የዘመን #ዓይናማዊነት በእናታዊነት የምክር አገልግሎት በቅኔ ሲጸና።
የዘመን #ዓይናማዊነት በእናታዊነት የምክር አገልግሎት በቅኔ ሲጸና።
(መዝሙር ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፩)



#ምዕራፍ ፲፱።
#ጠብታ።
ቤተ - ሥርጉትሻ ማህበረ ቅንነት እንዴት አደራችሁ? እንደምንስ አረፈዳችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። ዓለም በየለቱ አዳዲስ ክስተቶች ታጌጣለች፤ ትደመማለች፤ ትጠሞናለች። በዚሀህ በ2026 የዓለም ዋንጫ ሂደት ዓለማችን በፋመ የጦርነት ወላፈን ሆና፤ የወላፈኑን ግርፊያ #ረብ የሚያደርግ ነፋሻ አየር የሆነው የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ የየለቱ ክስተታዊ ገጠመኞችም ነው።
ይህ የዓለም ዋንጫ ካስተናገዳቸው ጉልህ እና ጉልበታም ክስተቶች የጊዜውን ሁኔታ የገዛው የስፔን እና የፖርቹጋል ጨዋታ የፈጠረው ክስተት አንዱ ነው። በመጨረሻው የዋንጫ ቀን ከሚፈጥረው ውስጣዊ ስሜት በጣም የላቀው፤ ቃላት ሊገልጹት ያቃታቸው የክርስትያን ሮናልዶ የመራራ የስንብት ሂደት ክስተት አፈፃጸሙ የውስጥ ኦርጋኒክ ነበር።
በአንድ ወቅት ዘባስትያን የጀርመኑ ብሄራዊ ቡድን እና የባየር ሙንሽን ተጫዋች፤ ከብሄራዊ ቡድኑ ሲሰናበት፤ እንዲሁም የዶርት ሙንድ አሰልጣኝ ዩርግ ክሎፕ ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ሲሰናበቱ፤ የነበረው ስሜት ብሄራዊ መልክ እንደነበረው አስታውሳለሁኝ።
የክርስትያን ሮናልዶ ግን ከዚህ ይለያል። #ግሎባል ነው። ጥልቅ በጣም ጥልቅም ነው። የሁኔታው አፈፃጸም ደግሞ የቀጣይ የተስፋ ዕድል በመቀስ የተቆጠረበት ቅጽበት ፍጹም በሆነ በተለዩ ሁኔታ ነበር። ኤራ ነው።
ስለሆነም ይህን ፔጄ በዝም ብሎ እንደ አልባሌ ሊያልፈው ስላልፈቀደ ዛሬን ለክርስቲያን ሮናልዶ #የእናታዊነት አክባሪነት፤ አድማጭነት፤ ዕውቅና ሰጪነት አስተምኽሮ ትንሽ ልልት ወደድኩኝ። ይህ የዓለም የዋንጫ ዕድል ከዚህ ቀደም ላላገኙት ይሆን ዘንድ ስመኝ ከእማማ ሲዊዝ ቀጥሎ ክርስትያኖ የስንብቱ መቋጫ በዋንጫ ይሆን ዘንድ ዘለግ ያለ ምኞት ነበረኝ።
ታሪክ እራሱን መፃፍ የፈለገውን እንደ ልቡ የሆነው ወርኃ ሚያዚያ ዓይነት ክስተት ተፈጠረ እና የጋሼ ጸጋዬ "የወንድ ልጅ ዕንባው በሆዱ ነው" ያለው ተቃራኒው ተፈጸመ። ከውስጥ --- የገባ፤ ህሊናን --- የፈተሼ፤ እራስን የታገለ --- #ቅጽበት ተከሰተ። አብሮ ያነባው - ሚሊዮን። አብሮ የተከፋው - ሚሊዮን፤ አብሮ ጸጥ ረጭ ያለው - ሚሊዮን ነበር። ጊዜ ታሪክን ይሠራል፤ ጊዜ ታሪክን ይፈትናል።
