ዝም አትበሉ መንገርም ማናገረም መልካም ነው።

ግዙፉ የግንቦት 7 ፈተና።
„ደሴቶች ሆይ በፊት ዝም በሉ አህዛብም ሃይላችውን ያድሱ፤
ይቅረቡም በዚያን ጊዜ ይናገሩ፤ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ“
ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፵፩ ቁጥር ፩

ከሥርጉተ©ሥላሴ
 05.08.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


  • ·      መራረነት ጣፋጭነትም የእግዜሩ ሰውኛ ናቸው።

የዚህ ጹሑፍ ጭብጥ የሚመራቸው ይኖራሉ። ያው ሥርጉተ ሥላሴ እንደምትማራቸው ዓይነት። ግን ዘመኑ መራራን ማድመጥ አትራፊ ስለመሆኑ እዬታዬ ነው። መራራውን መናቅ ደግሞ የውድቀት መጀመሪያ ስለመሆኑም ዘመኑ ተመሰጠረበት።

ከመራራዎቹ አምክንዮች ነው ዛሬ ላይ ትርፍ እዬተዛቁ የሚገኙት። ከ66 አብዮት ማግስት ነገረ አማራ በጥርስ የተያዘ ግን በመናጆነት የተቸነከረ ጉዳይ ነበር። የመፍትሄው ቁልፍ ግን ከነገረ አማራ ላይ የተነሳ መንፈስ ብቻ ነበር። ማለት አማራነት መራራነት ነበር ግን በራሱ አቅም ውስጥ ጎልቶ እንዳይወጣ ቁልጭ ያለ መድሎ ነበር። አሁንም አለ ትሉ ይሆናል ጊዜው ልጅ ነው እና የአብዩን መንፈስ በዚህ መንቀስ ብዕሬ አትደፍረውም። ላያቸውም የምፈቅዳቸው የጊዜ ሰንጠረዦች አሉና ... 

ነበር ስል ግን አሁን የለም ለማለት አይደለም። አልተጀመረም ቀድሞ ነገር። ነገረ አማራ በፖሊሰ ደረጃ ነው ጭቆናውም፤ ግለቱም። ስለዚህ ተንስኤው የፖሊሲው መወገድ ብቻ ሳይሆን እጭ የሰሩ ጸረ አማራ እሳቤዎች ጊዜ ብቻ ነው ነቅሎ የሚጥላቸው። ዛሬ እንኳን በ እኛ አቅም ለተገኘ መባቻ የሚታዬውም፤ የመደመጠውም ድፍረት ማጣቱም እዬታዬነው። 

ይህን መሰረት ለማስያዝ በራስ ውስጥ የበቀለ አቅምን በመገንባት ብቻ የሚገኝ ነው። ይህም መራራ ጉዞ ነው። አሁንም አማራነት መራራነት ነው። የትኛውም አካል  ለድል ካበቃ ወይንም መሬት የረገጠ አቅምን ካገኘ በኋዋላ እንዲታጠፍ ወይንም እንዲሸበለል ይፈለጋል። በማወቅም በላማወቅም። ይህ የጅልነት መንገድ ነው።ያን መንገድ የሳተ ለውጥም አያቀጥልም። በጣም በእርግጠኝነት ነው ይህን የምናገረው። 

ያን አማራነትን ተቀብሎ ዋንኛ የትግል መስመር አድርጎ የተነሳው መንፈስም ቢሆን ቢሰተው መከራውን በእጥፍ ድርብ ቢያስጨምረው እንጂ የሚያገኛት ፍርፋሪ የመንፈስ ትርፍ የለም፤ በዬትኛውም መስፈርት ቢሆን። የአማራነት ፍልስፍና እና ፈተናው በራሱ አንድ የትምህርት ተቋም ነው። ስለምን ይህን እንደምል በትጋት እሰራበታለሁኝ። አሁንም የራሴ ብሎግ አለኝና። 

አማራነት ከእንግዲህ ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ከአማራ ሥነ - ልቦናዊ አቅም ማውጣት መሰረዝ ለነገ የአማራ ትውልድ ፈቅዶ ሞት የማወጅ ያህል የወንጀሎች ቁንጮ ነው። አማራ ህፃናት ሳትወለዱ ቅሩ ብሎ የመፍረድ ያህል ነው። የ አማራ ጋብቻ ይቁም ብሎ እንደ መገመደልም ነው።  የአማራ ተጋድሎ ሥረ - መሠረቱ በህልውና ክታብ ቢከተብ የተገባ ነው። አማራነት እንደ አደጋ ምልክትነት ነው የሚታዬው። 
  
ስለዚህ መራረነትን ስንቀበለው ጣፍጭነትን እንደሚያስገኝም አስበነው አምነንበት ሊሆን ይገባል። አማራነትን ስንቀበለው በታማኝነት ለመዝለቅ መቻል ያስፍልጋል። ወጀብ በመጣ ቁጥር ሰበር ቀለስ ልንል አይገባም። ምክንያቱም ትውልድን የማስቀጠል ተልዕኮ አለውና። ሌላው ስለ እኩልነት በሚናገርበት ወቅት እኛ ስለመኖር ነው ገና እዬታገልን ያለነው። ገና መኖራችን ስላልተቀበሉት ነው ተጋድሏችንም በሆነ ስንክሳር ዲሪቶ እንዲደለዝ የሚፈለገው። 

ዓላም ለመዝለቅ የሚያስችለው ግን አማራው የተነሰለትን ዓላማ እርግፍ አድርጎ በመተው ሳይሆን በዘለቀው ሃሳብ ውስጥ ሰክኖ በማስተዋል ቁምነገሩን መጥለፍ ሲችል ብቻ ነው። መከበር በተግባር እንጂ በሳይበር ጽ/ ቤት አይደለም። „ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳው“ እንደሚባለው ነው …
  • ·       ሬ ትንሽ ቆይታ ከግንቦት 7 ጋር አሰኜኝ።

ግንቦት 7 የበተናቸውን ነፍሶች ለመሰብሰብ ከመንበሩ ወርዶ ይቅርታ መጠዬቅ አለበት። ከልቡ ሆኖ ለበጣ የትም አያደርስም። እንዳለደረሰውም ህይወቱን አይቶታል። አማራን ባገለለ ማግሥት ያተረፈውን የሥነ - ልቦና አቅም አይቶታል። ለዚህ ነው ዝም አትበሉ መንገርም ማናገርም መልካም ነው በሚል ብዕሬና ብራናዬ በጋራ የሚሉትን ሊሉ የፈቀዱት  -  በአክብሮት።

ግንቦት 7 አንሳሳትም፤ አጥፍተን አናውቅም፤ የሰማዬ ሰማያት ቅዱስን ብፅአን ነን ስለዚህም ተጠያቂ አንሆንም የሚለውን መታበዩን ሰብሮ መውጣት አለበት። ይህ የሚሆነው ለምርጫ ድርድር ሳይሆን ሰው ናችሁ ብሎ ከማመን እውነት ነው። መፈጣራችን መቀብል አለበት ግንቦት 7።

ያለፈውን ረስተን የወደፊቱን እንይ አያስኬድም። የቅንጅት ችግር ፍርጥርጥ ተደርጎ ውይይት ተካሂዶበት ቢሆን ኖሮ ለዚህ ዳግሚያ ሽንፈት አይጋለጥም ነበር። ተሸንፍናል እኮ። ኦህዴድ እኮ  የኢህአዴግ አባል ድርጅት ነው። ፕሮግራሙ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፈሴቶ ፍልቀት የተሰላመ ነው። እኛም ሰጊድ ለኪ ያልልነት ለዚኸው ነው። አዲስ መንገዶች መከተሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ...   

