"ሆድ ሲያውቅ ..."

„ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ።“
„በውኑ ደንግል ረግረግ በሌለበት ቦታ ይበቅላልን?“
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፲፩)

ከሥርጉተ©ሥላሴ 21.07.2018
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)


  • ·       በር።

ዛሬን ደብሮታል። ደምኗል። እሜቴዋም ብቅ አልልም ብላ ጫጉላዋ ላይ ናት። እናም እኔም መውጣቱን አልፈለግሁትም። ስለዚህም ይህ ተኮለመ።፡
  • ·       ግራሞት ክራሞት!

ከያንያን ምክንያት አይደሉም፤ ወይንም የአዲስ አባባ ከንቲባ ሹመት ምክንያት አይደለም። መሰረታዊ ጉዳይ የጠ/ ሚር አብይ የፍቅር ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋው ነው መከራው። አጀንዳ ስለሚያሳጣ። ደጋፊ ስለሚያሳጣ። 

ጸረ የአብይ ጸረ አብይ መንፈስን ከሳተናው ድህረ ገጽ በስተቀር፤ ብሎጎች፤ ታላላቅ ሚዲያዎች፤ የኮሚኒቲ ራዲዮኖች ሁሉም የባጁበት ነው። ምክንያታዊ በሆኑ ጉዳዮች አይደለም ሲታመሱ የባጁት ሁሉም ሚዲያ። ለአገር ተቆርቋሪነት አልነበረም ሁሉም በጓዳው ደብቆ ያቆዬው የታቆረ ዓላማ እንጂ፤ ብጥብጡንም ሞከካረው መሬት ላይ እሱም ለግብ አላበቃም። ትንሽ ራፊ የ  ዕውቅና ከማሰገኘት በስተቀር ሞጋዳዊ ለውጡን፤ ሰላሙን በማወክ ያስገኘው ፋይዳ የለም። እንዲያውም እትጌ ኤርትራ የምሥራቹን ጀባ ብላ አቅልም ቀልብም በዚያ ላይ ሰከነ።
  
…. እራሱ  የአሜሪካ እና የጀርመን መንግሥት በጀት መድቦ የሚያሠራቸው ሚደያዎች ሳይቀሩ በምን ሁኔታ ላይ ሲታተሩ እንደነበሩ ይታወቃል። ይህ የለውጥ መንፈስ በጥዋቱ ተሰብሮ እንዲቀር በዕድሜ ሁሉ ሲያላግጡ ነበር። እንዴት ዶር አብይ አህመድ 14 ዓመት ትግል ውስጥ ገባ የሚል ታሪክ አዳመጥን የሚል የማጣጠል ተግባር ሁሉ ተደምጧል።

ለውጡ ከስቶ፤ ለውጡ መክኖ ወይንም ተሰብሮ ባልታወቀ አቅጣጫ እንዲያመራ ነበር በተቀናጀ ሁኔታ የተሠራበት። ትግል 10 ዓመት ላይም ይገባል። ይህን የቀደመውን የኢህአፓ፤ የሻቢያ፤ የወያኔ የተጋድሎ ታሪክ አቅርቦ መበርበር ነው። በደርግ ጊዜ የታዳጊ ወጣቶች የሚል መዋቅር ሁሉ በት/ ቤት ተጀምሮ ነበር …
  • ·       የሆነው

ቴዲ አፍሮ ወደ ባህርዳር ሲሄድ ዋ ትሄድ፤ ከሄድክ አደጋ ይመጣል ተብሎ ነበር። ይህን ያሉት የሚፈራ ነገር ስለነበረ ነው። ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለው አቋምን ፈረስቶች ፈርተውታል። 