(1) እያንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል።
(2) እያንዳዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል።
(3) እያንዳዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል። ፖስተኝነት የፍጥረት ሁሉ ነው።
እግዚአብሄር አምላክ ለሁላችን ይህን እኩል ሰጥቶናል። ይህ ጸጋ የጊዜ፤ የቦታ፤ የሁኔታ መመቸት ሲኖር እንደ ክርስትያን ሮናልዶ ያለ ሰብእና ይከሰታል። በአመዛኙ ብልህ ወላጆች ቀድመው የልጃቸውን የመክሊት ደረጃ አመሰጥረው ፈቃዱን ማመቻቸት ከቻሉ፤ መቀባት ሳይሾልክ፤ ምርቃት ሳይሰወር ተስጥዖ እና ባለተሰጥዖ ልጆች ይገናኛሉ።
"HEARTBREAKING! Cristiano Ronaldo BREAKS DOWN in Tears After Portugal's World Cup Exit vs Spain"
ብዙ በጣም ብዙ የብሄራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪወችም ይፈጠራሉ። በተለይ በያዝነው ዘመን ዕድሉ ሰፊ ነው። ይህም ሆኖ ቅብዓቸው አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ግን የጥቂቶች ነው። በእነ ፔሌ፤ ሮናልዶ፤ ሲዳን ዘመን የነበረው ተቀባይነት በዛሬው ዘመን ሊወናል ሜሲ እና ክርስትያኖ ሮናልዶ በተለዬ ሁኔታ ሁለቱ ላቅ ብለው የግሎባልን መንፈስ ይዞ የማቆዬት አቅም አግኝተዋል።
በእነሱ ዘመን የተነሱ የእግር ኳስ ጠበብቶች ብዙ ናቸው። ከእነዛ ውስጥ ዓለም #ሽልማቴ ብላ ያነገሰቻቸው ግን ሁለቱን ለይታ ነው። ይህ ዕድል ፈጽሞ የማይገኝ የላይኛው ስጦታ ነው።
በብሄራዊ ቡድን መመረጥ ልዩ ዕድል ነው። በብሄራዊ ቡድን ተመርጦ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅናው ሲጸድቅ ደግሞ የፈጣሪ ምርቃትን ላቅ ባለ ሁኔታ የሚገለጥበት ይሆናል። በክርስትያኖ ሮናልዶ ያዬነው የዕድል - ገዢነት፤ የዕድል - ዕውቅና፤ የጥረት - ግሎባል ተቀባይነት የፈጣሪ አምላክ #ሽልማት ነው።
ክርስትያኖ እና ልዕልቷ ድንቡልቡሏ በልዩ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር የተቀመመ የመግባባት፤ የመደማመጥ፤ የቃል- ኪዳን አፈፃጸም ስናይ ኑረናል። እሷን ሲያገኝ ክርስትያኖ ፈንጠዝያው፤ ሩጫው፤ #ድድድድድ እራሱ እንዴት አምሮበት ይፈጸም ነበር።
