"#ማንም ዜጋ መለመን የለበትም።" (ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ።) እንደ ምኞተወት ያድርግልን። አሜን።
"#ማንም ዜጋ መለመን የለበትም።" (ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ።) እንደ ምኞተወት ያድርግልን። አሜን።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
#እፍታ።
ትሁታዊ ሰላምታ አቀርባለሁኝ ለቤተ - ቅንነት እንዴት አደራችሁ? እንደምን አረፈዳችሁ? ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል በአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ዙሪያ የምጽፈው። የሚሞገቱበት ጠፍቶ ሳይሆን፤ በሴት የፖለቲካ ሊቃናት ላይ በአንፃራዊነት ለዘብተኛ ነኝ። የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት አዋን መድረክ አግኝተው፤ ወጥተው እኔ ታክዬ #ቲካቲካ የተገባ ነው ብዬ አላምንም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴቶችን ተጫኝ፤ የገበርዲን እና የከረባትም ስለሆነ ንጥረ ነገር የጎደለበት፤ የእናታዊ ጸጋ የተነነበት ስለሆነ ስኬቱም ሲትበሰበስ ነው የኖረው። በሰሞኑ የምግብ ማዕከል ምርቃት እና ንግግር መነሻነት ዛሬ የተሰማኝን ለመግለጽ አህዱ ብያለሁኝ።
ከንቲባ አዳነች አበቤ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ "ድረሽልኝ" ባሏቸው የኃላፊነት ደረጃወች ሁሉ በመገኜት የልብ አድራሻቸው ብቻም ሳይሆኑ፤ የቅርብ፤ የሚያምኑት፤ የማይጠረጥሩት ሰብ ከኖራቸው፤ ከንቲባ አዳነች አበቤ ነው ሊሆኑ የሚችሉት።
በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃወች ፈቃዳቸውን በመፈጸም ቁጥር ፩ የጠሚሩ አጋር ይመስሉኛል - የዛሬዋ የመዲናችን የአዲስ አበባ ከንቲባ። ናቸው አላልኩም። ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይመስሉኛል ነው ያልኩት። እምከታተለው በርቀት ስለሆነ።
#እንደ በር።
ዕድሜ ልኩን ታግሎ ኦነግ አንዲት አቅም ያላት አንስት ፖለቲካ ማብቀል አልቻለም። ኦፌኮ ጋር ፕሮፌሰር ዶር. መራራ ጉዲናን በአካል ሳገኝ በወጣቶች ፖለቲከኞች እና በሴት የፖለቲካ ሊቃናትን በማብቀል ዙሪያ እሞግታቸውም ነበር። ምንም ያዬሁት እስከዛሬ ድረስ የለም። በዚህ ዙሪያ ወጣት ፖለቲከኞችን በማምጣት እና ሴቶችን አምኖ ወደ ፖለቲካው ጎራ በማምጣት እረገድ ደፍሮ የጀመረው ለማይዝም ሰፊ ተግባር ፈጽሟል።
"የኦሮማራ" ሠርግ እና መልስ ጊዜ ከንቲባዋን ጎልተው ታዳሚ ሆነው ባላያቸውም። የሆነ ሆኖበሴት ፖለቲከኞች እና በወጣት ፖለቲከኞች ሁነት ጉዳዬ ስለሆነ ይህን ጭብጥ አብዝቼ እከታተለዋለሁኝ። ወደፊትም።