ስለዚህ ግጥም አድርጎ አሸንፎናል ኢህአዴግ። በምርጫውም በቀጣዩ ያሸንፈናል። ያን እዬሠራበት ነው ያለው። ሲጀመር „ይቅርታ“ ጠይቆ ነው። ደፍሮ „አሸባሪ“ ነበርኩኝ ብሎ ነው። ደፍሮ እንደ ድርጅት „ኢ- ሰባዓዊ ድርጊት ፈጽሜያለሁ ብሎ“ ነው። ደፍሮ „ሰርቄያለሁ በሙስና ተዘፍቄያለሁ“ ብሎ ነው።

ስለሆነም አቤቶ ግንቦት 7 የሄደባቸው መንገዶች በግልጽ ቋንቋ ሸፍጥ ነበሩ። ስለዚህ ቁልጭ ባለ አማርኛ ይህን በአደባባይ መቀበል ዝቅ ብሎ ይቅርታ መጠዬቅ አለበት።

የዋሻቸው ብዙ ነገሮች ናቸው። ሚዲያውም ዋሽቷል። በተለያዩ ድምፆች የአማራን ተጋድሎ ዘገባ ያቀረበበት መንገዱ መረጃው መዳፍ ላይ አለና ይህን ደፈር ብሎ ራሱን ዝቅ አድርጎ ይቅርታ መጠዬቅ ቢያሰከበረው እንጂ ከክብሩ ቅንጣት ታክል የሚቀንስበት አንዳችም ነገር የለበትም።

ዝም ብሎ ቢተው ግን ያው ጊዜውን እዬጠበቀ ፍንጩ እዬተውለበለበ ያደናቅፈዋል። በቀላል የጀመረው ጉግስ ነው አሁን ሊበርድ ያልቻለው። ነፍሴ በአማራ ውስጥ አለች ብሎ ግንቦት 7 አያስበው። ምክንያቱም ታማኝ ስላልሆነ ለማድመጥ እንኳን አቅም የለንም። ያን ጊዜ ግንቦት 7ን በተቀበለበት መንፈስ በዛ ውስጥ አማራ አለ ለማለት መድፈሩ አይገባውም። ብዙ ነገሮች ፈርሰዋል።

አሁን የአርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር መፈታት ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት ለትግል ያለው ትጋት ትንግርት ነበር፤ ግን አጀንዳው የሆነ ሰው ከምቀርባቸው ሁሉ ላገኝ አልቻልኩም። ምክንያቱም ጎንደር በአንዳርጋቸው ጽጌ ምክንያት ነው እና የተቀቀለው።

ምስጋናውም ቀርቶ፤ ይቅርታውም ቀርቶ አሁን አንቱታው የሥም የግለሰብ ሲሆን ነገን ሊያስቀጥል ይችላል ሲባል? አይችልም ነው። ለዛውም ለዘላቂ የነፃነት በትረ ሙሴነት ምንም ነው። ለግለሰቦች ሥም እና ዝና እንጂ ለዛ ደምን ለገበረ ህዝብ አለመሆኑን የሰሞናቱ የስሜን አሜሪካ ንግግሮች፤ የአዲስ አበባ አቀባባሎች እና ሁነቶች እያታዩ ነው።

ቀጣይነት የነበሩትን ደክመቶች ተጠያቂ ነኝ ብሎ በመቀበል ብቻ ሳይሆን ተሽሎም በመገኝት ብቻ ነው። ለዛውም በሽፍኑ፤ ድክመት ተከድኖ ጊዜን እንግፋው ቢባል ብክነት ነው … ዛሬ በጅ የሚል የለም።    
  • ·      ዘመቻው እና ብክነቱ።

አቅሙን ያከሰመው ግንቦት 7 ራሱ ነው። ያፈራን የማናቸውንም አቅም ይፈራል። የሌላውን አቅም ኢትዮጵያን ነፃነት ይጠቅማል ብሎ አስቦ አያውቅም። አይድገፍም። ፈጽሞ። በግልም ይሁን በጋራ አቅም ሲበትን እና ሲታገል ነው የተኖረው። ግንቦት 7 ለዚህ ነው አሁን  በእንብርክክ  የኢህአድግ አቅም ተጠዋሪ የተሆነው። ለዛውም ይህ የተስፋ መንገድንም ታግሎ ታግሎ ሳይሳላከት ስለቀረ እና ከአቅሙ በላይ የወጣ አቅም ስለሆነ ብቻ ነው ሽንፈቱን የተቀበለው። እትጌ ኤርትራም ደስታውን በማጣጣሟ ብቻ ሳይሆን ህጋዊ መሰረት ያለው እርምጃም በመወስዷ ነው። 

የሌላ አካልን ሆነ ግለሰበን አቅምን ግንቦት 7 እንደ ራሱ አድርጎ እንደ አንድ የኢትዮጵያ የመፍትሄ መንገድ አድርጎ አይወስደውም። ከእሱ ውጪ ያሉ አቅሞች ስጋቶቹ ናቸው። ውክል አካሎችም የሚከተሉት መርህ ይሄንኑ ነው። አንድም አቅም በቅሎ ጸድቆ አያውቅም ሲዊዘርላንድ። ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የሚከለከልበት አገር ነው ሲዊዘርላንድ። መጸሐፍት እንዳይሸጡ የሚታገትበት አገር ነው ሲዊዘርላንድ። ሲዊዘርላን አቅም ላላቸው ኢትዮጵውያን ግዞተኛ ናት። 

ለዚህም ነው ተግባራቸው በዬአካበቢው ሥም በመበከል እና በማህበራዊ ህይወትን በማመሳቀል የማፍያ ተግባራትን በትጋት ሲከውኑ የኖሩት። እሱም ጎሽ ቀጥልሉኝ እያለ ሲከበክባቸው የኖረውን ነፍሶች ሁሉ መግራት አሁን ግንቦት 7ይጠበቅበታል።