መሰጠትን ከእናት ጋር መክሮ፤ እናትን አድምጦ መነሳት ለዚህ መሰል ዕንቁ ጊዜ ያበቃል። እናትን በማክበር ወደር የለሽ አስተምኽሮ በክርስትያን ሮናልዶ አይተናል። እኔ ለእሱ ያለኝ ፍጹም ልዩ ክብር የሚመነጨውም ከዚህ ነው።
ክርስትያኖ የሴት አያቱ ስታስደምመን ከሰነበተችው ከአፍሪካዊቷ ደሴት #ከካፕ ቬርዴ እንደመጡ አንድ ጊዜ አንብቤ ነበር። ውህድ ማንነት ለሁለገብ የጸጋ ባለመክሊትነት ዕድል ይሰጣል። የካፕ ፓን አፍሪካዊነት፤ የፖርቹጋል አውሮፓዊነት የየራሳቸው የማንነት አቅም በውህድነት በቅብዓ ሲጸድቅ የተለዬ ጠይማዊ አልማዝነት ነው።
የካፕ ቬርዴ የጎል ጠባቂ ለእናቱ፤ ለሚታው የሰጠው ክብር የዓለም አጀንዳ ሆኖ ሰነባብቷል። ይህ የክርስትያን ሮናልዶ እናትን ህሊናዊ የማድረግ ብቃት ካፕ ቬርዴወች የተለዩ መሰጠት ይኖራቸው ይሆን ስል ሰንብቻለሁኝ። ብችል እዛው እቦታው ሄጄ እናታዊነት እና አገረ ካፕ ቬርዴ ምን እና ምን እንደሆኑ ባጠናሁት ነበር። የእናት ነገር ሁልጊዜም ለእኔ ሚስጢር ነው፤ የእናት ነገር #ሚስጢረኛዬም ነው።
1) እናት የመጀመሪያዋ የፊደል ገበታ ናት የሚል ዕምነት አለኝ።
2) እናት የመጀመሪያዋ የህይወት መምህር ናት የሚል ዕምነት አለኝ።
3) እናት የማህበራዊ ኑሮም መሥራች ናት የሚል እምነትም አለኝ።
ስለሆነም እናትን - እያጠና፤ እናትን - እያነበበ፤ እናትን - እየተረጎመ፤ እናትን እያመሳጠረ - እናትን #እያዳመጠ፤ መኖርን ለመቀበል የወሰነ እንደ ክርስትያን ሮናልዶ ዓይነት ልጅ ዓለም ዓቀፍ ሽልማትነቱ ከዚህም ጋር ተዋህዶ ሊቀርብ ይገባል ባይ ነኝ።
እናት #ናሳ ያለው አቅም ያህል በተፈጥሯዋ አላት። እምዬ አርቃ - ታስባለች። እናት #ነብይም ናት። ከተደመጠች። በዚህ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር የክርስትያን ወላጅ እናት ይህ ሊመጣ እንደሚችል ቀድመው አውቀዋል። ምስጋና ለአድናቂወቹ፤ ለወዳጆቹ፤ ለተከታዮቹ ሁሉ አቅርበዋል። ልጃቸውን እስከ መሰጠቱ ውስጡን አስብሎ የማየት አቅማቸው ከድንቅ በላይ ነው። ቀድመው ያዩት ነገር ነው የተፈጸመው።
እናት የማጽናናት አቅሟ ልዩ ነው። የትዳር አጋርም እናታዊ ጸጋ አላት። ሁለቱም ሴቶች ናቸው። ሴቶች #የአይዟችሁ ባይነት አንባሳደሮች ናቸው። ስለሆነም የክርስትያን ሮናልዶ የዓለም ዋንጫ ታሪክ አፈፃጸም ላይ የተፈጠረው ልዩ ክስተት እና የክርስትያኖ የተስፋ ወለምታ በሁለቱ አንስቶች ይጠገናል ብዬ አስባለሁኝ። ዕድለኝነቱ በእናቱ ቅርበት - በውስጥነት፤ በባለቤቱ - አኃታዊነት ሁሉም ነገር ወደ ተረጋጋ ህይወቱ ይመልሰዋል ብዬ አስባለሁኝ። በጣም አዝኗልና።