#ለማይዝም በብሄራዊ ደረጃ ይሁን በክልል ደረጃ የመምራት የተስፋ ዕድሉ በለጋነቱ ቢቀጭም፤ ሌጋሲውን ግን ጠቅላይ ሚር አብይ አስቀጥለውታል። ይህ መልካም ነገር ነው። ዶር. አብይ ይህን ያደረጉበት ገፊ ምክንያት አለ።
ካቢኒያቸውን 50 %፤ የኢትዮጵያን ፕሬዚዳንት በአንስት ፖለቲከኞች ማካተት ኢህአዴግ እያሉ ያዩት፤ የሰሙት የዓለም ፖለቲከኞች ልዩ መሻት ነበር። ያን ከልባቸው አድምጠዋል። ለተቀባይነታቸው አጋዥ ቱልም ነበር ይህ እርምጃ። ከዚህ በላይ ሴቶች ለመፈንቅለ መንግሥት አይጠረጠሩም።
ሌላው ሴቶች ልክ እንደ ተባት ጫናን ታግሰው የሚያልፋበት መንገድ ለስላሳ መሆኑም ይመስለኛል። ተብዓት ፒኮክም በሴት ፒኮክ የመከበብ ልማድ አለው ይባላል። ያው ጠሚር አብይ ፒኮክን ከልባቸው ስለሚያቀርቡ። አዬ እሳቸው ስንት ነገር እኮ ነው ያደረጉት።አጤ አንበሳን አልይህ ብለው ፒኮክ ይለፍ ሰጪ ሆነ።
#የጭብጤ መነሻ ሊንኩ ይህ ነው።
«29ኛው የተስፋ ብርሃን ማዕከል ስራ ጀመረ»
«28ኛው የተስፋ ብርሃን ማዕከል»
«በልደታ ሦስተኛው በአዲስ አበባ 28ኛው ሶስተኛ«
1) «#ማንም ዜጋ መለመን የለበትም። የዜጎች ክብር በጠበቀ ሁኔታ፤ ንጹህ ምግብ፤ ደረጃውን የጠበቀ ምግብ»
(ከከንቲባ አዳነች አበቤ) ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግሽፈቱን ተቋቁማ እንዲህ ማድረግ ከቻለች …………?
ብቻ ህልሙን ዕውን ያድርገው መዳህኒዓለም አባት ዓለም። የኢትዮጵያ መሪ ቁንጮው፤ የዓለሙ ሎሬት ተሸላሚ፤ የዓለም የሰላም አባት ዶር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ታምርት ፬ኛው በዓላቸው ላይ ጠንከር አድርገው፤ ከውስጣቸውም "ለማኝ ነን፤ ለማኝ ጥገኛ ነው፤ ለማኝ ሉዓላዊነት" የለውም ብለዋል። ይህ አገላለጽ ለጠቅላይ ሚሩ፤ ለካቢኔ አባላቶቻቸው፤ ለፓርላማቸው፤ ለህዝባቸው ሥነ - ልቦና እጅግ ፈታኝ፤ ቅስምን የሚፈትን ምን አልባት #አጉባጭ ሊሆን የሚችል ድምዳሜ ይመስለኛል። እኔ ደንግጫለሁኝ።
ዶር አብይ አህመድ በዓለም ዓቀፋ መድረክ እኩል ነገ አብረው አንገታቸውን ቀና ብሎ፤ በብሪክሱም፤ በአፍሪካ ህብረትም፤ ኢትዮጵያ በምታዘጋጃቸው ዓለም ዓቀፍ መድረኮችም ላይ ይህ ሃሳብ እንደምን መቻልን እንደሚያስችል አላውቅም። አገላለጹ የጠሚሩንም በራስ የመተማመን አቅማቸውን ካልተፈታተነ። እሳቸው ይህን እያሉን በልቶ፤ ጠጥቶ፤ መጠለያም ኑሮት መኖርን፤ ጽድት ባለ ሁነት የሚያከናውን ማህበረሰብ እየፈጠርን ነው እድምታው የከንቲባዋ።
2) «በከተማችን ውስጥ እነኝህ የተገነቡት የምገብ ማዕከሎች ሁሉ የእናንተ ናቸው። ንጹህ ምግብ፤ ደረጃውን የጠበቀ ምግብ፤ በክብር እጃችሁን ታጥባችሁ ፤በንጽህና መጥታችሁ፤ ከዚህ መመገብ ትችላላችሁ።» (ከንቲባ አዳነች አበቤ።) የአመጋገብ ሥርዓቱ በቀን አንድ ጊዜ ነው።
