#የአማራን ልጅ #ስለኢትዮጵያዊነት #ለማስተማር ማሰቡ እራሱ #የውርንጫ ድካም ነው። #መቅኗችን ኢትዮጵያችን ናት።

 

#መቅኗችን ኢትዮጵያችን ናት።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን። 
 
 
 No photo description available.
 
ክብሮቼ እንዴት አላችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። የአማራ ወላጅ #ዶክትሬኑ #ኢትዮጵያዊነት ነው። የትኛውም ቦታ አማራ ልጁን ሲያሳድግ ደቡብ ይሁን ሰሜን። ስሜን ይሁን ምዕራብ። ምዕራብ ይሁን ምስራቅ ስለፈላስፊት ኢትዮጵያ ቅንነት #መቅኗችን፤ ካልሽየሙ አድርጎ፤ መልቲ ቫይታሚኑ፤ ፕሮቲኑ፤ ሚኒራሉ፤ ንጥረ ነገሩ አድርጎ ነው ልጁን በኢትዮጵያኒዝም የከበረ ልዑቅ በራስ የመተማመን ተፈጥሯዊ ሙሉ አቅም እና ክህሎት አንፆ የሚያሳድገው። የአማራ ህዝብ በመላ ኢትዮጵያ በተለይ በከተሞች በስፋት ይገኛል። መገኜቱ ብቻ አይደለም፤ አብሮነቱን በጋብቻው፤ በቁቡ፤ በእድሩ፤ በቤተ አምልኮ ባዕቱ፤ በሥራ እና በመኖሪያው ሁሉ በተባ ኢትዮጵያዊነት አለምልሞ ነው የሚኖረው። ተጋብቶ ተዋልዶ። ተዛምዶ ተጎራብቶ። ተዋህዶ ተስማምቶ። 
 
አሁን ከሆነም ውጭ አገርም በብዛት የአማራ ልጅ ይኖራል። የትም ይሁን የትም የአማራ ቅን ወላጅ የቅንነቱ መሠረት የሆነችውን ዩንቨርስ እናቱን ኢትዮጵያን የውስጥነቱ መገለጫ አድርጎ አስጠንቶ ነው የሚያሳድገው። ለዚህ እኮ ነው "የአማራ ……… ብሎ" ተደራጅቶ ኢትዮጵያዊነቱ ነግስ፤ የተነሳበትን ተልዕኮ ሳስቶ የሚታየው። ኢትዮጵያዊነት ለአማራ ህዝብ #እንደሬሰው ነው። ካፒቴኑ ነው። #የኖህ መርከቡም ነው። ይህ እንደ ባቢሎን ግንብ የሚናድ አይደለም። የታነጸበት ንጥረ ነገሩ ነው።
 
እና ኢትዮጵያዊነትን ለአማራ ህዝብ ለማስተማር ማሰቡ በራሱ #የውርንጫ ድካም ነው ያልኩት ለዛ ነው። የአማራ ልጅ እናቱን ክብርት ኢትዮጵያን አቂሞ፤ ውዲት ኢትዮጵያን አኩርፎ፤ እማማ ኢትዮጵያን ቂም ቋጥሮባት እንዲያድግ ፈጽሞ አይደረግም። #ፈጽሞ። እናት ኢትዮጵያ ለአማራ ወላጅ የፊደል ገበታው፤ አናባቢ እና ተነባቢው እንጂ "ጠላትነት"የማይታሰብ ነው። የአማራ ህዝብ የኢትዮጵያን ክብር፤ ልዕልና እና ልቅና አይቀናበትም።
 
የአማራ ልጅ ዜግነቱ ሲጠየቅ ዜግነቴ ድህነት ብሎ አሳፋሪ መልስ አይሰጥም። ወይንም ዜግነቴ አዲስአበባዊ ነኝ የሚል ዝልፍልፍ እና የተዝለገለገ ላንቁሶ መልስ አይሰጥም። የአማራ ልጅ ዜግነቱን ሲጠየቅ ፈጽሞ አያመናታም። ጠርዝ ላይም አይቆምም። የአማራ ልጅ ዜግነቱን ሲጠየቅ በተደላደለ፤ በራስ መተማመን ሙሉ መንፈስ #ኢትዮጵያዊነት #ነዋ ብሎ ይመልሳል። የአማራ ልጅ ኢትዮጵያዊነቱ አያሳፍረውም፤ አያሸማቅቀውም። ፈጽሞ። ፈጽሞ። 
 
ለአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ከእግዚአብሄር ከአላህ የተሰጠ የክብር #አክሊል ተደርጎ ነው የሚወሰዱ። ሁሉም መልካም ነገር፤ ሁሉም ህግ የማክበር ጥበብ፤ ሁሉም የፈጠረኝ አምላክ አለኝ ብሎ የማመን ሙሉ አቅም እና ክህሎት፤ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተሰጠ ንጥረ ነገር ነው ብሎ ያምናል የአማራ ህዝብ። ኢትዮጵያን የሰጠኝ፤ የሸለመኝ አምላኬ ፈጣሪዬ እግዚአብሄር አላህ ነው ብሎ ያምናል። በዕምነቱ እንደጸና ይኖራል። የሥጋ እረፍት ሲኖርም በቋሚ ጽናቱ ልክ ሥርዓቱ ይፈጸማል።
 
ስለሆነም የአማራ ህዝብ በጋብቻው፤ በአብሮ መኖሩ ዓውደምህረት፤ በጥበብ ቤተኝነቱ፤ በአገልግሎት መስኩ፤ በማናቸውም የገብያ ሥርዓት ሁነቱ ሁሉ #ስንቁ ኢትዮጵያዊነት ነው። #ትጥቁም ኢትዮጵያዊነት ነው። ለአማራ ህዝብ የመንፈሱ የቅድስና ጉዞው የተቀዳው ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣምሮ፤ ተቀጣጥሎ፤ ተንጠላጥሎ፤ ተጠምኖ ሳይሆን ከጽንሱ ጀምሮ ሁኖበት የተገነባበት ፍሬ ነገር ነው ኢትዮጵያዊነት። አጥንቱ የተገነባው በኢትዮጵያዊነት ሊቅ ፍልስፌና ነው።
 
 የመከራው ሁሉ ማምረቻ እኮ ይህ ወደርየለሽ ጽናቱ እኮ ነው።
የሚገርመኝ የባለቀ መንፈስ የአማራን ህዝብ ስለኢትዮጵያዊነት እንዲያስተምር ሲታቀድ ነው። በድፍርስ - በጎሼ - በአጎረፈ ግርግር ዝልግል ስሜት ሲቀዝፍ የነበር ማንኛውም ሰብዕና ዝንቅንቅ ሰብዕናውን አጥርቶ እራሱን አንጥሮ፥ አጥቦም እራሱን ለማዳን ይጣር እንጂ የአማራ ልጆችን ኢትዮጵያዊነት ላስተምር/ ያስተምር ተብሎ መታሰቡ #ሰበርባራ እንኩቶ ጎዳና ነው።
 
"በኢትዮጵያዊነት በለማይዝም ሱሴ ዘመን" ኢትዮጵያዊነትን እንደ ቁሮ እንጨት ተለጣጥፎ በአቶ ንጉሡ ጥላሁን እና በቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በአሁኑ ወቅት እራሳቸውን አስከብረው የዕድሉ ተቋዳሽ መሆን ተስኗቸው ስደት ላይ የሚገኙት በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው መሪነት አቶ ጃዋር መሃመድ አማራ ክልል ባህርዳር እንዲገኙ ሲታሰብ የኪሳራው ቁልቁለት የተጀመረው ያ ንጊዜ ነበር።
 
ያን ጊዜ ከጃዋሪዝም እና ከቲሙ ምን እንዲያስተምር ታቅዶ አማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህርዳር ላይ ያ ሁሉ ሽር ጉድ እንደተደረገ እስካሁን አልገባኝም። እስከ ዛሬ የማይገባኝ #ፍሬፈርስኪ ውሳኔ ነበር። የሳሙና አረፋ የሚመስል የሚኩረፈረፍ ግብታዊ ስሜትን ለመጋት ፈቅደው የተሰበሰቡትም በእጅጉ አዝኜላቸው ነበር። ቁመው እየተንቀጠቀጡ ጥያቄ ያቀረቡትን ሳይ ደግሞ በእጅጉ ስቄም ነበር። በውነቱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅም #መነዳደል ያዬሁበት አጋጣሚም ነበር። 
 
