#ኢትዮጵያዊነት በራስ መተማመን ነው። (Confidence) (Vertraun) ነው። #ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሮኛ ዲፕሎማትም ነው። እኛ ነው ልኩ መሆን ያቃተን።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
ማህበረ ትህትና እንዴት አደራችሁ? እንደምን አረፈዳችሁ? እንዴትስ ዋላችሁ? ሁለት ተወራራሽ ዕርዕስ በአንድ ጭብጥ።
እስቲ እኛን በእኛነት፤ እኔ በእኔነት፤ ሁላችንንም በሁለመናነት አመጣጥኖ፤ ቀምሮ፤ መጥኖ ያበጀንን ኢትዮጵያዊነትን መርምሩት። ቅጥልጥል፤ ቀንድ እና ልጥፍጥፍ የሚያሰኛቸውን ወገኖቼን አይመለከትም ጥያቄው። እንደ ሰው አስበን፤ ሰው ሆነን እንዘልቅ ዘንድ ውስጣችን እራስ እጉሩ ያሰበለ እንዲሆን ያደረገውን ጀግናውን ማንነት ከህሊናችን ሁነን እንሰበው።
#አይደፈሬው ደፋሪውን ያስተምራል።
ሁልጊዜ፤ ለምንግዜም ኢትዮጵያዊነት ኦክስጅናችሁ ሲሆን፤ የትኛውንም የፈተና ጋራ የመበገር አቅም ታገኛላችሁ። ኢትዮጵያዊነት የተደራጄ ተፈጥሯዊ የአቅም ልዩ መክሊት ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የተመጣጠነ፤ ህብራዊ የሆነ ቀለማም መሳጭ ጸጋ አለ። ረቂቅ የሆነ በራስ የመተማመን አቅም አለ። ይህ አቅም ዩንቨርስቲ ገብታችሁ ብትማሩት የማታገኙት እንደ ላሊበላ አለት ጸንቶ የሚያጸና፤ ረግቶ የሚያረጋ #የመሰጠት ዲካ ነው።
#እርግጥ ነው ኢትዮጵያዊነት ተፈሪ ማንነት ነው። በልኩ መሆን ሲሳን ይፈሩታል። ይገባልም።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያዊነት የሚቀናበት ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት በጥበብ ውስጥ የሚዘልቅ የዊዝደም ጎዳና ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መንፈስ ሲቀማጠል ይደለዋል። ለምን? እርግጠኛ የሚያደርግ ልዩ ኢነርጂ ስላለው። ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው። ኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ነው። ኢትዮጵያዊነት ብርቱ ነው። ብርታቱ የሚነሳው አምላክ አላህ አለ ብሎ ከማመኑ ይመነጫል።
#ኢትዮጵያዊነት ባለማግኔት ማንነት ነው።
ልትሸፍትበት ቢጀማምርህ ፍልሚያውን ስለማትችለው ወይ ከቆሎው፤ ወይ ከቆጮው፤ ወይ ከድፎው፤ ወይ ከሚጥሚጣው፤ ወይ ከብርንዶው፤ ወይ ከዝልዝሉ፤ ወይ ከቋንጣው፤ ወይ ከፍርፍሩ፤ ወይ ከጨጨብሳው፤ ወይ ከቃተኛው ብቻ ምን አለፋህ ያው አንተው ያገለልከው እራስህ ስትጣደፍ ትገኛለህ። ይህ አገርም ውስጥም ኖርክ፤ ተሰደድክም እየተከተለ በአቅሙ ሥር የሚያንበረክክህ ኃያል ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት።
ከሌላ አገር ዜጋ ጋር በጋብቻ፤ በጓደኝነት ተገናኝ። አለኝ የምትለው የትውስት ያልሆነ፤ ቅጂ ያልሆነ፤ ውራጅ ያልሆነ ንጥር የራስህ የአኗኗር ዘይቤወችን በዓይነት ማቅረብ ትችላለህ። በሁሉም መስክ። የማንነት ቀውስ ከሌለብህ አራት ዓይናማው ኢትዮጵያዊነት ጎብጦ ሳይሆን፤ ተሰባብሮ ሳይሆን፤ ተኖ ባክኖ ሳይሆን ቀና ብሎ አለሁ የሚል የይሁንታ ንጉስ በርህርህናም ነው። ኢትዮጵያዊነት።
ኢትዮጵያዊነት ምን አጥቶ? ምን ቀርቶበት? ብሄራዊ አበባ፤ ብሄራዊ ዐዲስ ዓመት በተለዬ ቀመረ፤ ብሄራዊ የፊደል ገበታ ከዜማዊ ቃና ጋር፤ ብሄራዊ የራሱ የቀን አቆጣጠር፤ የፊደል ገበታ፤ የዓውደ ዓመታት ሥርዓት ያለው አንቱ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ቀመር ከዩንቨርስቲወች በላይ፤ በላይ ነው።