ከፋና ዘገባ 28ኛው የሚል አለ፤ ከዘሃበሻ ፌቡ ያገኜሁት ደግሞ 29ኛው ይላል። የትኛው ትክክል እንደሆን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁነት ይናገረው።
#ሃሳቡ። እና የተስፋ ቃሉም። ተስፋ ለእኔ የሚዲያወቼ ሁሉ ካፒቴን ነው።
ሃሳቡ ጥሩ ነው። ከሁሉም ተስፋ በዚህ ፕሮጀክት ቃሉ መጠቀሱ ተስፋም ነው። ዓለም ባለችበት ሁኔታም ሆነ ኢትዮጵያ ባለችበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይቻላል ወይ? ይዘልቃል ወይ የሚሉ አሉ። ፌክ ነው የሚሉ ሚዲያወችን አይቻለሁኝ። አዳምጫለሁኝ።
ለዚህ ሊረዳ የሚችለው ተጨባጭ የሆነ መረጃ መስጠት ነው። በዘለቄታ ታቅዶ እንደ ፕሮጀክት የተያዘ ወይንስ ለጊዚያዊ የህዝብ ቁጣ መቆጣጠሪያ የሚለውን ሃሳብ ማቆየት ይገባ ይመስለኛል። ጎንደሬወች "የፊት የፊቱን ይላል ጓያ ነቃይ" ይላሉ። የመረጃ እጥረት ይኑር፤ ወይንም አለመተማመኑን እርግጥ ለማድረግ እነኝህን ሃሳቦች ከንቲባ ጽህፈት ቢመልስ ባይ ነኝ። ለነገሩ ላም እረኛ ምን አለ ለኢትዮጵያ የእኛ ዘመን ፖለቲከኞች ያልተለመደ ቢሆንም፤ ሃሳቡን አቀርባለሁኝ።
1) አዲስ አበባ ውስጥ ስንት የምግብ ማዕከላት አሉ?
2) በምግብ ማዕከላት ውስጥ ተጠቃሚወች ምን ያህል ናቸው? ቢቻል በፆታ እና በዕድሜ።
4) የምግብ ማዕከሎች አድራሻ የት ነው?
5) የምግብ ማዕከሎችን ለማግኜት ኮንታክት ፐርሰኑ ማን ነው? የስልክ ቁጥሩ፤ ማህበራዊ ሚዲያም ካለው ጨምሮ ማሳወቅ።
6) ልደታ ላይ ሦስተኛው እንደሆነ ተነግሯል። ኃላፊነትም የሚወስደው ዳሽን ባንክ መሆኑን ገልጸዋል ከንቲባዋ። "ሃብታሞችን ያብዛልን" የሚል ምርቃንም ሰጥተዋል።
7) የመገቢያ ማዕከሉ ሁነኛ ተጠሪ፤ ቋሚ ስፖንሰር፤ ተባባሪ አካላት ማን ናቸው? ስፖንሰሮቹ ፈቅደው ወይንስ ፈርተው?
ስምንተኛ) የመመገቢያ ማዕከላት በጋራ በተገነቡ ቤቶች አዳራሽ ብቻ ወይንስ ለአገልግሎት ምቹ ቦታ ላይ ናቸው ያሉት ወዘተ የሚሉ ዝርዝር መረጃ በዳታ ማቅረብ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በተሟላ ባለሙያ የሚንቀሳቀሰው ከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃወችን አሟልቱ የመስጠት ግዴታ አለበት። መረጃ ነው የፋክትን ህልውና የሚጠብቅ።
1) ይህ ጅምር ለምርጫ ወቅት ወይንስ ………?
2) ይህ ተስፋ ለጊዚያዊ……… ወይንስ?
3)ይህ ፕሮጀክት ታቅዶ ………ወይንስ?
4) የመመገብ አገልግሎቱ አባ እና እማ ወራዋን ወይንስ መላ ቤተሰብን?
5) አንድ እማ እና አባ ወራ እግር የጣለው እንግዳ ቢኖርበትስ ……… እንግዳ ይዞ መሄድ ይፈቀዳል ወይ? " እጃችሁን ታጥባችሁ ብቻ መምጣት" መባሉን ዘንግቼው አይደለም።
6) አንድ ቋሚ ተመጋቢ የጤና እክል ቢገጥመውስ? አገልግሎቱ ቤቱ ድረስ ይሄድለታል------ን?