ፈርስቶች ወጣቶች ናቸው። ወጣትነት ደግሞ ነገሮችን በጥልቀት የማዬት አቅሙ ውሱን የሚያደርግ የዕድሜ ፈተና አለበት። ወጣቶችን አትቸኩሉ ማለት ዕድሜያችሁን ዝለሉት የማለት ያህል ነው። በዛ ላይ በአማራ ላይ ያለው ሰቆቃም ብቻ ሳይሆን የአለመደራጀቱ ጥቃቱን ዋቢ አልባ በማድረጉም ጭምር ነው እንጂ አማራ ሆኖ ተፈጥረው አማራነቴ ይቅደም አይሉም ነበር። መቼም ፈተኝ ፖለቲካዊ አቋም ነው። እኔ እደነግጣለሁኝ ይሄን ስሰማ።

የሚገርመው ለኢትዮጵያዊነት እና ለታሪኳ ተቆርቋሪነት የነበረውም መንፈስ ደግሞ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ሲመጣ በዛ አቋሙ መጽናት አልቻለም። ፈራው! ስለዚህ በዝንቅ ጉዞ ላይ ነው የነበርነው ማለት ነው። 

እንዲያውም ለእኔ ፈርስት አማራነቴ የሚሉት ግልፆች ናቸው። ሊከበሩም ይገባል። ድብቅ አይደሉም። ስሜታቸውን ነው የገለጡት። ያሉበትን ምክንያት በስክነት መርምሮ ይህን አመክንዮ ወደ ትክክለኛው ምልከታ ለማምጣት የሚችል ሁነኛ የአማራ ድርጅት ደግሞ አልተገኘም። ሁነኛ የአማራ ሚዲያ አልነበረም። ሁነኛ ሊሂቅ እራሱ ቅን የሆነ፤ ንጹህ የሆነ፤ አዎንታዊ የሆነ አልተገኘም። 

እራሱ የአብይን መንፈስ እኮ ተቀናቃኝ ሆነው የወጡ የአማራ ሊሂቃንን አዳምጫለሁኝ እስኪገርመኝ ድረስ።

ሁሉም ነገር ቀርቶ ኢትዮጵያ ከፍ ስትል እንዴት ሊጎረብጥ ይችላል? ስለዚህ ወጣቶቹን መንፈሳቸውን ገርቶ፤ ቀስ አድርጎ አለስልሶ፤ የሚያነሷቸውን አብይ አጀንዳዎች አዳምጦ፤ ብስጩነታቸውን ችሎ አወያይቶ፤ ቁስላቸውን አስታሞ የራስ ለማድረግ የጣረ ድርጅት የለም።

ህብረ ብሄር የሚባለውም „መደራጀትህ የኢትዮጵያ ስጋት ነው፤ መደራጀትህን የመረጥከበት ጊዜ አጓጉል ነው፤ አንተ የወያኔን አጀንዳ እያራመድክ ነው“ በሚል ነው የተዋከቡት ወጣቶቹ።

ሰለዚህ እንደዚህ ወከባ ላይ ያሉትን ወጣቶች ሁሎችን አቅርቦ በሰፋ ሆደ ሰፊነት ምንድነው ውስጥህ የሚለህ የሚል አሰባሳቢ እናት የሆነ የአማራ መንፈስ ውጪ አገር አልነበረም። ሁሉም በራሱ አጀንዳ ተኮፍሱ የእኔ ካልሆነ ወይንም የድርጅት አባል ካለሆንክ ነበር ጉዳዩ። ለመደራጀትም ግልፃዊ መርህ የተከተለ አይደለም። ራሱ መንፈስን ለማቅረብ።

መሆን የነበረበት ግን አብሶ አማራን እንወክላለን ብለው ከተደራጁት ከአማራ ሰብዕና ፈንገጥ ብሎ የመጣውን ዕይታ ለመግራት ከድርጅት ውጪ የሆነ ግን አማራዊ ጉዳትን አድምጦ ወደ ትክከለኛው አቅጣጫ የሚመራ ብቁ መንፈስ አልተገኘም። እኔ እንዲያውም የጀርመን የአማራ ደጋፊ ድርጅት የሚለው መንፈስ የተሸለ ጤነኛ መንፈስ ነበረው፤ ትጋቱም የውስጥ ነበር። 