ከዚህ የሚያምሱነን ንጉሶችን ወቅሶ ይቅርታ መጠዬቅ አለበት ግንቦት 7። ግንቦት 7 ከለብለብ ጉዞ ወጥቶ ወደ እውነተኛ የብቃት ደረጃ ለመሸጋገር አራሱን መመርመር በእጅጉ ይኖርበታል።

በሃሳብ ደረጃ የሚበልጠው መንፈስን አሸንፎ ለመውጣት የምጥ ጊዜው ነው ለግንቦት 7። ከሌሎች ድርጅቶች በበለጠ ለግንቦት 7 ይህ ዘመን ፈታኙ ዘመኑ ነው።

ከዛ መንበር ወርዶ እንደ አንድ ተወዳደሪ ፓርቲ ሆኖ በሃሳብ ልቅና አሸንፎ ለመውጣት መከረኛ ፓርቲ ቢኖር ግንቦት 7 ነው። ከፈለገው ፓርቲ ጋር ቢዋህድም ቢጣመርም ፈተናው እጅግ ግዙፍ ነው።

እግዜሩ ረድቶት ኦህዴድን መዋህድ እስከ አልቻለ ድረስ ፈተናው እጅግ መርግ ነው። ስለዚህ ሲከተለው የነበረው ማናቸውም ስንኩል መንገዶች ሁሉ መለወጥ አለበት። ከሶሻሊዝም ፍልስፍናዊ ዴሞክራሲያዊ ማክላዊነት መርህም ለመውጣት እራሱን ማሸነፍ አለበት። ከእውነት ራሱ መለወጥ አለበት። ይችላል ወይ? አላውቅም።
  • ·       ለግንቦት 7 አገር ቤት በመሄድ ረገድ ፈንጣጣ ነው።

አገር ቤት በመግባት እረገድ ውሳኔው እኔን አስደንግጦኛል። ምን ተይዞ? ደመ ከልብ መሆንም እንዳለ ማሰብ የተገባ ነው። የአብይን መንፈስ ለማገዝ እኮ ብዙ መንገዶች አሉ። በሎቢ ሥራ ማገዝ።

ግንቦት 7 የሚያሰማራቸውን ሃሳብ በታኝ ወታደሮችን ማስቆም፤ በድርጅቱ መንፈስ ውስጥ ያሉ ግን አዋኪ መንፈሶችን አርቆ መግራት ይገባዋል። ያን ካደረገ ያቆሰለውን፤ የቃጠለውን መንፈስ ሁሉ መጠገን ይችላል። እኔ እራሴ አዳምጬው አላውቅውም።

እራሱ ጋዜጠኛ ሲሳይን አጌናን ሁልጊዜ እንደምለው ማዳመጥ ብፈልግም ግን ጠቅላላ መንፈሱ ስላልተመቸኝ ካቆምኩት ቆዬሁ፤ ድሮም እፍታን ብቻ ለዛውም ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ከኖረ ብቻ ነው እምታደመው። እፍታ ደግሞ ተዘግቷል። ስለማላዳምጠውም ነው ሙግቱ የቆመው።

ውይይቶች፤ ንግግሮች ሁሉ ኢትዮጵያን ሲገነቡ፤ ቅንነትን ሲያበረታቱ፤ አዎንታዊነትን ሲያግባቡ አልኖሩም፤ ይህን የአብይ መንፈስ ፊት ለፊት ወጥቶ ያጠቆረው ግንቦት 7 እስከ ሚዲያው በዘመቻ ነበር። አድክሞናል ሌት እና ቀን ካለ እረፍት አስርቶናል።

ግንቦት 7 በታሰበው መልክ ጠንካራ ቢሆን ምንም አልነበረም፤ በሌላ አቅም ኢትዮጵያን ትንሳኤ ከማሰብ ይልቅ ባለ አቅም፤ መዳፍ ላይ በተገኘ ስልት የተሻለውን መንገድ መከተል አትራፊ ነበር።

ነገር ግን እኛ እንሰበስባለን ግንቦት 7 በሙሉ ሃይሉ ተንቀሳቅሶ ብዙ መንፈስ ሲባትን ነው የባጀው። ያን መንፈስ ለመሰብሰብ እንደገና መሥራት ይጠበቅበታል።

ከተመሠረተ ጀምሮ ግንቦት 7 የጦርነት ቀጣና ነበር። ያልተጋጨው ድርጅት፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ አልነበረም። በዛ ዘልቆ ለድል በቅቶ ቢሆን ኖሮ መስዋዕትነቱ የተገባ ነበር ግን አልበቃም። አሁንም ተሸናፊ ነው።

ወደፊትም በዛ መስመር አንድ ስንዝር መራመድ አይቻለውም። ስለዚህ የተከተለው ስልት ይበለው ታክቲክ፤ መርሄ ይበለው በትሬ እንደገና መርምሮ መለወጥ አለበት። አለኝ ያለው መንፈስ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ፕሮ አብይ ሆኗል። እኔም የዛሬ ሁለት ዓመት ይህ እንዳይሆን አብክሬ በተከታታይ ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰዳዳል ብዬ ስጽፍ ነበር የባጀሁት። የሆነው ይሄው ነው። የቀረው የሃብት ርፍራፊ የለም።

ስለሆነም ይሄ  ሃሳብን እንደ ተቀናቃኝ አይቶ የማውገዝ፤ የማሳደድ የማግለል ጉዳይ ይቅርታ ሊጠይቅበት ይገባል ግንቦት 7። እሱ ከአብይ መንፈስ ጋር ተጋባሁ ቢልም ታች ያለው አልተነካም። ይህ የድብብቆሽ ጨዋታ መቆም አለበት።

ወደ ራስ መመለስ ከታች እስከ ላይ መንፈሱን ጤናማ ማድረግን ይጠይቃል። አገር ቤት ሄዶም መሰሉ እንዳይፈጠር። ይህም  የአመራር ጥበብን ክህሎት ይጠይቃል። ተመክሮም። የአተረፈው የአብይ መንፈስ ነው። እሱን ፍለጋ ነው ሺዎች የተመሙት። የት ላይ እንዳለ ግንቦት 7 ሆነ ሚዲያው ኢሳት አይቶታል በጠራራ ጸሐይ።

ያ በዬቀኑ ሲበተን የነበረው የብራና ፍጆታ ሁሉ ለክቶታል ከንቱ ሆኖ መቅረቱን። የቅድስት ኦርቶዶክስ ውሳኔ እና ምዕመን በራሱ አንድ ትልቅ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
  • ·      አብይ መንፈስ እና የግንበት 7 ቃል ኪዳን። 