የደነቀኝ በኮከብነቱ አገባቡ እና በመጨረሻው የዕድሜ ጸጋ ምክንያት፤ ስንብቱ የግሎባሉን መንፈስ እንደ ማግኔት የመሳብ አቅሙ ፍጹም የሆነ የመሰጠት የውሃ ልክ ነው። ተፈጥሮበታል። ዕድለኛ ነው። ሚሊዮኖች እኔን ጨምሮ በተፈጠረው ክስተት የውስጥነት ተስፋ ስብራት ጋር አብረን አንብተናል። አብረን - ተጨንቀናል። አብረንም - አዝነናል።
#የክርስትያኖ ጸጋው ትውልድን የማነጽ አቅሙ አንቱ ነው።
ምራቁን በዋጠ ዲስፕሊን የተያዘው የክርስትያን ሮናልዶ ቅብዓ ልዩ ጥንቃቄ ይደረግለት ነበር። የእናት - አያያዙ፤ የቤተሰብ - አስተዳደሩ፤ ደርጀት ብለው የሚመጡ የስፖንሰር ዕድሎች ለውጣቱ የማይበጁ ከሆነ #የማይቀበልበት የማስተዋል ብቃታዊ መንገዱ፤ የአኗኗር ስታይሉ እርጋታ፤ ሁለመናው ቁምነገር ገብ የሆነ የትውልድ አብነት የመሆን አቅሙ ያሰበለ ነው።
ክርስትያኖ የቢራ ማስታወቂያ አይሰራም እንኳንስ የሌላ። በጣም ጠንቃቃ ህሊናው የተደራጄ፤ መንፈሱ የተደራጄ፤ በዘመን ውስጥ ከእሱ የሚጠበቀውን የኃላፊነት ጣሪያና ግድግዳ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰብዕና ያለው ነው። እርግጥ ነው በአንዳንድ የእግር ኳስ ተንታኞች አግሬሲብ- ነው፤ ይኮራል የሚል ትችት ሲያቀርቡበት እሰማ ነበር።
ይህም ሰውኛ ነው። ማሽን - አይደለም። ሰው ነው። በዛ በላይ ወጣት ነው የነበረው። በምልሰት ወጣትነታችን ስናስበው ስቶር የማይችለው ግድፈት ፈጽመናል - ሁላችንም። በሙሉ ዕድሜ እንኳን እንደ ወጣትነት ዘመን ቱግ ቱግ ይመጣል።
ሌላው ቅናት ያለባቸው የእግር ኳስ ቤተሰቦች ማጣጣላቸው፤ መናናቃቸው የአቅም ማነስ ሁኔታ የሚፈጥረው የማንነት ቀውስ ነው። ይህን በምልሰት የ2019 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት/2014 በብራዚል አሰናዳችነት የተካሄዱ የጨዋታ ሁኔታን፤ በተይ በክርስትያኖ ላይ በተሳለ ፋስ ማት ይወርድ ነበር። ይህን ስፖርታዊ ትንታኔወችን ብታደምጧቸው ታገኙታላችሁ። በመንግሥት ሚዲያ ፎቶውን ሲያንከባልሉት ሁሉ አይቻለሁኝ።
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና ደፋሮቹ የሲዊዝን በየዘመኑ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዕድል ማግኜትን ሳይቀር፤ አብዝተው ሲያብጠለጥሉት ነበር። ዘንድሮ ምን ሊሉ ይችሉ ይሆን ብያለሁኝ። ማን ከዚህ እንደደረሰ? ማን በጊዜ ድግዝግዝ እንዳለበት።
#የፖርቹጋል አበርክቶ።