ተፅዕኖ ፈጣሪነት እኮ እርቃን ተሁኖም ይኮናል እኮ። ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ማለት ለዛች ክስስተት ብቻ እንጂ ለእዮራዊ ጀነት ቅብዓ፤ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን በዲስፕሊን ለሚወጣ የመሪነት አቅም አቻ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። ይህን ከዩክሬን ጠቅላላ መከራ ጋር በስፋት የእኔ ብለን ብናጠናው ማረጋገጥ እንችልበታል። በዚህ መንፈስ ያለ ማንኛውም፤ የትኛውም ፖለቲከኛ ምኞት አቅም ሳይሆን የውድቀት መግቢያ በር ስለመሆኑ ሊረዳው ይገባል ባይ ነው። እችላለሁ ስለተባለ አይቻልም። መቻል ጥበብ ዊዝደም ስልት እና ክህሎት ስለሚጠይቅ። 
 
ከሞት እንኳን የክት እና የእዳሪ፤ ቤተኛ እና የዳር ተብሎ በሚታሰብበት #የጥላቻ አይዲወሎጂ ውስጥ በኢትዮጵያዊነት ተጸንሶ፤ በኢትዮጵያዊነት ተወልዶ፤ በኢትዮጵያዊነት አድጎ ለቁም ነገር ለበቃ የአማራ ልጅ መምህሩ የዚህ ተፃፃራሪ በሆነ ኢትዮጵያን አቂሞ፤ ኢትዮጵያዊነትን #አኩርፎ፤ በቀልን ጸንሶ ብቻ ሳይሆን የበቀል መንገድ ጠራጊ መሪም ሆኖ፤ ፓን አፍሪካንስቱን ኢትዮጵያዊነት አጣጥሎ የትግሉን መስመር የቀየሰ፤ ያደራጄ፤ የመራ #ዘባጣ ጉዞኛ በውነቱ ለአማራ ልጆች ሞዴል ሆኖ ያስተምር ዘንድ መታሰቡ በራሱ እንኩቶ ጉዞ ነበር። ወደፊትም አቤቱ ብልጽግና የተቀዳበትን ምንጩን እራሱን አጥርቶ፤ መነሻውን ያስተካክል ዘንድ ውክልናውን ከሰጠው በዓት ላይ ይጀምረው። የመርዙ ሾንኮፍ እዛ ስላለ። 
 
አሁን ከሰሙኑ እንኳን ትልቅ ጳጳስ አባት አቡነ ገብርኤል "#አጥንት ከቦታው ይመለስ" ሲሉ በአደባባይ አስተምረዋል። " ፍየላችን፤ በጎቻችን፤ መሬታችን ይፈልጉታል እኛን ግን ……" ሲሉ አንጠልጥለው የተውት "መነኮሰ ሞተን" የፃድቃን አስተምህሮ የሳተ ንግግር አዳምጫለሁኝ። እሳቸው ይሆናሉ በእሬቻ ጭፍጨፋ ተመድን ከጎን ያሰለፋት፤ ወይንም በልጃቸው እሬሳ ላይ ተቀምጠው የተደበደቡት ወይዘሮ ታደሉን ዕንባ እንዲታበስ ያደረጉት? የአማራ ልጅ የፈጸመው #ትንግርት ነበር።
 