የአብይ መንፈስ ግንቦት 7 ግንቦት 7 ስላለ፤ የአብይ መንፈስ ኢሳት ኢሳት ስላል የሚሆን ነገር የለም። አብይ የትናንት ነው እኛ ግን ሲፈጠር ጀምሮ ግንቦት 7 ሲቆስል አብረን ቆስለን፤ ሲከስል አብረን  ከስለን፤ እሱም ያን መስዋዕትነታችን ከቁጥር ሳያገባ  ራሱ አቁስሎን፤ አክስሎን፤ አስገልሎን፤ የመኖራችን ሰላም አሳውኮ፤ ከምንኖርበት ማህበረስብ አስወጥቶን በውስጥ ቋያ አቃጥሎን ኗሯል።

…  በተጨማሪም የአብይን ሰውኛ መስመር ከማንም እና ከምንም ከድርጁቱም ከኦህዴድ፤ ከራሱ ከአብይ መንፈስም በላይ የሥርጉተ  ብዕሯ እና ሳተናው ብራና ፤ በተጨማሪም በተገኘው የሳይበር መስመር ሁሉ ተተግቶለታል።

ነገር ግን ሥርጉተ ትናንትም ልብ እንዲገጠምላት አትፈቅድም፤ ወደፊትም እንዲሁም። ትናንትም በፕሮፖጋንዲስት አለደገፈችም ወደፊትም አትደገፍም።

ሥርጉተን ደጋፊም ሞጋችም የሚያደርጋት መርህ ነው። አማራነቴን ወደ ኋላ በል አታስፈልገኝም ከእንግዲህ አልለውም። በፍጹም። አማራነቴ የደረሰበት ግፍ እና በደል የውስጤ ቋያ ነው። 

ቢያንስ ሰው ነሽ አማራም ብትሆኝም እንድባል ዕውቅና እንዲሰጠው እፍለጋለሁኝ። ከእሳር ከእንጨት ከአሽዋ አልተፈጠርኩምና።ተጋድሎውም የተገባው ክብር እና ልዕልና ሊሰጠው ይገባል። አሸናፊ ስለመሆኑም ሊዘከር ይገባል። "ሰው አለው ያግባሽ" ከሆነ ግን ነገም ብክነት ነው በወዘተረፈ ...

ስለዚህ አማራነቴ ተገሎ ብቻ ሳይሆን ተሰቅዞ መኖሩ እንዲቀጥል አልሻም። ይህ ሚስጢር ነው ከግንቦት 7 ጋር ሆነ ከኢሳት ጋር ያለው የተቃርኖ ተደሞው መታረቅ ያለበት ቁም ነገር። ስለምን ነገ ንጉሠ ነገሥት አይሆኑም ኢሳትም ግንቦት 7ም። ለእኔ ጉዳዬ ከእኔ የተነሳ ሰውነት ብቻ ነው። ኦህዴድን የደገፍኩት በዛ መንፈስ ነው።

ኦህዴድን የደገፍኩት አማራን ሰው ነህ፤ ድጋፍ ያስፈልገኛል ብሎ ባህርዳር ስለዘመተ ነው። አቅሙን የአማራነቴን ስላወቀ፤ ስለተቀበለ ከአለ አንተ የእኔ መንፈስ አሸናፊ ሆነ መውጣት አይችልም ብሎ ስላመነ ብቻ ነው።

ኦህዴድ ታማኝነቱን ያወለቀ፤ ያሾለከ ቀን ደግሞ፤ በቃሉ ያልተገኘ ቀን ደግሞ ከራስ በላይ ንፋስ ይሆናል …። ቀጪውም ፈጣሪ ነው። እኛ እንጂ ሚኒያ ፖሊስ ይሁን ሜኖ ወይንም አቶ ጃዋር መሃመድ ሆነ ፕ/ ህዝቃኤል ገቢሳ አይደሉም ቀን ከሌት የታታሩለት። በድምጽ እንዲያሸነፍም ያደረጉለት። የሎቢንም ሥራ የሠሩለት። አማራ እና የአማራ መንፈስ እንጂ። 

ኦህዴድን አሸናፊም ያደረጋቸው የአማራ አምላክ ብቻ እና ብቻ ነው።  ስለዚህ እንደ ከሰልን እኛ ስነቀበል ተቀበሉን፤ እኛ ስንወደው ውደዱልን፤ እኛ ስናነግሰው አንግሱልን አይሆንም አብይሻ ይህንን ልብ በለው። ይህ ማለት እኔ ሥርጉተ ሥላሴ የአማራነት ደም የለኝም ብሎ ራስን መካድ ነው። ክህደት ቢኖርብኝ ፓርቲዬን ኢሠፓን የፖለቲካ ሰብዕናዬን ሙሉ አድርጎ የቀረጸውን ጓድ ገ/ መድህን በርጋን ክጄ በስንት አዳዲስ ጃኬቶች በተጠቀልኩ ነበር። ይህን ከማድርግ ብሞት ይሻለኛል። 
   
አብይን መንፈሱን፤ ለማን መንፈሱን ስደግፈው የወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌሰቶ፤ ህገ መንግሥቱን፤ ብሄራዊ መዝሙሩን፤ ባለኮከቡን ሰንደቅዓላማውን ተቀብዬ አይደለም። ብሄራዊ መዝሙሩ ሲዘመር እኔ አልነሳም። የእኔ መንፈስ የለውም እና።  

በወያኔ ሃርነት ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖቴን እና የዘር ሐራጌን አማራነቴን ሊያጠፋ ለተነሳ ማንፌስቶ፤  አማራነቴን እና ማተቤን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቴን ከ9 የሸነሸነ የህሊና ቋዬ ፈቅጄው ወድጄው አይደለም ኦህዴድን የደገፍኩት። ኦህዴድ ሰውኛ ተፈጥሮኛ ነው በማለት እንጂ ... 

የቅደስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን በጠላትንት ፈርጆ ከማናቸውም ፖለቲካዊ ተሳትፎ 27 ዓመት ሙሉ አግልሎ ባይታዋር ያደረገ ነው ኢህአዴግ። ስለዚህ በዚህ ድርድር የለም። ነገር ግን መንገድ ሲጀመር ለማሻሻል፤ ለመለወጥ ለዛውም ይቅርታ ተጠይቆበት ሲሆን ሊደገፍ ይገባል ከሚል ቅናዊ፤ አዎንታዊነት ነው … ሙሉ መንፈሴን ካማንም እና ከምንም በቀደመ ሁኔታ የተቀበልኩት። ከዚህ ሌላም የፈጣሪ ምርቃትም አለበት ብዬ ሰልማምን ከገሃዱ ዓለም ይልቅ መንፈሳዊ ገዢ ሁነቶች ስለሚመሩኝም ጭምር ነው። 
  • ·      ስለምን ትኩረቱ በግንቦት 7 ላይ ሆነ።