የባስኮ ደጋማ እናት ፖርቹጋል ኃያላን ይባሉ ከነበሩት ከስፔን፤ ከኡቶማን ቱርክ፤ ጸሐይ አይጠልቅባትም ይባልለት ከነበረው ታላቋ ብርታንያና ተርታ የሚሰልፍ አገር ነው የነበረው።
ፖርቹጋል ባስኮ ደጋምን ያህል የአገር አሳሽ ፈላስፋ አትላስ ማለት ይቻላል፤ የዛ ዘመን የጂኦግራፊ #ጉጉል የነበረ ጥበበኛ ባለ ተሰጥኦ መሃንዲስ ነበር። ዛሬም ቢሆን የተባበሩት መንግሥታት የሚመሩት ፖርቹጋላዊ ናቸው። በኢትዮጵያ የነፃነት ትግል ውስጥነት የአውሮፓ ህብረት ወሳኝ ሰው እቴጌ አና ጉምዝ የእኛ ዘመን ድንቅ ናቸው።
ሌሎችም በርካታ ጠበብቶች ፖርቹጊዜች ለዓለም ቀና ተግባር ፈጽመዋል። በእግር ኳሱ ዘርፍ በብሄራዊ ደረጃ ሳይሆን፤ በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ዘውድ የደፋው፤ ተወዳጁ፤ ተደናቂው ክርስትያኖ ሮናልዶ ለእግር ኳስ ንጹህ አፍቃሪወች ኢጎ ለሌባቸው የሐሤት ምንጭ ነው። የሰው ልጅ ከሚችለው በላይ በመኖር ሂደት ውስጥ ይፈተናል፤ ይፈተላልም። ያን ጫና ረብ ያደርገዋል ዓለም ዓቀፋ የእግር ኳስ ኢቬንት።
እግር ኳስ የመኖር ሥልጣኔን ያበራል። እንደ መንፈስ ቅዱስ ያረጋጋል። በዘመናችን ያለው ግሎባል የህውከት ዜና፤ የሲቢሉን ሥልጣኔ፤ የሚሊተሪው ሥልጣኔ እያነደደው፤ ሁለመናው ጭንቅ ላይ ባለበት ጊዜ፤ የተቃጠለው አየር ጸበል እርጨት ………እርጨት እያደረገ ቀልባችን #ተግ ይል ዘንድ ያደረገው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ሂደት ነው።
የሚገርመው በዚህ ሰሞን ትንሽ ለራስ ብቻ ሳይሆን፤ የተሰጠንን ጊዜ ለማድመጥ ስንፈቅድ እንኳን ይህን የሚያጣጥሉ፤ የሚቃራኑ፤ ህውከት ለመፍጠር የሚኳትኑ አይጠፋም። መኖር ፖለቲካ ብቻ አይደለም። መኖርን በሚያኖሩ የሥልጣኔ ሁለገብ ስጦታወች ሁሉ የማድመጥ፤ በሙሉ አቅም የመሳተፍ ሰጪውም ነሽውም እንደራሴው የራስ ውሳኔ ነው። የማንም ፍቃድ አያስፈልገነም ወደ መሰጠን አጀንዳ የማተኮር ውሳኔ።
እኔ ስለምወደው ይሁን ትኩረት ስለምሰጠው ጉዳይ አጀንዳ መራጭ አያስፈልገኝም። የራሴው ጌታ እኔው ስለሆንኩ። የራሴን የመብት እና የግዴታ ጣርያና ግድግዳም አሳምሬ አውቀዋለሁኝ። እኔ ጎርፍ አምጥቶ ደለል የሰራብኝ ደራሽ ፖለቲከኛ አይደለሁም። በጋሜ እና ቁንጮዬ በብቁ ሊቃውንት የተቀየሰ ነው የዘርፋ ተሳትፎዬ ቅኝት።
በሌላው ጉዳይም አንከር የሆኑ ባለሙያወች ናቸው የቀረጹኝ። ከዛ በላይ ደልደል ካለ ፈርኃ እግዚአብሄር ካለው ቤተሰቤ መፈጠሬ ሆነ ያደግኩበት ከተማ ሞቴሮፖልነት ጥብቅብቅ ካለ የዕሳቤ አድማስ ባሻገር የማዬት ዕድሌን በር ከፍቶልኛል። ስለዚህም እግር ኳስ ለእኔ የመልካምነት ሐዋርያ ነውና ጊዜው እንዲያልፈኝ አልሻም። በህይወቴ ውስጥ ለመዝናናት ብዬ እማጠፋው ጊዜ የለም። አለ ከተባለ እግር ኳስ ነው። ስለሆነም በሙሉ አትኩሮት ያለኝ ጊዜ ሁሉ በሐሤት እሸልመዋለሁኝ።