7) ወደ መመገቢያ ማዕከሉ መሄድ ለማይችሉ በአካል፤ በመንፈስ፤ በዕድሜ የአዲስ አበባ ነዋሪወችስ ለመድረስ ምን ታስቧል?
8) ከአዲስ አበባ ከተማ ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው የሚገኙትን፤ ምን አልባት ደብረብርሃን የተፈናቃዮች ማዕከል ውስጥ አዲስ አበቤወች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነሱስ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ተካተዋል----ን? ካልተካተቱ ወደፊት ምን ታስቧ--- ል? ተፈናቃይ ቢሆኑም ግን ነባር አዲስ አበባዊነትን የእኛ ናቸው ብሎ ያስባልን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት። አጥርቶ መጀመር ለዘለቄታ ተግባር ወሳኝ ነውና። ሰውኛነት ሆነ ተፈጥሯዊነት ሩብ ወይንም እርቦ ዕሳቤ አይደለምና።
ስምንተኛ) በህመም ምክንያት ጥሬ ጨው፤ ቅባት የተከለከሉም ሊኖሩ ይችላሉ። ተቋቋሙ በተባሉት በ28 የመመገብያ ማዕከሎች ተገልጋዮች ለእነሱስ የተለዬ አቀራረብ ታስቦበት ይሆን?
9) ይህ ፕሮጀክት ቋሚ በጀት አለው ወይንስ ----? የሚለውን የማስረዳት አቅም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያስፈልገዋል።
#በቀን አንድ ጊዜ።
አገልግሎቱ በቀን አንድ ጊዜ ምሳ ብቻ እንደሆን መግለጫው ላይ ተረዳሁኝ። የአንድ ጊዜው ያዬሁት ቡፌ ነው። ይህ ለአንድ ቀን ለፎቶ ወይንስ ከንቲባ ጽህፈት ቤት በቡፌ ሊያዘልቀው ይችላል ወይ? በአዘቦቱ ቀን መሰሉ ይቀጥላል----ን?
ቡፌ ከሆነ አንድ ተመጋቢ ደጋግሞ የማንሳት ዕድል ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህ ምሳውን ጥግብ ብሎ በልቶ ያተረፈውን ቋጥሮ ማታም ጫር ጫር ስታደርገው ሊቀማምስ ይችላልን? ከተፈቀደ የራሱን ቀሪ ምግብ መቋጠሪያም ተመጋቢው ይዞ ሊሄድ ይገባል። ያዬሁት የመመገቢያ ትሪ ሰፊ ነው። ቁርጥም፤ ዶሮ እስከ እንቁላሏም አይቻለሁኝ።
#ከዚህ ቀደም እና አሁን።
ከዚህ ቀደም ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለአዲስ አበባ ተማሪወች ምግብ የመመገብ ተግባር እንደጀመሩ ዜና አዳምጫለሁኝ። አሁንም ያ አሻራ እንደ ቀጠለ ዜና ተከታትያለሁኝ። ይህ ጥሩ ነገር ነው።
አቅም የሌላቸውን ወላጆች ይደግፋል። በተጨማሪም ተማሪወችም ስለምግብ ማሰባቸው ቀርቶ ስለትምህርታቸው እንዲያስቡ ይሆናል። እርግጥ ነው የጥራት ችግር አለ ሲባልም እሰማለሁኝ። ክትትል ማጠናከር ይገባል።
በሌላ በኩል ግን ይህንንም ዕድል ያላገኙ በየከተማው ያሉ ሚሊዮን ተማሪወች እንዳሉም ማሰብ ይገባል። ችግሩን ለመፍታት ብሄራዊ ትልም በዚህ ዘርፍ ቢኖር መልካም ነው። የየከተሞች ከንቲባ ጽህፈት ቤቶች አስበውበት በስሜት ሳይሆን በሚቻል አቅም መጥነው ቢጀምሩት ጥሩ ሃሳብ ነው።
#ያልተመቸኝ። የከበደኝም።
አገላለጹ ከበደኝ። እኔ የገባኝን ያህል ብተረጉመው ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ያሰቡትን፤ ያለሙትን ህልማቸውን ይሞግታል፤ ያሳጣል ----ም፤ ፊት ለፊትም ምርጫ አለ። #Timing ማድመጥ ይገባል፤ የእኔ የህይወት መርህ ነው።
"ንጹህ ደረጃውን የጠበቀ።" ?