አሁን ምን ደረጃ እንደ ደረሰ ባለውቅም። ከዚህ መንፈስ ውጪ የነበረው የመንፈስ አቅም ያለው ደግ መንፈሱ አንብዛም ጎልቱ አላዬሁትም። ማለት ለድርጅት ቅንነት ነው መርህ ሊሆነው የሚገባ። ከቂም በቀል የጸዳ መስር ነው ሊያስቀጥለው የሚችል። አዊንታዊነት ነው ወደ ሰዋዊ እና ተፈጣሯዊነት ሊያመጣው የሚችለው። ግን በኖረው የፖለቲካ መስመር ነው አዲሱ የአማራ መንፈስ ተጋፍቶ የተወጣው። ነፍስ ባማን ላይ ሌላ ዝብሪት፤ ሌላ የቁርሾ ማወራራጃነት።

ብዙ ድርጅቶች መግለጫቸውን አነባለሁኝ፤ ስብሰባዎችን እከታተላለሁኝ ግን ዋናውን የአማራን የህልውና ተጋድሎ በጥንቃቄና በብልህነት ተልዕኮውን ያማከለ ነበር ለማለት አልደፍርም። ያማ ቢሆን አርበኞቹ ሲፈቱ የእኛ ይባሉ ነበር። አላዬንም አልሰማንም። አገር ቤትም ተደራጀ የሚበለው አብን ለዲኮሬሽን ካደረገው ውጪ በፖለቲካ አቅሙ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደለም።

ከጀምሩ ያላመረ ቤት ደግሞ መጨረሻውም ያው ነው። ከመንፈሱ ተነስቷል ብዬ አላስብም። ቅራሪ ለቀማ መሄድ አያስፈልግም ሚሊዮን በታጋበት መንፈስ ውስጥ ሰው ጠፍቶ ሰማያዊ ፓርቲን ጡረተኛ ጥወራ የሚያስኬድም፤ ቀለሙን አንግሦ የማውጣትም አቲካራ ባልተገባ ነበር … 

የተበተነው የአማራ መንፈስ፤ የተጎዳውን ሥነ - ልቦና በግራ ቀኝ የሚዋከበውን ሁኔታ እንደ እናት አሰባስቦ፤ አቀራርቦ፤ አስታራቂ መንፈስ ፈጥሮ የሚያገናኝ ድልድይ አልነበረውም ትናንትም ዛሬም። ልክ ሌላው ድርጅት ሲናኮር በነበረበት መልኩ ነበር የተቀጠለው።

አብሶ ከአማራ ክልል ባዕትህ ነው ተብሎ ከተሰጠው ውጪ ያሉ አማራ ነን የሚሉ ወገኖችን ውጪ አገር እንኳን ለመቅረብ፤ በጥሩ ሁኔታ ለመያዝ፤ አቅማቸውን ለመጠቀም ያዬሁት ነገር አልነበረም። የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ተልዕኮው ሰፊ ሆኖ ሳለ በተጠበቀ ሳጥን ውስጥ ተጠርንፎ የተያዘ ኩድኩድ ነበር።

የነበረው የአማራ ድርጅት አማራን በሙሉ ያቀረበ፤ አቅርቦም በሙሉ ጸጋው ተጠቃሚ ለመሆን የተጋ አልነበረም። አንድ እንኳን ነፍስ ያለው የቴሌ ኮንፈንስን ለማደረጀት ያልቻለ ነበር። ያው በተለመደው የሴራ ፖለቲካ ነው ሲታመስ የተባጀው። ይህን ማድረግ ስላልተቻለ በክፍተቱ ሌሎች መንፈሱን የሚከፍል፤ አንጥፎም የሚገዛ አዲስ ተለጣፊ ካሊሲ ተበጀለት። ስለምን? ኃላፊነቱን የወሰዱት ሊሠሩ የተገባውን መርኃዊ ጉዞ ስለሳቱ።