ትክክለኛ ጥያቄ ነው። አገር ምድሩን መሪው እሱ ስለነበር ነው። ጎልቶው የወጡትን በመወሰድ፤ በመዋጥ፤ አሻም ያለውን ምድማዱን በመመንጠር፤ በመጫንም አውራው መንፈስ የእሱ ስለነበር ነው።

በተሟላ ብቃቱ እና ፖለቲካዊ ቁመናው፤ በብልህ ጥበቡ እና ከሁሉም በላይ ልብን በሚገዛው ትህትናው ኦህዴድ አሽንፎት ነው እንጂ የቤተ መንግሥት እጮኛው እሱው ነው የነበረው አቤቶ ግንቦት 7 ። አውሮፓ ህብርትም አጽድቆለት ነበር። እትጌ ኤርትራም ሰፍ ብላ ጠብቃው ነበር።  ቢኦኤ VOA ራሱ ወያኔ ከተሸነፈ ግንቦት 7 ቢሆንለት ምኞቱ ነበር ኦህዴድ ከሚሆን። በጣም በተደራጀ ሁኔታ ቢኦኤ ሠርቶበታል።

ግን ሰው ካሰበው እግዚአብሄር በለጠ እና የሆነው ሆነ። እኔ ለቅባ ጉዳዬ አይደለም። ተግባሩ የእኔ ሳይሆን የፈጣሪው ስለነበር። የፈለገ ይንገሥ ግን ዕውነትን በሚመለከት የራሴ መርህ፤ የራሴ መንገድ፤ የራሴ ሎጅክ አለኝ። የማይላጥ፤ የማይጋጥ። ምን እንዳለኝ፤ ምን እንደሚፈቀደልኝ፤ ምን እንደምችል እና እንማልችል አሳምሬ አውቃለሁኝ። 
  • ·      ግንቦት 7 በራሱ ውስጥ ይፈጠር።

ግንቦት 7 ከቀስት ደመና ጀምሮ የማዬው መንገዱ በራሱ ውስጥ የመፈጠር ፍልስፍና የለውም። ቅንጅት ሲፈጠር ድርስ ቶሎ አንዳርጋቸው፤ አላይንሱ ሲመጣ ፍጠንልኝ ደረስልኝ አንዲ፤ ግንቦት 7 ሲፈጠርም ድረስለት አንዳርጋቸው ነው እኔ በግሌ የታዝብኩት። በውስጡ ያለመብቀል ስስነቱን የአርበኛ አንዳርጋው ጽጌ እስር እና የገጠመው ፈተና ሊያስተምረው ይገባል ለወደፊቱ።

በሌላ በኩል አቅም በመጣ ቁጥርም ያን መጠመንም የትም አያደረሰውም። ይህም „በድምጻችን ይሰማ“ የነበረው ትልቁ ግድፍት ነው። የሰላም ፋውንዴሽን ማንን አክብሮ እንደጠራ እና የማን መልዕክት እንደናፈቅ አይቶታል ግንቦት 7 ቁጭ ብሎ።

ሌላው ፖለካዊ ዕድማታም ባይኖረውም በውጩ ሲኖደስ ላይ የነበረው ምልክታም የእኔ የማለት በዛ የመማለል ፍላጎት ነበረው ቢሆንም፤ ይህም ቢሆን አባቶች በራሳቸው መንገድ 7 ቀን የታቀደውን ጉባኤ በሦስት ሰዓት ከውነው እርቁን የተቀበሉበት መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ አዲሱን ያወጡትን መግለጫ ሙሉ ለሙሉ ሽረው እምነታቸው በይስሃቅ ላይ አድርገው አብርሃሙ አብረው ወደ ባዕታቸው ለመሄድ መወሰናቸው በራሱ ትልቅ ተቋም ነው ከተማረበት ግንቦት 7።  

ሁሉንም የመቆጣጠር ነገር ራስ በሰሩት ስራ እንጂ በጥገኝነት ከሆነ ኮከብ ቆጣሪ አድርጎ ቆሞ ቀር ያደርጋል። ስለዚህ በራስ መንፈስ ውስጥ አንቱታን ማብቀል ግድ ይለዋል ግንቦት 7።

ሌላው የሄ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን የመልቀም ጉዳይ ይህም ከቀስተ ደመና ጀምሮ አብሮ የተወረሰ መንገድ ነው። አሁን ሰማያዊ ፓርቲም ተከተል ዓለቃህን ብሎበታል። ይህም የሚያስኬድ አልሆንም። አርበኛ አትሌት ሊሊሳ ፈይሳ የወሰደው እርምጃ ታላቅ ምስክር ነው። ከዚህም ባሻገር ሌሎችም በግለሰብ ደረጃ የተጠጋቸው ሁሉ የራሳቸው ሰብዕናን በመገንባት ላይ እንደሚታታሩ ቁልጭ ብለው እዬታዬ ነው።

ምን ለማለት ነው ግንቦት ሰባት መፈጠር ያለበት በራሱ አቅም ውስጥ ነው። በራሱ ውስጥ የራሱን ችግኞች የማብቀል ሥራ መሥራት መትጋት አለበትም። „የሰው ወርቅ አያደምቅም“ የሰው እልፍኝ የሰው ነው። 

እርግጥ ነው እንደ ዕድል ሆኖ እራሱ ከብክቦ ባነገሳቸው መንፈሶች ላይም አትራፊ አልነበረም ግንቦት 7። አሁን የጋዜጠኛ መሳይ መኮነን፤ የአቶ ኤርምያስ ለገሰ ፖለቲካዊ የምክር አገልግሎት የመንገድ ቅዬሳ ብሂል፤ የጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ መጣጥፎች በራሳቸው እጅግ አስገማች እና የድርጅቱን አዎንታዊ አቅም፤ የቅንነት ውስጥነት ግምት ውስጥ ያሰገባ ግንቦት 7ን በውል የሠፈረ አመክንዮ ነበር። 

በዝምታ ውስጥ የሰከኑት ናቸው ሥማቸው ነግሶ ያሰከበሩት። በዝምታ ውስጥ ያሉ በርካታ ፍሬ ነገሮች አሉ። አቅም ባይኖር እንኳን ተከብሮ መኖርን የሚወስደው የለም። ይህንን መምራት እና ማስተካከል እንኳን አልተቻለውም ግንቦት 7። ለዛውም የስንት ብቃት ማዕድ ሆኖ።
  
ስለዚህ የእኔ ብሎ በተለዬ ሁኔታ ከብክቦ አሳድጎ፤ አዳጎሱ የምርጫውን መስፈርት አሟልተውልኛል ብሎ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሆኑልኛል ብሎ አልቆ አጎልብቶ የሚወጣበት መስፈርቱ የግንቦት 7  አትራፊ አይደለም። የጎደለው ብሎን አለ።

