ በኋላ ቢዘናጋ ኖሮ የአማራ አጀንዳነት የዶግ አመድ ሆኖ ነበር። ውጭ የሚኖሩ ስኩን፤ ጭምት የጎጃም ሊቀ - ሊቃውንት በእርጋታ በመራመድ ተጋድሎውን በጨዋነት እና በቁጥብነት በጥንቃቄ እዚህ ደረጃ አድርሰውታል።
የጎጃም ሊቀ - ሊቃውንታት፤ ሊሂቃኑ ልባሞች ናቸው። ችኩል አይደሉም። አቅል አላቸው። አቅማቸውም ሙሉዑ ነው። ጠሚ አብይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሳይክለፈለፋ የመንፈስ ትጥቃቸውን ሳይፈቱ፤ ሳይዘናጉም በተደራጀ አቅም ተጋድሎውን ያስቀጠሉ አኩሪ ኮከብ ናቸው። አቶ አቻምዬለህ ታምሩ ስለወልቃይት ጠገዴ፤ ፕ/ ዶር ሃብታሙ ተገኜ በራራን ጥናታዊ በሆነ ሁኔታ መጽሐፍ ጽፈዋል። ለአማራ ህዝብ ማኒፌስቶ ከዚህ በላይም የለም። ቢጠና - ቢሠራበት።
የጎጃም ህዝብም በዬጊዜው ቋሚ እና ጠንካራ የአደባባይ ሰልፍ በማድረግ የአማራ ህዝብ ተጋድሎ የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆን ትርታ ሆኗል። የጎጃም አማራ ሊቀ - ሊቃውንታት እንደ ሌሎቻችን አገር ገብቶ ቤተሰብ ማዬት ይሹ ነበር። ግን አላደረጉትም። ለደቂቃ "ከመደመር" ሂደት ጋር አልተገናኙም። ጠንክረው በሃሳብ ሲሞግቱ ነው የነበረው። ጭምቱ ዶር ሰማህኝ ጋሹን ጨምሮ። ልቅና እና ልዕልናቸው በአደብ እና በጨዋነት ነው የሚያስተናግዱት። ለእኔ ዕውነቶች ናቸው።
ለመሆኑ ኮሌ ደመቀ ዘውዱ ሰሞኑን ሠራሽ ዴሞክራሲያቸው የአርበኛ ጎቤ ነፍስ ሰላም ትሰጠወት ይሆን???? እንደዛ ብር ብሎ ቤቱን፤ ትዳሩን ልጆቹን በትኖ ጥቃት ላወጣ ጀግና፤ ለደም መላሽ ወንድም መልሰወት ምን ይሆን???? ልጃቸውም አሁንም እዬታገለ ነው። ወላጅ እናታቸው እንደ አዘኑ አለፋ። የሁላችንም ወላጆች ለዓይነ ሥጋ ሳንበቃ ነው መራራ ስንብት የሆነው። ዋጋም፤ ተመንም ሊወጣለት ለማይችለው ግብር እንዲህ እና እንዲያ ሲሆን ዘመን ይዳኜው።
ኮነሬልደመቀ ዘውዱ ሆይ!
በጣም ብዙ የአማራ ወጣት ተምሳሌው አድርጎ፦ በመንፈሱ ፈቅዶ እና ወዶ ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ዘበኛ ለሆነወት ምን መልስ ይሰጡት ይሆን? አዲስ አበባ እንደሰነበቱ ሰምቻለሁኝ?
የመልስ ጉዞው በቀጥታ ከአዲስአበባ ሰቲት ይሆን ይሆን? የጎንደሬ አማራ አክባሪወቸወትን ዓይንስ እንደምን ያዩ ይሆን??? ለዘመን የሚቀር፤ የሚተርፍ ዕውነትስ በእርስወ ዘመን ምን ይኖር ይሆን??? ለለበጣ ነበርን ያ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴያችሁ በኽረ አታጋይ ጥያቄያችሁ???
በዬትኛው የይቅርታ ዓይነት ከተጋድሎው መንፈስ ጋር መልሰው ይገናኙ ይሆን? ነገረ ጎንደር ሲቀበል እንጂ ከውስጡ ሲያርቅ በብልህነት ነው። ግብረ ምላሹን አብረን እምናዬው ይሆናል። ቂም፤ ቅሬታ የለብኝም። በጭራሽ። ያን ሳደርግ ምርቃቴን እዮር ያለ ይግባኝ እንደሚያነሳው አውቃለሁኝ። በዬትኛውም የትግል ዘርፍ ጠንቃቃነቴን እንዳመልከው ጥሩ ዕድል ስለሰጡኝ አመሰግነወታለሁኝ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። ሳናውቃችሁ የተገበርንበት፥ የተቀቀልንበት ዘመን የቆጥ የበረከት ይሁን። አሜን። ከእንግዲህ ግን አይደገምም።
"ልብ ያለው ሸብ።"
"ሙያ በልብ" እንደ ይትባህላችን - ይፈቀድለታል።
ማህበረ ቅንነት ደህና እደሩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን ቸር እንሁን።
ቅን አስበን ቀና እንሁን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15/10/2024
ፍቅር ሲያልቅ፦ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥትም፦ ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