በአባልነት አቀበባል እና አደረጃጃትም ግልጽ አቋምም የለም። አገር ቤትም ያለው መከራ ይሄው ነው። በትግራይ ልጆች ግን ይሄ መሰል ቀልድ የለም። ለዚህም ነው ለረጅም ጊዜ የማይገበር ሆኖ 27 ዓመት ሙሉ ቀጥቅጦ የገዛው ወያኔ ሃርነት ትግራይ፤ ምናልባትም መንፈሱ ወደ 50 ዓመት ሊዘልቅም ይችላል፤ ከላይ እስከታች የቤቱ አገነባብ በታቀደ የተከወነ ስለሆነ።

አሁን ሁሉንም ቃለ ምልልስ ተመልከቱት፤ ሌላ ሰው ማግኘት አልተቻለም። ወንበሩን የያዙት እንሱው ስለሆነ ጠያቂውም፤ ተጠያቂውም፤ ሪፖርተሩም፤ ተንታኙም ያው እንሱ ናቸው። የ ሰብዕዊ መብት ድርጅቱ ሳይቀር ሰብዕናን በታረደበት አገር የዛው ዘር አባወራ ሰብሳቢ። በቃ ቲያትሩ ይሄው ነበር። „አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ …“ አቃቢ ህጉም፤ መርማሪውም፤ አዛዡም፤ ሃኪሙም  የእስር ቤቱ እኮ ነው ያው እሱ በእሱ ነው።

ወደፊትም ተተኪ ለማውጣት እስክልተሠራ ድርስ ቀጣይ ነው የሚሆነው። አማራ ቡቃያን ማውጣት ቀርቶ የወጣውን ቡቃያ ብቃት ለመጠቀም ፈቃደኛ አይደለም። ማብቀል እና ማብቃት በአማራ ሊሂቃን የማይታሰብ ጉዳይ ነው። አይደለም በራሳቸው መዋቅር አልፈው ተርፈው ወዲያ ማዶ ተሻጋረው ሁሉ እገዳ ያስጥላሉ። ስለዚህም ነው ብቻቸውን እንደባከኑ ካለ ውርስ ቅርስ የሚያልፉት።

  • በመደራጀቱ ስለተስፋው።    

የሆነ ሆኖ የአማራ መደራጀት ከምንም ግን ይሻል ነበር። በሎቢ ደረጃም ጥሩ ተግባር ፈጽሟል በመኖሩ። አብሶ አማራ እየገዛ ነው የሚለውን ጠናና አመለካከት ግርቶ ልኩን ይዞ እንዲቀመጥ አድርጎታል። በዚህ ጉዳይ ዛሬ ዓለም አቅፉ ሚዲያ ሁሉ ግልጽና ጥርት ያለ አቋም የያዙት በአማራ መንፈስ ውስጥ ያሉ ቅኖች የከወኑት ተግባር ነው።

በሌላ በኩል መዝሙሩም „አማራ ነን“ ትልቅ ህሊናዊ መንፈስን የመግራት ጉልበታም አቅም ያለው ነው። ለዛሬ አይደለም ለነገ ታላቅ የሥነ - ልቦና ግንባታ ተቋም ነው። አማራነትን መንፈሱን በተገባው መልክ አሰባስቦ አደራጅቶ በማውጣት ደረጃ ግን ያዬሁት ነገር የለም።

ተቋማዊ አቅሙ አገር ቤትም ውጪ አገርም ለናሙና የምጠቅሰው እኔ የለኝም። ልክ እንደ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በዛው ደረጃ ነው ያለው። ስለምን? እራስን አሸንፎ የወጣ የእልህ መንፈስ ስሌለው። የትውልዱ ብክንት ሳያሆነ የራስ ሥም እና ዝና ነው ጣዖቱ ….