ሌላው በሰው ሃሳብ ላይ ዘው የሚለውን ነገር በፍጹም ሁኔታ ማቆም አለበት። ምክያቱም ካለፉት ዓመታት እንደታዬው አቃጁ መርሃ ግብሩን ሲሰበው እሱ ማህል ላይ ነው የቀረው። በተናገረው ቃል ውስጥ መዝለቅም ማፍራትም አልተቻለውም። ይህ ወደል የፖለቲካ ግድፈቱ ነበር የግንቦት 7።

በተገመተው ልክ መሆን ተስኖት እንዲህ መሆኑ እጅግ ያርመጥምጣል ለእኔ። ቢያንስ ክብሩ እንዳለ በዛ ውስጥ ተፎካካሪ ሆኖ ቢወጣ  የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህብራዊነት ጠረኑ ጥሩ በሆነ ነበር። ግን የሚሆን አልሆነም። 

ወደፊትም አጀማመሩ እራሱ ያማረ ስላልሆነ ተስፋ የለኝም … ያን ክብሩን የማስመሰል ቢያንስ በመንፈስ ያለውን ሃብት የማመጣጠን አቅሙን በሚመለከት … ጥሩ የፖለቲካ አማካሪ አልነበረውም ወይንም ብልህ ምክርን የሚቀበል መንፈስ አልታደለም።

ስለዚህ ወደፊት በራሱ ሃሳብ ወስጥ ማቀድ እና መንቀሳቀስ፤ የሚያወጣቸውን ሰዎች ጎልተው ስለወጡ ሳይሆን ሰብዕናቸውን የመረመርም፤ ጽናታቸውን ከሥረ መሠረታቸው የማጥናት፤ አጉልቶም አኮስሶም ሳይሆን ልኩን የጠበቀ ሚዛናዊ አያያዝን በመርህ ደረጃ መከተል፤ የራሱን ሥራ እዬሠራ በውሰጡ በበቀለ አቅም ዜናውን መሥራት መጀመር ይኖርበታል። የሌላ ድርጅት የቀን ከሌት ዘጋቢ እና ተንታኝ ከሚሆን። 

እውነትን መደፈር፤ ድርጅቱን እንጂ ግለሰቦችን ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጎ የማውጣት አዳጋውን ስላዬው፤ ካለፈው ተምሮ ለተነሳበት ዓላማ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መትጋት፤ ጥገኝነትን፤ መጠለልን ማራቅ፤  በአቅሙ ልክ መመኘት፤ ሥማቸውም ዝናቸውም ለማይታወቀው ግን ለእውነት አርበኞቹ ምስጋን ማድረግ፤ ቀን ከሌት የደከሙ የለፉ የታታሩ አሉና። ለናሙና ሙንሽኖች፤ ፍራንክፈርቶችን ማንሳት እችላለሁኝ እኔ። ድካማቸው እንዲህ ቢሆንም፤ ባይሳካም ለተልዕኮው ግን እነሱ ሁሉመናው ነበሩ ኢጎኢስት አልነበሩም።

ግንቦት 7 ተጽዕኖ ፈጣሪ መልቀሙን ማቆም ይሄ በትምህርት ደረጃ፤ በብሄረሰብ፤ በአካባቢያዊ ስሜት በመሰሳለው ያለው ዝበት የሚታይበትን ምልከታ ማቆም አብሶ ለአጃቢነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ከውስጡ ካለ? ? ? አማራም ሰው ነው ማመን ያስፈልጋል አማራ ሰው ነው እኛ እንደምንፈልገው የፖለቲካ ዕውቅና እሱም ይፈልጋል ብሎ ማሰብ። 

አማራነትን ተቀበሉት ተብሎ የሚያስለምን ምንም ነገር የለም። ከተቀበሉት ግን ለዛም መታመን ነው። ታማኝነትን መርህ ማድርግ። ይህ ማለት አማራ ለግንቦት 7 መልሶ ያደግድጋል ማለት ሳይሆን፤ ብሄራዊ መሪ ለመሆን ከዚህ መነሳት ግድ ይላል ነው።

ይቅርታ መጠዬቅን መማር ይኖርበታል ግንቦት 7 ከብዙ በጥቂቱ … ሲደዋህዱ ወይ ሲጣመሩ አገር ምድሩ ሚዲያው ያጨናንቃል ተዋህዱ፤ ተጠማሩ ሲባል። ችግሩ ሲፈርሱ  ደግሞ ውሾን ያነሳ ውሾ ሆኖ የውሻማ ሞትነት መሆን የለበትም።

 በዚህ ምክንያት አብርን ነበርን በዚህ ምክንያት ፈረስን ተብሎ በይፋ  በአደባባይ ሊገለጥ ይገባል። አሁን እኮ የሚታዬው ጨዋታው ፈረስ ዳቦው ተቆረስ ዓይነት የልጆች ጨዋታ ነው። 

ያንያህል በተንጠራራ ፍላጎት ላይ የነበረው አገር አድን ንቅናቄው እንዲህ ሲበተን የተደመጠ ነገር የለም። በዚህ ውስጥ የባከኑ ነፍሶች እጅግ ያሳዝኑኛል። ሚዲያ ሁሉ ተጀምሮ ነበር። ግንቦት 7 በምን ሁኔታ ተፈጥሮ በሰከነ ፖለቲካዊ ጉዞ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚሰለፍ እንጃ ነው …

ግንቦት 7 ስህተቶቹ፤ ግድፈቶቹ ላይ መድፈር አይችልም። በዛው ድክምት ላይ መቀጠል ለነገም መቅኖ ቢስ ነው። በማህል ትውልድ ይባክናል … አቅም ይባክናል፤ ከሁሉ ማህበራዊ ዕሴታችን ተንዷል በግንቦት 7 ምክንያት። ይሄ ውጭ በምኖረው ላይ ሲሆን አገር ቤት ደግሞ ጎንደር ካለ አበሳው ባልተወለደው፤ ባልተዘመደው በሌለበት ሁኔታ የግራ ቀኙ የቂም ማወራራጃ ሆኗል። ተጥዷል፤ ተርመጥምቷል። ጋይቷል።
  • ·      ያልተጋባ ዳገት።  

ይልቅ ለግንቦት 7 የምለው ከቆሞስ ኢንጂነር ሰመኘው የግፍ ህልፈት ወዲህ አገር መግባቱን ብዙም አጓጊ አይደለም። ተግ ይበል። ጥሞና ይኑረው። ያጉ፤ ያልሰከኑ ጉዳዮች አሉ። አንድ መንግሥት ብቻ አይደለም ያለው  ኢትዮጵያ ውስጥ። ሦስት መንግሥት ነው ያለው። ውሉ ያልታወቀም የሽፍቶች ቡድን አገር ቤት አለ። ይህ የሽፍቶች ቡድን ያኮረፉ ግለሰቦች የፈጠሩት ነው። ሁለቱ ግን  የአዲስ አባባው እና የመቀሌው ነው።