መኖርን በማሰልጠን ምን ቸግሮት፤ የተልባ ጭልቃ፤ የሱፍ ጭልቃ፤ የኑግ ጭልቃ፤ የሰሊጥ ጭልቃ ሌላው አገር ባልተጠቀመበት ኢትዮጵዊነት ይራቀቅበታል። የአዋዜው፤ የድልሁ፤ የአብሽ ጁስ፤ የእልበት ድግስ፤ የሽንብራ አሳ፤ የተልባ ፍርፍር፤ የገብስ ቆሎ፤ የገብስ በሶ፤ የገብስ ጭኮ፤ የአሳ የዶሮ የሥጋ የምስር የአብሹ ወጥ፤ በጠላው፤ በሊፍተሩ፤ በጠጁ፤ በቡቡኙ፤ በኮረፌው ዝግጅት ሂደቱ እራሱ፤ ዓውዱ በራሱ የጥበብ እንብርት ነው።
የአለባበስ ዘይቤው፤ የሸማው የጥበቡ፤ የጥልፋ፤ መዋቢያው የአደሱ፤ የኩሉ፤ የእንሶስላው የጉርሽጡ፤ የፀጉር ስታይሉ፤ የእድሩ የሰንበቴው የቁቤው የሰርጉ የመልሱ የቅልቅሉ፤ የሃዘኑ የተዝካሩ የፍታቱ ሂደቱ የራሱ ሥርዓት ያለው መሳጭ፤ ሰጪ ለጋስ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት የእንኳን ደህና የጣችሁልኝ የብሥራት ዜናም ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከክብሩ ወርዶ በማንነት ቀውስ የሚታመስ አይደለም። ወይንም ከተሰጠው በላይ ተንጠራርቶ አገር ምድሩን ልመስ ላተራምስ አይልም። ኢትዮጵያዊነት በራስ የመተማመን አቅሙ የተመጣጠነ በአለው ልክ ጸንቶ የሚገኝ የዕውቀት ዘርፍም ነው።
ከዩንቨርስ ፍልስፍና እስከ ዝቅተኛው እህልን ከእብቅ ለመለየት በሚደረገው ሂደት የራሱ የሆነ፤ የእኔ የሚለው ያለው ማንነት ነው። በታሪክ፤ በትውፊት፤ በወግ በልማድ በተፃፈም ባልተፃፈም ድንጋጌ፤ በሃይማኖት ዶግማ እና ቀኖናም፤ በሥርዓተ መንግሥት አደረጃጀት እና መርህ የተትረፈረፈ ዲታነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት እንደ አንፖል ያገኜ አለሎ ሲልክበት እንኩትኩት የሚል አይደለም። ኢትዮጵያዊነት #ደንጋጣ ማንነት አይደለም። ኮሽ ባለ ቁጥር አይበረግግም። ፍጹም #የተረጋጋ ስኩን የመቻል እና የማስቻል ሙሉ አቅም ያለው ዓራት ዓይናማ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት።
ስለሆነም አዲሱ ትውልድ በኢትዮጵያዊነት ክብር፤ ልዕልና፤ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና እና ልቃና ላይ በሚታዩ ባልሰከኑ የአዬር ለውጥ ምክንያት ሊታወክ አይገባም። በሌላ አገር አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የተለያዩ አገር ተማሪወች ይኖራሉ።
ከአፍሪካ ኢትዮጵውያን ይለያሉ። በአኗኗር ዘይቢያቸውም ጸጥተኛ ስለሆን። በአኗኗር ዘይቢያችን እንለያለን። ሥራ መውደድ ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊነቱም ትንግርት ነው። ኢትዮጵያዊነት የፊደል ገበታነቱ በሁሉም የአኗር ዘርፍ ያለው ነው።
ሌላው ባለ ይሉኝታው ኢትዮጵያዊነት ምን ይሉኝን ሰንቆ ለህግ ተገዢነቱን ፈቅዶ በሥርዓት የሚኖር ጨዋ ህዝብን ያወለደ፤ ያሳደገ፤ ያሰበለ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። በውነቱ ዝልቁ ኢትዮጵያዊነት መቻልን አብዝት ፈጣሪው አላህ የሰከው በላ #አደብ ማንነት፤ እራሱን የገዛ ምራቁን የዋጠ ማንነት ነው - ኢትዮጵያዊነት።
እንደ ማንኛውም ማንነት ኢትዮጵያዊነት ፈተነኛ ነው። ወጀብ፤ አውሎ፤ ጦሮ በአሻቸው አቅጣጫ፤ በሚያሰኛቸው ጊዜ ከች ይላሉ። ኢትዮጵያዊነት በእልህ፤ በቁጣ፤ በማናኽሎኝነት፤ በመታበይ፤ በብልጠት ሳይሆን #በብልህነት ያስታግሳቸዋል። በዬአጋጣሚው ያልተመጣጠኑ ጉዳዮች ሊከሰቱ ይችላሉ።
ግን ኢትዮጵያዊነት በራሱ ጊዜ #የሚያረገርጉ ሁነቶችን ያሰክናቸዋል። ያረጋጋቸዋል። ብስጩ ወጀቦችን #ረብ ያደርጋቸዋል። ኢትዮጵያዊነት አብሮ አይቆጣም። ኢትዮጵያዊነት አብሮ አይበሳጭም። ኢትዮጵያዊነት እላፊ አይሄድም ጥበበኛ ነውና። ኢትዮጵያዊነት ችሎትም ነው። ይዳኛል። ኢትዮጵያዊነት የወጣለት #ተፈጥሮኛ #ዲፕሎማት ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
06/04/026.
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