"ስትመጡ ታጥባችሁ ኑ።" ?
"#በክብር እጃችሁን ታጥባችሁ።"?
"በንጽህና መጥታችሁ።" ?
"ዜጎች፤ አገራችን" ከማለት ውስጥን የሚያቀራርበው የኢትዮጵያዊ ዜጎቻችን ቢባል፤ የተሻለ አቅም ያለው አገላለጽ ይሆን ነበር።
#ያልተመቹኝ አገላለፆችን ለማስመቸት ምን ቢደረግ?
ቁልፋ ጉዳይ ቢያንስ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የከንቲባቸው ንግግር አጭር ግልጽ፤ የሰብዓዊ ክብርን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የማይጫን ሆኖ ሊያዘጋጅ ይገባል።
ይህ ፕሮቶኮል የሚባል የዓለም የሰብዕና አደረጃጀት እና አመራር ዲስፕሊናዊ ቀመር #በኦሮሞ ፖለቲካዊ ባህል የሚታወቅ አይመስለኝም። ብሄራዊ መዋቅርም የለውም። የተዘለለ ግን ቁልፍ ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው ሁልጊዜ ፋውል በመንግሥት፤ የበዛ ግድፈት በብልጽግና አካላት የሚደመጠው። የተፃፈ የማንበብ ልምድ ሥርዓት ነው፤ ከብዙ የአፍ ወለምታም ይታደጋል።
አንዳንዱ የአገላለጽ ዘይቤ ፋስ ይሆናል፤ አንዳንዱ ለተስፋ ተብሎ ተስፋን መቃብር የሚልክ ይሆናል። አንዳንዱ ደግሞ የሥነ - ልቦና ቅጥቀጣም ይሆናል። ለነገሩ በንግግር ጥበብ ሁልጊዜ ተናጋሪ ከተሆነ የአዘቦት እንጂ የፖሊሲ አመንጭ ነው ተብሎ ኦዲየንሱ አክብሮ፤ ጓጉቶ፤ ናፍቆትም አያዳምጥም። የእራስንም ክብር ይፈትናል ሁልጊዜ ተናጋሪነት።
ቁጥብነት፤ የበለጠ ለአድማጭነት ጊዜ መስጠት፤ ሰፊ ጊዜ ለጥሞና መስጠት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህሉ አይደለም። ይህን ከፊደል "ሀ" መጀመር ይቻላል። ቢፈቀድ።
ያልተፃፋ፤ ድንገተኛ ንግግሮች መሪያቸው ግንፍል ግንፍል የሚል ስሜት፤ ያልተከረከመ እልህ፤ ያልታረመ መቆጨት ይሆን እና ንግግሩ የታቀደለትን ግብ ሳይከውን ይጨነግፋል። ሌላም መዘዝ ያመጣል። የራስን መሠረታዊ መሠረት ሊንድ ይችላል።
የከንቲባው ንግግር በሥርዓት ታርሞ ተጽፎ ተነቦ ቢሆን ኖሮ እኔ አልጽፍበትም ነበር። በዘፈቀደ መሪነት የማይሆን ቀመር ነው። መሪነት ከሥርዓት በላይ መሆን ማለት አይደለም። መሪነት ትሁት አገልጋይነት ሲሆን፤ ትህትና እራሱ ስርዓትን ይሻል።
በዚህ የመገቢያ ማዕከል የመክፈቻ ንግግር ላይ ከንቲባ አዳነች አበቤ #ፈራተባ እያሉ እንጂ በልበሙሉነት እንደሌላው ጊዜ አልተናገሩም። ያነሷቸው የጭብጥ የአገላለጽ ዘይቤ ግን ለእኔ ስሜት የቀረቡ ሳይሆኑ የከበዱኝ ነበሩ። ምክንያቱም ህዝባዊ ንግግሮች በዚህ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን በአወንታዊም ይሁን ባሉታዊ ሁኔታ፤ ቀንተውም ይሁን ጎብጠው ተደራሽ ይሆናሉ።