አሁን ደግሞ ሌላ አራተኛም ይኖራል፤ ከፍ አድርጎ  ኢትዮጵያ መንግሥት ያንጠለጠለውን አውሮዶ ያፈረጠው ለት ያውቀዋል። ማውጣት ቀላል ነው ማውረዱ ደግሞ ያንኑ ያህል ፈተና ነው። 27 ዓመት የፈጀው ተጋድሎው መከራው ይሄው ነው፤ ስናወጣ ስልትም ጥበብም ፈጽሞ የደረቀብን ነን እና። ልክ አናውቅም። መጠን የለንም።

እና እናማ አደብ ግዙ ግንቦቶች ነው … ባትሄዱ እመርጣለሁ እኔ። ብትሄዱም  ከአብይ መንፈስ የተሻለ ዓላማም፤ የሃሳብም አቅም የላችሁም፤ ይህን እናንተው ታውቁታላችሁ፤ ስለዚህ አላስፈለጊ መስዕዋዕትነት ባትከፍሉ ምርጫዬ ነው።

 መርሃችሁን እንጂ እናንተማ ታስፈልጉኝአለችሁ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም። እራሱ ኢሳት ከዛው የኮሮስፖንዳስ ሰራተኞችን ቀጥሮ በ አንሰተኛ ቢሮ ማሰራት እንጂ ሙሉውን ሃይል ይዞት ቢገባ አደጋው ሰፊ ነው። አንድ ቦንብ ይበቃዋል አዲሱን ቢሮ ለማጋዬት። 

ተፎካካሪነቱ አሊ የሚባል አይደለም። መፎካከር ብቻ ሳይሆን አሸንፎ መውጣትም ይችላል ኢሳት እንደ ሚዲያ። ግን በቀደመው የአማራ ተጋድሎን በማግለል ዕሳቤ ሳይሆን  ከእውነት ጋር ከታረቅ ነው። አማራም አምላክ አለው እና። ከልባችን አልቅሰናል። አዝነናል። ወደፊትም በዝበቶች ዙሪያ ኤሉሄያችን አይቀሬ ነው።

ኢሳት ከኦቢኔ ጋር ባይወዳደር ጥሩ ነው። ኦቢኤን አገር ቤት ሙሉውን ሃይል ይዞ ለመግባት ችግር የለበትም። የባጀት ችግርም ሊኖርበት ይችላል። ግንቦት 7ም ቢሆን ከአቶ ጆዋር መሃመድ ጋር አለመወዳደር ነው የሚበጀው።  አቶ ጆዋር አህመድ ሰብዕናው ለእኔ ግራጫማ ነው። እሱን ለመተርጎም ይከብዳል።

 እርግጥ ነው አቅሙን የሚመራ አዎንታዊ የፖለቲካ ሊሂቅ አባት ካገኘ፤ ከግራጫመነት ወደ ቤዥ የማይለወጥበት ምክንያት የለም። የሆነ ሆኖ አቶ ጆዋር መሃመድ ዲታ ነው የመንፈስ ደጋፊዎቹ ብዙ ናቸው። ምቹ ሁኔታም አለው የሱን መንፈስ የሚቀበሉ አካላትም አይጠፉም። የበቃ የመንፈስ ሃብት መሬት ላይ አለው ማለት ነው። ጽኑ ጠባቂም አለው። 

አቶ ጆዋር መሃመድ ይህችን ዕድሉን አጥፏት ቢሆን ኖሮ ግን መለመላውን ቀርቶ ነበር። ሙቀቱ እንዳለ ሳይፈልስ አገረ ቤት ገባ፤ አሁን ነገ ካልከበደው  የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ ሙሉው ሴኔት የሄደ ያህል ሸር ጉዱ የጉድ አሳይቶናል ... 
  • ·      አደብ እንደ አማራ።

በዚህ ውስጥ አደብ መግዛት ያለበት የአማራ ማህበረሰብ ነው። አማራ ጥንቁቅ ብቻ ሳይሆን ቆቅ መሆን አለበት። ሁሉንም ፍቅራችን፤ ታማኝነታችንም፤ ሁለመናችን ሰጥተን አይተነዋል። በትርፍነት ማሟያ ስለመሆነችን ደግሞ ዕለታዊ ስንቃችን ነው።
  • ·      ፍጹም ግንቦት 7 ከወያኔ ጋር ሰውር ድርድር የለውም።

ይሄ አንገቴን እምሰጥለት ጉዳይ ነው። ደምሂት እንደሆነ ትንሳኤው ከመጣ ለዛ አስቦት ነው። አንዳንድ ጹሁፍ አነባለሁኝ ግንቦት 7 ከወያኔ ጋር ድርድር እንዳለው። ይህ በፍጹም ስህተት ነው።

የወያኔ ሃርነት አባላት ግን በግንቦት 7 ውስጥ ሊኖሩት ይችላሉ ገንዘብ የከፈለን ዲታዎችን ስለሚያሰባስብ እንደ ኢንሹራንስ ድርጅት።
ይህም ብቻ ሳይሆን ስልት እና ስትራቴጂውም የ66ቱ ዓይነት ስለሆነ ተመሳሳይ ነው። ሸምቅ ውጊያን እንደ ድል አስገኝ ሃይል በ21ኛው ምዕተ ዓመት ማሰብ በራሱ ከዛ የተቀዳ ነው።

በአውሮፓዎች መልካም ፈቃድ የመንግሥት ሽግግርን የሙጥኝ ማለቱም ከዛ የተዋሰው ነው። የደንቡ የቋንቋ ፈሊጥም ከዛው ጋር የተቀዳ ነው። የመንግሥት ምሥረታ እሳቤው ወያኔ ትግራይን ታላቅ የማድረግ ህልም ሲኖረው ግንቦት 7 ደግሞ ማህል አገር እና ደቡብ ህዝቦችን ያማከለ ነው።

ስለዚህ በውስጥ የፖለቲካ የመሻት ፍጥጫ አምሳያ መንትዮሽ ናቸው። አቅምን የማሰደድም በሚመለከት ግልባጭ ነው የግንቦት ስልት። በሌላ በኩል በጸረ አማራነት ሳይሆን የአማራ ሥነ - ልቦናዊ አቅም ጎልቶ እንዳይወጣ በመጫን ረገድ ከወያኔ በባስ ሁኔታ በሰውር የተከደነ አምክንዮ ነበር በግንቦት 7 የፖለቲካ ፍልስፍና።