ዛሬ "ሆድ ያባውን ብቅል" ያወጣዋል ሆኖ ያን ያህል #መስቃ የሚሰማበት፤ የበቀል ቁስል ያገረሽ ዘንድ መስቀል ተይዞ፤ ጥቁር የክብር ሰማያዊ ልብስ ተለብሶ፤ የመጨረሻው የክነት ጉልላት ተሰጥቶ በይፋ ጥላቻ የታወጀው። አቤቱ ብልጽግና ከ፰ የመከራ፤ የችግር፤ የዕንባ፤ የሳቁም ስለ አሉ የእነሱም ዘመን በኋላ ወደ 60ወቹ የጥላቻ ዶክተሪን፤ ተመልሰው #ኮሶ ፥ አሳንጋላን ትውልዱን ስለሚመግቡት ሊያስስበው፤ ሊያወግዘው ሲገባ ጸጥ እረጭ ነው ያለው። አቤቱ ብልጽግና እንዲሾሙለት አቅዶ ያሳካው አባት የእሱን የሥልጣን ዘመን እንዲህ በጥላቻ ጠቀራ ሲለብስ በዝምታ ማለፋ የጤና ነው ወይ እንድል ተገድቻለሁኝ። እግዚአብሄር የሰጠው ታላቅ እድል ቅጥቅጥ፤ ጥቅጥቅ ነው ያለው። ሃግ ባይም አልተገኜም። 
 
በዚህ አጋጣሚ አደባባይ ሚዲያን ከሙሉ አክብሮት ጋር አመሰግናለሁኝ። ተርጉመው ጉዳዩን እንድናውቅ አድርገውናል። ቤተ መቅደስን የሚያረክስ እንዲህ ያለ ያበለቀ ዕሳቤ ምርቃታችን ተነስቶ ማት ስለሚያመጣ ከስሜታዊነት ወጥተን አቅም ያላችሁ ወገኖቼ ብትጸልዩበት ፍላጎቴ ነው። ማህጸነን እንደ ዱባ ይቀረድዳል። ድፍረቱም መታበዩም መስቃውም። ወደ መነሻው እንሂድ ቢባል መዘዙ ብዙ ነው። ለትውልድም አይጠቅምም። 
 
«የጉድ ዘመን!!!! ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በኦሮምኛ ምን እያሉ ነው?»
(Adebabay Media)
 
"ስብከት" ልለው አልችልም የበቀል፤ የጥላቻ፤ የቂም ሐተታ ገዝፎ በሚታይበት ቦታ ሁሉ ስለኢትዮጵያዊነት ለማስተማር አቅሙ ከኖረው ጥረቱ ከራሱ የማህበራዊ መሠረቱ ቢነሳ #ኦሮምያ ላይ እመክረዋለሁኝ። በየዘመኑ መርዝ እንዲያገርሽ ሲደረግ የጎደለ ነገር መኖሩ ታውቆ እዛ ላይ ነው ርብርብ ሊደረግ የሚገባው። ብልህነት ካልሾላለከ።
 
አሁን እኔን ኢትዮጵያዊነትን ላስተምርሽ ብሎ የሚነሳ ለእኔ ዕብን እና ደመነፍስ ነው። ልክ በእኔ ማንነት ትክክል የተገነቡ የኢትዮጵያ ልጆች እንዳሉም አስባለሁኝ። ይህ የኢትዮጵያዊነት ጸጋ እና በረከት ያልጎደለብን ሰብዕናወች ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገነም። ለዛውም ድንገቴ ደራሽ ፕሮፖጋንዲስት ልካችን ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።
 
አቤቱ ብልጽግና ሆይ! ኢትዮጵያዊነትን ለመማር ፕሮፖጋንዲስት ካማረህ ከራስህ ጀምረው። ካቢኔህ ላይ፤ ሸንጎህ ላይ። እራስህን መንታ መንገድ ላይ አድርገህ Aንም፥ Bንም፥ Cንም እንዳይከፋው እንግልትት ከምትል ጥርት ባለ አቋም፤ በማይወላውል ጽናት በምትለው ልክ ለመሆን እግዚአብሄር ያብቅህ፤ አላህ ያብቃህ፤ አሜን። 
 
የአማራ ልጆችን ግን ስለ ኢትዮጵያዊነት ተማሩ፤ ፊደል ቁጠሩ ብለህ መዋለ ንዋይ አታፍስል። ተጠናቀን ስለተፈጠርን። ክውን ብለን ካለ ቂምም ስላደግን። እኛን ለቀቅ ብታደርገን ስል በትህትና እና በአክብሮት እጠይቃለሁኝ። አቤቱ ብልጽግና ኢትዮጵያዊነትን አማራ ክልል ላይ አስተምራለሁ ብለህ ወጪ አታብዛ። ኪሳራ ስለሆነ። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06/12/2025
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።