ስለዚህም ጉዳቱ ይሁን ጠጋኝነቱ መጠነ ሰፊ ነውና የአነጋገር ዘይቤ፤ የሥንኝ አጠቃቀም ሁነት፤ ጠንቃቃነት በእጅጉ ያስፈልጋል። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ክብር ለሚገባው ጨዋ እና ቻይ ህዝብ በተጨማሪ የአገላለጽ ዝበት ውስጡ እንዳይጎዳ ማድረግ የኃላፊነት ግዴታ ነው። ብዙ መከራ ያስተናገደ ትናንት ዛሬም እንዲሁ በስጋት ውስጥ ያለ ጭምት ህዝብ ነው ያለን።
"#የበጉነት መንደር።"
ከ16 ዓመታት በላይ እየተጋሁበት ያለ ሁለት ጭብጦች አሉ። በወቅቱ ተመድንም፤ አውሮፓ ህብረትንም ጠይቄ ነበር።
1) የፍቅር ተፈጥሮ እንደ ማህበራዊ ሳይንስ፤ ተፈጥሯዊ ሳይንስ፤ እና ሃይማኖታዊ አስተምኽሮወች ካሪክለም ተነድፎለት በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ልጆች ይማሩት። የፍቅር ተፈጥሮ ሙያ ይሁን ሙያተኞች መምህራን፤ ኤክስፐርት፤ ተመራማሪ፤ ሳይንቲስት ይኑሩት፤ ዓለምም በአጀንዳ ትወያይበት። ክፋ ሃሳብን በልኩ መፋለም የሚቻለው ይህ መንገድ ሊሆን ይገባል። የስቢሉን ስልጣኔ፤ የሚሊተሪው ስልጣኔ እያጠፋው ነገ ጤነኛ ትውልድ ለመፍጠር ጋዳ ይሆናል።
2) የህግ ሙያ ዩንቨርስቲ ለሚገቡት ብቻ ሳይሆን ህግ የማህበረሰቡ የዕውቀት ዘርፍ ሊሆን ይገባል። ልጆች የዩንቨርስቲ፤ የኮሌጅ መግቢያ አገኙም፤ አላገኙም ከመዋለ ህፃናት ጀምሮ የየአገራቸውን ህገ - መንግሥት እና፤ የተመድን የታህሳስ 10/1948 ድንጋጌ እንደ ህሊና አቅማቸው ልዩ ተጨማሪ ካሪክለም ተዘጋጅቶ ሊማሩት ይገባል።
ነዋሪውም በኮሚኒቲው፤ በሚዲያው ትምህርቱን ሊያገኝ ይገባል የሚል ሃሳብ አለኝ። ህግ ተጣሰ ለማለት ህግ ጣሹ መብቱን እና ግዴታውን ማወቅ አለበት። ወንጀልን ለመቀነስ ድንጋጌወች እስከ አተረጓጎማቸው ማህበረሰቡ ሊያውቃቸው ይገባል ባይ ነኝ። የህግ ድንጋጌ ተርጓሚው ባለሙያው እንጂ ተማላው አይደለም። በሌላ በኩል አንድን ሰብ "ወንጀለኛ" ለማለት መብቱ እና ግዴታውን ጠንቅቆ እንዲማረው ሊደረግ ይገባል። አቶ "ለ" ወንጀሉን እንዳይፈጽም ድንጋጌወችን ቀድሞ ተምሮታል ወይ? የእኔ አርጉሜንት ይህ ነው።
በተለይ በፍቅር ተፈጥሮ ጥልቅ ነው። ውቅያኖስ። በውስጥነት ትህትና፤ ቅንነት፤ አወንታዊነት፤ መጽናናት፤ ምህረት፤ እርቅ፤ ይቅርታ፤ ደግነት፤ ያልፋል፤ ይቻላል፤ ይሆናል፤ አመሰግናለሁ፤ መጨመት፤ ይሁንታ፤ መኖር፤ ቅንነት፤ ማድመጥ፤ በራስ መተማመን ወዘተ በሚሉ ሥያሜወች ትምህርት ቤት፤ ኮሌጅ፤ ዩንቨርስቲ ዓለማችን አላትን ብዬ ሞግቻለሁኝ?