ኦህዴድ እና ምህንድስናው ግን የተለዬ ነው። ከልቤ ብሎ ለሚያጠናው፤ ለሚመረምረው። ለዚህም ነው ኦህዴድ አሁን ሐገርን የሚያክል አደራ ተረክቦ እያስደመመን ያለው። ውስጡ ያለውን ስርክራኪ አሸንፎ በንጽህና በመወጣቱ አሸነፊ የሆነው በዚህም ነው። ኦህዴድ የተንኮል ድርጅት አይደለም።

በነገራችን ላይ ኦህዲድ ዛሬ ካለበት የፖለቲካ አቋም ሌሎች አንደርሳለን ብለው ቢያስቡት 24 ሰዓት ተስርቶም የሚደረስበት አይሆንም። ስለምን? ኦህዴድ ልክ እንደ ሲዊዞች የጤና ተቋም በተጠባባቂነት በሁሉም መንገድ ዝግጁ መንፈሶችን አደራጅተዋል። ሲዊዞች የማህጸን ሀኪም ቢታመም፤ ፈቀድ ቢወጣ ተተኪ ሀኪም አለ፤ የጠቅላላ ህክምና የቤት ሀኪም እንዲሁ እክል ቢገጥም አንሰሪንግ ማሽን ላይ ስልኩ ስለሚቀመጥ በቀጥታ ሄዶ መታከም ይቻላል …

ኦህዴድ ከፌድራል ወደ ክልል ሲመልስ አካላቸው ለዛ ቦታ ዝግጁ ናቸው። ወይንም ከክልል ወደ ፌደራል ሲልክ ለዛ ቦታ ብቁ ሰው አዘጋጅቶ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታስቦ የማያውቅ የተከደነ ገመና ነው። እንዲህ ይሆናል? እከሌ እክል ቢገጥመው እከሌ ይተካዋል የለም። እራሱ ሰው እና እንጨት ተሰባሪ መሆኑ እራሱ ታስቦ አያውቅም። ቢገጠምም ተተኪ ምድረ በዳ ነው። ኦህዲድ ግን ተፎካካሪ ሆኑ የሚወጣው በዓይነት ስንዱ ነው። የበለጠን ማውጣት ነው ሞቶው።

አሁን በምደባ ብዙ ሮሮ ይሰማል። ስንዱ አይደለማ ሌላው፤ አልተዘጋጀም፤ አላሳነዳም፤ እንደገናም የሚመራቸውን አቅም አለጠናም። አያውቃቸውም ማንም ምን ክህሎት እንዳለው። አሁን ብአዴን ፕ/ አበባው አያሌውን የመሰለ ርጉ ርቱ ሊሂቅ አቅምን ማስጠጋት አይሻም እንኳስ ፈልፍሎ - የት ነህ - ማን ነህ - ምን ፕሮ ፋይል አለህ? ምን ሰብዕና አለህ ብሎ ሊመረምር ይቅር እና። የጉደለውን ሞልቶ ሊያጠናክር ቀርቶ ብቁዎችን እንኳን አያውቃቸወም። ያው በጎርማዴ በሸራፊ ነው መጪ እያለ ያለው እስኪ መጪው የነሃሴ ጉባኤ ከተኖረ ይታያል … ሁልጊዜ ሁለት ሰው ነው መግለጫ ሲሰጥ የሚሰተዋለው … አወያዮችም ከተወያዩች በታች ናቸው …

ስለዚህ ቦታው ሁሉ ክፍት ነው። በዛ ላይ አቤቶ ወያኔ ግጥም አድርጎ ሰዎቹን ሞልቶበታል። ለዚህ ነው ቀይ ስንዴው ሲገለበጥ ነጩ ስንዴ ብቅ የሚለው። ሽግሽጉ፤ ሹመቱ በአንድ አቅጣጫ የሆነበትም ምክንያት ይሄው ነው። የለማ መንፈስ በቆዬባቸው ጊዜዎች በመንፈሱ ሰዎቹን ሊስት አድርጎ ቆይቷል። አጋጣሚው ሲረዳው መሰስ እያደረገ ቦታ ያስይዛል። ይህ ደግሞ የተገባ ነው።