እኔ ሰው ብዙም አልቀርብም። ተሎም አልቀላቀልም። አባቴ አቨይ መምህር እና የቤተ- መጸሐፍት ባለሙያ ነበር። አቨይ የሚታወቀው በዝምታው፤ በቁጥብነቱ ነበር። ያን የወረስኩ ይመስለኛል። ፍራቻዬ ግን መለየትን ነው። እኔ ስቀርብ ከሚሰጠኝ ደስታ እጥፍ ስለይ አዝናለሁኝ። ስለዚህ ግንኙነቴን ቆጥቤ መኖርን ወሰንኩለት።
የክርስትያን ሮናልዶ የስንብት ሂደት መጸሐፍ ያጽፋል። ቅፅበቱ ብቻዋን አንድ የፎቶግራፍ መጸሐፍ መሆን ይችላል። የቅጽበቱ ትዕይንት ፊልምም መሆንም ይችላል። የሚሊዮኖችን ስሜትን በፈቃድ የገዛ፤ የሚሊዮኖችን መንፈስ በፍቅር - የሾፈረ፤ የሚሊዮኖች ውስጥ በተፈጥሯዊነት የመራ ፍፃሜ ነበር። መለየትን ስለምፈራው ሆዴ በጣም ነበር የተረበሸው። አይደለም የሰው ልጅ ያላመድኳቸው እርግቦቼ እንደ ወጡ፤ ቤት ሳይመለሱ ሲቀሩ ከውስጤ ነው የማዝነው።
በዚህ የክርስትያኖ ከብሄራዊ ቡድኑ፤ ከዓለም የእግር ኳስ ዕይታ መለየት መራራ ነበር። ስለሆነም በሚሊዮኖች ያለ ደንበር ዕውነተኛውን የፍቅር ተፈጥሮ አይቸበታለሁኝ። ያውም በልግስና። ያውም ሁሉም ዓይነት የልዩነት ደንበር ተደርምሶ።
ቅጽበቱ በአህቲ ልቦና የእግር ኳስ አፍቃሪ ቤተሰቦችን በውስጥነት ሐዲድ አገናኝቷል። ከአዕምሮ በላይ የሆነ የሚሊዮኖች ንጹህ የሆነ የፍቅር ስጦታ አይቸበታለሁኝ። የስፔኑ ታዳጊ የማል የራሱን ደስታ አልነበረም ያጣጣመው። የማጽናናት ተምሳሌት ነው የሆነው። እራሱን አስችዬ እጽፍበታለሁኝ። አስተምሮናልና። ሐዋርያነት እኮ ይህ ነው። "የሚያጽናኑ ብጹዓን" ናቸው ይላል አካል የሌለው የእግዚአብሄር አገልጋይ ቃለ ወንጌል።
"ፍቅር ያስታግሳል፤
ፍቅር ያስተዛዝናል፤"
(ወደ ቆረንቶስ ምዕራፍ ፲፫ ቁጥር ፬)
የሁኔታው አፈፃጸም ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) ነበር። አረማመዱ፤ አተያዩ፤ ውስጡን የገለጸበት ንቅናቄ፤ ሁኔታውን የተቀበለበት ግብረ - መልስ ልዩ ግርማ ሞገስ ነበረው። ከውስጣችን ለውስጣችን መከፋቱ ጉዝጉዝ ብሎ ተደላድሎ ይቀመጥ ዘንድ ያደረገበት ሁኔታ እንኳንስ መተርጎም፤ እንኳንስ ማመሳጠር ማንበብ አልተቻለም። ረቂቅ ነበር። ተፈጥሮው ቅኔኛ ነው።
#እርገት ይሁን።