 ይህ እንግዲህ በዘመነ ቅንጅትም ያልተገለጠ ግን ከአማራ ተጋድሎ ጋር እውን የሆነ ልባዊ ጉዳይ ነው። በዚህ ዕሳቤ በሙሉ ማለት እስኪያስብል ድረስ ህብረ ብሄር ነን የሚሉትም፤ የዞጎችም ሁሉም በአንድነት እርግት ያደረኩበት የሚያስማማቸው ሃሳብ ድር አማራነትን የመጫን ተኮርነት ነው።

ነገር ግን ግንቦት 7 ከወያኔ ጋር የወስጥ ድርድር የተሰወረ ጋብቻ በፍጹም የለውም። ልሁንም ቢል ሎጅኩ አያስኬደውም። የፈለገ ነገር ቢመጣ ይህን መሰልን አመክንዮ አልቀበለውም። ለዚህም ነው አገር ቤት እገባለሁ ሲል እማይመቸኝ። 

 አሁንም እኮ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መንፈሱ አቅሙ ሙሉው እንዳለ ነው። አልተነካም። አልተደፈረም። በማባበል፤ በማታለል፤ በማቆላመጥ ግን በጥበብ እና በስልት ለመያዝ ተሞክሯል። እስከመቼ ለሚለው እዬጠፋን በማጣፋት ፖለቲካዊ ግርድሾ

ሌላው ያልታወቁ የተሰወሩ መንገዶችም ዕድሉ አላቸው … እልህና ቁጭቱ ዘመኑን ማስከን ቢሞክሩም ሌላ ድፍን ድብልብል ያሉ ነገሮችም አሉ። ስለሆነም ያው በተለመደው ንቀቱ ግንቦት 7 ባያዳምጠኝም አገር ቤት ባይገቡ ምርጫዬ እንደሆነ ልግልጽ ግድ ይለኛል። 

አንዲትም ቅንጣት ከ2013 ጀምሮ 2015 ዘሃበሻ ላይ // ከ2015 - 2018 ሳተናው - አሁን ከግንቦት 1/2018 ጀምሮ ከቀንበጥ ብሎጌ ከተናገርኩት ካሰብኩት ፍሬ ያለፈራ የለም። ወድቆ በኖ የቀረ የለም ልብ ላለው።

ስለምን? የገበሬ ልጅ ነኝ እና። ሥርጉተ ሥላሴ የፖለቲካ ጎርፍ ያመጣው ስብዕና አይደለም ያላት። በፖለቲካ ዘርፍ ያላት ተመክሮ ብዙ እጅግ ብዙ ዕድሎችን አስተናግዳለች፤ በጋዜጠኛነትም። ብዙም ተመክሮ ሸምታለች። ለዚህም ነው ዘንበል ቀና የማትለው …  ባለፈው ጊዜ አቶ ሃብታሙ አያሌውን በሚመለከት ያልኩት ነበር።

ሰሞኑን አዋዜ አንድ ዜና ሠርቷል። „ኮ/ ደመቀ ዘውዱ ከነቤተሰቡ እንዲደመሰስ አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ ያመኑበትን ነበር፤ ነገር ግን ያሰቀሩት አቶ ደመቀ መኮነን ነበሩ።“ እንግዲህ ይታያችሁ ይሰማችሁ ያን ጊዜ ሃብትሽ እስር ቤት ነው። 

በሌላ በኩል ደግሞ „ጠ/ ሚር አብይ አህመድን ከሞት ለማትረፍ ቤቱ ያስቀመጠው እና ሽፋን የሰጠው አቶ ደመቀ መኮነን ነው ይለናል።“ እንግዲህ እሱ የኢሳትም፤  የኦ ኤም ኤንም አንባሳደር ሆኖ ዲሲ ላይ ነው ያለው፤ ሱፉን ለብሶ እዬተንጎባለለ የሚሠራ አገናኝ ሁሉ ብዬ ጽፌያለሁኝ።

ላንድ የኢሜል ወዳጄም ሃብትሽ አንቅጩን ጽፌለት ነበር።  ሌላው በኦህዴድ በአብይ መንፈስ ላይም የጻፍኩትን ማንበብ ነው። አሁን ግንቦታውያን እንደ ሥርጉትሻ ለማውያን ሆነዋል። ተመስገን ነው …

ሥርጉተ ሥላሴ በአቅሟ ልክ ነጥራ እንዳትወጣ ነበር ከ2006 እስከ 2017 ተጋድሎው የነበረው። ዘመኑ ጥሩ ነው የተገባውን በተገባው መልክ ኮለል አድርጎ አንተርትሮ፤ አበጥሮ፤ ሰላልቆ አንገዋሎ ፍሬ ዘሩን በመንሹ አንቱ አሰኝቶታል።

ሲዊዝሻም ኢትዮጵያዊ የአደራ ልጆቿን መክራ በአምክንዮ አድምቃ አያታለሁኝ። ዛሬ ከሁሉ ልቃ የሥርጉትሻ የቀንበጥ ታዳሚነቱን አንደኛ ደረጃ ላይ የተኮፈሱት ሲውዝ ያሉ ወገኖቼ ናቸው። ይኸው ነው።  በፀና መሰረት ላይ የተገነባ ማንነት ወርቅ ነው። ይነጥራል እንጂ አይፋድስም፤ ይደምቃል እንጂ አይወይብም።

የትውስት ያልሆነ የራሱ መንፈስ ያለው አያልቅበትም … ስለዚህም ቅልብስ ብሎ ሸሽጉኝን የሙጥኝ አይለም፤ ድፍሩ ጥሪቱ ነው። ትምህክቱ ደግሞ ያበራከተለታል ፈጣሪው አምላኩ።

ሥርጉተ ሞቅ ካለው ጋር አድርሻ ስትለቅም፤ እውቀኙ ብላ ስትባክን ስትንከራተት አትገኝም። በተደላደለው መንፈሷ ውስጥ በገደመቻት ድንኳኗ ሆና በልተጠመነ አቅሟ ዘልቃ ዕውነትን ስትተክለው ፈቅዳው ነው።  

እሱ ይሁነው ለኢትዮጵያ አዲሱ መንግሥት የማዬው ሁሉ ነገር ከሰነበተለት … ማጣሪያውም፤ ሠርግ እና መልሱም ድብልቅልቅ ብሏል። ይህን የሚያርም የሚያርቅ ፈር የሚያስዝ አንድ አቅም ያለው ብቁ አካል ያስፈልገዋል። 

ወጀብ በበዛ ቁጥር መርከቧ ሚዛኗን የሚፈታታነው አውሎ አያሌ ነውና። ዴሞክራሲውን ገና ሳትጀመረው ኢትዮጵያ …

የኔዎቹ ኑሩልኝ።  ዛሬ አከሰከስኳችሁ አያደለም? ለያውም ቃጠሎ ነው እሳት … ሙቀቱ አይሏል ... 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።