  • ·       ህዴድን ከኦንግ ጋር? የተመክሮ ችግር ነው …

ከዚህ ባሻገር ኦህዴድን ከኦነግ ጋር ማጣመር ከወንጀሎች በላይ ነው። በዛ  በኦህዴድ ውስጥ ቀጥተኛ የሆነ የኦንግ አቋም ያላቸው የሉም ማለት ባልችልም በለማ መንፈስ እና በ አብይ መንፈስ ግን ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። የትኛው ነው ዛሬ በዘር ፖለቲካ የተጠመደ ቀርቶ ህብረ ብሄር ነኝ የሚል „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የሚል። ማን? ሁሉም እኮ አምቆ አምሎ ዬያዘው ገማና አለበት።

መዋቅሩን ሁሉ ስትፈትሹት፤ ተቋም የሚባለውን ስተመረምሩት እኮ ዘሩን ወይንም በጋብቻ የሚቀርበውን ነው ደርድሮበት እምታገኙት። በቃ ዕውነቱ ይሄው ነው። ሰውዬው የሱ ዘር ባይሆን ሚስቱ ናት፤ ሚስቱ የእሱ ዘር ባትሆን ባልተቤቱ ነው። መስመርም የሚዘረጋው በዚህ መንፈስ ውስጥ ነው። አሁንም በአብይ መንፈስ ለመጠቀም የሚሞከረው በዛ መስመር እንጂ በተግባር ነጥሬ አሸንፌ የለም። አልነበረምም። ማን ቢወልድ ማን ነው?

ስለዚህ በለማ እና በአብይ መንፈስ ቆሻሻ የሆነ የልዩነት መንፈስ ፈጽሞ የለም። ፓርቲያቸው አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ግን ይሠራሉ የማንን ጎፈሬ ያበጠራሉ። ግን ብቃቱን የጠበቀ፤ ክህሎቱን ያሟላ ነው።

ዕውነት የሆነው ነገር ሰነፍ፤ ፋውል የሆነ አይደለም ለመንግሥት መዋቅር ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከእንግዲህ በ አላዛሯ ኢትዮጵያ በሞተ ተስፋ ላይ ነው ያሉት። ለዚህ ነው አሁንም ቅድም የሽግግር መንግሥት የሚሉት። ሥራ አይወዱም ተፎካካሪ ፓርቲዎች። እነሱ ሚዲያ ነው የሚወዱት። እውነቱ ይሄ ነው።

ማን ማንም ተካ? የማን ተተኪ ማን ነው? የለም። ባለ 44 ዓመቱ ታጋይ፤ ባለ 27 ዓመቱ ታጋይ፤ ባለ 20 ዓመቱ ታጋይ፤ ባለ 10 ዓመቱ ታጋይ ያው አንድ ዓይነት ሰው ነው የሚደመጠው። ምክንያቱም የማደራጀት ተግባር ላይ አይደለም የሚሠራው። የሚሠራው ፕሮፖጋንዳ ብቻ ነው። የሞገድ፤ የቴሌፎን፤ የኔት ሥራ በቃ። እና ለፖለቲካ ድርጅቶችም የአብይን መንፈስ ሞግቶ ለማሸነፍ መሬት ላይ አፈር ግጦ መስራትን ይጠይቃል። ለወደፊትም ይህን ፈተና የሚያልፈው አሁንም ቢሆን ኦህዴድ ነው። 