ተዘርዝረው የማያልቁ የሐሤት፤ የፍሰኃ፤ የሰናይ፤ የፍንደቃ፤ የሳቅ፤ የተስፋ መሙላት፤ የስኬት ማስበል፤ የዕውቅና ሥልጣኔ፤ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ውህድ ድል፤ የሽልማት ከፍተኛ እርከን፤ የተደማጭነት ብቃት አቅም እና ልቅና፤ የመኖር ደረጃ ከፍታ፤ ለእናት ሊሰጥ የሚገባውን በመስጠት የተገኜው ቅንነት፤ ለእትብት በዕት ሊሰጥ የሚገባውን በመስጠት፤ ለአህጉር ይሁን ለግሎባሉ ሊሰጥ የሚገባውን በገፍ በመስጠት ጊዜን ሳያባክኑ፤ ሁሉንም በተሰጠ የጊዜ ማዕቀፍ የከወነ ጀግና፤ አሻራው ደማቅ እና ዝልቅ ነው።
በሂደቶች ሁሉ ታቅዶም ይሁን ድንገቴ የክፋ ሃሳብ ቤተኞች የሚያሰናዱትን መሰናክል አልፎ፤ ብዙ ድሎችን አስመዝግቦ፤ ቋሚ አበርክቶን ከሚጠበቀው በላይ ያሳካ ጀግና ስንብቱ ባልተጠበቀ ቅጽበት ቢሆንም እግዚአብሄር አምላክ እራሱ ይህን ያሰናዳበት ምክንያት አለው እና "ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነው ሁሉ ያለእርሱ የሆነ አንዳች ነገር የለም" እና ይህን መቀበል ግድ ይሆናል።
ይህ ዕድል በራሱ ሚሊዮኖች በተገኙበት፤ ሚሊዮኖች ከውስጣቸው እያነቡ የስንብቱ ሂደት መከወኑ ሌላ ሚስጥር የሆነ ጸጋ ነው። ቀሪው ጊዜ ለጨዋው የቤተሰብ አባወራ፤ ለምርጥ የእናት ክብር አንጋሹ፤ ብቁ የኳስ ልብ ለአደረገው መልካም ነገር፤ ለሰጠን የፍሰኃ ጊዜ ሁሉ አመሰግነዋለሁኝ። በሁሉም መስክ አብነትነቱ አንድ ቋሚ የትውልድ ጠቃሚ ካሪክለም ሊሆን የሚገባም ነው።
ይህን በመሰለ የሚሊዮኖች በውስጥ ፍቅር አሸኛኜት በራሱ መታደል ነው። የፍቅር ተፈጥሮን ሚሊዮኖች ቤተኛ ሆነው፤ ሚሊዮኖች ፍቅር ሆነው፤ ሚሊዮኖች ፍቅር ሰጥተው በታላቅ ክብር፤ በታላቅ ተመስጦ አሸኛኜት ማግኜት #መመረጥ ነው።
የሚሊዮኖች ፍቅሩ --- አልተገዛም፤ የሚሊዮኖች ፍቅሩ -- አልተሸመተም፤ የሚሊዮኖች ፍቅሩ በካድሬ--- አልተገኜም፤ የሚሊዮኖች ፍቅሩ በአክቲቢስት ኮኦርድኔት አልተደረገም።
ስለሆነም ንጹህ ሐሤትን ለመስጠት ሚሊዮን የኳስ አፍቃሪ ለመገበ፤ ቅን የኳስ አጤ ክርስትያኖ ሮናልዶ እግዚአብሄርን ሊያመሰግን ይገባል። ከመታደል በላይ ነውና። ይህን የአክል የሚሊዮን ውስጥነት ጸጋ በገፍ ያለ ደንበር ማግኜት ዕፁብ ድንቅ ነው።
አጤ ክርስትያን ሮናልዶ የዘመን፤ ለዘመን፤ ስለዘመን #ዓይናማ ቅኔ ነው። ለዛውም ምራቁን የዋጠ #ዓራት ዓይናማ ትንታግ ሊጋባ። ቀሪ ህይወቱን ፈጣሪ አምላካችን፤ አባታችን አማኑኤል ይባርክለት። ጥበቃውም አይለየው። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
09/07/026.
ጊዜ ታሪክን ይሰራል።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