ሥሞች በራሳቸው የፍቅር ተፈጥሮን የዕውቀት ዘርፋን የህሊና ማሳ አለምላሚ ስለሚሆኑ። ዩቱብ ቻናሌ ላይ በዝርዝር ለአረዳድ እንዲያመች በግራፊክ ሁሉ ሠርቸዋለሁኝ። ፔጅም አለው።
በተጨማሪነት የማነሳው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ፖድካስት ነበረ። "መሪ" የሚል። የፖድካስቱ መሥራቾች ሁለት ወጣቶች ናቸው። አንዱ በቡና ሌላው በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።
በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው የፕሮጀክቱ ሥያሜ "#እሺ" ነው። ይህን ስሰማ በጣም ነው የተደሰትኩት። ቀጣዩ ትውልድ ይህን መሰል የላቀ የቀደመ ዕሳቤ ሲኖረው መማር ዩንቨርስቲ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቦታ ይገበያል። "እሺታ" ለእኔ ትርጉሙ፤ አፈፃጸሙ፤ ቃናው፤ ምቱ ብርሃን ነው።
ከዚህ አንፃር ሳዬው "#የበጎነት መንደር።" ሥሙ እራሱ ተቋም ነው። ነዋሪውን ብቻ ሳይሆን አላፊ አግዳሚውንም ያስተምራል። ይህን ይዘን በመላ ኢትዮጵያ ከመኖር የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ሁሉ ዕድሉን ሊያገኙ ይገባል። ከቅርቡ ከደብርብርሃን የተፈናቃዮች ማዕከል መጀመር ቢቻል ጥረቱ ለውስጣችን ተደራሽ ይሆናል። አድማጭም ይኖራል። ዕውቅናም ሰጪም በገፍ ይሆናል።
የዜግነት እርሾ፤ የዜግነት እርቦ ስለሌለው በየተፈናቃዮች ማዕከል ይህን መሰል ተግባር ሊዳረስ ይገባል። አንድም ቀን የመንግሥት ቋሚ መሪ አካላት ሄደው ያላዮቸው፤ አቋጥረዋቸው የማያውቁ፤ በባይተዋርነት ያሉ፤ የሰፈራ ማዕከሎች አሉ። ማፈራረቅም ይቻላል። የሌሎች አገር ስደተኞችን አለንላችሁ መልካም ቢሆንም፤ የራስን ውስጥም ሰውኛነትን ተግባራዊ የሚደረግበት የአፈፃጸም ሂደት ሊኖር ይገባል። ጥረቶችን የሚያስነክሱ ሃሳቦች የሚመነጩት ሌሎችንስ የሚል ጥያቄ ስላለ ነው።
ጥያቄ ለዳሽን ባንክ ነው። አቤቶ ዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች ከተሞች ላይ በተለይ ጠንከር ያለ የገቢ ምንጭኽን በቀጣይ ይህን መሰል የርህርህና ተግባርህን ለመጀመር አስበህበታል ወይ? በተለይ ሰላማቸው ከተረጋጉ እና ሥራህም ካልተቆራረጠብህ ከተሞች ላይስ?
በመጨረሻ ለብልፄው አሁን ጥድፊያ ላይ ያለህበትን ሁኔታ አይቻለሁኝ። የወረት እንዳይሆን፤ ጥረቱን የማስቀጠል ሞራሉንም፤ አደቡንም ነገ የምናዬው ይሆናል። አሉታዊነትን በህሊና ከማቀድ፤ አወንታዊነትን ቅደም ማለት ለራስም፤ ለማህበረሰብም ጤና ስለሚጠቅም።
ቸር አስበን፤ ቸርእንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ.
Sergute©Selassie።
20/05/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት፤ ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