የማደራጀት ፍልስፍናው ገብቷቸዋል ኦህዴድች። በዛ ላይ ማብቃትን በሴራ እና በአምቻ በጋብቻ አይደለም የሚሠሩበት። ለክልላቸው ህዝብ እንዴት ባገኘው ዕድል ተጣቃሚ አድርገን ከጉስቁልና ህይወቱ እናላቅቀዋለን ነው። በአገር ደረጃም ያሉት እንዴት ኢትዮጵያ አንግቷን ከደፋችበት ቀና አድርገን የአፍሪካ ናሙና እንደርጋታል ነው። ለተሰለፉበት ቦታ እና መዋቅር ሃላፊነታቸውን የሚወጡበት ትጋት ነው አጀንዳቸው።

አሁን እንዲያውም በመንፈሳቸው ኤርትራንም የኛ ውስጣችን የሚል ስሜት እንዳላቸው ነው የተረዳሁት። ይሄ ቅንነት ከማን መቼ አለና? ሳቅ የማያስደስትን፡ ስምምነት የማያስቧርቀን፤ ሰላም የማያስፈነድቅን እኛ እኮ ጉደኞች ነን። እነሱ ደግሞ ከእኛ በእጅጉ የራቁ ናቸው። ዛሬ አይደለም ነገም ያሸንፋሉ! ቅኖች ስለሆኑ።

ሴራ አይደለም አሁን ኢትዮጵያን እዬመራት ያለው። ተንኮል አይደለም  የኢትዮጵያ አስተዳደሪ ዛሬ። ምቅኝነት አይደለም የኢትዮጵያ ሙሴ። ህውከት አይደለም ዛሬ ኢትዮጵያን እዬመራት ያለው … ቅንነት - ንጽህና - ፍቅር ምህረት - እርቅ - አድማጭነት - ዕንባ አባሽነት - ብሄራዊነት ነው … ጊዜውም የላቸውም … ቀን እና ሌት ነው እዬባከኑ ያሉት። እኔም ተናግሬ ነበር ሰነፎች ወዮላችሁ ብዬ።
ሰነፍ ሞገድ ላይ ወይንም አቋራጭ ምንጣፍ ሸመታ ይማስን፤ እንትንም ከጋኘ ውራጅ ነገር።  … 

ትጉሃን እዬቀደሙ - እዬተከበሩ - እዬተሾሙ ይሄዳሉ። ሰሞኑን ለዶር ገዱ አንዳርጋቸው፤ ለዶር ለማ መግርሳ የተሰጠው ማዕረግ  ለአማራ ታገድሎ እና ለኦሮሞ ንቅናቄ የተሰጠ ዕውቅና ነው። ያን ያዳመጡ‘ ያን የተረጎሙ፤ ያን ያመሳጠሩ፤ ያን በማስተዋል ተጠበቡት። በቃ ለዚህ በቁ። ከራሳቸው ክልል አልፈው አፍሪካንም የሰላም ቀጠና ለማድረግ መንገድ ጠረጉ ብልህነቱ ይሄው ነው።

አሁን አጀንዳ ሲጠፋ ከዚህ እክሌ፤ ከዛ እከሌ ተሸሞ … ታግሎ ሲያሸንፉ ነው ይህ መዘባነን የሚገኘው። የነፃነት አርበኞችን ያስፈታው ይህ መንፈስ እንጂ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አቅም አልነበረም።

ባለቀ ጊዜ የሰማያዊ ሸር ጉድ ከቁጥር የሚያስገባው የለም። ገድሉ የተሠራው ተጋድሎን ባደመጡ፤ አፈጸጸሙን በብቃት በታካኑበት ወጣት ሊሂቃን ነው። በገዱ እና በለማ መንፈስ ቅኝት ነው ዛሬ የተገኘው። ዕውነቱ ይሄው ነው …


ዕውነት ስትተከል ትበቅላለች!
ዕውነት ስበቅል ትጸድቃለች!
ዕውነት ስትጸድቅ ታፈራለች!
እውነት ስተፈራ ታሰብላለች!

ሰብላችን የመጠበቅ፤ በጸሎት የመርዳት መደበኛ ሥራችን ነው ለቅኖች!

የኔዎቹ ኑሩል።

መሸቢያ ጊዜ! 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።